“ጋዜጠኛው. . .ጋዜጠኛው፣
ጋዜጠኛው
ኑሮው ልቤን ነካው”
—- ድምጻዊ ቴዎድሮስ ሞሲሳ
ከሰሞኑ በአቶ ጸጋዬ ደበበ ባለቤትነት የሚተዳደረው ሱፐር ደብል ቲ ጄኔራል ትሬዲንግ ስም በመገናኛ ብዙሃን አየር ላይ ናኝቶ ነበር። ኩባንያው ከፈጸማቸው የተለያዩ የመብት ጥሰቶች እና አስጸያፊ ድርጊቶች ባለፈ፣ ብዙዎች ትኩረት የሰጡት እነዚህን ተግባራት “በጽኑ” ለማስተባበል የገንዘብ እና የሃሳብ ስምሪት ተላልፎላቸው በተንቀሳቀሱ ጋዜጠኞች ላይ ነበር። ጉዳዩን በተመለከተ ከመነሻው አንስቶ በትኩረት እየተከታተለ ሲዘግብ የቆየው ጋዜጠኛ ኤልያስ መሰረት፣ ጋዜጠኞቹን በ”አልጀዚራ” እና በ”ኩኪስ” ምድብ ከፍሎ ሰይሟቸው እንደነበር የምታስታውሱ ይመስለኛል። በራሱ ይፋዊ የፌስቡክ ገጽ ላይ የሁለቱ የጋዜጠኞች ምድቦች ምንነት ከዚህ እንደሚከተለው አብራርቶት ነበር፣
“አልጀዚራ:-
በዚህ ምድብ ያሉት ልክ እንደ አልጀዚራ ጋዜጠኞች ትልልቅ የቪድዮ እና የፎቶ ካሜራዎችን ተሸክመው በጋዜጣዊ መግለጫዎች፣ ድግስ፣ ኮንሰርት፣ ኮንፈረንስ፣ የዝነኞች ቤቢ ሻወር፣ ሰርግ… ወዘተ በመሄድ ምስል የሚቀርፁ በመምሰል ይገኛሉ። ብዙዎቹ ግን ቪድዮ መቅረፅ የማይችሉ፣ ካሜራቸውን የውጭ በር ማለፊያ አርገው የሚጠቀሙ ናቸው፣ ከዛም የተገኘውን ምግብም ሆነ የኪስ አበል በመጠቀም ኑራቸውን ይገፋሉ።
ኩኪስ:-
እነዚህኛዎቹ ቁጥራቸው በዛ ያለ ሲሆን አዲስ አበባ ውስጥም ሆነ ክፍለ ሀገር ዝግጅት አለ ሲባል በፍጥነት በመገኘት ይታወቃሉ። ኩኪሶች የሚሰሩበት የሚድያ ተቋም የላቸውም፣ ስራቸው የሚሰጣቸውን መረጃ በግል የፌስቡክ ገፃቸው ማጋራት ነው። የጋዜጠኛ መለያ የሆኑትን እንዴት? መቼ? ለምን? የሚሉ ጥያቄዎችን አይጠይቁም። ተፅፎ የሚሰጣቸውን ጋዜጣዊ መግለጫ (press release) በቀጥታ ያጋራሉ፣ የኪስ አበል እና ኩኪስ/ድግስ ይቋደሳሉ።”
በርግጥም፣ የዛሬ ሳምንት ዓለምገና የዘመቱት ጋዜጠኞች በሁለቱም ምድብ ውስጥ የሚቀመጡ መሆናቸው አያጠራጥርም። እኔም ከጋዜጠኞቹ መካከል አንዷ ነኝና ያለምንም ርህራሄ ራሴን በሁለቱም ምድብ ውስጥ ነው የማስቀምጠው። ምክንያቱም መጀመሪያ ዘገባ ለመስራት እንደቅድመ ሁኔታ የምመለከተው ጉዳይ ውሎ አበል እና ምግብ ነው። ዝግጅቱ “ጠቀም ያለ” ውሎ አበል ካለው፣ ኪሴም ሆነ ጥርሴ ፈገግ እያሉ ዜናውን አሽሞንሙኜ እሰራዋለሁ። ነገር ግን የረባ ምሳ ወይም ኮክቴል የሌለው ዝግጅት ላይ ለዘገባ ከተመደብኩ፣ ዜናውን አኮስምኜ ለአንባቢ አቀርበዋለሁ። አንባቢዎቼ ይህ አካሄዴ በዋናነት ከራሴው የድህነት ሁኔታ (የገንዘብ ድህነት) ጋር እንደሚያያዝ ልታውቁልኝ ይገባል።
የዛሬው ጽሑፌን ዋና ትኩረት “ጋዜጠኝነት እና ድሕነት” በሚል ርዕስ ስር ለመቀንበብ ነበር ዋና ዓላማዬ። ይህ ርዕስ ከሚፈልገው ሰፊ የንባብ አቅም እና ጊዜ የተነሳ ሃሳቤን ወደ ግላዊ ልምዶች እንድቀይር ተገደድኩ። ጽሑፌ የሁለቱ ምድብተኛ ጋዜጠኞች ነባራዊ ሁኔታ ምን እንደሚመስል ይዳስሳል።
ከሁሉም በላይ “የዓለምገና ትዝብቴ” የተሰኘው የጉዞ ማስታወሻዬ የራሳቸውን ጎራ ቀልሰው በሚንቀሳቀሱ “ጋዜጠኞች” ዘንድ አቧራ ማስነሳቱን እዚህ ላይ ለመጥቀስ እወድዳለሁ። የአቧራው መቡነን አንዳንድ ጉዳዩ በቀጥታ የማይመለከታቸውን ዜጎች እያሰቃየ እንደሚገኝ የተለያዩ መረጃዎች ደርሰውኛል። እንግዲህ መራር ሃቅ ሲወጣ፣ ተጓዳኝ እና አላስፈላጊ ጉዳት ለሚገጥማቸው ሰዎች ከወዲሁ ሃዘኔን እየገለጥኩ፤ ወደ ዋና ነጥቤ ልመለስ።
እኔ ወደ ጋዜጠኝነት ሞያ ከገባሁ ወደ አስርት ዓመታት ገደማ እየተጠጋሁ ነው። በዚህ የጋዜጠኝነት ሕይወቴ ክፉንም ደጉንም ተመልክቼአለሁ። የሞያተኞቹን ደግ እና ዕኩይ ተግባራት ወይም ባሕርያት ታዝቤያለሁ። ከሁሉም የሚደንቀኝ ነገር አንዳችም ሞያዊ አቅም ሳይኖራቸው የጋዜጠኝነት መድረኩን ያጣበቡ ሰዎች መብዛታቸው ነው። በተቃራኒው ደግሞ፣ የሞያው ፍሬ ነገር ገብቷቸው ለመስራት እየሞከሩ፣ ግና በገንዘብ ዕጥረት የሚሰቃዩ በርካታ ጋዜጠኞች አሉ።
በኢትዮጵያ ከመንግስት ቀጥተኛ ቁጥጥር ውጪ ባሉ የግል መገናኛ ብዙሃን ተቀጥረው የሚሰሩ ጋዜጠኞች በጋራ የሚያሰቃያቸው አንዳች ሕመም አለ፤ እርሱም “ድህነት” ይባላል። በተቋማቸው የሚከፈላቸው ገንዘብ ከቤት ኪራይ እና ከዕለት ጉርስ ባለፈ፣ ሌላ የተሻለ ነገር የሚያሰራ አይደለም። ይህም የደመወዝ ዝቅተኝነት ወደ “አልጀዚራ”ነት ይገፋፋቸዋል። ተቋማቸው አሰማርቷቸው ከሚሄዱበት ዝግጅት ሌላ፣ ራሳቸውን ደብቀው ባልተጠሩበት ድግስ ላይ ድንኳን ሰባሪ ሆነው ይመጣሉ፤ ችግር የወለደው ዕርምጃ!
ሌሎቹ — ከላይ በጥቂቱ የጠቃቀስኳቸው — በድሮ ዓመታት በመጽሔቶች፣ በጋዜጦች እና በሌሎች የመገናኛ ብዙሃን ዘዴዎች ላይ ተቀጥረው ሲሰሩ ወይም ተቋማቱን በባለቤትነት ሲያስተዳድሩ የነበሩ “ጋዜጠኞች”፣ አንድ የፌስቡክ ገጽ ወይም የዩቲዩብ ቻናል ከግለሰብ በመግዛት፣ አዲስ የ”ሚዲያ” ስም በመሰየም የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ናቸው። እነዚህ ግለሰቦች በየጋዜጣዊ መግለጫው፣ በየሁነቱ የሚገኙ በመሆናቸው በጣም ይታወቃሉ (በዓለምገናው ጉዞ ላይ በተነሷቸው ፎቶግራፎች ላይ በሰፊው የታዩት ናቸው)። ለእነርሱ ድንኳን መስበር የዕለት ተለት ገቢ እንጂ ተጨማሪ ገንዘብ አይደለም። የትኛውም ዓይነት ሁነት ቢጠፋ፣ ሕልውናቸው ያከትማል፤ ዕድሜም አይኖራቸውም።
የሰዎቹን ስም አልጠራም፤ ነገር ግን በየሁነቱ ወይም በየጋዜጣዊ መግለጫው፣ ጠጋ ብለው ቢሞክሩት የማይሰራ ማይክራፎን ከሎጎ (አርማ) ጋር አሰርተው ሲደቅኑ የሚያዩዋቸው ሰዎች ያውቋቸዋል — ይህንን ጽሑፍ ሲያነብቡ። “የማይሰራ ማይክራፎን?” በማለት የምትደነቁ አንባቢዎቼ እንደምትኖሩ ርግጠኛ ነኝ።
አትደነቁ፤ ሌሎች የቴሌቪዥን ጣቢያዎች አርማዎቻቸውን ያነገቡ ማይክራፎኖችን ስለሚይዙ “ተዓማኒ ናቸው” ብለው ለሚያስቡ፣ ለእነዚህ ሰዎች፤ ይህ የማጭበርበር ስራቸው “የመጠቀ እና የተመሰጠረ” መስሎ ነው የሚታያቸው። ግና ማይክ ደቅነው የቀረጹትን ዝግጅትም ሆነ ቃለ መጠይቅ በፌስቡክ ገጻቸው ወይም የዩቲዩብ ቻናላቸው ላይ ለተከታዮቻቸው ሲያጋሩ አንመለከትም፤ ለምን? “አልጀዚራ” ስለሆኑ!
የሚያሳዝነው ነገር እነዚህን ሰዎች በአክብሮት ጠርተው፣ “ሞቅ ያለ” ውሎ አበል ከፍለው የሚጋብዟቸው መንግስታዊ እና የግል ተቋማት መኖራቸው ነው። የየተቋማቱ የሕዝብ ግንኙነት ክፍሎች ስለእነዚህ “ጋዜጠኞች” ምንነት እና ስራ ለማጣራት ጊዜ የላቸውም። ስራ በዝቶባቸው ሳይሆን፣ ከሰዎቹ ጋር የጥቅም ሽርክና ስላላቸው ነው። የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊዎችን ልብ ይሏል!
ይግረማችሁና እነዚህ ሰዎች የዕዝ ማዕከል አላቸው። ማዕከሉ በትልቅ ሕንጻ ውስጥ የሚገኝ ከመሰላችሁ ተሳስታችኋል። በአንድ የአዲስ አበባ ኮስማና ሰፈር ውስጥ በሚገኝ አረቄ ቤት ግለሰቦቹ ተሰባስበው ከየመረጃ ምንጮቻቸው የመጡትን የ“ይዘገብልኝ” ደብዳቤ ይከፋፈላሉ፤ የዓይኑ ቀለም ያላማራቸው “የሚመታ” (በሃሜት ስሙ የሚጠፋ) ግለሰብ ካለ፣ ወሬ ይቀመማል፤ ይሰራጫል። በቀረው ጊዜ ደግሞ፣ ሌሎች አጓጉል ተግባራትን ያከናወናሉ። (ለአንባቢ ክብር ስል፣ ድርጊቶቹን ከመጥቀስ እቆጠባለሁ!)
ጋዜጠኞቹን በአበል የሚያሰባስብ አንድ ግለሰብ ደግሞ አለላችሁ፤ ስሙን አልጠቅስም። ይህ ሰው ብዙ ዓይነት ማዕረግ አለው። ጋዜጠኛ፣ ፕሮሞተር፣ የማስታወቂያ ባለሞያ…ብዙ ቅጽል ስሞች አሉት። በየጋዜጣዊ መግለጫው ለሚመጡ ሪፖርተሮች የውሎ አበል መክፈል ያለማመደው “እርሱ ነው” ይባላል። ይህም ከዘጠኝ ዓመታት በፊት ማለት ነው። ቀስ በቀስ የክፍያ መጠኑን በማሳደግ ጋዜጠኞችን በቁጥጥሩ ስር ማዋል ችሏል። ይሁንና ሰውዬው መሰረታዊ የጋዜጠኝነት ዕውቀት የሌለው “ምስኪን” ሰው ነው። ሆኖም ግን ድፍረት ብቻ ነው እዚህ ደረጃ ያደረሰው። ኢትዮጵያ ውስጥ ድፍረት ወለድ ስራዎች በየጊዜያቱ የወለዱት ጥሩ ልጅ የላቸውም፤ ከብልሹነት በስተቀር!
እነዚህ የሙሉ ጊዜ “አልጀዚራ” እና “ኩኪስ” ጋዜጠኞች የኢትዮጵያን የጋዜጠኝነት መድረክ በአቅመ ቢስነታቸው ጥልቀት እየበከሉት ነው። ይህም ቢቀር እንኳ፣ ጥያቄ የሚያነሱ እና ከእነርሱ የቡድን ጠገግ የራቁ ጋዜጠኞችን ጠልፈው ለመጣል ብሎም ለመስበር እየተንቀሳቀሱ ነው። ከኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ሕጋዊ የዲጂታል ሚዲያ ፈቃድ ሳይኖራቸው፤ የንግድ ፈቃድ እና የግብር መክፈያ ቁጥር (ቲን ነምበር / TIN Number) ሳያወጡ በሃሰተኛ ማሕተም እና የመገጣጠሚያ ደብዳቤ ብዙ ሺሕ ብሮችን ወደ ሒሳብ ቁጥራቸው ገቢ የሚያደርጉ ናቸው። እናም፣ እስከ መቼ ነው ዝም የሚባሉት?
እነጳውሎስ ኞኞ፣ እነሙሉጌታ ሉሌ፣ እነበአሉ ግርማ ያቀኑት የጋዜጠኝነት ክብር ወደ ቀድሞው ስፍራ ለመመለስ ጊዜው መቼ ነው?