ጸሐፊ፦ ዶ/ር ዓለሙ ካሳ ረታ
ጸሐፊውን ለማግኘት፦ alemukreta@yahoo.com
መግቢያ፦
ከጥቂት ጊዜ በፊት አንዱ ልጄ ቲክቶክ ሲመለከት፣ አንድ ተናጋሪ “Ethiopia is geographically in Africa, but culturally outside Africa” ሲል ሰማ። በሌላ አነጋገር፣ «ኢትዮጵያ በመልክዓ ምድር አፍሪካ ውስጥ ብትገኝም፣ በባህል ግን ከአፍሪካ ውጭ ናት» የሚል ነበር።
ልጄ ቪዲዮውን አቁሞ ወደ እኔ ዞረና፣ «ዳዲ፣ ይህ እውነት ነው?» ብሎ ጠየቀኝ።
በዚያን ጊዜ ለጥያቄው ብዙም ትኩረት ሳልሰጥ፣ «እንዴታ! እኛ አፍሪካውያን ነን። በባህልም ሆነ በሌላው ሁሉ አፍሪካውያን ነን» ብዬ መለስኩለት።
እሱም ተጨማሪ ጥያቄ ሳያቀርብ ወደ ቲክቶኩ ተመለሰ።
የእኛ ንግግር ለጊዜው በዚያው አበቃ። ለእኔ ግን ያ በአጭሩ ያለፍኩት ጥያቄ ከአእምሮዬ አልጠፋም፤ በመጀመሪያ ቀላል መስሎ የታየኝ ጉዳይ፣ ሳስበው ስለ ኢትዮጵያዊነት፣ ስለ አፍሪካዊነትና ስለ ታሪካዊ ማንነት የሚነሱ ጥልቅ ጥያቄዎችን የያዘ ሆኖ አገኘሁት። አንድ አገር በመልክዓ ምድር የአንድ አህጉር አካል ሆኖ፣ በባህል ከዚያው አህጉር ውጭ ሊሆን ይችላልን? የአፍሪካ ባህል የምንለውስ ምንድን ነው? ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ የታሪክና የሥልጣኔ መንገድ መከተሏ ከአፍሪካ የሚለያት ነው፣ ወይስ የአፍሪካን ታሪካዊ ብዝኃነት የሚያሳይ ነው?
ይህን ጥያቄ እያሰብኩ ባለሁበት ሰሞን፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ሌላ አነጋጋሪ ጉዳይ ሰማን አንዲት ኢትዮጵያዊት ወጣት “I am Ethiopian, I am not Black” «እኔ ኢትዮጵያዊት ነኝ፤ ጥቁር አይደለሁም» ብላ ተናግራለች የሚል ቪዲዮ በማኅበራዊ ሚዲያ ሲሰራጭ ተመለከትኩ። ንግግሯም የብዙዎችን ትኩረት ስቦ ውይይትና ክርክር አስነሳ።
ይህን ሳይ ከቀናት በፊት ልጄ የጠየቀኝ ጥያቄ እንደገና ትዝ አለኝ። ሁለቱ ንግግሮች በተለያዩ ሰዎች፣ በተለያዩ አጋጣሚዎች የተነገሩ ቢሆኑም፣ አንድ የጋራ ጥያቄ የሚያነሱ መሰሉኝ።
አንዱ ኢትዮጵያን በባህል ከአፍሪካ ይለያታል። ሌላው ኢትዮጵያዊነትን ከጥቁርነት የተለየ ማንነት አድርጎ ያቀርባል። እርግጥ ነው፣ አፍሪካዊነትና ጥቁርነት ፍጹም አንድ ትርጉም ያላቸው ቃላት አይደሉም። ነገር ግን ከሁለቱም ንግግሮች በስተጀርባ የማንነትና የታሪክ ግንዛቤ ጥያቄ እንዳለ ተሰማኝ።
በዚህ ጊዜ ለልጄ በቀላሉ የሰጠሁት መልስ በአእምሮዬ ውስጥ እንደገና ተመለሰ። «እኛ አፍሪካውያን ነን፤ በባህልም በሁሉም አፍሪካውያን ነን» ብዬው ነበር። ግን ይህን እውነት በታሪክ ማስረጃ አስደግፌ ብገልጽለት ኖሮ ምን እለው ነበር?
ይህ ጥያቄ ነው ይህን ጽሑፍ ለመጻፍ ያነሳሳኝ። ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ ታሪክ፣ ባህልና ሥልጣኔ ያላት መሆኑ የማይካድ ነው። ጥያቄው ግን ይህ ልዩነቷ ከአፍሪካ የሚለያት ነውን፣ ወይስ የአፍሪካን ታሪክ የበለጠ የሚያበለጽግ ነውን የሚለው ነው።
- አፍሪካንአንድዓይነት ባህል አድርጎ የማየት ስህተት
«ኢትዮጵያ በባህል አፍሪካዊት አይደለችም» የሚለውን አስተያየት ስንመረምር፣ በመጀመሪያ ልንጠይቅ የሚገባን ጥያቄ አለ። የትኛው የአፍሪካ ባህል?
የጥንቷ ግብፅ የሃይማኖትና የጽሑፍ ባህል? የኑቢያ መንግሥታት ታሪክ? የማሊ ንግድና የቲምቡክቱ የእውቀት ትውፊት? የስዋሂሊ የባሕር ዳርቻ ማኅበረሰቦች? ወይስ የኢትዮጵያ የግእዝ ሥነ ጽሑፍና የቆዩ የመንግሥት ተቋማት?
ከእነዚህ አንዱም ብቻውን አፍሪካን አይወክልም። ሁሉም ግን የአፍሪካ ታሪክ አካል ናቸው።
ክሪስቶፈር ኤህሬት (Ehret, 2002) እና ጆን ኢሊፍ (Iliffe, 2007) በአፍሪካ ታሪክ ላይ ባከናወኗቸው ጥናቶች አህጉሪቱ በተለያዩ የፖለቲካ፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖትና የኢኮኖሚ ተሞክሮዎች እንደተቀረጸች ያሳያሉ። አፍሪካ አንድ ወጥ የሆነ ማኅበረሰብ አይደለችም። በብዙ ሕዝቦች የተሠራች፣ በብዙ ታሪኮች የበለጸገች አህጉር ናት።
ይህን ልዩነት ማወቅ ለኢትዮጵያ ጉዳይ ወሳኝ ነው።
የጃፓን ባህል ከሕንድ ባህል ስለሚለይ ጃፓን ከእስያ ውጭ ናት የሚል ክርክር አናቀርብም። የግሪክ ታሪክ ከስካንዲኔቪያ ታሪክ ስለሚለይ ግሪክን ከአውሮፓ አናወጣትም።
ታዲያ ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ የሥነ ጽሑፍ፣ የሃይማኖትና የመንግሥት ታሪክ ስላላት ከአፍሪካ ለምን ትለያለች?
እዚህ ላይ የተደበቀው ግምት አፍሪካዊነት የተወሰነ አንድ ባህላዊ መልክ አለው የሚለው ነው። ኢትዮጵያ ከዚያ በሐሳብ ከተፈጠረ መልክ ስትለይ፣ ከአህጉሪቱ ውጭ እንደሆነች ትቆጠራለች። ሆኖም ችግሩ የኢትዮጵያ ልዩነት አይደለም። ችግሩ ስለ አፍሪካ ያለን ጠባብ ግንዛቤ ነው።
ይህ በኢትዮጵያ ውስጥም የሚታይ እውነታ ነው። ኢትዮጵያ አንድ ቋንቋ፣ አንድ ሃይማኖት ወይም አንድ ባህል ብቻ ያላት አገር አይደለችም። የተለያዩ ሕዝቦቿ በብዙ የታሪክ መንገዶች ተገናኝተው፣ ተጋጭተው፣ ተባብረውና ተጽዕኖ ተለዋውጠው ዛሬ ያለውን ማኅበራዊ ሕይወት ፈጥረዋል።
የኢትዮጵያን ታሪክ የአንድ ባህል ታሪክ ብቻ አድርጎ መተረክ እንደሚያጎድለው ሁሉ፣ የአፍሪካን ታሪክም በአንድ ዓይነት ባህል መገደብ ያጎድለዋል።
- ከአክሱምእስከላሊበላ፦ የኢትዮጵያ ሥልጣኔ በአፍሪካ ታሪክ ውስጥ
ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ለመለየት ከሚቀርቡ ክርክሮች አንዱ ከጥንታዊ ሥልጣኔዋ ጋር ይያያዛል። በተለይም አክሱም ከዓረቢያ፣ ከሜዲትራኒያንና ከሌሎች የጥንቱ ዓለም ማዕከላት ጋር የነበራት ግንኙነት አንዳንድ ጊዜ አፍሪካዊነቷን የሚያዳክም ማስረጃ ተደርጎ ይቀርባል። ታሪኩ ግን የሚያሳየን ሌላ ነገር ነው።
በሰሜናዊ ኢትዮጵያና በዛሬዋ ኤርትራ ክፍሎች የተመሠረተው የአክሱም መንግሥት፣ በጥንታዊው ዓለም ከነበሩ አስፈላጊ የፖለቲካና የንግድ ኃይሎች አንዱ ነበር። በአዱሊስ ወደብ አማካይነት የቀይ ባሕርን የንግድ መረብ ተጠቅሟል። ሳንቲሞችን አስመቷል፤ ታላላቅ ሐውልቶችን አቁሟል፤ በግእዝ የጽሑፍ ባህል አዳብሯል። ክርስትናንም በጥንታዊው ዘመን ከተቀበሉ መንግሥታት አንዱ ሆኗል (Munro-Hay, 1991)።
የአክሱምን ታሪክ በጥልቀት ያጠናው ስቱዋርት ሙንሮ-ሄይ የመጽሐፉን ርዕስ Aksum: An African Civilisation of Late Antiquity ብሎ መሰየሙ በራሱ ትኩረት የሚስብ ነው። አክሱምን ከዓለም ጋር የተገናኘ ሥልጣኔ አድርጎ ሲመረምር፣ ከአፍሪካ ታሪክ አይነጥለውም። ምክንያቱም ከዓለም ጋር መገናኘት ከአፍሪካ መውጣት አይደለም።
አክሱም ከዓረቢያ ጋር ተገበያይታለች፤ ይህ ግን ዓረባዊ አላደረጋትም። ከሜዲትራኒያን ዓለም ጋር ግንኙነት ነበራት፤ ይህም አውሮፓዊ አላደረጋትም። ክርስትናን ተቀብላለች፤ ይህም ከአፍሪካ የባህል ታሪክ አላስወጣትም።
ይህን ለመረዳት አክሱምን ብቻ ማየት አያስፈልግም። የምዕራብ አፍሪካ መንግሥታት በሰሃራ አቋራጭ ንግድ ውስጥ ተሳትፈዋል። የምሥራቅ አፍሪካ የባሕር ዳርቻ ማኅበረሰቦች ከሕንድ ውቅያኖስ የንግድ ዓለም ጋር ተሳስረዋል። ግብፅ ከሜዲትራኒያንና ከምዕራብ እስያ ጋር ለረጅም ዘመናት ግንኙነት ነበራት (Ehret, 2002; Iliffe, 2007)።
እነዚህ ግንኙነቶች የአፍሪካን ታሪክ የሚያጠፉ አይደሉም። የአፍሪካን ታሪክ የሚያበለጽጉ ናቸው።
እዚህ ላይ አንድ ጥንቃቄ ያስፈልጋል። የጥንቱን የአክሱም መንግሥት ከዛሬዋ ኢትዮጵያ ጋር በሁሉም ድንበርና ማንነት ማመሳሰል አይቻልም። በተመሳሳይም በሆሜር፣ በሄሮዶተስና በጥንታዊ የሃይማኖት ጽሑፎች ውስጥ የሚገኘው «ኢትዮጵያ» የሚለው ስም ሁልጊዜ የዛሬዋን ኢትዮጵያ አያመለክትም። በጥንታዊ ግሪክ አጠቃቀም ይህ መጠሪያ ከግብፅ በስተደቡብ ያሉ የተለያዩ ሕዝቦችን ሊያመለክት ይችል ነበር (Gardner, 1977)።
ሆኖም የእነዚህ ጥንታዊ ማጣቀሻዎች ትርጉም አይጠፋም። ከሰሜን ምሥራቅ አፍሪካ ጋር የተያያዙ ሕዝቦች በጥንታዊው የሜዲትራኒያን ዓለም አስተሳሰብ ውስጥ ቦታ እንደነበራቸው ያሳያሉ። ይህ የአፍሪካ ታሪክ ከሌሎች የዓለም ታሪኮች ጋር ከጥንት ጀምሮ እንደተሳሰረ የሚያስታውስ ነው።
የኢትዮጵያን የሥልጣኔ ታሪክ ስንመለከት ግን በአክሱም ብቻ መቆም አንችልም። ከአክሱም ዘመን ብዙ መቶ ዓመታት በኋላ በላስታ ተራሮች መካከል የተፈጠረው የላሊበላ የድንጋይ ውቅር ሕንፃ ጥበብ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ በአንድ ዘመንና በአንድ ከተማ ብቻ እንደማይገደብ ያሳያል።
በዋናነት ከ12ኛው እስከ 13ኛው ክፍለ ዘመን ከዛግዌ ሥርወ መንግሥት ጋር የሚያያዙት የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት በተራ የግንባታ ዘዴ አልተሠሩም። ከድንጋይ ተራራ ተፈልፍለው፣ ግድግዳዎቻቸው፣ ዓምዶቻቸውና ውስጣዊ ክፍሎቻቸው ከአንድ የድንጋይ አካል እንዲወጡ ተቀርጸዋል። ይህ ሥራ የሥነ ሕንፃ ዕውቀት፣ የሰው ኃይል አደረጃጀት፣ የሃይማኖታዊ ምናብና የረጅም ጊዜ ጥረት ውጤት ነው።
ላሊበላ የኢትዮጵያ ክርስትና ትውፊት አስደናቂ መገለጫ ብቻ አይደለችም። በአፍሪካ ምድር የተፈጠረ የሥነ ሕንፃ ብቃት ማስረጃም ናት። የድንጋይ አብያተ ክርስቲያናቱ ዛሬም ሕያው የእምነት ማዕከላት መሆናቸው የታሪካዊ ቅርስና የማኅበረሰብ ሕይወት ትስስርን ያሳያል (UNESCO World Heritage Centre, n.d.)።
አክሱም በቀይ ባሕር ንግድ፣ በሳንቲም ምትና በሐውልቶቿ የምናውቃት ሥልጣኔ ናት። ላሊበላ ደግሞ በድንጋይ ውቅር ሕንፃዎቿ የምናደንቃት ናት። ሁለቱ በተለያዩ ዘመናት ተፈጥረዋል፤ የተለያዩ የፖለቲካና የማኅበራዊ ሁኔታዎችንም ያንጸባርቃሉ። ነገር ግን ሁለቱም በአፍሪካ ውስጥ የተገነቡ የሰው ልጅ የፈጠራ ሥራዎች ናቸው።
እንግዲህ አክሱምን ስናደንቅ ወይም በላሊበላ የተፈለፈሉትን አብያተ ክርስቲያናት ስንመለከት፣ ከአፍሪካ የተለየ ሥልጣኔ እያየን አይደለም። አፍሪካ ራሷ ምን ያህል የተለያዩ የሥልጣኔ መንገዶችን እንደፈጠረች እያየን ነው። የኢትዮጵያ ሥልጣኔ አፍሪካዊነቷን የሚክድ ማስረጃ ሳይሆን፣ የአፍሪካን የሥልጣኔ ታሪክ የሚያበለጽግ አስተዋፅኦ ነው።
- ከአፍሪካየተለየውሥልጣኔው ነው ወይስ የሥልጣኔው ትረካ?
አክሱምና ላሊበላ በአፍሪካ ምድር የተፈጠሩ የሥልጣኔ መገለጫዎች ከሆኑ፣ ታላቅነታቸውን ለማስረዳት ከአፍሪካ ውጭ የሆነ ምንጭ መፈለግ ለምን ያስፈልጋል? ይህ ጥያቄ ከሕንፃዎችና ከቅርሶች ታሪክ አልፎ ወደ ታሪክ አጻጻፍ ይወስደናል። ታሪክ የተፈጸሙ ክስተቶች ዝርዝር ብቻ አይደለም። እነዚያ ክስተቶች በማን እንደተመዘገቡ፣ እንዴት እንደተተረጎሙና ለየትኞቹ ትውልዶች በምን መንገድ እንደተላለፉም ጉዳይ ነው።
ለረጅም ዘመናት በአንዳንድ የዓለም ታሪክ አተራረኮች ውስጥ የግሪክ፣ የሮምና የአውሮፓ ሥልጣኔዎች የሰው ልጅ እድገት ማዕከል ተደርገው ቀርበዋል። የእነዚህ ሥልጣኔዎች አስተዋፅኦ የማይካድ ነው። ችግሩ ግን የአውሮፓ ታሪክ የሌሎችን ሕዝቦች ለመመዘን ብቸኛ መለኪያ ሲሆን ይጀምራል።
ጃክ ጉዲ The Theft of History በተሰኘው መጽሐፉ የአውሮፓን ታሪካዊ ተሞክሮ የዓለም ሁሉ የእድገት መለኪያ አድርጎ የማቅረብ ዝንባሌን ተችቷል። በእሱ ትንታኔ ውስጥ የሌሎች ማኅበረሰቦች አስተዋፅኦ በቂ እውቅና ሳያገኝ መቅረቱ የታሪክ ግንዛቤያችንን ያዛባል (Goody, 2006)።
የሴኔጋሉ ምሁር ሼክ አንታ ዲዮፕም በThe African Origin of Civilization ውስጥ የጥንቷን ግብፅ ታሪክ ከአፍሪካ ታሪክ በመነጠል የመተረክ ዝንባሌን ተችቷል። የአፍሪካ ሕዝቦች ለጥንታዊ ሥልጣኔ ያበረከቱት አስተዋፅኦ በታሪክ ውስጥ ተገቢውን ቦታ እንዲያገኝ ተከራክሯል (Diop, 1974)።
የዲዮፕ አንዳንድ የዘርና የጥንታዊ ሕዝቦች ማንነት መደምደሚያዎች በምሁራን መካከል አከራካሪ መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም። ሆኖም ያነሳው መሠረታዊ ጥያቄ አሁንም ጠቃሚ ነው፤ የአፍሪካ ሥልጣኔዎች ለምን አንዳንድ ጊዜ ከአፍሪካ ውጭ በሆኑ ተጽዕኖዎች ብቻ ይብራራሉ?
ይህ ክርክር ለኢትዮጵያም አስፈላጊ ነው። አክሱም ሳንቲም ኣሳትማለች፣ ሐውልት አቆመች፣ የጽሑፍ ባህል አዳበረች ስንል፣ የአፍሪካ ሥልጣኔ ምን ያህል የተለያዩ መልኮች እንደነበሩት ማየት አለብን። በላሊበላ የተፈለፈሉትን አብያተ ክርስቲያናት ስናደንቅም በአፍሪካ ውስጥ የተፈጠረውን የሥነ ሕንፃ ጥበብ እያደነቅን ነው። እነዚህን ስኬቶች ከአፍሪካዊነት ጋር ማስታረቅ ካልቻልን፣ የምንመረምረው የኢትዮጵያን ታሪክ ብቻ ሳይሆን የራሳችንን የሥልጣኔ መለኪያም መሆን አለበት። ኢትዮጵያን ከአፍሪካ የለያት ታሪኳ ነው፣ ወይስ ስለ ታሪኳ የተነገረው ትረካ? ይህን ጥያቄ የበለጠ ግልጽ የሚያደርገው የኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ነው።
- ዓድዋ፦የአንድአገር ድል የአንድ አህጉር ተስፋ ሲሆን
መጋቢት 1 ቀን 1896 እ.ኤ.አ. በሰሜናዊ ኢትዮጵያ የተካሄደው የዓድዋ ጦርነት ትርጉሙ ከጦር ሜዳው ድንበር ያለፈ ክስተት ሆነ። በዳግማዊ ምኒልክ መሪነት፣ በእቴጌ ጣይቱና በበርካታ የጦር አዛዦች ተሳትፎ የተሰለፈው የኢትዮጵያ ሠራዊት የጣሊያንን ወራሪ ጦር ድል አደረገ።
ዓድዋን ልዩ ያደረገው የአፍሪካ ሠራዊት የአውሮፓን ሠራዊት ማሸነፉ ብቻ አልነበረም። በአፍሪካ ሌሎች ክፍሎችም የቅኝ ግዛት ወረራን የተቋቋሙ ሕዝቦች ነበሩ። የዓድዋ ልዩ ታሪካዊ ክብደት ግን ኢትዮጵያ የጣሊያንን የቅኝ ግዛት ጥረት በመመከት ሉዓላዊነቷን ማስጠበቅ መቻሏ ነበር (Jonas, 2011)።
በዚያን ዘመን አውሮፓውያን ኃያላን መንግሥታት አብዛኛውን አፍሪካ እየተቀራመቱ ነበር። የቅኝ ግዛት ወረራ አንዳንድ ጊዜ አፍሪካውያን ራሳቸውን ማስተዳደር አይችሉም በሚል የዘረኝነት ግምት ይጸድቅ ነበር። ዓድዋ ይህን ግምት በተግባር ተፈታተነ።
ለኢትዮጵያውያን ዓድዋ የሉዓላዊነት ድል ነበር። በቅኝ ግዛት ሥር ለነበሩ አፍሪካውያን ደግሞ የአውሮፓን ወረራ መቋቋም እንደሚቻል የሚያሳይ ምልክት ሆነ። ከአፍሪካ ውጭ ለሚኖሩ የአፍሪካ ዝርያ ሕዝቦችም ከዘር የበላይነት አስተሳሰብ ጋር በተያያዘ ትግል ውስጥ የተስፋ ምሳሌ ሆነ።
እዚህ ላይ ግን ታሪክን ከማጋነን መጠንቀቅ አለብን። ኢትዮጵያ ዓድዋን ለመላው አፍሪካ ወክላ አልተዋጋችም። የመሪዎቿ ዋና ዓላማ የራሳቸውን መንግሥት ሉዓላዊነት ማስጠበቅ ነበር። የኢትዮጵያ መንግሥትም በዚያ ዘመን የግዛት ማስፋፋትና የውስጥ የሥልጣን ትግሎች ነበሩበት።
ነገር ግን የታሪካዊ ክስተቶች ትርጉም በተሳታፊዎቻቸው የመጀመሪያ ዓላማ ብቻ አይወሰንም። ለኢትዮጵያ ነፃነት የተቀዳጀው ድል ከድንበሯ በላይ ተሻግሮ ለሌሎች ሕዝቦች ትርጉም አገኘ።
ይህ የኢትዮጵያን ታሪክ ከአፍሪካ ታሪክ የሚያገናኝ እጅግ ጠንካራ ማስረጃ ነው። ኢትዮጵያ በሌሎች አፍሪካውያን የፖለቲካ ምናብ ውስጥ የነፃነት ምልክት ሆና ተቀምጣለች። በደቡብ አፍሪካ በተነሳው የነፃ የአፍሪካ ቤተ ክርስቲያናት እንቅስቃሴ ውስጥም «ኢትዮጵያ» የሚለው ስም ራስን የመወሰንና ከአውሮፓዊ ተቋማዊ የበላይነት የመላቀቅ ምልክት ሆኖ ተጠቅሟል (Cobley, 1991)።
በዚህ የ«ኢትዮጵያዊነት» እንቅስቃሴ ውስጥ ኢትዮጵያ የአንድ መንግሥት ስም ብቻ አልነበረችም። የአፍሪካውያንን ክብርና የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ምኞት የምትወክል ምልክት ነበረች። ታዲያ ሌሎች አፍሪካውያን በኢትዮጵያ ውስጥ የራሳቸውን ክብር ሲያዩ፣ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ክብር ለማየት ከአፍሪካ መለየት ለምን ያስፈልጋቸዋል?
ይህን ጥያቄ የበለጠ አስገራሚ የሚያደርገው ኢትዮጵያ በሃያኛው ክፍለ ዘመን በአፍሪካ የነፃነትና የአንድነት እንቅስቃሴ ውስጥ የተጫወተችው ሚና ነው። በዓድዋ የተገለጠው የሉዓላዊነት መንፈስ፣ ከዓመታት በኋላ በአህጉራዊ የፖለቲካ ትብብር ውስጥ አዲስ መገለጫ አገኘ።
በግንቦት 25 ቀን 1963 እ.ኤ.አ. የአፍሪካ ነፃ መንግሥታት መሪዎች በአዲስ አበባ ተሰብስበው የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን መሠረቱ። ኢትዮጵያ የዚህ ታሪካዊ ሂደት መሥራች ተሳታፊና የዲፕሎማሲ ማዕከል ሆነች። አፄ ኃይለ ሥላሴም በድርጅቱ ምሥረታ ውይይቶች ውስጥ ሚና ተጫወቱ። የድርጅቱ ቻርተር የአፍሪካ አገሮችን አንድነት፣ ሉዓላዊነትና ከቅኝ ግዛት ነፃ መውጣት ዋና ዓላማዎች አድርጎ አስቀመጠ (Organization of African Unity, 1963)።
ይህ የኢትዮጵያ ብቻ ስኬት አልነበረም። ከመላው አፍሪካ የመጡ መሪዎችና እንቅስቃሴዎች የተሳተፉበት የጋራ ታሪክ ነበር። ኢትዮጵያ ግን የዚያ ታሪክ የውጭ ታዛቢ አልነበረችም። በውስጡ ነበረች።
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በኋላ ለአፍሪካ ኅብረት መመሥረት ተቋማዊ መሠረት ሆነ። አዲስ አበባም የአህጉራዊ ዲፕሎማሲ ማዕከል ሆና ቀጠለች (African Union, n.d.)። እንግዲህ የኢትዮጵያ አፍሪካዊነት በካርታ ላይ ያለ እውነታ ብቻ አይደለም። በአፍሪካ የነፃነት ትግልና በአህጉራዊ ተቋማት ምሥረታ ውስጥ የተመዘገበ ታሪክም ነው።
5. ኢትዮጵያዊነትና ጥቁርነት፦ የማንነት ልዩነት ወይስ የታሪክ የተዛባ ግንዛቤ?
ከአክሱም ሥልጣኔ እስከ ላሊበላ፣ ከዓድዋ ድል እስከ አፍሪካ አንድነት ድርጅት ምሥረታ ድረስ የተመለከትናቸው ታሪካዊ ክስተቶች ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ጋር ያላት ግንኙነት በመልክዓ ምድር ብቻ የሚገደብ እንዳልሆነ ያሳያሉ። ኢትዮጵያ የአፍሪካ ታሪክ ተመልካች ሳትሆን በታሪኩ ውስጥ የራሷን አሻራ ያሳረፈች አገር ናት። ሆኖም በመግቢያችን የጠቀስነው «ኢትዮጵያዊት ነኝ፤ ጥቁር አይደለሁም» የሚለው ንግግር ከአገርና ከአህጉር ታሪክ ባሻገር ሰዎች ራሳቸውን እንዴት እንደሚያዩና በሌሎች እንዴት እንደሚታዩ እንድናስብ ያደርገናል።
ኢትዮጵያዊነት፣ አፍሪካዊነትና ጥቁርነት በአንድ ሰው ማንነት ውስጥ ሊገናኙ ቢችሉም፣ ሦስቱ መጠሪያዎች አንድ ትርጉም የላቸውም። ኢትዮጵያዊነት ከአገር፣ ከዜግነት፣ ከታሪክና ከባህል ጋር የተያያዘ ማንነት ነው። አፍሪካዊነት ከአህጉራዊ መገኛና ከአፍሪካ ሕዝቦች ታሪካዊ ትስስር ጋር ይያያዛል። ጥቁርነት ደግሞ በተለያዩ አገሮችና ዘመናት የተለያየ ትርጉም ያገኘ የዘርና የማኅበራዊ ማንነት መጠሪያ ነው። እነዚህ ማንነቶች የተለያዩ መሠረቶች ቢኖሯቸውም፣ አንዱ የሌላውን መኖር አያስቀርም።
በአሜሪካ ውስጥ «ጥቁር» የሚለው መጠሪያ ከባርነት፣ ከዘር መድልዎና ከእኩልነት ትግል ጋር የተሳሰረ ረጅም ታሪክ አለው። የአሜሪካ የዘር አመዳደብ በሰዎች የራስ ግንዛቤ ብቻ ሳይሆን በሕግ፣ በፖለቲካና በማኅበራዊ ግንኙነቶችም ተቀርጿል። በኢትዮጵያ ውስጥ ግን ሰዎች ራሳቸውን በአገራቸው፣ በቋንቋቸው፣ በብሔራቸው፣ በሃይማኖታቸውና በአካባቢያቸው የሚገልጹባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ። ይህ ማለት በኢትዮጵያ የቆዳ ቀለም ልዩነትና ከዚያ ጋር የተያያዙ አድልዎዎች አልነበሩም ማለት አይደለም። ይልቁንም የማንነት አመዳደብ በሁለቱ ማኅበረሰቦች ውስጥ በተለያዩ ታሪካዊ ሁኔታዎች እንደተቀረጸ ያሳያል።
አንድ ኢትዮጵያዊ ወደ አሜሪካ ሲመጣ፣ ከአገሩ ይዞት የመጣው የማንነት ግንዛቤ ከአዲሱ ማኅበረሰብ አመለካከት ጋር ላይጣጣም ይችላል። እሱ ራሱን በኢትዮጵያዊነቱ፣ በቋንቋውና በባህሉ ሲገልጽ፣ በአሜሪካ ውስጥ ደግሞ በቆዳው ቀለም መሠረት ሊመደብ ይችላል። እሱ ራሱን የሚያውቅበትና ሌሎች የሚያዩበት መንገድ ሲለያይ፣ የማንነት ግንዛቤው አዲስ ጥያቄዎችን ሊያስነሳ ይችላል። ይህ ልዩነት ሊብራራ እንጂ ሊያስሳልቅ የሚገባ አይደለም። ሰዎች ያደጉበት ማኅበረሰብ፣ የተማሩት ታሪክና ያሳለፉት ሕይወት ለራሳቸው የሚሰጡትን ትርጉም ይቀርጻሉ።
ይሁንና የማንነት አረዳድ ልዩነት ብቻውን ሁሉንም ነገር አያብራራም። ኢትዮጵያዊነትን ለመግለጽ ከጥቁርነት መራቅ ያስፈልጋል የሚለው አስተሳሰብ የበለጠ ማብራሪያ ይፈልጋል። ኢትዮጵያዊ መሆንና ጥቁር መሆን እርስ በርስ የሚቃረኑ ማንነቶች ካልሆኑ፣ አንዱን ለማክበር ሌላውን መካድ የሚያስፈልግ ለምን ይመስላል? ይህ የተለየ የባህል ግንዛቤ ውጤት ነው፣ ወይስ ጥቁርነትን ዝቅ አድርጎ የሚመለከት የቆየ አስተሳሰብ ተጽዕኖ?
ለረጅም ዘመናት በቅኝ ግዛትና በዘረኝነት አስተሳሰቦች ውስጥ አፍሪካዊነት ከኋላቀርነት፣ አውሮፓዊነት ደግሞ ከሥልጣኔና ከእድገት ጋር ተያይዞ ቀርቧል። ይህ የተዛባ አመለካከት በታሪክ አጻጻፍ፣ በትምህርትና በማኅበራዊ ግንኙነቶች አማካይነት ለብዙ ትውልዶች ተላልፏል። የአፍሪካ ሕዝቦች የራሳቸው የሆነ የሥልጣኔ ታሪክ እንደሌላቸው፣ የተገኙባቸውም ስኬቶች ከውጭ በመጡ ተጽዕኖዎች ብቻ እንደተፈጠሩ የሚያቀርቡ ትረካዎች የዚህ አመለካከት አካል ነበሩ።
እንዲህ ያለ ግንዛቤ በሰዎች አእምሮ ውስጥ ሲሰርጽ፣ የራስን ታሪክ ለማክበር ከአፍሪካዊነት መራቅ የሚያስፈልግ ሊመስል ይችላል። አንድ ሰው በአክሱም ሥልጣኔ ይኮራል፤ የላሊበላን የሥነ ሕንፃ ጥበብ ያደንቃል፤ በዓድዋ ድል ይኩራራል። እነዚህን ሁሉ የአገሩ ክብር አድርጎ ይቀበላል። ያ ሁሉ የተፈጠረበትን አህጉር ግን ከዚያው ክብር ጋር ማያያዝ ይቸገራል። የኢትዮጵያን ታላቅነት ከአፍሪካ ልዩ በመሆኗ ለማስረዳት ይሞክራል። በዚህም የራሱን ታሪክ እያከበረ የዚያኑ ታሪክ አህጉራዊ መሠረት ያሳንሳል።
ይህን አስተሳሰብ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ማጠቃለል ግን ትክክል አይደለም። ብዙዎች ኢትዮጵያዊነታቸውን፣ አፍሪካዊነታቸውንና ጥቁርነታቸውን እርስ በርስ የማይጋጩ ማንነቶች አድርገው ይቀበላሉ። ሌሎች ደግሞ ለእነዚህ መጠሪያዎች የተለያየ ትርጉም ይሰጣሉ። አንድ ሰው «ጥቁር አይደለሁም» ሲል በአሜሪካ ውስጥ ካለው የዘር አመዳደብ ይልቅ የራሱን ብሔራዊ ማንነት ለማጉላት እየሞከረ ሊሆን ይችላል። ሌላ ሰው ግን ተመሳሳይ ቃላትን ጥቁርነትን በሚያሳንስ አመለካከት ተነሳስቶ ሊጠቀምባቸው ይችላል። የሁለቱን ልዩነት ሳንመረምር በአንድ ፍርድ ማጠቃለል የለብንም።
አፍሪካዊነትን ከጥቁርነት ጋር ሙሉ በሙሉ ማመሳሰልም የአህጉሪቱን ማኅበራዊ እውነታ አይገልጽም። አፍሪካ በቋንቋ፣ በባህል፣ በታሪክና በሕዝቦቿ ማንነት እጅግ የተለያየች አህጉር ናት። የሰሜን አፍሪካ ሕዝቦችን ብንመለከት እንኳ፣ አፍሪካዊ መሆን በአንድ የቆዳ ቀለም ወይም በአንድ የዘር መጠሪያ ብቻ እንደማይወሰን እንረዳለን። የአፍሪካ ታሪክ በብዙ ሕዝቦች፣ በብዙ ባህሎችና በብዙ የማንነት መገለጫዎች የተሠራ ነው።
የኢትዮጵያዊነት ክብር የሚመነጨው ከራሱ ታሪክ፣ ከሕዝቦቿ ተሞክሮና ከባህላዊ ቅርሶቿ ነው። ይህን ክብር ለማረጋገጥ ጥቁርነትን መካድም ሆነ አፍሪካዊነትን ማሳነስ አያስፈልግም። ኢትዮጵያዊነትን ከአፍሪካዊነት ጋር በተቃራኒ ማስቀመጥ የሁለቱንም ታሪካዊ ትርጉም ያጎድላል። ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ የሥልጣኔ መንገድ አላት፤ ያ መንገድ ግን በአፍሪካ ታሪክ ውስጥ የተጓዘ ነው። ልዩነቷ ከአህጉሯ የሚያስወጣት ሳይሆን ለአህጉሪቱ ታሪክ የምታበረክተውን የራሷን ድርሻ የሚያሳይ ነው።
6. በማኅበራዊ ሚዲያ ዘመን ታሪክን መረዳት
ልጄ በቲክቶክ የሰማውን ንግግር አሁን መለስ ብዬ ሳስበው፣ የዛሬው ትውልድ ታሪክን እየተማረበት ያለው መንገድ ያሳስበኛል። በጥቂት ሰከንዶች ውስጥ የሺህ ዓመታትን ታሪክ የሚያጠቃልል ቪዲዮ ይቀርባል። ተናጋሪው በእርግጠኝነት ይናገራል፤ አንዳንዴም ንግግሩን በምስሎችና በሙዚቃ ያጅበዋል። ተመልካቹም ያንን እርግጠኝነት እንደ እውቀት፣ የቀረበውንም ሐሳብ እንደ ታሪካዊ እውነት ሊቀበለው ይችላል። ሆኖም በእርግጠኝነት መናገርና በማስረጃ መናገር ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው።
«ኢትዮጵያ በመልክዓ ምድር አፍሪካ ውስጥ ብትገኝም፣ በባህል ከአፍሪካ ውጭ ናት» የሚለው ንግግር ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው። በመጀመሪያ ሲሰማ ጥልቅ የታሪክ እውቀት የተመሠረተበት ሊመስል ይችላል። ትርጉሙን በጥሞና ስንመለከተው ግን አፍሪካ አንድ ወጥ ባህል አላት የሚል የተሳሳተ ግምት እናገኛለን። አፍሪካን በአንድ ባህል፣ በአንድ ሃይማኖት ወይም በአንድ የሥልጣኔ መንገድ የሚገልጽ ሰው፣ ከዚያ ምስል የተለየችውን ኢትዮጵያ ከአህጉሯ ውጭ አድርጎ ሊያስባት ይችላል። የኢትዮጵያን ልዩነት ማወቅ ብቻ አይበቃም፤ ያንን ልዩነት የያዘውን የአፍሪካ ሰፊ ታሪክ ማወቅም ያስፈልጋል።
በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ እንዲህ ያሉ ንግግሮች በተለይ ለወጣቱ ትውልድ የሚኖራቸው ተጽዕኖ ቀላል አይደለም። ታሪክ ስለ ቀድሞ ዘመናት የሚነግረን ብቻ ሳይሆን፣ ዛሬ ራሳችንንና ሌሎችን እንዴት እንደምናይ የሚቀርጽ እውቀት ነው። ልጆቻችን ስለ ኢትዮጵያ፣ ስለ አፍሪካና ስለ ማንነታቸው የሚሰሙትን ሁሉ እንደ እውነት እንዲቀበሉ ከመጠበቅ ይልቅ፣ የሰሙትን እንዲመረምሩና ማስረጃ እንዲጠይቁ ማበረታታት ይገባናል። ጥያቄ ማቅረብ የእውቀት መጀመሪያ ነው። የእኛም ኃላፊነት ጥያቄዎቻቸውን በቀላል መልስ ማብቃት ሳይሆን፣ መልሱን በማስረጃ መፈለግን ማስተማር ነው።
የኢትዮጵያን ታሪክ በትክክል ማወቅ የሌሎችን ሕዝቦች ታሪክ ማሳነስ አይጠይቅም። የአክሱምን ሥልጣኔና የላሊበላን የሥነ ሕንፃ ጥበብ ለማድነቅ አፍሪካን ሥልጣኔ የሌላት አህጉር አድርገን ማቅረብ አያስፈልገንም። በዓድዋ ድል ለመኩራት የሌሎችን አፍሪካውያን የነፃነት ትግል ዝቅ ማድረግ አያስፈልግም። የራሳችንን ታሪክ ከፍ ለማድረግ የሌሎችን ታሪክ ዝቅ ማድረግ ከጀመርን፣ ለረጅም ጊዜ አፍሪካን በዝቅተኛነት የሚያሳየውን የተዛባ አስተሳሰብ በሌላ መልክ እየደገምነው ነው። የኢትዮጵያ ታሪክ በራሱ የሚያስከብረው ብዙ ነገር አለው። ያንን ክብር ለማሳየት ሌሎችን ማሳነስ አያስፈልግም።
መደምደሚያ፦ ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ማን ለያት?
ልጄ በስልኩ ያየውን ቪዲዮ አቁሞ «ዳዲ፣ ይህ እውነት ነው?» ብሎ በጠየቀኝ ጊዜ፣ እንዲህ ያለ ረጅም ሐሳብ ውስጥ እገባለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር። በወቅቱ በቀላሉ የመለስኩለት ጥያቄ ግን በኋላ ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ፣ ስለ አፍሪካዊነትና ስለ ማንነት በጥልቀት እንዳስብ አደረገኝ።
ኢትዮጵያ በመልክዓ ምድር አፍሪካ ውስጥ ብትሆንም፣ በታሪክና በባህል ከአፍሪካ የተለየች ናትን?
ይህን ጥያቄ ይዘን ወደ ጥንታዊው የአፍሪካ ታሪክ ተመለስን። የአክሱምን ሥልጣኔና የላሊበላን ጥበብ ተመለከትን። የአፍሪካ ሥልጣኔ በታሪክ መጻሕፍት ውስጥ እንዴት እንደተተረከ መረመርን። የዓድዋን ድልና በአፍሪካ ሕዝቦች የነፃነት ትግል ውስጥ ያገኘውን ትርጉም አስታወስን። ኢትዮጵያ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምሥረታ የነበራትን ድርሻም ተመለከትን። በመጨረሻም ኢትዮጵያዊነት፣ አፍሪካዊነትና ጥቁርነት የሚሉትን ማንነቶች በታሪካዊና በማኅበራዊ አውድ ለመረዳት ሞከርን።
ከዚህ ሁሉ የምንረዳው ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ታሪክ ውጭ የቆመች አገር እንዳልሆነች ነው። የራሷ የሆነ የሥልጣኔ መንገድ መከተሏ ከአህጉሯ አይለያትም። የአክሱም መንግሥት ከቀይ ባሕር ማዶ ከነበሩ ሕዝቦች ጋር መገበያየቱ አፍሪካዊነቱን አላጠፋውም። የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት በድንጋይ መቀረጻቸው ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ውጭ አላደረጋትም። የኢትዮጵያ ሃይማኖታዊ ትውፊቶች ከሌሎች የዓለም ክፍሎች ጋር መገናኘታቸውም ከአህጉሯ ያላትን ታሪካዊ ትስስር አያጠፋውም። የዓድዋ ድል የኢትዮጵያን ልዩ የነፃነት ታሪክ እያሳየ፣ ለሌሎች አፍሪካውያንም የተስፋና የመቋቋም ምልክት ሆኗል።
አፍሪካ በአንድ ቋንቋ፣ በአንድ ሃይማኖት ወይም በአንድ የሥልጣኔ ታሪክ የምትገለጽ አህጉር አይደለችም። በብዙ ሕዝቦች፣ በብዙ ባህሎችና በተለያዩ ታሪካዊ ተሞክሮዎች የተሠራች አህጉር ናት። ኢትዮጵያም በዚህ ሰፊ ታሪክ ውስጥ የራሷ የሆነ ቦታ አላት። ልዩነቷን ለመግለጽ ከአፍሪካ መለየት አያስፈልጋትም። የኢትዮጵያን ታሪክ ማክበር የሌሎችን አፍሪካውያን ታሪክ ማሳነስ አይጠይቅም። የራሳችንን ማንነት በጥልቀት ማወቅ ከሌሎች ጋር ያለንን ታሪካዊ ትስስር እንድንረዳ ያግዘናል እንጂ እንድንክደው አያደርገንም።
ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ማን ለያት የሚለውን ጥያቄ በታሪክ ማስረጃ ስንመረምረው፣ ከአህጉሯ የሚያወጣት ምንም ዓይነት ታሪካዊ መሠረት አናገኝም። የምናገኘው የኢትዮጵያን ልዩነት ከአፍሪካዊነቷ ጋር ማያያዝ የተሳነው፣ አንዳንዴም የአፍሪካን ታሪክ በተዛባ መንገድ የሚመለከት አስተሳሰብ ነው።
ለልጄ በዚያን ቀን የሰጠሁት አጭር መልስ ዛሬም አልተለወጠም። የተለወጠው መልሱን የምረዳበት ጥልቀት ነው። ኢትዮጵያ አፍሪካዊት ናት። የራሷ የሆነ ታሪክ፣ ባህልና ሥልጣኔ ያላት አፍሪካዊት አገር። ልዩነቷ ከአፍሪካ የሚለያት ሳይሆን፣ የአፍሪካን ታሪክ ከሚያበለጽጉት ብዙ ልዩነቶች አንዱ ነው። God bless Africa and its people!1
ማጣቀሻዎች
African Union. (n.d.). About the African Union. https://au.int/en/overview
Cobley, A. G. (1991). The “African national church”: Self-determination and political struggle among Black Christians in South Africa to 1948. Church History, 60(3), 356–371. https://doi.org/10.2307/3167472
Diop, C. A. (1974). The African origin of civilization: Myth or reality (M. Cook, Ed. & Trans.). Lawrence Hill.
Ehret, C. (2002). The civilizations of Africa: A history to 1800. University Press of Virginia.
Gardner, J. W. (1977). Blameless Ethiopians and others. Greece & Rome, 24(2), 185–193. https://doi.org/10.1017/S0017383500018489
Goody, J. (2006). The theft of history. Cambridge University Press.
Iliffe, J. (2007). Africans: The history of a continent (2nd ed.). Cambridge University Press.
Jonas, R. (2011). The battle of Adwa: African victory in the age of empire. Belknap Press of Harvard University Press.
Munro-Hay, S. C. (1991). Aksum: An African civilisation of late antiquity. Edinburgh University Press.
Organization of African Unity. (1963). Charter of the Organization of African Unity. https://ulii.org/en/akn/aa-au/act/charter/1963/charter/eng@1963-05-25
UNESCO World Heritage Centre. (n.d.). Rock-hewn churches, Lalibela. https://whc.unesco.org/en/list/18