AMHARA ADVOCACY GROUP IN EUROPE
amharaadvocacy.eu · editors@amharaadvocacy.eu

ለፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፣
እንደ ታዋቂ የአካዳሚክ እና የአእምሮ ሐኪም፣ ስለ ማህበራዊ ሳይኮሎጂ እና የግጭት አፈታት ቅድመ ሁኔታዎች ያለዎት ግንዛቤ ከጥያቄ የሚገባ አይሆንም። በብሔራዊ የውይይት ሂደት ወቅታዊ አቅጣጫ አስመልክቶ በቀጥታ ለእርስዎ ለመጻፍ የተገደድንበት ዋናው ምክንያት ካልዎት የኃላፊነት ድርሻ የሚይዙት አቋም ወሳኝ በመሆኑ ነው።
የሰላም መሰረታዊ ምሰሶዎች በሌሉበት ሁኔታ እውነተኛ እና ተአማኒ ብሔራዊ ውይይት ሊደረግ እንደማይችል ግልጽ የሆኑ እውነታዎችን አፅንዖት መስጠት አለብን።
- ሀሳብን የመግለጽ ነጻነት ማክበር፡- ተዓማኒነት ያለው ውይይት ለማካሄድ መሰረታዊ መብቶች መጠበቅን ይጠይቃል። በአሁኑ ሰዐት ካባቢው በከፍተኛ የፍርሃት ድባብ ውስጥ ይገኛል፤ በመሆኑም አገዛዙን የሚተቹና ተቃውሞ የሚያቀርቡ በእስር፣ በስቃይ እና ከህግ አግባብ ውጭ ለሚወሰዱ እርምጃዎች ሰለባ ሆነዋል። ፍትህ ያላገኘው የኢንጂነር ስመኘው በቀለ ግድያ፣ ያለ መከሰስ መብታቸው ተገፎ የታሰሩ የፓርላማ አባላት አቶ ዮሐንስ ቧያለው እና አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ ወይዘሮ መስከረም አበራ፣ ጋዜጠኛ ሲሳይ ጎበዜ፣ አቶ ታዲዎስ ታንቱና እና ሌሎች በርካታ የህግ ጥሰቶች መሬት ላይ ላለው አሳዛኝ እውነታ በእማኝነት ያገለግላሉ።
- የህሊና እስረኞችን መፈታት፡- በቀና መንፈስ የሚደረግ ድርድር ቢሆን ኖሮ የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት ባስፈለገ ነበር። የችግሩ ባለድርሻ የሆኑ ምሁራን፣ ጋዜጠኞች እና ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን አስሮ፣ አገዛዙ ራሱ የፈጸመውን ወንጀል “እኛ ፈጽመናል” ብለው በግዳጅ ፈርመው ከእስር እንዲለቀቁ በማስጨነቅ ላይ ባለበት ወቅት የሚተላለፍ የምክክር ኮሚሺን የአንድ ወገን ውሳኔ የሚተገብር አካል ነው፤ ወደፊትም በህግ ያስጠይቃል።
- ሊሂቃንን ያካተተ ድርድር፡- አገር አቀፍ የለውጥ እና የሽግግር ውይይት ሁሉንም ቁልፍ የፖለቲካ ተዋናዮችን ተሳትፎ ይጠይቃል። ሆኖም ግን ከብልጽግና ካድሬዎችና ደጋፊዎች ውጭ የሆኑ ተቺ እና ባለድርሻ ምሁራንን ያገለለ በመሆኑ ዘላቂ መፍትሄ ሊያመጣ አይችልም። በተጨማሪ አገዛዙና ባለስልጣናቱ በተመካካሪዎች ላይ የሚፈልጉትን ውሳኔ ብቻ እንዲያሳልፉ በማስፈራራትና በገንዘብ ጫና በመፍጠር ላይ መሆናቸው በገሀድ እየታየና እየተሰማ ባለበት ወቅት፣ የሰብሳቢው ዝምታ እንደ መስማማት ይቆጠራል።
- በጠላትነት ተፈራርጆ የሚካሄድን ጦርነት ማስቆም፡- በክልሎች — በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል-ጉሙዝ እና በትግራይ — ውስጥ የሚነሱ ቅሬታዎችን በከባድ የጦር መሳሪያ እና በድሮን ጥቃቶች ምላሽ በመስጠት የሰው ህይወት፣ ሀብትና ንብረት እያወደመ ውይይት ሊካሄድም ሆነ ሊሳካ አይችልም። ለዜጎች ፖለቲካዊ ጥያቄና ተቃውሞ መግደልን የመጀመሪያ ምላሽ አድርጎ የወሰደ አገዛዝ፣ የድርድሩ ዓላማና ግብ የገጽታ ግንባታ እና ከጠቅላይ ሚኒስትርነት ወደ ፕሬዚደንታዊ ስርአት በመቀየር የአገዛዝ ዘመኑን ለማራዘም እንጂ ለዘላቂ መፍትሄ አለመሆኑ ግልጽ ነው።
በእነዚህና በሌሎች መዋቅራዊ እንቅፋቶች ምክንያት፣ ለአገዛዙ ካድሬዎችና ለተመረጡ ተጠቃሚዎች ብቻ የተወሰነ ውይይት የሰላም መንገድ ሳይሆን የስልጣን መጠቅለያ ዘዴ ነው።
የተከበሩ ኮሚሺነር፣ የአዕምሮ ውርስዎን ከግምት ውስጥ በማስገባት ይህ ሂደት ለኢትዮጵያ ህዝብ ወይም ለጠባብ የፖለቲካ አጀንዳ የሚያገለግል መሆኑን በጥልቀት እንዲያስቡበትና ትክክለኛውን ውሳኔ በመውሰድ ከትውልድና ከታሪክ ተጠያቂነት ራስዎትን እንዲታደጉ እናሳስባለን። ቢያንስ በዚህ ደረጃም ቢሆን፣ ጉዞው ወደ እርቅ የሚያሸጋግር ድልድይ ከመሆን ይልቅ እንደ አምባገነናዊ አስተዳደር ማንበሪያ መሳሪያ ሆኖ ከመታወስ አደጋ ላይ ከሚወድቅ ሂደት እራስዎትን እንደሚያገልሉ ተስፋ እናደርጋለን።
ከአክብሮት ሰላምታ ጋር፣
Amhara Advocacy Group in Europe (AAGE) · amharaadvocacy.eu