ግርማ አውግቸው ደመቀ
(ጥቅምት 2019)
መግቢያ
አንድ ወዳጄ የሪፖርተር ጋዜጣን “ላልተወሰነ ግዜ መታገድ”ን የሚገልፅ ዜና ልኮልኝ ለማንበብ በቃሁ። በህዳር 2 ቀን 2026 በኢትዮጵያ ሚዲያ ባለሥልጣን (EMA) በማህበራዊ ሚዲያ ገጽ በኩል ይፋ የተደረገው ይህ ዕገዳ፤ የህትመት ውጤቱ ባለቤት በሆነው ሚዲያ ኤንድ ኮሚዩኒኬሽን ሴንተር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ላይ የብሔራዊ ደኅንነት ጥቅም እና ሌሎች ከባድ ውንጀላዎችን ጠቅሷል። እግዱ የሚከተለውን ይላል፤ “የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ሴንተር ኃ.የተ.የግል ማህበር (ሪፖርተር አማርኛ፣ ዘሪፖርተር እንግሊዝኛ ጋዜጣ እና የኦንላይን ስርጭቱ) የህግና የሙያ ስነ ምግባር ግዴታዎችን ተሟልተዉ ተግባራዊ እስኪደረጉ ድረስ የምዝገባ ምስክር ወረቀቱ ከሰኞ ጥቅምት 23/2019 ዓ/ም ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ ከህትመትና ከስርጭት ሙሉ በሙሉ ታግዶ እንዲቆይ የተወሰነ በመሆኑ ይሔው ተግባራዊ እንዲደረግ ባለስልጣኑ በጥብቅ ያሳስባል።” እንዲህ ያለ ውሳኔ በሪፖርተር ላይ ይደረሳል ብዬ አልጠበቅኩም ነበርና አዘንኩ። ከጥቂት ቀናት በኋላም—ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን እና ኢትዮጵያን ኢንሳይደርን ጨምሮ—የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የጉዳዩ ባለቤት ነኝ የሚል የመንግሥት ተወካይ ሰጠ የተባለውን ማብራሪያ የዘገቡትን ለማንበብ በቃሁ። ከመታገዱም ጀርባ የተሰጠው ይኸው ማብራርያ መሰል ገለፃ የበለጠ የሚያሳስብ ሆኖ አገኘሁት።
ሪፖርተር የደረጀ ተቋም ነው። በሁለት ቋንቋ በሳምንት ሁለቴ ሳይዛነፍ የሚታታሙ ሁለት ጋዜጦች አሉት። ለረጅም ዓመታት እንደሪፖርተር በስራ ላይ የቆየ የግል ሚዲያ በኢትዮጵያ ኖሮ አያውቅም። ሪፕርተር እንደ አሸን ከፈሉት የዩቱብ ቻናሎች ዛሬ ቢዘጋ ነገ ምንም ጉዳት ሳይደርስበት ስሙን ቀይሮ ይመጣል የሚባል አይደለም። ይህ በወያኔ ግዜ በየቀኑ በሚባል ደረጃ ዛሬ ተከፍተው ነገ የሚዘጉ፣ እንደገና ስማቸውን ለውጠውም ሆነ ሳይለውጡ እንደሚከፈቱት ጋዜጦችም የሚወሰድ አይደለም። ሪፖርተር ባለቤት ያለው የግል ንግድ ተቋም ቢሆንም፣ እንደእኔ እምነት የሀገር ሀብት ነው። የሀገር ሀብት ደግሞ ሀብቱን በሚጠብቀው አካል ጉዳት ሊደርስበት አይገባም። በዚህ ፅሁፍ ለምን ሪፖርተር የተለየ ትኩረት የአቢይ መንግሥት ሰጥቶት ወደነበረበት ጊዜ ሳያልፍ መመለስ እንደሚገባው አስተያየቴን አሰፍራለሁ።
ሪፖርተር እንደ ብሄራዊ ጋዜጣ
ሪፖርተር የሀገር ሀብት ነው ስል፣ ባለቤቱን አማረ አረጋዊን ዘንግቼ አይደለም። አቶ አማረ ይህን ጋዜጣ ታላቅ ተቋም ለማድረግ የከፈሉትን መስዋእትነት ወይም ያለፉበትን ውጣ ውረድ በቅርበት የማውቀም የለምና ስለሱ የምለው የለኝም። ይልቁንም፣ አቶ አማረ የወያኔ ሰው ነበሩና በተለይ ከመነሻው ወገንተኝነታቸው በየእትሙ ይታይ ነበር። ሌሎች ጋዜጦች በሚውተረተሩበት ሰዓት በግዳጅ ይመስል በእያንዳንዱ የመንግሥት መስሪያቤት/ቢሮ በህዝብ ሀብት እየተገዛ የሚገባው—ካልተሳሳትኩ—ብቸኛው የግል ጋዜጣ ነበር። በእርግጥ፣ በአንዳንድ መስሪያ ቤቶች ሌሎች የግል ጋዜጦች በተወሰነ ደረጃ ሊኖሩ ይችላሉ። እንደሪፖርተር ግን በመላ ሀገሪቱ የዚያን አይነት እድል ያገኘ እስከማውቀው ድረስ ሌላ ጋዜጣ አልነበረም። የዚህ አይነት እድል ያላቸው—አግባብነቱን የማንጠይቀው—የመንግሥት ጋዜጦች ናቸው። ከዚህም በላይ፣ ከማናቸውም ጋዜጣ የተለየ ጥራትም ሆነ እውቅና ባልነበረው ሰዓት፣ ሌላው ጋዜጣ አንዲት ማስታወቂያ ለማግኘት በሚቸገርበት ወቅት፣ ሪፖርተር ከሸክም የሚከብድ ሆኖ በሀያ እና ሰላሳ ገፅ ማስታወቂያ ታጅቦ ይወጣ ነበር።
ይሁን እንጅ ሪፖርተር ሁሌም ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖለት እዚህ የደረሰ አይደለም። ጨርሶውንም እንዲያከትሙ ከተፈረደባቸው ከጅምራቸው ጠንካራ የነበሩ ሚዲያዎች ተርታ ባይመደብም፣ ሪፖርተርም በተለይ ወደኋለኛው የወያኔ ዘመነ መንግሥት ባለቤቱን ጨምሮ የራሱን ዋጋም ከፍሏል። ቁም ነግሩ ግን ያ አይደለም። አሁን የደረሰበት ነው። በዚያ የመንግሥት ድጋፍ ባልተለየውም ወቅትም ሆነ አሁን በደረሰበት፣ ሪፖርተር በይዘት ስፋቱ እና ጥራቱ ላይ ጥያቄ የሚነሳበት አይደለም። በወገንተኝነቱ በሚፈረጅበትም ወቅት እንኳ ሪፖርተር ሚዛናዊ ለመሆን የሚጥር ከምሆኑም በላይ ማህብረሰብ አስተማሪና አንቂ የሆኑ ከፖለቲካው ራቅ ብለው ለሚፃፉ የስነ–ጽሑፍ፣ የስነ–ጥበብ፣ እና የባህል ሥራዎች መድረክ ነበር። በሁለቱም ቋንቋ በሚወጡት ጋዜጦች የህዝብ የውይይት መድረክ የሆኑ በርካታ አምዶች ያደረጉት አስተዋፆ በቀላሉ የሚካድ አይደለም።
ቀጥተኛ እና ኢቀጥተኛ የመንግሥት ድጋፍ ተደርጎለትም ሆነ ሳይደረግለት ሪፖርተር ላለፉትት ሰልሳ ዓመታት ያህል ሳያቋርጥ ደረጃውን እና ጥራቱን ጠብቆ የመረጃ ምንጭ ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል። ጨርሶውን በየትኛውም መስፈርት ብንመዝነው ከማናቸውም ታዋቂ የዓለም ጋዜጦች ተርታ ሊቀመጥ የሚያስችለው ደረጃም ላይ ደርሷል። ይህን ያህል ስም ባገኘበት እና ጥራት ባጎለበት ሰዓት ሪፖርተርን መዝጋቱ ማንን ነው የሚጎዳው ብለን መጠየቅ ከዜጋው ሳይሆን ቅድሚያ የሚሰጠው ይህን የመዝጋት ውሳኔ ካሳለፈው የመንግሥት አካል መሆን ነበረበት።
ተቋም መገንባት ቀላል ነገር አይደለም። በህትመት ያለ ሰው አንድ ጋዜጣ እንኳን ማውጣት ምን ያህል ጥረትና የበርካታ ባለሙያ ርብርብ እንደሚያስፈልግ ያውቀዋል። በሪፖርተር ደረጃ የተደራጀ እና ጥራት የጠበቀ ጋዜጣ ማውጣት ደግሞ አስተዳደራዊ ብቻ ሳይሆን፣ ሙያዊ ብቃት፣ እንዲሁም የስራ ቅልጥፍናን የሚያኪያሂድ ቢሮክራሲ መዘርጋትን ይጠይቃል። አቶ አማረ በፊትም ሆነ አሁን ባላቸው የፖለቲካ አቋም የማንስማማ ብንኖርም፣ አንድ ነገር ግን መካድ አይቻልም። ይህን የመሰለ ተቋም ለመንገባት የሚጠይቀውን ጥረት ብቻ ሳይሆን፣ የሚያስፈልገውን ሙያዊ ብስለት እና የአስተዳደር ችሎታ አቶ አማረ እንዳላቸው መገመት አያዳግትም።
ሪፖርተር በእርግጥ ከግለሰብም በላይ ነው። አሁን ለደረሰበት ደረጃ ሙያዊ ብቃት ያላቸው አርታዒዎቹ እና ሌሎች ሰራተኞቹ፣ አምደኞች፣ አጠቃላይ አንባቢው እና ሌሎች ባለድርሻዎች ሪፖርተር እንደተቋም እዚህ እንዲደርስ ያደረጉት አስተዋጽዖ በቀላሉ ወደጎን ሊባል አይችልም። ለዚም ነው ሪፖርተር ሀገራዊ ተቋም ነው የምንለው።
የተደራጀ ተቋም አስፈላጊነት
እንደሪፖርተር ያሉ ጋዜጦች/ተቋሞች መንግሥት ሊዘጋቸው ሳይሆን ድጋፍ ሊያደርግላቸው የሚገቡ ናቸው። ይህን የምለው ሪፖርተር በሚያወጣቸው ፅሁፎች መንግሥት አላስቀየመም ወይም አስቀይሟል በሚል ፍረጃ ውስጥ ገብቼ አይደለም። ያን ለማድረግ በጥንቃቄ በየጊዜው የወጡትን ስራዎች መገምገም ያስፈልጋል። ይህ ሰፊ ግዜ የሚጠይቅ ጥናት ያስፈለገዋል። ወደአንድ ፖለቲካ አመለካከት ማዝመም ደግሞ የአጠቃላይ ሚዲያዎች ባህሪ ነው ማለት ይቻላል። ለምሳሌ የኒው ዮርኩ ታይምስ ወደግራ ያዘመመ ሲሆን፣ ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል ደግሞ በቀኝ ዘመምነት ይፈረጃል። እነዚህ ጋዜጦች ግን በየትኛውም መስፈርት አስተማሪነታቸው፣ የፖለቲካ አካሂድ ጠቋሚነታቸው፣ ለመንግሥት የህዝብን ብሶት እና አመለካከት የሚያንፀባርቁ መሆናቸው የሚካድ አይደለም።
ሪፖርተር እንደተቋም አሁን የደረሰበትን ላለማድነቅ አይቻልም። ሪፖርተር እጅግ የተደራጀ ምናልባት እንደሀገር እራሱ ኢትዮጵያ ልትኮራበት የሚችል ትልቅ ሀገራዊ ተቋም ነው። አሁን ባለንበት ዘመን በሪፖርተር ደርጃ ኢትዮጵያ አለኝ የምትለው ጋዜጣ አለ ወይ ብለን እራሳችንን እንጠይቅ። ህብረተሰብን ከማስተማር፣ ለመንግሥት አጋዥ የፖሊሲ ማስተካካያ፣ ማረሚያ፣ እና ጠቋሚ ከመሆን አንፃር የሪፖርተርን ያህል በአሁኑ ግዜ ያለ አይመስለኝም። እንደዚህ አይነት ሚዲያ ወገንተኝነት የበዛበት ወይም ማህብረሰብን እና ሀገርን የሚጎዱ ፅሁፍች ቢሰራጭበት እንኳ በመመካከር እንዲታረም ይደርጋል እንጅ ማገድ አማራጭ አይደለም። ከታገድም ስህተትን አርሞ ወዲያው እንዲከፈት ከማድረግ ይልቅ፣ ማንንም ሊያሳምን የማይችል ደረጃውን ያልጠበቀ ማብራሪያ ማቅረብም ከመንግሥት አይጠበቅም።
ሚዲያ የህዝብ አፍ ነው። ልብ ያለው መንግሥት ህዝብን ለማስተዳደር ትልቅ ግብዓት የሚሆነው ሚዲያው ነው። የመንግሥት ያልሆኑ ሚዲያዎች ብዛት ብቻ ሳይሆን ጥራታቸው እና ተቋማዊ ብቃታቸው የሰከነ መንግስት እና ሀገር መኖሩንም ማሳያ ናቸው። ጋዜጣም ከተፈጠረ ጀምሮ ያለውን ይህ ነው የማይባል ትልቅ አስተዋፆ ለማወቅ ሊቅ መሆን አያስፈልግም። ዛሬ ዓለማችን ዲሞክራሲ እና ፍትህ በከፍተኛ ደረጃ የሚለካበት ዋንኛው በሚዲያው አማካይነት ነው። ጋዜጣ/ሚዲያ መፈጠሩ እና መኖሩ ሳይሆን ተቋማዊ ብቃቱ ነው ታላቅነቱን የሚገልፀው።
ማጠቃለያ
ሪፖርተር የሀገር ሀብት ነው። የኢትዮጵያም ኩራት ነው። መንግሥት ሊዘጋው ሳይሆን ምናልባት ጣልቃ መግባት ከተገባው ማድረግ ያለበት—ሁላችንም ሀላፊ ነን እና ባለቤቱ ካለፈ—ቀጣይነት እንዲኖረው ከባለቤቱ ጋር መምከር ነው። አቶ አማረ እዚህ አድረሰውታል፣ እስካሉ ድረስ እያገዙ በተቋምነቱ ጥራቱን እንደጠበቀ እንዲቀጥል ማድረግ፣ ሲያልፉም ሳይቋረጥ ሊቀጥልበት የሚችልበትን መንገድ፣ እስካሁን ካልታሰበበት፣ ማሰብ ይገባል። በዛሬው ግዜ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይህን በዓለም ላይ የጋዜጣ እና የመጽሐፍ አስታሚዎች በአመዛኙ በዲጂታል ሕትመት ምክንያት ታላቅ ፈተና ገጥሟቸዋል። በርካቶችም ከገበያው ውጭ ሆነዋል። መንግሥትን ሊያሳስበው የሚገባው ይህ ጉዳይ መሆን አለበት። በጉዳዩ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ የሪፖርተር ጋዜጣ ወደነበረበት ግዜ ሳይወስድ መመለስ ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎች በጋዜጣም ሆነ በመጽሐፍ ሆነ ህትመት ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች የሚታገዙበትን መላ መፈለግ ነው።
ሚዲያ በቀጥታ የሚጠቅመው ከህብረተሰብ እኩል ማለት ይቻላል መንግሥትን ነው። አለ ጠንካራ እና ሚዛናዊ ሚዲያ የሰከነ/ፍትሀዊ መንግሥት አለ ማለት ይከብዳል። ይህን መንግሥት ማለቴ ብቻ አይደለም። ማንኛውንም መንግሥትንም ማለቴ ነው። ለዛሬው ብቻ ሳይሆን ለመጭው መንግሥት እና ትውልድ ይህን ተቋም እንዲቀጥል በፅኑ ቢታሰብበት መልካም ነው። ተመልሶ ቢከፈት እንኳን፣ ታግዶ መቆየቱ እንደገና ለማንሰራራት ለሪፖርተር ሊከብደው ይችላል። በመክፈት ውሳኔ ላይ መንግሥት ግዜ አያጥፋ።
ከመንግስት ቸር ወሬ ያሰማን!