በላይነህ አባተ abatebelai@yahoo.com
የአንደኛ ደረጃ ትምህርት በጀመርንበት ዘመን አባ የሻነው የምንላቸው የተከበሩ መምህር ነበሩን፡፡ አባ የሻነው ሊረሱ ከማይችሉትና መዘንጋትም ከማይገባቸው መምህሮቻችን አንዱ ናቸው፡፡ አባ የሻነው እንደ ንድፍ ጥጥ የተከመረው ደጉራቸው ፍሬ እንደ ከበደው መልካም ጤፍ ሰብል ወድቆ የራስ ቅላቸውን እስተ ግንባራቸው የሸፈነው፣ እንደ አረፋ የነጣው ጢማቸውም ሰልካካውን ቀይ ፊታቸውን ዙሪያውን እንደ አጥር ያጠረው፣ ፍትው ብሎ የነጣ ጭራ ከእጃቸው የማይለይ ግርማ ሞገሰን የተጎናጸፉ መምህር ነበሩ፡፡ አባ የሻነው የአማርኛም የሥነ-ምግባርም መምህር ነበሩ፡፡
አባ የሻነው ግብ የሚሳካው ተስፋ ካለመቁረጥና ከልምድ ከመማር መሆኑን በምሳሌ ሲያስተምሩ የትልን ታሪክ እንዲህ ሲሉ ይተርካሉ፡፡ ራሳቸውንም እንደ ተማሪ በመቁጠር “እስቲ ዛሬ ደሞ ተትሏ እንማር!” ይላሉ፡፡ “ትሏ ዛፍ ለመውጣት ስትሞክር ወደቀች፤ አንድ በሉ፡፡ እንደገና ሞክረች ግን ነጠረች፤ ሁለት በሉ፡፡ አሁንም እንደገና ስትንጠለጠል ዘች አለች፤ ሶስት ብሉ፡፡ ዘች ታለችበት ተነስታ እንደገና መንገዷን ቀይራ ተንጠለጠለች፤ ግን ተመልሳ እርፉቅ አለች፤ አራት በሉ፡፡ እርፉቅ ታለችበት ተነስታ አሁም ግንዱን በትንሹ ወጣች፤ ግን እንደገና ተንደባለለች፤ አምስት በሉ፡፡ ተተንደባለለችበት ተነስታ ተበፊቱ የበለጠ ርቀት ዛፉን ወጣች፤ ግን ተመልሳ ነጠረች፤ ስድስት በሉ፡፡ ተነጠረችበት ተነስታ ለሰባተኛ ጊዜ ስትሞክር ሰማይ የደረሰውን ዛፍ ምንም እንከን ሳይገጥማት ወጣችው” እያሉ ይተርካሉ ጨረቃ የመሰለ ፈገግታ እያሳዩና እንደ ስጋጃ የተነጠፈውን ጺማቸውን እያፍተለተሉ፡፡
ለመታየትና ለመደነቅ ተብሎ ስለሚደረግ ኢመለኮታዊ ባህሪ አደገኛነት ሲያስተምሩም የቄንጠኛዋን ልጃገርድ ታሪክ እንዲህ ሲሉ ይተርካሉ፡፡ “አንድ ልጃገረድ ብስክሌት ማሽከርከር ለመደች፡፡ ከጊዜ በኋላም በሲኒማ ያየችውን የቄንጥ አነዳድ አሳይታ ተጓደኞቿ አድናቆትን ለማትረፍ ሁለት እጆቿን ወደ ሰማይ ሰቅላ፣ የግራ እግሯንም ወደ ጎን አንጠልጣላ በቀኝ እግሯ ብቻ ለማሽከርከር ስትሞክር ገደል ገባችና አረፈች፡፡ እንደ አለመታደል ለቄንጥ ስትል አጥንቷ ተሰባብሮ ቆማ መሄድ እንኳ የማትችል ሆነች“ ይላሉ፡፡
አባ የሻነው በራስ ከመተማመን ይልቅ የሰሙትንና ያዩትን ሁሉ እንደ ጉጉትና ጦጣ መኮረጅ ስለሚያስከትለው መዘዝ ሲያስተምሩም የጦጣዋን ታሪክ እንዲህ ሲሉ ያስተምራሉ፡፡ ““በአንድ ዘመን አንድ ጸሐፊ ከዛፍ ሥር ወረቀቱን በብዕሩ እየጠነቆለ ሲጽፍ ጦጣ ተዛፉ ቅርንጫፍ ተደብቃ ታየው ነበር፡፡ ይኸንን ስትመለከት የሰነበች ጦጣ ጸሐፊው የሚያደርገውን ሁሉ ለመኮረጅና ወረቀትን በብእር ለመውጋት ትመኝ ነበር፡፡ በዚህ ምኞቷም ጸሐፊው እግሩን ለማፍታታት እቃውን ጥሎ ከዛፉ ዘወር ሲል ትወርድና በበዕሩ ወረቀቱን ስትዘነቁል ቆይታ ሲመለስ ወደ ዛፉ ቅርንጫፍ ትዘል ነበር፡፡ ይህ የጦጣዋ ድርጊት ያስቸገረው ጸሐፊም ጦጣዋን የሚገላገልበትን ዘዴ ሲያሰላስል ሰንበተ፡፡ አንድ ቀን እንደ ተለመደው ጦጣዋ ካለችበት ዛፍ ሥር ተቀምጦ አንገቱን በዶሮ ላባ መገዝገዝ ጀመረ፡፡ ከዚያም በዶሮ ላባው ፋንታ የሰላ ካራ ከዛፉ ሥር አስቀምጦ እንደ በፊቱ እግሩን ሊያፍታታ ሥፍራውን ለቆ ሄደ፡፡ ጸሐፊው ሥፍራውን ለቆ መሄዱን ያየች ጦጣም ወርዳ ጸሐፊው ያደረገውን ለማድረግ ካራውን አነሳችና ስትገዘግዘው አንገቷ እንደ ሸንኮራ አገዳ ተቆርጦ ወደቀ“ ብለው ሲተርቱ አንገቷ ተቆርጦ ሲወድቅ በእዝነ ልቡናቸን እየታየን “እግዚኦ መሐርነ ክርስቶስ” እንላለን፡፡ እርሳቸውም “አይዟችሁ ተረትና ምሳሌ ነው” ብለው ያረጋጉና የተረቱበንት ምክንያትና ቁም ነገር ያስተምራሉ፡፡
የእነ አባ የሻነውን ትውልድ ገንቢ ትምህርት ተከትለን በራሳችን ሃይማኖት፣ ፍልስፍና፣ ባህል፣ ታሪክና ተሞክሮ ላይ የተመሰረተ ማህበረሰብ መገንባቱን ትተን አንዴ ምስራቁን ሌላ ጊዜ ምእራቡን እየኮረጅን የተከትልነው መንገድ ሁሉ እንደ ጦጣዋ አንገታችንን ገዝግዞ የሚቀነጥስ ካራ ሆኖ አረፈው፡፡
ቀንበርን ተሞፈር፣ ሞፈርን ተድግር፣ ድግርን ተወገል፣ ወገልን ተማረሻ አስማምቶ እያረሰ አገር በገነባው አርሶ አደር ግብር ጥበብ ቅሰሙ ተብለን ወደ ምዕራብና ምስራቅ ስንላክ ለራሱ ሃይማኖት፣ ፍልስፋና፣ ባህልና ታሪክ ባይተዋር በሆነው ባዶ የራስ ቅላችን የምእራቡንም የምስራቁንም አተላ አስገብተን እየመጣን ሶሻሊዝም፣ ኮሙኒዝም፣ ካፒታሊዝም፣ እምፔሪያሊዝም እያልን መስበክ ጀመርን፡፡ በጥራዝ ነጠቅ እውቀት በኮሚኒስት ማንፌስቶ ፍቅር ሙዝዝ አልን፤ በአልባንያ ሶሻሊዝም ሰከርን፤ አበድን፡፡ በአስተዋይነቱ፣ በጀግንነቱና በመንፈስ ልእልናው ተለምኖ መሪ የሚመረጥበትን የጎበዝ አለቃ ሥርዓት እርግፍ አርገን ትተን በካድሬ ልፍለፋ፣ በአፈና ወይም በገንዘብ ድለላ ገዥ ወንበር የሚቆናጠጥበትን ሕገ አራዊት ዘረጋን፡፡ “ የግራ ክንፍ፣ የቀኝ ክንፍ፣ አምስተኛ እረድፍ እየተባባልን ተናከስን፣ ተባላን፡፡ መፈክር ሲያሰማ በስህተት ቀኝ እጁን ያወጣ በኮረንቲ የሚጠበስበት አረመኔ አገዛዝ ፈጠርን፡፡ ማእከላዊ መንግስት ብዙም በሕዝብ የእለት ከእለት ኑሮና አስተዳደር ጣልቃ በማይገባበት ዘመን የአፍሪካ የዳቦ ቅርጫት የተባለችዋን የግዮን ምድር የርሃብ ምልክት አደረግን፡፡ እግዚአብሄር ሰውን በአምሳሉ ፈጠረው በሚለው እምነታቸው እንግዳ ሲመጣ በሚገባ መግበውና አልጋቸውን ለቀው ከሚያሳድሩ ቅድመ አያቶች ተወልደን ፋኖዎች ደቁሰው የመልሷቸው ቅኝ ገዥዎች ለመጥፊያችን የሳሉትን ካርታ ኮርጀን አገር እንደ ሽንኩርት በቋንቋ ቢለዋ ከፋፍለን ሕዝብን እርስ በርሱ እያስተላለቅን እንገኛለን፡፡
የአምስት ሺህ ዘመን የተዋበ የባህል ልብስ አውልቀን የምዕራባውያን የባህል ሳልቫጅ መልበስ መረጥን፡፡ የቅዱሳን መጻሕፍትና የእምነት መሰረት ያላቸውን የእነ ቅዱስ ዳዊትን ዋሽንት፣ ክራራ፣ ጸናፅል፣ ከበሮ፣ በገናና ክራርን ትተን ስልጡን ለመባል በጊታርና በሳክስፎን ማበዱን መረጥን፡፡ በእነ ቅዱስ ያሬድ ጥበባት የተመሰረቱትን ወረቦች፣ መዝሙሮችና ዘፈኖች ትተን ከምዕራብ በኮረጅነው ዜማና ዳንስ እንደ ጥንዚዛ እየተንፈራገጥን ሰለጠን አልን፡፡ አርበኛ ጸጉሩን በማጎፈሩ ስንስቅ ኖረን ፈረንጅ አፍሮን ሲከፈክፍ እኛም አብረን ከፈከፍን፡፡ ቁምጣ ለባሹን ዜጋ “ያልሰለጠነ ባላገር” ስንል ኖረን ፈረንጅ ቁምጣ መልበስ ሲጀምር እኛም ለመሰልጠን ኮርጀን ቁምጣ እንደተቀቃ ቆዳ ወጥረን “መዘነጥ” ጀመርን፡፡ ሱሪያቸውን ከመቀመጫቸው ዝቅ አድርገው ሲሄዱም እንደነሱ ለመሰልጠን ሱሪያችንን ተጭናችን አስረን መዥገር እንደ ጠፈገጋት ላም እየተሽመደመድን መጓዝ ጀመርን፡፡ የቅድመ አያቶቻችንን የፍልስፍናና የቅኔ ሥልጣኔ ወርውረን የምእራቡን የራዲዮና የቴለቪዝን መርሐ ግብር እንደ ጦጣዋ አንድ በአንድ እየኮረጅን በራሳችን የፈጠራ ችሎታ አፈር መለስን፡፡ የአመዝራነት ሲኒማ ሲያሳዩ፣ እኛም እንደ ጦጣዋ ኮርጅን የአመንዝራነት ድራማ ማዥጎድጎዱን ጀመርን፡፡
ዓለም መጣፍ ከመጀመሩ በፊት የተፈጠረውን፣ አናባቢን ከተነባቢው አዋህዶ የያዘውን፣ ጊዜና ሥፍራ ቆጣቢውን፣ ለሰምና ወርቅ ግጥም አመቺውን፣ ለቅኔና ፍልስፍና ተስማሚውን የረቀቀ ፊደል ጠልተን የባዕዳን ፊደል ከወደ ምዕራብ ቀላወጥን፡፡ እምነትን፣ ፍልስፍናን፣ የጊዜ ቀመርን፣ ባህልንና ታሪክን አምቆ የያዘውን የጊዜና የዘመን አቆጣጠር አጥፍተን የቅኝ ገዥዎችን ለመረጠብ ፈርስ እንደ ሸተተው ጅብ በማነፍነፍ ላይ ነን፡፡
አብዛኛው የዓለም ሕዝብ በአሕዛብነት በሚኖርበት ዘመን ኦሪትን ስንከተል ነቢዩ ኢሳያስን “እንሆ ድንግልም ትፀንሳለች ወንድ ልጅም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ትለዋለች” ምዕ ፯፡፲፬ ሲል የተነበየውን ተከትለን፣ የኢሳያስን ትንቢት ሲያነብ ፊሊጶስ ያገኘውን የኢትዮጵያውን ጃንደረባ ምስክርነት አምነን፤ ሥራ ፰፡ ፳፮ ፣ ክርስቶስ ሕግና ሥርዓትን ልቀይር አልመጣሁም ልፈጽም እንጅ ማቴ ፭፡፲፯ ባለው አምነን ብሉይን ከሀዲስ ያዋሀድን የመጀመርያዎቹ የከርስቲያን አገር ሆን፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ቅኝ ገዥዎች አፍሪካን፣ ኤስያንና ላቲን አሜሪካን በባርነት ቀንበር ለመቀፍደድ ባዋቀሩት የስለላ “የሃይማኖት” ወጥመድ እየገባን ራሳችንን ጠልፈን ስንጥል እንውላለን፡፡ ህልቆ መሳፍርት የሌላቸው የሃይማኖትና የፍልስፍና ብራናዎቻችን መፈተሹን ትተን የእኛን ቅዱሳት መጻሕፍት ሰርቀው መልሰው አጣመው ሲሰብኩን ዴዝሞንት ቱቱ እንዳለሉት* አንገታችንን ደፍተን ቀና ስንል የእነሱ “መጽሐፍ ቅዱስ” ከኛ እጅ ጥንታዊ ቅርሶቻችን ከእነሱ እጅ ገብተው እናገኛቸዋለን፡፡ የቅድመ አያቶቻችንን ሃይማኖት ለማጥፋት መስቀልን፣ መጻሕፍትንና ቤተክርስትያንን እናቃጥላለን፤ ምዕመናንንም እናርዳለን፣ እናሳርዳለን፡፡
ሊቃውንት ቅድመ አያቶቻችን ስለ ሥነ-መለኮት፣ ስለ ተፈጥሮ፣ ስለ ህይወት፣ ስለ ነፍስ፣ ስለ አካል፣ ስለ እንሰሳት፣ ስለ እጸዋት፣ ስለ ምድር፣ ስለ ከዋክብት፣ ስለ ፀሐይና ስለ ጨረቃና የተፈላሰፉትንና የተቀኙት ሳንፈትሽ የራስ ቅላችንን በምዕራቡና በምስራቁ አመለካከትና ርዕዮተ ዓለም እንሞላለን፡፡ የእኛን ፈላስፋዎችና ዝቅ ያደረግን መስሎን “ደብተራ” ብለን እየተሳለቅን የደብተራን ትርጉም እንኳ የማያውቀውን የድንቁርና ገመና ፀሐይ ስናስሞቅ እንውላለን፡፡
ጥንታዊ ታሪክ ጸሐፊያንንና ነቢያት “የፍትህ ምድር” ያሏትን አገር በአደራ ተቀብለን እርቅና ሽምግልናን ገና ከባርነት ሙሉ በሙሉ ካልተላቀቁት እንደ ደቡብ አፍሪካ ታሉ አገሮች ለመረጠብ ስንለምን የማናፍር አይን አውጣዎች ሆን፡፡ ሥራ የሌለው እምነት የሞተ፣ ፍትህ የሌለው እርቅርም ቅጥፈት፣ ለሱባኤ ያላደረሰ ንስሀም ውግዘት መሆኑን ተሚያምኑና አምነውም በሥራ ካዋሉ ቅድመ አያአቶች ተወልደን ሽማግሌ እንደ ኬንያና ናይጄርያ ታሉ አገሮች የምንረጠብ የትውልድ ማፈሪያዎች ሆን፡፡
ሥሩ ተመንግሎ የወደቀ ዛፍ እንኳን ሊያቀጠቅጥ እየተፈለጠ ከእሳት ከመማገድ እንደማይድን ሁሉ እምነቱን፣ ፍልስፍናውን፣ ባህሉንና ታሪኩን ያጠፋ ሕዝብም ሊያጠፉት በሚያደቡ ጠላቶች እየተቆራረጠና እርስ በእርሱ እየተናከሰ ከመጥፋት የማይድን መሆኑን መገንዘብ አቃተን፡፡
በሃይማኖታቸው ምሰሶነት፣ በአጥንታቸው ግድግዳነት፣ በማተባቸው ማገርነት፣ በደማቸው ምርግነትና በባህላቸው ጣራነት ገንብተው የጠበቋትን አገር አፍርሰን “አዲሲቷን ኢትዮጵያን እንገነባለን” የሚል መፈክር መደንፋት ከጀምርን ውለን አደርን፡፡ በአደራ የተቀብልናትን የአምስት ሺ ዘመን እመቤት ልእዋላዊነት መጠበቅ ሳንችል አፍርሰን እንሰራታለን እያልን ስንደነፋ የሚያሳፍር ህሊና የሚገታ ልጓምም አጣን፡፡
የጎደሉንን ወይም የሌሉን የሳንይንስ ውጤቶችና ጥበባት መርምረን ከሌሎች መቅሰም አስፈላጊና ጠቃሚም ነው፡፡ ያልቸገሩንን ሃይማኖትን፣ ባህልን፣ የቀን ቀመርንና ሆሄያትን መቀላወጥ ግን ሳይቸግር ጨው የሚያስበድር የኩረጃ በሽታት ነው፡፡ ይህ የኩረጃ በሽታ አይምሯችንን እንደ ምች ስለመታው እንደ አባ የሻነው ጦጣ አንገታችንን በካራ ገዝግዘን እየጣልን ነው፡፡ አንገታችን ጨርሶ ተቀንጥሶ ሳይወድቅ ነቢዩ ኤርምያስ “እውንን ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዝንጉርጉነትን ይለውጥ ዘንድ ይቻልዋልን” ኤርም ፲፫፡ ፳፫ ያለውን በጥሞና ማሰላሰል ጠቃሚ ነው፡፡ በነቢዩ ኤርምያስ ትንቢት እንድንካተት ያደረገን ቀለማችን ብቻ ሳይሆን በዚያን ዘመን እየሩሳሌም ድረስ የዘረጋነው ሃይማኖታችን፣ ፍልስፍናችንን፣ ባህላችንንና ታሪካችን ነው፡፡ ነብር ዝንጉርጉነቱን ቀይሮ ሮዝ አሳማ ቢመስል አሳማ በይ እንደሚውጠው፣ ከአገጩ ጉቶ አብቅሎ ፍየል ቢመስልም ፍየል አራጅ ስልቅጥ እንደሚያደርገው ተገዝቦ ዝንጉርጉርነቱን ጠብቆ ተነክብሩ እየኖረ ነው፡፡ ቅድመ አያቶቻችንም ነፃነታቸውን ጠብቀው ተከብረው የኖሩት እንደ ነብሩ መልካቸውን ስላልቀየሩ ነው፡፡ ሥር በሰደደ የኩረጃ ሸቀን እየተቀየረ የመጣው የእኛ የልጅ ልጆቻቸው መልክ ነው፡፡ ይኸንን የኩረጃ ሸቀን ፈውሰን መልካችንን ጠብቀን መኖር የመጽሐፉ ቃል ሲሆን የመልካምድርና የመንፈስ ሉአላዊነታችንን አስከብረን እንደ ነብር በክብር መኖርም የአባቶቻችን የአደራ ቃል ነው፡፡ የአደራ ቃልን መጠበቅም ሰውነት፣ እምነት፣ ማተብ፣ በረከትና ፀጋ ነው፡፡ አመሰግናለሁ፡፡
*When the missionaries came to Africa, they had the bible and we had the land. They said “Let us pray” we closed our eyes. When we opened them, we had the bible and they had the land” Desmond Tutu.
ተመሳሳይ ጦማሮች (All lastl accessed in July, 2026)
- ወጣትሆይ ለህልውናህም ሆነ ለክብርህ ወደ ባህልህ፡-https://deregenegash.wordpress.com/2019/04/14/%E1%8B%88%E1%8C%A3%E1%89%B5-%E1%88%86%E1%8B%AD-%E1%88%88%E1%88%85%E1%88%8D%E1%8B%8D%E1%8A%93%E1%88%85%E1%88%9D-%E1%88%86%E1%8A%90-%E1%88%88%E1%8A%AD%E1%89%A5%E1%88%AD%E1%88%85-%E1%8B%88%E1%8B%B0/
- ፍትህየሌልው እርቅ የሞተ ነው፡- https://amharic.borkena.com/2022/11/12/%E1%8D%8D%E1%89%B5%E1%88%85-%E1%8B%A8%E1%88%8C%E1%88%88%E1%8B%8D-%E1%8A%A5%E1%88%AD%E1%89%85-%E1%8A%A0%E1%88%81%E1%8A%95%E1%88%9D-%E1%8B%A8%E1%88%9E%E1%89%B0-%E1%8A%90%E1%8B%8D/
- ፍትህ የሌለው እርቅ ሥራ እንደሌለው እምነት የሞተ ነው!https://ethiopanorama.com/?p=63327
- በወይፈኑ መልስ፡- https://ethiopanorama.com/?p=86154
- መነኩሴ ዓለምን ታፈቀረ ጭድ እሳት ዳር ከተከመረ! https://amharic.borkena.com/2024/03/16/%E1%88%98%E1%8A%90%E1%8A%A9%E1%88%B4-%E1%8B%93%E1%88%88%E1%88%9D%E1%8A%95-%E1%89%B3%E1%8D%88%E1%89%80%E1%88%A8-%E1%8C%AD%E1%8B%B5-%E1%8A%A5%E1%88%B3%E1%89%B5-%E1%8B%B3%E1%88%AD-%E1%8A%A8%E1%89%B0/
- “ወጣት ተመልከት እንዳትሳሳት https://ethiopanorama.com/?p=73623
- የባህልና የእምነት ጣራ ሲያፈስ ክህደት፣ ቅጥፈንትና ሌብነት እንደ ዶፍ ሳያቋርጥ ይወርዳል! https://amharic.borkena.com/2022/09/24/%E1%8B%A8%E1%89%A3%E1%88%85%E1%88%8D%E1%8A%93-%E1%8B%A8%E1%8A%A5%E1%88%9D%E1%8A%90%E1%89%B5-%E1%8C%A3%E1%88%AB-%E1%88%B2%E1%8B%AB%E1%8D%88%E1%88%B5-%E1%8A%AD%E1%88%85%E1%8B%B0%E1%89%B5%E1%8D%A3/
- The Best Predictor of Future Behavior is Past Behavior: https://borkena.com/2023/02/16/ethiopia-the-best-predictor-of-future-behavior-is-past-behavior/
ሐምሌ ሁለት ሺ አስራ ስምንት ዓ.ም.