በጎች ሲታረዱ አሩሲ ወለጋ፣
ዱለት እያስከተፍክ ቆራርጠህ ፍሪንባ፣
ካምቦ ቁጭ ብለህ ጳጳስ ዱለት ብላ፡፡
ይኸንን አላዩ ይኸንን አልሰሙ፣
አቡነ ሚክኤል ጴጥሮስ ሰማእቱ፣
ፋሽሽት ሞሶሎኒን ፍልሚያ የገጠሙ፣
በበጎቹ ፋንታ አንገትን የሰጡ፡፡
የሰማእት ሐዋርያት ስሞች ተሸክመህ፣
ጳውሎስና ጴጥሮስ ማትያስ እየተባልክ፣
ለፍርኦን ለቄሳር በፍርሃት እየሰገድክ፣
ጳጳስ ተዝካርን ዛቅ በጎች እያስፈጀህ፡፡
ካባን አሳምረህ ቄንጠኛ ቆብ ደፍተህ፣
ሪዝ አንዠርግገህ ጺምህን ከፍክፈህ፣
ቅባት ተቀባህተህ ሽቶህን ረጭተህ፣
ተዙፋን ቁጭ ብለህ ሕዝብ ሽቅብ ሲያይህ፣
ልብሴን ነወር በሉት ሆነኮ ነገርህ፡፡
የምዕመን አስራት ዝቀህ እየዘረፍክ፣
በሉመዚን ሰፈህ ሞዝቦልድ እየተኛህ፣
በቅንጦት ስትኖር ቆብ ተራስህ ደፍተህ፣
የምንኩስና ሕግ ህሊናህ አይገዛህ፡፡
በጎች ሲታረዱ ያልተረዳህ መስለህ፣
የሰማእት ሬሳ ዙሪያ ክብብ አርጎህ፣
እንደ ሰጎን ስትኖር ራስ ተምድር ቀብረህ፣
የጨበጥከው መስቀል ማተብህ አይከስህ!
በሆድህ ብትያዝ ለነፍስህ ብትሳሳ፣
ለአጭር ምድር ህይወት ሰማዩን ብትረሳ፣
ጥቅም ስታሳድድ ታሪክህ ቢግማማ፣
ሞትን አታመልጣት ከች ትላለች ደርሳ፣
እስከዚያው “ይመችህ” ፈልሰስ በል ከተማ፣
በግን እያሳረድክ ጳጳስ ተዝካር ብላ፡፡
እረኛቸው ፍትፍቱን ሲስቅ በአውሬ እየተነከሱ ከነማተባቸው ለወደቁ በጎች!
በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)
መስከረም ሁለት ሺ አስራ ዘጠኝ ዓ.ም,