ምስል ፩፦ የአንሚ (UNMEE) የ25 ኪሎ ሜትር ጊዜያዊ የደህንነት ቀጠና (TSZ) ካርታ። ምንጭ: African Arguments / Ethiopia Eritrea Temporary Security Zone | African Arguments
ባለፉት ጥቂት ወራት የኢትዮ–ኤርትራ ግንኙነት እንደገና ሻክሮ፣ በድንበራቸው አካባቢ የጦር ደመና አንዣቧል። ይህን ውጥረት ለማርገብ ከተለያዩ ወገኖች በርካታ መላምቶችና የመፍትሔ ሃሳቦች እየተሰነዘረ ይገኛል። ከእነዚህም መካከል ዋነኛው፡ ሁለቱን ተፋላሚ ኃይሎች የሚያራርቅ የደህንነት ቀጠና መተግበር ያሻል የሚለው ምክረ–ሐሳብ ይገኝበታል።
ለምሳሌ ጆና ብሮዲ እና ሮበርት ሶፍጄ የተባሉ አጥኚዎች በ”ስሞል ዎርስ ጆርናል” (Small Wars Journal) ላይ በሰሞኑ ያሳተሙት የጥናት ውጤት እንደሚያስረዳው፤ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የሚቀሰቀስ ጦርነት የዓለም አቀፍ መርከቦችን ማጓጓዣ ወጪ በእጅጉ ይጨምራል። ከዚህም በላይ በሁቲዎች ጥቃትና በሆርሙዝ ወሽመጥ አለመረጋጋት ምክንያት ቀድሞ የነበረውን ቀውስ የሚያባብሰው በመሆኑ፣ ቀይ ባሕር ወደ ለየለት አደገኛ ቀጠና እንዳይቀየር ለመከላከል በ1992 ዓ.ም ሁለቱን ሠራዊቶች ለማራራቅ ተተግብሮ የነበረውን ሞዴል እንደገና መጠቀም እንደሚገባ መክረዋል። (በነገራችን ላይ፣ ሮበርት ሶፍጄ የዩናይትድ ስቴትስ የባሕር ኃይል ኮርፕስ የአውሮፓና አፍሪካ ኃይሎች የቀድሞ አዛዥ የነበሩ ጡረታ የወጡ ሜጀር ጄኔራል ናቸው።)
ይህ አማራጭ በዓለም ዙሪያ ግጭቶችን በማስቀረት ረገድ ውጤታማነቱን ያስመሰከረባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት አይደሉም። በቆጵሮስ ደሴት “አረንጓዴ መስመር”፣ በእስራኤልና ሶሪያ መካከል በጎላን ኮረብታ ላይ የተበጀው ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነፃ ቀጠና፣ በፊንላንድና ስዊድን መካከል የሚገኘው የአላንድ ደሴቶች፣ እንዲሁም በሁለቱ ኮሪያዎች መካከል ያለው ከወታደር ነፃ ድንበር (DMZ) ሁነኛ ማሳያዎች ናቸው።
ሆኖም “ሜንዲንግ ዎል” በሚለው ዝነኛ ግጥሙ “ጥሩ አጥር ጥሩ ጎረቤት ይፈጥራል” የሚለውን አባባል ያቀበለን ገጣሚው ሮበርት ፍሮስት፤ “ለመሆኑ አጥሩ ለምን ዓላማ ያገለግላል?” ብለው ሳይጠይቁ ግድግዳ የመገንባቱን አግባብነት በምፀት ሞግቷል።
በብሉይ ኪዳን ሥርዓት የሕዝቡን በደል ተሸክሞ ወደ በረሃ ይላክ የነበረው “የጦስ ፍየል” (Scapegoat) ማኅበረሰቡን ከጥፋት እንደሚታደገው ሁሉ፣ የደህንነት ቀጠናውም የሁለቱን ባላንጣዎች ቁጣና ቅጣት በላዩ ላይ ተቀብሎ ያለ አበሳው መስዋዕት ይሆናል፤ ሰላሙን ለሌሎች አስገኝቶ ራሱ ግን ቀዳሚ ሰለባ ሆኖ ይቀራል። ከአንድ ክፍለ ዘመን በኋላ፣ ያ ጥያቄ ዛሬም ውጥረት በማያጣው የአፍሪካ ቀንድ እንደ አንድ መፍትሄ ብቅ ብሏል።
ከቀድሞው ውጥረት ማስታገሻ እስከ አዲሱ የጂኦፖለቲካ ጥያቄ
ከ1990–1992 ዓ.ም. ተከስቶ የነበረውና በወቅቱ በአውሮፓ ጋዜጦች “ትርጉም የለሽ እና ዕብደት የተሞላበት ጦርነት” (“Senseless” and “Absurd” war) እየተባለ ይጠራ የነበረው አጥፊ የኢትዮ–ኤርትራ ትዝታ ድጋሚ እንዳይቀሰቀስ ተሰግቷል። ጦርነት ከተቀሰቀሰ የሚሳተፉት የሁለቱ አገራት መደበኛ ሠራዊቶች ብቻ አይሆኑም። ይልቁንም በርካታ አካላት የሚካተቱበትና ውጊያውም የመስፋፋትና የመወሳሰብ አደጋ ይኖረዋል። ኃያላን መንግሥታት ጉዳዩ በእርጋታ እንዲያዝ ቢመክሩም፣ በሚዲያ የሚስተጋቡ ድምፆች ግን ወደ ግጭት ያደሉ ይመስላሉ። ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት በኩልም አሳዶ መምታት “Hot Pursuit” የሚለው ጽንሰ–ሐሳብ እንደ ተገቢ ቀጣይ እርምጃ ሲንጸባረቅ ይታያል።
በዚህ ውጥረት ውስጥ፣ ቀድሞ ተተግብሮ የነበረውን የ25 ኪሎ ሜትር “ጊዜያዊ የደህንነት ቀጠና” መመለስ ዛሬም ሌላ ጥፋትን ይከላከል ይሆን? የሚለው ጥያቄ ጠለቅ ያለ ምርመራን ይጋብዛል። አማራጩ ጦርነትን ለአፍታ ለማስቀረት ሊረዳ ቢችልም፣ ሐሳቡን እንዳለ ከመቀበል ይልቅ “በእርግጥ ዘላቂ ሰላም ያመጣል? ወይስ አደጋውንና ዋጋውን ወደ ሌላ አካል ማዛወሪያ ብቻ ነው?” ብሎ መጠየቅ ያሻል።
ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠው ምላሽ በኢትዮ–ኤርትራ ድንበር ወሰን ብቻ የሚታጠር ሳይሆን፤ ከዱር አራዊት እስከ አርብቶ አደሮች ምድር፣ ከኃያላን አገራት ሚዛን እስከ ታሪካዊ ቀውሶች ሰፊ ጂኦፖለቲካዊ አውድ የሚወስደን ጉዳይ ነው።
የተፈጥሮ እና የታሪክ የወሰን ደንቦች
ልብ ስለማንለው እንጂ ሰዎች ዓለም አቀፍ ድንበሮችን ከመፍጠራቸው እጅግ ቀደም ብሎ፣ ተፈጥሮ የራሷን የወሰን ደንቦች አበጅታ እንደነበር ለመረዳት የዱር እንስሳት ባዮሎጂስቱ ዴቪድ ሜች ይፋ ያደረጉትን የጥናት ውጤት መመልከት ጠቃሚ ነው። ግራጫ ተኩላዎች ክልላቸውን ከተቀናቃኝ የተኩላ መንጎች በጽኑ ስለሚከለክሉ እያንዳንዱ የተኩላ መንጋ የራሱ ነጻ የተከለለ የስምሪት ስፍራ አለው። ሆኖም በሁለት መንጎች የስምሪት ስፍራዎች መካከል በሁለቱም መንጎች የማይደረስበትና የሚከባበሩበት ሰፊ ስፍራ ይፈጠራል።
በሚያስደንቅ መልኩ፣ ይህ አይነኬ የድንበር ስፍራ (“No Wolfs Land”) እንደ አጋዘን ላሉ ታዳኝ እንስሳት ምቹ ግጦሽና የመሸሸጊያ ይፈጥርላቸዋል። ለሁለቱም ተፎካካሪ አዳኝ የተኩላ መንጋዎች ዋስትና አደገኛ የሆነው አማካይ ቀጠና በተቃራኒው ለታዳኝ አራዊት አስተማማኝ ከለላ ይሆናል ማለት ነው።
የተለያዩ ማኅበረሰቦችም ቢሆኑ የደህንነት ስፍራን ለማስፈን (“የማርያም መንገድ እንዲሉ”) የተለያዩ ስርዓቶችን ይመሰርታሉ። ለምሳሌ በተፎካካሪ የሥልጣን ግዛቶች መካከል እንደ ተራራ፣ ረግረጋማ ስፍራ፣ ወንዝ፣ የሳር ሜዳ ያሉ መሬቶች እንደ ተፈጥሯዊ ድንበር መለያ ተደርገው ጥቅም ላይ ይውሉ ነበር። በመካከለኛው ዘመን አውሮፓ “ማርች” በመባል የሚታወቁ የድንበር ከለላ ተብለው የተሰየሙ ቦታዎች፣ ወታደራዊ ቅድመ–ማስጠንቀቂያ በመስጠትና ከኃያላን ጎረቤቶች የሚሰነዘርንድንገተኛ ወረራና ጫና በመግታት ረገድ እንደ ውጥረት ማስታገሻ ሆነው ያገለግሉ ነበር። ስፍራው የግድ ሰዎች የማይንቀሳቀሱበት ባዶ ቦታ ሆነ ማለት ሳይሆን ተፎካካሪ ፍላጎቶች ስልታዊ በሆነ መንገድ በሰላም የሚስተናግዱበት ቦታ ነበር።
የኢትዮጵያ የአርብቶ አደር ወሰኖች ጠባይ
የኢትዮጵያ አርብቶ አደሮች የደህንነት ቀጣናን እንደ ውጥረት ማስተንፈሻ (Safety Valve) ስለመጠቀማቸው ተጨባጭና ሕያው ምሳሌ ማቅረብ ይቻላል። በደጋማው የአገሪቱ ክፍል የተረጋጋ የሰብልና የከብት እርባታ ስራ፣ በቆላማው ደግሞ የዘላን እና ከፊል ዘላን አርብቶ አደሮች የኑሮ ዘይቤ ይካሄዳል፤ በመሀከላቸውም በካርታ ላይ ያልሰፈረ፣ ግን ደግሞ በመደበኛነት የማይገሰስ ባህላዊ እና ምናባዊ ወሰን አለ።
በአዋሽ ሸለቆ የሚኖሩትን የከረዩና የኢቱ አርብቶ አደሮች እንደ አብነት ብንወስድ፤ በባህላቸው “ከሎ” በመባል የሚታወቁ ለችግር ጊዜ እንደ መጠባበቂያ የሚያገለግሉ ከንክኪ ነጻ የሆኑ የግጦሽ ስፍራዎች ያኖራሉ። እነዚህ የተከለሉ ቦታዎች በድርቅም ሆነ በሌላ ምክንያት መደበኛ የግጦሽ ስፍራዎች በሚመናመኑበት ወቅት ብቻ እንደ ሥነ–ሕይወታዊ ዋስትና (Ecological Insurance) በመሆን ያገለግላሉ።
የአርብቶ አደሩ አሠራሮች ዘወትር የሚተገበሩ፣ ፍትሐዊ እና ከግጭት የጸዱ ላይሆኑ ይችላሉ። ሆኖም በችግር ወቅት የሚከሰት ፉክክርና ፍጥጫ ወደ ግጭት እና ጦርነት ከመቀየሩ በፊት ጫናን በመቀነስ ረገድ የመደገፍና የውጥረት ማስታገሻ Ecological Shock Absorber) ሚና ይጫወታሉ።
ነገር ግን ኢትዮጵያ ከ1985 ጀምሮ በሥራ ላይ ያዋለችው በብሔርና ቋንቋ ላይ የተመሠረተው የፌዴራሊዝም አወቃቀር፣ የተዳከሙ ባህላዊ ተቋማት እና የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖዎች ተነባብረው፣ ቀድሞ ጉልህ ጠቀሜታ የነበራቸው አገር በቀል የደህንነት ማስጠበቂያ ሥርዓቶችን እየሸረሸሯቸው ይገኛሉ፤ በውጤቱም የግጭቶች መበራከትና አስከፊነት መጠን እያየለ መጥቷል።
የእነዚህ ተሞክሮዎች የሚያመላክተው፣ የጉዳዩ አድማስ ከአርብቶ አደሩ የደህንነት ማስጠበቂያ ስርዓት ዘልቆ የተሻገረ መሆኑን ነው። የፖለቲካ ጂኦግራፊ ምሁሩ ሮበርት ሳክ እንደሚያስረዱት፤ የሰዎች የመሬት ይዞታቸውን የመከለል ባሕሪ (Human Territoriality) ማለት አካባቢያዊ ቦታን በመቆጣጠር በሰዎች እንቅስቃሴና ሀብት አጠቃቀም ላይ ተፅዕኖ የማሳደር ስልት ነው። የኢትዮጵያ አርብቶ አደሮች ተሞክሮ የሚያሳየው፣ ወሰኖች ውጤታማ የሚሆኑት በፍጹም የማይታለፉ ግድግዳዎች ሲሆኑ ሳይሆን፣ የጋራ ሀብቶችን አጠቃቀምና የእንቅስቃሴ መብቶችን በሚያስከብሩ ዘርፈ ብዙ ባህላዊ ደንቦች ሲተዳደሩ ብቻ ነው። ባህላዊ ተቋማት በተዳከሙና እንቅስቃሴዎች በድንበር በታታጠሩ ቁጥር፣ የውጥረት ማርገቢያ የነበረው ያ ወሳኝ የማስተንፈሻ ስፍራ ራሱ ለግጭት ማቀጣጠያነት መዳረጉ አይቀሬ ነው።
ሀገር እንደ “ውጥረት ማርገቢያ”፡ ከሞንጎሊያ እስከ ወሎ
አንዳንዴ አንድ ሙሉ ሀገር ራሱ የሌሎች አገራት የደህንነት ማስጠበቂያ ቀጠና ሆኖ የሚያገለግልበት አጋጣሚ አለ። በሩሲያና ቻይና መካከል የምትገኘው ሞንጎሊያ ቀዳሚ ምሳሌ ናጥ ሞንጎሊያ ከሁለቱም ኃያላን ጋር ያላትን ግንኙነት በጥንቃቄ እያመዛዘነች “ሦስተኛው ጎረቤት” በተሰኘው ዲፕሎማሲያዊ ስልቷ ሚዛኗን ጠብቃ እየኖረች ነው። ኔፓል፣ አፍጋኒስታንና አርሜንያም ተመሳሳይ የጂኦግራፊ ዕድልና ፈተናን ያስተናግዳሉ። እነዚህ አገራት በኃያላን ጎረቤቶች መካከል ተሸንቅረው በመገኘታቸው ስትራቴጂካዊ የሚያደጋቸውን ያህል፣ በሌ በኩል የደህንነት ዋስትናቸውን ፈተና ላይ ይጥለዋል።
በሀገር ውስጥ ደረጃ ደግሞ ወሎ የዚሁ ተቃርኖ ግልጽ ማሳያ ሆና ትገኛለች። የወሎ መልክአ–ምድር አቀማመጥ ለብዝሃ–ቋንቋ፣ ለባህልና ለሃይማኖቶች መቻቻል በርካታ ትሩፋትን እንዳጎናጸፏት ሁሉ፣ በሌላ በኩል ግን የሃያላን ተቀናቃኝ ጎረቤቶቿ ጦሮች መተላለፊያና የደም አውድማ አድርጓታል። ደራሲ ብርሃኑ ዘሪሁን “ማዕበል፡ የአብዮት ዋዜማ” በተሰኘው ድንቅ መጽሐፉ ታሪካዊቷን ወሎን እንዲህ ሲል ይገልጻታል፡
“የመልክአ ምድር አቀማመጥ የፈረደበት ይመስል፣ ትግሬው ወደ ሸዋ ሲዘምት፣ ሸዋ በትግሬ ላይ ክተት ሲል፣ አማራው አዳሉን ለመውረር ቆላ ሲወርድ፣ ኦሮሞው ለመበቀል ደጋ ሲወጣ፣ ወሎ ለብዙ ክፍለ ዘመናት ጦር ሲተላለፍበት፣ ሰራዊት ሲራኮትበት፣ ሲራገጥበት፣ ሲፋለምበት፣ ወታደር ሲመራበት፣ አንዱ ሲዘርፈው ሌላው ሲያቃጥለው ኖሯል…።” (ገጽ 57፤ 1973 ዓ.ም.)
ለደህንነት የተመሰረተ ቀጠና የባላንጣ ግዛቶችን ከቀጥታ ግጭት ሊታደጋቸው የሚችለው፣ በእነሱ ላይ ሊያርፍ የሚችለውን ከባድ ጫና እሱ ራሱ እየተቀበለ ውጥረቱን ስለሚያረግብላቸው ነው። ይህ ማለት ልክ በመኪና ላይ እንደሚገጠም የመጋጫ አካል (Crumple Zone) ነው፤ የመኪናውን ውስጣዊ ክፍል የሚታደገው እሱ ራሱ አፈፍ ብሎ በመጨፈለቁ ነው። ደግሞም ያ ክፍለ–አካል ለዚህ ድርሻው ፈቃደኛ መሆኑን የሚያማክረው አካል የለም።
የደህንነት ቀጠናው ነዋሪዎች ግን እንደ ብረት ግዑዝ አይደሉም፤ ፈቃዳቸውና ስቃያቸው ዋጋ አለው። በጂኦፖለቲካዊ ቋንቋ ሲገለጽ፣ የእነዚህ መካከለኛ ቀጠና ነዋሪዎች ለአካባቢው ሰላም ሲሉ ያልተመጣጠነ ከባድ ዋጋ ይከፍላሉ።
ይህ አሳዛኝ እውነታ የጂኦግራፊ ምሁሩ ጆን አግኒው “የይዞታ ወጥመድ” (Territorial Trap) ብለው የጠሩትን አስተሳሰብ ያጎላል። ይኸውም፣ የፖሊሲ አውጪዎች ድንበርን በካርታ ላይ እንደ ታሸገ ባዶ ዕቃ የመመልከትና በዚያ መሬት ላይ የሚኖሩትን ሕያው የሰው ዘር ትስስርና ማኅበረሰቦችን የመዘንጋት አዝማሚያ ነው። በወታደራዊ ካርታ ላይ እንደ ባዶ የመለያያ መስመር የሚታይ ቀጠና፣ በመሬት ላይ ግን የሰዎች ሕይወት የሚካሄድበትና የዚያን የመራራቅ ከባድ ዋጋ በግንባር የሚከፍል ምድር ነው።
የ25 ኪሎ ሜትሩ ሙከራ እና የ21ኛው ክፍለ ዘመን የቴክኖሎጂ ፈተና
ከ1990–1992 ዓ.ም የኢትዮ–ኤርትራ ጦርነት በኋላ በኤርትራ ግዛት ውስጥ ተቋቁሞ የነበረው የ25 ኪሎ ሜትር “ጊዜያዊ የደህንነት ቀጠና”፣ ላጭር ጊዜ የተኩስ ልውውጥ ማስቆሙ አይዘነጋም። ሆኖም የፖለቲካ ውጥረቱ ባለመብረዱና በሰላም አስከባሪው (አንሚ) እንቅስቃሴ ላይ በደረሱ ገደቦች ሳቢያ ተልዕኮው በአጭሩ ከሽፏል።
የኤርትራው ተሞክሮ ያረጋገጠልን መራራ እውነታ ቢኖር—በ25 ኪሎ ሜትር አካላዊ መራራቅ ብቻ ስር የሰደደውን አለመግባባት ማስወገድ አለመቻሉን ነው። የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራኑ ጆን ኸርዝ እና ሮበርት ጄርቪስ “የደህንነት ማቅማማት” (Security Dilemma) ብለው እንደገለፁት፤ አንዱ ሀገር ራሱን ለመከላከል ብሎ የሚወስደው እርምጃ በሌላኛው ዘንድ እንደ ጥቃት አደጋ ስለሚታይ፣ የእርስ በርስ መጠራጠርና ስጋት አዙሪትን ይፈጥራል። የደህንነት ቀጠና ሠራዊቶችን አካላዊ በሆነ መንገድ ሊያራርቅ ይችላል፤ ሠራዊቶቹን ለጦርነት የሚያንቀሳቅሰውን የፖለቲካ ስጋትና ፍርሃት ግን በራሱ ሊቀርፈው አይችልም።
ይባስ ብሎ፣ ዛሬ የጦርነት ጂኦግራፊው ሥር ነቀል በሆነ መንገድ ተቀይሯል። ድሮኖች ያንን ርቀት በደቂቃዎች ያቋርጣሉ፤ የረጅም ርቀት ተወንጫፊዎች ከቀጠናው ተሻግረው ውድመት ያደርሳሉ። ሳተላይቶች፣ የሳይበር ጥቃቶችና የኤሌክትሮኒክስ አየር ላይ ውጊያዎች አንድም ወታደር ከካምፕ ሳይንቀሳቀስ ድንበር ተሻግረው አደጋ የሚያደርሱበት ዘመን ተፈጥሯል።
አካላዊ ርቀትና የመሬት አቀማመጥ አሁንም ቢሆን ዋጋ አላቸው፤ ነገር ግን ቀደም ሲል ሲያበረክቱት የነበረውን የደህንነት ዋስትና መጠን ዛሬ ሊሰጡን አይችሉም። በወታደራዊ ታሪክ ምሁሩ ኦማር ብራድሌይ አባባል እንደሚታወቀው፡ “ጄኔራሎች ሁልጊዜ ያለፈውን ጦርነት ለመዋጋት ይዘጋጃሉ”። የ21ኛውን ክፍለ ዘመን የዘመናዊ የድሮንና የሳይበር ጦርነት ሁኔታ በቅጡ ሳናገናዝብ፣ የ20ኛውን ክፍለ ዘመን የደህንነት ቀጠና አሠራር እንደገና ለመተግበር መሞከር አደገኛ የሆነ የሐሰት ደህንነት ስሜት ብቻ ነው ሊፈጥርብን የሚችለው።
ከአካላዊ ርቀት ወደ ፖለቲካዊ ጥበብ
የደህንነት ማስጠበቂያ ቀጠናን ለማቋቋም ሁለቱም መንግሥታት በቅድሚያ መስማማት አለባቸው፤ ከተስማሙም በኋላ አፈጻጸሙ ከወረቀት ውልና ከባዶ መሬት በላይ ብዙ ነገሮችን እንደሚጠይቅ ግንዛቤ ሊወሰድ ይገባል።
የከባድ መሣሪያዎች ገደብ፣ የድሮኖችንና የቅኝት በረራዎችን የሚገዙ ደንቦች፣ እንዲሁም ጥሰቶችን ለማጣራት የሚያስችሉ ግልጽ አሠራሮች ሊኖሩ ይገባል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ያለ አስተማማኝ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት፣ ዘመናዊ የቁጥጥር ሥርዓቶች እንኳ በሂደት ዋጋ ቢስ መሆናቸው አይቀሬ ነው።
ኢትዮጵያና ኤርትራ የጂኦግራፊ ተዋሳኝነታቸውን መለወጥ አይችሉም፤ ማኅበረሰቦቻቸውን የሚያጋምዱትን የኢኮኖሚ፣ የታሪክና የደም ትስስሮችም ሊሸሹ አይቻላቸውም።
የደህንነት ማስጠበቂያ ቀጠና መፍጠር ሌላ ወታደራዊ ጥፋት እንዳይከሰት ሊረዳ ይችላል። ነገር ግን ስኬቱ መለካት ያለበት በሠራዊቶች መካከል ባለው አካላዊ ርቀት ብቻ ሳይሆን፣ በድንበር ማኅበረሰቦች ደህንነት፣ በቁጥጥሩ አስተማማኝነትና ለዲፕሎማሲ በሚከፍተው ዕድል ጭምር ነው። እናም ዋናው ፈተና ሁለቱን ሠራዊቶች ማራራቅ ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም በመካከላቸው ያለው ምድር የጦር አውድማ እንዳይሆን መታደግ ነው። ለሁለቱ ሀገራት የሚበጀው እውነተኛ ትምህርትም አጥርና ካርታ በጭራሽ መልካም ጉርብትናን ሊተኩ አለመቻላቸው ነው።
ከጦርነት አዘቅት በፊት
አደራዳሪዎችና ተጽዕኖ ፈጣሪ አካላት በካርታው ላይ ሌላ የ25 ኪሎ ሜትር መስመር ለማስመር ከመነሳታቸው በፊት፣ አንድ መሠረታዊ ጥያቄ ሊጋፈጡ ይገባል።
ኢትዮጵያ የአሰብን ወደብ በጉልበት ብትይዝ እንኳ ዘላቂ ደህንነት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን አታገኝም። በሌላ በኩል፣ ኤርትራም ኢትዮጵያን የመሰለች ግዙፍ ሀገር በቀጭን የመሬት ሰርጥ ታፍና በትግዕስት ፀንታ መኖር እንደማትችል በማያሻማ ሁኔታ መገንዘብ ይኖርባታል። የባሕር በሩ ጉዳይ ፍትሐዊና “ሁለቱንም ወገን አሸናፊ በሚያደርግ” (Win-Win) መንገድ ከተፈታ ብቻ አስመራም ሆነች አዲስ አበባ ዘላቂ ሰላምና የጋራ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ይችላሉ።
ስለሆነም የሁለቱ አገራት ወዳጆችና ኃያላን — በፍቅርም ይሁን በጫና — ከጦርነቱ በፊት ውይይት እንዲጀመር ርብርብ ማድረግ ያለባቸው ነገ ሳይሆን ዛሬ ነው። መቶ ሺዎች ካለቁና ሀገር ከወደመ በኋላ በአልጀርስ ወይም በፕሪቶሪያ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ እናድራድራችሁ ውይንም እንደራደር ማለት ትርጉም የለሽ ስላቅ ነው። ጦርነት ሳይነሳ የሚደረግ የሰላም ጥረት የሰከነ አእምሮ ማሳያ ነው፤ “ከልብ ካለቀሱ እንባ አይገድም” እንዲሉ፣ ሰላምን አስቀድሞ መፈለግ ከታሪክ ውድቀት ይታደጋል።
በካርታ ላይ የሚሰመር መስመር ሠራዊቶችን ያራራቅ ይሆናል፤ ሁለቱን ሀገራትና ሕዝቦች ዘላቂ ሰላም ማጎናፀፍ የሚችለው ግን የፖለቲካ ጥበብና ዲፕሎማሲ ብቻ ነው። እናም ዋናው ጥያቄ መስመሩ የት ጋር ይሰመር የሚለው አይደለም—ሰላሙ ለማን፣ እና በማንስ መስዋዕትነት?
ዳንኤል ካሳሁን (Ph.D.)
ኢሜይል daniel.kassahun@gmail.com።
ኢትዮጵያ፦ የታሪክ ወይንስ የጂኦግራፊ እስረኛ?