ተከሳሾችም በፍ/ቤቱ ታሪክ ይቅር የማይለው ፣ የቆሸሸ ፣ አሳዛኝና አሳፋሪ እንዲሁም ፍርደ ገምድል የሆነ የፖለቲካ ውሳኔ ነው በማለት በእጅጉ ማዘናቸውን ለማወቅ ተችሏል።
አውሎግሶን አንድነት-Awulogson Andinet ፣ ሀምሌ 1/2017 ፣ አዲስ አበባ- ኢትዮጵያ
በእነ የተከበሩ ዮሃንስ ቧያሌው መዝገብ በሌሉበት የተከሰሱትን 36 ሰዎችን ጨምሮ 52 ተከሳሾች የተካተቱበት ሲሆን ከእነዚህም መካከል 16 የሚሆኑት ሂደቱን በማ/ቤት ሆነው እየተከታተሉ ይገኛሉ።
በእስር ላይ እያለ ባጋጠመው የጤና መታወክ ምክንያት ካልተገኘው ከ46ተኛ ተከሳሹ አማረ መለሰ በስተቀር 15 የፖለቲካ እና የሕሊና እስረኞች በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ተገኝተዋል።
1) አማራን እና የአማራ የፖለቲካ እስረኞችን ስም በማጥፋት ወንጀል ተከሶ እና በተደጋጋሚም እንዲቀርብ ትዕዛዝ ተጽፎለት በእንቢተኝነት ፍ/ቤት ለመገኘት ያልቻለውን የኦህዴድ ብልጽግና አገዛዝ አክቲቪስትን በተመለከተ ውሳኔ ለመስጠት ፣
2) በፌደራል ፖሊስ የተወሰዱ የተከሳሾች ንብረቶች እንዲመለሱ በሚል በተደጋጋሚ ትዕዛዝ ቢሰጥም ምላሽ ያልተሰጠበትን ጉዳይ በተመለከተ እና
3) በመጨረሻም ዐቃቤ ሕግ ማንነቱ ሳይጠቀስ በድብቅ ከመጋረጃ በስተጀርባ ሆኖ ይመስክርልኝ ሲል ባቀረበው አቤቱታ ላይ በከሳሽ ዐቃቤ ሕግ እና በተከሳሽ ጠበቆች መካከል የተደረገውን ክርክር መርምሮ ብይን ለመስጠት በሚል ለሀምሌ 1/2017 ቀጠሮ የተያዘ መሆኑ ይታወሳል።
በዚህም መሰረት ፍ/ቤቱ የአክቲቪስት ስዩም ተሾመን ጉዳይ በተመለከተ ከሰዓት እናየዋለን በማለቱ እንዲሁም የንብረት ጉዳይን በተመለከተ በተደጋጋሚ እንደሚያደርገው የጠራ ምላሽ ሳይሰጥበት አድበስብሶት አልፏል።
በመቀጠልም ማንነቱ ያልተገለፀ ምስክር ከመጋረጃ በስተጀርባ ሆኖ ይመስክርልኝ ሲል ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን አቤቱታ በሙሉ ድምፅ በመቀበል ለ2 ዓመት ያህል በግፍ እስር ላይ በሚገኙ ተከሳሾች ላይ ተደብቆ ይመስክርባችሁ የሚል ውሳኔ ማሳለፉን ችሎቱ አሳውቋል።
ተከሳሾችም በፍ/ቤቱ ታሪክ ይቅር የማይለው ፣ የቆሸሸ ፣ አሳዛኝና አሳፋሪ እንዲሁም ፍርደ ገምድል የሆነ የፖለቲካ ውሳኔ ነው በማለት በእጅጉ ማዘናቸውን ለማወቅ ተችሏል።
ከመጋረጃ በስተጀርባ በመሆን ሊመሰክር አይገባም በሚል ያቀረቡትን በርካታ ሕጋዊ የመከራከሪያ ነጥቦችን ሁሉ ውድቅ በማድረግ ነው ከ15 ዓመት እስከ እድሜ እና ሞት ያስቀጣል በሚል ለቀረበው የሽብር ክስ ነው በመጋረጃ ተጋርዶ በድብቅ ይመስክርባቸው ሲል ፍ/ቤቱ የወሰነው።
አማራነትን የወነጀለው ክስ የተቀነባበረ እና የፈጠራ ፖለቲካዊ ክስ መሆኑ በግልጽ እየታወቀ በአገዛዙ ጫና እና አስፈጻሚነት ስር በወደቀው ፍ/ቤት ይህ ብዙዎችን ያስገረመና ያሳዘነ ውሳኔ ተወስኗል።
ተከሳሾችም በጉዳዩ ላይ መክረን ምላሽ እንሰጣለን ማለታቸው እንዳለ ሆኖ ፍ/ቤቱ መጋረጃው እና ማንነቱ ያልታወቀው “ይታያል ከሩቁ” ሲል ዐቃቤ ሕግ ቅጽል ስም የሰጠው ምስክር ተዘጋጅቶ ሀምሌ 9/2017 እንዲመሰክር ሲል ትዕዛዝ ሰጥቷል።
አቻምየለህ ታምሩ