በበላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)
እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር ከ1933 እስከ 1945 ዓ.ም ሂትለር ከስድስት ሚሊዮን አይሁዳውያን በላይ መጨፍጨፉ የሚታወቅ ነው፡፡ የሚገርመው ነገር በዚህ ጭፍጨፋ ወቅት ተገደው ሳይሆን በውድ የጭፍጨፋው ምክንያት ራሳቸው አይሁዳውያን እንጅ ሂትለር የሚመራው የናዚ ፓርቲ እንዳልነበረ በቃልም በጽሑፍም የሚያሽቃብጡ የአይሁድ ምሁራን ነበሩ፡፡ ከእነዚህም ምሁራን ውስጥም ማቅስ ናውማን እና አልፍሬድ ፔይሰር የሚባሉት በምሳሌነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ [1-3]
ማቅስ ናውማን የታወቀ የሕግ ባለሙያ አልፍሬድ ፔይሰርም የታወቀ ሐኪም ነበር፡፡ ሂትለር ዘራቸውን እየለዬ አይሁዳንን ሲጨፈጭፍ፣ ከቤት ንብረታቸው ሲያፈናቅል፣ የትምህርት እድልንና የመንግስትም ሆነ የግል ሥራ እድል ሲነሳ ክናዚ ካድሬዎች ጋር ሆነው “ጥፋተኞች ለናዚ ፓርቲ ታማኝ ያልሆኑ አይሁዳውያን ናቸው” እያሉ ይሰብኩ ነበር፡፡ አይሁዳውያን ከጭፍጨፋም ሆነ ከሌላው እንግልት የሚድኑት ለናዚዎች ሰጥ ለጥ ብለው በመገዛትና ታማኝት በማሳየት ብቻ ነው እያሉ ያሽቃብጡ ነበር፡፡ [1]
እነዚህ በቀለም ትምህርት እጅጉን የላቁት ሊቃውንት እንደዚህ እያሉ የሰበኩት ዘርን እየለየ ለማጣፍት የመጣ እሳት በልመናና ለጥ ገጥ ብሎ በመገዛት እንደማይጠፋ ለመገንዘብ ተስኗቸው ሳይሆን የሂትለርን እግር በመሳምና የሕዝባቸውን ሥጋ በመብላትና ደሙንም በመጠጣት የራሳቸውን ምቾት ለመጠበቅ ነበር፡፡ ዳሩ ግን ማሽቃበጥ ብዙም ስለማያራምድና ስለማያዛልቅ ሂትለር በ1935 ዓ.ም. የኑሬምበርግ ሕግ እየተባለ የሚጠራውን ዘረኛ ሕግ ሲያጸድቅ አሽቃባጮቹ ማቅስና አልፍሬድም እንደማኛውም አይሁድ የጀርመን ዜግነታቸውን ተነጠቁ፡፡ የራሱን ወገን የከዳን እንኳን ሂትለር ማንም ስለማያምን ብዙም ሳይቆዩ የናዚ ፓርቲ ሰለባም ሆኑ፡፡ አሽቃባጩን ማቅስ ናውማንን ናዚ ወህኒ ቤት ሲወረውረው እጁን በመነጸሩ ብርጭቆ በመገዝገዝ ራሱን ለማጥፋት ሞከረ፡፡ የማቅስ ናውማንን እጣ ፈንታ ያየው አልፍሬድ ፔይሰር ደሞ ወደ ስዊድን ሽምጥ ፈረጠጠ፡፡[1]
በተመሳሳይ መንገድ ክ፲፱፹፫ ዓ.ም ጀምሮ በፈረንጅና በአረቦች ትከሻ ተወንበር ቁጢጥ ያሉ የዘር “ነፃ አውጭ” ግንባሮች እየተተካኩ በሚሊዮኖች የሚገመት አማራ በተለያዬ መንገድ ጨፈጨፉ፡፡ በመላ አገሪቱ አማራን እያሰሩ ሲያንገላቱ፣ ሲያመክኑ፣ ከቤትና ንብረቱ ሲያፈናቅሉ፣ የሥራና የትምህርት እድል ሲነሱ ከሀዲ የአማራ ምሁራንና ሌሎችም የተፈጥሮና የተሞክሮ እውቀት ማይማን “ነፍጠኛው አማራ ከእልቂት የሚድነው ላልመከረበት ሕገ መንግስት ለጥ ገጥ ብሎ ሲገዛ ነው እያሉ በቀጠጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ለአማራ ዘር አጥፊዎች በማሽቃበጥ እንጀራቸውን መጋገር ጀመሩ፡፡ እነ ክፍሌ ወዳጆ፣ እንድርያስ እሸቴና ሌሎችም ዲግሪ ጫኝ ምሁራን ተብዮች ታሪክ የማይዘነጋቸው የአማራ ማቅስ ናውማንና አልፍሬድ ፔይሰር ሆነው አረፉ፡፡ ጌቶቻቸው የማይፈልጉትን እንክርዳድ ለመቃም “የአማራን ቋንጃ እንሰብራለን!” እያሉ በአደባባይ ሲደነፉ የኖሩ ሂትለሮችን ለማገልገል የጋማ ከብቱን ብአዴንን በገመድ ሲጎትቱ የኖሩት እንደ ስኳር ላሹ ታምራት ላይኔ፣ አዲሱ ለገሰ፣ አያሌው ጎበዜና በእነሱ ዱካ እየተተኩ እስካሁን ድረስ የአማራን ዘር አጥፊዎች በማገልገል ያሉት ከሀዲዎች ሂትለር እንደ አገዳ መጦ የወረወራቸውን ማቅስ ናውማንና አልፍሬድ ፔይሰር አስንቀው ቁጭ አሉ፡፡
አልፍሬድ ፔይሰር በዚች ምድር የኖረው 84 ዓመታት ሲሆን ማቅስ ናውማን ደሞ 64 ዓመታት ብቻ ነው፡፡ [1] ክህደታቸው ግን እስክ ዳግም ምጣት ስለማይረሳ ይኸው ዛሬ ከብዙ አስርተ ዓመታት በኋላ እንዳነሳነው ከሺህ ዓመታት በኋላም በተከታታይ ትውልዶች የሚነሳ ነው፡፡ በምድር ለሚቆዩባት ለዚች ብናኝ ዘመን ጎምዥተው “የአማራን ቋንጃ ልንሰብር መጣን” እያሉ የሚደነፉትን ሂትለሮች ያገለገሉና በማገልገል ላይ ያሉ ከሀዲ አማራዎች ታሪክም እንደ ማቅስ ናውማንና አልፍሬድ ፔይሰር አሳፋሪ ታሪክ እስከ ዳግም ምጣት ሲነሳ ሲጣል የሚኖር ነው፡፡ ከሁሉ ከሁሉ መጠንቀቅ ለልጅልጅና ለዘር ማንዘር ከሚተርፍ ከእንደዚህ ዓይነቱ አሸማቃቂና አዋራጅ ተግባር ነው፡፡ አመሰግናለሁ፡፡
ዋቢ
- The Jews who voted for Hitler by Timothy W. Ryback, The Atlantic October, 2026 page 18-22
- Max Naumann Still Loyal to Nazi Oppressors of His Race; Hits Zionists and Eastern Jews, https://www.jta.org/archive/dr-max-naumann-still-loyal-to-nazi-oppressors-of-his-race-hits-zionists-and-eastern-jews
- Hitlers Enables Include Conservative German Jews https://momentmag.com/hitlers-enablers-included-conservative-german-jews/?srsltid=AU7gw4WFfr0xEyg9PUEi6AWK4O2CE5u6vmFu9GFMJAWJ6LU1bzH1yBEH
መስከረም ሁለት ሺ አስራ ዘጠኝ ዓ.ም.