ንጉሤ አሊ
ምርጫ ዲሞክራሲያዊ የመንግሥት አስተዳደር በዳበረባቸው አገሮች በህገ መንግሥታቸው በተደነገገው መሰረት ማሕበረሰቡ ሊያስተዳድሩ ይችላሉ ብለው እምነተ የጣሉባቸውን ግለሰቦች ወይንም የፖለቲካ ፓርቲዎችን በመምረጥ ለተወሰነ የገልግሎት ጊዜ ለስልጣን የሚያበቁበት ሂደት ነው ። በመሆኑም መራጩ ሕዝብ ድምጹን የሚሰጠው ያለፈውን ገምግሞ ቀጣዩን ፖሊሲ አይቶና ተገንዝቦ ፍላጎቴን ሊያሟላልኝ ይችላል ላሉት አካል የሚሰጥ ውክልና ማለት ነው ።
እንዲህ አይነቱን ዲሞክራሲያዊ ውክልናን እውን ለማድረግ የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች መሟላት አለባቸው ። ምርጫን ለማካሄድ አስቻይ የሰላምና የጸጥታ ሁኔታዎች ከተሟሉ ምርጫው ነጻና ፍትሃዊ ወይንም ተወዳዳሪነት ያለው እንዲሆን ከተፈለገ የሚከተሉትን ቅድመ ሁኔታዎችን ያሟላ መሆን አለበት ።
1/ ምርጫዎች ከአድሎ የጸዱ መሆን አለባቸው ። የመምረጥ መብታቸው በህግ የተገደበ ያልሆኑ ማናቸውም ዜጎች የመምረጥ መብታቸውን በመተላለፍ እንዲገለሉ ማድረግ አይቻልም ፤
2/ ተወዳዳሪዎች የምርጫ ቅስቀሳ እና ከመራጮቻቸው ጋር የመገናኘት (በአዳራሽ ስብሰባ ወይንም በአደባባይ ሰልፍ) መብታቸው መገደብ የለበትም ፤
3/ ምርጫዎች በመደበኛና በሕገ መንግሥቱ ውይንም በምርጫ ሕጎች በተደነገገ የጊዜ ገደብ እና ሁኔታዎች መካሄድ አለባቸው ፤
4/ የምርጫ ሂደቱን ለመተግበር ኃላፍነት የተሰጠው አካል (የምርጫ ቦርድ) ከሌሎች መንግሥታዊ አካላት በተለይም ከሥራ አስፈጻሚ አካል ሙሉ በሙሉ ነጻና ገለልተኛ መሆን አለበት ፤
5/ ነጻና ሚስጥራዊ የድምጽ አሰጣጥን እና ትክክለኛ ተአማኒነት ያለው ቆጠራ ተደርጎ ውጤቱ ለመራጩ ሕዝብ ይፋ ማድረግ ይኖርበታል ፤
6/ በምርጫ ሂደቱም ሆነ በድምጽ ቆጠራና ሌሎች ከምርጫው ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት ነጻ የሆነ ህግ ትርጓሚ አካላት መኖር አስፈላጊ ነው ፤
እነዚህ ከላይ ከብዙ በጥቂቱ የተጠቀሱት ለዲሞክራሲያዊ ምርጫ አስፈላጊ ቅድመሁኔታዎች ምርጫን ሰላማዊ እና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ አሂዶ የስልጣን ሽግግር ለማድረግ የሚረዱ አይነተኛ መሳሪያዎች ናቸው ።
ወደ አገራችን ኢትዮጵያ ስንመጣ በአሁኑ ተጨባጭ ሁኔታ እነኚህ የምርጫ መስፈርቶች ሊሟሉ ይቅርና ካሁን ቀደም የሚፈጽሙትን ህገ ወጥ የማጭበርበሪያ ምርጫ አይነት ለማክሄድ የሚያስችል ሁኔታ የለም ። ምክንያቱም ኦነግ መር የሆነው የብልጽግና አገዛዝ ተቀዳሚ የመንግሥት ተግባር የሆነውን የሀገርና የሕዝብን ደህንነትና ሰላምን ማስፈን ባለመቻሉ ከአዲስ አበባ ውጭ ያሉ የሀገሪቷ ክፍሎች በሙሉ ከአገዛዙ ቅጥጥር ውጭ ናቸው ። አዲስ አበባም ቢትሆን በህግ ባልተደነገገ የአስቸኳይ ጊዜ ስር ወድቃ በሚሊታሪ እንድትተዳደር ተደርጋለች ።
ጦርነትን የስልጣን ማስቀጠያ ያደረገው የአብይ አህመድ አገዛዝ የስልጣን ዘመኑ ማብቂያው የተቃረበ በመሆኑ ምርጫ ካላካሄድኩ ህጋዊ ቅቡልነት (legitimacy) በተለይም በውጭው ዓለም መንግሥታት አጣለሁ ብሎ ስለሰጋ በማንኛውም መንገድ ለማካሄድ ያለ የለለ ኃይሉን ተጠቅሞ ለማካሄድ አጃቢ ድርጅቶችን በማስተባበር ላይ ይገኛል ።
ከሁሉም በላይ የሚያስገርመው ፣ ውሽትና ቅጥፈትን የአገዛዙ መርህ ያደረገው የአብይ ብልጽግና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ገና ተጠቃሚ ያልሆነውን ሕዝባችንን ምርጫውን በበይነ መረብ እንዲያካሂድ እናደርጋለን እያሉ ማላገጣቸው ነው ። ዶሮን ሲያታልሏት በመጫኛ ጣሏት እንዲሉ ቁጥር ፈብርከው ይህንን ያክል ድምጽ አገኝን ብለው ራሳቸውን ለማታለል ካልሆነ የሚታለል ዜጋ አይኖርም ። በፈቃደኝነት ያጣውን የሕዝብ ድምጽ ራሱን ዋሽቶና አታሎ ተመረጥኩ ብሎ ቢያውጅ እንኳ ዳግም አምስት ዓመት የመግዛት ህጋዊ ቅቡልነት (legitimacy) አገኘ ማለት ስላይደለ በማንኛውም ሰዐት ተገዶ የሚያፈቅራትን ሥልጣን ያጣል ።
የዐማራ የህልውና ትግልና የኦህደድ ብልጽጋና የቅጥፈት ምርጫ ፦
ከላይ በመጠኑም ቢሆን ለመግለጽ እንደሞከርኩት ምርጫ በአንድ ስርአተ መንግሥት የሕብረተሰቡ ድሞክራሲያዊ መብቶች መተግበሪያ አንዱ ህደት እንጂ በራሱ የዲሞክራሲ አልፋና ኦሜጋ አይደለም ። ስለሆነም ነው ከንጉሠ ነገስቱ የሥልጣን ማብቂያ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ብዙ ምርጫዎችን አካሂደን ዲሞክራሲያዊ ስርአትን ማንበር ያልቻልነው ።
የዐማራ ሕዝብ ራሳቸውን የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጭ ድርጅት (ትህነግ) እና የኦሮሞ ነጻ አውጭ ድርጅት (ኦነግ) ብለው የሚጠሩ ጽንፈኛ የጎሣ ድርጅቶች የከፈቱበን መንግሥት መር የዘር ማጽዳት ፣ የዘር ማሳሳትና የዘር ማጥፋት ወንጀልን ለመቋቋም ነፍጥ አንስቶ በመፋለም ላይ ይገኛል ።
የዐማራ ሕዝብ ትግል ራስን ከጥፋት ለመታደግ የሚደረግ ተጋድሎ በመሆኑ ፍትሀዊና የህልውና ትግል ነው ። የህልውና ትግል ደግሞ በህይወት የመኖርና ያለ መኖር ጥያቄ በመሆኑ ለምርጫ የሚቀርብና በምርጫ ሚወሰን ባለመሆኑ ስር ነቀል የሆነ ለውጥ ለማምጣት መታግል አማራጭ የለለው ብቸኛው መንገድ ነው ።
የምርጫ ተሳትፎን አስመልክቶ የዐማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን) መግለጫን አስመልክቶ ፦
የዐማራ ሕዝብ በሁለቱ ጽንፈኛ ድርጅቶች የተቀናጀ ዘርና እምነት ተኮር የዘር ማጥፋት የተጀመረው መንበረ ሥልጣኑን ከተቆናጠጡ ከ1991 ዓም ጀምሮ ቢሆንም የሀገር መከላከያ ሰራዊትና ሎጅስትክን በመጠቀም ግልጽ ጦርነት የተከፈተበት በአብይ አህመድ የሚመራ የኦነግ ብልጽግና ባለ ተራ የጎሣ አገዛዝ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ ነው ።
በሌሎች ክልሎች በተለይም በኦሮሚያ በዐማራ ተወላጆች ላይ ይካሄድ የነበረው የዘር ማጥፋት ዘመቻ አድማሱን አስፍቶ ከነሐሴ 2023 ጀምሮ ከልለው በሰጡት አስተዳደር ግልጽ ጦርነት ታውጆበት በአገር መከላከያ ሰራዊት ፣ በኦሮሚያ ታጣቂዎችና እሾህን በአሾህ እንዲሉ በቅጥረኛ የዐማራ ተወላጆች የተከፈተበን እልቂት ለመመከት የዐማራ ፋኖ የጎበዝ ሀለቃውን እየመረጠ በሚኖርበት አካባቢ ነፍጡን አነሳ ። ያልጠበቀውና ያልተደራጀበት ድንገተኛ የመከላከል ተግባር በመሆኑ እስከ አፍንጫው የታጠቀውን የአገዛዙን ሰራዊት የመገዳደር አቅም ውስንነት ቢኖረውም ከመሳሪያ ጋር ያለው ባህላዊ ቁርኝት የላቀ በመሆኑ ምንም አይነት ስልጠና ሳያስፈልገው ከጠላት እየቀማ በመታጠቅ በሕዝቡ ስንቅ አቀባይነት በተናጥል ማለትም አንድ ማዕከል ሳይኖረው የአገዛዙን ሰራዊት ሶስት አመት ሙሉ መፈናፈኛ አሳጥቶታል ።
የዐማራ ፋኖ በአራቱም ክፍላተ ሀገራት (ሽዋ ፣ ቤተዐምሓራ ፣ ጎንደርና ጎጃም) በተናጥል ሲያካሂዱ የነበረውን የህልውና ተጋድሎ በማቀናጀት አንድ ግዙፍ ድርጅት የዐማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን) በሚል በማቋቋም ትግሉ ማዕከላዊ አመራር ያለው ወጥ እንዲሆን በማድረግ አገዛዙን በማፍረክረክ ላይ ይገኛል ። ሽንፈቱን በጦር ሜዳ የተከናነበው የብልጽግና አገዛዝ ባንዳዎችን በማስኮብለል ፣ የውስጥ ሰርጎ ገቦችን በማስረግ ፣ የማህበራዊ ሚዲያ ሰራዊትን በገፍ በማሰማራት ያልቻለውን ፣ የስልጣን ምንደኞችን በመጠቀም በምርጫ ስም ሊያጭበረብር ቢሞክርም አፋብን እኛም አውቀናል ጉድጓድ ምሰናል እንዳለችው እንሰሳ ቀድሞ በመንቃት መልዕክቱን ወገኑ ለሆነው ዐማራ አውቆም ይሁን ሳያውቅ የጠላትን ተልእኮ ለሚፈጽመው ዐማራ ፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ፣ ለሚዲያዎች እና ለዓለም ህብረተሰብ ጭምር የአገዛዙን የተለመደ የማጭበርበሪያ ምርጫ ያጋለጠና ይህንን ጨፍጫፊ አገዛዝ ከስልጣን እንዲወገድ በመታገል ፋንታ አጅቦ ለዳግም ጭፍጨፋ የአምስት ዓመት ሰርቲፍኬት እንዲያገኝ የሚረዳን ከአገዛዙ ለይቶ እንደማያይና እንድሚታገለው መግለጹ ወቅታዊና ተገቢ መልዕክት ነው ።
የዐማራ ሕዝብ የሚታገለው ተራ የዲሞክራሲ መብቶች እንዲከበሩለት ሳይሆን ተፈጥሮ የለገሰችውን የመኖር መብቱን ሊያሳጡት ከተነሱ ጠላቶቹ ጋር በመሆኑ ይህንን ተጋድሎ ለማደናቀፍ ከሚሞክሩ ኃይሎችም ሆነ ክስተቶች ጋር ጭምር መሆኑን በመረዳት ያወጣውን መግለጫ በትችት ሰበብ ለመኮነን ጥረት የሚያደርጉ ግለሰቦችና ሚዲያዎችን ተገንዝቤአለሁ።
ሕዝባችን የዘር ፍጅት እየተካሄደበት ጭምር ከሰላሣ ዓመት በላይ በሰላማዊ መንገድ ችግሩ እንዲፈታ ጥሯል ፣ ሌላው በዘር ተደራጅቶ እሱ ግን በእብዶች አገር አንድ ጤናማ ካለ እብዱ እሱ ነው እንዲሉ ከኢትዮጵያዊነት ማማ አልወርድም ብሎ እራሱን ለጥቃት እና ለዘር ፍጅት ዳርጓል ። መዘግዬት ይሻላል ከመቅረት እንዲሉ ተደራጅቶ ራሱን መከላከል መጀመሩን እንደ ወንጀል በመቁጠር ሌላ ምክንያት ሲያጡ የብልጽግናን የስልጣን ማራዘሚያ የቅጥፈት ምርጫ በዐማራ ክልል እንዳይካሄድ የማስገንዘቢያ መግለጫ ማውጣቱን እንደ ወንጀል ለመቁጠር የሚዳዳቸው ግለሰቦች ማንነታቸውን ከመግለጽ በዘለለ በዐማራው የህልውና ትግል ላይ የሚያመጡት ቅንጣት ታክል ተጽዕኖ አይኖርም ።
የዐማራ ሕዝብ የሀሰት ትርክት ተፈብርኮበት ፣ በጠላትነት ተፈርጆ ፣ እምነቱ ፣ ባህሉና የማንነት አሻራው እንዲጠፋ መደረጉ አልበቃ ብሎ ከነ አካተው ከኢትዮጵያ መድር እንዲጠፋ ጦርነት ታውጆ ተዘምቶበት ሳይቀር ራሱን ለመከላከል የሚያካሂደውን ፍትኃዊ ተጋድሎ የሚያሰናክል ምርጫን በመቃወም ያወጣውን መግለጫ ተከትሎ በክልሉ ለመወዳደር የተመዘገቡ ሳይቀሩ ውድቅ ማድረጋቸው ትልቅ ውጤት በመሆኑ ተቺ መስለው ለሚያደናግሩ ውሾች ይጮኃሉ ግመሉ ግን ይጓዛል ብሎ ማለፉ የሚበጅ ይመስለኛል ።
ፋኖ ወይንም አንጋፋው ድርጅት አፋብን የዐማራን ሕዝብ ህልውና በመታደግ የኢትዮጵያን ሏላዊነት አስጠብቆ ከሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ጋር በሰላም ፣ በእኩልነት እና ፍትህ በሰፈነባት ሀገር አብሮ ለመኖር የሚታገል መሆኑን በመረዳት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ከፍርኃት ቆፈን ተላቆ በሚቻለው ሁሉ የአብይ አህመድን አፓርታይዳዊ አገዛዝ ለማስወገድ ይድርሻውን መወጣት ይኖርበታል ።
በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪው ዓለም የሚኖር የዐማራ ተወላጅ የተጀመረው የህልውና ትግል በፋኖዎቻችን አሸናፊነት መጠናቀቁ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የመኖር እና ያለ መኖር ጥያቄ መሆኑን ተረድተን ለዐማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ ሁሉ አቀፍ ድጋፍ በማድረግ ለውጤት እንዲበቃ ማድረግ የውዴታ ጊዴታችን ሊሆን ይገባል ። እህታችን የሰብአዊ መብት ታጋይ እና መምህርት መስከረም አበራ እንዳለችው “የዐማራ ሕዝብ የህልውና ትግሉን የግድ ማሸነፍ አለበት ያ ሳይሆን ቀርቶ ቢሸነፍ ሌላው ቀርቶ ባሪያ ሆኖ ለመኖር አይፈቀድለትም “ ።
በአካል በውጭው ዓለም እየኖርክ በመንፈስህ ከእናት ሀገርህ ያልተለየህ ኢትዮጵያዊ ወገኖቼ ፋሺስቱ የብልጽግና አገዛዝ ከምትወዳት እናት ሀገርህ ጋር ያለህን የትስስር ገመድ ለመቁረጥ የማይቻል ሙከራ መጀመሩን በአማካሪው ዳኒኤል ክብረት አማካኝነት ገልጾልናል ። ይሄውም በህይወት ቀርቶ ሞተን እንኳን አስከሬናችን ኢትዮጵያ መቀበር እንደለለበት ሲናገሩ “ማን ሞቶ ባቆያት አገር የዲያስፖራ አስከሬን ከውጭ መጥቶ ይቀበራል “ ሲሉ የብልጽግናን የአስከሬን ክልከላ እቅድ ይፋ አድርገዋል ። ጆሮ ያለህ ስማ አዕምሮ ያለህ አስተውል ይህ አፓርታይዳዊ የብልጽግና አገዛዝ የጥፋት ሴይፉን የመዘዘው በህያዋን ላይ ብቻ ሳይሆን በሙታንም ላይ ጭምር ነው ።