ሚያዝያ 8 ቀን 2018 ዓም(16-04-2026)
በዚህ እርእስ ስር ለመጻፍ ያነሳሳኝና ያስገደደኝ የስልሳዎቹ ትውልድ ተብሎ የሚጠራው የእኔ ትውልድ ባሳለፋቸው የህይወት ዘመኑ በተለይም በተሳተፈባቸው የለውጥ ትግሎች ዙሪያ አውቆና ፈቅዶ ያልተሠሩና ያልነበሩትን ድርጊቶች እንደተፈጠሩ አድርጎ በማውራት በተለይም አዲሱ ወጣት ትውልድ በአንጋፋው ትውልድ ላይ ጥላቻ እንዲያድርበት ሰፊ ዘመቻ በመካሄድ ላይ መሆኑን በመገንዘቤ ሌላው ቢቀር ወጣቱን ትውልድ ከአሉቧልታና ከተሳሳተ አመለካከት ለማዳን ይረዳል በማለት ይህንን ጽሑፍ ለማቅረብ ህሊናዬ አስገድዶኛል።ከቶም ቢሆን ግን የተከሰቱትን ስህተቶች ለመሸፋፈንና ለመካድ ምንም ፍላጎትና ዓላማ አለመያዜን በቅድሚያ ለመግለጽ እወዳለሁ።
በማንኛውም ወቅት ያለ ትውልድ የራሱ የሆነ አመለካከትና ግንዛቤ ይኖረዋል።ለሚኖርበትና ለሚካፈለው የህብረተሰብ ኑሮ፣ባህል፣እምነት፣ንቃትና ግንዛቤ ተጋላጭ ነው። በእሱና ባካባቢው የሚገጥሙትን ችግሮች ለማሶገድ ሁኔታውና አቅሙ ብቻም ሳይሆን ንቃተ ህሊናው በሚፈቅድለት መጠን ትግል ያደርጋል።ምንም ጊዜ ቢሆን እጁን ሰጥቶ አይቀመጥም።ለመኖር ሲል ብቻም ሳይሆን ኑሮው ትርጉም ያለው እንዲሆን ፣ከራሱ አልፎም ለተከታይ ትውልድ እንዲተርፍ ለማድረግ የሰውነት ባህሪው ያስገድደዋል።ይህ የተፈጥሮ ግዴታ በሰው ልጆች ብቻ ሳይወሰን በማንኛውም ህይወት ባለው ፍጡር ዘንድ የሚኖር የመኖርና ያለመኖር አስገዳጅ ሕግ ነው።
የህብረተሰብ ችግር በብዙ መልኩ የሚከሰት ሲሆን ምክንያቶቹም ብዙ ናቸው ግን በሁለት ዋና ክፍሎች ማለትም ሰውሠራሽ(ሰው አመጣሽ)እና ፣ ተፈጥሮ ሠራሽ(ተፈጥሮ አመጣሽ) ተብለው ሊመደቡ ይችላሉ።የተፈጥሮ አመጣሹ ችግር የውሃ መጥለቀለቅን፣የሰደድ እሳትን፣መሬት መንሸራተትን፣የሳተገሞራን፣የመሬት መንቀጥቀጥን…ወዘተ ሲያካትት እነዚህን ችግሮች ለመከላከል የታደለ ህብረተሰብ ከሆነ ማለትም አገራዊና ሕዝባዊ አቋምና ችሎታ ያለው ስርአት ባለቤት ከሆነ በቅድሚያ ዝግጅት በማድረግ የአደጋውን መጠን ለመቆጣጠርና ለመቀነስ ይሞክራል። የሰው ሠራሽ ችግሮች ደግሞ በማንነቱና በሚከተለው ሃይማኖት ምክንያት ዝርፊያ፣ወረራ፣ማፈናቀል፣መግደል፣ማሰር፣ማፈን፣በጉልበት ማንበርከክ፣ሰብአዊና የዜግነት ክብሩንና መብቱን መግፈፍ፣አንዱ ለሌላው ባሪያና አገልጋይ እንዲሆን ማድረግ፣…ወዘተ ከብዙ ጥቂቶቹ ናቸው።እነዚህንም ችግሮች እንዳይከሰቱ የሚቆጣጠር አገራዊ ተቋም መዘርጋትና ስርዓት ማስፈን ወሳኝ ነው።
እኛም ኢትዮጵያውያን በነዚህ ከላይ በተጠቀሱት ችግሮች ውስጥ አልፈናል።የእኔ ትውልድ(የስልሳው ትውልድ)እነዚህ ችግሮች እንዲወገዱ በድፍረትና በህብረት የተነሳና ብዙ ትግል ያደረገ ፣መስዋእትነትንም የከፈለ ትውልድ ነው።ከአባቶቹና ከአያት ቅድመአያቶቹ የወረሰውን አገር ወዳድነትና ጀግንነት ወርሶ ለአገሩ ነጻነትና ክብር የተሰለፈ አገር ወዳድ ትውልድ ነው። ሌሎቹ ከደረሱበት እድገት አንጻር ለማድረስ በመንፈሳዊ ቅናት ህልም ሰንቆ የተነሳ ትውልድ ነው።ለወገኑም ካለበት ብስቁል ኑሮ እንዲገላገል ፣ፍትሕ ከጎደለው የበታችነትና ዝቅተኛ ተጠቃሚነት በማላቀቅ በሰውነት ደረጃ ተከብሮ እንዲኖር ካለው ሰብአዊ ስሜት እራሱን አሳልፎ ለመስጠት የተዘጋጀና የሰጠም ትውልድ ነው። በዚያ ለጋ ዕድሜው ለህይወቱ ሳይሳሳና ሳይፈራ የወደፊቱም በግሉ የሚኖረው የተሻለ ኑሮ ሳያጓጓው ሠው ሠራሹን ችግር ሰው ሆኖ ለማሶገድ እስከጦር ሜዳ ድረስ የተሰለፈ ጀግና ትውልድ ነው።
የእኔ ትውልድ ከደረሰበት የንቃተ ህሊና ደረጃ ለመድረስ ምክንያቱ ያለበት ውስጣዊ ሁኔታ አንዱ ሲሆን የዓለም ሁኔታና በዓለም ላይ የሰፈነው አመለካከት ሌላው ተጨማሪ ቀስቃሽና ጉልበት ሆኖታል።የችግሩን መነሾና መፍትሔውንም እንዲያውቅ እረድቶታል።ለሰው ሠራሹ(ሰው አመጣሹ)ችግር ምክንያቱ ሰው ሠራሹ የመደብ መከፋፈል እንደሆነና ለዚያም በሰው ልጆች መካከል ፍትሃዊ የጥቅም እኩልነትና ግንኙነት አለመኖሩ እንደሆነ በመረዳት የመደብን መከፋፈል ለማጥፋትና እኩልነትን ለማስፈን የታጠቀው የህሊና መሳሪያ በጊዜው የነበረው የጸረ ዘረፋና የጸረ ወረራ ትግል የሚካሄድበት ፍልስፍና የግራው ማለትም የሶሻሊስት ፍልስፍና መኖሩ ነው።እያንዳንዱ ትውልድ የገጠመውን ችግር ለመፍታት የሚገለገልበት ራእይ የሚነድፍበት ዓለምን የሚያይበትና የሚረዳበት ፍልስፍናና መንገድ መኖር ስለሚገባው የእኔም ትውልድ በዘመኑ ያገኘው መሳሪያ ከላይ የተገለጸው የሶሻሊስቶች ፍልስፍና ነው።በዚህ ፍልስፍና የተመሩ አገራት ወጣቶች ያገራቸውን ልዑላዊነት ማስከበራቸውና ሕዝቡ ከውጭና ከውስጥ ዘራፊዎች እጅ መላቀቁ ለእኔ ትውልድ የሞራል ማነቃቂያ ሆኖታል።የሶሻሊስት ፍልስፍና ለዓለምአቀፉ ወጣት የፖለቲካና የማህበረሰብ ችግር መፍቻ ቁልፍ ሆኖታል። አምባገነኖችንና ቅኝ ገዢዎችን ለማሶገድ አስችሎታል።ምንም እንኳን በብዙ መከራና ፈተና ያለፈ ቢሆንም፣እስከአሁንም ድረስ ችግሮቹ እስከወዲያኛው ባይፈቱም ትግሉና ትንቅንቁ እንደቀጠለ ነው።ወራሪና ዘራፊ አምባገነኖች ግንባር ፈጥረው የሞት የሽረት ትግላቸውን አላቆሙም።በተለይም በአገር በቀሉ ተባባሪዎቻቸው በኩል አገራትን በእጅ አዙርና በቀቀጥታ በመያዝ ካለፈው በባሰ የዘረፋ ሰንሰለት ቀፍድዶ ለመያዝ የማይገለብጡት ድንጋይ የለም።የአንድ አገር ሕዝብ በጎሳና በሃይማኖት ጎራ ለይቶ እርስ በርሱ እንዲጨፋጨፍ፣በጠላትነት እንዲሰለፍና ህብረቱ እንዲላላ ብሎም አገሩን አፍርሶ ደካማና ለወራሪዎች የተመቼ አካባቢ ለመፍጠር እንዲችል የተቀመረ ሴራ ተቀባይ በማድረግ ለአንዱ ወገን መሣሪያና ገንዘብ በማፍሰስ ሌላውን አገር ወዳድ ለማንበርከክ ፍልሚያቸው ቀጥሏል።ለዚያ ደግሞ ዋናው ጠላትና ቅድመ ዒላማ ተደርጎ የተወሰደው አገርወዳዱ የእኔና ተከታዩ የአሁኑ ትውልድ ነው።በሁለቱ ትውልዶች መካከል ያለውን ትስስር ለመበጠስ የማይመዘዝ ትርክት የለም።የእኔ ትውልድ(የስልሳዎቹ)ለአገሩ ክብርና ለወገኑ እኩልነትና ለፍትህ ያደረገውን ተጋድሎ በአገር ክህደት እዬተረጎሙ ዋጋ ለማሳጣት የሚደረገው ዘመቻ ተጠናክሮ ቀጥሏል።እንደ እውነቱ ከሆነ ያ ትውልድ፣ፍጹም አገር ወዳድ ፍጹም ሕዝብ ወዳድ ነበር፣ፍጹም ለእኩልነትና ለአገር ልኡላዊነት የቆመ ትውልድ ነበር እንጂ ጸረ ለውጥ የሆኑ ወይም ለአምባገነን አገዛዞች ዘብ ቆመው የሰው ደም በእጃቸው ባፈሰሱ በገደሉና በዘረፉ አረመኔዎች በኩል እንደሚባለው አገር አጥፊ ትውልድ አልነበረም።
በገባርነት የሚኖረውን ዜጋ የመሬቱና የላቡ ውጤት ባለቤት ለማድረግ መሬት ላራሹ የሚል መሪ ቃል አንግቦ የታገለና ያታገለ ፤የዲሞክራሲ መብቶች ይከበሩ ብሎ የጮኸ፣ሕዝባዊ መንግሥት ይቋቋም ብሎ ለስርዓት ለውጥ አደባባይ የወጣ፣ትምህርት ለሁሉም ብሎ የጠዬቀ፣ ዳቦ ለተራበ በማለት ምግብ ለሁሉም ይዳረስ እርሃብና ቸነፈር ይወገድ ፣የሠራተኛው መብት ይከበር…ወዘተ የሚሉ ሕዝባዊና አገራዊ ጥያቄዎችን አንስቶ የታገለና መስዋእትነትም የከፈለ ትውልድ ነው።ታዲያ እምኑ ላይ ነው አገር ከሃዲነቱና ጸረ ሕዝብነቱ?
የአስራአንድ ዓመት ልጅ ከሶስት ታላላቅ ወንድሞቹ ጋር በቤቱ ደጃፍ ላይ ከተገደለው ጀምሮ፣እርጉዝ ሴት በማህጸኗ ከያዘችው ሊወለድ ከተቃረበ ጨቅላ ጋር የገደለ፣ከሟች ቤተሰብ የገደለበትን የጥይት ዋጋ የሚጠይቅ፣ዜጎችን ካለፍርድ ገሎ ለቀብር ስርዓት ያላበቃና የሰውን ክብር ገላ አሲድ ነስንሶ ጉድጓድ ውስጥ የጣለ፤ አምባ ገነንና ጨካኝ(አረመኔ) ስርዓት እንደ አገር ወዳድ ተቆጥሮ ጉሮ ወሸባዬ ሲባልለት የሞተውና የቆሰለው በእስርቤት የማቀቀው ያ የኔ ትውልድ ወጣት ግን እንደ አገር ከሃዲ ተቆጥሮ ሲወገዝ መስማት የተለመደ ሆኗል። በደርግ ዘመን የተጀመረው በኢሕአዴግ የተወረሰው አሁን ላለው አገዛዝ የደረሰው ጸረ ሕዝባዊነት ፣ጸረ ኢትዮጵያዊነት ስርአት ደጋፊዎች እንደ ብሔራዊ መዝሙር እዬተቀባበሉ የሚያወርዱት በያ ትውልድ ላይ የሚያስተጋቡት ውንጀላ ሆኗል።
ለዚያ ምክንያቱ ደግሞ ውዥንብሩንና ስም ማጥፋቱን ወደ ጎን ብሎ በራሱ ትውልድ ዘመን የሚፈጸመውን ሰው ሠራሽ ወንጀልና በደል ዘረፋና ግድያ እንዲሁም የአገርን መፍረስ አደጋ ለመከላከል የቀድሞውን ትውልድ የትግል አርማ ይዞ ወንጀለኞችን በሕግ ለመጠዬቅ የተነሳ ወጣት ትውልድ በመኖሩ ፍርሃትና ቅናት በመቀስቀሱ ነው።ወድቀው እንደቀሩት የፖለቲካ ድርጅቶች ወድቆ ያልቀረ ድርጅት ይዘው ብቅ በማለታቸውና በድፍረት ስርዓቱን ወጥረው በመያዛቸው ነው።
መካድ የማይገባው ነገር ቢኖር በትግል ውስጥ ብዙ ስህተቶች መፈጸም እንደሚችሉና የእኔም ትውልድ ባሳለፈው የትግል ጉዞ ብዙ ስህተቶች እንደፈጸመ መካድ አይገባም።ነቅተዋል በቅተዋል በሚባሉት ምሑራንና የትግሉ መሪዎች መካከል የነበረው አላስፈላጊ ንትርክና ክፍልፍል ተነጋግሮ ልዩነትን ማሶገድ ወይም ማጥበብ የሚቻልበት የፖለቲካ ባሕል ስላልነበረ እንዲካረርና በጠላትነት ጎራ እንዲሰለፍ አድርጎታል።በተለይም በአመራር ዙሪያ የሚፈጸሙት ስህተቶች ለተራው አባልና ደጋፊም ቢሆን እንግዳና ባዳ ነበሩ።ለመጠዬቅና ለማረም የማይቻልባቸው ስጋቶች ነበሩ። ዴሞክራሲያዊ መድረክ ባለመኖሩና ባለመለመዱ የጠዬቀና የተቃወመ ከጠላት በኩል ከሚደርሰው ባላነሰ መንገድ በተለይም ስም በማጥፋትና ስብእናን በሚነካ መንገድ ማጠልሸቱ አንዱ የትግል መንገድ ነበር ማለት ይቻላል።ያም ውስጣዊ አንድነት እንዲቦረቦርና እንዲዳከም አድርጎታል።የማታ ማታም አንዱ ወገን የሚታገሉትን ስርዓት ተጠግቶ ሌላውን የማጥቃት ዘመቻ ውስጥ ከቶታል።አንዱ በሌላው ላይ ጠመንጃ መዟል፣ተኩሷል፣ተጋሏል።በዚያም አምባገነኑ አገዛዝ ተጠቃሚና አሸናፊ ሆኖ እንዲወጣ አድርጎታል።ሁለቱንም በልቷል። በአንድ መድረክ ላይ ትግል የጀመሩ ወጣቶች ጎራ ለይተው በጠላትነት ተሰልፈው የትግላቸው ምዕራፍ በዚያው ሊጠናቀቅ ችሏል።አሁንም ድረስ በህይወት ያሉትየአመራር አባላት ተቀራርበው የነበረውን ስህተት አምነው ለተተኪው ትውልድ ተመክሮ ለመስጠት ድፍረትና ፍላጎት አላሳዩም።ሁሉም የራሱን ጎራ ብጹእና ቅዱስ አድርጎ በማቅረቡ ቀጥሎበታል።
በዚህ አይነቱ የመከፋፈልና ልዩነት አባዜ ውስጥ የሌሎቹም አገራት ታላላቅ የፖለቲካ ድርጅቶችና ትግሎች ያለፉበት መንገድ እንጂ በኢትዮጵያውያኖች ብቻ የተከሰተ አይደለም።የሩስያ፣ የቻይና፣የቬትናም፣የኮሪያ፣የአንጎላ፣የሞዛምቢክ፣የሮዴዝያ(ዚምባብዌ)የደቡብ አፍሪካ…ወዘተ አብዮታውያን የገጠማቸው ችግር ነው።ልዩነቱ ሌሎቹ በብልሃትና በዘዴ አንዱ ሌላውን በማካተት ወይም በማሶገድ ትግሉን ለውጤት ሲያበቃ እኛና መሰሎቻችን ግን ከነበርንበት ለባሰ ሁኔታ ተጋልጠን አገራችንንም አጋልጠን መበተናችንና በእኛ ኮቴ የዛሬዎቹ አገር ጠሎች እንዲፈጠሩ ሁኔታውን ማመቻቸታችን ነው።ባዶ ቤት በቁንጫ ይወረራል እንዲሉ!
ለትግሉ መፈረካከስ የተለያዩ ምክንያቶች ይኖሩታል።
1 ትግሉ በተማሪ ትግል ማህጸን ውስጥ የተወለደ ስለሆነ የልምድና የንቃት ጉድለት በመኖሩ፣የብዙሃን ስብስብ ስለሆነ የተለያዩ ፍላጎቶች ስለሚንጸባረቁበት የዓላማና የፖለቲካ መስመር ጥራት ለመኖሩ እንቅፋት ሆኗል።
2 የህብረተሰቡን የእድገት ደረጃ ባለመገንዘብ የትግሉን ወይም የአብዮቱን ደረጃ ያለመረዳት ማለትም በጫጨ ኤኮኖሚና የፖለቲካ ንቃተ ህሊና ለሶሻሊስ ስርዓት መደላድል ሳይፈጠር ማለትም ከባላባታዊ ስርዓት የዴሞክራሲን ስርዓት ዘሎ ሶሻሊዝም መዳረሻ መሆኑ ቀርቶ መነሻ ተደርጎ መወሰዱ፤በዚህም መስፋፋትና ማደግ የሚኖርበት ብሔራዊ የኤኮኖሚ ደረጃ ባለበት እንዲረግጥና በአርሶ አደር ኤኮኖሚ ግብአት ተወስኖ እንዲቀር ማድረጉ፤አገር ወዳድ ሃብታሞችን ማበረታታት ቀርቶ እንደ ጠላት ተቆጥረው ያላቸውን ተቀምተው ወደ ድህነት እንዲያሽቆለቁሉ የሚያደርግ የምቀኝነት አቋም እንደ ዘመናዊና እድገታዊ ፖለቲካ ተደርጎ መወሰዱ።ሌላው ቀርቶ መተዳደሪያ የሆነችውን አንድ ክፍል የኪራይ ቤቱንና እራፊ የእርሻ መሬቱን ባላባት ተብሎ መነጠቁ የድሃውን ቁጥር እንዲያሻቅብ ሲያደርገው የመሥራት ስሜት እንዲሞት አድርጓል። አነሰ ሲሉ ተቀነሰ!
3 በወጣትነት(በልጅነት)አይምሮ እልህና ጀብደኝነት ስለተጸናወተው አቅምን ያላገናዘበ ትግል ውስጥ መሰማራቱ፣ማለትም በገጠሩ ትግል በማተኮር ማእከላዊ መንግስትን ከሕዝቡ በመነጠል መክበብና ማስጨነቅ ሲገባ ሃይል ሳይጠነክር በከተማና በገጠር የትጥቅ ትግል በማካሄድ ሃይሉን ማመናመኑና ለጠላት ጥቃት ተጋላጭ መሆኑ
3 የፖለቲካ ድርጅትና እንቅስቃሴ ነጻነት ስላልነበረ የፖለቲካ ባሕልና ልምድ ባለመኖሩ፣ፖለቲካ የህብረተሰብ ኑሮ መቀዬሻ መሆኑ ቀርቶ የበቀልና የምቀኝነት መሣሪያ ሆኖ ማገልገሉ፣
4 ለገንጣይና አስገንጣይ ግለሰቦችና ቡድኖች ክፍተት መኖሩ ብቻም ሳይሆን በወሳኝ ቁልፍ ቦታዎች ላይ መቀመጣቸው። በዴሞክራሲ ስም ለአሁኑ የጎሳ ፖለቲከኞችና ለሚከተሉት አገር የመበተን ፖለቲካ የተመቼ ሁኔታ መፍጠሩ፤ የተፈለፈሉበት ማህጸን ሆኖ ማገልገሉ
እነዚህ ድክመቶች በዋናነት የድርጅቱን መሪዎች የሚመለከት ሲሆን ተራ አባላቱም ቢሆኑ በዝምታ ያለፉት ከሆነ በመጠኑ ከተጠያቂነት አያመልጡም።ተጠያቂነታቸው ግን ከስህተታቸው ታርመው የተሻለ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ እንጂ ከትግል ዓለም እንዲወገዱ ወይም እንዲርቁ የሚያደርግ መሆን የለበትም።እያንዳንዱ ዜጋ የአገር እሴት ነውና!በተለይም በትግል ዓለም ውስጥ ያለፈ የብዙ ተመክሮ ባለቤት ስለሆነ ከስህተቱ ሌላውን ተተኪ ትውልድ ሊመክርና ሊያርመው ይችላል።
አሁንስ ምን ማድረግ ይገባል(ይቻላል)?
መውደቅና መነሳት የተለመደ ነው።ወድቆ መነሳት የጥንካሬ ምልክት ነው።ወድቆ መቅረት ግን የድክመትና የችንፈት ማሳያ ነው።ሲነሱ ግን ዳግም ላለመውደቅ ካለፉት ተምሮ በጠንካራ ካስማ ላይ የቆመ እምነትና ዓላማ ይዞ ለውስጥና ለውጭ አፍራሽ ሃይሎች ሳይንበረከኩና በር ሳይከፍቱ ሕዝብን የጀርባ አጥንት አድርጎ በግልጽነትና በቁርጠኛነት ለቆሙበት ዓላማ መስዋእት ለመሆን መቁረጥ ያስፈልጋል።ጀግና ሆኖ ሌላውም በጀግንነት እንዲነሳ ምሳሌ መሆን ያስፈልጋል።ሌላውም ዜጋ የሚደረገው ትግል የራሱና ለራሱ ጥቅምና ክብር መሆኑን ተረድቶ አብሮ የመቆምና የመሰለፍ ግዴታ አለበት።ሌላው ሞቶና ቆስሎ፣ታስሮና ተሰዶ እኔ እጄን አጣጥፌ የበረከቱ ባለቤት ልሁን ቢል የሚፈቅድለት የሞራል ህግ የለም።ፍትሃዊም አይደለም።በሰው ደም መጠቀም ማለት ነው። አገር የሁሉም ዜጋ የጋራ ንብረት ነው።ስለሆነም ለጋራ ጥቅምና ንብረት ለእኩልነት ድርሻና መብት ሁሉም የበኩሉን ማበርከት ይኖርበታል።አሁን በትግሉ ሜዳ ላይ ካሉት ጋር የሚሰለፉበት ጊዜ እንጂ ባለፈው ትውልድ በተፈጸሙ ስህተቶች ምንም የማያውቀውን፤መወለዱ ሳይቀር ያልታሰበውን ለምን ለeግል ተሰለፍk በሚል መልኩ በቅናትና በጥላቻ ተነሳስቶ እዬወቀሱና እያወገዙ የወጣቱን ሞራል ለመስበር መሞከር ከአገዛዙና ከአምባደነኖች ጋር መወገን ማለት ነው።
ያለፈን ስህተት ዳግም ላለመሳሳት መስተዋትና ማስታወሻ፣ መማሪያም አድርጎ መጠቀም እንጂ ለመጠፋፋት መሣሪያ መሆን አይገባውም።ያለፈውን ትውልድ በጎ ተግባር በመርሳት ወይም በመበከል የሚገኘው ትርፍ ሳይሆን ኪሳራ ነው።ሌላው ለትግል እንዳይነሳሳ የሞራል ስብራት እንዲያድርበት ማድረግ ነው።ገንቢና ቀና ሂስ ማድረግ የቀናዎች ድርሻ ሲሆን አፍራሽ ሂስ ማድረግ ግን የአፍራሾች ድርሻ ነው። አሁን በመንቀሳቀስ ላይ ያሉትን የፖለቲካ ድርጅቶች በተለይም ጎሰኝነትንና ያለውን አገዛዝ በመቃወምና በማጋለጥ ላይ ያሉትን አገር ወዳዶች በተሳሳተ እይታ መመልከት ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል።ህጻን ልጅ ቆሞ ለመሄድ ሲሞክር እንዳይወድቅ እጁን ይዘው ያራምዱታል እንጂ ወግድ ብለው አይገፉትም።የሚወዱትን ልጅ ያለበትን ቁሻሻ ያጸዱለታል እንጂ ዓይንህ ላፈር አይሉትም።አገርን ከጎሰኝነት፣ከአምባገነኖች፣ከዘራፊዎችና ከወራሪዎች ለማዳን የተሰለፈውን በዘመኑ ትውልድ የሚመራ የፖለቲካ ቡድን ተጠግቶ መምከርና መርዳት የእውነተኛ ለውጥ ፈላጊ ድርሻ ነው። በስም ማጥፋትና ዘለፋ የሚታገሉትን በማንቋሸሽ ለማንበርከክ መሞከር የእውቀትና የእውነት ድህነት ማሳያ ነው።ቅናትና ምቀኝነት የወለደው በሽታም ነው።
የአሁኑ ትውልድ በአባቶቹ ለተፈጸመው ጥፋት ተጠያቂ አይሆንም።የዛሬው ትውልድ ለሚፈጽመው ጥፋትም የነገው ትውልድ አይጠዬቅም ፣አይወቀስም።ትውልድ የሚታዬው በኖረበት የጊዜ መስተዋት ነው።የሚመዘነውም በኖረበት ሚዛን ነው።ሆኖም ግን የነገው ትውልድ ከስህተት ላይ እንዳይወድቅ በተመሳሳይ አገዛዝ ስር እንዳይኖር የተመክሮ ውርስ አሳልፎ የመስጠት አደራና ግዳጅ አለበት። ቤቱን አጽድቶ ማስረከብ ይገባዋል፤በንጹህ ቤት የተወለደ ልጅ ለበሽታ አይጋለጥምና!
ለተመሳሳይ ውድቀት ላለመዳረግ ካለፉት የተሻለ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ማስፈን የወደፊቱ መዳረሻ መሆን አለበት።በተያዘው የጎሳ ፉክክርና የስልጣን ቅብብሎሽ የሚመጣ ለውጥ አይኖርም።ቢኖር ከእሳቱ ወደ እረመጡ ከመሆን ያለፈ ሳይሆን በጦርነት አዙሪት ውስጥ ሲሽከረከሩ መኖር ይሆናል።ከዚያም ባለፈ አገር አልባ የመሆኑን ዕድል ከፍ ያደርገዋል።ስለሆነም በኢትዮጵያዊነት ለተሻለ ፍትሃዊ ስርዓት ከመታገልና ከማስፈን የተሻለ አማራጭ የለንም።
ለዚያ መጀመሪያው
ሀ/ በጎሳና በጠባብ(በክልል) እይታ የተበከለውን ዜጋ ወደ ኢትዮጵያዊነትና ሰውነት ደረጃ መመለስ
ለ/ ሃይማኖት የግል አገር የጋራ የሚለውን መንፈስ ማሳደግና የልዩነትና የንትርክ ምክንያት አለመሆናቸውን ማስረገጥ
ሐ/ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሕግ አደባባይና በዜግነት ደረጃ እኩል መሆኑን ማረጋገጥ
እነዚህን መመሪያዎች ሁሉም ከተቀበለ የምናልመውና የምንመኘውን ለውጥ ለማምጣት ከባድ አይሆንብንም።
እውነትና ጀንበር እያደር ይጠራል!አለባብሰው ቢያርሱ ባረም ይመለሱ!
አገሬ አዲስ