በሥልጣን ሽግግር ስም የርስት ወረራን ህጋዊ የማድረግ አደገኛ የፖለቲካ ስሌት
በዶክተር ሶስና ታደሰ
(የፖለቲካና ስትራቴጂያዊ ጥናት ክፍል)
መግቢያ፦ የ30 ዓመታት ዝምታ እና የዛሬው «ፍትሐዊ» መካሪነት ተቃረኖ
አቶ ልደቱ አያሌው «ጽምዶ እስከምን ድረስ?» በሚል ባወጡት መጣጥፍ፣ የብልፅግናን አገዛዝ በፍጥነት ለመጣል በሚል ሽፋን ከሕወሓትና ከቀጠናዊ ኃይሎች ጋር የሚደረገውን «ጽምዶ» (ትብብር) እንደ አወንታዊ የፖለቲካ ክስተት ለማስቆጠርና የርስት ጥያቄዎችን «ቀይ መስመር አታድርጉ፣ በስልት (Mechanism) ብቻ እንስማማ» ብለው ለመምከር ሞክረዋል።
ይሁን እንጂ ላለፉት 40 ዓመታት የወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ራያ ሕዝብ በሕወሓት የአፓርታይድ ስርዓት ሲጨፈጨፍ፣ ሲፈናቀልና ማንነቱ ሲካድ፤ አቶ ልደቱ አያሌው በሦስት አስርታት የፖለቲካ ዘመናቸው ለአንድም ቀን ድምፅ ሆነዋቸው አያውቁም።
ዛሬ ሕዝቡ በራሱ ደምና መስዋዕትነት ታሪካዊ ርስቱን ካስመለሰ በኋላ፣ አቶ ልደቱ «ወልቃይትና ራያን ቀይ መስመር አታድርጉት፣ ይሄ መመጻደቅ ነው» ብለው ለመሞገት የሚያስችላቸው ታሪካዊ ባለቤትነትም ሆነ ሞራላዊ የበላይነት የላቸውም!
እዚህ ላይ አንድ ሌላ ታሪካዊ ክህደት የፈጸሙበትን አጋጣሚ ማስታወስ እወዳለሁ፡፡ አቶ ልደቱ አያሌው፣ ሕወሓት በሁለተኛው ዙር ጦርነት ማለትም ሰኔ 2013 ጀምሮ ወደአማራ ክልል ወረራ መክፈቱን ተከትሎ፣ ከቀድሞው የኢሕዴን ሊቀመንበር ታምራት ላይኔ እና አቶ ያሬድ ጥበቡ ጋር በመሆን ‹‹ለሕወሓት የሰብዓዊ እርዳታ ኮሪደር ይከፈትለት›› በሚል የማኀበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ከፍተው እንደነበር ይታወሳል፡፡
በወቅቱ በጥላቻ የነደዱ የሕወሓት ታጣቂዎች አቶ ልደቱና ታምራት ላይኔ የተለዱበትን የላስታ ቀጠና፣ የጁ፣ ጋሸና በወረራ ይዘው ወደ ጎንደር ጋይንት እየተሻገሩ ነበር፡፡ በዚያ አስከፊ የጦርነት ወቅት እነዚያ በጥላቻ የነደዱ የሕወሓት ታጣቂዎች ከቆቦ ጀምሮ፣ ወልድያ፣ ኩል መስክ፣ ላሊበላ፣ ጋሸና፣ ወገል ጤና፣ ደላንታ፣ መቄት ንጹሃንን በጅምላ እየፈጁ፣ የ80 ዓመት አዛውንት ሳይቀር አስገድዶ መድፈር እየፈጸሙ ነበር፡፡
ይህን ማስታወስ ያስፈለገው ዋና ምክንያት፣ እነ አቶ ልደቱን በወቅቱ ይህን የጦር ወንጀል ከማውገዝ ይልቅ፣ በትግራይ ሕዝብ ስም ለሕወሓት የሰብዓዊ ኮሪደር በሁመራ በኩል ይከፈትለት፣ ከሱዳን የውጭ እርዳታ እህሎች ይግቡ የሚል የሸፍጥ ቅስቀሳ ላይ ነበሩ፡፡ በወቅቱ በነበረው ሁኔታ የሰብዓዊ እርዳታ ወደትግራይ መግባት ያልቻለው ሕወሓት በአማራ እና በአፋር ላይ ወረራ መክፈቱን ተከትሎ እንደሆነ ይታወሳል፡፡ እነ ልደቱ ግን የወልቃይት-ጠገዴ ጠለምትና ራያ ብሎም መላው የአማራ ሕዝብ ጉዳይ ግድ ሳይሰጣቸው “በሁመራ በኩል የሰብዓዊ እርዳታ ኮሪደር ይከፈት” የሚለውን የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻቸው ላይ ተጥደው ነበር፡፡
ይህ ታሪክ የመዘገበው እውነታ ነው፡፡ ይህ ክስተት ራስ ጠልነት ካልሆነ በስተቀር የሰብዓዊነት መለኪያ ሊባል አይችልም፡፡
እንዲህ አይነት የራስ-ጠልነት ታሪክ ያላቸው አቶ ልደቱ አሁን ደግሞ፣ ለአማራ የነጻነት ታጋዮች የባርነት ካምፕ የሆነውን ጥምዶ ዓላማው እንዲሳካ፣ የፋኖ ኃይሎች የርስት ጥያቄዎችን «ቀይ መስመር አታድርጉ፣ በስልት (Mechanism) ብቻ እንስማማ» ብለው ለመምከር ሞክረዋል።
ይህ አቀራረብ የአቶ ልደቱን ነባር የርስትና የማንነት ግዴለሽነት የሚያንፀባርቅ፣ የሕወሓትን መዋቅራዊ የጥፋት አቅም የሚያለሰልስ እና የአማራን ሕዝብ የሕልውና ትግል ወደ ሌላ የባርነት ካምፕ ለመንዳት የታለመ «የፖለቲካ አቋራጭ» (Political Shortcut) ነው።
1. «ትራንዚሽናል ኦፖርቹኒዝም» (Transitional Opportunism)፦ የልደቱ አያሌው አዲስ የፖለቲካ ካርታ
የአቶ ልደቱ መከራከሪያ መሰረታዊ ስህተት የሚጀምረው ከፖለቲካዊ ግቡ አወቃቀር ነው። ልደቱ የኢትዮጵያን ችግር «የሥልጣን ላይ አገዛዝን የመቀየር» (Regime Change) አጀንዳ አድርገው ብቻ ያዩታል። ለአቶ ልደቱ አገዛዙ ከተወገደና «ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት» ከተቋቋመ የፖለቲካው ስራ ተጠናቋል።
ነገር ግን የአማራ ሕዝብ እየታገለው ያለው በቀላሉ የሥልጣን ተዋናዮችን ለመቀየር ሳይሆን፣ ላለፉት 35 አመታት የተጫነበትን መዋቅራዊ የሕልውና አደጋ፣ የዘር ማጥፋትና የታሪካዊ ርስት ወረራ ለመቀልበስ ነው። ይህ ትግል አገዛዝን ለመጣል ብቻ የሚደረግ ሳይሆን ሥርዓትን ለመቀየር የሚደርግ ትግል ነው፡፡ የአማራ ሕዝብን የህልውና አደጋ ተጋላጭነት ያሳፈው ሥርዓት መዋቅራዊ ቅርጽ የያዘው ድኀረ-1983 በመሆኑ፣ ባለፉት 35 የኀልውናው አደጋ የሆነውን፣ የአገር ባለቤትነቱን የነጠቀውን ሥርዓት ለመገርሰስ የሚያድገው ትግል ነው፡፡
የአቶ ልደቱ ትረካ የሕልውና ጥያቄን ወደ ተራ «የስልጣን ሽግግር ፖለቲካ» (Transitional Politics) ዝቅ በማድረግ የትግሉን ማዕከላዊ አላማ ያደናግራል። ይህ እውነታ ዕድሜ ዘመኑን ከመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት (መአሕድ) ጀምሮ ላለፉት 30 ዓመታት በፖለቲካው ዓለም ከቆዩት አቶ ልደቱ አያሌው የተሰወረ ባይሆንም፣ ከ1966 ጀምሮ በአማራ ደም የሌሎች ሥልጣን ይቀደም የሚለውን ሀሳብ የሚጋሩት በመሆኑ የፈጠሩት የትግል ትርክት ማዛባት አንደሆነ እንረዳዋለን፡፡
2. የ«Mechanism» (ስልት) ማታለያ፦ የርስት ወረራን በዲሞክራሲያዊ ሽፋን የማፅደቅ ሴራ
አቶ ልደቱ በጽሑፋቸው፦ «በወልቃይትና ራያ ጉዳይ አማራ ወይም ትግራይ ይሁን በሚለው መፍትሔ ላይ አሁን መስማማት የለብንም፤ ይልቁንም በምን ስልት (Mechanism) እንዲፈታ መስማማት አለብን» ይላሉ። «ቀይ መስመር» የሚሉ አካላትንም «ይመጻደቃሉ» በማለት ይነቅፋሉ።
ይህ መከራከሪያ መዋቅራዊ የሆነ አደገኛ የፖለቲካ ወጥመድ አቅፎ ይዟል፦
- የ«Mechanism» አፓርታይድ፦ሕወሓት በ1980ዎቹ በወታደራዊ ሀይል የወሰዳቸውን የወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ራያ መሬቶች ላይ ከትግራይ ሰፋሪዎችን በማስገባት የስነ-ሕዝብ ምህንድስና (Demographic) ለውጥ አድርጓል። አሁን ላይ ቆሞ «በህዝበ-ውሳኔ ወይም በህገ-መንግስት ማሻሻያ እንፍታው» የሚል ስልት መቀበል ማለት፦ በወታደራዊ ወረራና በዘር ማጽዳት የተያዘን መሬት በዲሞክራሲያዊ ሽፋን ህጋዊ (Legitimize) ማድረግ ነው!
- የእጅ ማስያዝ አጣብቂኝ፦ሕወሓት ዛሬም ድረስ «ወልቃይትና ራያ የትግራይ ግዛቶች ናቸው፤ አንዲት ስንዝር አትቆረስም» እያለ በሚፎክርበት ሰዓት፣ የአማራን ሕዝብ ብቻ «ቀይ መስመር አታብዛ፣ በስልት ተስማማ» ማለት—የተወረረውንና የተጠቃውን ወገን ብቻ እጅ ማስያዝ (Asymmetric Disarmament) ነው።
💡 ሞጋች ጥያቄ 1፦
«በኃይልና በወረራ ተወስዶ ከፍተኛ የዘር ጭፍጨፉ የተፈጸመበትንና የስነ-ሕዝብ ስብጥሩ በወረራ የተቀየረን ርስት ‘በህዝበ-ውሳኔ ወይም በህገ-መንግስታዊ ስልት (Mechanism) እንፍታው’ የሚል ውል መቀበል፤ ቀድሞ የተፈጸመን የዘር ማጽዳትና የወታደራዊ ወረራ ውጤት በዲሞክራሲያዊ ሽፋን ማፅደቅ አይደለምን?»
3. “የፕሪቶሪያው ስምምነት” ተረት እና የሕወሓት የፖለቲካ ማደንዘዣ
ሕወሓት «በፕሪቶሪያ ወቅት ብልፅግና በአማራ ላይ አብረን እንዝመት ብሎ ጠይቆን እምቢ አልን» በሚል የሚያራግበው ትረካ፣ በወታደራዊ ተሸናፊነቱ ያጣውን የሞራል የበላይነት ለማስመለስ የተሰራ የሥነ-ልቦና ፕሮፓጋንዳ (Psychological Warfare) ነው።
በፕሪቶሪያ ስምምነት ወቅት (ጥቅምት 2015 ዓ.ም) ሕወሓት በከባድ ወታደራዊ ከበባና ውድቀት ውስጥ ነበረ። ከመቀሌ ውጭ ሁሉም የትግራይ ትልልቅ ከተሞች ተይዘውበት ነበር፡፡ መቀሌ በሰዓታት ውጊያ የመያዝ ዕድል እያላት፣ ሕወሓት የፈረመው “የፕሪቶሪያው ስምምነት” ለሕልውናው ሲል ተንበርክኮ እጁን የሰጠበት እንጂ፣ አቻ ሆኖ በጉልበቱ የፈጠረው ዕድል አልነበረም፡፡ በመቀጠል ኬንያ ላይ የተደረገው የከፋው አፍራሽ ስምምነት አሁንም አማራን ለመጉዳት ያለመ እንጅ ከማዕከላዊ መንግሥት «አብረን እንዝመት» የሚል ድርድር ቀርቦለት እምቢ ያለበት አይደለም፡፡ እንዲያም ሆኖ፣ ሕወሓት ይህንን የሐሰት ትረካ በመንዛት የትግራይን ሕዝብ ለማጽናናትና የአማራን ትግል (ፋኖን) በስነ-ልቦና ለማደንዘዝ ስትሞክር፤ አቶ ልደቱ ደግሞ «የርስት ጥያቄን በ mechanism እንፍታ» በሚል የፖለቲካ አቋራጭ ለዚሁ የሕወሓት ሴራ የንድፈ-ሐሳብ ከለላ ይሰጣሉ።
4. የአፍሪካ ኢንተለጀንስ (Africa Intelligence) ዘገባ እና የ«ጽምዶ» Ultimate ግብ
በወታደራዊ እና የደህንነት ጉዳዩች በልዩ ትኩረት የምርመራ ዘገባዎችን የሚያቀርበው፣ የፈረንሳዩ Africa Intelligence መጽሔት ባወጣው አዲስ መረጃ፣ በካርቱም፣ ፖርት ሱዳን እና በትግራይ (አክሱም) ሚስጥራዊ ቦታዎች የተካሄደው «ጽምዶ» የተባለው ስብስብ ውስጣዊ ተቃረኖውና አደገኛ ቀጠናዊ ባህሪውን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
https://www.africaintelligence.com/eastern-africa-and-the-horn/2026/06/01/distrust-clouds-tsimdo-the-growing-anti-abiy-front,110777076-art ,
ዘገባው ይፋ እንዳደረገው፦ «የጎጃም ክንፍ ከሕወሓት ጋር ለሚደረግ ጥምረት ይበልጥ ፈቃደኛነት ሲያሳይ፤ በአንፃሩ ለተከራካሪው የወልቃይት አቅራቢያ የሚገኙት የጎንደር ፋኖ ክንፍ ግን ይህንን ጥምረት በጽኑ ይቃወማሉ።» ይላል፡፡
ልደቱ «ወልቃይትና ራያን ቀይ መስመር አታድርጉት፣ ይሄ መመጻደቅ ነው» የሚሉት የጎንደሩን የፋኖ ክንፍ ይመስላል፡፡ በርስቱ ጉዳይ ታሪካዊ ባለቤትነት እና ሞራላዊ የበላይነት ያለውን የፋኖ ኃይል፣ ከመሰረታዊ የትግል ዓላማው መስመሩን ለማሳት፣ አበይት የሆነውን ጥያቄ (Grand Cause) ወደ ንዑስ ጥያቄ የማውረድ ዓላማ ያለው አቀራረብ ነው፡፡
ይህ ሁኔታ፣ በ2017 ዓ.ም በወቅቱ በነበረው አደረጃጀት የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል ጎጃም ቀጠናዊ ትስስር ኃላፊ የነበረው ፋኖ የቆዬ ሞላ ከሕወሓት ጋር አብሮ ለመስራት ለማሳመን ከተጠቀመው ምሳሌ ጋር ይመሳሰላል፡፡ የፋኖ አመራሩ “የነ ወልቃይትን ጉዳይ አራት ኪሎ ከገባን በኋላ ሻይ ቡና እያልን በጋራ እንወስናለን” ነበር ያለው፡፡ እንዲህ ያለው ታሪካዊ የክህደት ንግግር በአቶ ልደቱ ጽሑፍ ላይ በምሁራዊ ሸፍጥ መልኩ ቀርቧል፡፡
ጸሐፊው ወደ ጎን ገፍትረው ያለፉትና በ«ጽምዶ» ስም ሊተገበር የታሰበው የመጨረሻና የታለመ ግብ (Ultimate Master Plan) ምንድነው ?
- የሀገረ-መንግሥቱን አከርካሪ መስበር፦ኢትዮጵያን በደካማ የኮንፌዴሬሽን መዋቅር መበተን፤
- የዓባይንና የሕዳሴውን ግድብ የበላይነት በተኪ ጦርነት (Proxy War) ለግብፅ ማስረከብ፦በ1991ዱ የ«ፈሌገ ግዮን» ሰነድ መሠረት መተከልን ማዳከም/መነጠል እና የተከዜ ተፋሰስን በሕወሓትና በሱዳን አል-ቡርሃን ቁጥጥር ሥር ማድረግ፤
- የ«ታላቋ ትግራይ» ህልምን እውን ማድረግ፦ሕወሓት የወልቃይት-ሁመራን «የአማራውን የሆርሙዝ ቁልፍ» በመቆጣጠር፣ እስከ መተማና ቤኒሻንጉል ድንበር በመዘርጋት ትግራይን በ«ሶማሌላንድ ሞዴል» የመገንጠል አላማውን ማሳካት፤
- የጎንደርና የአማራ ሕዝብ መከበብ (Strategic Encirclement)፦ትግራይ እስከ መተከል፣ በደቡብ ደግሞ የ«ግዮን/ኮንፌዴሬሽን» ፍላጎት ያላቸው አመራሮች እስከ መተከል ሲመጡ፤ ሁለቱ አካላት በመተከል መስመር የቀጥታ ድንበር ይፈጥራሉ።
በዚህም ጎንደር የታሪካዊ ርስቶቿና የውጭ መውጫ ኮሪደሮቿ ተነጥቀው፦ ያለምንም የመተንፈሻ ኮሪደር በመሃል በጠላት የተከበበች ደሴት (Encircled Enclave) እንድትሆን ለማድረግ የታቀደው የጅኦፖለቲክስ ሸፍጥ ነው።
💡 ሞጋች ጥያቄ 2፦
«ዓለም አቀፍ የደህንነት ዘገባዎች እንኳ ‘ጽምዶ’ በግብፅና በሱዳን የተኪ ጦርነት ተደግፎ የወልቃይትንና የመተከልን ኮሪደሮች ለመክበብ የታለመ ሴራ መሆኑን እያረጋገጡ ባሉበት ሰዓት፤ አቶ ልደቱ ይህንን የከሰረ ጥምረት ‘የፖለቲካ ብስለት’ አድርገው ሊሸጡልን የሚሞክሩት በምን ስሌት ነው?»
5. የ«ተቤዥነት» (Helplessness) ስነ-ልቦና እና የ«ድርብ መከላከል» (Double Defense) ፅናት
አቶ ልደቱ «ብልፅግና ያጋረጠው አደጋ ከፍተኛ ስለሆነ ከማንም ጋር—እንኳንስ ከሕወሓት ጋር ይቅርና ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር እንኳ መተባበር ይገባል» ሲሉ ይከራከራሉ።
ይህ አቀራረብ የሚከተሉትን ስትራቴጂያዊ አደጋዎች ይፈጥራል፦
- የሥነ-ልቦና ስብራት፦የአማራን ሕዝብ የሕልውና ትግል «በራሱ አቅምና መርህ መቆም አይችልም» የሚል ተቤዥነት (Helplessness) ውስጥ በመክተት፣ ሁልጊዜም ቢሆን ከሌላ አዳኝ ኃይል ጋር መጣመር እንዳለበት አድርጎ ያስባል።
- ከነፃነት ታጋይነት ወደ ተራ ቅጥረኛነት፦ብልፅግናን ለመጣል ሲባል ከሕወሓት ጋር መጠመድ፣ የአማራን የትጥቅ ትግል ለቀጠናዊ ቁማርተኞች መጠቀሚያነት በማቅረብ ፋኖን ወደ «ዳግማዊ ኢሕዴን» ደረጃ ዝቅ ያደርገዋል። ከዚያም ሲከፋ ፋኖን በሕወሓቱ “አርሚ 70” ሞዴል የቀጠናው ቅጥረኛ ተዋጊ የማድረግ፣ ከኀልውና ታጋይነት አውጥቶ ወደ local agent ማውረድ ነው፡፡
- የመጥፋት አዙሪት፦አንድን አምባገነን (ብልፅግናን) ለመጣል ሲባል፣ ሌላኛውን ሥርዓታዊና መዋቅራዊ ጠላት (ሕወሓትንና ኦነግን) ማጠናከር ከተቃጠለ ቤት ወጥቶ ወደ ተናዳፊ እባብ ጉድጓድ የመግባት ያህል አደገኛ ነው።
በጅቡና በእባቡ (በብልፅግናና በሕወሓት) መካከል የቆመ አካል ሊያደርግ የሚገባው «ከሁለቱ አንዱን የመምረጥ ግዴታ ውስጥ መውደቅ አይደለም፤ ከሁለቱ ከመሃላቸው መውጣት ነው!»
ከመሃል መውጣት ማለት ከትግል መሸሽ ሳይሆን፣ የሌሎችን የፖለቲካ አጀንዳ ከመሸከም ወጥቶ በራስ መርህ፣ በራስ አቅም እና በራስ ድርጅታዊ ጥንካሬ ላይ ቆሞ ሁለቱንም አደጋዎች እኩል የመመከት (Double Defense) ፅናት ማሳየት ነው።
መደምደሚያ
አቶ ልደቱ አያሌው ያቀረቡት «ጽምዶ እስከምን ድረስ?» የሚለው ጽሑፍ፣ የብልፅግናን አገዛዝ በፍጥነት ለመጣል በሚል ስም የወልቃይት-ጠገዴ፣ ጠለምትና ራያን ደም ዋጋ ወደ ጎን ገፍትሮ «በሂደት በ Mechanism እንነጋገርበታለን» የሚል ማደንዘዣ የሚያቀርብ ፖለቲካዊ አቋራጭ (Political Shortcut) ነው።
የአማራ ሕዝብ ባለፈው ግማሽ ክፍለ ዘመን የደረሰበት መከራ የተረዱ፣ ይህን መዋቅራዊ የጥቃት መሰረት ከጥፋት ጥንስሱ (ሕወሓት) እስከ ውርስ አስቀጣዩ (ኦሕዴድ-ብልፅግና) ድረስ ያሉ ጠላቶችን ጠንቅቀው የተረዱ እውነተኛ ፋኖዎች መሬት ላይ ያሉ የሕዝብ መዋቅሮች የ«ጽምዶ»ን ወጥመድ ውድቅ በማድረግ፣ የአማራ አላማ ያለው እና በጥብቅ ዲሲፕሊን የሚገዛ አታጋይ ድርጅት በመፍጠር አማራ ኀልውናውን በክንዱ ያስከብራል፡፡ አማራን ማጥፋት የፖለቲካ እስትንፋሱና የኅልውናው መሠረት ያደረገውን ሕወሓት የትግል ‘አጋር’ ለማድረግ የሚደረጉ የትኛውም ጥረቶች ታሪካዊ ክህደት ተብለው ይመዘገባሉ፡፡
የአዋቂ አጥፊዎቹን አቶ ልደቱን ጨምሮ ነገ በታሪክ ፊት ለሚጠየቁ ሁሉ ማስታወስ የምንፈልገው እውነታ፡- ሕወሓት ትናንትናም ሆነ ዛሬ ጦር የሚሰብቀውና የሰበቀው አማራን ለማጥፋት እና አጽመ ርስቱ የሆኑትን ወልቃይት-ጠገዴ፣ ጠለምንት ራያና ኮረምን ለመውረር እና ታላቋን ትግራይ ለመመስረት ብቻ ነው። የዚህ የጥፋት ኃይል አጋር ሆኖ መሰለፍ ጸረ አማራነት ነው፡፡
የአማራ ሕዝብ በአሁኑ ወቅት እየታገለው ያለው ለፍትሕ፣ ለሕልውናው መረጋገጥ፣ ለታሪካዊ ርስቶቹ መከበር እና የሀገር ባለቤትነቱን በዘላቂነት ለማረጋገጥ እንጂ የሌሎች ስልጣን ፈላጊዎች ወይም የቀጠናዊ ኃይሎች መጠቀሚያ ለመሆን አይደለም።
በጥቅሉ የአማራ ሕዝብ አሸናፊ የሚሆነው አንዱን በዳይ በሌላው በዳይ ለመተካት ሲሮጥ ሳይሆን፤ በራሱ የእውነትና የፍትሕ ጥያቄ፣ በራሱ የአማራዊ መርህ እና በራሱ የተስተካከለ ድርጅታዊ ጥንካሬ ላይ ጸንቶ የራሱን አሸናፊ መስመር ሲጠርግ ብቻ ነው!!
ድል ለእውነተኛ አርበኞች
ድል ለአማራ ሕዝብ!!