የህወሃትና የአቢይ አህመድ አገዛዝ፣ ሁለቱም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ፕሮጀክቶች መሆናቸውን ያለመገንዘቡ አደገኛነት!
ፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር)
ሚያዚያ 18፣ 2018( April 26, 2026)
ይህ ፀሀፊ ወያኔ ስልጣን ላይ እንዴት እንደወጣና፣ ስልጣንንም ከጨበጠ በኋላ የማንን አጀንዳ ተግባራዊ ያደርግ እንደነበር በየጊዜው በሰፊው አትቷል። የህወሃት አገዛዝ ስልጣን ላይ በቆየበት 27 ዓመታት ያህል ተግባራዊ ያደረጋቸው የጎሳ ፌዴራሊዝምና የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ በምንም ዐይነት የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ወይም ደግሞ ጥቅምን ሊያገኙ ይችላሉ፣ በዚያው መጠንም መብታቸውና ነፃነታቸው ይጠበቃል የተባሉት የተለያዩ ብሄረሰቦች አጀንዳዎች ሳይሆኑ፣ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና የግብረአበሮቹ እንደሆኑ ሳይታክተኝ በተደጋጋሚ በማቅረብ እንዲነበብ ለማድረግ ሞክሬያለሁ። ይሁንና አብዛኛው አንባቢ በተለይም ደግሞ ምሁራን ነን ባዮች ይህንን የመሰለውን በሳይንስና በሎጂክ የተደገፈውን ጽሁፌንና፣ ክሪቲካል አመለካከት ያላቸው አብዛኛዎቹ ምሁራን የሚጋሩትን አስተሳሰቤን አላዳምጥም በማለት ቀድሞ ህወሃት፣ ባለፉት ስምንት ዓመታት ደግሞ በአቢይ አህመድ የሚመራው የብልፅግና አገዛዝ ተብዬው በራሳቸው ህሊናና ዕውቀት ይመሩ ይመስል ጽሁፌን ለማጥላላት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። አንዳንዶችም ስሜን በሚዲያ በመጥቀስና በማንቋሸሽ በኢትዮጵያ ምድር ከሚታየውና ህዝባችን የሚኖርበትን ተጨባጭ ሁኔታ ለማሳየት የሞከረውን የቲዎሪና የኢምፔሪካል አቀራረቤን ተቀባይነት እንደሌለው ለማመልከት ሞክረዋል። ጥቂቶችም ይህ „ግለሰብ ጨቅላ በሆነ ጭንቅላት በመመራት ነው” እንደነ ዶ/ር ኢሌኒ ገ/መድህን የመሳሰሉትን ታላላቅ ምሁራን፣ የቀድሞው የመለሰ ዜናዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካሪ የነበረችውን ያጥላላት በማለት ወንጅለውኛል። ይሁንና እንደዚህ ብለው የወነጀሉኝ የፕሮፈሰር ማዕረግነት ያንጠለጠሉ ምሁራን ነን ባዮች ኢሌኒ ገብረ መድህን በዎል-ስትሪት እንደተላከችና የወያኔና የዎል-ስትሪትን ሰዎች ጥቅም ታስጠብቅ እንደነበር በፍጹም የተረዱ አይመስልም። ይህ ብቻ ሳይሆን እነዚህ ምሁራን ያልገባቸው ነገር ኢሌኒ ገ/መድህን ንጹህ በንጹህ በገበያ ኢኮኖሚ ስም የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ አጀንዳን የምታራምድና፣ ይህ ዐይነት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ብለው የሚጠሩት ደግሞ በምንም ዐይነት ድህነትን ሊቀርፍ እንደማይችልና፣ ከረዥም ጊዜ አንፃርም ኋላ-ቀርነትን እንዳለ በማስወገድ ኢትዮጵያን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት ሊያደርጋት እንደማይችል ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ እነዚህ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ የያዙ ኢኮኖሚስት ነን የሚሉ ምሁራን ያልገባቸው ነገር በኢኮኖሚ ታሪክ ውስጥ፣ ወይም ኢኮኖሚ ራሱን የቻለ ዘርፍ ሆኖ መዳበር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በህብረተሰብ ግንባታ ታሪክ ውስጥ ልዩ ልዩ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች እንደዳበሩና ተግባራዊም ለመሆን እንደቻሉ በፍጹም አልገባቸውም። በግልጽ እንደሚታወቀው እስከ 20ኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ ንጹህ በንጹህ የገበያ ኢኮኖሚ ተግባራዊ እንዳልተደረገ የካፒታሊስት አገሮች ታሪክ በሚገባ ያረጋግጣል። ይህም ማለት የገበያ ኢኮኖሚ እየተባለ የሚቆላመጠው የኢኮኖሚ ክንውን ካለመንግስት ጣልቃ-ገብነት፣ ከዚያም በላይ ካለሳይንስና ቴክኖሎጂ ራሱ ብቻውን ተግባራዊ ሊሆን እንደማይችል የተረጋገጠ ጉዳይ ነው። ሳይንስንና ቴክኖሎጂን የፈጠሩት ምሁራን ደግሞ ለራሳቸው ጥቅም በማሰብ ሳይሆን በግለሰብ ተነሳሽነት የሰውን ልጅ ከጨለማ ስርዓት ለማውጣት በማሰብ ብቻ ነው። አብዛናው ሳይንቲስቶችም ምንም ጥቀሜታ ሳያገኙ ነው በተለይም አንዳንዶቹ በድህነት ተሰቃይተው የሞቱት። ይህም ማለት ለገበያ ኢኮኖሚ መተግበር የግዴታ የማምረቻ መሳሪያዎች፣ ወይም በቴክኖሎጂ የዳበሩ ማሽኖች መኖር አለባቸው። ይህንን ሊያደርግ ወይም ሊያቀርብ የሚችል ደግሞ ግለሰብ ካፒታሊስቶች ሳይሆኑ በተቋም ደረጃ በመንግስት ድጋፍ አማካይነት የሳይንስና የቴክኖሎጂ የዕድገት ምርምር(Development and Research) ሲደረግና ሲደጎምም ብቻ ነው። ይህ ከመሆኑ በፊትና ካለመንግስት የተቀነባበረ ድጋፍ የካፒታሊስት ኢኮኖሚ በፍጹም ተግባራዊ ሊሆን አይችልም። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ የተሟላ ዕድገት ብቻ ነው የአገር ውስጥ ገበያ ሊያድግ የሚችለውና፣ በዚያው መጠንም የስራ መስክ ለሚፈልገው የስራ ዕድል በመስጠት ብሄራዊ ሀብት(National Wealth) ለማዳበር የሚቻለው። ይህም ማለት ለገበያ ኢኮኖሚ በተሟላ መልክ መዳበር የግዴታ በምርት(Production)፣ ክፍፍልና(Income Distribution) የፍጆታ አጠቃቀም(Consumption) መሀከል የጠበቀ ግኑኝነት መኖር አለበት ማለት ነው። በአንፃሩ የዎል-ስትሪት ተጠሪ የነበረችው ኤሊኒ ገ/መድህን፣ የዓለም የገንዘብ ድርጅትና(IMF) የዓለም ባንክ(World Bank) ስለገበያ ኢኮኖሚ በሚያወሩበት ጊዜ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ በሚደገፍና በአገር ደረጃ በተቀላጠፈ ተቋም ላይ በመመርኮዝና ዕርዳታ በማግኘት ሰለሚንቀሳቀስና በተከታታይነት ስለሚያድግ ኢኮኖሚ ሳይሆን ስለ ሸቀጣ ሸቀጥ ኢኮኖሚ ወይም በተዝረከረከ መልክ ስለሚካሄድ የንግድ እንቅስቃሴ ብቻ ነው። በሌላ አነጋገር ኢሌኒ ገ/መድህንም ሆኑ የዓለም የገንዘብ ድርጅትና(IMF) የዓለም ባንክ ካፒታሊዝም በምን ምልክ ከታሪክ አንፃር በክንዋኔ መልክ እያደገና እየተስፋፋ እንደመጣ የሚያውቁት ነገር የለም። በየዩኒቨርሲቲዎችም ውስጥ የእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በፍጹም አይታወቅም፤ በትምህርት መልክም አይሰጥምም። ስለሆነም ኢሌኒ ገ/መድህንን በማወደስ እኔን ሲያንቋሽሹኝ የነበሩት ኢትዮጵያውያን ኢኮኖሚስቶች የካፒታሊስት ኢኮኖሚ ከታሪክ አንፃር ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ እንዴት ተግባራዊ ለመሆን እንደቻለ የሚያውቁት ምንም ነገር የለም። ብቻ ትዕቢት በተሞላበት መንፈሳቸው በግልጽ ተሳድበዋል።
ለማንኛውም የመለሰ ዜናዊ አገዛዝ ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላና፣ እሱም ከሞተ በኋላ በኃይለማርያም ደሳለኝ፣ በኋላ ላይ ደግሞ በአቢይ አህመድ ከተተካ በኋላ ሶስቱም ጠ/ሚኒስተሮች ተግባራዊ ያደረጉት የኢኮኖሚ ፖሊሲ በምንመረምርበት ጊዜ የኢትዮጵያን ህዝብ ከድህነትና ከኋላ-ቀርነት በፍጹም ያላቀቀ ሳይሆን የባሰ ደሀና በኑሮው እንዲቀጭጭ ለማድረግ የበቃ ነው። እነዚህም የተለያዩት ጠ/ሚኒስተሮች ስልጣን ላይ ከመቀመጥ በስተቀርና ትዕዛዝ በመቀበል የውጭ ኃይሎችን አጀንዳ ተግባራዊ ከማድረግ በስተቀር ስለ ኢኮኖሚ ቲዎሪና ስለ ኢኮኖሚ ሳይንስ፣ እንዲሁም አንድን አገር በተሟላ መልክ ስለመገንባት ጉዳይ ምን ምን ነገሮች በቅደም ተከል መተግበር እንዳለባቸው ምንም የሚያውቁት ነገር የለም። ይህ ብቻ ሳይሆን ስለ ኢኮኖሚ በሚወራበት ጊዜ በቀጥታ ከሰው ልጅ ህይወት ጋር የተያያዘ መሆኑን የሚገነዘቡ አይደሉም። በሌላ አነጋገር፣ ሰለ ኢኮኖሚ በሚወራበት ጊዜ፣ በተለይም እንደኛ ባለ አገር ውስጥ ለማንኛውም ሰው የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ነገሮች(Basic Needs) መሟላት እንዳለባቸው በሚገባ መረዳት ያስፈልጋል። የሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎቶችም ማለት. 1ኛ) የተሟላ ዲዬት ወይም ምግብ፣ 2ኛ) ንፁህ ወሀ፣ 3ኛ) መጠለያ ወይም ቤት፣ 4ኛ) ህክምና፣ 5ኛ) መሰረተ ትምህርትና ሌሎችም ነገሮች እንደመሰረታዊ ፍላጎቶች መታየት አለባቸው። የሚያሳዝነው ነገር በዓመት በብዙ መቶ ሺሆች ዶላር ደሞዝ የሚያገኙት የዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ ኤክስፐርቶች ሰለዚህ ነገሮች መሟላት አስፈላጊነት የሚያውቁት ምንም ነገር የለም፤፡ወይም ደግሞ በፍጹም ደናት የላቸውም። አንድ ሰው በላ አልበላ ጉዳያቸውም አይደለም። ብቻ እንደኛ አገር የመሳሰሉትን ባለስልጣናት በነፃ ገበያ ስም በማታለል ድህነትንና ኋላ.-ቀርነትን ያስፋፋሉ። ከ1945 ዓ.ም በኋላም የተፈጠረው በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የሚመራው አዲሱ የዓለም ስርዓት በዓለም አቀፍ ደረጃ ኋላ-ቀርነትንና ድህነትን ማስፋፋት ነው። ድህነትንና ኋላ-ቀርነትን እንደኛ በመሰለው አገር ውስጥ ለማስፋፋትና ለማጠንከር የመንግስትን መኪና በሚሊታሪ፣ በፀጥታ ኃይል፣ በፖሊስ፣ በቴክኖክትራቶችና በቢሮክራቶች በማደለብ በአንድ አገር ውስጥ ያልተስተካከልና ሀብትን የሚያዘርፍ ሁኔታ መፍጠር አለበት። በዚያው መጠንም በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠርን በአምላክ ምስል የተፈጠረን ህዝብ አቅመ ቢስ ማድረግ ይችላል። ይህ ዐይነቱን ስርዓተ-አልበኝነትን የሚያስፋፋ፣ የእግዚአብሄርንና የተፈጥሮን ህግ የሚጥሰውን የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ብለው ይጠሩታል። ይህንን ዐይነቱን ሰይጣናዊ ድርጊትን የሚያስፋፋ የውጭ ኃይልን ታላቅ ኃይል ብለው ያሞግሱታል።
በተከታታይ ጽሁፌ ለማሳየት እንደሞከርኩት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት፣ ማለትም ከ1945 ዓ.ም በኋላ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በኢኮኖሚ.፣ በፖለቲካና በሚሊታሪ የበላይነትን ከተቀዳጀበትና፣ ኃያል መሆኑን ማስመስከር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያም ሆነ፣ በተቀሩት የሶስተኛው ዓለም አገሮች፣ በተለይም በደቡብና በማዕከለኛው የአሜሪካ አገሮች የተቋቋሙት አገዛዞች ወይም መንግስታት በሙሉ እያንዳንዱን አገር በተሟላ መልክ ለማሳደግ ሲባል ከታች ወደ ላይ መወሰድ ያለባቸው መሰረታዊ ነገሮች እንዳይተገበሩ እንቅፋት መፍጠር ነው። በዚህ መልክ የመንግስታትን መኪናዎችንና የሚቆጣጠሩትን ሰዎች ፋሺሽቶች በማድረግ በአንድ አገር ውስጥ የሚያስፈራ ወይም ጨቋኝ ስርዓት መፍጠር ነው። ጆን ጋልቱን የሚባለው የስዊድኑ የሶስዮሎጂ መምህር Imperialism and Structural Power በሚለው ግሩም መጽሀፉ ለማረጋገጥ ችሏል።፡እሱ ብቻ ሳይሆን እነ ሳሚር አሚንና አንድሬ ጉንደር ፍራንክ የተባሉት ታላላቅ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ተመራማሪዎችና ሌሎችም የአሜሪካን ምሁራን በሚገባ መልክ አሳይተዋል። በተለይም በስድሳዎቹና በሰባዎቹ ዐመታት በ20ኛው ክፍለ-ዘመን ሰለ ዕድገትና ስለ ፀረ-ዕድገት ወይም ስላልተስተካከለ ዕድገት(Unequal Development) የጦፈ ክርክር በሚደረግበት ዘመን የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ግብረ-አበሮቹ በሚቆጣጠሯቸው ዓለም አቀፋዊ ተቋማት አማካይነት እንደኛ ባለው አገር ውስጥ ሁለ-ገብ የሆነና ድህነትንና ኋላ-ቀርነትን ለአንዴም ለመጨረሻ ጊዜ የሚያስወግድ ሳይንሳዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ እንዳይሆን ልዩ ልዩ ልዩ መሰናክሎችን እንደፈጠሩ በሰፊውና በጥልቅተ ለማብራራት ተችሏል።
ከዚሁ ሁኔታ በመነሳት እንዴት በመለሰ ዜናዊ የሚመራው ህወሃት፣ ቀጥሎ ደግሞ አቢይ አህመድ ስልጣን ላይ እንደወጡ እንመልከት። ህወሃት በ1978 ዓ.ም ሲመሰረት የአልባኒያውን የሶሻሊስት መንገድ ተግባራዊ አደርጋለሁ በማለት ነው የተመሰረተው። ይህም ማለት የማርክሲስት ሌኒኒስት ድርጅት ነኝ በማለት ነው የተመሰረተው። በሌላ ወገን ደግሞ የማርክሲዝምን ሌሊኒዝምን መሰረተ-ሃሳብ በመቀበል የተቋቋመ ድርጅት ቢያስመስለውም የትግራይን ብሄረሰብ መብት አስከብራለሁ ብሎ የሚንቀሳቀስና፣ ብሄራዊ አጀንዳ ካላቸው በጊዜው የግራ አመካከት አለን ከሚሉ ጋር ለመተባበር የማይፈልግ ነበር። ይህም ማለት አስተሳሰቡ ጠባብና በመሰረቱ የማርክሲዝምን መሰረተ አስተሳሰብ የሚፃረር ነበር። ማርክስ እንደሚለው በዓለም ላይ ያላችሁ ወዝአደሮች በሙሉ ተባበሩና ሶሽሊስታዊ ስርዓትን በየአገሮቻችሁ ውስጥ መስርቱ ነው። በሌላ ወገን ግን ለማርክስና ለኤንግልስ ሶሻሊስታዊ ስርዓትን በአንድ አገር ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ የግዴታ ሳይንስና ቴክኖሎጂ በከፍተኛ ደረጃ ማደግ አለባቸው። በሌላ አነጋገር፣ የምርት የማምረቻ መሳሪያዎች ወይም ኃይሎች(Productive Forces) በከፍተኛ ደረጃ መበልፀግ ወይም መዳበር አለባቸው። በሁለተኛ ደረጃ፣ የሰፊው ህዝብ፣ በተለይም የወዝአደሩ ንቃተ-ህሊና በከፍተኛ ደረጃ ማደግ አለበት። በማርክስና በኤንግልስ አስተሳሰብ መሰረት የሶሻሊዝምን ስርዓት ከላይ ወደ ታች በሰው ላይ በመጫን ተግባራዊ የሚሆን ሳይሆን በሰፊው ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው ያስፈልጋል። ከዚህ ሁኔታ ስንነሳና ማርክስም እንደሚያስተምረን አንድ በምርት ኃሎችም ሆነ በንቃተ-ህሊና ባልዳበረ ህብረተሰብ ውስጥ የሶሻሊስት ስርዓትን ተግባራዊ ማድረግ በፍጹም አይቻልም። አሁንም በሌላ አነጋገር፣ በአብዛኛው መልኩ በእርሻ በሚተዳደር፣ ወይም ከእጅ ወደ አፍ በሚተገበር ኢኮኖሚ(Subsistence Economy) ውስጥ የሶሻሊስት ስርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ በፍጹም አይቻልም። እነ መለሰ ዜናዊ ማርክሲዝምን እንደመመሪያ አድርገው ሲቀበሉ ይህንን በፍጹም አልተረዱም፤ ወይም ደግሞ በፍጹም አላነበቡም። አንብበዋል ቢባል እንኳ የብሄረሰብን አርማ ይዘው መነሳታቸውና የተከተሉትም የጦርነት ትግል ሙሉ በሙሉ የማርክሲዝምን አስተሳሰብ የሚፃረር ነው። ምክንያቱም በማርክስ አስተሳሰብ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የግዴታ በከፍተኛ ደረጃ የጭንቅላት ስራ ማካሄድ ያስፈልጋል፤ በበቂው ማንበብና መገንዘብ ያስፈልጋል። በሌላ አነጋገር በመሳሪያ ላይ የተደገፈ ትግል የሚሉት ነገር የመጨረሻ መጨረሻ በአንድ አገር ውስጥ በሳይንስና በቴክሎጂ ላይ የተመሰረት ሁለ-ገብ ኢኮኖሚ እንዳይተገበር እንቅፋት ይሆናል ማለት ነው። ስለሆነም ነው እነመለሰ ዜናዊ ከውስጥ ሆኖ የሚቀናቀናቸውን ሁሉ ወይም የእነሱን አስተሳሰብ አልቀበልም ያለውንና ቀና አመለካከት ያለውን የትግራይ ተወላጅ እየመነጠሩ ያስወገዱት፣ ወይም የገደሏቸው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ድርጅታቸው ፀረ-ሴት የነበረና፣ አንዳንድ ግለሰቦች በወጣት ሴቶች ላይ ይፈፅሙ የነበረው ወንጀል በጣም ለጆሮ የሚዘገንን ነበር። እነዚህ ወንጀለኞች ናቸው የኋላ ኋላ ላይ ስልጣን ላይ ለመውጣት የቻሉትና አገርንም ለማፈራረስ የበቁት። በማስረጃም እንደተረጋገጠው የህወሃት፣ ወይም የወያኔ ካድሬዎች አንዳንድ የደርግን መኮንኖችን ጠለላ በማድረግና ስርገው በመግባት በቀይና በነጭ ሽብር የርስ በርስ ጦርነት ዘመን በተለይም ተራማጅ የሚባሉትን ኃይሎችን እንደጨረሱ ይታወቃል። አንዳዶችም የሲአይኤ መሳሪያ በመሆን ግድያውን እንዳጧጧፉት ይታወቃል። በሌላ አነጋገር፣ የአሜሪካኑ የስለላ ድርጅት በአብዮት ውስጥ ሰርገው የገቡትን የወያኔ ካድሬዎችንና የአንዳንድ የማርክሲዝምን ካባ ለብሰው ይንቀሳቀሱ የነበሩትንና የአመራር ቦታ የያዙትን በመጠቀም ነው የቀይና የነጭ ሽብር ግድያ እንዲጧጧፍ ለማድረግ የበቃው።
ይህ ዐይነቱ ድርጅት ነው የኋላ ኋላ ላይ በአሜሪካን ጉያ ስር በመውደቅና በሲአይኤ በመመከር በአጠቃላይ ሲታይ በህዝባችንና በታሪካችን ላይ ጦርነትን ለማወጅ የበቃው። ይህም የሚያረጋግጠው እነመለስ ዜናዊ ለይስሙላ የማርክሲዝምን ርዕዮተ-ዓለም ተቀበልን ቢሉም በመሰረቱ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም አንድን ጥንታዊ አገር የማውደም ፕሮጀክቶች ናቸው ማለት ይቻላል። ስለሆነም ስልጣን ላይ ሲወጡ የከፋፍለህ ግዛውን የጎሳ ፌዴራሊዝምን ፖሊሲ ነው ተግባራዊ ማድረግ የጀመሩት። ይህም ቢሆን የአሜሪካንና የእንግሊዝ ኢምፔሪያሊዝም የከፋፍለህ ግዛው ፖሊሲ ነው። ይህ ዐይነቱ ፖሊሲ ደግሞ እራሱን የምዕራቡን ካፒታሊዝም የሪፓብሊካንና የግለሰብአዊ ነፃነት፣ እንዲያም ሲል የህግ የበላይነት የሚባለውን መርሆ እንዳለ የሚፃረር ነው። ካፒታሊዝም የኋላ ኋላ ላይ ሙሉ በሙሉ እንደ ስልተ-ምርት(Mode of Production) ተግባራዊ መሆን የቻለው በፊዩዳል ስርዓት ዘመን የነበረውን ዲስፖታዊ ወይም የአንድ ግለሰብ ፈላጭ ቆራጭነትን በመፃረርና በመጣልም ነው። በእኛ አገር የጎሳ ፌዴራሊዝም ተግባራዊ እንዲሆን ጫና ያደረጉት የአሜሪካንና የእንግሊዝ ኢምፔሪያሊዝም ለኢትዮጵያ ህዝብና ለተሟላ ዕድገቱ ቢያስቡ ወይም ቢጨነቁ ኖሮ የጎሳ ፌዴራሊዝም በአገራችን ምድር ተግባራዊ እንዲሆን ጫና ባላደረጉ ነበር። በሌላ አነጋገር፣ የአሜሪካንና የእንግሊዝ ኢምፔሪያሊዝም ዋና ዓላማ እርስ በርሱ የሚጠራጠርና የሚበላላ ህብረተሰብ በመፍጠር ወደ ውስጥ ያተኮረ በሳይንስና በቴኮኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የካፒታሊስት ኢኮኖሚ እንዳይገነባ ማድረግ ነው። በእርግጥም እንዳየነው ይህ ዐይነቱ የጎሳ ፌዴራሊዝም የህወሃትን አምባገነናዊና የከፋፍለህ ግዛው ስርዓት ያጠናከረና በዚያው መጠንም የፕላንቴሽን ኢኮኖሚ እንዲስፋፋ ያደረገ ነው። በዚያው መጠንም የጥሬ-ሀብት ዘረፋ እንዲካሄድ በማድረግ በየክልሉ ያሉትን የየብሄረሰቦች ተወካዮች ነን የሚሉትን ግለሰቦች ያደለበ ነው። በመሰረቱ ይህ ዐይነቱ የጎሳ ፌዴራሊዝም በየክልሉ ለሚኖረው ብሄረሰብ ዕውነተኛ ነፃነትን አላጎናፀፈውም። በየክልሉም ውስጥ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ለገበያ ኢኮኖሚ መዳበር የሚያገለግል በስራ ክፍፍል ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በፍጹም ተግባራዊ ለመሆን አልቻለም። ይህም ማለት በአሜሪካንና በእንግሊዝ ኢምፔሪያሊዝም የሚደገፈው የጎሳ ፌዴራሊዝም ዋና ዓላማው ለየብሄረሰቦች የተሟላ ነፃነትን ለማጎናፀፍና ብቃትነት ያለው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለማዳበር ሳይሆን እርስ በእርሱ የሚጠራጠር ህብረተሰብ በመፈጠር በዘለዓለማዊ ውዝግብ ውስጥ እንዲኖር ማድረግ ነው። ይህ ዐይነቱ ሰይጣናዊ ፖለቲካ እንግሊዝና ፈረንሳይ አንዳንድ የአፍሪካ አገሮችን የቅኝ ግዛቶቻቸው ሲያደርጉ ህዝቡን በጎሳና በሃይማኖት በመከፋፈል ጠንካራ ማህበረሰብ እንዳይመሰርት ያደረጉት ተቀጥያ ተግባር ነው። በዛሬው ወቅትም በዓለም አቀፍ ደረጃ የዓለምን ማህበረሰብ በወዳጅና በጠላት በመከፋፈል፣ የእኔን አስተሳስብ ያለተከተለና የእኔ ጭራ ያልሆነ ጠላቴ ነው በማለት ሁለት ጎረቤት አገሮችን ወይም ወንድማማችና እህትማማች ህዝቦችን እንዲጠላሉና፣ እንዲያም ሲል ጦር ተማዘው እንዲገዳደሉ የሚያደረግ የአሻጥር ፖለቲካ ነው። የአሜሪካንና የእንግሊዝ ኢምፔሪያሊዝም ከዚህ አልፈው በመሄድና አገራችንና ህዝባችንን በመናቅ በተለይም ህወሃት ከስልጣን ላይ ከተገለለና ትግራይ ውስጥ ከመሸገ በኋላ የህወሃት ጠበቃ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። ህወሃት ጦርነት ከፍቶ ለጊዜው ከተዳከመ በኋላ እንዲያንሰራራ ያደረጉት በሱዳን በኩል የጦር መሳሪያ በማቀበል ነው። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ምድር አንድ ነገር ይከሰታል ብለው በማሰብ እያደራጁትና እያስታጠቁት ነው። ስለሆነም ሁላችንም መገንዘብ ያለብን ጉዳይ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በምንም ዐይነት የኢትዮጵያ ህዝብ አጋር ሊሆን አይችልም። የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ህወሃትን በማጠናከሩና በጦርነት እንዲገፋ ማድረግ የትግራይ ህዝብም በፍጹም ተጠቃሚ የሚያደርገው ሊሆን አይችልም። ጦርነቱ እንዲቀጥል በማድረግ በዘለዓለማዊ ፍዳ ውስጥ እንዲኖር ያደርገዋል እንጂ። ባጭሩ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ከእዚህ ዐይነት ከመሰለው ፋሺሽታዊና አሸባሪ ድርጅት ጎን መሰለፉ የሚያስደንቅ ሊሆን አይችልም። እራሱ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም እስካሁን ድረስ በኃያልነት ለመቆየት የቻለው አገሮችን በማከረባበትና በዓለም አቀፍ ደረጃም ጦርነትን በማካሄድ ስለሆነ በእዚህ ዐይነቱ ሰይጣናዊ ስራው ይገፋበታል። ስለዚህ ማንኛውም ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ጎን የቆመና እሱን የሚለማመጥ፣ እንዲያም ሲል በኢትዮጵያ ህዝብ ስም የሚነግድ ኢትዮጵያዊ ኃይል መኮነንና መገለልም ያለበት ነው።
ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ የእኛ አገር ምሁራን፣ በተለይም በውጭ አገር በመኖር የአሜሪካን ኢምፔሪሊዝም አፍቃሪና አሽከር የሆኑት ግለሰቦች ይህ ዐይነቱ የአሻጥርና የአገር አፍራሽ ፖለቲካ ለምን እንደማይታያቸው ነው። የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና ግብረአበሮቹ በግልጽ የዓለምን ህዝብ በሚያተራምሱበት ጊዜና፣ እኔ የምለውን ያልተቀበለ ጦርነት እናውጅበታለን በማለት አንድን አገር እንዳለ በቦምብ እየደበደቡና ንፁሃን ህዝቦችን በመግደል ማንነታቸውን እያረጋገጡልን ባሉበት ወቅት ይህ ዐይነት ግልጽ ወንጀላቸው ለእኛ ኢትዮጵያውያን ምሁራን ለምን እንደማይታያቸው ግራ የሚያጋባ ነገር ነው። በሌላ ወገን ደግሞ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም አፍቃሪና አሽከር ከሆኑ ለምን እጃቸውን አጣጥፈው አይቀመጡም። ለምን የኢትዮጵያ ነገር ያገባናል እያሉ ምንም ዕውቀት የሌላቸውንና የዓለም ፖለቲካ የሚባለውን የወንበዴዎች ፖለቲካ የማይገባውን ምስኪኑን ኢትዮጵያዊ ያሳስቱታል። እነዚህ በGlobal Alliance for the Rights of Ethiopians (GARE) በሚል ስር የተሳበሰቡት አሳሳች ግለሰቦች እንደ አክሎግ ቢራራ፣ መስፍን መኮንን፣ መስፍን ተገኑና፣ በኒዎርክ ከተማ የምትኖርና ከሚገባው በላይ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም አፍቃሪ የሆነችና ግራ የተጋባች ፅጌረዳ ሙሉጌታ የምትባል ሴት፣ ሌሎችም በአሜሪካን ኢትዮጵያውያን ፐብሊክ አፌርስ ኮሚቴ( The American Ethiopian Public Affairs Commitee( AEPAC) እና ከስሩ የተጠቃለሉት ወደ ሰባት የሚያክሉ ድርጅቶች ነን የሚሉ ከፍተኛ የታሪክ ወንጀል በመስራት ላይ ይገኛሉ። እነዚህ የተለያየ ስም ይዘው የሚንቀሳቀሱ ኢትዮጵያውያን ነን የሚሉና የኢትዮጵያም ነገር ያገባናል የሚሉ የአሜሪካ ዜግነት ባላቸው ግለሰቦች የተቋቋሙት ድርጅቶች፣ ይሁንና ምንም ዐይነት የፍልስፍና አመለካከትና ሳይንሳዊ ግንዛቤ ይሌላቸው በመሰረቱ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የኒዎ-ኮሎኒያል ፕሮጀክትን ተግባራዊ ለማድረግ የሚታገሉ ናቸው። በሌላ አነጋገር፣ውድ እናት አገራችንን የአሜሪካን ቅኝ-ግዛት በማድረግ ህዝባችን ነፃነቱን በማጣት የተሟላና ባህላዊ አገር እንዳይገነባ ለማድረግ የሚታገሉ ናቸው ማለት ነው። በመሰረቱ እነዚህ ኢትዮጵያውያን ነን የሚሉና በአሜሪካ በመኖር የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው የሚያራምዱት ፖለቲካ የሚሉት ፈሊጥ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምን የፋሽሽት አጀንዳ ነው። በተለይም በአሁኑ በዶናልድ ትረምፕ የአገዛዝ ዘመን በዚህ መሰረት “ተደራጅተውና” የኮንግረስ ሰዎችን በመለማመጥ መንቀሳቀስ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም አገሮችን የማውደም አጀንዳና ጥሬ-ሀብታቸውን የመዝረፍ ዓላማውን በፍጹም አልገባቸውም። የአሜሪካኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር የሆነው ማርኮ ሩቢዮ በሙኒክ የደህንነት ስብሰባ ላይ በጥር ወር 2026 ዓ.ም ላይ ባደረገው ንግግር በተለይም የአፍሪካን አህጉር የቅኝ-ግዛት ለማድረግ ዓላማ እንዳለቸውና ማድረግም እንደሚፈልጉ በግልጽ ተናግሯል። ባጭሩ እነዚህ ኢትዮጵውያን የአሜሪካን ዜግነት ያላቸው ድርጅት አለን የሚሉትን በግልጽ መዋጋት ያስፈልጋል። እጅግ አደገኛና ለዝንተ-ዓለሙ የኢትዮጵያ ህዝብ በድህነት ዓለም ውስጥ እንዲኖር ለማድረግ የሚሯሯጡ ናቸው ነው። ይህም ማለት በአስተሳሰባቸው በጣም ወደ ኋላ የቀሩና ኋላ-ቀርነትን በአገራችን ምድር ፈርጥሞ እንዲቀር የሚታገሉ ናቸው። በሌላ አነጋገር፣ የአሜሪካንን የፋሺዝም አጀንዳ በአገራችን ምድር ተግባራዊ ለማድረግ የሚሯሯጡ ናቸው ማለት ነው። የሚያሳዝነው ነገር እነዚህ የአሜሪካን ዜግነት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ከአርባና ከሃምሳ ዓመት በላይ አሜሪካን አገር እየኖሩ አብዛኛው የአሜሪካን ህዝብ በምን ዐይነት ሁኔታ ውስጥ እንደሚኖር ለመገንዘብ ያልቻሉ ናቸው። በትላልቅ ከተማዎች ውስጥ በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ አሜሪካውያን የቤት ኪራይ መክፈል ሰላማይችሉ በየፓርኮች ውስጥ ይተኛሉ። በተለይም ጥቁር አሜሪካውያን እንደሁለተኛ ዜጋ የሚታዩና እንዲሸማቀቁም የሚደረጉ ናቸው። በዚህ ላይ የአሜሪካኑ የአገር ውስጥ የስለላ ድርጅት ኤፍቢአይ በተለይም በወጣት ጥቁር አሜሪአውያን ላይ የሚፈጽመው ግፍ በጣም የሚያሳዝን ነው። የድረግ ሱሰኛ እንዲሁን ራሱ በመሽጥ ወጣቶችን እያበላሻቸው ይገኛል። በሌላ ወገን ደግሞ የአሜሪካን መንግስት ለመከላከያ በሚል. ወይም ለጦር መሳሪያ ግዢ በብዙ መቶ ቢሊዮን ዶላር በመመደብ ይገዛል። ይህም የጦር መሳሪያ የሚያግለግለው በዓለም አቀፋ ጦርነትን ለማካሄድና የተወሰኑ አግሮችን ለማተረማመስ ነው።
ይህንን ካልኩኝ በኋላ ላይ ለማረጋገጥ እንደሞከርኩት በመለሰ ዜናዊ የሚመራው ማፊያዊ ቡድን የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ፕሮጀክት የሆነውን ያህል በአቢይ አህመድ የሚመራው የብልፅግና የወንበዴዎች ድርጅትም በመሰረቱ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና የግበረ-አበሮ´ቹ ፕሮጀክት ነው። በህወሃትና በአቢይ አህመድ የሚመራው የብልፅግና ፓርቲ መሀከል በቅርጽ ቢለያዩም ዋናው ዓላማቸው የጥቁር ህዝብ ምሳሌ የሆነችውንና በአደዋ ላይ በአፄ ምኒልክ መሪነት በኢጣሊያን ወራሪ ኃይል ላይ ድል የተቀዳጀችውን አገራችንን ኢትዮጵያን ታሪኳንና ባህሏን እንዳለ ማውደም ነው። ይኸው እንዳየነው አቢይ አህመድ ስልጣንን ከተቀዳጀ ከዛሬ ስምንት ዓመት ጀምሮ የኢትዮጵያን የእርቶዶክስ ሃይማኖት ለማውደም ያልሞከራው ወንጀላዊ ስራ የለም። ቤተ-ክርስቲያኑን በመከፋፈል በቀሳውስቱ ዘንድ መተማመን እንዳይኖር ለማድረግ በቅቷል። ቁጥራቸው የማይታወቁ የሃይማኖት መሪዎችም እንዲሰደዱና እንዲገደሉም አድርጓል። የፔንጤ ቆንጤ ሃይማኖት እንዲስፋፋ በማድረግ ጥንታዊውን የክርስትናን ሃይማኖት አዳክሟል። የፔንጤ ቆንጤ ሰባኪዎች ከምስኪኑ ተከተዮቻቸው ገንዘብ በመሰብሰብ ተንደላቅቀው የሚኖሩ ናቸው። ዋና ዓላማቸውም ጠቅላላውን የኢትዮያጵያ ህዝብ በማዳከም ምርታማ ስራ እንዳይሰራና እራሱን እንዳይችል ማድረግ ነው። በመሰረቱ እነዚህ በሃይማኖት ስም የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ልክ እንደ ኢትዮጵያ መንግስት ተብዬው የአሜሪካ ኢምፔሪያሊዝምና የግብረ-አበሮችን አገርን የማዳከምና ባህልን የማውደም ስራ የሚሰሩ ናቸው። ግራ የተጋባ ህዝብና መሪ የሌለው ህዝብ በመፍጠር የመጨረሻ መጨረሻ ላይ በሩን ክፍት በማድረግ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም አገራችንን እንዳለች እንዲቆጣጠራት ማድረግ ነው። በሌላ አነጋገር፣ ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ ወደ አሜሪካ ኢምፔሪያሊዝም ቅኝ-ግዛትነት መለወጥ ነው። ከዚህ ውጭ በፍጹም ሊታይ የሚችል ነገር አይደለም።
በአጠቃላይ ሲታይ አቢይ አህመድ ስልጣንን ከተቀዳጀ ጀምሮ እነ መለሰ ዜናዊ ተግባራዊ ሲያደርጉ የነበሩትን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማካሄድን ነው የቀጠለው። እንደምንከታተለውና የኢትዮጵያም ህዝብ ኑሮ እንደሚያረጋግጠው ህዝባችን በከፍተኛ ድህነት ውስጥ፣ በተለይም በኑሮ ውድነት የሚሰቃይ ነው። በኢኮኖሚ ታሪክና በኢኮኖሚ ሎጂክ ውስጥ በማይታወቅ ሁኔታ የኢትዮጵያ ብር ባለፉት 36 ዓመታት በተከታታይ ከአሜሪካን ዶላር ጋር ሲነፃፀር ዝቅ እያለ መጥቷል። በዚያው መጠንም የኢትዮጵያ ብር የመግዛት ኃይሉ በከፍተኛ ደረጃ ዝቅ ብሏል። የአገራችን የኢኮኖሚ ፖሊሲ አውጭዎች ከዓለም የገንዘብ ድርጅት ጋር እየተመካከሩና ትዕዛዝም እየተቀበሉ ተግባራዊ የሚያደርጉት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ዋናው ዓላማው ግልጽ የሆነላቸው አይመስልም። በሳይንስም ሊያስረዱም አይችሉም። በዚህ ዐይነቱ በሳይንስ፣ በፍልስፍናና በሎጂክ የማይደገፍ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነትም ወደ ውስጥ ያተኮረ፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተና እርስ በርሱ የተያያዘ ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ አውታር አልተዘረጋም። የስራ መስክም ለሚፈልገው ሰፊ ህዝብ የስራ መስክም አልተከፈተለትም። በሙያ ማሰልጠኛ እጦት የተነሳ በየመንገዱ የሚንቀዋለለው ወጣት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ነው። በሌላ ወገን ደግሞ ይህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ብለው የሚጠሩት ለዘረፋ የሚያመች በመሆኑ ጥቂት የሆኑ የብልፅግና ፓርቲ አባላትና የአገዛዙ አቀንቃኞች ተንደላቅቀው የሚኖሩበትን ሁኔታ እንመለከታለን። ባጭሩ አቢይ አህመድ ስልጣንን ከጨበጠ ከዛሬ ስምንት ዓመት ጀምሮ በከፍተኛ ደረጃ የብልግና ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋ አድርጓል። ግብረ-ሰዶማዊነትም ተቀባይነት እንዲኖረው ለማድረግ ችሏል። ይህም በራሱ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም እንድን ህብረተሰብ የማባለግ ሌላው ፕሮጀክቱ ነው። በዚህ አማካይነት ሰጠት ብሎ በመግባትና የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍልን በመቆጣጠር ባህላዊና እሴት ያለው ህብረተሰብን እንዳይገነባ ያደርጋል። ባጭሩ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ዋናው ፕሮጀከት በአንዳንድ አገሮች ውስጥ የብልግና ኢንዱስትሪ በማስፋፋት ታሪካዊና ባህላዊ ስራ እንዳይሰራ ማድረግ ነው። ሁሉም ነገር ብዥ ያለበትና የኑሮ ትርጉምንም ሊረዳ የማይችል ህዝብ መፍጠር ነው።
ይህንን ካልኩኝ በኋላ አቢይ አህመድና አገዛዙ አገራችንን በሁሉም አቅጣጫ ለማዳከምና ሰፊውን ህዝብ አቅመ-ቢስ ለማድረግ ሲል በተለይም በአማራው ወገናችን ላይ ጦርነት በመክፈት ቁጥራቸው የማይታወቁ ወገኖቻችንን አስገድሏል። በአዚህ ዐይነቱ ዘር ተኮር ጦረነትም የመጨረሻ መጨረሻ ዋናው ዓላማው ምን እንደሆነ በግልጽ የሚታወቅ አይደለም። ይሁንና ግን አካሄዱና ጦርነቱ ኢትዮጵያን እንዳለች ለአረቦችና ለአሜሪካኖች በመሸጥ ህዝባችንን መበታተን ነው። በሌላ አነጋገር፣ ስራው ሁሉ ሰይጣናዊ የሆነ ነው። ይህንንም ሰይጣናዊ ኃይልና ግብረአበሮቹን፣ ወይም የሚያመልኩትን ካለመታከት ማጋለጠና መዋጋት ያስፈልጋል። እነዚህ ኃይሎች ህሊናቸውን የሸጡ ስለሆነ በማስተማር መመለስና ሰውም ማድረግ በፍጽም አይቻልም። ከዚህ በተጨማሪም ከእንደዚህ ከመሳሰሉት ሰይጣናዊ ኃይሎች ጋር ለሚቀጥለው ምርጫ መወዳደር አለብን ብሎ ማሰብ አቢይ አህመድ እስካሁን ድረስ የሰራውን መጠነ ሰፊ ወንጀል ዕውቅና እንደመስጠትና በዚያውም ግፋበት እንደማለት ይቆጠራል፡. ስለሆነም ማንኛውም ድርጅት ወይም ፓርቲ አለኝ የሚል በሙሉ በምርጫ ውስጥ መሳተፍ የለበትም። የአቢይ አህመድ የወንበዴዎች ስብስብ የሆነው ብልፅግና የሚባለውና፣ የህወሃት ማፊያና ገዳይ ቡድን ከማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ መገለል ያለባቸውና እስካሁን ድረስ ለሰሩት ወንጀል ተጠያቂ መሆን ያለባቸው ናቸው። ጦርነት ከፍተው ህዝባችንን የጨረሱትና የብልግና ኢንዱስትሪን ያስፋፉትን እንደ ፖለቲካ ኃይሎች መቁጠርና ከእነሱ ጋር ተቀምጦ ስለፖለቲካ መወያየት ራስንም እንደ ወንጀለኛ ያስቆጥራል። ስለሆነም ማድረግ ያለብን እነዚህ ሁለት ኃይሎችና ለአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በስውርም ሆነ በግልጽ የሚሰሩ ግለሰቦችና ድርጅቶች በሙሉ ከኢትዮጵያ ምድር መወገድ አለባቸው። እነዚህ ሁሉ ኃይሎች ከአገራችን ምድር ሲጠፉ ብቻ ነው ሰላም ሊስፈን የሚችለው፤ አገርንም በጋር መገንባት የሚቻለው።
የመጨረሻ መጨረሻ ለማሳሰብ የምውደው ነገሩ ግልጽ ከሆነና የህወሃትም ሆነ በአቢይ አህመድ የሚገዛው የብልጽግና ፓርቲ፣ በመሰረቱ ምንም ድርጅታዊ ቅርጽ የሌለው የባላጌዎች ስብስብ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና የግብረ-አበሮቹ ፕሮጀከት ከሆነ ለምንድን ነው ኢትዮጵያን አድንልን በማለት የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምን የሚለማመጡት? የህዝብ ተጠሪዎች ነን የሚሉት የኮንግረስ ሰዎችም ምንም አቅም የሌላቸውና፣ በጥልቅ መንግስት(Deep State) ቁጥጥር ስር ያሉ ናቸው። በኑሮአቸውም ተንደላቀው የሚኖሩና አብዛኛዎቹ የዎል-ስትሪት ሰዎች ጋር የጠበቀ ግኑኘነት ስላላቸው ለኢትዮጵያ ህዝብ፣ በተለይም ለአማራው ያስባሉ ወይም ይጨነቃሉ ብሎ መገመት የዋህነትን ነው የሚያሳየው። የአሜሪካንን አገዛዝ ወይም የመንግስቱን መኪና የሚያንቀሳቅሱት የስለላ ድርጅቱና የሚሊተሪ ኢንዱስትሪ ውስብስብ ነገሮች ናቸው። የእነዚህ ዋና ዓላማም በዓለም አቀፍ ደረጃ ጦርነትን ማስፋፋትና ጥሬ-ሀብን መዝረፍ ነው። በአጠቃላይ ሲታይ በጠቅላላው በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የአገዛዝ መዋቅር ውስጥ የተጠቃለሉት ምንም ዐይነት የሰው ባህርይ የሌላቸው ናቸው። ባህል፣ ታሪክና ማህበራዊ ነገሮች ምን እንደሆኑ የማይገባቸው ናቸው። መንፈሳቸው ሁሉ በሰይጣናዊ አስተሳሰብ የተቀረፀ ስለሆነ ለሌላው ያስብሉ ብሎ ማሰብ እጅግ አደገኛ አመለካከት ነው። ሰለ ሰው ልጅም ምንም ደንታ የሌላቸው በመሰረቱ አመለካከታቸው ወይም ርዕዮተ-ዓለማቸው ፋሺዝም ነው። ይህ ከሆነ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምን መለማመጡ ራስንም እንደ ፋሽሽትነት ያስቆጥራል።
ከዚህ በተረፈ በውጭ አገር እየኖራችሁ በዩቱብ ቻናል መልክ ስለ ኢትዮጵያ ዜና የምታስተላልፉ በመሰረቱ ድንቁርናን ነው የምታሰራጩት። ምንም ዐይነት ግልጽ የሆነና ምሁራዊ የሆነ ሀተታ ስታሰራጩ በፍጹም አይታያም። በስንተኛው ክፈለ-ዘመንም እንደምትኖሩ በፍጹም ግልጽ የሆነላችሁ አይመስልም። ስልታችሁና የሳይንስም መሰረታችሁ ምን እንደሆኑ በፍጹም አይታወቁም። ገንዘበ ለመሰብሰብ ሲባል ብቻ የምታሰራጩት ዜና አንዳንዱ የሚታወቅ ቢሆንም ከበሰተጀርባው ያለውን ነገር በግልጽ ለማስቀምጥ የምትችሉ አይደላችሁም። ችሎታውም የላችሁም። የምትጋብዟቸው ሰዎችም በቂና ሳይንሳዊ ግንዛቤ ሊሰጡ የሚችሉ አይደለም። በአጭሩ ቀድሞ ሀዋሃት፣ ከስምንት ዓመት ጀምሮ ደግሞ አቢይ አህመድና አገዛዙ በራሳቸው ህሊናና ዕውቀት እንደሚገዙ አድርጋችሁ ነው ለማቅረብ የምትሞክሩት። በሌላ አነጋገር፣ ክበስተጀርባው የአሜሪካን ኢምፐሪያሊዝምና ግብረ-አበሮቹ፣ እንዲሁም የሚቆጣጠራቸው የዓለም አቀፍን ስም የተከናነቡት እንደነ የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት(IMF) የመሳሰሉት እንደሌሉበት አድርጋችሁ ነው ለማቅረብ የምትሞክሩት። ይህ ዐይነቱ አቀራረብ ሳይንሳዊ ያልሆነና በከፍተኛ ደረጃም የሚያዘናጋ ነው። ለነፃነትና ለተሟላ፣ ወይም ለሁለ-ገብ የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያመች አይደለም። ስለሆነም ከእንደዚህ ዐይነቱ በሳይንስና በሎጂክ በማይደገፍ፣ በተጨማሪም የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ በትክክል ከማያንፀባርቅ የተሳሳተ ዘገባ መራቅ አለባችሁ።
ከዚህ በተረፈ የኢትዮጵያ ጉዳይይ ወይም የብሄረሰቤ ጉዳይ ያገባኛል እያላችሁ በየሚዲያው እየተጋበዛችሁ የሚሆን የማይሆን ነገር የምትናገሩ አላችሁ። የየራሳቸሁ የፌስቡክ ያላችሁም የስድብ ጋጋታ ከማውረድ በስተቀር ሳይንሳዊ ሀተታና ለተወሳሰበው የአገራችን ችግርም መፍትሄም ለማቅረብ የምትችሉ አይደላችሁም። የአንድን አገር ችግር በዕውቀት አማካይነት ብቻ ነው መረዳትና ለሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ የሚሆን መፍትሄ ለመሰጠት የሚቻለው። አስቸጋሪው ነገር ባላፉት 20ና 30 ዓመታት ጊዜያችሁን በመወትወትና ከዕውቀት ውጭ በሆነ መልክ በማቅረብ ጭንቅላታችሁ በአጉል ትረካና በመለፍለፍ ተቀርጿል። ባጭሩ በተሳሳተ ትረካና በስድብ ጋጋታ የተቀረፀውን ጭንቅላታችሁን ማስተካከል በፍጽም አይቻልም። የሚቻል ከሆነ ሰፊውን ህዝብ ከማሳሳት ይልቅ አርፋችሁ ብትቀመጡ ትግሉን እንደማገዝ ይቆጠራል። ሌሎች የዚኸኛውን ወይም የዚያኛውን ብሄረሰብ ጉዳይ ያገባኛል፤ የኢትዮጵያም ሆነ የአማራው ጉዳይ ያገባኛል ብላችሁ በየሚዲያው እየተጋበዛችሁ ገለጻ ለመስጠት የምትሞክሩ አላችሁ። አንዳንዶቻችሁም በአብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ዕውቅናን አግኝታችኋል። ይሁንና ግን ምን ዐይነት ርዕይና ፍስልፍና፣ ሳይንሳዊ የአስራር ስልታችሁም ምን እንደሆነ በፍጹም የሚታወቅ ነገር የለም። ዝም ብሎ አገዛዙን ከመወንጀል በስተቀር የህወሃትም ሆነ የአቢይ አህመድ አገዛዝ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ፕሮጀክቶች እንደሆኑ በፍጹም ለመገንዘብ አትችሉም። የዓለም ፖለቲካ የሚባለውንም በየዋህነት መነፅር ስለምትመለከቱ የአሜሪካን ኢምፐሪያሊዝምን እንደ ቅዱሳዊ ኃይል አድርጋችሁ ነው የምትቆጥሩት። አንዳንዶቻችሁም በአሜሪካን ኢምፐሪያሊዝም ድጋፍ ስልጣን ላይ ከወጣችሁ በኋላ ያንኑ የህወሃትንና የአቢይ አህመድን የአገዛዝ ስልት በሌላ መልክ ተግባራዊ ለማድረግ ታስባላችሁ። ስለሆነም የኢትዮጵያ ህዝብ የሚፈልገውን ዘላቂነት ያለውን ሰላምንና የተሟላ ዕድገትን ተግባራዊ የማድረግ ችሎታ የላችሁም። ከእነዚህ በፖለቲካ ስም እዚህና እዚያ እንቀሳቀሳለን ብለው ግራ ከሚያጋቡት ውስጥ በአስተሳሰባቸው ወደ ኋላ ከቀሩት ውስጥ ገዱ አንዳርጋቸውና ልደቱ አያሌው ይገኙበታል። እነዚህና ሌሎችም በየሚዲያው እየተጋበዙ ኢ-ሳይንሳዊ ገለጻ ለመስጠት የሚሞክሩ በማዕከለኛው ክፍለ-ዘመን የሚኖሩ ነው የሚመስሉት። ጭንቅላታቸው በዘመናዊ ወይም ለተሟላ ስልጣኔ በሚያመች አስተሳሰብ የተቀረፀ አይደለም
ከዚህ ሁኔታ ስነሳ የኢትዮጵያ ሁኔታ ጨልሞ ነው የሚታየኝ። ሁላችንም ከመደናበር በሰተቀር በአንዳች ስልት፣ ፍልስፍናና ሳይንሳዊ ዕውቀት በመመራት ለመታገል የምንችል አይደለንም። አብዛኛዎቻችንም በዕድሜያችን የገፋንና በተሳሳተ ትረካ ጭንቅላታችን ስለተቀረፀ ያንኑ እየደጋገመን ከማውራት በስተቀር ምንም ዐይነት መፍትሄ ለመለገስ የምንችል አይደለንም። አብዛኛው ህዝባችንም ግራ የተጋባ በመሆኑ አገራችንም የወንበዴዎች መፈንጫ ለመሆን የበቃች አገር ሆናለች። በአሁኑ ወቅት ማንም የሚታመን ኃይል የለም። ጊዜው ያለፈብን ይመስላል። ቀደም ብሎ ከሃያና ከሰላሳ ዓመት በፊት መሰራት በነበረበት ዕውቀትን መሰረት ባደረገ ላይ ከመረባረብና ጥልቅ ጥናት ከማድረግ ይልቅ ጊዜያችንን በሆነው ባልሆነው በማሳለፍ በህዝባችንና በታሪካችን ላይ ትልቅ የታሪክ ወንጀል ፈጽመናል፤ እየፈጸምንም ነው። በዚህ ላይ አለመደማመጥና የኤሊት ትዕቢተኝነት በመንገስ ግልጽነት ላለው ምሁራዊ ውይይት ወይም ክርክር ዝግጁ አይደለንም። እንደሚታወቀው ለአንድ አገር የሚደረግ የነፃነት ትግል በትዕቢተኘነትና በአውቅሁኝ ባይነት መካሄድ ያለበት ነገር አይደለም። አንድን ህዝብ ከተተበተበት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የሚሊታሪ ቀውስ ለማላቀቅና ዕውነተኛ ነፃነትን ለማጎናፀፍ ትህትናንና ከፍተኛ ዕውቀትን ይጠይቃል። በዚህ አካሄድ ብቻ ነው የተወሳሰበውን የአገራችንን ችግር ለመፍታት የሚቻለው። መልካም ግንዛቤ!!
fekadubekele@gmx.de
www.fekadubekele.com
https://www.youtube.com/watch?v=efeIgqmfZ5E
https://youtu.be/XI9NG068TwI?is=mQWNCau5uep_3KJ6
https://www.facebook.com/share/r/18XGbW69hN/
ማሳሰቢያ፤ ስንቶቻችሁ ጽሁፌንና በተከታታይ እንደምታነቡና ድረ-ገጼንም እንደምትጎበኙ ለማወቅ ችግር ነው፡፡ አስተያየትም ለመስጠት ዝግጁ አይደላችሁም። በአንድ በኩል ለአገሬ አስባላሁ እያላችሁ፣ በሌላ ወገን ደግሞ እንደዚህ ዐይነት ጽሁፍ ሲወጣ አንብቦ አስተያየት መስጠት ወጪን የሚያስጠይቅ አይደለም። በሌላ ወገን ደግምሞ ከ15 ቀናት በፊት ባወጣሁት ጽሁፌ ላይ ለማሳሰብ እንደሞከርኩት እንደዚህ ዐይነት ሳይንሳዊ ጽሁፍን ለማዘጋጀት ከፍተኛ ዝግጅትን ይፍልጋል፤ ጊዜንም መሰዋት ያስፈልጋል። ዝም ብሎ የሚጻፍ ነገር አይደለም። ይህ እየታወቀ አንድም ግለሰብ ይህንን የመሰለ ጥናታዊ ጽሁፉ በሃሳብም ሆነ በቁሳቁስ ለመርዳት ዝግጁ የሆነ በፍጹም የለም። በጣም የሚያሳዝን ሁኔታን ነው የማየው። ታዲያ በዚህ መልክ እንዴት አድርጎ ለአንድ አገርና ህዝብ መታገልና የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት ማድረግ ይቻላል? ለመሆኑ እንዴት ነው የምናስበው? ችግራችን ምድን ነው? ይህ ጸሀፊ ሱስ ስላለበት አይደለም የሚጽፈው። ከሞራላዊ ግዴታ በመነሳት ትክክል ነው ብሎ የሚያስበውን ሳይንሳዊ መንገድ በመከተል ነው የሚታገለው። ይህም ቢሆን አንድ ቀን ሊቆም ይችላል። በሌላው ወገን ግን አያሌ ጽሁፎቼን ላነበበና የቪዲዮ ስርጭቴንም ለተመለከተ የሚገነዘበው አንዳችም መዘላበድና አሳሳችነት የላቸውም። በአጭሩ ሳይንሳዊ የአሰራር ስልትን´ በመከተል ብቻ ነው የምስራው። ስለሆነም ይህንን ዐይነቱ ግልጽነት ያለውን ጽሁፍ ማገዝ ያስፈልጋል። ድረ-ገጼንም በመጎብኘት አስፈላጊውን መረጃ ማግኘት ይቻላል።