ለዚህ ቅሬታ መነሻ የሆነኝ የአእምሯዊ ንብረት ጥበቃ ባለስልጣን የሚባል መንግስታዊ ተቋም ሲሆን ከረጅም ዓመታት ጀምሮ አልፎ አልፎ በመሄድ የድርሰት ሥራዎቼን አስመዘግባለሁ፡፡ በቅርቡ አገልግሎት ለማግኘት ወደ ተቋሙ ስሄድ ተቋሙ አዲስ የህንጻ ግንባታ እያከናወነ እንደሆነና ከጎኑ ወደሚገኝ ሌላ ህንጻ በኪራይ እንደተዘዋወረ ተነገረኝ፡፡ ወደ ተከራየው ህንጻ ስሄድ ህንጻው በመገንባት ላይ ያለ ከግንባታ ድምጾች እና ብክለት ያልጸዳ በተጨማሪም ሊፍት የሌለው እና አራተኛ ፎቅ ድረስ በእግር መውጣትና መውረድ የሚጠይቅ ነው፡፡የተገልጋዮች መዝገብ ቤት የሚገኘው በቀድሞው ጊቢ ውስጥ በፈረሰ ሕንጻ በጀርባ በር ወጥቶለት ሲሆን ለተገልጋዩ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው መዛግብት እና ማስረጃዎች ቀርቶ ጥቅም ላይ የማይውሉ ንብረቶች ሊቀመጡበት የማይገባ በግንባታ ህንጻ አቧራ ሽታና እርጥበት ተጋልጦ ተቀምጧል፡፡ የበለጠ የሚያሳዝነው የመዝገብ ቤቱ ሠራተኞች ጨለማ በሆነ ለከፍተኛ የግንባታ ብናኝና ሽታ ተጋልጠው በፈረሰ ህንጻ ስር እንደ ምርኮኛ የዕለት ተዕለት ሥራቸውን ያከናውናሉ ፡፡ተገልጋዩም መዝገብ ቤት የሚያስኬድ ሁኔታ ሲያጋጥመው አራት ፎቅ ወርዶ ወደ ቀድሞ የተቋሙ ጊቢ ፤ በዚህ ዘመን ለ የመንግስት ሠራተኞች ይገኙበታል ተብሎ የማይታሰብ “ መዝገብ ቤት” መሄድ ግዴታው ይሆናል፡፡
ሌላው ዋና ጉዳይ የዘመኑ ኦንላይን አገልግሎት በመርህ ደረጃ የተገልጋዩን ጊዜ ፣ ገንዘብ የሚቆጥብና እንግልትን የሚቀንስ እና ፈጣን አገልግሎትን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ የአእምሯዊ ንብረት ጥበቃ ባለስልጣን የኦንላየን አገልግሎት ጀምሯል በአካል መምጣት ሳያስፈልግ በኦንላይን አገልግሎት ማግኘት ይቻላል የሚል ፕሮፓጋንዳ ብሰማም ያየሁት የተገላቢጦሹን ነው፡፡
ከተወሰነ ጊዜ በፊት መጽሀፍ ለማስመዝገብና የኮፒራይት ሰርተፊኬት ለማግኘት በሄድኩበት ጊዜ የማመልከቻ ፎርም በጽሁፍ እንድሞላ ይዜ የመጣሁትን ሥራ በሀርድ እና በሶፍት ኮፒ እንዳቀርብ ተጠይቄ በማቅረብ በአፋጣኝ ሰርተፊኬቱን ማግኘት ችያለሁ፡፡ አሁን ግን “ኦንላየን” በተባለው ማመልከቻ እንድሞላ ከተደረግሁ በኋላ በተጨማሪ ድሮ የሞላሁትን ፎርም መሙላት እንዳለብኝ ተነገረኝ ፡፡ ይህ አሰራር በዚህ ዘመን ተቀባነት የሌለው እና ቀድሞ የነበረው አሰራር እንዳለ ሁኖ ተጨማሪ ድካም ካለው ምኑን ሲስተም ሆነ ፤ አራት ፎቅ በድካም የወጣን ደንበኛ እንዳይመለስ አድርጎ ማንገላታት መሆኑን ብገልጽም ማንም ሊረዳው የማይችልና አሁን ከፈለግሁት አገልግሎት ጋር የማገይገናኝ ምላሽ ተሰጥቶኛል ፡፡በተመሳሳይ የድርጅት ሎጎ ሊያስመዘግቡ የሚሞክሩ ባለጉዳዮች ኦንላየን ከተመዘገቡ በኋላ የውስጥ ሠራተኞች ያመለከቱትን ማመልከቻ ወደ ሌላ ሲስሰተም እንዲገለብጡ እንደሚደረግ ታዝቤያለሁ፡፡ አሁን ኦንላየን አገልግሎት እየሰጠ ነው የተባለው ሲስተም በቀጥታ ተቋሙ ወደ ሚጠቀምበት ዳታቤዝ በቀጥታ እንዲገባ ማድረግ የማይችል ነው ፡፡ የመብት መቀዳደም እንዳይኖር እና ሥራው ውሀ ቅዳ ውሃ መልስ መሆኑን ቅሬታቸውን ያቀረቡ ባለመብቶች “ጥቅማቸው የተነካ ደላሎች” የሚል ስም በመስጠት እንዲሸማቀቁ እንደሚደረግም የተቋሙ የዘወትር ደንበኞች ይናገራሉ ፡፡መብቱን ገፍቶ ለሚጠይቅ ባለጉዳይም ከጠየቀው ፈጣን አገልግሎት ጋር የማይገናኝና እነሱም ያልገባቸውን የማደናገሪያና የማጭበርበሪያ ምላሽ እንደሚሰጡ በተመላለስኩባቸው ወቅቶች መገንዘብ ችያለሁ፡፡ሁሉም እንደሚያውቀው አሁን ሲስተም ብለው ያቀረቡት አደናጋሪ ሲስተም ሪፖርት የሚቀርብላቸው ሌላ ተቋም ላይ ያሉ የመንግስት የበላይ ኃላፊዎች ተገልጋይ ሆነው እስከመጨረሻው ስለማይመለከቱና ስለማያጣሩ ተቋሙ ዘመናዊ ሲስተም ይጠቀማል የሚል የተሳሰተ መረጃ ይይዛሉ፡፡
አንድ የመንግስት ተቋም የሚቋቋመው ለተገልጋዩ ማህበረሰብ በተሰጠው ኃላፊነት እንዲያገለግል ለአገር እደገትም አስተዋጽኦ እንዲደርግ ቢሆንም ፡፡ በሕንጻ ግንባታ ሰበብ አሁን የሚመጣን ተገልጋይ ማንገላታት ፣ሠራተኞችን ለአደጋ እና ለቋሚ ጉዳት ማጋለጥ፣ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን የተገልጋ መዛግብት እና ማስረጃ በምንቸገረኝ በጉሮኖ ውስጥ መጣል ጥቅማ ጥቅም ተከብሮለት መንግስት ካስቀመጠው ሹመኛ ቀርቶ ህሊና ካለው ተራ ዜጋ እንኳ አይጠበቅም፡፡ ከተቋሙ ውሳኔ ሰጪዎች ድርጊት እንደተረዳሁት ይህ አዲስ ህንጻ የሚገነባው ለተገልጋይ እና ለሠራተኞች በማሰብ ሳይሆን በአዲስ ህንጻ ግንባታ ስም የምትገኝ ጥቅም ወይም በአከራይ ተከራይ መካከል የምትገኝ ጥቅም ወይም ከተገልጋይ እና ከሠራተኛ የተሻለ የሥራ ቦታ ከመፍጠር ጋር የማይገናኝ ሌላ አይነት ጥቅም እንዳለ በማስላት የሚሰራ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡
መንግስት ዲጂታል ኢትዮጵያ በሚል መርሀ ግብር መንግስታዊ አገልግሎቶችን ቀልጣፋ ለማድረግ የጀመረው እንቅስቃሴ ተገልጋዩ በሙሉ የሚደግፈው ቢሆንም እንደ አእምሯዊ ንብረት ጥበቃ ባለስልጣን ያሉ ተቋማት ሲስተም ይጠቀማሉ ለመባልና በአግባቡ ተቋማት ድረስ መጥተው በማያዩ በመንግስት የበላይ ሹመኞች ዘንድ ርካሽ እና የውሸት ተቋማዊ ምስል ለመፍጠር ፣ የሀሰት ሪፖርት በማቅረብ መንግስትን ያታልላሉ፡፡ ሲስተም በሚሉት ማደናገሪያ አገልግሎት ማቀላጠፍ ቀርቶ ያልነበረ እንግልትና ስቃይ በተገልጋይ እና በሠራተኞች ላይ ይጭናሉ፡፡በዚህ ብቻ አያበቃም መብታቸውን የሚጠይቁ ተገልጋዮች የመንግስት ፕሮግራም ተቀዋሚና አጭበርባሪ በሚል ማሸማቀቂያ ተግባራቸው እንዲሸፈን ያደርጋሉ፡: ሹመኞቹ ዋነኛ ዓላማቸው እስከቻሉት ድረስ መንግስትንና ተገልጋዩን በማታለል የራሳቸው ምቾት ጥቅም ማረጋገጥ ነው፡፡ የመንግስት ተቋም ለሹመኞች መጠቀሚያ የተሰጣቸው ርስት እንጂ የህዝብ አገልጋዮች መሆናቸውን የሚያመለክት ምንም ተግባር የለም ፡፡ ተገልጋይ አማራጭ በማጣት ወደ ተቋም ይሄዳል እንጂ መገልገል መብቱ መሆኑን የሚያውቅበት መንገድ የለም፡፡ በሹመኞቹ አስከፊ ተግባራት ተገልጋይ በመንግስት ላይ እምነት እያጣ ይመጣል፡፡ በመሆኑም የአእምሯዊ ንብረት ጥበቃ ባለስልጣን የመንግስት ተቋም ከሆነ እና የበላይ ተቆጣጣሪ አካል ካለ እየተበደለ ያለው ተገልጋይ ብቻ ሳይሆን መንግስትም ጭምር በመሆኑ ጉዳዩ ላይ ላዩን ብቻ ሳይሆን በሚገባ ተጠንቶ ጥብቅ ርምጃ መወሰድ አለበት፡፡
ታዛቢ ነጋ አስመላሽ