አንዱ ዓለም ተፈራ
መስከረም ፲ ፬ ቀን፣ ፳ ፻ ፲ ፱ ዓ. ም. (9/24/2026)
በአገራችን ሰፍኖ ያለው የፖለቲካ ትግል፤ የራሱ የሆነ የአካሄድ እና የእድገት ኡደት አለው። የዐማራ ህልውና ትግልን ትክክለኛነት ለምናምን፣ እና መሪ ድርጅቱን የዐማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄን (ዐፋብን) ለምንደግፍ፤ ይሄን ኡደት እየተከታተልን፤ የየራሳችንን ግንዛቤ እያሳደግን ነው። የዐፋብን አባላት፤ በየመድረካቸው ተወያይተው የሚደርሱበትን ውሳኔ፤ ያለማቅማማትና ያለ ተዐቅቦ መቀበልና በሥራ ላይ ማዋል አለባቸው። እኛ በበኩላችን፣ በዚህ ሂደት፣ ጭፍን የዐፋብን አምላኪዎች ወይንም ጭፍን ነቃፊዎች አይደለንም። እንደግለሰብ፤ ግራ ቀኙን በመረዳትና ሙሉ መረጃ በመሰብሰብ፤ የየራሳችን አቋም እንወስዳለን። በዚህ ሂደት፤ ዐፋብን በሚወስዳቸው እርምጃዎች፤ ሙሉ መረጃውን ሳንይዝ፤ የየራሳችንን ስሜት መለኪያ በማድረግ፤ እንዲህ መሆን የለበትም! እንዲያ ነው መደረግ ያለበት! የሚል መደምደሚያ ላይ አንሮጥም። የኔን የግል ስሜት፤ ማለትም ለአንድ አካል፣ ጉዳይ ወይንም ክንውን ያለኝን መውደድ ወይንም ጥላቻ፤ የትግሉን አካሄድ መለኪያ መሆን አላደርግም። ይህ የግል ጉዳዬ አይደለም። የዐማራ ህልውና ትግል፤ ከኔ ከአንድ ግለሰብ በላይ ነው። የፖለቲካ ትግል፤ የዛሬ ተጨባጭ ሁኔታን ለመቀየር፤ የሚደረግ ጥረት ነው። ትናንት የነበረው ክንውን፤ ለዛሬው ተጨባጭ ሁኔታ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያለው ቢሆንም፤ የዛሬው የፖለቲካ ትግል፤ ዛሬ በሕዝቡ ላይ ያለውን በደል ለማስወገድ የሚደረግ ጥረት ነው። ባጭሩ፤ የዛሬ የፖለቲካ ትግል የሚያነሳቸው፤ የዛሬ ጉዳዮችን ነው። የትናንት በደል አይረሳም። ያ ግን በቦታውና በጊዜው፤ ማንም ወደደም አልወደደም፤ በሥልጣን ላይ ያለው ክፍል እስካመነበት ድረስ፤ ነገ በፍርድ የሚታይ ይሆናል። በዚህ ስሌት፤ አሁን የታወጀውን ትብብር ለህልውና፤ ዙሪያ ገቡን ይሄ ጽሑፍ ይመረምራል። የትብብር ለህልውና መታወጅ፤ እንደምታው ምንድን ነው? ጠንካራና ሊሻሻሉ የሚችሉ ጎኖቹ ምንድን ናቸው? መደረግ ያለባቸው ጥንቃቄዎች፤ ምንድን ናቸው? እና በቀጠናው ያለውን የፖለቲካ አሰላለፍ በመዳሰስ፤ ከኛ ምን ይጠበቃል? የሚሉትን ጥያቄዎች ጽሑፉ ይመለከታል።
በአገራችን፤ ስርዓቱን ለመለወጥ የሚደረገው ትግል፤ የተጀመረው ዛሬ አይደለም። ገና ራሱን የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር (ትሕነግ) በሚል የሰየመው ቡድን፤ የአገራችንን ስርዓት፣ በገዢዎችና በተገዢዎች መካከል ያለ ቅራኔ ሳይሆን፤ “በገዢው የዐማራ ብሔር እና በተቀሩት ተገዢ ብሔሮች መካከል ነው! አገሪቱም የኢትዮጵያዊያን ሳትሆን፤ የብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝቦች ናት!” የሚል የፖለቲካ ፍልስፍና አንግቦ፤ ይሄንን የፖለቲካ ፍልስፍናውን እና የአስተዳደር ዘይቤውን ዘለዓለማዊ ለማድረግ፤ ሕገ መንግሥት አጽድቆ፣ ክልሎችን መሥርቶ፣ አስተዳዳሪዎች መድቦ፤ የበላይነቱን በተቆጣጠረበት ጊዜ ነበር። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ፤ በተለያዬ መንገድና በየራሳቸው፤ “ተበደልኩ!” በሚሉት ጉዳይ ላይ የተመሠረተ ትግል፤ ቀደም ሲል የነበሩትና አዳዲስ ተጨማሪዎች ተመሥርተው፤ አገራችን የጦር ሜዳ ሆና፤ የሕዝቡ ኑሮ ከዕለት ዕለት እየከፋ ቀጥሏል። በሥልጣን ላይ ያለው አብይ መራሹ የአክራሪ ኦሮሞዎች ገዢ ቡድን፤ ራሱን ተረኛ ነኝ በማለት፤ ያንኑ ፍልስፍና አጥብቆ ይዞ፣ አክራሪ ፀረ ዐማራ ተግባሩን አስፋፍቶና ዐማራን ለማጥፋት ያለ የሌላ ጉልበቱን እያፈሰሰ፤ እየቀጠለ ነው። አሁን በአገራችን፣ በኢትዮጵያ፣ ያለውን የፖለቲካ አሰላለፍ ብንመለከት፤ ሁለት ሰፈሮች ጎልተው ወጥተዋል። በርግጥ እንደማንኛውም የኅብረተሰብ ጉዳይ ሁሉ፤ ይሄ ምደባ፤ ጥርት ያለ ነጭና ጥቁር መሰመር የለዬ አይደለም። ነገር ግን፤ መሠረታዊ ወለሉ፤ ግልጥ ነው። የአክራሪው ኦሮሞ ገዢ ቡድን አንዱን ሰፈር ይዟል። ያንን የሚቃወሙ ደግሞ ሌላውን ሰፈር ይዘዋል። በነዚህ በሁለተኞቹ ሰፈር፤ የውስጥ የምንነትና የግብ ልዩነት አለ። በከፍተኛ ደረጃ ያለው ምደባ ግን፤ ሁለት ሰፈር ነው።
በሁለተኛው ሰፈር ያሉት፤ የየራሳቸው ግብ፣ አካሄድና ዓላማ ያላቸው ድርጅቶች ናቸው። እዚህ ላይ ጽሑፉ የሚያተኩረው፤ አሁን በታወጀው የትብብር ለህልውና ውስጥ የተካተቱትን ነው። ይሄ የጸሐፊውን ምኞት በማሰብ ሳይሆን፤ በመግለጫው በትክክል መዘርዘሩን በማጤን ነው። እኒህ በትብብር ለህልውናው የተሰባሰቡ ድርጅቶች፤ አንድ የጋራ የሆነ ጠላት አላቸው። ኢትዮጵያ የሁላችን አንድ አገር ናት! ብለው ያምናሉ። ይሄ እስከገዛቸው ድረስ፤ አንድ ሰፈር ናቸው፤ የሚያስብል መንገድ አለ። እንግዲህ ይህ ጽሑፍ፤ ይሄ የታወጀው የትብብር ለህልውና ምን ይከተለዋል! የሚለውን ይመረምራል።
በመጀመሪያ ደረጃ፤ ይህ የትብብር ለህልውና መታወጁ፤ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል መድረክ ላይ፤ ትልቅ እርግብግብታ ፈጥሯል። በሚወዱትም ሆነ በሚጠሉት፣ በጥንቃቄ በሚመለከቱትም ሆነ በጥርጣሬ ዳር ለመቆም በሚፈልጉት ዘንድ፤ የተለያዬ አመለካከትን አብቅሏል። ይሄ የሚጠበቅ ነው። አክራሪው የኦሮሞ ገዢ ቡድን፤ የተጠናከረ፣ የተቀናጀና ጉልበታም ተቃዋሚ እንዲኖር አይፈልግም። እንኳንስ በትጥቅ የታጀበ፣ በመላ አገሪቱ የተስፋፋና በግልጥ፤ ላስወግድህ ነው! ብሎ የተነሳ ይቅርና፤ በፓርላማ፤ ትክክል አይደለህም! ብሎ የተቃወመውን ሁሉ እስር ቤት የሚወረውር ገዢ ቡድን ነው። እናም እንዲህ ተሰባስበው ለገዢው ቡድን አማራጭ ሆኖ የሚቀርብ አካል ሲነሳ፤ እንቅልፉ ጥሎት እንደሚሄድ የታወቀ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ፤ በዚህ ዘረኛና ጠባብ አገር አፍራሽ ገዢ ቡድን የተማረረው የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ አማራጭ መኖሩ ሲታወጅለት፤ ተስፋው በጣም ያድጋል። ዝም ብሎ ከመገዛት፤ የተለዬ አማራጭ እንዳለ በማመን፤ የዚህን ገዢ ቡድን ፍጻሜ ለማምጣት፤ በሚችለው ሁሉ ይተባበራል። ባይሳተፍም፤ በማለገም ወይንም ዝም ብሎ፤ ለገዢው ቡድን ተባባሪነቱን ይነፍገዋል።
ይህ ሁለት ነገሮችን ወደ መድረክ ያመጣል። በመጀመሪያ ሕዝቡ በዚህ ገዢ ቡድን ላይ ያለውን ፍርሃት በማስወገድ፤ ጥገኝነቱን ይቀንሰዋል። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ፤ ሕዝቡ አማራጭ አለ! በማለት ተስፋው ያድጋል። ከዚያ በኋላ፤ አብይ መራሹ የአክራሪ ኦሮሞዎች ገዢ ቡድን፤ “ሽፍቶች!” “የውጪ ኃይላት መሳሪያዎች!” ብሎ የሚነዛው ቅስቀሳ፤ ውሃ አያነሳለትም። አንድ ሆነውና ኃይላቸውን አሰባስበው መነሳታቸው፤ በገዢው ወገን ፍርሃትን ማሳደሩ ብቻ ሳይሆን፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ፤ አስተዳደሩ አገሪቱን መቆጣጠር የማይችል እና አማራጭ ጉልበት ያለው አካል እየመጣበት ያለ መሆኑን ያውጃል። በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ሠራተኞች፤ የራሳቸውን መዳኛ እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል። ነፍሴ አውጭኝ ሩጫ ይጀመራል። በክፍላቸው የሚገኘውን ንብረት እየዘረፉ ለነጋቸው መጋፈፉን ይያያዙታል። አንቆ ይዟቸው የነበረው ፍርሃት ሲገፈፈ፤ ዐማራው ከትግሬው፣ ኦሮሞው ከሲዳማው መነጋገር ይጀምራል። የሚችለው ከአገር ሲሸሽ፤ የሚቀረው ለራሱ ሲል እየተደራጀ በያለበት ሂያጁን ለመሸኘት፣ መጪውን ለመቀበል ይሯሯጣል። ይሄ ሁሉ ተደማምሮ ገዢውን ቡድን ይቦረቡረዋል። ኡደቱ ራሱ ሚዛኑን ወደ ታጋዩ ክፍል እንዲያጋድል ያደርገዋል።
ትብብር ለህልውናን ገባ ብለን እንመለከት። ይህ ትብብር ለህልውና፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ወዳጆች ብቻ የተሰባሰቡበት አድርገን ለመቁጠር፤ የሚያስችለን አግባብ የለም። ትናንት ለዚህ ሁሉ ችግር ፈጣሪዎችና መሠረቶች የነበሩ አካላት እንዳሉበት፤ መረዳት አለብን። ጠንካራ ጎኖቹ፤ አንድም ኢትዮጵያን እንደ አገራችው መቀበላቸው ነው። ሌላም አብረው ይሄንን ፀረ ኢትዮጵያዊያን እና ፀረ ኢትዮጵያ የሆነ ገዢ ቡድን ተባብረው ለመጣል መስማማታቸው ነው። ቀጥሎም፤ የሽግግር መንግሥት ለማቋቋምና ለሕዝብ የበላይነት ቦታ መሥጠታቸው ነው። ይህ ትልቅ ዕድል ይዞ መጥቷል። ለለውጥ ፈላጊዎች፤ በኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ፤ እኒህ በትብብር ለህልውና የተሰባሰቡት ድርጅቶች ብቻ ወሳኞች መሆን የለባቸም። በርግጥ፤ እነሱ ናቸው አሁን ከፍተኛውን መስዋዕት እየከፈሉና ገዢውን ቡድን ታጥቀው እየታገሉ ያሉት። ቀሪዎቹ፤ ቢቻል አሁኑኑ ከነሱ ጋር የትግሉ አካል በመሆን፤ የምንፈልገው እንዲመጣ መታገል አለብን። ባይቻል ደግሞ፤ በያለንበት በመደራጀትና ግንኙነቶችን በመፍጠር፤ የትግሉ አካል መሆን አለብን። በደፈናው ሶፋ ላይ ተቀምጠን፤ አዛዥ ናዛዥ ለመሆን መጣሩ፤ የትግሉ አካል አያደርገንም።
ሊሻሻሉ የሚችሉና ሊያጋጥሙት የሚችሉት እንቅፋቶች እንመልከት። አሁን ቢያንስ በትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪና በኦሮሞ ነፃነት ግንባር በኩል፤ ለራሳቸው ደጋፊዎች የሚሆን አፍራሽ መልዕክቶችን ሲረጩ አጢኛለሁ። በትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር በኩል፤ አንዳንድ የአመራር አባላት፣ ወልቃይት እና ራያ የነሱ እንደሆነና እንደሚመለስላቸው ሲናገሩ አዳምጫለሁ። በኦሮሞ ነፃነት ግንባርም በኩል፤ መሪው፣ በወለጋ የሚንቀሳቀሰው ፋኖ፤ የአብይ ፈጠራ እንጂ፤ እየደረሰበት ባለው የመጥፋት አደጋ፤ አልጠፋም ብሎ የተነሳ የዐማራ ፋኖ መሆኑን አለመቀበሉን አስተውያለሁ። ምንም እንኳ ባልተረጋጋ መተባበር ሂደት፤ የፖለቲካ በላይነት ቦታ ለመያዝና የያዙትን ለማጠናከር ሩጫ እየተካሄደ መሆኑን ብረዳም፤ አፍራሽነቱን ግን መካድ አልችልም። ምን ያህል ለትብብሩ ቁርጠኝነት አላቸው? የሚል ጥያቄ እንድወረውር አድርጎኛል። በኔ በኩል፤ አንድም በቦታው የተቀመጠውን ሕገ መንግሥት እንደሚያፈርሱትና ሁሉ በኢትዮጵያዊነቱ የትም መኖር የሚችልበትን ስርዓት እንደሚያስከትሉ በማሳሰብ፤ የክልሎችን መፈርስ ማወጅ አለባቸው። አለያም ሁሉም የሚያምኑበትና የሚስማሙበት ተከታይ እውነታ ብቻ ነው መነገር ያለበት። ዋናው የትብብር ለህልውና ጉዳይ፤ አብይን መጣል ብቻ ሳይሆን፤ በቦታው ትክክለኛ የሆነ የሕዝቡን ተቀባይነት ያገኘ የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት ማቋቋም መሆን አለበት። ያ ደግሞ በሕዝቡ ፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባዋል። በርግጥ ይሄ ሁሉ በዝርዝር ከሚከተለው መገለጫቸው ውስጥ ይካተታል! የሚል ፍላጎት እናም እምነት አለኝ።
መከተል ያለበት፤ ሕዝቡን እንዴት ሊያደራጁት እንደሆነ፤ ዓላማቸውን በግልጥ ማስረዳት ነው። ይሄን ግን፤ ሕዝቡ ለነሱ ብቻ መተው የለበትም! እላለሁ። አሁኑኑ በያለበት ሕዝቡ እየተሰባሰበ መደራጀት አለበት። በንጉሠ ነገሥቱ የመውደቂያ ዋዜማ፤ የሳቸውን መውደቅ እንጂ፤ መተኪያውን በማዘጋጀት በኩል ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ባለመኖሩ፤ ደርጋማው የአረመኔው መንግሥቱ ኃይለማርያም ቡድን መጥቶ፤ እናንተ አርፋችሁ ተቀመጡ፤ እኔ ሁሉን እሠራዋለሁ! አለና፤ አምባገነን ስርዓቱን አነገሠ። ቀጥሎም አረመኔውን መንግሥቱን፤ ሕዝቡ ልጆቼን ላንተ ሥልጣን አልገብርም! ብሎ ሲነሳ፤ በጎን ትሕነግ ሰተት ብሎ ገባና፤ ኢትዮጵያን ከዚያ በፊትና ከዚያ በኋላ የሚያሰኝ አዲስ ሰርዓት ዘረጋ። ከዚያም የኢትዮጵያ ወጣቶች፤ አትከፋፍሉን፤ በዘር መለያየት በቃ! ብሎ የተነሱበትን ዓላማ፤ “ኢትዮጵያ! ኢትዮጵያ!” እያለ አብይ ገባና፤ የአምባገነን ስርዓቱን አጠናክሮ፣ የሥልጣን ኮርቻው ላይ ተፈናጠጠ። አሁንም ሌላ አምባገነን እንዲከተል አንፈልግም። እናም ሕዝቡ የራሱ የሆነ ማስተማመኛ ተቋም ሊመሠርት ይገባዋል። በባህላችን ብዙ የሽምግልና ሂደቶች የሚከናውኑባቸው በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው አሠራሮች አሉን። በተመሳሳይ መንገድ፤ በቋሚነት የሕዝቡን ፍላጎት ከአምባገነን መንግሥት የሚጠብቅ ተቋም መፍጠር አያቅተንም። እስካሁን ዐፋብን ብዙ ተስፋ የሚሠጡ ተግባራትና አሠራርን አሳይቶናል። ያ ምን ያህል ቀጣይ ይሆናል? ይሄን መመለስ ያለብን እኛ ነን፤ ተደራጅተን አስፈላጊ ተቋማትን በመፍጠር።
አንድ መታየት ያለበት ሀቅ አለ። ይሄ ትብብር ለህልውና በአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ መድረክ የሚፈጥረው፤ የአሰላለፍ ሂደት ነው። በአገራችን ካለው ሁኔታ አኳያ፤ የሱዳንን የፖለቲካ ሀቅ ብንመለከት፤ በመካከላቸው ያለው አገር አፍርስ ጦርነት፣ ከኛ አገር ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው። ሁላችን እንደምናውቀው፤ አብይ የደቡብና ምዕራቡን የፈጥኖ ደራሽ መሪ ሚቲን ደግፎ፤ የአረብ ኢሚሬትስ አሽከርነቱን አንግቦ፤ በማያገባን አደገኛ ጦርነት ውስጥ ከቶናል። በሌላ በኩል፤ የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር፤ ከኤርትራ መንግሥትና ከግብፅ ጋር በመወገን፤ የአል ቡርሃንን መንግሥት እየደገፉ ነው። ይሄ ለዐፋብን ምን ይፈጥራል? የሚለው ከባድ ጥያቄ ነው። የሶማሊያ የፖለቲካ ሁኔታ በአገራችን ላይ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አለው። በደቡብ ኢትዮጵያ በኩል፤ ድጋፍና ተቃውሞ ለተለያዩ ድርጅቶች በመሥጠት፤ የሱማሊያ መንግሥትም ሆነ ተቃዋሚዎቹ፤ የአገራችንን የውስጥ የፖለቲካ ሂደት፤ እየበረዙት ነው። በየመን ያለው የእርስ በርስ ውጊያ፤ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። የቀይ ባህርን ከፍተኛ ጠቃሚነት በማጤን፤ ቅርብና ሩቅ ያሉ ኃይላት፤ ለመርከቦቻቸው ሰላማዊ መንገድ ለመክፈት ሲሉ፤ ዙሪያ ገቡን ፈትሸው፤ የጦር እርዳታና ጣልቃ ገብነቱን ጀምረውታል። ኤርትራ፤ ለህልውናዋ ስትል፤ በኢትዮጵያ የሚካሄደውን የፖለቲካ ትግል፣ ለራሷ ፍላጎት ማሟያ ለማድረግ እንደማታርፍ እውቅ ነው። ይሄን ሁሉ በማጤን፤ የዐፋብንን ጉልበት የምናጠነክርበትን እና በአፍሪካ ቀንድ ዘንድ የአገራችን ትክክለኛ የፖለቲካ ቦታ የሚጸናበትን መንገድ ለማስተካከል መሻት አለብን።
በመደምደሚያ፤ ትግሉ እንዲሳካና ቀጣዩ አስተማማኝ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን የሚከተል የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም፤ ከኛ ምን ይጠበቃል? የሚለውን እንመልከት። በመጀምሪያ፤ ይሄን የተፈጠረውን ትብብር ለህልውና፤ በሙሉ ልባችን በመቀበል፤ ሊሻሻሉ የሚገባቸውን ለሚመለከታቸው በማቅረብ እንዲሟላ ማድረግ። ቀጥሎ፤ በዚህ በትብብሩ ውስጥ፤ ዐፋብን የጎላ ሚና እንዲጫወት፤ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግና ዐፋብንን ማሳደግ። ይሄንን ማድረግ የምንችለው፤ በየበኩላችን ከምናደርገው ጥረት በላይ፤ በትብብርና አንድ ማዕከል በመፍጠር፤ በፋኖዎቻችን ዘንድ ተደማጭነትን ስናተርፍ ነው። እናም በውጪ ያለን ደጋፊዎች ወደ አንድ እንሰባሰብ። ከዐፋብን ጋር መዋቅራዊ ትስስር እንመሥርት። ከዚያም ድርጅታዊ ተልዕኮዎችን፤ የዲፕሎማሲ፣ የጥብቅና እና የንብረት ማሰባሰብ ሂደትን እናከናውን። ድጋፋችን ትርጉም የሚኖረውና አመርቂ የሚሆነው፤ አንድም በዝተን በአንድነት ተደራጅተን ስንገኝ፣ ሌላም ድርጅታዊ ትስስር ሲኖረን ነው። በቋሚነት የተወሰነ ወርሃዊ የአባልነት መዋጮ በማድረግ፣ አስተማማኝ እና የታወቀ ድጋፍ ማድረግ እንችላለን።
አመሰግናለሁ።