ጋብቻ አንድ ወላጅ እጅግ ከሚደሰትበት ጊዜ ዋነኛው ነው።ተራው ሰው ልጁን የሚያገባው ከእሱ እንዳይርቅ ይፈልጋል።ለምን የልጁን የጋብቻ ሁኔታ በቅርቡ መከታተል ይፈልጋል።የኢኮኖሚውን ሁኔታ ያጠራል። የቤተሰቡን ማንነት ያጠናል። ከዛ ለጋብቻው ፈቃደኝነቱን ይገልፃል።ንጉስ ልጁን ሲድርስ ፣የፖለቲካውን ሁኔታ ይቃኛል፤የሚድርለትን ሰው ማንነት ይመረምራል፤ከዛ ይድራል።
የንጉስ ልጅ መሆን ሁሉም የሚመኘው ነው፤ግን ችግርም አለው። ለፖለቲካው ሲባል ልጆች ይሸጣሉ። ከወላጆቻቸው ርቀው ይሄዳሉ፤ቋንቋውን ከማያውቁት ሰው ጋር ይኖራሉ። አንዳንዶቹም እንደውም በሀይማኖት ከሚለዩት ሰው ጋር ለመኖር ይገደዳሉ። እንዲህ አይነቱ ሁኔታ ከገጠማቸው አንዷ የጅማ አባ ጂፋር 11 ልጅ ናት።
ጅማ አባ ጂፋር 11 የካዎ ጦና ሀይል ተረድተዋል፤እስካሁን ማንም ሊቋቋመው፣ ሊመክተው የቻለ የለም። ይህን ልጅ በጋብቻ ቢይዙት የተሻለ መሆኑን ተረድተዋል። ከፋ ፣ወላይታ፣የእሳቸው ጅማ ያካባቢው ሀያል መንግስታት ናቸው። ሶስቱ ሀይሎች አንድነት ከፈጠሩ በአካባቢው ያለውን የባርያ ንግድ መቆጣጠር ይችላሉ። ከተዋጉ ፣ግጭት ከፈጠሩ ግን ስርዓቱ እንዳለ ይፈርሳል። ጅማ አባ ጅፋር በሰላም ፖለቲካውን ማሸነፍ እንደሚቻል አሳይተዋል። የሁለቱም ቋንቋ የተለያየ ኦሮምኛና ወላይትኛ ነው።ሀይማኖትም እስልምናና ልማዳዊ እምነት ነው። የካዎ ጦና የመጀመርያ ሚስቱ የዳውሮ ንጉስ ልጅ ናት። ንጉስ ብዙ ሚስት ማግባቱ የተለመደ ነው። ሰርጋቸው የሚገርም ሆነ። በደቡብ ከታዩ ሰርጎች እጅግ ደማቁና የእነሱን ታላቅነትና ሀይል ያሳየ ነበር።
ጅማ አባ ጅፋር ልጃቸው ለሚገጥማት ችግር፣ የዘየዱት በሺ የሚገመቱ ሰዎች አብረው መላክ ነው። ሼሆች ፣ሴት አገልጋዮች፣ባለሙያዎች ፣አጫዋቾች፣ባሮች ይገኙበታል።በሰው ሀገር ብቻዋን ለሆነች ልጅ ለንጉስ ልጅ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ናቸው። የነዚህ በወላይታ የሚገኙ ብቸኛው የእስልምና ሀይማኖት ተከታዮች ናቸው። የአፍ መፍቻ ቋንቋቸውን ኦሮምኛን እርስተውታል። የሚግባቡት በወላይትኛ ነው።መነሻቸው ጅማ መሆኑን አትርሱ።
ታሪኩ የተፈፀመው የዛሬ 145 ዐመት አካባቢ ነው። በስድስት ትውልድ ውስጥ እንዴት ቋንቋው ጠፋ። ከጅማ እንደመጡ የሚገልፁት የእስልምና ተከታዮች ናቸው። ቋንቋቸው ቢጠፋም ሀይማኖታቸው አልጠፋም። ምርምር ሊያደርግ የፈለገ ካለ ፣ያሉት ቦዲቲ ከተማ አጠገብ ነው ። የጋብቻ ስርዓታቸው እንዴት ያለ ነው? በወላይታ ጎሳ የራሱን ጎሳ አያገባም፤ጋብቻቸውን ማጥናት ያስፈልጋል። ብዙ የሚጠኑ ነገሮች ይኖራቸዋል። እንዲህ አይነቱ ጋብቻ በተለያዩ የሀገራችን አካባቢ ይገኛሉ። ከሌላ አካባቢ የመጣን ነን የሚሉ ይኖራሉ?
ካዎ ጦና ለጥሎሽ ብዙ ሺ ባሮች መስጠቱ አይቀርም። እነዚህን ደግሞ ጅማ አካባቢ ማግኘት ይቻላል? ቋንቋቸው ጠፍቷል፤እስልምናን ተቀብለዋል። የወላይታን ፍንጭ የሚያመላክቱ ሰዎች ይገኙ ይሆን? ምርምር ማካሄድ ለዚህ መድሃኒቱ ነው።
* * *
ጅማ አባ ጅፋር ሚኒሊክ እንዲገብሩላቸው ጠየቋቸው። ለስብሰባ ተቀመጡ። በጣም የሚያከብሩዋቸው ወሎዬዎችም በስብሰባው ተጠርተዋል። በጅማ እስልምናን ተገቢውን ምሁራዊ ስፍራውን እንዲይዝ ያደረጉት ወሎዎች ከሀገራቸው ያባረራቸውን መንግስት ላይ የሚሰጡትን አስተያየት ለማድመጥ ጎግተዋል። ወሎዬዎቹ ‘’ሚኒሊክ ሀይማኖቱን በተመለከተ ችግር የለበትም፤የተናገሩት ሁሉ እውነት ነው። እኛ እዚህ በሳቸው ደግነት ነው የደረስን። እኛን የበደለን ዮሐንስ የተባለው ንጉስ ነው። መንግስቱን በተመለከተ እርስዎ ይወስኑ!!ሀይማኖቱን በተመለከተ ችግር ያለ አይመስለንም’’አሏቸው።
ጅማ አባ ጅፋር በመጨረሻ ለሚኒሊክ ሊገብሩ ወሰኑ። አንድ ቀን የሚኒሊክ ሰዎች መጡ። ‘’እርስዎ የጋብቻ ዝምድና አላችሁ ይባላል፤ደም እንዳይፋሰስ እንዲረዱን እንፈልጋለን። እስቲ ሄደው እርስዎ ያናግሩልን፤ገብር ብለን ብንልክበት የሰማነው ጥሩ አይደለም’’
‘’ለኔስ እሺ ይላል ብላችሁ ነው፤ካዎ ጦና አስቸጋሪ ሰው ነው።’’ሄደው ሞከሩ።የሚሆን ሰው አይደለም።እንዳልቻሉ አስታወቁ።ተዋግቶ መጨረሻ ቦረዳ ጭላሼ በተባለ ቦታ ቆስሎ ተያዘ።
* * *
ካዎ ጦናና ጅማ አባ ጅፋር አዲስ አበባ ተገናኙ።ሚኒሊክ ባደረጉላቸው ጥሪ መሰረት ነው የመጡት። የተለያዩ ሀገር ባላባቶች ፣ንጉሶች ጨዋታ ይዘው ቤቱ ደምቆ ነበር።ሳያስቡት ሚኒሊክ ቢገቡ ሁሉም ደንግጠው ከመቀመጫቸው ተነሱ።አንድ ሰው ብቻ ከተቀመጠበት ንቅንቅ አላለም። ካዎ ጦና ነበር። ጅማ አባ ጅፋር ተቆጡ። ’’አንተ ንጉሱ እኮ ናቸው የመጡት ፤ ማ መሰሉህ?’’
‘’እኔ እንደ ንጉስ ተዋግቼ ተማርኬ ተይዣለሁ፤ አንተ ሳትዋጋ እጅህን ሰጥተሀል። እኔ አሁንም ንጉስ ነኝ። ’’አሉ ፈርጠም ብለው።
‘’እውነቱን ነው።’’ብለው ምንይልክ ነገሩን አበረዱት ።
* * *
ቦረዳዎች(ቦረዳ የፀረ_ባርነት ትግል ታስተባብር የነበረች የንጉስ መቀመጫ ትንሽ ግዛት ናት።የወላይታን የባርነት አገዛዝ ለማስወገድ ሀይል ታሰባስብ ነበር።ዶርዜ ፣ደረማሎ ፣ጎፋ ለሚገኙ የካዎ ግዛቶች ወታደራዊ ጥሪ እያደረገች ጥቃቱን ተከላክላለች።አሁን ለተፈጠረው ፖለቲካዊ አንድነት መሰረት ነች። አፄ ሚኒሊክ ሠራዊት በአካባቢው ሲደርስ ካዎ ጦናን ህዝቡና የቦረዳ ንጉሱ ወግተዋል።እንድያውም ጦናን ያቆሰለው የኛ ሰው ነው የሚሉ የቦረዳ ሰዎች አሉ) ወደ አዲስ አበባ ቤተ መንግስት መጡ።’’እኛ ከእናንተ ጋር ጓድ ሆነን አብረን ተዋድቀናል፤ቆስለናል፤ሞተናል፤ድል አደረግን።ያሸነፍነውን ሰው ከደልቦ አጠገባችን አምጥታችሁ ሁምቦ ሾማችሁት። ወጋን፤ወግቶ ህዝባችንን ባርያ አርጎ ሸጠው።እንዴት ሚኒሊክ እያሉ እንሸጣለን።አሁን መሳ የተባለው መሬታችን በእሳቸው እንደተያዘ ነው።’’ የቦረዳ ህዝብ አመረረ።በቤተ መንግስቱ ታላቅ ስብሰባ ተካሄደ።ካዎ ጦና ወደ አዲስ አበባ ተጠሩ።ከዛ በኋላ ወደ ሀገራቸውም አልተመለሱም።መቃብራቸውም ባለወልድ ቤተ ክርስትያን ሆነ።አሁንም ያሉት እዛው ነው።
===============================