እሁድ፣ ሚያዝያ ፲ ፰ ቀን ፳ ፻ ፲ ፰ ዓ. ም. (04/26/2026)
ጭምቅ ሃሳብ
አሁን ኢትዮጵያ ያለችበትን የፖለቲካ ሁኔታ፤ ማንኛውም የወገኑ ሁኔታና የአገሩ ጉዳይ የሚያሳስበው ሁሉ፤ አደጋ የከበበው እና በጣም አስጊ መሆኑን ይረዳል። በዚህ ጽሑፍ፤ ይሄን አሁን ያለንበትን ተጨባጭ እውነታ፤ ገዢው ቡድን ምርጫውን ለማካሄድ የተነሳበት ምክንያት፣ ሕዝቡ ለመምረጥ ያለው ፍላጎት፣ እና የፖለቲካ ድባቡ እያወጀ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ይመረመራል። የታሰበው ምርጫ ትርጉምና ሂደት፣ በትክክል ሕዝቡን የማሳተፉ ጉዳይ እና የሚከተለው ውጤት ምን እንደሚሆን ይተነተናል። የተወዳዳሪዎች መሯሯጥ እና የብልፅግና ትክክለኛ ተወዳዳሪ ሆኖ መቅረብ ይታያል። በርግጥ ለውጥ፤ የረጅም ጊዜ ሕዝባዊ ትግል ውጤት በመሆኑ፤ ማንኛውም ሕዝባዊ ተቃውሞ ባደባባይ የሚገለጥበትን መንገድ ማደናቀፍ ስለማይገባ፤ በምርጫው የመሳተፉ ጉዳይ፤ የየግል ድርጅቶች መብት ሆኖ፤ ለሕዝብ አጉል ተስፋ መሥጠቱ ግን፤ በተለይም፤ “እኛ እናቸንፋለንና ለኛ ድመጽ!” ሥጡን ማለቱ፤ ተገቢ አለመሆኑን በትክክል መረዳት ያስፈልጋል። እያንዳንዱ መራጭ፤ ግለሰቡ ባለበት የኑሮ ሁኔታ ስለሚወስን፤ ብዙዎች ትክክለኛ አማራጭ በሌለበት ሀቅ፤ ብልፅግናን ቢመርጡ፤ የማንም ጥፋት ተደርጎ ሊወሰድ፤ ወይንም ምርጫው ትክክለኛ ተብሎ ሊወሰድ አይገባም። ትክክለኛ ምርጫ የሚካሄደው፤ ነፃ መራጭ ሕዝብ ኖሮ፣ ይሄው መራጭ ሕዝብ ከፍላጎቱ አንጻር፣ አማራጮች ቀርበውለት፣ እያንዳንዱ ግለሰብ ያለግዴታ፤ በፈቃዱ የፈለገውን የሚመርጥበት ሀቅ ሲኖር ነው። ይህ ደግሞ፤ ነፃ መራጭ አለ! ብለው ሌሎች ስለተናገሩ ሳይሆን፤ ራሱ ነፃ ነኝ! ብሎ ለመምረጥ ፈቃደኛ ሆኖ የሚቀርብ ሲኖር ነው።
መግቢያ
ለአንድ ምርጫ ወሳኝ የሚሆኑ አስፈላጊ ጉዳዮች አሉ። የመጀመሪያው ጉዳይ፤ ሰላም በአገር መኖር ነው። ቀጥሎ ደግሞ፤ በመራጩ ሕዝብ እና ምርጫውን በሚያካሂደው ሥልጣን የጨበጠ አካል መካከል ያለው ግንኙነት ነው። በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ የመራጩ ሕዝብ እምነትና ፍላጎት ይቀርባል። ከዚያ፤ የምርጫው ሂደት፣ ተመራጮችና ብቃታቸው፣ ምርጫውን የሚያካሂደው አካል ሀቀኝነት ይመጣሉ። እኒህ ቀጥለው ሲመረመሩ፤ እስከዛሬ የተካሄዱትን ምርጫዎች ማገናዘብ ግድ ይሆናል። ይህ ሁሉ በተጨባጭ እየተደረጉ ካሉ እውነታዎች አኳያ ይመዘናል።
የምርጫ ክንውን ታሪክ በአገራችን
ለአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ምርጫ የሚለው ጉዳይ፤ ቀደም ሲል በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን፤ ለፓርላማ የሚመረጡ ሰዎች፣ ምረጡኝ! እያሉ በሕዝቡ መካከል ዘመቻቸውን ሲያደርጉ ነው። እናም ላለፉት ስድሳና ሰባ ዓመታት፤ የምርጫ ክንውን በተደጋጋሚ ወቅቱን ጠብቆ ሲመጣ ነበር። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ለፓርላማ የሚወዳደሩ እጩዎች አሉ። በርግጥ በደርግ፣ በትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር፤ አሁን ደግሞ በተረኛው የብልፅግና ጊዜ ተመሳሳይ የምርጫ ሂደት፤ በአገራችን ተሰምቷል። የትክክለኛ ምርጫ ሽታው ቀርቧቸዋል የተባሉት እንኳ፤ ውጤታቸው ምን እንደሆነ ታዝበናል። ለምሳሌ የቅንጅት መወዳደርና አቸናፊዎቹ ለእስር ቤት መዳረግ፤ ሁሉን ግልጥ አድርጎ ይነግረናል።
ለዚህ ታሪካችን ዋና መሠረቱ፤ ምርጫውን የሚያካሂደው አካልና፣ ተመርጦ አቸናፊ ለመሆን የተነሳው አካል፤ አንድ መሆኑ ነው። ተመራጩ እና የምርጫው ሂደት ባለቤት አንድ አካል በሆነበት ጉዳይ፤ ምን ዓይነት የምርጫ ሂደት ሊኖር ይችላል? “ምርጫ አለ!” መባሉ ብቻውን በቂ አይደለም። ምርጫው በትክክል መካሄዱ ወሳኝ ነው። እስካሁን ድረስ የምርጫ ታሪካችን የሚነግረን፤ ደርግ፤ ምርጫ አዘጋጅቶ ደርግ አቸነፈ! የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር፤ ምርጫ አዘጋጅቶ ራሱ አቸነፈ! አሁንም ተረኛው ብልፅግና በተለያዬ ስም አዘጋጅቶ፤ ራሱ አቸነፈ! ነው። እናም፤ የቀረበልን ምርጫ አቸናፊው ከወዲሁ ይታወቃል።
በትክክል በአገራችን የታሰበው ምርጫ፤ በሌሎች ተመሳሳይ የአስተዳደር ዘይቤ ከሚከተሉ መንግሥታት የተለዬ አይሆንም። በሌሎች አገራትና ከላይ እንዳሰፈርኩት በራሳችንም አገር ምርጫ ሲካሄድ፤ ሁለት ጎልተው የሚታዩ ነፀብራቆች አሉ። የመጀመሪያው ትክክለኛው ሂደት ሲሆን፤ ሌላው ለውጪ መንግሥታትና ታዛቢዎች ተሞሽሮ የሚቀርበው ድግስ ነው። በዚህ ድግስ፤ ሀቀኛ ለመምሰልና ትክክለኛ ምርጫ እንደሚካሄድ ለማሳየት ጥረቱ ኃያል ነው። የመግለጫ ጋጋታ፣ የአዋጅ ነጎድጓድ ይደረደራል። በአሁን ሰዓት፤ “የቴዎድሮስ ካሣሁንን ዘፈን አዳምጣችኋል!” በሚል ሰዎች እየታሰሩ ባለበት አገር፤ በሕግ የሰፈረውን እና የምርጫ ቦርዱ ያቀረበውን እንመልከት።

“2. የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፓለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011
ምርጫን ፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባን እና ተያያዥ ሥነ ምግባርን የሚገዛው ህግ “የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፓለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011” ተብሎ ይጠራል። አዋጁ ሦስት ቀደም ሲል የነበሩ የተለያዩ ህጎችን ማለትም የኢትዮጵያ የምርጫ ህግ አዋጅ ቁጥር 532/1999፣ የተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 573/2000 እና የፓለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 662/2002 በመሻር በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነሐሴ 18 ቀን 2011 ዓ.ም. ፀድቆ ሥራ ላይ ውሏል።
የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ የተሻሻለበት ዓላማ ምርጫ ሁሉን አቀፍ፣ ነፃ ፍትሃዊና ሰላማዊ እንዲሆን ለማድረግ፣ የዓለም አቀፍ የምርጫ መርሆችን አካቶ እንዲይዝ ለማስቻል፣ ዜጎች በቀጥታና በነፃነት በመረጧቸው ተወካዮች እራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ስልጣናቸውን በተግባር ላይ ለማዋል፣ ፓለቲካ ፓርቲዎች የፓርቲ ፕሮግራምና ዓላማቸውን ማራመድ እንዲችሉ፣ ዜጎችና ፓርቲዎች በምርጫ ሥርዓት ውስጥ የሚኖራቸውን መብትና ግዴታ ለመደንገግ እና ለምርጫ ሂደት ለሚነሱ አለመግባባቶች አስተዳደራዊ እና የዳኝነት መፍትሄ የሚሰጡ ተቋማትን እና አሰራራቸውን ለመወሰን ነው። የምርጫ ህጉ በዋናነት ስለ ምርጫ ደንብና መርህ፣ ስለፓለቲካ ፓርቲዎች፣ ስለምርጫ ታዛቢዎችና የመራጮች ትምህርት አሰጣጥ፤ በምርጫ ስለሚነሱ አቤቱታዎች እና ክርክሮች እና ስለምርጫ ሥነ ምግባር የሚተነትኑ ዋና ዋና ክፍሎችን ይዟል።”
መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ! ይሏል እንዲህ ነው። “ሁሉን አቀፍ” ሲል፤ ዐማራን አይመለከትም። ትግሬን አይመለከትም። አክራሪ ኦነግ በሚንቀሳቀስበት ያለውን ኦሮሞ አይመለከትም። የደቡብ ኢትዮጵያ ፋኖ በሚንቀሳቀስበት የለውን አይመለከትም። ፍትሃዊ ሲል ደግሞ፤ ዘፈን ማዳመጥ ወንጀል በሆነበት ተጨባጭ እውነታ ውስጥ ነው።
ሰላም
በአሁኑ ሰዓት በአገራችን በኢትዮጵያ ውስጥየ ያለውን የሰላም ሁኔታ የሚያውቅ የለም። ገዢው ቡድን፤ ያለጦርነት አልኖርም! በሚል መመሪያ፤ ሰላም እንዳይኖር በየቦታው ጦርነት እየጫረ ነው። በአገራችን እየተካሄዱ ያሉት ጦርነቶች በሙሉ፤ ይሄ አብይ መራሹ የአክራሪ ኦሮሞ ገዢ ቡድን የፈጠራቸው ናቸው። በትግራይ ክልል፤ ብልፅግና በዚያ አካባቢ ስላም እንዳይኖር፤ የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባርን ከሁለት ከፍሎ፤ አንዱን ደግፎ ሌላውን ጠላት አድርጎ፣ በመካከልከሁለቱም የሌለ ሌላ አስተዳዳሪ መድቦ፤ ሕዝቡን ለስቃይና መከራ ዳርጎታል። የማያልቅ ጦርነት በቦታው ተንሰራፍቷል። በዐማራ ክልል፤ በዐማራ ላይ የዘር ማጥፋት ዘመቻ ከፍቷል። ትምህርት ቤቶችን የጦር ምሽግ፣ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶችን እስር ቤቶች፣ የሃይማኖት ተቋማትን መሪ አልባ፤ አድርጓቸዋል። በአንጻሩ፤ ሕዝቡ በቃኝ! ብሎ ቀኝ እጁ የሆነውን ፋኖን መሪ አድርጎ ተነስቷል። በኦሮሞ ክልል፤ ራሱ በፈጠረው የአስተዳደር ብልሹነት፤ አንድም ራሱ ያስታጠቀው ቡድን ሕዝብን እየገደለና የፈለገውን እያደረገ ነው። ሌላም ከብልፅግናው የበለጠ አክራሪ ታጥቆ ተነስቶ፤ ሕዝቡን ቁም ስቃይ እያሳዬ፣ በራሱም በብልፅግና ላይ ተነስቶበታል። በትክክል በአገራችን ያለውን የጦርነት እውነታ የሚገልጥ ምስል ላቅርብ፤

በኢትዮጵያ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎችና የግንኙነት አሰተሳሰራቸው
ይህ ነው እንግዲህ በአገራችን ያለው የሰላም ሁኔታ።ስምምነት
የመራጩና የአስመራጩ ግንኙነት
አስመራጩ፤ ሁላችን እንደምናውቀው፣ የመንግሥትን ሥልጣን የጨበጠው፣ የአክራሪ ኦሮሞ ገዢ ቡድን ነው። ሌላ ስሙ፤ የኦሮሞ ብልፅግና ነው። ምርጫው የሕዝብ ባለቤትነት የለውም። እናም ሕዝቡ፤ ባለቤት ባለሆነበት ምርጫ እንዲሳተፍ ነው የተፈለገው። ባለጉዳዩ፤ ብልፅግናና ብልፅግና ብቻ ነው። ተፎካካሪ ድርጅቶች ያዘጋጁት ወይንም ባለቤት የሆኑበት ጉዳይ አይደለም። የፈለገው ብልፅግና ነው። አጀንዳው የዚሁ ድርጅት ነው። እናም ሕዝቡ፤ ተደረገ ለማስባል የቀረበ ተጎታች ነው። ስለዚህ ምርጫው ትክክለኛ ምርጫ አይደለም። ሕዝቡ ነፃና ፈቃደኛ ሆኖ ያልተሳተፈበት ምርጫ፤ ትክክለኛ ምርጫ ሊሆን አይችልም። ይህ ነው፤ ምርጥ በተባለው ሕዝብ እና ራሴን ለማስመረጥ ደግሻለሁ ብሎ የተነሳው ቡድን ግንኙነት። ባጭሩ፤ምርጫውን የሚያካሂደው አካል ሀቀኝነት የለውም። እናም ሕዝቡ ገዢውን አካል አያምነውም።
የመራጩ ሕዝብ እምነትና ፍላጎት
“ምረጥ!” ተብሎ እየተገደደ ያለው ሕዝብ ዋና ፍላጎቱ፤ በሰላም ውሎ ማደር፣ ሕይወቱን ለነገ ለማብቃት መብላትና መጠጣት፣ ሥራ ማግኘት፣ ማረስና ገበያ መውጣት፣ በጥቅሉም መኖር ነው። ሲኖር፤ ማስብ ይችላል። ማስብ ሲችል፤ የአገርን ጉዳይ የኔ ብሎ፤ በኅብረተሰቡ ክንውን ይሳተፋል። አሁን ሕዝቡ ሰላም እፈልጋለሁ እያለ ነው። ብልፅግና ሰላምን የማይገኝ የቅንጦት ዕቃ አድርጎታል። ሕዝቡ በዚህ አብይ መራሽ የአክራሪ ኦሮሞዎች ገዢ ቡድን ላይ ምንም ዓይነት እምነት የለውም። እናም ምርጫው የራሱ ጉዳይ ስላልሆነ፤ እንዴት አድርጌ አልፈዋለሁ! ነው እያሰበ ያለው። ብልፅግናም ሕዝቡን አስገድጄ እንዴት በ99.99% አቸናፊ እባላለሁ! ነው ስሌቱ። ታዲያ ይሄ በምን ሂሳብ ምርጫ ይባላል! አንዳንድ ማጣቀሻዎችን ላቅርብ። ይህ ከገዢው ቡድን የምርጫ ቦርድ የተገኘ ነው። ምርጫዎችን አስመልክቶ ለቀረበለት ጥያቄ የተሠጠውን መልስ እንመልከት።
ጥያቄ – የፓለቲካ ፓርቲዎች የፀጥታ ሁኔታን አስመልክቶ የሚያቀርቡትን አቤቱታ ቦርዱ ምን ምላሽ ሰጥቶታል?
መልስ – የጊዜ ሰሌዳው ከመውጣቱ አስቀድሞ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፓለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተከታታይ ምክክሮች ማድረጉ ይታወሳል፣ በዚህም መሰረት የተነሱት ዋና ዋና ጉዳዮች ሁለት ሲሆኑ አንደኛው ፓርቲዎች እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ አለብን የሚሉት ችግሮች ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ያሉ የፀጥታ ችግሮች ናቸው። ያንን መሰረት አድርጎ የጊዜ ሰሌዳ ከመውጣቱ አስቀድሞ ቦርዱ ሁለት ዋና ዋና ተግባራትን አከናውኗል። አንደኛው በመንግስት በኩል የምርጫ ጸጥታ እቅድ ዝግጅት እንዲኖር እና ቦርዱ ምርጫን የተመለከቱ እቅዱ ቴክኒካዊ መረጃዎችን እና ሁኔታዎችን ያካተተ እንዲሆን በሂደቱ በመሳተፍ ማረጋገጥ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በየክልሉ ያሉ በፓርቲዎች የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት የሶስትዮሽ መድረክ ማዘጋጀት ነው፣ በዚህም መሰረት በየክልሎቹ ፓርቲዎች የሚያጋጥማቸውን ችግር ለመፍታት የሶስትዮሽ ውይይቶች መከናወን ጀምረዋል።እነዚህ ውይይቶች እስከአሁን ሶስት ክልሎች ላይ የተደረጉ ሲሆን በዚህ ውይይትም ገዥው ፓርቲ፣ በክልሎቹ የሚንቀሳሰቀሱ ፓርቲዎች እንዲሁም ቦርዱ ተገኝተው ዝርዝር አቤቱታዎች ላይ ውይይት በማድረግ መፍትሄዎች ላይ መስማማት ላይ እንዲደርሱ ጥረት እየተደረገ ነው። እነዚህ አሰራሮች ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ይረዳሉ ብሎ ቦርዱ ያምናል።
ይሄ ከላይ ከተወሰደው ጥቅስ ጋር አብሮ የተቀመጠ መረጃ ነው።
የምርጫው ሂደት
ከላይ ከነኃላፊው አካል ምልክት ቀድቼ ያስቀመጥኩት፤ በሕግ የሠፈረውን ነው። ነገር ግን ቃላት በራሳቸው እውነት ቢሆኑ፤ በኢትዮጵያ የሚደረገው የምርጫ ዝግጅትና ሂደት፤ የወርቅ ዋንጫ ያገኝ ነበር። ነገር ግን፤ ከላይ ባቀረብኩት የምርጫ ታሪክ፣ የአስመራጩና የሕዝቡ ግንኙነት የሚነግረን ሌላ ታሪክ ነው።
አብይ መራሹ የአክራሪ ኦሮሞዎች ገዢ ቡድን፤ በፈለገው ጊዜ፣ በፈለገው ቦታ፣ በፈለገው ዓይነት መንገድ ምርጫውን አዘጋጅቷል። የአገሪቱን ንብረት፣ መንግሥታዊ መዋቅሩን፣ እያንዳንዱን ከምርጫ ጋር የተያያዘ ግለሰብ (ከተፎካካሪ እጩዎች በስተቀር) ይዟል። እያንዳንዱን የዜና ማሰራጫ መድረክ ተቆጣጥሯል።
ተመራጮችና ብቃታቸው፣
ለማንኛውም ውድድር፤ ተወዳዳሪዎችን የሚያቀርብ አካል፤ ለዚያ ቦታ ብቃት አላቸው፣ ሕዝቡም ይሄንን አውቆ ይመርጣቸዋል! የሚል እምነት ኖሮት ነው። በብልፅግና የሚታየው ግን፤ የፓርቲ አባል የሆነ፣ ከላይ የሚወርድለትን የሚፈጽም ሰው ብቻ እንዲሆን ነው እየተደረገ ያለው። እናም በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነቱ፤ በምርጫ አዘጋጁ በኩል በግዴታ የተወሰነ ነው፤ የማዳበሪያ እቀባ፣ በመንግሥት ጥቁር ሰነድ ውስጥ የመግባትና ሌሎች ማስፈራሪያዎች ናቸው ተመራጩን ያጀቡት። ስለዚህ፤ ብቃት ሳይሆን አገልጋይነት ነው መለኪያው። በተፎካካሪዎች በኩል፤ ሊወዳደሩ በተፈቀደላቸው የምርጫ ቦታዎች ሁሉ፤ ከብልፅግና ተወዳዳሪ እጅግ የላቁና ለቦታው ብቁ የሆኑ ይቀርባሉ። ጉዳዩ ደግሞ ምርጫ ተካሄደ ለማስባል እንጂ ትክክለኛ ምርጫ ለማካሄድ ስላልሆነ፤ ባንድ መንገድ ሆነ በሌላ ማደናቀፊያዎችን በማስቀመጥ፤ ተደማጭነታቸውን ብሎም ተቀባይነታቸውን ለማሳነስ ብልፅግና ቆሞ ተነስቷል። ሚዛኑ የመብቃት ሳይሆን አገልጋይ ሆኖ የመገኘት ነው።
ምርጫው ለሕዝቡ ምን ፋይዳ አለው?
በመጨረሻም ጥያቄው፤ ምርጫው ለሕዝቡ ምን ፋይዳ አለው? የሚለው ነው። በመራጮቹ በኩልና በተመራጮቹ በኩል፤ ደፋሮች የሚያምኑበትን በተቻለ መጠን ለመግለጥ የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ። የአብይ መራሹ የአክራሪ ኦሮሞዎች ገዢ ቡድን በበኩሉ፤ ምርጫውን እንዳዘጋጀው የራሱ መጨፈሪያ መድረክ ያደርገዋል። ውሻውም ይጮኻል፤ ግመሏም ትጓዛለች እንደተባለው፤ አምባገነኑም ራሱን ወደሰማይ ከፍ ያደርጋል። ሕዝቡም ብሶቱን አንግቦ ውስጥ ውስጡን እንደ ረመጥ በስሎ በመጨረሻ ይነሳል። ሕዝብን ያቸነፈ ኃይል የለም። በሥልጣን ላይ የተቀመጠ፤ በተግባሩ የወንበሩ ይወሰናል። ብልፅግናን በተግባሩ ስንመዝነው፤ አንድ ሐሙስ ቀርቶታል።