
እንዴ? ሁለተኛው አንቀጽ እኮ ገዳዩ ባርቆበት እንጂ ሆን ብሎና አስቦበት እንዳልገደላት በማያሻማ ሁኔታ ይገልጻል፡፡ ታዲያ መግደልን ምን አመጣው? የሁላችንም እህት የሆነችው ሟች ቤተልሄም የክ/ጦር አዛዥ እህት ስለሆነች ባርቆበት ብትሞትበት እሱም ይሙት ይባላል? ይህማ ኦሪታዊ የሀሙራቢ ሕግ ነው፡፡ እናም ከጅምሩ በዚህ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን “የገደለ ይገደል” ብሎ ሕግ መቅረጽ በራሱ ትክክል አይመስለኝምና ይከለስ፤ ይጠና፤ ይሻሻል፡፡ በስህተት አንድ ሰው ሞተብን፤ በሌላ ስህተት ደግሞ ትግሉን የሚጠቅም ሌላ ሰው ተገደለብን፡፡ ከሁለት ያጣ ጎመን ሆንን፡፡ “የገደለው ባልሽ የሞተው ወንድምሽ፡፡ ሀዘንሽ ቅጥ አጣ ከቤትሽም አልወጣ” ተብሎም ሙሾ ወረደልን፡፡ የት ነው ያለነው? ምን ነካን?
ፋኖ እንዲህ ከሆነ ኦሮሙማ እያደረገ ያለውን ባያደርግ ነበር የሚገርመው፡፡ አሁን ነው መሸሽ ማለት አሁን ነው፡፡ አማራ አንድዬ ይሁንህ፡፡ የኢንጂኔር ክበር ተመስገን ክ/ጦር፥ ባርቆበት ገዳዩን በማካተቴ በኔም ላይ ሞት ካልፈረደብኝ የሁለቱንም ሟቾች ነፍስ ይማር እላለሁ፡፡ በበኩሌ የቀረኝ ነገር የቀረችኝን ጥንጥዬ ዕድሜ ስለዚች ትንግርተኛ ሀገር ምንም ነገር እንዳልሰማ ጆሮየን በጨርቅ ጠቅጥቄ የምኖርበት የስደት ሀገር ማፈላለግ ነው፡፡ ንቃተ ኅሊናው በዚህ ልክ የወረደ የማኅበረሰብ “ነፃ አውጪ” ነገ ሀገርን የመረከብ ዕድል ቢያገኝ ምን ሊፈጠር እንደሚችል የአሁን ምልክቶች ከፍ ባለ ድምፅ እያስተጋቡ ነውና መጪው ጊዜም አደጋ አለው፤ ከአሁኑ ባልተናነሰም ያስፈራል፡፡ ኢትዮጵያን የፈጠራት ይሁናት፡፡
ለማንኛውም የተጀመረው የአማራን ኅልውና ትግል ስኬታማ ለማድረግ ከተፈለገ ንጹሕ ኅሊናንና ትክክለኛ የፍትኅ ሚዛንን መጠቀም አማራጭ የለውም፡፡ የክርስቶስን ቃል ሁሌ እንደምንጠቅሰው ብዔል ዘቡል ብዔል ዘቡልን አያወጣም፡፡ ሰበብ ፈልጎ ማዳን እንጂ ሰበብ ፈልጎ መግደል የነፃነት ትግል ዓላማና ግብ ሊሆን እንደማይችል ሁሉም ወገን ካልተገነዘበ ነገረ ሥራችን ሁሉ ታጥቦ ጭቃ ነውና ፋኖ ነኝ የሚል በተለይ ያስብበት፡፡ ጭንቅላቱን እቤቱ ትቶ ሆዱን ብቻ ይዞ ጫካ የወጣ የፋኖ አባል እየተጣራ አስፈላጊው እርምጃ ካልተወሰደበት ሦስተኛ ዓመቱን እያገባደደ ያለው ትግል መቶኛውን እንደማያገባድድ ማንም እርግጠኛ መሆን አይችልም፡፡ አንሸዋወድ፤ በባዶ የተስፋ ሙሌትም ሥነ ልቦናዊ ኮሮጇችንን አንቀብትት፡፡ “ሆድን በጎመን ቢደልሉት ጉልበት በዳገት ይለግማል” ይባላልና የሰበር ዜናዎች ጋጋታ ከቀበሌና ወረዳዎች ካላለፈ ዋጋ ቢስ ነው – እስኪያሰለቸን አየነዋ! በወታደራዊ የዕዝና የኮር፣ የክፍለ ጦርና የብርጌድ፣ የሻለቃና የመቶ አወቃቀር ብዛት ብቻ ጠላትን ማሸነፍ አይቻልም – የሕዝብ ፍቅርና እውን ሊሆን የሚገባው የነፃነት ተስፋ በአጭር ጊዜ ለሚጠናቀቅ የድል ስኬት ዋና ግብኣቶች መሆናቸውን መረዳት ይገባል፡፡
በሌላም በኩል ገና በበረሃ “King” የሚል ቲሸርትና ከናቴራ የምትለብሱ አመራሮችም የሥልጣን ፍቅራችሁን ሰከን ረገብ አድርጋችሁ ትግሉ ላይ ብታተኩሩ ንግሥናውንም ሆነ ጠ/ሚንስርነቱን የሚከለክላችሁ አይኖርም – የልጅነት ጊዜያችሁን ሰውታችሁ ለፍታችሁበታልና፡፡ ራሣችሁን ከትዝብት ታደጉ፤ አጠገባችሁ የሚገኛ ጓደኛችሁና ጠባቂያችሁ ሳይቀሩ ይታዘቧችኋል፡፡ አማራ ባይናገር ቀላል አይምሰልህ፡፡
ፋኖ ትክክለኛ መስመሩን ካልያዘ ልድገመው ትልቅ አደጋ በአማራውያን ላይ ከውስጥም ከውጭም ተደቅኗል፡፡
አማራዬ እግዜር ይሁንህ፡፡ ወደላይ ማንጋጠጥህን ግን አትርሣ፤ ትልቁ ተስፋህ እሱ ነውና፡፡
ትልቁ ሀገራዊ ችግራችንን ልጠቁም፡፡ በ”የማይቆነጥጡት ልጅ ሲቆጡት ያለቅሣል” በሚለው ሥነ ቃል ይህ ችግራችን ሊገለጽ ይችላል፡፡ በሀገራችን መንግሥታት ብቻ ሣይሆኑ የወደፊት ተስፈኛ መንግሥታትና የትጥቅ ትግል ቡድኖችም ራሣቸውን የሕዝብ ልጅና አገልጋይ አድርገው አይቆጥሩም፤ ራሣቸውን እንደጌታ ሕዝቡን እነሱ እንደፈጠሩት የቤት ዕቃና እንደሎሌ ይቆጥሩታል፡፡ በዚህ አመለካከትና እምነታቸው እየተጓዙ ራሣቸውንም ሕዝባቸውንም ሀገራቸውንም ለከፋ ጉዳት ይዳርጋሉ፤ ሁላችንም አልታደልንም፡፡ ይህን አለመታደል እግዚአብሔር የሚሣነው ነገር የለምና በበረከቱ ይለውጥልን፤ አሜን፡፡