
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የጦር መሳሪያ የታጠቀ ማንኛውም አካል ከጥቅምት 27/2014 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት አምስት ተከታታይ ቀናት እንዲያስመዘግብ የክልሉ መንግስት ጥሪ አቀረበ
የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ በየነ እንዳስታወቁት አሸባሪው ሕወሃት የከፈተውን ጦርነት ለመቀልበስ ሃገራችን በህልውና ዘመቻ ላይ ትገኛለች ያሉት አቶ መለሰ፣ የክልሉ መንግስትና ሕዝብ ዓይነተ-ብዙ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል፡፡
በተለይም በመተከልና ካማሺ ዞኖች ባሰለፋቸው ቅጥረኞች በንጹኃን ዜጎች ላይ ካደረሰው ጥቃት ባሻገር በነዋሪዎች ላይ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ስ-ልቦናዊ ጉዳት ሲያደርስ መቆየቱንም ነው ያስታወቁት፡፡
በክልሉ በህግ ማስከበር ላይ ከሚገኙት የሃገር መከላከያ፣ የፌዴራል ፖሊስና የክልል ልዩ ኃይሎች ባሻገር ሚሊሻዎችን በማሰልጠል የጸጥታ ሥራውን እንዲያግዙ እየተደረገ መሆኑንም በመግለጫው ተናግረዋል፡፡
አሁንም “እኔ ያልመራኋት ኢትዮጵያ ሃገር ሆና አትቀጥልም” በሚል ሃገርን ለማፍረስ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው አሸባሪ ቡድኑ በአማራ እና አፋር ክልሎች ዘግናኝ ጥቃቶችን መፈጸሙን አስታውሰው፣ ይህንን በኢትዮጵያውያን ላይ የተነሳ የጥፋት ኃይል ለመደምሰስ በሚደረገው ጥረት ሁሉ የክልሉ ሕዝብና መንግስት ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
በክልሉ ማሳሪያ የታጠቁ ማንኛውም አካላት መሳሪያቸውን በማስመዝገብና ሕጋዊ በማድረግ ለሃገራዊ የክተት ጥሪው የድርሻቸውን እንዲወጡ የጠየቁት አቶ መለሰ፣ መሳሪያ እያላቸው በተጠቀሱት ቀናት በማያስመዘግቡ አካላት ላይ አስፈላጊው ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ አስረድተዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጠረፋማ ከመሆኑ ባሻገር፣ ሃገራዊ ፕሮጀክት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ምዕራፍ ኃይል የሚያመነጭበት ዓመት በመሆኑ፣ የክልሉ መንግስትና ሕዝብ ከፌዴራል መንግስት ጋር በመሆን የግድቡን ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ ብለዋል፡፡
የቀድሞ ሃገር መከላከያ ሠራዊትን፣ ከዚህ ቀደም በክልሉ የጸጥታ አካላት የነበሩና በክብር የተሠናበቱ፣ ዕድሜው ብቁ የሆነ ወጣት እንዲሁም መላው የክልሉ ሕዝብም በተደራጀ መልኩ አካባቢያቸውን በመጠበቅ ለሃገራዊ የክተት ጥሪው ዝግጁ እንዲሆንም አቶ መለሰ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
እንደ ሃገር የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአግባቡ ለመተግበር አደረጃጀት ተፈጥሮ ወደሥራ መገባቱን ጠቁመው፣ የክልሉ ሕዝብ ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ትግበራ መሳካት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም መጠየቃቸውን የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡