ኤፍሬም ማዴቦ(emadebo@gmail.com)
ህዝባዊ መንግስት ይፈጠር፣አገራዊ ዕርቅ ይደረግ፣ ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት ይመስረት የሚሉ ጥያቄዎች ባለፉት ሃምሳ አመታት አራት ኪሎን ለተቆጣጠሩ አገዛዞች ሁሉ የቀረቡና ዛሬም በመቅረብ ላይ ያሉ፣ ነገር ግን በፍጹም መልስ አግኝተው የማያውቁ ጥያቄዎች ናቸው። እነዚህ ሦስት ጥያቄዎች መልስ ያላገኙት፣ከ1966 ዓ.ም. ጀምሮ ኢትዮጵያን የመሩ መንግስታት ሁሉ ከራሳቸው የሥልጣን አድማስ ባሻገር ለህዝባዊ ጥያቄዎች ምንም ደንታ የሌላቸው አምባገነኖች ስለሆኑ ብቻ አይደለም። እኛም ጠያቂዎቹ ለጥያቄዎቹ አለመመለስ ያደረግነው አስተዋጽኦ አለ። ህዝባዊ መንግስት፣አገራዊ ዕርቅና፣ ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት ቅደም ተከተል ያላቸውና አንዱ ከሌላው በፊት መመለስ ያለበት ወይም የአንደኛው ጥያቄ መልስ ማግኘት ለሌላው ጥያቄ መልስ ማግኘት ቅድመ ሁኔታ ሊሆን ይችላል። እኛ ግን በአንድ በኩል እነዚህን ሦስት ጥያቄዎች ባለፉት ሃምሳ አመታት የጠየቅነው ቅደም ተከተላቸውን ሳንጠበቅ ሁሉንም በተመሳሳይ ግዜ በጅምላ ነው የጠየቅነው፣ በሌላ በኩል ደግሞ የጠየቅናቸው ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙ አንድ ላይ ቆመን በመንግስት ላይ የፈጠርነው ጫና እምብዛም ነው። ከአምባገነናዊ ሥርዓት ወደ ህዝባዊ ሥርዓት የሚወስደን የሽግግር ግዜ ሳይኖር ስለአገራዊ ዕርቅ ማውራት አንችልም። ይህ የሚነገረን ደሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ህዝባዊ መንግስት እንዲፈጠርና በአገራዊ ዕርቅ ሂደት ውስጥ እንድናልፍ በመጀመሪያ የሽግግር ግዜ ያስፈልገናል ማለት ነው፣የሽግግር ግዜ ካስፈለገን ደሞ በሽግግር ግዜው ውስጥ አገር የሚመራ የሽግግር መንግስት ያስፈልጋል ማለት ነው።
ከቀዳማዊ ኃይሌ ሥላሴ ፊውዳል አገዛዝ ወደ ህብረተሰብዓዊት ኢትዮጵያ የተደረገውን ሽግግር የመራውና ከሽግግሩ በኋላም ሙሉ በሙሉ የአገራችንን ሥልጣን የተቆጣጠረው ወታደራዊው ደርግ ነበር። ከደርግ ሥርዓት ወደ ኢህአዴግ አገዛዝ የተደረገውን ሽግግር የመሩትና ከሽግግሩ ዘመን በኋላ በህዝብ ተመረጥን ብለው ኢትዮጵያን ለ27 አመታት የመሩትም ህወሓቶች ናቸው። በ2010 ዓ.ም. ህወሓቶች ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላና ዛሬም ድረስ ኢትዮጵያን እየመራ ያለው የዚሁ የህወሓት ሥርዓት ርዝራዥ የሆነውና በጠሚ አቢይ አህመድ የሚመራው ብልፅግና ፓርቲ ነው። ከህወሓት ሥርዓት ወደ ብልፅግና የተደርገውን ሽግግር “ሽግግር” ብሎ መጥራት አስቸጋሪ ነው፣ ምክንያቱም በህወሓት መራሹና በብልፅግና መራሹ አገዛዞች መካክል ህገመንግስቱን፣የብሔር ፓለቲካንና የፌዴራል ሥርዓቱን አወቃቀር በተመለከተ ይህ ነው ተብሎ ሊነገር የሚችል ልዩነት የለም።
ኢትዮጵያ ውስጥ የሽግግር መንግስት በመጣ ቁጥር፣ሽግግሩ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች አገርን ያለምንም ተጠያቂነት ለምምራት ወይም ህዝብን ረግጦ ለመግዛት እነሱን እራሳቸውን የሚያሸጋግሩበት ሂደት እንጂ፣ኢትዮጵያን ከአምባገነናዊ ሥርዓት ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚወስድ ሽግግር ሆኖ አያውቅም። እኛ ኢትዮጵያዊያን ካሁን በኋላ የሽግግር ግዜ ሂደቱ ምን መምሰል አለበት፣የሽግግር መንግስት እንዴት ይፈጠራል የሚለውንና ከሽግግሩ በኋላ የሚመጣው ህዝባዊ መንግስት እንዴት ይመሰረታል የሚለውን ጥያቄ ባለፉት ሃምሳ አመታት ከሄድንበት መንገድ በተሻለ መልኩ መመለስ አለብን። ካሁን በኋላ የሚኖረን የሽግግር ግዜ ልክ እንደስሙ ኢትዮጵያን ከአምባገነናዊ ሥርዓት ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚወስድ ሽግግር መሆን አለበት።
የዛሬዋ ኢትዮጵያ ምን ትመስላለች?
ኢትዮጵያ ውስጥ በደርግ ዘመን ቀይ ሽብርን የመሰለ ዘግናኝ ወንጀል ተፈጽሟል፣ኢህአፓ፣መኢሶንና ደርግ በየከተማው እርስ በርስ ተገዳድለዋል፣የብሄር ልህቃን የየራሳቸውን ብሔር ነጻ እናወጣለን በሚል የጫካ ውስጥ ትግል አካሂደዋል፣በመጨረሻም የደርግ ሥርዓት በብሔር ኃይሎች ተሸንፎ ከሥልጣን ተወግዷል። ህወሓት በብሔር የተሸነሸነች ኢትዮጵያን ፈጥሮ ከዚህ ቀደም በታሪካችን ታይቶም ተሰምቶም በማይታወቅ መልኩ በተለያዩ ብሔሮች መካከል ግጭት እንዲፈጠር አድርጓል። ዛሬ ህወሓት ከሥልጣን ከተባረረ ከሰባት አመት በኋላ፣ኢትዮጵያ የአፍሪካ የብሔር ግጭትና የርስ በርስ ጦርነት ምልክት ሆናለች። ትግራይ፣አማራና ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ሰላምና መረጋጋት አለመኖሩ ብቻ ሳይሆን፣ እነዚህ ሦስት ክልሎች ከፌዴራሉ መንግስት ቁጥጥር ውጭ ናቸው። አማራ ክልል የፌዴራል መንግስትና የፋኖ ኃይሎች ጦርነት ከጀመሩ ከሁለት አመት በላይ ተቆጥሯል። ኦሮሚያ ክልል ኦነግ ሸኔ ከፌዴራል ኃይሎች ጋር ውጊያ ከጀመረ ሰነባብቷል። ጦርነት የማይሰለቻቸው ህወሓቶች ትግራይን ወደ አራተኛ ዙር ጦርነት እየወሰዷት ነው። ቤንሻንጉል ጉሙዝና ጋምቤላ ውስጥ የታጠቁ ኃይሎች በሚሰነዝሩት ተከታታይ ጥቃት በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው። የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) የብልፅግና መራሹን አገዛዝ በመቃወም እንደገና ወደ ትጥቅ ትግል ለመግባት እያኮበኮበ ነው። ከእነዚህ ፖለቲካዊ ችግሮች ባሻገር ኢትዮጵያ በከፍተኛ ኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችም እየታመሰች ነው። እነዚህ ነገሮች ሁሉ የሚያሳዩን ኢትዮጵያ ከፍተኛ ፖለቲካዊ፣ማህበራዊና ኤኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ መግባቷንና፣ይህ ቀውስ በአስቸኳይ ዕልባት ካልተደረገለት አገራችንን የመበታተን አደጋ ውስጥ ይዟት ሊገባ እንደሚችል ነው።
አብዛኛው ኢትዮጵያዊ አገሩን ስለሚወድና ለዚች ለሚወዳት አገሩ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የተከፈለውን መስዋዕትነት በግልፅ ስለሚረዳ፣ኢትዮጵያ የመፍረስ አደጋ ላይ ናት ሲባል፣”ሟርተኞች ዝም በሉ ኢትዮጵያ አትፈርስም” ይላል። ኢትዮጵያ እንድትፈርስ የሚፈልጉ እጅግ በጣም ጥቂት ኃይሎች ናቸው፣ግን እነዚህ ጥቂት ኃይሎች ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሌት ከቀን ሲሰሩ እኛ ኢትዮጵያ እንዳትፈርስ የምንፈልግ ብዙሃን እጃችንን አጣጥፈን ቁጭ ብለን የምንመለከት ከሆነ፣ኢትዮጵያን ከመፍረስ የሚያድናት ምንድነው? ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት 50 አመታት ኦሮሞን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል የታገለ የትጥቅ ድርጅት(ኦነግ) አሁንም እየተዋጋ ነው፣ትግራይ ውስጥ 17 አመት የትጥቅ ትግል ያካሄደና ለ27 አመታት 4 ኪሎን የተቆጣጠረው ህወሓት ዛሬም የትግራይ ባጠቃላይ የኢትዮጵያ ስጋት ነው፣የትግራይን ኃይሎች እንዳስተነፈስኩ አማራውንም ማስተንፈስ አለብኝ ብሎ አማራ ክልል ጦርነት የጀመረው አቢይ አህመድ፣ አማራው የህልውና ትግል ውስጥ እንዲገባ ስላደረገው፣ ፋኖ እራሱንና የወጣበትን ህዝብ ለመከላከል ዛሬ በሁሉም የአማራ አካባቢዎች የትጥቅ ትግል እያካሄደ ነው። ጋምቤላ፣ቢኒሻንጉል-ጉሙዝና ሶማሌ ክልሎች ውስጥ ጋህነን፣ ቤህነን እና ኦብነግ በመባል የሚጠሩ የታጠቁ ኃይሎች አሉ። እነዚህ በሰሜን፣በምስራቅና በምዕራብ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የታጠቁ ኃይሎች አንድ ወጥ የሆነ ኢትዮጵያዊ አጀንዳ የላቸውም፣እንታገልለታን ለሚሉት ህዝብም በግልፅ ያስቀመጡት የፍትህ፣የነጻነት፣የእኩልነትና የዲሞራሲ ፕሮግራም ወይም ፍኖተ ካርታ የላቸውም። ይህ የሚያሳየን በኢትዮጵያ እንደ አገር መቀጠል ላይ የተደቀኑ አደጋዎችን ስፋትና ጥልቀት ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ ነገ ሳንል በአፋጣኝ የሽግግር መንግስት መመስረት አለብን ስንል፣ አላማው በየሜዲያው ላይ በተከታታይ እንደምንስማው ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ግዜ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር አድርጋ የፍትህ፣የነጻነትና የዲሞክራሲ አገር እንድትሆን ብቻ አይደለም። እንዲያውም ህልውናዋ ባልተረጋገጠ አገር ውስጥ ዲሞክራሲ መገንባት አንችልምና፣ የመጀመሪያውና አንገብጋቢው አላማችን አገራችን ኢትዮጵያን ከተደቀነባት የህልውና አደጋ ማዳንና የኢትዮጵያን እንደ አገር ቀጣይነት ማረጋገጥ ነው። ይህንን የምናደርገው ደሞ የፖለቲካ ባለድርሻዎችን አሰባስበን በምናካሄደው ድርድር ሳይሆን፣ የሚስማማ ከሆነ በሥልጣን ላይ ያለውን መንግስት፣ከላይ በስም የተጠቀሱትን የታጠቁ ኃይሎች፣የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችን፣ሲቪክ ማህበራትን፣ምሁራንን፣ወጣቶችን፣የሙያ ማህበራትን፣የሴቶች ማህበራትን፣የብሔር ልህቃንን፣የሃይማኖት መሪዎችንና የንግዱን ማህበረሰብ በአገር አቀፍ ደረጃ ቁጭ ብለው እንዲደራደሩና አካታች የሆነ፣በግልጽ የተቀመጠ የስራ ዘመንና ሥልጣንና ሃላፍነት የሚኖረውን የሽግግር መንግስት እንዲመሰርቱ በማድረግ ነው።
ዛሬ ምሁሩ፣ልህቁ፣የንግዱ ማህበረሰብ፣ የሙያ ማህበራት ወጣቶችና በአጠቃላይ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ አገሩ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ሽግግር ማድረግ አለባት ብሎ ያምናል፣ነገር ግን ይህ የፖለቲካ ሽግግር እንዴት ይጀመራል ወይም ማን ይጀምረዋል በሚለው ሃሳብ ላይ ልዩነቶች አሉ። የፖለቲካ ሽግግር ሲባል የአንድ አገር የአስተዳደር ሥርዓት ከአምባገነንነት ወደ ዲሞክራሲ የሚሸጋገርበት፣ በአመራር፣ በተቋማትና በፖሊሲ ላይ ከፍተኛ ለውጦች የሚደረጉበት ውስብስብ አገራዊ ሂደት ነው። የፖለቲካ ሽግግር ምንጩ አንዳንዴ አብዮት፣አንዳንዴ የታጠቁ ኃይሎች የሚያደርጉት የትጥቅ ትግል፣አንዳንዴ ደሞ ህዝባዊ እምቢተኝነት ሊሆን ይችላል። ኢትዮጵያ ውስጥ የመጨረሻ ውጤታቸው ዴሞክራሲ ባይሆንም ከንጉሳዊ ሥርዓት ወደ ወታደራዊ አምባገነን ሥርዓት የተደረገው የፖለቲካ ሽግግር መነሻው አብዮት ነበር፣ ከደርግ ሥርዓት ወደ ኢህአዴግ/ህወሓት አገዛዝ የተደረገው ሽግግር መነሻው የትጥቅ ትግል ነበር፣ከህወሓት ሥርዓት ዛሬ በሥልጣን ላይ ወደሚገኘው የብልፅግና ፓርቲ አመራር ለተደረገው ሽግግር ደሞ መነሻው ቄሮ፣ፋኖ እና ዘርማ በሚል ስም የተካሄደው የህዝባዊ እምቢተኘት ትግል ነው። ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ በአንድ በኩል ሳይወዱ ተገደው የህልውና ትግል ውስጥ ገብተው አገዛዙን መሳሪያ የሚታገሉ ኃይሎች አሉ፣በሌላ በኩል ደሞ ብልፅግና መራሹ መንግስት በህዝብና በአገር ላይ የሚፈጽመው ወንጀል አንገፍግፏቸውና በየቀኑ እየከፋ የሚሄደው የኑሮ ሁኔታ መሸከም ከሚችሉት በላይ ሆኖባቸው አገዛዙን በህዝባዊ እምቢተኝነት መጋፈጥ የጀመሩ ኃይሎችም አሉ። ይህ የሚያሳየን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚቀጥለው የፖለቲካ ሽግግር መነሻው የትጥቅ ትግል፣ህዝባዊ እምቢተኝነት ወይም የሁለቱም ውጤት ሊሆን እንደሚችል ነው። ስለዚህ እኛ ኢትዮጵያዊያን የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ከሥልጣን ተወግዶ ወደሚቀጥለው የፖለቲካ ሽግግር ሂደት ውስጥ ከመግባታችን በፊት በጋራ ልንሰራቸው የሚገባ ብዙ ነገርች እንዳሉና ከእነዚህ ብዙ ነገሮች ውስጥ አንዱና ዋነኛው የሚቀጥለው የሽግግር ሂደት ምን መምሰል አለበት የሚለውንና በአገራችን የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የመጨረሻው አምባገነን አገዛዝ መሆን አለበት ብለን ከምናምነው ከጠሚ አቢይ አህመድ አገዛዝ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚደረገውን ሽግግር የሚመራ የሽግግር መንግስት እንዴት ይመሰረታል የሚለውን ጥያቄ አግባብ ባለው መልኩ ካሁኑ መመለስ መጀመር ነው።
በሚያዚያ ወር 2010 ዓም ወደ ሥልጣን ሲመጡ፣ “ስንኖር ኢትዮጵያዊ፣ስንሞት ኢትዮጵያ” ብለው ያስጨፈሩን ጠሚ አቢይ አህመድ እውነትም ኢትዮጵያን የሚወዱ ከሆኑና የኢትዮጵያን እንደ አገር መቀጠል ከራሳቸው አብልጠው የሚመለከቱና ለዚህ ፍላጎታቸው ሞትም ቢሆን ወደኋላ የማይሉ ከሆነ፣ኢትዮጵያ ውስጥ የሽግግር መንግስት እንዲፈጠርና አገራችን ከገባችበት የህልውና አደጋ ውስጥ እንድትወጣ ሥልጣናቸውን በፈቀደኝነት ከመልቀቅ ጀምሮ ሁሉንም ነገር ማመቻቸት ያለባቸው ጠሚ አቢይ አህመድ እራሳቸው ናቸው። ጠሚ አቢይ አህመድ ሥልጣናቸውን በፈቃዳቸው ለቅቀው እሳቸው የሚመሩት መንግስት በሽግግር መንግስት እንዲተካ መደረጉ ጠሚ አቢይ አህመድን በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው ሰው ያደርጋቸዋል፣ደሞም የፖለቲካ ስብዕናቸውንና ቅርሳቸውን ከትውልድ ትውልድ እያጎላው ይኖራል እንጂ ምንም የሚቀንስባችው ነገር የለም። ናይጄሪያን ጄኔራል አቦሳንጆን ጨምሮ እነ ሳኒ አባቻ፣ሞርታላ መሐመድ፣ኢብራሂም ባባንጊድና መሐመድ ቡሃሪን የመሳሰሉ ወታደራዊ አምባገነኖች መርተዋታል። ዛሬ የናይጄሪያ ህዝብ ጄኔራል ኦልሱገን ኦቦሳንጆን ከሁሉም አብልጦ የሚያደንቃቸውና እንደ አገራዊ ጀግና የሚመለከታቸው፣በ1991 ዓም ተመስርቶ ዛሬም ድረስ የቀጠለው የናይጄሪያ አራተኛው ሪፑሊክ እንዲመሰረትና፣ናይጄሪያ ከወታደራዊ አገዛዝ ወደ ዲሞክራሲ ሽግግር እንድታደርግ በፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን በመልቀቃቸው ነው። ጠሚ አቢይ አህመድም የጄኔራል ኦቦሳንጆን ፈለግ ቢከተሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ባጠቃላይ አፍሪካ ውስጥም ተከታታይ ትውልድ ሲዘክራቸው ይኖራል።
የሽግግር መንግስት ማለት ምን ማለት ነው?
የሽግግር መንግስት ማለት እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የብሔር ግጭትና የእርስ በርስ ጦርነት በሚካሄድባቸውና፣ በህዝባዊ አመጽ ወይም በአብዮት በሚናጡ አገሮች ውስጥ በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት ሲወድቅ፣ አገርን ለማረጋጋት፣ አዳዲስ ህጎችንና ደንቦችን ለማውጣትና በመጨረሻም የተረጋጋ፣ቋሚና የአብዛኛው ህዝብ ተቀባይነት የሚኖረው ሥርዓት በምርጫ እንዲፈጠር ለማድረግና፣ባጠቃላይ በፖለቲካ ሽግግሩ ወቅት አገርን ለመምራት የሚቋቋም ግዜያዊ አስተዳደር ነው። ጠቅለል ባለ መልኩ የሽግግር መንግስት በአሮጌውና አዲስ በሚፈጠረው አስተዳደር መካከል እንደ ድልድይ ሆኖ የሚያገለግል መንግስት ነው። የሽግግር መንግስት ብዙና የተለያዩ ስራዎች ይሰራል ሆኖም የሚከተሉት ስራዎች የሽግግር መንግስት የሚሰራቸው ዋና ዋና ስራዎች ናቸው-
- መደበኛ የመንግስት ስራዎችን መስራት
- የአገር ደህንነት፣ሉዓላዊነት፣ የግዛት አንድነትና የዜጎች በህይወት የመኖር ዋስትና እንዲከበሩ ማድረግ
- አገርን ማረጋጋት፡ ህግና ሥርዓት ወደነበረበት እንዲመልስ ማድረግ፣ ቀውሶችን መቆጣጠርና ህዝብ መሰረታዊ አገልግሎቶችን እንዲያገኝ ማድረግ
- ህጋዊና ተቋማዊ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ ማድረግ፣ለምሳሌ፣ ህገ መንግሥታዊ ማሻሻያ፣የመንግስት ቅርፅ ለውጥና የምርጫ ሥርዓት ማሻሻያዎች በተግባር ላይ እንዲውሉ ማድረግ
- የዲሞክራሲ ጅምሮች ጠንካራ መሰረት እንዲኖራቸው ማድረግ፣ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ እንዲካሄድ በማድረግ ዲሞክራሲያዊ ሽግግሩ የተሳካ እንዲሆን ማድረግ
ኢትዮጵያ ውስጥ የሽግግር መንግስት እንዴት ይቋቋማል?
አገራችን ኢትዮጵያ በየቦታው የብሔር ግጭት የሚቀሰቀስባትና አመታት ያስቆጠረ የእርስ በርስ ጦርነት የሚካሄድባት አገር ናት። ኢትዮጵያ ውስጥ የእርስ በርስ ጦርነቱ በመካሄድ ላይ እያለ ወይም ጦርነቱ እንዳቆመ የሽግግር መንግስት ለመመስረት ሚዛናዊነታቸውን የጠበቁ አንዳንድ ሁኔታዎች መሟላት አለባቸው። ለምሳሌ፣የሽግግር መንግስቱን የሚመሰርቱ አካላት ህጋዊነት፣ተቀባይነትና አካታችነትና መረጋገጥ አለበት። ከዚህ በተጨማሪ የሽግግር መንግስቱ በአፍሪካ ቀንድ፣በአፍሪካና በአለም አቀፍ ደረጃ ድጋፍ ይኑረው አይኑረው መታወቅ አለበት። ኢትዮጵያ ውስጥ የሽግግር መንግስት ሲቋቋም አካታች (Inclusive )፣ህጋዊነት ያለው ( Legitimate) ከሆነና፣ግልፅ የሆነ አላማና የስራ ቅደም ተከተል እንዲሁም ኢትዮጵያን ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚወስድ በግልፅ የሚታይ ፍኖት ካርታ ያለው ከሆነ፣ በሽግግሩ ሂደት ውስጥ ሊከሰቱ የሚችሉ ትልልቅ ችግሮች ወይም አንዳይክስቱ ያደርጋል ከተከሰቱም በፍጥነት መፍትሄ ማግኘት ይቻላል። ከዚህ በተረፈ የሽግግር መንግስት ሲቋቋም በየአገሩ ውስጥ ባለው ፖለቲካዊ፣ማህበራዊና ኤኮኖሚያዊ አውድ ውስጥ ስለሆነ የሚቋቋመው፣ አንድ ወጥ የሆነና ለሁሉም አገሮች የሚሰራ የሽግግር መንግስት ሞዴል የለም። ሆኖም ኢትዮጵያ ውስጥ የሽግግር መንግስት ሲቋቋም የሚከተሉትን የስኬት አመልካቾች በጥንቃቄ መከተል ይኖርበታል-
አካታች ውይይትና ድርድር
ኢትዮጵያ ውስጥ የሽግግር መንግስት ለመመስረት አካታች የሆነ ውይይት/ድርድር በአገር አቀፍ ደረጃ መካሄድ አለበት። ይህ ውይይት/ድርድር የወደፊቷ ኢትዮጵያ ጉዳይ የሚመለከታቸውን ባለድርሻዎች ሁሉ ማካተት መቻል አለበት። አካታችነትና የሚመለከታቸውን ባለድርሻዎች ሁሉ ወደ ድርድር ጠረጴዛ ማምጣት እጅግ በጣም ወሳኝና ቁልፍ እርምጃ ነው። ባለድርሻ ሲባል የፖለቲካና ሚሊታሪ ልህቃንን ብቻ ሳይሆን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን፣የሙያ ማህበራትን፣ ወጣቶችን፣ሴቶችን፣የንግዱን ማህበረሰብ፣የብሔረሰብ ተወካዮችን፣የሃይማኖት መሪዎችንና የታጠቁ ኃይሎችን ማካተት አለበት።
ግልጽ የሆነ የህግ ማዕቀፍ፣ሥልጣንና ሃላፊነት
በብዙ አገሮች በተለይም እኛው አገር ኢትዮጵያ ውስጥ በ1966፣በ1983 እና በ2010 ዓ.ም. ሦስት ግዜ በተከታታይ እንዳየነው የሽግግር መንግስታት በሽግግሩ ወቅት ትልቁ ትኩረታቸው ከሽግግሩ በኋላ እንዴት እራሳቸውን ሥልጣን ላይ ማቆየት እንደሚችሉ ነው። እንዲህ አይነቱን አዝማሚያ ለመከላከል፣የሽግግር መንግሥት ከመቋቋሙ በፊት ምን አይነት ሥልጣንና ሃላፊነት እንደሚኖረው፣ምን ያክል ግዜ በሥልጣን ላይ እንደሚቆይና የሚቀጥለውን ምዕራፍ (ብዙውን ጊዜ አጠቃላይ ምርጫ) በግልፅ የሚያስቀምጥ ጊዜያዊ ህገ መንግሥት ወይም የሽግግር ግዜ ቻርተር ያስፈልጋል።
ደረጃ በደረጃ የሚደረግ የደህንነት ዘርፍ ማሻሻያ
እንደ ኢትዮጵያ አይነት ብዙ የታጠቁ ቡድኖች ባሉበትና የእርስ በርስ ጦርነት በሚካሄድበት አገር ውስጥ ደህንነት ከምንም ነገር በላይ አስፈላጊ የሆነና ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው። ስለዚህ ከሽግግር መንግስቱ ተቀዳሚ ስራዎች ውስጥ አንዱና ዋነኛው የቀድሞ ታጋዮችን ትጥቅ ማስፈታት፣ እንዲበተኑ ማድረግና ከማህበርሰቡ ጋር ተቀላቅለው ሰላማዊ ኑሮ የሚኖሩበትን ሁኔታ መፍጠር ነው። ከዚህ በተጨማሪ የደህንነት ተቋም፣የአገር መከላከያ ሠራዊትና የፖሊስ ኃይል ከፖለቲካ ነፃ ሆነው በአዲስ መልክ እንዲዋቀሩ ማድረግ የሽግግር መንግስት መስራት ከሚገባው ተቀዳሚ ስራዎች ውስጥ አንዱ ነው። እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት የታጠቁ ቡድኖች አባላት ትጥቃቸውን ከፈቱ በኋላ፣በቀጥታ መከላከያ ሠራዊቱን፣ፌዴራል ፖሊሲን ወይም አካባቢያዊ ፖሊሲን መቀላቀል ይችላሉ፣ሆኖም ይህ በግዳጅ ሳይሆን በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት።
ዓለም አቀፍ ድጋፍ እና ቁጥጥር
የሽግግር መንግስት ተቀባይነት እንዲኖረውና የሚሰራቸውን ስራዎች ለማስፈጸም የገንዘብና የጠበብቶች እርዳታ ማግኘት እንዲችል አለም አቀፍ ድጋፍ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። አለም አቀፉ ማህበረሰብ በድርድሩ ግዜ ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎች ያቀርባል፣የታጠቁ ኃይሎች ትጥቃቸውን ፈትተው ከማህበረሰቡ ጋር ሲቀላቀሉ የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል፣ምርጫ ሲካሄድ የገንዘብ ዕርዳታ ከማድረግ ባሻገር የምርጫ ታዛቢዎችን ያቀርባል፣የሽግግሩ መንግስት በተቀመጠለት የግዜ ገደብ ውስጥ ሃላፊነቱን መወጣቱንና፣በሽግግሩ ሂደት ውስጥ በተለያዩ ተቋማት፣ለምሳሌ በሽግግሩ መንግስት፣በአገራዊ ጉባኤ፣በሽግግር ግዜ ፍትህና በእውነትና ዕርቅ ኮሚሺን የተወሰኑ ውሳኔዎች ተግባራዊ መሆናቸውን ይቆጣጠራል።
ኢትዮጵያ ውስጥ የሽግግር መንግሥት እንዴት ይመሰረታል?
ኢትዮጵያ ውስጥ የሽግግር መንግሥት እንዴት ይመሰረታል የሚለው ጥያቄ ለውይይት ክፍት የሆነና በውይይት የሚዳብር ሃሳብ ነው፣አንድ ሁላችንም መረዳት ያለብን ነገር ቢኖር ግን፣የሽግግር መንግስት ከዚህም ከዚያም የተሰባሰቡ ሰዎች የሚያቋቁሙት ተቋም አይደለም። የሽግግር መንግስት የሚሰራቸው ስራዎችና የሚወስናቸው ውሳኔዎች ቅቡልነት እንዲኖራቸው፣ የሽግግሩን መንግስት የሚመሰርቱ አካላት ስብስብ ግልጽ፣ገለልተኛ፣ ኢትዮጵያ ውስጥና ከኢትዮጵያ ውጭ የሚገኙ የተለያዩ ባለድርሻዎችን ያካተተና አገራዊ ስምምነት ያገኘ ስብስብ መሆን አለበት። ኢትዮጵያ ውስጥ የሽግግር መንግስት እንዴት ይመሰረታል የሚለውን ሃሳብ አቶ ልደቱ አያሌው በስፋት ሄደውበታል፣ይህ ጥያቄ እጅግ በጣም ቁልፍና የአገራችንን ወደፊት የሚወስን ጥያቄ ነውና፣አገር ውስጥም ውጭ አገርም ያሉ ኢትዮጵያዊያን የፖለቲካ ልህቃንና ምሁራን፣ኢትዮጵያ ውስጥ የሽግግር መንግሥት እንዴት ይመሰረታል የሚለውን ጥያቄ በስፋት ቢመለከቱትና ሃሳባቸውን ለማህበረሰቡ ቢያጋሩ እግጅ በጣም ጠቃሚ ነው የሚል ዕምነት አለኝ።
ኢትዮጵያ ውስጥ በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት አለ፣ የታጠቁ ኃይሎች አሉ፣የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ፣የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች አሉ፣ሲቪክ ማህበራት አሉ፣ምሁራን አሉ፣ወጣቶች አሉ፣የሙያ ማህበራት አሉ፣የሃይማኖት መሪዎች አሉ፣አካባቢያዊ ልህቅ አለ(Regional Elites)፣የሴቶች ማህበራት አሉ፣የንግዱ ማህበረሰብ አለ። የሽግግር መንግስት ምስረታን በተመለከተ የመጀመሪያው ቁልፍ ጥያቄ እነዚህ አካላት በአገር አቀፍ ደረጃ ተሰባስበው ኢትዮጵያ ውስጥ አካታች ነው ተብሎ የሚታመንበትና የብዛኛው ኢትዮጵያዊ ቅቡልነት ያለው የሽግግር መንግስት መፍጠር ይችላሉ ወይ የሚለው ጥያቄ ነው። ሁለተኛው ቁልፍ ጥያቄ በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት እሱ እራሱ የሚካተትበት የሽግግር መንግስት እንፍጠር የሚል ጥያቄ ከእነዚህ አካላት ስብስብ ቢቀርብለት ይስማማል ወይ የሚለው ጥያቄ ነው። የእነዚህ ሁለት ጥያቄዎች መልስ አዎንታዊ ከሆነ፣የሽግግር መንግስት የመፍጠሩ ሂደት ውስብስብ ቢሆንም አስቸጋሪ ላይሆን ይችላል፣የጥያቄዎቹ መልስ አሉታዊ ከሆነ ግን(በተለይ በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት ፈቃደኛ ካልሆነ) የሽግግር መንግስት መፍጠር ይቻላል፣ነገር ግን ይህንን የሽግግር መንግስት ወደ ሥልጣን ለማምጣት ብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ መግባት አለብን። ኢትዮጵያ ውስጥ የሽግግር መንግስት መፈጠሩ ካልቀረ የአፈጣጠሩ ሂደት፣የሽግግር መንግስቱን የሚፈጠሩት አካላት ማንነት፣የተሰባሰቡበት መንገድና በሽግግር መንግስቱ ውስጥ የሚካተቱት አካላት እነማናቸው የሚለው ጥያቄ መልስ አብዛኛውን የኢትዮጵያ ህዝብና የፖለቲካ ልህቅ የሚያስማማ መሆን አለበት። ጠቅለል ባለ መልኩ በአገራዊ ውይይት/ድርድር ጠረቤዛ ዙሪያ ተቀምጠው የሽግግር መንግስት የሚፈጥሩ አካላት ለሚከተሉትን ዝርዝሮች ከፍተኛ ትኩረት መስጠት አለባቸው –
- ከላይ በስም የተጠቀሱት ባለድርሻዎች ስብስብ በጠረቤዛ ዙሪያ ተቀምጦ በሽግግሩ ግዜ አገር የሚመራ ግዜያዊ መንግስት ማቋቋም አለባት
- የሽግግሩ መንግስት መስራት የሚገባውን ዋና ዋና ስራዎች ዝርዝር ቅደም ተከተል ማስቀመጥ አለበት
- በሽግግር ሂደቱ ውስጥ ውሳኔ እንዴት እንደሚወሰን በግልጽ ማስቀመጥ አለበት
- የሽግግሩ መንግስት እራሱ በቀጥታ ከሚሰራቸውና የሚያቋቁማቸው አገራዊ ኮሚቴዎች ከሚሰሯቸው ስራዎች ስፋትና ጥልቀት አኳያ፣የስራ ዘመኑ ስንት አመት መሆን እንደሚገባ መወሰን አለበት
- በሽግግሩ ዘመን ኢትዮጵያ በአገራዊ ምክክርና በሽግግር ግዜ ፍትህ ሂደት ውስጥ ማለፍ እንዳለባት በግልጽ ማስቀመጥና፣ ለሚቋቋመው የሽግግሩ መንግስት መመሪያ መስጠት አለባቸው። አገራዊ ምክክሩ በወደፊቷ ኢትዮጵያ ትላልቅ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ያሳልፋል፣የሽግግር ግዜ ፍትህ ደሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ግማሽ ምዕተ አመታት የተፈጸሙ አገራዊ ወንጀሎችን ተመልክቶ ውሳኔ ያሳልፋል
- በሽግግር መንግስቱ ውስጥ የካቢኔ አባላት የሆኑና በሌላም የሽግግር መንግስቱ ተቋም ውስጥ አገራዊ ውሳኔ የመወሰን ሥልጣንና ሃላፊነት የተሰጣቸው ግለሰቦች፣ከሽግግሩ መንግስት በኋላ በሚደረገው የመጀመሪያው አገራዊ ምርጫ ላይ ለውድድር መቅረብ አይችሉም የሚል ግልጽ መመሪያ ለሽግግር መንግስቱ መስጠት አለበት
እነዚህንና ከላይ የተቀመጡትን 6 ስራዎችና ሌሎችም ስራዎች ከተሰሩ በኋላ፣ስብስቡ በሽግግር ግዜ ውስጥ አገሪቱን የሚመራውን አካል ይሰይማል፣ከዚህ በተጨማሪ የሽግግር ግዜው መንግስት የተሰጠውን ሃላፊነት በአግባቡ እየተወጣ መሆኑን በቅርብ የሚከታተል 7 አባላት ያሉት ከማንም ነጻና ገለልተኛ የሆነ አካል ያቋቁማል። የሽግግር መንግስቱና የሽግግር ግዜ መንግስቱን የሚቆጣጠረው አካል በይፋ ስራቸውን ይጀምራሉ።
ኢትዮጵያ ውስጥ የሚቋቋመው የሽግግር መንግሥት እንዲሰራቸው የምንጠብቀው ስራዎች ምን ይመስላሉ?
አቶ ልደቱ አያሌው የሽግግር መንግስትን በሚመለከት በቅርቡ ሜዲያ ላይ ባወጣው ሰነድ ላይ፣”በሰላማዊም ሆነ በትጥቅ ትግል የምናምን፣ በሀገር ውስጥ እና በስደት የምንገኝ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች በ “X” ከተማ በጋራ ተሰባስበን ከግልና ከቡድናዊ ስሜት በላይ የኢትዮዽያንና የህዝቦቿን የጋራ ህልውናና ጥቅም በማስቀደም በአካሄድነው ሰፊ ውይይት እና ድርድር ሁሉን-አቀፍ የሽግግር መንግስት ለማቋቋም ተስማምተናል” ይላል። ይህ ስምምነት ምናባዊ ስምምነት ይሁን ወይም በእርግጥም የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች በአካል ወይም የዘመኑ ቴክኖሎጂ በፈጠረው መሳሪያ ተሰብስበው ያደረጉት ስምምነት ለመሆኑ ብዙም የሚታወቅ ነገር የለም። ኢትዮጵያ የሽግግር መንግስት ያስፈልጋታል በሚለው ሃሳብ ላይ ከአቶ ልደቱ አያሌው ጋር ሙሉ በሙሉ እስማማለሁ፣የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች ተሰባስበው የሽግግር መንግስት ለማቋቋም ስምምነት ላይ ደረሱ በሚለው ሃሳብ ላይ ግን በፍጹም አልስማማም። ኢትዮጵያ ውስጥ የሚቋቋመው የሽግግር መንግስት እንዴት መቋቋም እንዳለበት አቶ ልደቱም ሆነ ማንም ኢትዮጵያዊ የራሱን ሃሳብ ማቅረብ ይችላል፣ ነገር ግን የሽግግር መንግስት የተወሰኑ ሰዎች ወይም የፖለቲካ ኃይሎች ተሰባስበው የሚያቋቁሙት ተቋም አይደለም። በግልጽ ለመናገር ኢትዮጵያ ውስጥ የሚቋቋመው የሽግግር መንግስት ሁሉንም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች ባካተተ መልኩ ቢቋቋምም አካታች ነው ሊባል አይችልም፣ ምክንያቱም የወደፊቷ ኢትዯጵያ ምን መምሰል አለባት የሚለውን ውሳኔ በመወሰኑ ሂደት ውስጥ ትልቅ ሚና የሚጫወት ተቋም ለማቋቋም መሰባሰብ ያለባቸው የፖለቲካ ባለድርሻዎች ብቻ አይደሉም፣ሌሎችም ብዙና የተለያዩ ባለድርሻዎች አሉ። በተለይ ኢትዮጵያን በመሰለ በብሔር ፖለቲካ በተጨማለቀ፣በተከፋፈለና ሃምሳ አመት ሙሉ እርስ በርስ ሲባላ በኖረ ማህበረሰብ ውስጥ የሚቋቋም የሽግግር መንግስት ግልጽና አካታች በሆነ መልኩ መቋቋም አለበት። ስለዚህ በውጭ አገር የምንኖር ኢትዮጵያዊያን በየፊናችን እየተሰባሰብን የሽግግር መንግስት አቋቋምን፣የወደፊቷን ኢትዮጵያ ህገ መንግስት አረቀቅን ወይም እያረቀቅን ነው የሚለውን ቀልድ ማቆም አለብን። የኛ ስራ እነዚህ ሁለት ቁልፍ ስራዎች እንዴት መሰራት እንዳለባቸው የሚያሳይ ፍኖተ ካርታ ማስቀመጥ ነው፣ስራው ግን ከኛ ባሻገር ብዙ የተለያዩ ፖለቲካዊ፣ማህበራዊና ኤኮኖሚያዊ ባለድርሻዎች በተለይ አገር ውስጥ የሚገኙ ባለድርሻዎች ተሰባስበው በስምምነት የሚሰሩት ስራ ነው።
ሌላው ከአቶ ልደቱ አያሌው ጋር የምስማማው ኢትዮጵያ ውስጥ የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ከመውደቁ በፊት፣በጠሚ አቢይ አህመድ መንግስትና ወደፊት በሚፈጠረው ህዝባዊ መንግስት መካከል እንደ ድልድይ ሆኖ የሚያገለግል የሽግግር መንግስት መቋቋም አለበት በሚለው ሃሳብ ላይ ነው። ሆኖም የሽግግር መንግስት ከመቋቋሙ በፊት፣የሽግግር መንግስት እንዴት እንደሚቋቋም፣እነማንን ማካተተ እንዳለበት፣የሚሰራቸው ስራዎች ምን እንደሆኑ፣ውሳኔ እንዴት እንደሚወስንና ለምን ያክል ግዜ በስራ ላይ እንደሚቆይ በግልጽ የሚያስቀምጥ አካል መኖር አለበት። ይህ አካል የአገሪቱን ቁልፍ ባለድርሻዎች ብቻ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የፖለቲካ፣የሚሊቴሪ፣የሲቪክ፣የሃይማኖት፣የብሔር፣ባለድርሻዎችና፣ምሁራንን፣የንግዱን ማህበረሰብ አባላት፣ወጣቶችንና ሴቶችን ማጠቃለል አለበት። በኔ እምነት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚቋቋመው የሽግግር መንግስት የሚከተሉትን ስራዎች መስራት አለበት-
- መንግስት በየትም አገር ውስጥ የሚሰራቸውን መደበኛ ስራዎች መስራት
- የታጠቁ ኃይሎች መሳሪያቸውን ፈትተው ከማህበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው ሠላማዊ ኑሮ እንዲኖሩ ማድረግ
- ኢትዮጵያ ውስጥ ሠላምና መረጋጋት እንዲፈጠር ማድረግ
- የጦር ኃይሎች፣የፖሊስና የደህንነት ተቋሞች ከፖለቲካ ነጻ ሆነው እንዲደራጁ ማድረግ፣
- ከፖለቲካ ተፅዕኖ የጸዳና የህዝብ ተወካዮችን ለመረጣቸው ህዝብ ተጠያቂ ማድረግ የሚችል ሜዲያ ማደራጀት
- የሽግግሩ ዘመን ከመገባደዱ በፊት ሁሉን አቀፍ አገራዊ ምክክር ጉባኤ እንዲካሄድ ማድረግ
- የእውነት፣የሰላምና የዕርቅ ኮሚሽን ማቋቋም
- የሽግግር ግዜ ፍትህ እንዲካሄዱ ማድረግ
- ነፃ እና ፍትሀዊ ምርጫ አካሂዶ በህዝብ ለተመረጠ መንግስት ሥልጣን ማስረከብ
ከእነዚህ ከተጠቀሱት ስራዎች በዘለለ ግን የሚቋቋመው የሽግግር መንግስት አገራዊ የምክክር ጉባኤን የሚያደራጅ ኮሚሺን፣የሽግግር ግዜ ፍትህ ኮሚሺን እና የእውነትና የዕርቅ ኮሚሺንን ማቋቋም እንጂ፣እነዚህ ተቋሞች የሚሰሩትን ስራ መስራትም በስራቸው ጣልቃ መግባትም የለበትም። ለምሳሌ፣አቶ ልደቱ እንደሚለው፣ የሽግግር መንግስቱ የህገ መንግሥት አርቃቂ እና አፅዳቂ ኮሚሽን ማቋቋም የለበትም፣ይህ ስራ የአገራዊ ጉባኤው ስራ መሆን አለበት። አቶ ልደቱ የሽግግሩ መንግስት የስራ ዘመን 3 አመት ይሆናል የሚል ሃሳብም አስቀምጠዋል፣ይህ በጣም የምቃወመው ሃሳብ ነው። የሽግግሩ መንግስት ዕድሜ የሽግሩ መንግስት ከመመስረቱ በፊት በግልጽ መቀመጥ አለበት በሚለው ሃሳብ ላይ እስማማለሁ፣ሆኖም ግን የሽግግሩ መንግስት እራሱና፣ የሽግግሩ መንግስት የሚያቋቁማቸው የተለያዩ ተቋማትና ኮሚሺኖች(አገራዊ ጉባኤ፣የሽግግር ግዜ ፍትህ ኮሚሺን፣የአውነትና ዕርቅ ኮሚሺን) የሚሰሯቸው ስራዎች ዝርዝር፣ ስፋትና ጥልቀት በግልጽ ከመታወቁ በፊት ከወዲሁ የሽግግር መንግስቱን ዕድሜ በቁጥር ማስቀመጥ ትክክል ነው ብዬ አላምንም። ለምሳሌ፣ አገራዊ ጉባኤው ከማለቁና የሽግግር ግዜ ፍትህ ሂደት ከመጠናቀቁ በፊት የሽግግር መንግስቱ የስራ ዘመን ቢያልቅ ምን ሊደረግ ነው? የሽግግር መንግስት እንዴት ይመሰረታል በሚል ጥያቄ ላይ የየራሳችንን ሃሳብ በየሜዲያው በጽሁፍ የምናቀርብ ሰዎች፣ የሽግግር መንግስት ለመመስረት ሃላፊነቱ የተሰጠው አካል፣የሽግግር መንግስት ከመመስረቱ በፊት የሽግግር መንግስቱ በስንት አመት ሃላፊነቱን ጨርሶ በህዝብ ለተመረጠ መንግስት ሥልጣኑን እንደሚያስረክብ በግልጽ ማስቀመጥ አለበት ማለት እንችላለን፣ እኛው እራሳችን አመት ወስነን ስናስቀምጥ ግን፣አንደኛ በሌሎች ስራ ጣልቃ እንገባለን፣ሁለተኛ- ትክክል ላይሆን የሚችል ሃሳብ በሰው አዕምሮ ውስጥ እንዲገባ እናደርጋለንና መጠንቀቅ አለብን።
በሽግግሩ ዘመን ህግ የሚያወጣው ማነው?
በሽግግር ሂደት ውስጥ በህዝብ የተመረጠ የህግ አውጪ አካል ሊኖር ስለማይችል፣የሽግግሩ መንግስት የሚያወጣቸውን ህጎች በተመለከተ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ አለበት። በሽግግሩ ግዜ መሰራት ያለባቸውን ስራዎች ለመስራትና የአገርን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ አስፈላጊ ከሆኑ ህጎች ውጭ ያሉት ሌሎች ህጎች በህዝብ የተመረጠ መንግስት እስኪፈጠር ቢቆዩ ይመረጣል። የቀኃስና የደርግ ሥርዓት ከሥልጣን ሲወገዱ ያቋቋሙት የህግ አውጪው ተቋምም አብሯቸው ነው የተወገደው፣ይህ አጋጣሚ የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ከሥልጣን ሲወገድ ሊደገም የሚችል አጋጣሚ ነውና፣በሽግግሩ ዘመን ማን እንዴት ህግ ያወጣል የሚለውን ጥያቄ የሽግግሩ መንግስት ከመመስርቱ በፊት መመለስ አለበን። የሽግግር መንግስቱን የሚፈጥረው አካል የሽግግር መንግስቱን ሥልጣንና ሃላፊነት፣የሽግግር መንግስቱ እንዴት ውሳኔ እንደሚወስንና የሽግግር መንግስቱን የስራ ዘመን በግልጽ ያስቀምጣል የሚል ሃሳብ በዚህ ጽሁፍ ውስጥ በተደጋጋሚ ተገልጿል። አሁንም መድገም የምፈልገው በሽግግሩ ሂደት ውስጥ ማን እንዴት ህግ እንደሚያወጣ በዝርዝር ማስቀመጥ ያለበት የሽግግር መንግስቱን የሚፈጥረው አካል መሆን አለበት። ይህ እንዳለ ሆኖ ግን፣የሽግግር መንግስቱን የሚያቋቁመው አካል በሽግግሩ ዘመን የሚወሰኑ ዉሳኔዎችና የሚወጡ ግጎች፣የሽግግር ግዜው መሪ ወይም የተወሰኑ ቡድኖች ጫና እንዲኖረው ምንም አይነት ቀዳዳ መክፈት የለበትም። በነገራችን ላይ በሽግግሩ ዘመን ህግ የሚያወጣው ማነው በሚለው ሃሳብ ላይ አቶ ልደቱ ያቀረቡት ሃሳብ እኔም የምጋራው ሃሳብ ነው።
በአቶ ልደቱ የሽግግር መንግስት ሰነድ ውስጥ በጣም ግራ ካጋቡኝ ሃሳቦች ውስጥ አንዱ የሽግግር መንግሥቱን ዕቅድ በተሟላ ሁኔታ እውን ለማድረግ ከባለ ድርሻ አካላት ምን ይጠበቃል የሚለውን ጥያቄ ሲመልስ፣ ገዢውን ፓርቲ ብልፅግናን እንደ አንድ ባለድርሻ ወስዶ ከዚህ ፓርቲ የሚጠበቁ ነገሮችን ይዘረዝራል። እኔ እስከገባኝ ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ የሽግግር መንግስት ተቋቁሞ ዕቅዱን በተሟላ ሁኔታ እንዴት እውን ያደርጋል የሚል ጥያቄ የምንጠይቅ ከሆነና ስለሽግግሩ መንግስት ስኬት ስናወራ በሥልጣን ላይ ያለው የሽግግሩ መንግስት ነውና ስለ ሌላ ገዢ ፓርቲ ሰለሚባል አካል ማውራት የምንችል አይመስለኝም። ከዚህ በተረፈ፣የሽግግር መንግሥቱ መዋቅሮች የውሳኔ አሰጣጥ ሥርዓት ምን ዓይነት ይሆናል፣የሽግግር መንግሥቱ የስራ አስፈጻሚ/ካቢኔ እንዴት እና በማን ይቋቋማል፣.የሽግግር መንግሥቱ የሽግግር ጊዜ የመተዳደሪያ ቻርተር እንዴት ይጸድቃል፣የሽግግር መንግሥቱ የመጨረሻ ግብ ምንድን ነው በሚል አቶ ልደቱ ያቀረቧቸው ሃሳቦች ብዙ ጥያቄዎችን የሚያጭሩ መልካም የውይይት ሃሳቦች ስለሆኑ እኔም የምገዛቸው ሃሳቦች ናቸው።
የሽግግሩን መንግስት ፍጻሜ የሚያመልክቱ ኩነቶች ምንድናቸው?
በዚህ ጽሁፍ ውስጥ የሽግግሩን መንግስት ፍጻሜ የሚያመልክቱ ኩነቶች ምንድናቸው የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የምሞክረው ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታዎች ተነስቼ ሰለሆነ፣መልሱ ለሁሉም አገሮች እንደ ሞዴል ሆኖ ማገልገል አይችልም። ኢትዮጵያ ውስጥ የሽግግር መንግስት ተመስርቶ የተሰጠውን ሥልጣንና ሃላፊነት ተወጥቶ የሥልጣን ዘመኑ እየተገባደደ መሆኑን የሚያሳዩ ብዙ ኩነቶች አሉ፣የሚከተሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው-
- ኢትዮጵያ ውስጥ ሠላምና መረጋጋት በመስፈን ላይ መሆኑ
- የታጠቁ ኃይሎች ትጥቃቸውን ፈትተው ሰላማዊ ኑሮ መጀመራቸው
- የመከላከያ፣የፖሊስና የደህንነት ተቋሞች ከፖለቲካ ነጻ ሆነው መዋቀራቸው
- ነጻና ገለልተኛ የሆነና መንግስትን ተጠያቂ ማድረግ የሚችል ሜዲያ ተደራጅቶ ስራውን መስራት ሲጀምር
- የሽግግር ግዜ ፍትህ ኮሚሺን ስራውን ሲያጠናቅቅ
- የእውነትና ዕርቅ ኮሚሺን ስራውን ሲያጠናቅቅ
- አገራዊ የምክክር ጉባኤ ተካሂዶ በህገ መንግስት መሻሻል፣በፌዴራል ሥርዓት አወቃቀር፣በክልሎች አደረጃጅት፣በምርጫ ሥርዓት፣በመንግስት ቅርፅ፣በአዲስ አበባ ጉዳይ፣በአገራዊ የስራ ቋንቋ(ዎች) ጉዳይ፣በባንዲራ ጉዳይና በሌሎችም ትልልቅ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ አሳልፎ ውሳኔዎቹ ተግባራዊ መሆን ሲጀምሩ
እነዚህ ከላይ የተቀመጡት 7 ጉዳዮች ሁሉም በጣም አስፈላጊ ጉዳዮች ናቸው፣ሆኖም ከእነዚህ ውስጥ የወደፊቷ ኢትዮጵያ ምን መምሰል አለባት የሚለውን ቁልፍ ጥያቄ የሚመልስና፣ባለፉት ሃምሳ አመታት ኢትዮጵያዊያን ጎራ ለይተው እንዲጨራረሱ ያደረጉ ጉዳዮች ተቋማዊ በሆነ መልኩ ዕልባት የሚያገኙበትን ውሳኔ የሚወስነው አገራዊ የምክክር ጉባኤው ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ አካታች በሆነ አገራዊ መድረክ ላይ ውሳኔ ማግኘት ከሚገባቸው ጉዳዮች ውስጥ ህገ መንግስቱ፣የምርጫ ሥርዓቱ፣የመንግስት ቅርፅ፣ የክልል አወቃቀር፣በፌደራልና በክልል መንግስታት መካከል ያለው ግኑኝነትና የሥልጣን ክፍፍል፣የአዲስ አበባ ጉዳይና የባንዲራ ጉዳይ ዋና ዋናዎቹ ናቸው። እነዚህ ዋና ዋና ጉዳዮች ውሳኔ ሲያገኙ፣ለምሳሌ፣ክልሎችን ከቋንቋ ባሻገር ብዙና የተለያዩ መመዘኛዎችን አስቀምጠን እንደገና በአዲስ መልክ ብናዋቅር፣በፌዴራሉ መንግስትና በክልሎች መካከል ያለው ግኑኝነትና የስራ ሃላፊነት በግልጽ ሲቀመጥ፣አብላጫ ድምፅ የምርጫ ሥርዓትን ትተን ከተመጣጣኝ የምርጫ ሥርዓት ዝርያዎች ውስጥ አንዱን ብንመርጥና የፓርላማ ሥርዓትን ትተን ፕሬዚደንታዊ ሥርዓትን ብንከተል እነዚህ ለውጦች ከዛሬዋ ኢትዮጵያ ፍጹም የተለየች ኢትዮጵያ እንድትፈጠር ለማድረጋቸው ምንም ጥርጥር የለውም። እነዚህ ለውጦች እውን ሲሆኑ የሽግግር መንግስቱም በአንድ በኩል ርዕሰ ብሔርም የመስተደድሩ መሪም የሆነውን ሰው (ፕሬዘደንት) በአገር አቀፍ ደረጃ ያስመርጣል፣በሌላ በኩል ደሞ የምክር ቤት አባላትን ተመሳሳይ በሆነ መንገድ አስመርጦ ሥልጣኑን በምርጫ ለተመረጠ መንግስት ያስረክባል።