በበላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)

ይህ ሳምንት የሰው ልጅ መለኮትን በዲናር የሸጠበት ሳምንት ነው፡፡ ይህ ሳምንት ደቀመዝሙሩ መምህሩን ዶሮ ሳይጠባ ሶስቴ የካደበት ሳምንት ነው፡፡ ይህ ሳምንት “የኦሪት ሊቃውንት” ነን ይሉ የነበሩ ፈሪሳውያን በሐሰት ወንጀል ክርስቶስን ከጲላጦስ ችሎት ያቀረቡበትና ሕዝብንም በማሳሳት “ስቀለው ስቀለው” ብለው ያስጮኹበት ወቅት ነው፡፡ ይህ ሳምንት እውነት በእሾህ ተጠቅጥቃ የደማችበት፣ እጅና እግሮቿ ተግንድ በምስማር ተከርችመው ሲው ያለችበት ሳምንት ነው፡፡ ይህ ሳምንት የህመም ሳምንት ነው፡፡ ይህ ሳምንት ህማማት ነው፡፡
እንደዚህ ሳምንት ሁሉ ይህ ዘመንም የታመመ ነው፡፡ ይህ ዘመን አራዊት ለማዳ ሲሆኑ ሰው ግን ወደ አውሬነት ሚቀየርበት ዘመን ነው፡፡ ይህ ዘመን በመንፈስ ልእል መገዛት የጅልነንትና ያለመሰልጠን፤ ዓይኑን በጨው የታጠበ ቃጣፊና እንደ ጩልሌ ሞጭላፊ መሆን ደግሞ የስልጣኔ ምልክት ሆኖ የሚታይበት ዘመን ነው፡፡ ይህ ዘመን ውሸት፣ ቅጥፈት፣ ስርቆት፣ አጭበርባሪነትና ክህደት የዘመናዊነት መለኪያዎች የሆኑበት ዘመን ነው፡፡ ይህ ዘመን ሰው መለኮትን በዲናር በመሸጡ የይሁዳን ያህልም የማይፀጸትበት፤ ወላጅ ልጁን፣ ልጅ ወላጁን፣ ወንድም ወንድሙን፣ እህት እህቷን፣ ጓደኛ ጓደኛውን አሳልፎ በመስጠቱ ሐፍረት የማያሳይበት ዘመን ነው፡፡ ይህ ዘመን በምላስም ሆነ በጡጫ ወንበር የተቆናጠጠ ገዥ ዜጎችን እንደ በግ እያሳረደ ተንደላቆ በመኖሩ የሚመጻደቅበት፣ የሃይማኖት መሪ ነኝ ባዩ መስቀልን፣ ቆብና ጥምጣምን የፍትፍትም የፍተወትም መዛቅያ ቁና ሲያደርግ የሚገታው ማተብ ያጠረበት ዘመን ነው፡፡ ይህ ዘመን ክፉ ዘመን ነው፡፡
የዘመን ክፋት ሲነሳ ጠቢቡ ሰለሞን “ከፀሐይ በታች አዲስ ነገር የለም” ያለውን ማስታወሱ ተገቢ ነው፡፡ የዘመን ክፋት ዛሬ እንዳልተጀመረና የአሁኑም የመጨረሻው እንደማይሆንም ልብ ማለቱ ጠቃሚ ነው፡፡ ተክርስቶስ ልደት አራት መቶ ዓመታት በፊት ክፉ ዘመን ተከስቶ ድንቁርናን፣ ውሸትን፣ ክህደትን፣ አጭበርባሪነትንና ኢፍትሐዊነትን በእውቀት፣ በፍትህና በመንፈስ ልእልና ሳሙና ለማጠብ የጣረውን ሶቅራጥስን መብላቱን መንገዝብም ትምህርት ነው። ያ ዘመን ሶቅራጥስን እንዲበላ ሶፊስት የተባሉ ፈሪሳዊ የውሸት ካድሪዎችና በእነሱ ስብከት የተወናበደው ሕዝብ የይገደል ድምፅ እንደሰጠ ታሪክ ሲያስታውሰው የሚኖር ነው፡፡ [1]
በዚያ ሶቅራጥስን ቅርጥፍ አድርጎ በበላው ክፉ ዘመን የሰው ልጅ ክፋትና ተንኮል ብዛትና ጥልቀት አስመርሯቸው ገንዘብና ስልጣንን ብቻ ሳይሆን ምድራዊ ዓለምን በጥቅሉ ንቀው ቤተ-አልባ ሆነው፣ ተራቁተውና ተፈጥሮ ያፈራውን እየተመገቡ የሚኖሩ የበቁ ፈላስፋዎች ነበሩ፡፡ እነዚህ ፈልሳፋዎች እየሰረቀ፣ እየቀጠፈ፣ እያጭበረበረ፣ ለባለስልጣን እያጎበደና ጓደኛውን እየከዳ ለገንዘብ አሳልፎ እየሰጠ ገንዘብ አግበስብሶ በአካል “አምሮበት” ተሚኖረው ከንቱ ሕዝብ አንጻር ሲታዩ በአካል እጅግ ተቆማሽደው እሚታዩ ነበሩ፡፡ ለህይወታቸውም ስለማይሳሱ እንደዚያ ዓይነት ሕዝብና አገዛዝ ላወጣው ባህልና ሕግም ተገዥ አልነበሩ፡፡ በእነዚህም ምክንያቶች በዚያ ከንቱ ሕዝብ ሲኒክ(ውሻ) ፈላስፎች ተብለው ተጠሩ፡፡ [2] ከነዚህ የሲኒክ ፈልሳፎች ውስጥ አንደኛው የሲኖፑ ዳዮጅንስ (Diogenes the Sinope) ነበር፡፡ ዳዮጅንስ በዚያን ዘመን ዓለምን አንቀጥቅጦ የገዛው “ታላቁ” አሌክሳንደር ኑሮህን ለማሻሳል ምን ላድርግልህ ብሎ ከተቀመጠበት ሜዳ ሄዶ ሲጠይቀው “ዘወር በል ፀሐይን አትከልክልኝ” ብሎ በማባረሩ ተገርሞ “የዓለም ገዥ አሌክሳንደር ባልሆን ኖሮ የምመርጠው ዳዮጅንስን መሆን ነበር” ብሎ የመሰከረለት የበቃ ሰው ነው፡፡ [3]
ከአራት መቶ ዓመታት በኋላም ክፉው ዘመን ቀጥሎ በፈሪሳውያን ካድሬዎች ስብከት ሕዝብ ተታሎ የሰውን ልጅ ኃጥያት ለማጠብ የመጣውን ክርስቶስ “ስቀለው! ስቀለው !” ብሎ እንዳሰቀለው፣ ሐዋርያው ጴጥሮስ ሳይቀር ሶስቴ እንደካደው ቅዱሱ መጽሐፍ እሚያስተምረው ነው፡፡ [4] የክርስቲያኖች ሰቆቃ ቀጥሎ በቄሳሩ ኔሮ ዘመን ቅዱስ ጴጥሮስና ጳውሎስ አንገታቸውን እንደተቀሉ የሚታወቅ ነው፡፡ [5] ቄሳሩ ኔሮ እንኳን ሌላውን እናቱን፣ ሚስቱንና ወንድሙን ለስልጣን ሲል ገሎ በፈንታው አፈር እስቲበላው በአድር ባይ ሕዝብ ትከሻ ተንጠልጥሎ የኖረ ጉድ ነው፡፡[6]
በዚህ ዘመን ጦቢያም ለስልጣን፣ ለገንዘብና እድሜውን በአምስትም በአስር ዓመትም ለማስረዘም ሲል አገርና ሕዝቡን ብቻ ሳይሆን የትዳር ጓደኛውን፣ ወላጁን፣ ልጁንና ጉደኛውን አሳልፎ መስጠት ስግጥጥ እማይለው እንደተትረፈረፈ የሚታይ ነው፡፡ ሶፊስታዊ ምሁራን ካድሬዎች በአገሪቱና በሌላው ዓለም በዝተው ተባዝተው እንዳሉም እሚታወቅ ነው፡፡ ውርጋጡ ፈርኦን የበግ ለምድ እንደሚለብስ አውልግ ቀበሮ የሙሴን ካባ ደርቦ ሲመጣ “ባህር አሻጋሪውን ሙሴ ተከተሉ” እያሉ ሳይታክቱ የሰበኩ፣ ሕዝብን አታለው መቀመቅ የከተቱንና እንበለ-ሙሲያውያን ብለን የሰምናቸው ለዚህ ምሳሌ ናቸው፡፡ እንበለ-ሙሲያውያን የተባሉትም ሙሴ ሳይኖር ሙሴ መጣ እያሉ በመስበካቸው ነው፡፡ የጦቢያ እንበለ-ሙሲያውያን፤ የጎልጎታ ፈሪሳውያንና የአቴንስ ሶፊስቶች ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ሶስቱም በሰሩት እኩይ ተግባር ራሱን ያጠፋውን ይሁዳን ያህል እንኳ ፀፀት ተስምቷቸው ንስሀ ያልገቡ ናቸው፡፡
እንበለ-ሙስያውያን “የሰውን ልጅ መርጦ ባልተወልደበት ጎሳ ከፋፍሎ በሚያናክስ እርኩስ መንፈስ ተነቅረው ያደጉ ከንቱዎችን በነቢያት ስም እየጠሩና ሕዝብን በስብከት እያወናበዱ ተወንበር ስለሰቀሉ ቅዱሳን መጻሕፍትና ነቢያት የመሰከሩለት የጎመራው የጦቢያ የእምነት፣ የባህልና ታሪክ አዝመራ ተቃጥሎ ምድሪቱን የውሸት፣ የቅጥፈት፣ የሌብነት፣ የክህደት፣ የከርሳምነት፣ የአሕዛብነትና የአረመኔነት አረም እንደለበሰች እሚታይ ነው፡፡
ይህ እርኩስ አረም በጦቢያ ለግማሽ ክፍለ-ዘመን ያህል ስልተዘራ አሁን ያለንበት ዘመን የዳዮጅንስን ዘመን የሚያስታውስ ነው፡፡ ዳዮጆንስ እንኳን ሌላው ሕዝብ በእውቀት የበለጸጉት እነ ፕሌቶ የእውነትና የግብር ሰዎች ሆነው ስላላገኛቸው “የእውነት ሰው ያያችሁ!” እያለ ሲጮህ የኖረና ተሕዝብ መሐል ሆኖ የሰው እርሃብ ሲያሰቃየው የነበረ ሰው ነው፡፡ ሰው ለማግኘትም በቀን ብርሃን ሳይቀር ላንባዲና አብርቶ ይፈልግ እንደነበር ደራሲያን የዘገቡት ነው፡፡ [7] ያኔ አቴንስ ግሪክ ውስጥ እውነተኛ ሰው ፈልጎ ሳያገኝ ያለፈውን ዳዮጀንስን ታሪክ ጸሐፊው ሄሮዱተስ “ወደ ፍትሐዊ ሰዎች አገር ሄደህ ፈልግ” ብሎ ተመቃብር ቢቀሰቅሰውና ወደ ዛሬዋ ኢትዮጵያ ሄዶ ላንባዲናውን ቀንም ሌትም እያበራ ቢፈልግ እውነተኛ ሰው ለማግኘት መቸገሩ እማይቀር ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው የዓባይን እናት ውሀ መጥማቱን፣ ገታም ሙሽ መውለዱን ነው፡፡
ዋቢ (All accessed in March, 2026)
- The Trial of Socrates: https://www.famous-trials.com/socrates/833-h
- The cynics University of Chicago, https://penelope.uchicago.edu/encyclopaedia_romana/greece/hetairai/diogenes.html
- An encounter to remember, Diogenes response to Alexander the Great An Encounter to Remember – Kosmos Society
- The verdict of Pilate ማር 15:15፤ ሉቃ 23:24-25:
- Peter and Paul were killed during the reign of Nero : The Bible Hub https://biblehub.com/library/pamphilius/church_history/chapter_xxv_the_persecution_under_nero.htm
- The Life of Nero:https://penelope.uchicago.edu/Thayer/E/Roman/Texts/Suetonius/12Caesars/Nero*.html
- Diogenes Seeking an Honest Man https://www.artic.edu/artworks/30477/diogenes-seeking-an-honest-man
መጋቢት ፴ ሁለት ሺ አስራ ስምንት ዓ.ም.