አዳምን ሄዋንን ከእግዚአብሔር ሲለዩ፣
የቋንቋ የጎሳ በለስ እያስጋጡ፣
ጋብቻ ሲያፈርሱ ጎረቢት ሲያጣሉ፣
አሳባቂ እባብን ሰይጣንን አስናቁ፡፡
የብሉይ የሀዲስ ውህደትን ሲንዱ፣
ማተብን ተመስቀል ቆርጠው ሲያለያዩ፣
እምነትን ከሥራ አጣልተው ሲያፋቱ፣
አምላክን ተከዳው ተሳጥናኤል ባሱ።
አገር እንደ ሽንኩርት በቋንቋ ሲከትፉ፣
ፊደልን ተረጥበው ልሳን ሲለያዩ፣
ሕዝብን እርስ በርሱ በጥርስ ሲያናክሱ፣
የክፋትን አባት ቆሪጥን አስናቁ!
ኢየሱስን አስረው በርባንን ሲፈቱ፣
በመንደር ሰፈሩ ዘራፊ ሲለቁ፣
ወላዲት አምላክን በምር ሲያስለቅሱ፣
ከፈሪሳውያንም ከጲላጦስ ከፉ፡፡
ሕግና ሥርዓትን ስብእናን ሲያጠፉ፣
ክህደትን፣ ቅጥፈትን፣ ውሸትን ሲዘሩ፣
ሙስና ዘረፋ ሌብነት ሲያስፋፉ፣
ክንፍ ታለው ሳጥናኤል የፈጠኑ ሆኑ፡፡
በህጻን አዛውንት በእርጉዝ ሲጨክኑ፣
ዓይን በጦር ሲያስወጡ በድን ሲያስጎትቱ፣
የአምልኮትን ሥፍራ አማኙን ሲያጋዩ፣
ከሰዶም ገሞራ እሳት ቛያም ከፉ፡፡
የእግዚአብሔርን ሰዎች እግር እየነቀሉ፣
ከቤት ንብረታቸው እያፈናቀሉ፣
ዳግም ዘጽአትን በኦሪት ሲያጽፉ፣
ዘንዶን ታመለከው ተፈርኦን ባሱ፡፡
እንደ ሄሮድስ ሂትለር ነገ እነሱም ሊያልፉ፣
ምስጥ ሊያነክታቸው አፈሩን ሲለብሱ፣
እምነትን ታሪክን ባህልን አጠፉ፣
አገር ቆራረጡ ደምን አፋሰሱ፣
ዘር እያበጠሩ ሰውን አሳደዱ፣
ታሪክ ከትብ መዝግብ ከሳጥናኤል ከፉ፡፡
በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)
ግንቦት ሁለት ሺ አስራ ስምንት ዓ.ም.