በበላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)
“አንዴ ካታለልከኝ አሳፋሪው አንተ ነህ፤ ሁለተኛ ካታለልክኝ ግን ማፈሪያው እኔ ነኝ”

በሃይማኖቻችንና በባህላችን ማታለል የመስርቀን ያህል አሳፋሪ ነበር፡፡ እንደ አለመታደል ግን ይህ አድግ የተባለው ተምች አገሪቱን ከወረራት ጊዜ ጀምሮ ማታለልና ማጭበርበር “የቤተ መንግስት” ቋንቋና መመርያ ሆኗል፡፡ ይህ ያልተባርከ ቋንቋና መመርያም “ከራሴ በፊት ለኢትዮጵያ እናቴ” በሚል ቅቤ ተነቅሮ የሚያድገውን አማራን ሰለባው ሲያደርግ ኖሯል፡፡ ይህ አማራ ላይ አፈ ሙዙን ያነጣጠረው የማያባራ ማታላያ ዛሬ ደሞ “አገራዊ ምክክር” በሚሉት የበግ ለምድ በለበሰ ቀበሮ መልክ ብቅ ብሏል፡፡ በግ ለምዱን የለበሰውን ቀበሮ መለየትና ግብግብ መግጠም አቅጦት ከዘፍጥረት ጀምሮ እስካሁን ድረስ በቀበሮ መነጠቁን ቀጥሏል፡፡ አማራም ቆዳውን የለበሰ አይኑን በጨው የታጠብ ቀጣፊና አታላይን አንጠርጥሮ መለየትና አንቅሮ መትፋት ተስኖት ለግማሽ ክፍለ-ዘመን በጭራቆች እየተነጠቀ ለህልውናው የሚያሰጋ አደጋ ተደቅኖበታል፡፡ የተደማሪ ምሁራን፣ ጋዜጠኞች፣ የሰብአዊ መብት ጠባቂና የፖለቲካ ተንታኝ ነን ባዮች የራዲዮና የተሌቪን ድስኩርም የአማራን መታለልና የህልውና አደጋ አባብሶታል፡፡
የተማሩትና የተመራመሩት በቀላሉ ተታላይ ለመሆን ይመስል የአማራ ምሁራን ፊደል በቅጡ ባልቆጠሩ ካድሬዎች ይታለሉና ተታለልን ሳይሆን አታለሉን ይላሉ፡፡ አታለሉን ብለው የሚያሳብቡት ድክመቱን ከራሳቸው ጫንቃ አውርደው አማራን እንዲጠሉና እጭበርባሪ፣ ቀጣፊ፣ ዘራፊና አረመኔ እንዲሆኑ ተደርገው ባደጉት ጭራቆች ትከሻ ለመጣል ነው፡፡ መታለሉን ያወቀና ተታለልኩ ያለ ካለፈው የመማር እድል አለው፡፡ አታለሉኝ ወይም አንዘላዘሉኝ እንጅ ተታለልኩ ወይም ተንዘላዘልኩ የማይልና ራሱን ፈትሾ ትምህርት የማይወስድ ደግሞ ዳግም የመታለልና የመንዘላዘል እድሉ ሰፊ ነው፡፡ ፈረንጅ እንኳ “አንዴ ካታለልከኝ አሳፋሪው አንተ ነህ፤ ሁለተኛ ካታለልክኝ ግን አሳፋሪው እኔ ነኝ” የሚል ተረት አለው፡፡
በተለምዶ ደርግ እየተባለ የሚጠራው አገዛዝ በአብዛኛው የኢትዮጵያን ሕዝብ ያልተወደደ ስለነበረ የትግሬ ነፃ አውጭ ነን ባዮች በሱዳን ተሽከርካሪዎች፣ በግብጽና በምዕራባውያን ትከሻ ተወንበር ቁጢጥ ሲሉ የደርግ ሰራዊቲም ሆነ የአማራ ሕዝብ “ከደርግ የባሰ አይመጣም” በሚል መንፈስ ካለ ብዙ ተቃውሞ እንደተቀበላቸው የሚታወቅ ነው፡፡ እንዲያውም በልዋጭ- ልዋጭ የሱዳን እቃ እህል ሲሸምቱና የስንቅ መጫኛ አህያ ሊገዙ በእግዜአብሔር እንግዳ መልክ ሲቀርቡ “እምቦሳ እሰሩ” እያለ በደንብ እየመገበና እቤቱ እያሳደረ የእግዚአብሔር እንግዳን በሚቀበልበት ባህሉ አማራ አስተናገዳቸው፡፡ ወንበሩን በጨበጡ ማግስት ጀምሮ ባጎረሳቸው ሕዝብ ላይ ያወረዱትን የመከራ ቸነፈር ለአማራ መንገር ለቀባሪው ማርዳት ነው፡፡ የንብረት ዘረፋውን፣ የእርስቱን መነጠቅ፣ ከመንግስት ተቋማት መገለል፣ በወህኒ ቤት እየታጎረ የአካልና የስነ ልቡና ጣጣቴ መተኮስና መሰለብ፣ ሴቶችን በወሊድ መቆጣጠሪያ ክኒንና መርፌ ማምከን፣ በባሩድ በመደዳ መፍጀትና በሌሎችም አረመኔ መንገዶች የተፈጸሙ ዘግናኝ ግፎች ታሪክ መዝግቦ የያዛቸውና ለዘላለም የሚኖሩ ናቸው፡፡
ጭፍጨፋውና መከራው ያንገፈገፈው ሕዝብ እምጾና በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች አልቀው የትግሬ ነፃ አውጪ ወንበሩን ለቆ ሲሄድ አማራ ራሱን አደራጅቶ ህልውናውን ማስከበር ሲገባው ስልጣኑን እንኩ ብሎ እንደገና ለተረካቢ ጨፍጫፊዎች አስረከበው፡፡ ተረካቢ ጨፍጫፊዎችም አማራ ለኢትዮጵያ ያለውን የጠበቀ ፍቅርና ሥነ-ልቦና እንደ ድክመት በመቁጠር “ኢትዮጵያ ሱስ ናት፤ ስንኖርም ስንሞትም ኢትዮጵያዊ” የሚሉ ማተለያ ዘፈኖችን ይዘው ብቅ አሉ፡፡ የአማራ ምሁራን፣ ጋዜጠኞችና የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪንና የፖለቲካ ተንታኝ ነን ባዮችም ተደምረው ይኸንን ዘፈን ከራስ እስከ እግር ጥፍር እስተሚያልባቸው ድረስ እየጨፈሩና እየዘፈኑ የአማራን ሕዝብ አታለው ዳግም ወደ ገደል አፋፍ ወሰዱ፡፡ ተወልዶ ሲነቀር ጀምሮ “ከራሴ በፊት ለኢትዮጵያ እናቴ” የሚለውን ዜማ ሲሰማ የኖረ እማራም ለሃያ ሰባት ዓመታት የደረሰበትን ግፍና ግፉን በመቃወም የተውለትን እንደ ፕሮፌሰር አስራት፣ አሰፋ ማሩና ሳሙኤል አወቀ ያሉ ሰማእታትን ሳይቀር ረስቶ አገሪቱን ከመፈረካከስ እስካዳኑ ድረስ በሚል መንፈስ በደስታ እንባ እየተራጨ በመላው ዓለም ተቀበላቸው፡፡
ይኸንን የመሰለ የሕዝብ ድጋፍ ያገኙ እነ ኢትዮጵያ ሱሴም ወዲያው ተወንበሯ ቁጢጥ እንዳሉ በደስታ እንባ በተቀባላቸው አማራ ሕዝብ ላይ የደረሰውን ግፍ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም ለአማራው መንገር አሁንም ለቀባሪው ማርዳት ነው፡፡ የስልጣን ዘመናቸው ወር ሳይሞላ በሻሸመኔ፣ በዝዋይ፣ በአርሲ፣ በከፋ፣ በወለጋ፣ በመተከል፣ በደራና ሌሎችም ሥፍራዎች የደረሰውን የህጻናት፣ የእርጉዞች፣ የእናቶች፣ የአባቶች ጭፍጨፋ፣ እስከሬን ጉተታ፣ የንብረት ውድመት በስንክሳር እንጅ በአንድ ጦማር ዘርዝሮ መጨረስ የማይቻል ነው፡፡
ይህ ከግራኝ መሐመድ ወዲህ በዓይነቱም ሆነ በጥልቀቱ ወደር የሌለውና ጣሊያን እንኳ ያላደረገው ጭፍጨፋ፣ የቤተክርስትያን ቃጠሎ፣ የአይን በጉጠት መውጣትና አስከሬን ጉታታ ያንገፈገፋቸው የአማራ ወጣቶች በፋኖነት ተደራጅተው እንደ ቅድመ አያቶችቻው እምቢኝ ማለት ሲጀምሩ እነ “ስንኖርም ስሞትም ኢትዮጵያዊ” አሁንም ግራኝ መሐመድን አስታጥቃ ተላከችው ቱርክ ድሮን እየተረጠቡ የአማራን ሐዘንተኛ ሳይቀር ዳስ ወስጥ በድሮን መጨፍጨፉን ቀጠሉ፡፡ በባንዳ መንገድ መሪነት የተረጨው የሞሶሎኒ የማስታርድ ጋስና ቦንብ የአማራን ፋኖ እንዳላንበረከከው ሁሉ በከሀዲያን አመልካችነት ጭራቆች የሚወረውሩት የቱርክ ድሮንም የዘመኑን የአማራ ፋኖ ብጥቅ አላረገው ሲል ድርድርና ሽምግልና የሚሉ ማታለያዎችን ደጋግመው ሞከሩ፡፡ ድርድና ሽምግልናው እንደ “ኢትዮጵያ ሱሴ” መፈክር ሁሉ ማተለያ መሆኑ ሲታወቅባቸው ደሞ አማራ አገርና ኢትዮጵያ ሲሉት ከንፈሩን ጥሎ ይከተላል በሚል “አገራዊ ምክክር” የሚሏት መጥለፊያ ገመድ ይዘው ብቅ አሉ፡፡ መለኮት እንደፈጠረው ሰው ቅንጣት ይሉኝታና ሐፍረት ስለማይሰማቸው የአገራዊ ምክክር ተሳታፊዎችን ራሳቸው መርጠው፣ የምክክሩን ሰነድም ራሳቸው ሞነጫጭረው፣ ራሳቸው ደንብ አውጪና አመካካሪ ሆነው ብቅ አሉ፤ የስምምነት ድሪቶም ደርተው አሳዩ፡፡ ይህ የስምምነት ድሪቶ አማራ ሳይሳተፍበት እየተገዛበት ካለው ሕገ-አራዊትም የከፋ መሆኑን ልብ ይበሉ፡፡
ስልጣንና ገንዘብ እዝነ ልቡናና ህሊናን ብቻ ሳይሆን አይንና ጆሮንም ስለሚደፍን የአማራን ቅዱስ የሽምግልና ባህልና ታሪክ ዘወር ብለው ማየትና መስማት ትተው አማራን ስለምክክርና ሽምግልና ሊያስተምሩ ቃጡ፡። በአማራ ባህል ምክክርም ሆነ ሽምግልና መለኮታዊ ኃይልን ያቀፈ መንፈሳዊ ግብር መሆኑን ሳቱ፡፡ በአማራ ዘንድ ሽምግልና ኑዛዜን ንስሀን፣ ዳኝነትን፣ ፍርድን፣ ፍትህን፣ ይቅር በሉኝ ባይነትና ይቅርታ ተቀባይነትን የሚያጠቃልል ቅዱስ ተግባር መሆኑን ለመማር ሰነፉ፡፡ ጭራ ስላወናወኑ ብቻ ሽማግሌ የሆኑ መስሏቸው እነ ኤፍሬም ይስሀቅ የፈረንጅን ድርድር ሽምግልና ብለው ጭምልቅልቅ እስካረጉት ድረስ ስናድግ የምናውቀው ሽምግልና ከአድሎ ሙሉ በሙሉ የፀዳና በራስ ልጅ ሳይቀር ፍርድ የሚያስፈርድ የተቀደስ መንፈሳዊ ተግባር እንደነበር ለማመን ተቸገሩ፡፡
ልጅ ሳለሁ ሁለት ጎረምሳ ወንድማማች ያጎቴ ልጆች መንገድ ገፍተው የተከሉትን ተክላቸውን የረገጠ አንድ ሰው ፈነከቱ፡፡ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ፈንካቾችና ተፈንካቹ ለእርቅ ተስማሙ፡፡ የፈንካቾቹ አባትና ሌሎች አጎቶቼ ሽማግሌ የመምረጡን ዕድል ሙሉ በሙሉ ለተጎዳው ለተፈንካቹ ሰጡ፡፡ ይህንን ሽማግሌ የመምረጡን እድል የተረከበው ተፈንካችም የፈንካቾችን አባት፣ አጎታቸውንና የእኔን አባት ለሽምግልና መርጧቸው እርፍ አለ፡፡ ተፈንካቹ ለሽምግልና የመረጣቸው የፈንካቾች አባት፣ ሌላው አጎታችንና አባቴ የተጣለባቸው አደራ ከሰማይ የወረደ ያህል ተሰማቸው፡፡ ይህ አደራ የከበዳቸው እነዚህ ሽማግሌዎች ባንድ ድምፅ በልጆቻቸው ፈርደው ከዚያ በፊት በዚያ ዘመን ለእንደዚህ ዓይነት እርቅ ተከፍሎ የማይታወቅ ገንዘብ እንዲከፍሉና ድንጋይ ተሸክመው እግሩ ስር ወድቀው ተፈንካቹን ከልብ ይቅርታ እንዲጠይቁ አድርገው አስታረቁ፡፡ በሽማግሌዎች ፍትሐዊ እርቅ የረካው ተፈንካችም “ፍትህ ይበቃኛል” በሚል መንፈስ የሰጡትን ገንዘብ አልቀበልም ብሎ መለሰው፡፡ ፈንካቾችም ገንዘቡን አንቀብለም ብለው ትተውለት ሲሄዱ ሌላ ጊዜ ከደጃፋቸው ጣለለቻው፡፡ ሽምግልናው እርቅን ወለደ እርቅም ፍትህን አነገሰ፡፡ ፍትህን ያነገሰው እርቅም ሰላምና ፍቅርን አሰፈነ፡፡ የሰፈነው ፍቅርም ለጋብቻ አደረሰ፡፡
ከዚህ በፊት አማራን ለማጥመድ የተሞከሩት ኤፍሬም ይሳቃዊ ድርዶችም ሆነ “ሽምግልና” ተብዮች ከእንደዚህ አይንቱ የአማራ የሽምግልና ባህል እጅግ ተቃራኒና እንደ ላቲኑ ፊደል ከውጭ በእርጥባን የተገኙ የባህል ሸቀኖች ናቸው፡፡ አሁን አገራዊ ምክክር እያሉ አማራን ዳግም ጠልፎ ለመጣል የሸረቡት ገመድ ከእነ ኤፍሬም ይስሀቅ አይንቱ ድርድርም እጅግ የከፋና የአማራን ህልውና ከመቼው የበለጠ የሚፈታተን ነው፡፡ እንደዚህ አይነቱ ምክክር ወይም ድርድር ስልጣን የጨበጠ ወይም ጉልበት አለኝ ብሎ የሚያስብ ሁሉ አሻፈረኝ የሚልን ነፃነትና ክብር ፈላጊን ጠልፎ እግር ለማሳም የሚጠቀምበት ወጥመድ ነው፡፡ ከሽምግልና በተቃራኒ እንደዚህ አይንቱ ምክክር ወይም ድርድር ውስጥ ይሉኝታ፣ ህሊና፣ ኑዛዜ፣ ንስሀ፣ ዳኝነት፣ ፍርድ፣ ፍትህና ይቅርታ የሉም፡፡ ድርድር ውስጥ ጉልበት እንጅ መለኮታዊ መንፈስ የለም፡፡ ሽምግልና ውስጥ አሸናፊው የተጎዳ ሲሆን በምክክር ወይም በድርድር አሸናፊው የጎዳ ነው፡፡ የድርድር ድሪቶ ክር ነገ እሚቦጨቅ ሲሆን ሲሆን የሽምግልና ቃልኪዳናዊ ውል ግን ዘላለማዊ ነው፡፡ ይህ ኢመለኮታዊ አገራዊ ምክክር አማራን ዳግም ጠልፎ ለመጣል የተሸረበ ገመድ መሆኑን ለመረዳት ሙሉ የሰው አይምሮ ሳይሆን ከእንሰሳት የምንጋራው ህብለሰረሰርም በቂ ነው፡።
ይልቁንስ አማራ የሚያሰፈልግው ምክክር ከራሱ ከሰፊው የአማራ ሕዝብ ጋር ነው፡፡ አማራን ለግማሽ ክፍለ-ዘመን እየተካሄደበት ካለው የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋና እርስት ነጠቃ የሚያድነው የርዕዮት ዓለም፣ የእምነት፣ የጎጥና ሌሎችምን ጅላጅል ስሜታዊ ልዩነቶችን ድርምስምስ አርጎ የሰበረ ልባዊ ምክክር ነው፡፡ አማራ የሚያሻው እንደ እምነቱ፣ እንደ ባህሉና እንደ ታሪኩ በበቁ ሽማግሌዎች የሚመራ ልባዊ የአማራ ሕዝብ ምክክር ነው፡፡ አማራ ከዳር ዳር ተመካክሮ በአንድ መስመር ከመጣ ህልውናውን የማረጋገጡና የእርስቱ ባለቤት የመሆኑ እዳ ገብስ፤ መንገዱም ጨርቅ ነው፡፡ አመሰግናለሁ፡፡
ነሐሴ ሁለት ሺ አስራ ስምንት ዓ.ም