ረቡዕ፣ ሚያዝያ ፳ ፩ ቀን ፳ ፻ ፲ ፰ ዓ. ም. (04/29/2026)
ጭምቅ ሃሳብ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ የሥልጣን ዘመናቸው እየረዘመ ነው። ረዘመ የሚለውን መመዘኛ፤ በሕዝቡ ላይ እየደረሰ ካለው በደል፣ በአገራችን ሰላም ካለመኖሩና የአገራችን ሀብት በጥቂቶች እየተጋፈፈ፣ አብዛኛው ሕዝብ በረሃብ አለንጋ እየተቆላ፤ ከመሆኑ አኳያ ነው። በዚህ ጽሑፍ፤ በጣም አጭር በሆነ መንገድ፤ የአክራሪ ኦሮሞ ገዢ ቡድን ቁንጮ የሆነው አብይ አሕመድ፤ እንዴት ወደ ሥልጣን እንደወጣ፣ አስተዳደሩ ምን ዓይነት እንደሆነ፣ እንዴት በሥልጣን ላይ እየቆዬ እንደሆነ፣ የወደፊቱ ምን እንደሚመስል፣ እና መጨረሻው ምን ሊሆን እንደሚችል ተተንትኗል። በማጠቃለያም፤ የአብይ አሕመድ መጨረሻ፤ እንደ ሃንጋሪው ቪክተር ኦርባን ነው ወይንስ እንደ ሶሪያው በሺር አል አሳድ? የሚለው ተመላክቷል። ቪክተር ኦርባን፤ በሕዝብ ድምጽ ተቸንፎ ሥልጣኑን ያስረከበ፤ የሃንጋሪ አምባገነን ነበር። በሺር ሃፊዝ አል አሳድ፤ ከአባቱ ከሃፊዝ አል አሳድ፤ እንደ ርስት የአገር መሪነቱን ሥልጣን ተረክቦ፤ ልጁን እንዲተካው እየኮለኮለ፤ “በሥልጣኔ የመጣ አገር ገደል ትግባ!” በማለት፤ እስከመጨረሻው ድረስ የሶሪያን ወጣት ወደ ጦርነት እየማገደ፣ በመጨረሻ በአማጺያን የትጥቅ ትግል ተቸንፎ፤ ካገር የወጣ አምባገነን ነበር። አብይስ?
መግቢያ
በየካቲት ፲ ፱ ፻ ፷ ፮ ዓ. ም.፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት ወጥቶ፣ የስርዓት ለውጥ ለማድረግ ተነቃነቀ። በወቅቱ የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ቢወድቅም፤ ሕዝቡ ተደራጅቶ ሥልጣን የሚወስድበት የራሱ የሆነ መንገድ ባለማዘጋጀቱ፤ በበቦታው ተደራጅቶና ጠመንጃ ታጥቆ የነበረው የጦር ሠራዊቱ፤ ሥልጣኑን ነጠቀ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ፤ ላለፉት ሃምሳ ሁለት ዓመታት፤ አገራችን ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የተገደሉበት፣ በዚያው ልክ ደግሞ የተሰደዱበት፣ በዚያው ልክም የደኸዩበት ሀቅ ነግሧል። በዚህ ወቅት፤ የኢትዮጵያዊያን ዕሴት የነበረው፤ ራስን የወገን አካልና የአገር ባለቤት አድርጎ የማስብ እምነቱ ቀረና፤ በግለሰብ የራስን ህልውና መጠበቅና ውሎ ለማደር መጨነቅ፤ ቦታውን አፈራግጦ ያዘ። ይሄን ኩነት በሚመለከት፤ ለወደፊት ብዙ ጥናት የሚደረግበትና ምሁራን የሚጨነቁበት ይሆናል። እኛ ደግሞ አሁን በሂደቱ ውስጥ ያለን፤ ለምን እንደሆነ ከመመርመር ይልቅ፤ የዛሬን ለማለፍ ለየራሳችን ስንሯሯጥ እንገኛለን! አብዛኞችን ማለቴ ነው። ለምንድን ነው በ፲ ፱ ፻ ፷ ፮ ዓ. ም. የሽግግር መንግሥት፣ ቢያንስ እንኳን ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት ያልተቋቋመው? ከዚያ ወዲህስ ወቅቱን የጠበቀ የሽግግር መንግሥት ለማቋቋም አመቺ ሁኔታዎች አልተፈጠሩም ወይ? ለምን? ከተፈጠሩስ ለምን አልተጠቀምንባቸውም? የሚሉ ጥያቄዎች ወደፊት ይነሳሉ፤ አሁንም እንዲሁ። በወታደር ጠመንጃ የመጣውን የመንግሥቱ ኃይለማርያም አረመኔ መንግሥት ተከትሎ፤ አገራችንን ቁልቁል ወደ ተሳሳተ መንገድ ያስገባና ከመደብ ትግሉ ወደ ኢትዮጵያን በ“ብሔር” ጭቆና መንዝሮ፤ ከፋፋይ ወደሆነ አጥፊ ስርዓት የወሰደ፣ ራሱን “የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር!” ብሎ የሚጠራ ዘረኛ ቡድን፤ ሥልጣኑን ጨበጠ። ይሄን በዘር የተከፋፈለ እና በሙስና የተሞላ የአድልዖ ስርዓት በመቃወም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ “አትከፋፍሉን!” ብሎ፤ በአንድነት ተነሳ። በዚህም ጊዜ እንደ ፲ ፱ ፻ ፷ ፮ ዓ. ም.ቱ፤ እምቢ ብሎ ከተነሳው ሕዝብ እጅ፤ የዚሁ ገዢ ቡድን አካል የሆኑ ጥቂት ግለሰቦች ወጥተው፤ ሥልጣኑን ጨበጡ። ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ወደ ሥልጣን የወጣ አካል፤ ውሎ አድሮ ሥልጣኑን አንድ ግለሰብ ሰብስቦ ይወስደዋልና፤ አሁን አብይ አሕመድ ሥልጣኑን የግሉ አደርጎታል። ኢትዮጵያዊነትን በማውለብለብ ሥልጣኑን ካደላደለ በኋላ፤ የራሱን አገልጋዮች በኃላፊነት በየቦታው አስቀምጦ፤ “ኦሮሞ!” ሆነ። ከዚያም ሥልጣኑ የግሉ የሆነ፤ የአክራሪ ኦሮሞዎች መንግሥት መሠረተ። እስኪ ይሄ ሂደት፤ ታሪኩን እና የወደፊቱን እንመርምር።
እንዴት ወደ ሥልጣን መጣ?
የመጀመሪያው ጥያቄ፤ አብይ አሕመድ እንዴት ወደ ሥልጣን መጣ? ነው። የት እንዳደገና የጥንቁልናውን ግንዛቤ የት እንዳገኘ፣ ሰባተኛ ክፍል ያላጠናቀቀ እንዴት የዶክትሬት ባለቤት እንደሆነ ማስረዳቱን እንተውና፤ አብይ አሕመድ የ“ትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር” መንግሥት ኮሎኔል ከመሆኑ እንነሳ። በየ“ትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር” ስለላ ክፍል ያደገና በዚሁ ተቋም የተካነ ነው። የኦህዴድ መሪ ሆኖ፤ በመለስ ዜናዊ ስንብት ምክንያት በተከፈተው ቀዳዳ፣ ኃይለማርያም ደሳለኝን ተክቶ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ ወሰደ። ሕዝቡ የጠየቀው፤ “አትከፋፍሉን!” ነበር። ሕዝቡ የፈለገው፤ “ሰላም!” ነበር። “ኢትዮጵያ!” “ኢትዮጵያ!” እያለና አረንጓዴ ብጫ ቀዩን የአገራችንን ሰንደቅ ዓላማ እያውለበለበ፤ የሕዝቡን አቅል ሳበ። ቀጥሎም፤ ኢትዮጵያ የሚለውን ፅንሰ ሃሳብና እምነት የያዙትን ማጥፋት ያዘ። በሂደቱም የአክራሪ ኦሮሞ ክፍልን አቀፈና አሳደገ። ከዚያም፤ በዓለም ዙሪያ እንደታዩት የአምባገነኖች ተግባር ሁሉ፤ ማንኛውንም ግለሰብ ሆነ ተቋም፤ “ይቃወመኛል!” ያለውን፣ በተለይም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት አጥብቆ የያዘውን ክፍል፤ ማሳደድና ማጥፋት ያዘ። በዐማራ ላይ የያዘው ዘመቻ፤ የዚህ አካል ነው።
እንዴት ነው አስተዳደሩ?
አብይ አሕመድ የራሱ የሆነ የአስተዳደር ዘይቤ የለውም። ከ“ትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር” የተረከበውን በአካባቢ በቋንቋና በትውልድ ትስስር የተመሠረተ አገር ከፋፋይ የፖለቲካ ፍልስፍናና የአስተዳደር መመሪያ፤ ለራሱ ሥልጣን ማራዘሚያ በሚረዳው መንገድ ተጠቀመበት። እዚህ ላይ መሰመር ያለበት፤ አብይ፤ ለራሱ ለአንድ ግለሰቡ ሥልጣን እንጂ፤ ለኢትዮጵያዊያን በጠቅላላ ሆነ ለኦሮሞ በተለይ የቆመ እንዳልሆነ ነው። በርግጥ በዙሪያው፤ እሱን የመሰሉ አገልጋዮችን ከኦሮሞና ከሌሎችም አካባቢዎች ቡችሎቹ ቢኮለኩልም፤ የሥልጣኑ ብቸኛ አውታር፤ አብይ ነው። በአገራችን ዙሪያ የተፈጠሩት የክልል በረት መሪዎችን ሿሚና ሻሪ ራሱ ነው። እናም በሙሉ የሱ አገልጋዮችን በየቦታው መድቧል። ይሄ የአንድ ሰው አምባገነን አስተዳደር ነው።
እንዴት ነው በሥልጣን ላይ እየቆዬ ያለው?
አገር በውስብስብ ሁኔታ ውስጥ ስትገባ፤ የሥልጣን ክፍተት ይከሰታል። የአገሪቱ ኢኮኖሚ መድቀቅ፣ የሥራ አጦች ብዛት፣ በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት የሕዝቡ ኑሮ አሽቆልቁሎ ሲወርድና በገዢውና በተገዢው መካከል አብሮ የመሄድ ችግር ሲፈጠር፤ የአተዳደር ቀውስ ይነግሣል። ያን ጊዜ ገዢው የመግዛት ፈቃዱ ብቻ ሳይሆን ችሎታውም ጥሎት ይሄዳል። በየካቲት ፲ ፱ ፻ ፷ ፮ ዓ. ም.፣ ግንቦት ፲ ፱ ፻ ፹ ፫ ዓ. ም.፣ እና ሚያዝያ ፳ ፻ ፲ ዓ. ም. የሆነው ይሄ ነው። በነኚህ ሶስት የተለያዩ ጊዜዎች፤ ቦታውን ሊሞሉ የቻሉት፤ በቦታው የሁኔታውን አጋጣሚ የተጠቀሙ ብልጦች ናቸው። በመጀመሪያው፤ ሕዝቡ መስዋዕት ከፍሎ የተነሳበትን ንቅናቄ፤ ደርግ የበትረ ሥልጣኑን ወሰደ። በሁለተኛው፤ ሕዝቡ ልጆቼን ላንተ ጦርነት አልገብርም! ብሎ ባመጸበት ጊዜ፤ መለሰና ግብረ አበሮቹ ክፍተቱን ሞሉት። በሶስተኛው ደግሞ፤ መለስ ሞቶ ሕዝቡ በየቦታው ሲነቃነቅ፤ በኃይለማርያም ደሳለኝ ተሸጋግሮ አብይ ተፈናጠጠበት። በመጀመሪያ ሥልጣኑን ሲጨብጥ፤ ሕዝቡ የፈለገውን አረንጓዴ ብጫ ቀዩን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማ በማውለብለብና “ኢትዮጵያ!” “ኢትዮጵያ!” በማለት፤ በመላ አገራችን ተቀባይነትን አገኘ። ተኩላ የበግ ቆዳ በላዩ ላይ ቢያጠልቅም፤ ያው ተኩላነቱን አይለውጥምና፤ ውሎ አድሮ፤ “ኢትዮጵያ” “ኢትዮጵያዊነት” የሚሉ ቃላትም ሆነ ግንዛቤ አሽቀንጥሮ ጣለ። ከዚያም የግል አምባገነንነቱን፤ በሌሎች አገሮችና በተለያዩ ጊዜያት እንደተተገበረው ሁሉ፤ ቀስ በቀስ ሥልጣኑን በጁ አደረገ። እንግዲህ ከዚያ በኋላ ትርክት እየፈጠረ፤ ሰባተኛው ንጉሥ፣ እናቴ ጠቅላይ ሚኒስትር ትሆናለህ ብላኛለች፣ እኔን አምላክ ለዚህ የፈጠረኝ! የሚል በተነ።
ከላይ እንደጠቀስኩት፤ ይሄንን ሂደት ሲመራ፤ “አብይ!” የሚለው አገር፣ “አብይ!” የሚለው ሕዝብ፣ “አብይ!” የሚለው ታሪክ አልፎም አምላክ ሆነ። እንዲህ ያሉ ገዢዎች በዙሪያቸው የሚኮለኩሉት፤ አሜን ባዮች፣ ለሆዳቸው ያደሩ፣ ትክክል እና ትክክል ያልሆነ ለሚለው ግድ የሌላቸው፣ እናም የዛሬን እንጂ የትናንት ወይንም የነገ አርቆ አስተዋይነቱ የሌላቸውን ነው። እኒህ፤ ለሆዳቸው የሚበጀውን እና የሾማቸው የሚፈልገውን መናገርና ማድረግ ስለሆነ፤ በየዕለት ተዕለቱ ይሄንን ሲተገብሩ ይውላሉ። በዚህም ሿሚያቸውን ከተጨባጩ እውነታ ያገልሉታል። ነጋሪዎቹ ከአክራሪ ኦሮሞ ቅርንጫፍ የተሰበሰቡ በመሆናቸው፤ አፍቃሪ ኦሮሞና ፀረ ዐማራ አባዜያቸው፤ ወደ መጨረሻ መቃብራቸው ይወስዳቸዋል። አብይ መስማት የሚፈልገው ይነገረዋል። ያንን እና ያንን ብቻ ያምናል። በዚህም እውነት ሃሰትን አቸንፎ እስኪወጣ ድረስ፤ ሥልጣን ላይ ይቆያል። ይህ ነው የአብይ በሥልጣን ላይ መቆየት ጠቅላላ ትርጉሙ።
የወደፊቱ ምን ይመስላል?
የሥልጣኑ ድልድል በዚህ ሁኔታ እያለ፤ የሕዝቡ ተጨባጭ የኑሮ ሁኔታ ደግሞ፤ አስተዳደሩ በሚያደርሰው በደል፣ በአገራችን የነገሠው የተበላላጭ “የክልል በረቶች” ስምሪት፣ እና የዓለም አቀፉ የፖለቲካ ውጥረት፤ በአገራችን ያለውን ሁኔታ ሊያስቀጥለው አልቻለም። ፋኖ የዚህ ሁሉ ውጤት ነው። በደቡብም ፋኖ ተነስቷል። የጊዜ ጉዳይ እንጂ፤ በመላ ኢትዮጵያ ፋኖ ያብባል። በገዢው ቡድን ተጠልለው ያሉ አገልጋዮች፤ ሚዛን ዓይተው ወዳዘመመው ያንኳትታሉ። ሕዝቡ ኑሮው እየከፋበት ነው። አሁን ያለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ፤ ባለበት መቀጠል አይችልም። ውጥረቱ የከረረ ነው። እናም አንድ ቦታ ይበጠሳል። የሚታየው ተስፋ ሳይሆን፤ ጭንቀት ነው። በየከተማው ያለው መሪ ያጣ የሚመስለው ያስተዳደር ሂደት፤ ግለሰብ መሪዎች፤ ራሳቸውን ለመጥቀም፤ ሕጉን ወደ ጎን በመተው፣ የራሳቸውን ሥልጣን ለጥጠው በማስፋት፣ ሕገ ወጥ ድርጊቶችን ይሠራሉ። ድህነቱ እያየለ ይሄዳል። በተለይም ከቤንዚን ጋር የተያያዙ ነገሮች በሙሉ ዋጋቸው ያሻቅባል። እናም ሙስና፣ አድልዖ፣ ልመና፣ በጠራራ ፀሐይ ዝርፊያ እየበዛ ይሄዳል። ብሎም ገዢ መግዛት የሚያቅተው ሀቅ ይፈጠራል። ተገዢም በገዢው ላይ እምነት ማጣት ብቻ ሳይሆን፤ ሕጉንም መጣስ፣ ራሱን የሁሉ ነገር ማዕከል አድርጎ በራሱ መተዳደርና ገዢውን ለማስወገድ ይጥራል። ይህ ሊሆን የሚችል ተብሎ የሚገመት ብቻ ሳይሆን፤ እየሄድንበት ያለው መንገድ የሚወስደን መዳረሻ ነው።
መጨረሻው ምን ይመስላል?
እንግዲህ አገር ያለ መሪና ተመሪ፣ አስተዳዳሪና ተስተዳዳሪ፣ ሕግና ሕግ አስከባሪ፣ . . . ሰላም ኖሮ፣ ሕዝቡ አስተዳዳሪዎችን የኔ ብሎ መቀጠል አይችልም። የንጉሠ ነገሥቱ የመጨረሻ ወቅት የነገረን ይሄንኑ ነው። የደርግም መጨረሻ ያው ነበር። የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባርም፤ ያንኑ ነበር የተከተለው። አሁን በዚያ ሁኔታ ላይ ነን። አይቀሬው ይመጣል፤ ነገር ግን፤ ይህ አይቀሬ ምን ይመስላል? ነው ጥያቄው። አብይና ቁንጮ የሆኑት የአክራሪ ኦሮሞ ገዢው ቡድን አባላት፤ ያጋፈፉትን የሕዝብ ገንዘብ እስካሁን ብዙ እንዳስወጡና አረመኔው መንግሥቱ ኃይለማርያም መሳሪያ ልግዛ ብሎ ያገራችንን ገንዘብ አሟጥጦ እንደፈረጠጠ፤ ይዘው ይፈረጥጡ ይሆን? ወይንም ተቸንፈናል! ብለው ሥልጣን ያስረክቡ ይሆን? እዚህ ላይ፤ ሕጉም እኔ! አገርም እኔ! ዶክተርም እኔ! የነጋዴ መሪም እኔ! የሃይማኖት አዋቂና አባትም እኔ! ከሚል አእምሮ፤ ይሄን ያስባል! ብሎ መገመት ያስቸግራል። ይልቁንም እኔ አምላክ ነኝ! እናም እኔ ያልኩትን አድርጉ! የሚል ትዕዛዝ በመሥጠት፤ ብዙ ያገራችንን ወጣቶች በጦርነት የሚማግድ ሊሆን ይችላል። ግራም ነፈሰ ቀኝ፤ ቀኑ እየተቆጠረ ነው።