መረብ ሚዲያ
በከተማዋ እራሳቸውን የሓራ መሬት ታጣቂ ብለው በሚጠሩት በነጌታቸው ረዳ ሚኒሻዎች እና በራያ አላማጣ ሚኒሻዎች መካከል ነው ዛሬ መስከረም 23/2019 ዓ/ም ረፋድ ጀምሮ ከባድ ውጊያ የተቀሰቀሰው።
አገዛዙ አላማጣ ከተማ በነጌታቸውና በነአቶ ፃድቃን ገ/ተንሣይ ሚኒሻዎች እንዲሁም በፌደራል ፖሊስ ብቻ ነው መጠበቅ ያለባት፡ ሌላው አያስፈልግም የሚል መመሪያ ማውረዱን ተከትሎ ነው የግጭቱ ስረ-መሠረት መነሻ።
ሰሞኑን በራያ ግንባር እየተካሄደ በሚገኘው ውጊያ ከአገዛዙ ጎን ተሰልፈው እየተዋጉ የሚገኙትና አላማጣ ከተማ ከደረሱ በኋላ አታስፈልጉም ተብለው የተገፉት የአላማጣና የአከባቢው ሚኒሻዎች፡ “አገዛዙ አላማጣን ጨምሮ ድፍን ራያን ለነጌታቸው ረዳ ታጣቂዎች አሳልፎ ሰጥቶብናል” በሚል ተደጋጋሚ የቅሬታ መግለጫ ሲያወጡ መሰንበታቸውን መረብ ሚዲያ ተመልክቷል።
ብልፅግና ከወራት በፊት አላማጣ ከተማን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ ለደህንነታቸው ሰግተው ወደ ቆቦ ተፈናቅለው የነበሩ የከተማዋ ነዋሪዎች ዛሬ ወደ ቤታቸው ሊመለሱ ስለሆነ፡ በከተማዋ የነበሩ ዘመዶቻቸው የአቀባበል ዝግጅት እያሰናዱ ባለበት ነው እራሳቸውን የሓራ መሬት ብለው የሚጠሩት ታጣቂዎች በሕዝቡ ላይ ተኩስ የከፈቱት።
በሕዝቡ ላይ የተከፈተውን ተኩስት ተከትሎ የከተማዋ ሚኒሻ አባላት በሓራ መሬት ታጣቂዎች ላይ አፀፋዊ ተኩስ መክፈታቸውን መረብ ሚዲያ ለማረጋገጥ ችሏል።
በተኩስ ልውውጡ በርካታ ንፁኋኖች ሙትና ቁስለኛ ሲሆኑ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ከባድ ውጊያ እየተካሄደ ነው።
(ምስል፦ከማህደር)