ጄኒራል ተፈራ ለብአዴን ባላቸው ስስ ልብ (አብሮ አደግ ስለሆኑ) “ትርፍ አንጀት” በሚል ቀላል ዘለፋ አልፈውታል። ትርፍ አንጀት አላስፈላጊ የሆነ አካል ሲሆን ከታመመና በጊዜ ካልተወገደ የሚገድል ነው። ብአዴን መወገድ ያለበት፤ ለአማራ ምንም በጎ አስተዋጽኦ የማያደርግ፣ ባደረ ቁጥር አማራን ወደ ከፋ ሞት የሚወስደው ትርፍና አደገኛ ቅጥል አካል ነው ማለታቸው ሁሉንም ያስማማል። ብአዴንን ግን ይህ ብቻ ይገልጸዋል ወይ?
ሌሎች ደግሞ አገር ሲያረጅ ጃርት ያበቅላል በማለት ብአዴንንም ሆነ ኢህአዴግን (ብልጽግና ወሕወሃት) ባጠቃላይ የጃርቶች ስብስብ፣ ሰው የተከለውን ማውደም እና እሾህ መርጨት ካልሆነ በስተቀር ፋይዳ እና ጠቀሜታ በሌለው አውሬ መስለው ይገልጹታል። ጃርት ማለትስ ብአዴንን በበቂ ይገልጸዋል ወይ?
ሕወሃትና ኦነግ ጥምረት ፈጥረው ጥቃት በፈጠሩባቸው የደቡብ ወሎና ሰሜን ሸዋ አካባቢዎች አባት የልጁን፤ ባል የሚስቱን፣ ልጅ የእናቱን እግር ይዘው አጥቂው መሳሪያ የደገነ ትግሬ ወይም ኦሮሞ አንድ ወይም በቡድን ሆኖ የአማራ ሴቶችን እንዲደፍሩ አድርገዋል። ከወሲባዊው ጥቃት በዘለለ ማሕበረሰቡን የረጅም ዘመን የሥነ ልቡና ተጠቂ ለማድረግ የተሠራ ወያኔያዊ/ኦነጋዊ ግፍ ነበር። የአንዱ ኢትዮጵያዊ መዋረድ የሌላውም ኢትዮጵያዊ፣ አፍሪካዊም ጭምር መዋረድ መሆኑ ያልገባቸው ደናቁርት የሥነ ልቡና ጥቃቱ የአጥቂውንም ወገን እንደሚያነቅዘው አላስተዋሉም። እነዚህ የአማራ ሰዎች በጠላቶቻቸው ተገደው በጦርነት ድባብ ውስጥ ያደረጉት የውርደት ድርጊት ነበር።
ብአዴንስ? ብአዴን ማለት መሣሪያ ሳይደገንበት በፈቃዱ እናቱን፣ እህቱን፣ ሚስቱን (ወገኑን/ ክልሉን) እግር ይዞ የሚያስደፍር ነውረኛ ማለት ነው። ከሦስቱ ቅጽሎች ይህኛው የበለጠ ይገልጸዋል። እግር ያዥ። ፈጣሪው (ሕወሃት) ብአዴንን የፈጠረው ይህንን ተግባር በአግባቡ እንዲወጣ በማሰብ ነበር። አላሳፈረውም።
ዛሬም ብአዴን በኦህዴድ እልቅና ሥር የተፈጠረበትን በአግባቡ እያከናወነ የሚገኝ ታማኝ አገልጋይ ባርያ ነው። አሥራ ሁለት ሺህ ወገኖቹን አሳዶ፣ አፍኖ፣ ይዞ ያሳሰረ። በመቶሺህ የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ከወገን የተላከላቸውን እህል በመጋዘን እንዳለ ያቃጠለ። ከተሞቹና መንደሮቹ ሲቃጠሉ ከባንክ ዘርፎ፣ ሸሽቶ የሚሮጥ። ከሌላ ክልል ተፈናቅለው የሚመጡ ወገኖቹን የሚያንከራትት፣ ያለ መጠለያ በየሜዳው፣ በየጫካው እንዲወድቁ የሚተው። የአማራን ገዳዮች እየጋበዘ የሚሸልም። ንጹሐን ወገኖቹ በመቶዎች ሲገደሉ ሌላ አቅም ቢያጥረው እንኳን የሐዘን ቀን ማወጅ የማይችል። የአገሪቱ የሠራዊት የሥልጣን እና የአስተዳደር እርከኖች በሙሉ በአማራ ጠል ኃይሎች ሲሞሉ ድግስ እየበላ በዝምታ የተባበረ። የሌላ ክልል ጦር ክልሉ ውስጥ ገብቶ የክልሉን መለዮ ለብሶ በክልሉ ተወላጆች ላይ አፈና፣ ግድያ ሲያካሂድ የሚተባበር።
ይህንን እግር ያዥነት ግን ብአዴን ግንባር ቀደምና አንጸባራቂ ሆኖ ይተውን እንጂ በሞኖፖሊና ለብቻው የያዘው ሙያ አይደለም። ከብአዴን ውጭ በዚህ እግር ያዥነት የተሠማራው አማራም ቁጥር ቀላል አይደለም። ማንም አማራን ተገድዶም ሆነ ወድዶ፣ ፈቅዶ ሕዝቡ አሁን የምናየው ውርደት እንዲደርስበት የሚያደርግ፣ የመከራ ዶፍ እንዲዘንብበት የሚተባበር አማራ ሁሉ ግብሩ እንደሚያሳየው በእግር ያዥነት እያገለገለ ያለ ባርያ ነው።
በድን በሚል ስድብ ብአዴንን ለመግለጽ የሞከሩም አሉ። አልረሳሁትም። ይህ ግን ከሸክሙ ይልቅ ተሸካሚውን የሚሰድብ ነው። በድን ነገርን ተሽከሞ ዘላለም የሚደፈጠጥ፣ በተወሰነ ደረጃ ራሱም በድን የሆነ ተፈጥሮ ቢኖረው ነው ስለሚያሰኝ። የሕዝቡ ትእግሥት በድን አያስብለውም። ይሁንና ትእግሥትም ልክ አለው። የማይካደው ሐቅ የብአዴንን ማንነት ከተረዳ በኋላ ተሸክሞ መቀጠሉ ሕዝቡን ለፈርጀ ብዙ ወቀሳ ለታሪክም ጠባሳ የሚዳርገው መሆኑ ነው።
__
በኦሮሚያ፣ ቤንሻንጉል፣ በጋምቤላ የሚደረገው ዘር ተኮር የንጹሐን ጭፍጨፋ የተወገዘ ይሁን!
የንጹሐን ደም ለሁላችንም መዐት የሚያመጣ ነውና እጃችሁ ያለበት ብታድቡ፣ በስማችሁ ወንጀሉ የሚፈጸምም ወገኖቻችን ተዉ ብትሉ፣ ብታወግዙ፣ ዛሬ ብታለቅሱ ይሻላል።