አንዳንዴ ኑሯችን በራሳችን እንድንቀልድ ያስገድደናል (ዳዊት ከበደ ወየሳ)

(ዳዊት ከበደ ወየሳ)

አንዳንዴ ኑሯችን በራሳችን እንድንቀልድ ያስገድደናል:: ካለፉት በርካታ አመታት ጀምር በአዲስ አበባ የሚታየውን የመብራት መቆራረጥ የተመለከተ ሰው በሙሉ ያዝናል:: ይህ ሃዘን ወደ ብሶት ቁጣ ተቀይሮ ሰሞኑን በተከታታ ህዝቡ በመብራት ሃይል ላይ የተቃውሞ ሰልፍ በማድረግ ቁጣውን እየገለጸ ነው:: አንድነት ፓርቲም ይህን አስመልክቶ “የ እሪታ ቀን” ብሎ የሰየመውን የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀምሯል:: እኛ ከውጭ ሆነን ነገሮችን ስንመለከታቸው እውነት የማይመስሉ እውነቶችን እያየን መገረማችን አልቀረም:: ይህንን ግርምት በቀልድ ቢጤ ብናዋዛው ብለን ስናስብ ደግሞ የሜትሮሎጂ አየር ትንበያ ታወሰን:: መብራት ሃይል በሜትሮሎጂ ዜና አይነት የሰሞኑን የመብራት መጥፋት እና መጥፋት ዘገባ ምን ብሎ ቢያቀርብልን ይገርመናል:: እስኪ በራሳችን እየሳቅን የመብራት ሃይልን… ሜትሮሎጂያዊ ዜና ከዚህ በታች እናንብብ::

የሰሞኑ የአዲስ አበባ የመብራት ሃይል… ይቅርታ የመጥፋት ሃይል ትንበያ ከዚህ በመቀጠል ይቀርባል:: በሰሜን አዲስ አበባ… ከበላይ ዘለቀ ጎዳና እስከ ፒያሳ፣ ውቤ በርሃ፣ አራዳ፣ ዶሮ ማነቂያ፣ ሰራተኛ ሰፈር፣ ከቸርችል ጎዳና እስከ ቴዎድሮስ አደባባይ ድረስ መጠነኛ የሆነ የመብራት መቆራረጥ ይደርሳል:: ከዚያ ወረድ ብሎ በስቴዲየም እና አካባቢው, መስቀል አደባባይ, ከእስጢፋኖስ እስከ መገናኛ 22 ማዞሪያ እና ኮተቤ ድረስ… እንዲሁም በካዛንቺስ አካባቢ ደብዛዛ እና ፈዛዛማ የመብራት ብርሃናት ይታያሉ::

በቦሌ እና ቦሌ ቡልቡላ መብራት እንደበጋ መብረቅ ብልጭ ድርግም ይላል:: ከላፍቶ እስከ ሳሪስ; ወሎ ሰፈር፣ ጎፋ ማዞሪያ፣ ቄራ፣ ሳር ቤት፣ እንዲሁም ከአየር ጤና እስከ ሜክሲኮ አደባባይ ነጎድጓዳማ የመብራት መቆራረጥ ያጋጥማል:: በጨርቆስ እና አካባቢ… እንደከዚህ ቀደሙ ደረቅ አየር እና ድፍን ጨለማ ሆኖ ይሰነብታል::

ተጨማሪ ያንብቡ:  ከማግለል ማሳተፍ ይቅደም! (ልጅ ተክሌ በኢሳት ላይ ላቀረበው አስተያየት የተሰጠ ምላሽ)

የአዲስ አበባ ምእራባዊ ዞን… ከተክለሃይማኖት ሰፈር ጀምሮ በአብነት አድርጎ እስከ ሰባተኛ እና መርካቶ ድረስ፣ መሳለሚያ፣ ኮልፌ ከዊንጌት እስከ ቡራዩ ድረስ ምንም አይነት የኤሌክትሪክ ስለማይኖር ከመብራት አደጋ ነጻ ይሆናሉ::

በመሆኑም ክቡራን ደንበኞቻችን፤ በተለይም የንግዱ ህብረተሰብ ይህንኑ አውቆ አካባቢ በካይ የሆኑ የናፍጣ ጄነሬተሮችን እንዲጠቀም እናሳስባለን:: የባንክ አገልግሎት ሰጪዎች፣ የኮምፒዩተር ቤቶች… መብራት ቢመጣም እንኳን ኔትዎርክ ስለሌለ፤ ጽጉር ቤት እና ምግብ ቤቶችም… መብራት ብንሰጣችሁ ውሃ ስለማይኖር፤ ይህንን ተግዳሮት ግምት ውስጥ በማስገባት ነፋሻማ የሆነውን ቫት እና መብረቃማውን የሽያጭ ታክስ በመክፈል የዜግነት ግዴታችሁን እንድትወጡ ከወዲሁ እናሳስባለን::

በአጠቃላይ አዲስ አበባ እና ሌሎች ከተሞች ምሽቱን ጧፋማ፣ ኩራዛማ እና ሻማማ በመሆን ይሰነብታሉ:: ዛሬ ከሳተላይት ያገኘነው ተንቀሳቃሽ ምስል እንደሚያሳየው… አዲስ አበባ ከላይ ወደ ታች ስትታይ እንደክሪስማስ ዛፍ ብልጭ ድርግም ትላለች:: በዚህም ምክንያት ምሽት ሲሆን; አዲስ አበባን በአነስተኛ አውሮፕላን የሚጎበኟት ቱሪስቶች ቁጥር በእጥፍ ጨምሯል:: ከዘርፉ የሚገኘው የገቢ መጠን በመጨመሩ መንግስት ለዚህ አዲስ የስራ መስክ ትኩረት በመስጠት የማበረታቻ ገንዘብ እንደሚመድብ አስታውቋል:: ለስራውም መሳካት… መብራት ሃይል የሰፈር መብራቶቹን በፈረቃ በማብራት እና በማጥፋት; ምሽቱን “በብልጭ ድርግም” የሚያደምቀው መሆኑን በደስታ ገልጿል::

Share