በመጀመርያው ቀን ሰርቶ ቢዘረጋት፣
ፍጥረታት ይሙሉብሽ ብሎ ቢመርቃት፣
ተጉያው አምልጣ ሳጥናኤል ያቀፋት፣
ማተብ የቦጨቀች አለም ደሊላ ናት፡፡
ጠዋት ተእንቅልፍ ንቂ ማታ ተኝ ቢላት፣
ቀኑን ሌሊቱንም ቅንዝንዝ ያረጋት፣
ለሆስታና እርጋታ ጥሞና የራቃት፣
ጠልፋ የምትጥል አለም ክልፍልፍ ናት፡፡
ፍሬ እንድታፈራ ዘሩን ቢዘራባት፣
አረም አሚካላ በቅሎ እሚፋፋባት፣
አለም እንደ ጠሮ አስራ እምትይዝ ናት፡፡
ከተራራ አውጥቶ እያሳየ ዝቅዝቅ፣
ክርስቶስን ሳይቀር ተፈተን ያለባት፣
አለም ከተማዋ የሳጥናኤል ግዛት፣
አሸብራቂ አብለጭላጭ ኃጥያት የሞላባት፡፡
አረንጓዴ ለብሳ ብትመስል ያማረባት፣
ውስጧ ሲከፈት ግን ባዶና ደረቅ ናት፣
ዓለም አባካኝዋ በረከት የራቃት፡፡
አርቴዋን ለብሳ ብታውድ በመአዛ፣
ልብሷ ሲገፈፍ ግን ሽታዋ አያስጠጋ፡፡
ወደ ፊት ተጓዘች ሰለጠነች ሲሏት፣
ፊቷን ዘወር አርጋ ወደ ኋላ እምትነጉድ፣
አለም ወረተኛ ቅጥ አንባር የጠፋት፡፡
ከጥንት እስከ ዛሬ ታሪኳ ሲዳሰስ፣
አዳምን የጣለች አስገምጣ በለስ፣
ክርስቶስን አስራ የፈታች በርናባስ፣
በእውነት መቃብር ላይ የምታነግስ ውሸት፣
አለም ፍርደ ገምድል ሚዛንም የሌላት፡፡
በዘረፋ ስርቆት በሙስና አክብራ፣
ቱጃሩን ዲታውን እንቅልፍ የምትነሳ፣
በጭካኔ አረቄም ስልጣንን አስክራ፣
ገዥን አንቦቅቡቃ ጥላ እምታስፈራ፣
አለም አጋም ቀጋ ደለቶም የምትወጋ!
በወርቅ በአልማዝ ጌጧ እያንበረከከች፣
ስንቱን ምሁር ነኝ ባይ እግሯን ያሳጠበች፣
ባለ ዲግሪ አስተውል አለም አዋራጅ ነች፡፡
በዛቢያዋ እንደ እንዝርት ዑደት እየዞረች፣
ሽንጥና ወገቧን እያውረገረገች፣
አስርቱ ቃላትን ሕግን ያስቦጨቀች፣
ቅስና አስፈርሳ ቆብንም ያስጣለች፣
ካህን ተአለም ራቅ የሰይጣን እጅ ነች፡፡
ፍቅረኛ ልብ ወዳጅ መስላ እየቀረበች፣
የስንት ጀግና ሱሪ ቀበቶ ያስፈታች፣
የሳምሶንን ፀጉር ተኝቶ የላጨች፣
ሕዝብ ሆይ ተገንዘብ አለም ደሊላ ነች፡፡
በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)
ሐምሌ ሁለት ሺ አስራ ስምንት ዓ.ም.