ጥር 10 ቀን 2018 ዓ.ም./ January 18, 2026

የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ መመስረት የአማራ ህዝብ ድል፣ የኢትዮጵያ ትንሣዔ ዋዜማ ነው!
በሕልውና ትግል ውስጥ ያለው የአማራ ህዝብ እንዲሁም ሰላም፣ ፍትሕ እና እኩልነት ናፋቂ ኢትዮጵያውያን፣ የአፍሪካ ቀንድ እና የአካባቢው ቀጠና ሰላም እና መረጋጋት እንዲኖረው የሚሹ ኃይሎች እና የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በጉጉት ሲጠብቀው የነበረው የፋኖ አንድነት እውን ሆኖ የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን) መመስረቱ የፈጠረብንን ደስታ እና ከፍተኛ አድናቆት በቅድሚያ ለመግለጽ እንወዳለን።
ይህ የአማራ ፋኖ አንድነት እንዲመጣ ያለመታከት ለደከሙት ሁሉ ያለንን ታላቅ አክብሮት እና ምስጋና እየገለጸን እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እንወዳለን! ይህንን አንድነት ለማምጣት ሲደክሙ ለነበሩ እና ይህንን ቀን ሳያዩ ላለፉት ጀግኖቻችንም ክብር እና የሰማዕትነት ዝክር ይገባቸዋል።
ይህ አንድነት እንዳይመጣ ጠላት ያልፈነቀለው ድንጋይ እንዳልነበረ የሚታወቅ ሲሆን አሁንም የተመሰረተው አንድነት እንዳይፀና ያለ የሌለ ኃይሉን እና የተንኮል ሴራውን አጠናክሮ እንደሚጠቀም በመገንዘብ የአፋብን አመራሮች እና ታጋዩ ብሎም ድጋፍ ሰጪው ኃይል በሙሉ የተፈጠረውን መሪ ድርጅት ነቅቶ እንዲጠብቅ እና የህልውና ትግሉን ከግቡ ለማድረስ እንዲተጋ ለማሳሰብ እንወዳለን።
አፋብን በትግል ፅናት በተፈተኑ መሪዎቹ እየተመራ በአጭር ጊዜ ውስጥ የአማራውን የሕልውና ትግል በድል በመደምደም ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ኃይሎች ጋር በመተባበር የህግ የበላይነት፣ ፍትህ እና እኩልነት የሰፈነባትን ኢትዮጵያን እውን እንደሚያደርግ ሙሉ እምነት አለን።
ዓለም አቀፍ የአማራ ህብረት የአማራ ፋኖ ወደ አንድነት እንዲመጣ የበኩሉን አስተዋጽዖ እንዳበረከተ ሁሉ የሕልውና ትግሉ ከግብ እንዲደርስ በተቻለ መጠን አፋብንን ለመደገፍ ቃል እየገባ ለፋኖ አመራሮች፣ በውጭ ላሉ የአማራ ማህበራት እና ድርጅቶች፣ ለሚዲያ እንዲሁም በድርጅት ላልታቀፉ አማራወች እና ፍትህ ወዳድ ኢትዮጵያውያን እና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚከተለውን ጥሪ ያቀርባል።
- የአፋብን አመራሮች እና ታጋይ ሰራዊቱ የተሸከማችሁት ትውልድን ከጥፋት የማዳን፣ አገርን ከመፍረስ የመታደግ ታላቅ አደራ እና ታሪካዊ ኃላፊነት በመሆኑ በትዕግስት፣ በታማኝነት፣ በፅናት እና በበሳል የአመራር ክህሎት የተጣለባችሁን አደራ እንድትወጡ ጥሪ እናቀርባለን።
- በውጭ ያላችሁ የአማራ ማህበራት እና ድርጅቶች ከምንም ነገር በላይ ስንጠብቀው የነበረው የፋኖ አንድነት እውን ስለሆነ ወደ ተማከለ እና አንድነት መምጣት እንድንችል ጥብቅ ጥሪ እያስተላለፍን በዚህ ረገድ የተጀመሩ ጥረቶችንም ማጎልበት ይገባል እንላለን።
- በውጭ የሚኖረው አማራ አፋብን ተገቢውን ስራ በስፋት መስራት እንዲችል የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት፣ የፋይናንስ፣ የሚዲያ፣ የዲፕሎማሲ እና አድቮኬሲ ድጋፉን ማቄን ጨርቄን ሳይል በተጠናከረ መልኩ ለማካሄድ ቆርጦ እንዲነሳ ጥሪ እናቀርባለን።
- የአማራ ህልውና ትግልን ትኩረት ሰጥታችሁ የምትሰሩ ሚዲያዎች በሙሉ ይህ የተመሰረተው የአማራ ፋኖ አንድነት ተገቢውን ድጋፍ እና ዕውቅና እንዲያገኝ በመናበብ እና በመተባበር ከምንጊዜውም በላይ በርትታችሁ እንድትሰሩ ጥሪ እናቀርባለን:
- ሰላም፣ ፍትህ እና እኩልነትን የምትሹ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ይህን አስከፊ አገዛዝ በማስወገድ ስር ነቀል ለውጥ ሊያመጣ በሚችል መልኩ የተመሰረተውን የፋኖ ድርጅት ለመርዳት ትርጉም ያለው ድጋፍ እንድታደርጉ ጥሪ እናቀርባለን።
- በኢትዮጵያ ላይ የተንሰራፋውን አረመኔያዊ እና ዘረኛ አገዛዝ ለመጣል በመታገል ላይ ያላችሁ አካላት አገዛThን በአጭር ጊዜ ውስጥ በማስወገድ ሰላም እና ፍትህ በኢትዮጵያ ለማምጣት እንዲቻል ከተፈጠረው የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ ጋር ትርጉም ያለው ትብብር እንድታደርጉ ጥሪ እናቀርባለን።
- በቀጠናው አካባቢ ያላችሁ መንግሥታት እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የአማራ ፋኖ ብሄራዊ ንቅናቄ በኢትዮጵያ ሰላም እና ፍትህ በማስፈን ብቻ ሳይወሰን በቀጠናው መረጋጋት፣ ፀጥታ እና ሰላምን ማረጋገጥ የሚያስችል ታላቅ ኃይል በመሆኑ እውቅና ከመስጠት አንስቶ ተገቢውን ዘርፈ ብTh ድጋፍ እንድትሰጡት አክብሮታዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ድል ለአማራ ህዝብ!
ድል ለአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ!
ድል ሰላም፣ ፍትህ እና እኩልነት ለተጠሙ ኢትዮጵያውያን!