ነፃ ትርጉም – ይነጋል በላቸው (yinegal3@gmail.com)
የግጥሙ ርዕስ – ላሕሚ እንታይ ወሊዳ?
ምንጭ – ethiomedia.com
ላም እሳት ወለደች እንዳትልሰው ፈጃት እንዳትተወውም ልጅ ሆነባት
ከዚህ በታች ያለው ግጥም ከአንድ በትግርኛ የተጻፈ ግጥም ወደ አማርኛ ተርጉሜ ከ10 ዓመታት በፊት በዘሃበሻ ድረገጽ ለንባብ የበቃ ነው፡፡ አሁን ሰነዶቼን ሳገላብጥ አነበብኩትና እንደአዲስ ጣመኝ፤ እናም ለወቅቱ አንባቢያን አንዳች ስሜት ይሰጥ ከሆነ በሚል በድጋሚ ላክሁት፡፡ የተጻፈው በግሩም ኢትዮጵያዊ ትግራዋይ ነው፡፡ በወቅቱ የግጥሙ ባለቤት አሰር የጻፈልኝን የምሥጋና ኢሜልም ለግንዛቤ ያህል አያይዠዋለሁ፡፡ ዛሬ ዛሬ የሕዝቡ የጽሑፍ አስተዋፅዖና የንባብ ተሣትፎ እጅግ የወረደ ቢሆንም ያኔ የዛሬ አሥር ዓመትና ከዚያም በፊት ልዩ ነበር፡፡ አሁን ግን በስማም እንደተባለበት ሰይጣን ሁላችን ፈዘንና ደንግዘን እንደእንስሳ ከዕለት ጉርስ ከዓመት ልብስ ባላለፈ የሕይወት ጣጣ ውስጥ ተጠምደናል፡፡ ይህ አቢይ የሚባል ዐውሬ ልጅ የአንዲትን ታላቅ ሀገር ሕዝብ መተት በሚመስል ትብታብ ጠፍንጎ ወደ የዱርና የቤት እንስሳነት ለወጠን፡፡ የተራራ ናዳን የመበልጥ ችግርና ሰቆቃ እላያችን ላይ ተከምሮብን ምንም ሳይመስለንና ሳናንገራግር ፀጥ ረጭ ብለን እንኖራለን፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው በአንድ በኩል ስናስበው ደናቁርቱ ዘረኛ ገዢዎቻችን በዘር፣ በሃይማኖት፣ በጥቅማ-ጥቅምና በቋንቋ ስለከፋፈሉን መሆኑ አይካድም፡፡ መጨረሻው ይናፍቃል፡፡ አንድ ሞራለቢስ ከይሲ በምን ችሎታው እንዲህ እንዳደረገን ሲያስቡት ግራ ያጋባል፡፡ እርሱ ውስጥ የመሸገው እርኩስ መንፈሳዊ ኃይል ልዩ ነው፡፡ ምናልባት ይህ ሁሉ ውርጅብኝ የአቢ አቅም ነው ብሎ የሚያስም ይኖር ይሆናል፡፡ በውሸትና በተጭበረበረ የትምህርትና የሚሊተሪ ማዕረጎች የተጀቦነው የሰባተኛ ክፍል ምሩቅ አቢይ አህመድ በዐርባ ዓመት የተቅበዘበዘ የዕድሜ ተሞክሮ ይህን ሁሉ የክፋት ጥግ ያሳያል ብሎ መገመት ያስቸግራል፡፡ የሆነ ነገርማ አለው ወገን፡፡ አንድ አቢ ብቻውንና በራሱ አቅም ይህን ሁሉ ትንግርታዊ የውድመትና ጥፋት ተዓምር በስምንት ዓመታት ውስጥ ሊያከናውን ፈጽሞ አይችልም፡፡ ከሥሩ የደረደራውም ሁሉ ከርሱ የማይሻሉ ማይማንና ደናቁርት በመሆናቸው እንግሊዝኛ በመሰሉ የባዕዳን ቋንቋዎች ይቅርና በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንኳን ራሳቸውን መግለጽ የማይችሉ ተብታባ የአእምሮ ስንኩላን ናቸው፡፡ ለማንኛውም መልካም ንባብ፡፡
* * *
አጉል ዘመን ገጥሟት በረት ብትከሳ፤
ከብቶች በመዥገሮች አዩ ብዙ አበሳ፡፡
ጡቶቿን አቃጣይ የነበልባል ጥጃ ላም እሳት ወለደች፤
ብ’ተው በማይተዋት ዘልለው ባልጠገቡ ወይፈኖች ነደደች፡፡
የከበረው ባህል ባለጌ ረጋግጦት እንደጨው ቀለለ፤
ወፍ ዘራሾች ነግሠው ባጥለቀለቁት ደም ምድር ተበከለ፡፡
አዎ፣ ላም እሳት ወለደች!
እንደዮዲት ጉዲት እቶኑ የሚፋጅ ፤
ዕረፍት በማያ’ቅ ሠይፍ እንደነደርቡሾች እንደግራኝ አህመድ፤
ጭንቅላትን ገምሶ አንገትን ቆራርጦ ዜጎችን የሚያነድ፡፡
“አጥንትና ደሜ ይሄው የናንተው ነው፤
እኔ ከሌለሁኝ እናተም እንዲያው ነው፤
እርቧችሁ ጠግቤ፣ ብድንም ሞታችሁ፤
ማንም ስለሌለ ከኔ ‘ሚለያችሁ፤
እስከመጨረሻው አጅቡኝ ባካችሁ፡፡ ”
እያለ እሳት ጥጃው ሕዝብን ይማጠናል፤
መስሎት የማናውቀው ቁርበት ዘርጉ ይላል፡፡
ክፋትና ተንኮል ተፈጥሮው የሆነ፤
ሕግና ሥርዓትን ባዋጅ ያወደመ፤
የሰው ገላ ችቦ አንድዶ የሞቀ፤
ቆላ ደጋ ሳይል ሰደድ የለቀቀ፤
በገጠር ከተማ ቋያ ያዘነመ፤
ሁሉንም በመዝረፍ ራቁት ያስቀረ፤
መላ ከብትን ሸጦ በረት ያራቆተ፤
በዝረፍ እንዝረፍ የደንቆሮ ስብከት ሞኝን ያጃጃለ፤
ያልበላውን ዕዳ ትውልድ እንዲከፍል ቢል ያስተላለፈ፤
የሶላቶ ውላጅ ምድረ የሹምባሽ ልጅ፤
የባንዳ ጥርቅም የናት አንጀት በጣሽ፤
ላም እሳት ወለደች ታቅፎ የማይሳም ሣጥናኤልን ወራሽ፡፡
አዎ፣ ባንዳ ነገሠና ብዙ ታምር ታዬ፤
ጥላቻ ተዘርቶ ትርምስ በረዬ፤
ፍትህ ዐይኗ ጠፍቶ ዜጋ ተሰቃዬ፡፡
የከርቸሌ በሮች ሌት ተቀን ተከፍተው፤
ፍርድ ተገልብጦ ከሌለው ወዳለው፤
ይሉኝታና ሀፍረት ካድማስ ማዶ ርቀው፤
የ’ውነቱ አንገት ጠፍቶ ማተብ ማስቀመጫው፤
ተኖሮ ተሙቶ “አለን” እንላለን ላለፍ ላገደመው፡፡
እንጂ፤ ተቸግረን እንጂ እውነት ጠፍታብነ፤
ተሳስረን እንጂ ነው ፍትህ ወድማብነ፡-
ስርቆት ባህል ሆኖ እያስመሰገነ፤
ውሸት ጽድቅ ሆኖ ሃቅ እያስኮነነ፤
ክብር ውርደት ሆኖ ውርደት ሲሆን ክብር ፤
መች እናይ ነበረ ፍርድ እየተዛባ ስትፈራርስ ሀገር?
ከደጓ ላም ማኅጸን የተወለደው’ሳት፤
ኦሮሞን ካማራ ትግሬን ከኤርትራ አኙዋኩን ከኑዌር፤
ሊያናቁር ሊያናክስ ሊያደርጋቸው ጠላት፤
ነሰነሰ መርዙን ለሩብ ም’ት ዓመታት፡፡
ስለዚህ ወገኔ ትግራዩ ተነሣ፤
“በቃኝ!” በለውና ባንዴራህን አንሳ፤
ለመብትህ እምቢ በል ትግሉን ተቀላቀል፤
ዮሐንስ ይኩራብህ አሉላም አይፈር፤
የወንድሞችህ ደም ያንተም ደም ነውና፤
በምታውቀው ትግል የአርዮስን አረም ከሥሩ በመንቀል፤
የተሻመንከው ሕዝብ በሃሤት ይፈንድቅ፣ አብሮህ እልል ይበል፡፡
የጋራ ጠላትን በሚጠራርገው የማይቀር ጎርፍ ላይ፤
ምራቅህን ጨምር ታሪክ ተለውጦ እውናዊ ነፃነት በተግባር እንዲታይ፡፡
ማጠቃለያ
- የኦሮሞው ደም፣ የአማራው ደም፣ የኮንሶው ደም፣ የጋምቤላው ደም የትግራይ ሕዝብ ደም ነው!
- ህወሓትለአሁኒቷ ኢትዮጵያ ችግሮች ተባብሶ መቀጠልና ለውድቀታችን ዋና ተጠያቂ ነው!
- ህወሓትሳይውል ሳያድር ከሥልጣን ይወገድ!
- (ሁሉንም ወገን የሚያሣትፍ) ዴሞክራሲያዊየሽግግር መንግሥት አሁኑኑ በሀገራችን ይመሥረት!