(ጥር 10 ቀን 2018 ዓም)
በአማራ ህዝብ፣ ለፍትህ፣ እኩልነትና አንድነት በቆሙ ኢትዬጵያውያን እንዲሁም በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የአማራ ፋኖ አንድነት ዕውን ሆኖ የአማራ ፋኖ ብሄራዊ ንቅናቄ (አፋብን) የመመሥረቱን ብስራተ ዜና የአማራ ዲያስፖራ ግሎባል ፎረም አባላት የተቀበልነው በከፍተኛ ደስታና የተነሳሽነት ስሜት ነው።
የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ተጋድሎ ባልተማከለ አደረጃጀት ተጀምሮ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከዝቅተኛ አደረጃጀት ወደ ዕዝና የሁለት ድርጅቶች መዋቅር በማደግ ከፍተኛ ውጤቶችን ሲያዝመዘግብ የቆዬ ቢሆንም ትግሉን ይበልጥ አጎልብቶ በድል ለመቋጨት እንዲቻል አንድ ወጥ የፋኖ ድርጅት መመስረት አስፈላጊ ነበር። በዚህም ምክንያት የፋኖ አንድነት ምስረታ ከማንኛውም ጉዳይ ይበልጥ ቅድሚያና ትኩረት እንዲሰጠው የአማራ ህዝብ፣ መላው የፋኖ ኃይልና አመራር፣ ከዚያም አልፎ ኢትዬጵያ የምትገኝበት አደጋ ያሳሰባቸው ዜጎች ሲጠይቁና ግፊት ሲያደርጉ ቆይተዋል።:
የአማራ ዲያስፖራ ግሎባል ፎረም ከተቋቋመባቸው ዓላማዎች አንዱና ዋነኛው ለአማራው አንድነት መመስረት ድጋፍ ማድረግ ሲሆን፤ ኦገስት 2025 “አንድነታችን ለህልውና ትግሉ ድላችን” በሚል መርህ በአርሊንግተን /ቨርጅንያ ባካሄደው ዓለም አቀፍ ጉባዔ ላይም አንድነት ሊመጣ በሚችልበት ሁኔታ ላይ ምሁራንና የተለያዩ የአማራ ድርጅቶች ተወካዬችን በማሳተፍ ሃሳብ በማቅረብ የበኩሉን አስተዋፅኦ አበርክቷል፣ ሌሎች ተያያዥ ጥረቶችንም አድርጓል:: ከዚሁ ጋር ተያይዞ በዲፕሎማሲና አድቮኬሲ መስኩ አመርቂ ስራን ማከናወን እንዲቻል የዲፕሎማሲና አድቮኬሲ ግብረሃይል እንዲዋቀር በማድረግ አበረታች ተግባር እያከናወነ ይገኛል::
ፎረማችን የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል እና የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት ተዋህደው አንድ መሪ ድርጅት በመመስረት ይፋ ማድረጋቸውን በከፍተኛ አድናቆት ተቀብሎታል። ለዚህም ታሪካዊ ውሳኔ መላውን የአማራ ህዝብና ኢትዮጲያውያን እንኳን ደስ ያላችሁ እያለ ይህ አደረጃጀት ትግሉን ከማፋጠንም ባሻገር የፋኖዎቻችንንም ሆነ ደጋፊዎቻቸውን በስነ-ልቦና ፍፁም አንድነትንና መተሳሰብን በማላበስ የኦህዴድ መራሹን ብልጽግና የስልጣን እድሜ የማሳጠር ሂደት እንደሚያፋጥነው ሙሉ ዕምነታችን ነው:: በመሆኑም ይህ አንድነት እንዲፈጠር ከፍተኛ አመራርና ጥረት ላደረጉት የፋኖ መሪዎች፣ እንዲሁም ሂደቱን በታዛቢነት ለተከታተሉት አሸማጋዮች ከፍ ያለ ምስጋናውን እያቀረበ ለአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ ማንኛውንም ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛነቱን ያረጋግጣል:: በዚሁ መሰረት የአማራ መሪ ድርጅት የሆነውን አፋብንን ለማጠናከርና የህልዉና ትግሉን በአጭር ጊዜ ውስጥ በድል ለማጠናቀቅ እንዲቻል፤
- በሃገር ውስጥም ሆነ በውጪ ሃገራት የሚገኙ የአማራ ህልውና ትግል ደጀንና ደጋፊዎች ሁሉ ልዩነታቸውን አስወግደው በአስቸኳይ ትብብር እንዲፈጥሩ፤:
- የአማራ ዲያስፖራ አባላት ይህ የድል ብስራት ጅማሮ መነቃቃትን የሚፈጥር በመሆኑ እስካሁን ስናደርግ ከነበረው በበለጠ ተግባራዊ ተሳትፎ እንድናደርግ ለቀጣዩ የትግል ምዕራፍ የሚጠበቅብንን ድጋፍ ለማድረግ ራሳችንን ዝግጁ እንድናደርግ፤
- ይህ የአማራ የህልዉና ትግልና ድል የመላ ኢትዮጵያዊያን ድል በመሆኑ ሁላችንም ኢትዮጵያዊያን በጋራ በመቆምና የፋኖን የህልዉና ትግል በመደገፍ ለጋራ እጣ ፋንታ የጋራ ትግል እናደርግ ዘንድ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
አንድነታችን ለህልውና ትግላችን ድል!
ድል ለአማራ ፋኖ፤ ድል ለአማራ ህዝብ፤ ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!