September 28, 2013
9 mins read

መስከረም 17 – የአንጋፋው የሙዚቃ ንጉሥ ጥላሁን ገሰሰ ልደትና ትዝታዎች

ተከታዩን ጽሁፍ ዘ-ሀበሻ ከ6 ወር በፊት አውጥታው ነበር። ዛሬ መስከረም 17 የጥላሁን ገሰሰ ልደት ስለሆነ ለመታሰቢያ ይሆን ዘንድ ወደላይ አምጥተነዋል።
ከቅዱስ ሃብት በላቸው (ጋዜጠኛ)

የትንሳዔ በዓል ሲመጣ ትውስ ከሚሉኝ ሰዎች አንዱ ምትክ የለሹ ኢትዮጵያዊው የሙዚቃ ንጉስ አርቲስት ጥላሁን ገሰሰ ነው። በኢትዪጵያውያን የሙዚቃ አፍቃሪዎች ልብ ውስጥ ታላቅ ስፍራ የሚሰጠው ይህ የዘመናችን ታላቅ የኪነጥበብ ሰው ድንገት በሞት የተለየን ከአራት ዓመታት በፊት ሚያዝያ 11 ቀን 2001 ዓ.ም የትንሳዔ ዕለት ነበር። በዚህም የተነሳ የፋሲካ ሰሞን ድብልቅልቅ ባለ ስሜት መዋጡን እየተለማመድኩት መጥቻለሁ። የእምባ ከረጢቴ ባዶ እስኪሆን ድረስ ቢያነፋርቁኝም የጥልዬን ዘፈኖች ማድመጥ አብዝቶ ይመቹኛል። ዛሬም በዚሁ የመንፈስ ባህር ላይ እየተንገዋለልኩ ነው!!
ጥላሁን ለ53 ዓመታት በዘለቀው የመድረክ ቆይታው በሙዚቃ አፍቃሪዎች ዘንድ ዘላለማዊ የሆነ ስም ለመትከል ያስቻለው ልዩ ጣዕም ያላቸው ሙዚቃዎቹ፤ እንዲሁም በመድረክ ላይ በሚያሳየው ማራኪ እንቅስቃሴው ብቻ ሳይሆን ለአድናቂዎቹ በሚሰጠው አክብሮት ጭምር እንጂ!!
ጥልዬ! … በተለይም በዓል ሲመጣ ትውስ ከሚሉኝ ነገሮች አንዱ በልጅነት ዕድሜዬ ቤተሰቦቼም ሆኑ ጎረቤት ወዳጅ አዝማዶቻችን በጉጉት ከሚጠብቁት ነገር አንዱ የጥላሁን ገሰሰን አዲስ የሙዚቃ ስራ ነበር። የዋህ፣ ቅን፣ ደግ፣ ሩህሩህ፣ የዕውነት ጠበቃና እጅግ መልካም ሰው ነበርክና እግዚአብሔር አምላክ ነፍስህን ለገነት ያበቃልን ዘንድ ዘንድሮም ሆነ ወደፊት ስላንተ እንፀልያለን!! ስራዎችህም የትናንት፤ የዛሬ፤ ወይንም የነገ የሚባሉ ሳይሆኑ ዘላልማዊ ናቸውና በማይቀረው ሞት ተለይተኸን ስጋህ አፈር ቢለብስም ምንጊዜም እናስታውስሃለንና በመንፈስ ተለይተኸን አታውቅም!!

ሰዎች ስለ ጥላሁን ምን ብለው ነበር? ለትውስታም ይረዳ ዘንድ እስኪ አንዳንዶቹን ዛሬ ላካፍላችሁ!
«ጥላሁን ገሰሰ በአገራችን የሙዚቃ ድርጅት እንደተዓምር የተፈጠረ የአዕምሮ ሃኪም ነው» (ስሙ ያልታወቀ ሰው ከተናገረው)

«ጥላሁን ገሰሰ ለተፈጠረለት ዓለም፤ ግዴታውን በተሰጥዖው ተወጥቷል። ሕይወት ክቡር መሆኗን መስክሯል፤ እንግዲህ በዝች ምድር ይህን ያሕል የጣረ ሰው ምን አለ ደጋጉን ዳግመኛ ቢፈጥረው በማለት ያንጎራጎረው ታዲያ እንደርሱ ግምት ቢሆንማ ኖሮ እኛም ጥሌን በየዘመኑ ደግመን ደጋግመን ባገኘነው ነበር»፡አንጋፋው የዜማ ደራሲ አቶ ተስፋዬ ለማ 1985 ዓ.ም)

«ጥላሁን ከአባቶቼና ከእናቶቼ ጊዜ ጀምሮ፤ የኛ ሁሉ ታናናሾች ትንንሽ ልጆች ድረስ መወደድ የቻለ ታላቅ ሰው ነው። ለአንድ አርቲስት ደግሞ ከዚህ የበለጠ ትልቅ ስጦታ የለም። (አርቲስት ኩኩ ሰብስቤ)

«ጥላሁን ዘፈኑ ቀርቶ ለቅሶው ያረካኛል።» (ታላቁ ጋዜጠኛና ደራሲ ጳውሎስ ኞኞ)

«በዘመናችን ውስጥ ዋይ! ዋይ! የተሰኘውን የለቅሶ ቃል፤ ለዘፈን ቅላጼ ሆኖ ሲዘፈን የሰማነው በዘመናዊው የጥላሁን ድምፅ ነው። (ኣዲስ ዘመን ጋዜጣ 1956 ገብረ-አብ ተፈሪ)

«ጥላሁን አርቲስት አይደለም፤ ራሱ አርት ነው፤ ጥላሁን ሳይዘፍን የሚደመጥ ሰው ነው። እርሱን ገና መድረክ ላይ ሲያዩት ማልቀስ የሚቃጣቸው ብዙዎች ናቸው። ብቻ ጥላሁን የሰራቸው ስራዎችም ሆኑ ሌሎቹም ነገሮች ተደማምረው አንድ ትንሽዬ የመድረክ አምላክ ፈጥሯል» (ጋዜጠኛ ደረጄ ደስታ)

«ጥላሁን ነፍስ ያለው ሕያው ሃውልት ነው። በተለያየ ርዕስ የሁሉንም ህይወት እየዘፈነ ብዙ የኖረ ሰው ነው። ለዚህ ነው ጥላሁን ብዙ፤ ለኛ ደግሞ አንድ ስሙ ጥላችን ነው፤ በርሱ ተወደናል፤ በርሱ ተከብረናል » (አርቲስት ነዋይ ደበበ)

«ዘወትር ወደ መኝታዬ ከመሄዴ በፊት አንድ የጥላሁንን ሙዚቃ መስማት አለብኝ።» (ድምፃዊ ታምራት ሞላ)

«ከብዙዎቹ የአገራችን ታዋቂ ድምፃውያን ጋር አብሬ ሰርቻለሁ። ጥላሁን አንድ ካሕን ቤተ መቅደስን የሚያከብረውን ያህል መድረክን የሚያከብር ድምፃዊ ነው፤ ከመድረክ በፊት ሳጫውተው ቆይቼ ልክ ሙዚቃው ሲጀመርና መድረኩን ሲረግጥ ይቀየርብኛል። ሰውነቱም፤ ውስጡም፤ አይኑም ይለወጣል። ይህንን ሌሎቹ ላይ አይቼው አላውቅም።

«ሁሉም አርቲስቶች በየራሳቸው ችሎታና በየራሳቸው የድምፅ አወጣጥ በመዝፈን አድማጭን ይማርካሉ። ጥላሁን ገሰሰ ግን ድምፁን ከግጥሙ፤ ግጥሙን ደግሞ በውስጥ መንፈሱ አዋሕዶ ከአካላቱ እንቅስቃሴ ጋር አቀነባብሮ ሶስቱን በአንድ ጉልበት እንደመብረቅ የሚያሰራጭ ስሜት ያለው ድምፃዊ አላየሁም »

«ጥላሁን ገሰሰ ፈፅሞ የጥቅም ሰው አልነበረም፤ በጣም የሚገርመኝ ነግር ይህ ነው። አንድ ወቅት ላይ ሳናግረው አንተ እኮ ንጉስ መሆንህን ታውቀዋለህ? አልኩት። እርሱ ግን የምቀልድበት ነው የመሰለው። በዚህ የድምፃዊያን ንጉስነቱ ሊያገኝ የሚገባውን ጥቅም ለማግኘት እንኳን የሚጓጓ ሰው አልነበረም። ይህ ባህሪው በጣም ይገርመኛል። ብዙዎቹ የአገራችን አርቲስቶች ብልጭ ብለው ድርግም የሚሉት ቶሎ ገንዘብ፤ ሃብት፤ መኪና አግኝቶና ተዝናንቶ ይከስማል። አብዛኞቹ የጥቅም ጉዳይ ይጥላቸዋል። ጥላሁን ገሰሰ በዚህ ድምፁ ገንዘብ ለማግኘት የጓጓበት ጊዜ እኔ እስከማውቀው ጊዜ ድረስ አልነበረም። (ታዋቂው የቲያትር ደራሲ፤ አዘጋጅና ተዋናይ ጌታቸው አብዲ)

«ጥላሁን በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሱዳን፤ በሱማሊያ፤ ባጠቃላይ በምስራቅ አፍሪካ እጅግ ተወዳጅ የነበረ ታላቅ የሙዚቃ ሰው ነበር።
(የቀድሞ የስራ ባልደረባው ታዋቂው ኤርትራዊ ድምፃዊ በረከት መንግስተ አብ)

<<ክቡር ዶ/ር ጥላሁን ገሰሰ፤ ከአፅናፍ አፅናፍ እንደተወርዋሪ ኮኮብ በድምፁ የናኘ፤ የረቀቀ የጥበብ ክህሎቱን ያስመሰከረ፤ ባማረ ቅላጼ ውብና መሳች ዜማዎቹ፤ በሚያማልሉና በማይሰለቹ ግጥሞቹ የአ ዕላፍ ቀልብን የገዛ፤ ለግማሽ ም ዕተ አመት በላይ ክብርና ተወዳጅነትን ያተረፈ፤ የመድረክ እውቅና ድንቅ ከያኒ ብቻ ሳይሆን የሃበሻ የሙዚቃ ንግስናን ዘውድ የደፋ ታላቅ የጥበብ ሰው ነበር።» (የ ኤርትራ ቴሌቭ ዥን የጥላሁንን ሞት አስመልክቶ ከሰራው ድንቅና የተዋጣለት ዘገባ የተቀነጨበ) <<የሕይወቴ አንድ አካል ጎድሏል፤ እኔ ከንግዲህ ሙሉ አይደለሁም። የኔ ሙሉነት በጥላሁን ነበር።» የጥላሁን የቅርብ ወዳጅ አርቲስት ሙሃሙድ አሕመድ ጥላሁን ሲሞት በሰጠው አስተያየት) (ይህን አርቲክል ቢያነቡት ይጠቀማሉ - እዚህ ጋር ይጫኑ)

Go toTop