ርዕዮተ ዓለም የአንድን ሕብረተሰብ (ማህበረሰብ) ኢኮኖሚያዊ ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ የእድገት አቅጣጫ አመላካች ፍኖተ ካርታ ነው ። ይህ የተግባር መመሪያ በግለሰቦች ፣ በቡድኖች ወይንም በድርጅቶች የታቀዱ እቅዶች፣ አላማቸውና የግባቸውን ምንነት የሚገልጹበትና ማህበረሰቡን በማሳተፍ ተግባራዊ የሚያደርጉበተ የሰርአተ ማህበሩ የእድገት አቅጣጫ አመላካች ሰነድ ነው ።
እዚህ ላይ ማሳሰብ የምፈልገው ጽሑፌን በርዕዮተ ዓለም የጀምርሁት ስለእሱ ትንተና ለመስጠት ፈልጌ ሳይሆን በአገራችን ህገ መንግሥታዊ እውቅናን አግኝቶ የሚያጫርሰንን የጎሣ ፌደራሊዝም ላይ ሀሳብ ጫሪ በመሆን በመስኩ ሙያዊ ብቃት ያላቸውን ምሁራንን ለማነሳሳት ነው ።
ምሳሌዎች
ሀ/በካፒታሊዝም ስርአተ ማህበር፣
ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ርዕዮተ ዐለም ፣ የማምረቻ መሳሪያዎች የግል ባለቤትነት ፣ በነጻ ገበያ መርሆዎች ላይ ያተኮረ ማህበረሰብአዊ ግንኙነትና ግለሰብአዊ ነጻነት ላይ ያተኮረ ፕለቲካዊ አስተዳደር ነው ።
ለ/ በሶሻሊዝም ስርአተ ማህበር ፣
ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ርዕዮተ ዐለም ፣ የማምረቻ መሳሪያዎች በመንግሥት ባለቤትነት የሚያዙ ናቸው ፣ በማዕከላዊ መንግሥት ቁጥጥር ስር የሚገኝ የእዝ ኢኮኖሚና ማህበረሰብአዊ ግንኙነትና ግለሰብአዊ ነጻነት የሚጨፈለቅበት ፖለቲካዊ አስተዳደር ነው ። ሌሎችም የርዕዮተ ዓለም አይነቶች እንደ ሊበራሊዝም ፣ ወግ አጥባቂነት እና በዛ ያሉ ኢኮኖሚን ፣ ፖለቲካን እና የግል አመለካከቶችን የሚገልጹ ብዙ የርዕዮተ ዓለም ምሳሌዎች ይገኛሉ ። እነኚህን ሁለት ዋና የመንግሥታዊ ስርአቶችን የተጠቀምሁት ሌሎች ብዙ የርዕዮት ዓለም አይነቶች መኖራቸውን ዘንግቼ አይደለም ።
ከላይ የተጠቀሱት ምሳሌዎች እንድ ርዕዮተ ዓለም ለአንድ ማህበረሰብ ኢኮኖሚያዊ ፣ ማህበረሰባዊና ፖለቲካዊ የአደረጃጀት መርሆዎችን ስርአት እንዴት እንደሚቀርጽ የሚያሳዩ የተለመዱ ምሳሌዎች ናቸው ።
ወደ አገራችን ኢትዮጵያ መለስ ልበል ፦
ከ1966 ዓም በፊት የነበረውን የንጉሣዊ ስርአትን አስወግደን ድሞክራሲያዊ የመንግሥት አስተዳደር ለማስፈን በሚል ሽፋን ሁለት አይነት የርዕዮተ ዓለም ሙከራዎችን አድርገናል ።
1)በሶሻልስት ርዕዮተ ዓለም መደብ አልባ (ኮሚንዝም) ስርአተ ማህበር ከ75% በላይ ኋላ ቀር በሆነ የማምረቻ መሰሪያ የሚያርስ እና ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ምርት አምራች ገበሬ ባለባት አገራችን ያለ ወዛደር የወዛደሩን አምባገነናዊ ስርአት ለማንበር ብለን እርስ በርሳችን ተጨራረሰን አንድ ትውልድ ገበረን ።
2) አሁንም በሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም ከሶቬት ህብረትና ከቻይና ኮሚንዚም “የተሻለ” የአልባኒያን ኮሚንዝም ወደ አገራችን ለማምጣት በሚል ሽፋን ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሉ የጎሰኝነትን (Tribalism) ርዕዮተ ዓለም ይዘውብን መጥተው ለ27 ዓመታት በተህነግ አገዛዝ ከዚያም በኋላ እነሆ ለሰባት ዓመት በተለይ የዐማራውን ማህበረስብ በገሀድ የዘር ማጥፋት ወንጀል በስም የተለያዩ በተግባር አንድ በሆኑ ኦነግ ሰራሽ በኦሮሞ ሕዝብ ስም በተቋቋሙ ድርጅቶችና ሊህቃን እየተፈጸመበት ይገኛል ።
የጎሣ ብሔርተኝነት አንድን ሕዝብ በዜግነት ውይንም በፖለቲካዊ እሳቤ አንድነት ሳይሆን በጋራ ቅርስ ማለትም በጋራ ቋንቋ ፣ ሃይማኖት ፣ የዘረ ሐረግ እና ወጎች የሚገልጽ ርዕዮተ ዓለም ነው ። በስሙ የሚቋቋሙ አገዛዞች ይህንን የተለየ የጎሣ ቡድን የማገልገል ግዴታ ስላለበት ብሔራዊ ማንነትን የሚጋራቸውን የዘር ሐረግ የግሌ የሚላቸውን ጥቅሞች ይሻማኛል ከሚል ስግብግብነት የተነሳ እንዲጠቁና ከነአካተው እንዲጠፉ ይፈልጋሉ ። ለዚህም ነው በዐማራው ሕዝብ ላይ ግልጽ የሆነ አገዛዝ መር ጦርነት ታውጆ የዘር ማጥፋት ፣ የዘር ማሳሳት እና የማፈናቀል ወንጀል የሚፈጸመው ።
የጎሣ ብሔርተኝነት ቁልፍ ባህሪያት ፦
ሀ)የጎሣ ብሔርተኝነት ቁልፍ ባህሪያት ብቸኛ አባልነት ፣ በጎሣ ብሔርተኝነት ላይ የተመሰረተ አባልነት በዜግነት ከሚተላለፍ ይልቅ ከዘር የሚወረስ በመሆኑ ከጎሣቸው ወይንም ብሔራቸው ውጭ የሆኑ ብሔረሰቦች እንደ ዜጋ የእኔ በሚሏቸው ስፍራዎች አብሮ የመኖር ብሔራዊ መብት በመከልከል ክልላቸውን ከሌሎች ያጸዳሉ ። ለዚህም ነው የኦሮሚያ ክልል የማራውና የተዋህዶ ኦርቶዶክ እምነት ተከታዮች ሲኦል የሆነችው ።
ለ)የራስን ዕድል በራስ መወሰን ፣ የተወሰኑ የጎሣ ቡድኖች የራሳቸውን ዕድል በራስ የመወሰን መብትን ራስ ገዝ ወይንም ሉዓላዊ መንግሥት የመመስረት መብት አድርገው ይወስዱታል ። ይህንን አስተሳሰብ ወይንም የመገንጠል መብት አድርጎ መውስድ ህገወጥ ነው እያልኩኝ አይደለም ምክንያቱም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክሕገ መንግሥት ፣
አንቀጽ 39 የብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች ሕዝቦች መብት ተራቁጥር 1 የሚከተለውን ደንግጓል ፦
ቁጥር 1 “ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር ፣ ብሔረሰብ ፣ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከ መገንጠል ያለው መብት በማናቸውም መልኩ ያለ ገደብ የተጠበቀ ነው” ።
ልብ በሉ ሀገርን የሚያክል ትልቅ ነገር ለማፍረስና ሕዝብን ለመበታተን በሕገ መንግሥት ተብዬው የተቀመጠው የማፍረሻ መብት
በማናቸውም መልኩ ያለ ገደብ የተጠበቀ ነው ይላል ። በዚህ ድንጋጌ በማናቸውም መልኩ ያለገድብ ካለ ህጋዊ መንገድ የመከተል ግዴት የለበትም ማለት ነው ።
ቁጥር 4 “የብሔር ፣ ብሔረሰቦች ፣ ሕዝቦች የራሱን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል መብት ከስራ ላይ የሚውለው” ፣
(ሀ) “የመገንጠል ጥያቄ በብሔር ፣ ብሔረሰቡ ወይም በሕዝቡ የሕግ አውጭ ምክር ቤት በሁለት ሶስትኛ የድምጻ ተቀባይነት ማግኘቱ ሲረጋገጥ” ፣
እዚህም ላይ ልናስተውል የሚገባን ኢትዮጵያን እንደ ሀገር እንዳትኖር ለማፍረስ ሙሉ መብት የተሰጠው ለብሔራዊ ህግ አውጭ አካል ወንም ለፓርላማ እንኳን ሳይሆን መብት የተሰጠው ለክልሉ ህግ አውጭ አካል ነው ።
(ሐ) በዚሁ አንቀጽ ቁጥር አራት (ሐ) “የመገንጠሉ ጥያቄ በሕዝበ ውሳኔው በአብላጫ ድምጽ ሲደገፍ” ፣
ከ84 በላይ የሆኑ ዘውጌዎች ሀገር የሆነችውን ኢትዮጵያን ለማፍረስ መብት የተሰጠው ለአንድ ክልል ዘውጌ መሆኑ አስገራሚ ከመሆኑ በዘለለ ከክልሉ ነዋሪም በቀላል የድምጽ ብልጫ(with a simple voice majority) እንዲሆን መደንገጉ በአንዳንድ ክልሎች ብዙ ቁጥር ያላቸው ሌሎች ከጎሣዎች ስለሚኖሩ በከፍተኛ የድምጽ ብልጫ (absolute majority) እንዲሆን ቢደነገግ የመገንጠል ዐላማው ሊደናቀፍ ይችላል ከሚል እሳቤ መሆኑን ያረጋግጣል ። አቶ መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት አርፋችሁ ትቀመጡ ከሆነ ተቀመጡ እምቢ ካላችሁ ለኦነግ አስረክበናችሁ እንሄዳለን ያሉት ይንን ህጋቸውን በመተማመን ነበር ። የተረከቡን ኦነጎች ደግሞ አርፋችሁ ትገዙ ከሆነ ተገዙ እምቢካላችሁ በጎጥ ሸንሽነናችሁ እርስ በርስ ስትባሉ የምንፈልገውን ሁሉ ወስደን ባዶ እናስቀራችኋለን እያሉ ያቅራሩብናል ።
የጎሣ ብሔርተኝነት ከመደበኛው ወይንም ሲቪክ ብሔርተኝነት በምን ይለያል ?
የሲብክ ብሔርተኝነት ሁሉንም ዜጋ በፈቃደኝነት የሚያቅፍ ፣ ምክንያታዊ እና በምርጫ ላይ የተመሰረት ሲሆን የጎሣ ብሔርተኝነት ደግሞ በውርስ የሚተላለፍ ፣ ሌላውን የሚያገል ምክንያታዊ ያልሆነ እና በዘር የሚተላለፍ ነው ።
የሲብክ ብሔርተኝነት በሌላ አገላለጽ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት በመባል ይታወቃል ፤ ከባህላዊ የሊበራል እሴቶች ከነጻነት ፣ ከመቻቻል ፣ ከእኩልነት እና ከግለሰብ መብቶች ጋር የሚጣጣም ብሔርተኝነት ሲሆን በጽንፈኝነት ላይ የተመሰረተ አይደለም ።
ሲቭክ ብሔርተኝነት ብሔራዊ ማንነትን የሚገልጸው በጋራ የፖለቲካ እሴቶችና በዜግነት መብቶች ነው ። ያደጉት ዲሞክራሲያዊ ሀገሮች ለዚህ ምሳሌ ናቸው ምክንያቱም ማንም ግለሰብ በጎሣ ሳይለይ የህብረተሰቡ አባል ሊሆን ይችላል ። ለምሳሌ ስደተኞች የሚያስፈልጋቸው ከሚኖሩበት ሀጋራት የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለሞች እና ከባህላቸው ጋር መለማመድ ብቻ ነው የሚያስፈልጋቸው እንጂ የትውልድ የማንነታቸውን እሴቶች እንዲተው አይገደዱም።
በአገራችን ኢትዮጵያ ግን በሚገርም ሁኔታ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ኦሮምኛ የሆኑ ሳይቀሩ የዘር ሀረጋቸው ተቆጥሮ ዐማራ ደም ካለባቸው ይገደላሉ ወይንም ከአካባቢው ይባረራሉ ። ይህ የሚያመላክተን አንድ ኢትዮጵያዊ ስደተኛ በባዕድ አገር የሚያገኘውን ያክል መብት በገዛ ሀገሩ ሊያገኝ አለመቻሉን ነው ። የዚህ ሁሉ ምንጭ በሕገ መንግሥት የተደነገገው የብሔር ፌደራሊዝም እና ያንን ለማስፈጽም ስልጣን የተቆናጠጠው የኦህደድ ብልጽግና አገዛዝ ነው ።
የጎሣ ብሔርተኝነትና ዲሞክራሲ
ሀ) የጎሳ ብሔርተኝነትን በብዝሀ ብሔረሰብ ሀገር ዲሞክራሲያዊ ለማድረግ ይቻላል የሚል እምነት የለኝም ምክንያቱም ርዕዮተ ዓለሙና ያንን መሰረት አድርጎ የተዋቀረው መንግሥታዊ አደረጃጀት ከዲሞክራሲያዊ እሴቶች ጋር ስለሚጋጭ ነው ። የጎሣ ብሔርተኝነት እንደ መቻቻል ፣ እኩልነት እና ሁለንተናዊ የግለሰብ መብቶች ያሉ መሰረታዊ የድሞክራሲያዊ እሴቶችን የሚደፈጥጥ ሌላውን በጠላትነት ፈርጆ እንዲያጠቃ የሚያነሳሳ ጽንፈኛ ርዕዮተ ዓለም በመሆኑ ነው ።
ለ) አናሳ የብሔረሰብ ክፍሎችን አግላይ ነው በመሆኑም አናሳዎችን ከፖለትካ ተሳትፎ እና ከዜግነት መብቶች ያገላል ። ለዚህም ማረጋገጫው በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ ሌሎች የብሔረሰብ አባላት የመምረጥም ሆነ የመመረጥ ፣ በክልሉ ውስጥ የመኖር እና ሌሎችም ዓለም አቀፍ የሰብአዊና በህይወት የመኖር ድንጋጌዎች ሳይቀሩ የሚጣሱት ።
ሐ) የጎሣ ብሔርተኝነት ብዙውን ጊዜ ማህበረሰብን ለመለያየት ፣ አምባገነናዊ እና የብሔር ፋሺስታዊ አገዛዝን ለመመስረት እና ለማጠናከር ምክንያት ይሆናል ለዚህ መረጃ የወቅቱ የኦህደድ ብልጽግና አብይ አህመድ አገዛዝ በቂ ነው ።
መ) የጎሣ ብሔርተኝነት ብዙውን ጊዜ ማህበረሰቦችን ለመለያየት ፣ አምባ ገነናዊ አገዛዝን ለማጠናከር እና የዲሞክራሲያዊ ተቋማትን ለማዳከም አይነተኛ መሳሪያ ሲሆን ርዕየተ ዓለሙ ጎሣዎችን አንዱን በሌላው ላይ በማነሳሳት ለዘር ማጥፋት ወንጀል ምክንያት ይሆናል። በዐማራው ሕዝባችን ላይ የሚካሄደው የዘር ማጥፋት ወንጀል የዚሁ ማሳያ ነው ።
በሀገራችን ኢትዮጵያ በጎሣ መደራጀትና መንግሥታዊ ስርአቱም የጎሣ ፌደራሊዝም የሆነው በሕዝባችን ፍላጎት ሳይሆን በወቅቱ የደርግን አገዛዝ በጠብመንጃ አሸንፎ መንበረ ስልጣኑን የተቆጣጠረው ህወኃትና አጋሩ ኦነግ የጫኑበት የመከፋፈያ እና ሀገርን ማፈረሺያ የተቀበረ ቦንብ ነው ። ምንም እንኳን የስርአቱ መሀንዲሶች ተፈራርቀው የፈለጉትን ስልጣን ቢይዙም ብስሙ ሲምሉና ሲገዘቱ ለነበረው ብሔራቸው ያመጡት ነገር ቢኖር እልቂትና ችግርን ነው ። ታዲያ ይህንን ሕዝብ በጎሣ ለምን ተደራጀህ ብዬ ለመውቀስ የሚያስችልኝ አመክንዮ የለኝም ። ምክንያቱም ሁሉም ተገደው የተደራጁ ሲሆኑ ከፊሉ በውሸት ፕሮፓጋንዳ እና በጥቅም በተገዙ ልህቃኖቻቸው ተወናብደው ሲደራጁ የዐማራ ሕዝብ የተቃጣበትን የህልውና አደጋ በመቀልበስ ሉአላዊት ኢትይጵያን ከብተና ለመታደግ ተደራጅቶ በመዋደቅ ላይ ይገኛል ።
የዐማራ ሕዝብ በአጠቃላይና ነፍጡን ያነሳው የዐማራ አርበኛ እንደ ህወኃትና ኦነግ በኢትዮጵያ መቃብር ላይ የራሱን ጎጆ ለመቀለስ እንደማይታገል ዘወትር የሚገልጸው ሀቅ በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ከጎኑ ቆሞ ራሱንና ሀገሩ መታደግ ይኖርበታል ።
ጠቅለል ባለ አገላለጽ ርዕዮተ ዓለም በተግባር ላይ ያተኮረ የማደራጃ መርህ ነው ። ስለሆነም የታቀዱ እሳቤዎችን ላማሳካት እና ለመተግበር የማያሻማ ግልጽ የሆነ የተግባር መመሪያ ወይንም ማኒፌስቶ ያስፈልጋል ። ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ፣ የሲቭክ ድርጅትና ግለሰብ ሕዝቡንና እናት ሀገሩን ከጥፋት ለመታደግ እጅና ጓንት ሆኖ ለመስራት የመተማመኛ ርዕየተ ዓለማዊ ሰነዱን ይፋ ማድረግ ይኖርበታል ። ያረጀና ያፈጀ የጥላቻ ማኒፌስቶ አንግበው የምንገታገቱ ድርጅቶች ወቅቱን በዋጀ መልኩ አድሰውና ራሳቸውም ታድሰው ቢቀርቡ ለመከራ የዳረጉትን ሕዝብ ይታደጉታል ታርካቸውንም ለማደስ አጋጣሚ ይፈጥርላቸዋል የሚል እምነት አለኝ ።
ሕዝባችንስ ቢሆን ምን እስከሚሆን ነው የሚጠብቀው ዝምታው ከሞት ፣ ከመፈናቀል ፣ በረሀብ ከማለቅ ፣ ቤተ እምነቱንና አገልጋዮቹን ከመቀማት ስላላዳነው ይህንን አገዛዝ ለመምረጥ ሳይሆን ለማስወገድ መዘጋጀትና መነሳት አለበት ።
መፍትሔ ፦
በፍለፊት ተዋግተውን ያልተሳካላቸው የውጭ ጠላቶቻችን የቀበሩት የጎጥ ፈንጂ ፈንድቶ በጠላትነት እንድንተያይና ደም እንድንቃባ አድርጎናል ። ውስጣችን ገብቶ የሚቆጠቁጠን ህመም አክመን አብረን ተከባብረን ለመኖር መፍትሔው ሁሉንም ባለ ድርሻ አካላትን ያካተተ ገለልተኛ የሆነ አጠቃላይ የእውነት ፣ የፍትህ እና የእርቅ ኮሚሽን መቋቋም ይኖርበታል ። ኮሚሽኑ ሁሉንም የማህበራዊ ቡድኖችን ማለትም ተጎጂዎችን ፣ ወንጀለኞችን ፣ ሴቶችን ፣ ወጣቶችን እና የተገለሉ ቡድኖችን በማሳተፍ ያለፉትን የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለመፍታት የሽግግር ጊዜ ፍትህ ያስፈልጋል ። የሽግግር ጊዜ ፍትህ ከተረጋገጠ ብዙኃኑ የሚስማማበት ፍትህ እና እኩልነት የሰፈነበትን መንግሥታዊ ስርአት በመመስረት ተከባብሮና ተፈቃቅሮ መኖር ይቻላል የሚል እምነት አለኝ ።
መልካም ንባብ
ንጉሤ አሊ