October 20, 2024
9 mins read

አቶ ታዲዮስ ታንቱንም እንደ ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ?

ግርማ እንድሪያስ ሙላት

tadewes tantu
tadewes tantu
የሐሰት ትርክት ፈጣሪዎችንና ቀባጣሪዎችን፤ ባወቁት፣ በተማሩበትና በኖሩበት ልክ ስለ ፖለቲካ ትክክለኛነት  (Political correctness) ሳይጨነቁ፣  ‘ዶማ’ ን ፣ ‘ዶማ’ ብለው የሚገልጹት፤ አንጋፋው ጋዜጠኛና የታሪክ አዋቂ  ታዲዮስ ታንቱ ከታሰሩ ዓመታት ተቆጥሯል። በዘጠና ዕድሜ መዳረሻቸው ላይ መስዋዕትነት እየከፈሉ ያሉ የታሪክና የዕውነት አባት ታዲዮስ ታንቱን አለማንሳት፣ አለመጥቀስ፣ አለማስታወስ ውለታ ቢስነት ብቻ ሳይሆን ወጪት ሰባሪነት ነው።
በቀደመው  ኢሕአዴግ (ወያኔ) ጊዜ  ታዲዮስ ታንቱ በአገዛዙ ተይዘው ወደ ወሕኒ ቤት ተጋዙ። በመግቢያው በር ላይ ሁሉም ታሳሪዎች  ብሔራቸውን እየተጠየቁና እየተናገሩ ነበር የሚገቡት። ታዲያ የታዲዮስ ታንቱ ተራ ደርሶ:-
” ብሔርዎት?!” 
”ኢትዮጵያዊ”
ጠያቂውም:-
”አማራ ብለህ መዝግባቸውና አስገባቸው!” እንዳላቸው አብረዋቸው ታስረው ከነበሩ ሰዎች አድምጫለሁ። (ታዲዮስ ታንቱ የደቡብ ሰው መሆናቸውን ልብ ይሏል)
ታዲዮስ ታንቱ ለአማራው ከአማራው በላይ ተሰቃይተዋል። ተንገላተዋል። ተዘልፈዋል።የኢትዮጵያዊነት ውሉንና መሠረቱን ለቀጣፊዎች ለማስረዳት ብዙ ማስነዋል። የዘሩትም ዕውነት በብዙዎች ህሊና ውስጥ ተቀምጧል። መታደል ነው።

የታዲዮስ ታንቱ እስር፣ ምጸቱ፣ ፖለቲካው፣ ብልግናው፣ ጭካኔውን ላስተዋለው ዘግናኝ ነው።

ከምፀቱ እንኳን ብንጠቅስ አቃቢ ሕግ ”ምስክሬ” ብሎ ካቀረባቸው አንዱ ፕሮፌሰር  ብርሃኑ ነጋ መሆኑ  ነው። ቢያስገርመንም፤ አያስደነግጠንም። ብርሐኑ ነጋ የአድርባዮች ቁንጮ ነው። ታዲዮስ ታንቱም በነበራቸው የተለያዩ ቃለ – መጠይቆች ላይ የብርሐኑ ነጋን ”አድርባይነት፣ ፈታላነትና ጎባጣነት፤” ሳያለሰልሱ ይገልጹ ነበር። በዚያ ላይ እኚህን ቀጥተኛና ግልጽ፤ ቆራጥና አዋቂ የሆኑ ሰውን፤ የብርሐኑ ዓይነት ሰዎች ይጠየፏቸዋል። ለዚያም ይሆናል ለአቃቢ ህግ ብርሐኑ እራሱ ”ምሥክር ካልሆንኩኝ” ብሎ አቤቱታ ያቀረበው – የተባለው። አድርባይ ፕሮፌሰር ፤ ምስክር ብቻ ሳይሆን ”ሽጉጥ አውጥተህ ፤ ግደል!…” ቢባል ከመግደል አይመለስም።

”ለአመታት በእስር ላይ የሚገኙት  አቶ ታዲዮስ ታንቱ በተከሰሱባቸው የጥላቻ ንግግር ማሰራጨት እና የእርስ በእርስ ግጭት መቀስቀስ ወንጀሎች ጥፋተኛ መባላቸው ታውቋል፡፡” ይሄ ሰሞኑን የተለቀቀ ዜና ሲሆን፤ ፍርድ ቤቱ  ለሌላ ቀጠሮ ማለትም ለጥቅምት 12 ቀን 2017 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡”

ይሄ የጥላቻ ንግግር የሚባል ክስ  ጋዜጠኞችን፣ አማራዎችን፣ የአማራ ጠበቃዎችን  የኢትዮጵያ አርበኞችንና ለዕውነት የቆሙትን ሁሉ የሚያጠቃ  መሆኑ ደግሞ አሳሳቢም፣ አናዳጅም ያደርገዋል።

የጥላቻ ንግግር ?…

1. አብይ አህመድ ፤ ”ኦሮሞ ጠል ማህበረሰብ አዲስ አበባ ውስጥ አለ። የቀን ጅቦች፣ በአንድ ሌሊት መቶ ሺ ሰው ታርዶ ሊያድር ይችላል፣….” ወዘተ…. ለነገሩ  የአብይማ የጥላቻ ንግግር  የዶሮ ወጥ አሠራር  ድረስ ይሄዳል።

2. ሽመልስ አብዲሣ፤  ”አማራን እንዳይነሳ አድርገን ሰባብረነዋል።”

3. ጃዋር መሐመድ፤  ”እኛ ጋር ቀልድ የለም። አንድ ሰው ቀና ካለ በሜንጫ ነው አንገቱን የምንቆርጠው” ”Ethiopia out of Oromia”

4. በቀለ ገርባ፤ ”አንድም ኦሮሞ ከአማራዎች ጋር እንዳይገበያይ ኦሮምኛ ካላወራ አትግዛው፣ አትሽጥለት፣ ሴቶችም እንዳታገቡ”

ሌሎችም ብዙ መጥቀስ ይቻላል። ከላይ በመጠኑ የተናገሩትን ያስቀመጥኩት የፍቅር ስሜት ቀስቃሽ (Romantic) ወይም የሠላም ቋንቋ ሳይሆን የሚያጨራርስ፣ የሚያጋድል የሚያነታርክ የጥላቻ ንግግር መሆኑን ለማነጻጸር ነው። የተናገሩት ሰዎች ደግሞ በተለያየ የሥልጣን እርከን ላይ መገኘታቸውና ጠ/ሚ ሁሉ መሆኑን ሲያስቡ ታዲዮስ ታንቱን መክሰስ ውሃ አይቋጥርም። አያነሳም።አለያም የታሰሩት ከመጠንም፣ ከአቅምም በላይ ነው።

በዕውነቱ ሐሳብን በነጻነት በመግለጽ መብታቸው የተጠቀሙትና መከራ እየወረደባቸው ያሉት አዛውንት ላይ፤ ፍትሕ በእጅጉ አላግጧል። ጨክኗል። ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ በሥልጣናቸውም በምግባራቸውም በአስተሳሰባቸውም  ኢትዮጵያን ሲገድሉ ”አማራውንና ኦርቶዶክስ ኃይማኖትን አከርካሪውን ሰብረነዋል” ሲሉ የነበሩትን፣ ንጹሐኖችን ያለምንም ሐጢያታቸውና ወንጀላቸው በየ እስሩና ወሕኒው ሥልጣናቸውን መከታ በማድረግ ሲያግዙ፤  ንብረቱንም ሲዘርፉ የነበሩት ”አቦይ” ስብሐት ”ዕድሜያቸው በመጥናቱና በመግፋቱ” ነበር ፤ የመፈታታቸው ሰበብ እናም፣ ምክንያት።

ታዲያ፣ ታዲዮስ ታንቱ ዕድሜያቸው አልገፋምን?!   ዕድሜ ማስተዛዘኛ የሚሆነው ለስብሐት ብቻ ነውን?… እንጠይቃለን። እናዝናለን። ያሳስበናልም። 

ለተዛባውና ለተጣመመው፣ አድሎና ውስልትና ላለው የፍትሕ ስርዓታችሁ፤ የእኚህ አዛውንት መከራና እንግልት ትልቅ ማሣያ ነው። ። በእርግጥ ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስም ይህ ዕጣና መከራ ነበር ገጥሟቸው፣ ያለፉት። አሁንም  እየጠበቃችሁት ያላችሁት የአቶ ታዲዮስ ታንቱን መታመማቸውን ወይም መድከማቸውን መሆኑን ድርጊታችሁ በእጅጉ ያሳብቃል።

ግን ስንት ጊዜ ነው የሰው ሕይወት ስታመነዥጉ የምትኖሩት?!..እናም አቶ ታዲዮስ ታንቱን ቢቻል ካሳ ከፍላችሁ፣ አለያም ተጸጽታችሁ፤ ልቀቋቸው። ”ፕሮፖጋንዳ” ዝም ተብሎ በጭካኔና በዋልጌነት ተሰርቶ አይውቅም። ለናንተም ”ፖለቲካ” የሚሆነው ሕፃናቶችን በድሮን ባለማሰቃየትና ባለመጨፍጨፍ፤ እንዲሁም እኒህን መሠል አዛውንቶችን ባለማንገላታትና በመፍታት እንጂ፤ አስሮ እስከወዲያኛው በመግደል አይደለም።  እናም እጠይቃለሁ፣ እንጠይቃለንም። አቶ ታዲዮስ ታንቱንም እንደ ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ?!

 

ግርማ እንድሪያስ ሙላት

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop