ኤፍሬም ማዴቦ(emadebo@gmail.com)
ኢትዮጵያ የምትገኝበት የአፍሪካ ቀንድ የአለማችን ኃያላን አገሮች፣ታሪካዊ ጠላቶቻችንና ከፍተኛ የገንዘብ ክምችት ያላቸው አገሮች አይናቸውን የጣሉበትና ለረጂም አመታት ከቀውስ፣ ከግጭትና ከጦርነት ተላቅቆ የማያውቅ ቀጣና ነው። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ አፍሪካ ቀንድ ላይ ትልቋ አገር ኢትዮጵያ ደሞ በነጋበጠባ የብሔር ግጭት የሚከሰትባትና አእርስ በርስ ጦርነት ተላቅቃ የማታውቅ አገር ናት። የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ሥልጣን ላይ በቆየባቸው ባለፉት ሰባት አመታት ኢትዮጵያ ውስጥ የጥይት ድምጽ ያልተሰማበት ግዜ የለም። በ2011 እና በ2012 ዓም ሱማሌና ኦሮሞ፣ሱማሌና አፋር፣ጉጂና ጌዲኦ፣ቦረናና ገሪ ተዋግተዋል። ከጥቅምት 2013 እስከ ህዳር 2015 ድረስ የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግስትና የህወሓት ኃይሎች የብዙዎችን ህይወት የቀጠፈና ከፍተኛ ንብረት ያወደመ ጦርነት አካሂደዋል። ይህ ጦርነት ቆሞ ስድስት ወር በማይሞላ ግዜ የፌዴራል ኃይሎች ሌላ ዙር ጦርነት ከአማራ ኃይሎች ጋር ጀምረዋል፣ ዛሬ ይህ ጦርነት ሦስተኛ አመቱን ይዟል። ትግራይና ኦሮሚያ ክልሎች ፌዴራሉ መንግስት የማይቆጣጠራቸውና፣ የታጠቁ ኃይሎች ያሰኛቸውን ሁሉ የሚያድርጉባቸው ክልሎች ናቸው። ጋምቤላ ድንበር ጥሰው የሚመጡ ኃይሎች ንብረት የሚዘርፉበት፣ ዜጎችን አፍነው የሚወስዱበትና የሚገድሉበት ክልል ነው።
አገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ሳምንታት የማህበራዊ ሜዲያውንና የትልልቆቹን የአለማችን ሜዲያዎች ትኩረት ስባ ነበር። ትኩረቱ የኤኮኖሚ ዕድገት፣የአዳዲስ ማዕድኖች መገኘት ወይም ኢትዮጵያ የአፍሪካን ዋንጫ አሸነፈች ወይም ወደ አለም ዋንጫ አለፈች የሚል ሁላችንንም የሚያስደስት መልካም ዜና አይደለም። ይልቁንም ትኩረቱ በአንድ በኩል ኢትዮጵያ የተባበሩት አረብ ኢሜሬትን ትዕዛዝ ተቀብላ ለጄኔራል ሃምዳን ደጋሎ ኃይሎች የማሰልጠኛ ቦታ መስጠቷ ሲሆን፣በሌላ በኩል ደሞ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወታደርና ብዛት ያለው ከባድ የጦር መሳሪያ ወደ ትግራይ ድንበር እያስጠጋች መሆኗ ነው። ይህ በኢትዮጵያ መንግስትና በትግራይ ኃይሎች መካከል ይጀመራል ተብሎ የተፈራው ጦርነት የቀጣናውንና የአካባቢዉን አገሮች ብቻ ሳይሆን፣ እነዚህ ሁለት ኃይሎች ከ2013 እስከ 2015 ድረስ ለሁለት አመታት ባካሄዱት ጦርነት ትግራይ፣አፋርና አማራ ክልል ውስጥ የተፈጸመውን እጅግ በጣም ዘግናኝ የሆነ የዘር ማጽዳትና የጦር ወንጀል በቅርብ የተመለከተውን የአለም ህዝብ ሁሉ አስጨንቋል።
ለመሆኑ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ወደ ትግራይ የሚተመው ለምንድነው? የትግራይ ህዝብ የሚፈልገው ከረሃብ መገላገል፣ተፈናቅሎ ከሚኖርባቸው አካባቢዎች ወደ መኖሪያ ቦታው መመለስና ባጠቃላይ የሁለት አመቱ ጦርነት ካደረሰበት የኤኮኖሚና የስነልቦና ቁስል ማገገም ነው እንጂ እንደገና የጦርነት እሳት ውስጥ መግባት አይደለም፣ ደሞም ከትግራይ ጋር በሚደረገው ጦርነት በሁለቱም ወገን የሚሞተውና የሚቆስለው ኢትዮጵያዊ ነው፣በሁለቱም በኩል የሚወድመው ኃብትና መሰረተ ልማት የኢትዮጵያ ኃብትና መሰረተ ልማት ነው። ይህ ሁሉ እየታወቀ ለምንድነው ጠሚ አቢይ አህመድ የፖለቲካ ልዩነቶችን ሁሉ በጦርነት ብቻ ለማስወገድ እዚህም እዚያም የሚሯሯጠው? እኛስ ጦርነት የማንፈልግና የአገራችን አንድነትና ሉዓላዊነት ከምንም ነገር በላይ የሚገደን ኢትዮጵያዊያን መቼ ነው ጠሚ አቢይ አህመድን ነገረ ስራህ ሁሉ ጦርነት ብቻ ከሆነ በቃ አንፈልግህም ብለን፣አገራችን ኢትዮጵያን ለሁሉን አቀፍ የሽግግር ሂደት የምናዘጃት?
የብልጽግና ፓርቲ ደጋፊዎችን ጨምሮ ይህንን ጽሁፍ የሚያነብ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ከወገንተኝነት ተላቆ የኢትዮጵያን ጥቅምና ፍላጎት ብቻ እየተመለከተ እንዲመልስ የምፈልጋቸው ሦስት ጥያቄዎች አሉኝ፣ የመጀመሪያው ጥያቄ የኢትዮጵያ መንግስት ወደ ትግራይ ድንበር ወታደር የሚያስጠጋው ለምንድነው፣ከህወሓት ኃይሎች ጋር ለመዋጋት ከሆነ ለምንድነው ከህወሓት ጋር የምንዋጋው? ሁለተኛው ጥያቄ- ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ መንግስትና የህወሓት ኃይሎች ያደረጉት የሁለት አመት መራራ ጦርነት የተቋጨው በፕሪቶሪያ ስምምነት ነበር። የፕሪቶሪያው ስምምነት ደሞ ስምምነቱ በተፈረመ በ30 ቀን ውስጥ የህወሓት ኃይሎች ከባድና ቀላል መሳሪያቸውን ሙሉ በሙሉ መፍታት አለባቸው ይላል። ዛሬ የፕሪቶሪያው ስምምነት ከተፈረመ ሦስት አመት አልፎታል፣ ለምንድነው የህወሓት ኃይሎች ትጥቃቸውን እንዳይፈቱ የተደረገው ወይም የህወሓት ኃይሎች በስምምነቱ መሰረት ትጥቃቸውን ላለመፍታታቸው ተጠያቂው ማነው? ሦስተኛው ጥያቄ- የኢትዮጵያ ጦር አማራ ክልል የገባው የአማራን ኃይሎች በኃይል ትጥቅ ለማስፈታት ነው። ኢትዮጵያን የህልውና አደጋ ውስጥ የከተተውንና በአለም አቀፍ ደረጃ ስምምነት ተደርሶ ትጥቁን ይፍታ የተባለውን ህወሓትን ትጥቅ ለማስፈታት ስንዝር መራመድ ያልፈለገው ጠሚ አቢይ አህመድ፣ ሰኞ የክልል ልዩ ኃይሎች ትጥቃቸውን ይፍቱ የሚል ህግ አውጥቶ ማክሰኞ መሳሪያ ተሸክሞ አማራ ክልል ድረስ የዘመተው ለምንድነው? እዚህ ላይ ማሳሰብ የምፈልገው፣ አቢይ አህመድ ጦሩን አማራ ክልል ሲያዘምት በአንድ በኩል ትጥቁን ይፍታ የተባለው ህወሓት አስካፍንጫው እንደታጠቀ ነው፣ በሌላ በኩል ደሞ ኦሮሚያ ክልል ከ200ሺ በላይ ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀ ልዩ ኃይል ነበር።
የዚህ ጽሁፍ ጸሃፊ ኢትዮጵያ ውስጥ ከአገር መከላከያ ሠራዊት ውጭ የታጠቀ ሰራዊት በየትኛውም ክልል ውስጥ መኖር አለበት ብሎ አያምንም፣ክልሎች የሚያስፈልጋቸው ሰላምና ጸጥታ የሚያስከብር የፖሊስ ኃይል ነው እንጂ የታጠቀ ሠራዊት አይደለም። ትግራይና ኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ እስካፍንጫው የታጠቀ የክልል ልዩ ኃይል መኖር በዛሬዋ በብሔር በተከፋፈለችና የብሔር ፖለቲካ በነገሰባት ኢትዮጵያ ውስጥ ለአማራው ህዝብ የህልውና ስጋት ነው። የእነዚህ ሁለት ክልሎች ልዩ ኃይል ትጥቁን ሳይፈታ የአማራ ልዩ ኃይል ትጥቁን ይፍታ የሚለው ጥያቄ አዎንታዊ መልስ ያገኛል ብሎ መጠበቅ የሰሜን ኢትዮጵያን በተለይ የአማራውን ባህል አለማወቅ ነው። ይህ አለማወቅ ነው ላለፉት ሦስት አመታት አማራ ክልል ውስጥ ወንድማማቾች ጎራ ለይተው እርስ በርስ እንዲተላለቁ ያደረገው፣ይህ የራስን አገር አለማወቅ ነው ኢትዮጵያን የመበታተን አደጋ ውስጥ ይዞ እየገባ ያለው!
ህወሓት ከማዕከላዊው መንግስት ጋር ሲዋጋ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው የኃይል አሰላለፍና ዛሬ የፌዴራል መንግስትና የአማራ ኃይሎች ሲዋጉ ያለው የኃይል አሰላለፍ በጣም የተለያዩ ናቸው። ህወሓቶች ከፌዴራል ኃይሎች ጋር የተዋጉት እንደገና አራት ኪሎን ለመቆጣጠር ስለነበር ይህንን የማይፈልግ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ከፌዴራል መንግስት ጎን ተሰልፏል። ለማስታወስ ያክል፣ እስከ ፕሪቶሪያው ስምምነት ድረስ ከህወሓት ጋር የተጋፈጠውና ከተለያዩ ክልሎች የተሰባሰበው የኢትዮጵያ ኃይል “የጥምር ኃይሎች” እየተባለ ነበር የሚጠራው። የህወሓት ኃይሎች የሰሜን ዕዝን በተኛበት ጨፍጭፈው ጦርነቱ ከተጀመረ ጀምሮ እስከ ፕሪቶሪያው ስምምነት ድረስ የኤርትራ ኃይሎች ከኢትዮጵያ ጎን መቆማቸውንና ኢትዮጵያን ከትልቅ አደጋ ማዳናቸውን ጠሚ አቢይ በራሳቸው አንደበት ፓርላማ ውስጥ በማያሻማ ቋንቋ የተናገሩት እውነት ነውና እዚህ ላይ መድገም የሚያስፈልግ አይመስለኝም። ዛሬ በሚመታው የጦርነት አታሞ ግን የኤርትራ ኃይሎች በታሪክ ለሁለተኛ ግዜ ከህወሓት ኃይሎች ጎን ሊቆሙ እንደሚችሉ የሚያሳዩ መረጃዎች እዚህም እዛም ብቅ እያሉ ነው። ለምንድነው ከ2013-2015 ከፌዴራል ኃይሎች ጎን ተሰልፈው ኢትዮጵያን ከትልቅ አደጋ የጠሚ አቢይ አህመድን መንግስት ደሞ ከውድቀት ያዳኑት ፋኖና ኤርትራ ዛሬ በጠላትነት የተፈረጁት? ጠሚ አቢይ ፓርላማ ውስጥ ውለታቸውን ምንግዜም አንረሳውም ያለለት የኤርትራ መንግስት ዛሬ ከህወሓት ጋር ተሰልፎ ኢትዮጵያን እንዲወጋ ያነሳሳው ምንድነው? እንደ ዛፍ ቅጠል ከነፈሰው ሁሉ ጋር አብረን ከምንነፍስ እነዚህን ጥያቄዎች ጠሚ አቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጣበት ግዜ ጀምሮ ማድረግ ሲገባው ካላደረጋቸውና፣ማድረግ ሳይገባው ካደረጋቸው ነገሮች ጋር አያይዘን መመለስ አለበን።
የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተጀምሮ በተካሄደባቸው በመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ ወራት የአለም አቀፉ ማህበረሰብና የህወሓት ደጋፊዎች ትልቁ ጩኸት የኢትዮጵያ መከላከያ በአስቸኳይ ትግራይን ለቅቆ ይውጣ የሚል ነበር። በሰኔ ወር 2013 ዓም የኢትዮጵያ መከላከያ ትግራይን ለቅቆ ከወጣ በኋላ ግን የህወሓት ኃይሎች አርፈው ትግራይ ውስጥ አልተቀመጡም። እንዳውም ከአማራው ጋር የምናወራርደው ሂሳብ አለ ብለው ወደ አማራና አፋር ክልሎች ጉዞ የጀመሩት መከላከያ ትግራይን ለቅቆ ከወጣ አንድ ወር በማይሞላ ግዜ ውስጥ ነው። ይህንን የተመከተው የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት የአማራ ፋኖን ጨምሮ በየክልሉ ለሚገኘው ልዩ ኃይል የአገር አድን ጥሪ ሲያቀርብ፣ጥሪውን ሰምተው በፍጥነት ከፌዴራል ኃይሎች ጋር ሆነው ከህወሓት ኃይሎች ጋር በጀግንነት ተዋግተው መስዋዕትነት ከከፈሉ ኃይሎች ውስጥ ግንባር ቀደሙ ኃይል የአማራ ፋኖ ነው። ለምሳሌ፣ የህወሓት ከፍተኛ የመሳሪያ ክምችትና ተዋጊዎች የሚገኙበት ስትራቴጂያዊዉ የጋሸና ምሽግ የተሰበረው የፋኖ ኃይሎች በጨበጣ ገብተው በከፈሉት ትልቅ የህይወት መስዋዕትነት ነው።
ይህንን እውነት በተመለከተ ጠሚ አቢይ አህመድ ምስክርነታቸውን ሲሰጡ እንዲህ ነበር ያሉት- “ፋኖ ለአማራም ለኢትዮጵያም ኩራት ነው፣ይህ ምንም ጥያቄ የለውም፣በጀግንነት ተዋግቷል፣በጀግንነት ይዋጋል ለወደፊትም” ታዲያ ዛሬ ምን ነክቷቸው ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩና የሜዲያ አርበኞቻቸው ፋኖን የሻዕቢያ ተላላኪ እያሉ የሚጠሩት? ምን ተአምር ተፈጥሮ ነው በአንድ ወቅት ከፌዴራል መንግስት ጎን የተሰለፉትና ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ፓርላማ ውስጥ ያመሰገኗቸው ፋኖና ሻዕቢያ ዛሬ አንዱ ላኪ ሌላው ተላላኪ ሆነው ከፌዴራል ጦር ጋር የሚዋጉት? ለመሆኑ ፋኖ ነው ከፌዴራል መንግስት ጋር ውጊያ የጀመረው ወይስ የፌዴራሉ መንግስት ነው አማራ ክልል ድረስ ሄዶ ጦርነት የጀመረው? ደሞስ ማነው ተላላኪው? ካልገደልኩህ ሲባል አትገድሉኝም ብሎ እራሱን የሚከላከለው ፋኖ ነው ተላላኪ ወይስ የኤምሬቱ ፕሬዚደንት ሼክ መሐመድ ቤን ዛይድ አድርግ የሚለውን ነገር ሁሉ አሜን ብሎ የሚያደርገው አቢይ አህመድ ነው ተላላኪው? እነዚህን ጥያቄዎች ከስሜታዊነት ተላቅቀን በሰከነ አዕምሮ መመለስ ስንጀምር ነው ጠሚ አቢይ አህመድ በኢትዮጵያ እንደ አገር ቀጣይነት ላይ የጣለው አደጋ ፍንትው ብሎ የሚታየን።
ባለፉት ሁለት አመታት ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት አለባት የሚለው ሃሳብ አገር ውስጥም ከአገር ውጭም የብዙ ኢትዮጵያዊያንን ልብ ሰቅዞ የያዘ ሃሳብ ነው፣በነገራችን ላይ የብልፅግና ሜዲያ ሠራዊት ነገሩን ወደ አንድ ጫፍ ብቻ እየወሰደው ትርጉም ስለሚያሳጣው ነው እንጂ፣ኢትዮጵያ የባህር በር ያስፈልጋታል በሚለው ሃሳብ ላይ በኢትዮጵያዊያን መካከል ልዩነት ያለ አይመስለኝም፣ ልዩነታችን እንዴት ነው የባህር በር የምናገኘው የሚለው ጥያቄ ላይ ነው። ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት አለባት እንደሚለው አጀንዳ የጠሚ አቢይ አህመድን መንግስት የዲፕሎማሲ ጨቅላነት በተግባር ያሳየ ሌላ ምንም ኩነት ያለ አይመስለኝም። ይህ አጀንዳ ከጂቡቲ፣ከኤርትራ፣ከሶማሊያ ሪፑብሊክና ከሶማሌ ላንድ ጋር ሆድና ጀርባ እንድንሆን አድርጎናል። ኢትዮጵያ የባህር በር አገኘች “እንኳን ደስ ያለን” ተባብለን ከሶማሌ ላንድ ጋር የተፈራረምነውን ሰነድ የፊርማው ቀለም ሳይደርቅ ቀድደን ለመጣል ተገድደናል።
በቀላሉ የማይወጣው የፖለቲካና የኤኮኖሚ አጣብቂኝ ውስጥ የገባው ጠሚ አቢይ አህመድ፣ የባህር በር ጥያቄን የመሰለ የኢትዮጵያን ህዝብ የልብ ትርታ የሚጨምር ጥይቄ ይዞ የመጣው በእርግጥ ለኢትዮጵያ ጥቅም አስቦ ነው ወይስ ለራሱ የፖለቲካና የሥልጣን አጀንዳ የኢትዮጵያን ህዝብ ከጎኑ ለማሰለፍ ነው? የኢትዮጵያ ህዝብ ይህንን ጥያቄ ከስሜታዊነት ተላቅቆ ምክንያታዊ ሆኖ መመለስ አለበት። በፍጥነት እያደገ የሚሄድ 130 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ኢትዮጵያ የባህር በር ያስፈልጋታል በሚለው ሃሳብ ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይስማማል። የባህር በር ያስፈልገናል ሲባል ግን ያበደ ሰው አራት ኪሎን ተቆጣጥሮ ከጎረቤቶቻችን ሁሉ ጋር ካልተዋጋሁ ሲል አብረነው መዝመት ያለብን አይመስለኝም። 35 አመት ያለ ባህር በር ኖረናል፣ሌላ አምስት አመት ያለ ባህር በር መኖር አያቅተንም፣ለአቢይ አህመድ ሌላ አምስት አመት ከሰጠነው ግን፣የምናወራው ስለ ባህር በር ሳይሆን ስለኢትዮጵያ እንደ አገር መቀጠልና አለመቀጠል ይሆናል። እንዲህ አይነቱ የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች ኪሳራ ውስጥ ከመግባታችን በፊት ማድረግ የሚገባንን ሁሉ አድርገን የጠሚ አቢይ አህመድን የቁልቁለት ጉዞ ማስቆም አለብን። እኛ ኢትዮጵያዊያን በእርግጥም የባህርበር የምንፈልግ ከሆነ የዚህ ትልቅ አገራዊ ግብ እንቅፋት ጠሚ አቢይ አህመድና እሱ የሚመራው ብልፅግና ፓርቲ ናቸውና በፍጥነት ልናስወግዳቸው ይገባል። ኢትዮጵያ ትግራይ፣ አማራና ኦሮሚያ ውስጥ ከራሷ ጋር እየተዋጋች በሌላ በኩል ደሞ የባህር በር ማግኘት አለብን በሚል ከጎረቤት አገር ኤርትራ ጋር የምትዋጋ ከሆነ ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት የሚያቅት አይመስለኝም። እንኳን በአገር ደረጃ በቤተሰብ ደረጃም እርስበርሱ የሚባላ ቤተሰብ ከጎረቤት የሚሰነዘርበትን ጥቃት መከላከል አይችልም።
ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ ቁም ስቅሉን የሚያየው ዙሪያውን በጦርነትና በግጭት ተከብቦ ወጥቶ መግባት ባለመቻሉ ብቻ አይደለም። ጠሚ አቢይ አህመድ ተው ይቅርብህ ተብሎ ሲለመን አሻፈረኝ ብሎ ተግባራዊ ያደረጋቸው አውዳሚ የኤኮኖሚ ፖሊሲዎች በፈጠሩት የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነትም ነው። በአቢይ አህመድ ኢትዮጵያ ውስጥ በየቀኑ እየተመዘዘ የሚያድግ ነገር ቢኖር የዕቃዎች ዋጋ ነው፣ በዚህ የተነሳ የመንግስት ሰራተኞች ትርፍራፊ ፍለጋ ሆቴል ቤት በራፍ እየሄዱ ደጅ መጥናት ጀምረዋል። ለወትሮው በማህበረሰቡ ውስጥ የከፍተኛ ኑሮ ምልክት የነበሩ የህክምና ዶክተሮች የቤት ኪራይ መክፈል አቅቷቸዋል። ኢትዮጵያ ከ5 ሚሊዮን በላይ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ያሉባት አገር ናት፣አማራ ክልል ያሉ ብዙ ትምህርት ቤቶች ወታደራዊ ካምፕ ሆነዋል። ዘጠኝ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ወደ ትምህርት ቤት አይሄዱም፣ለዚህ ዋናው ምክንያት ጦርነት፣የኑሮ ውድነት፣የተመጣጠነ ምግብ እጥረትና መፈናቀል ነው። እስከመቼ ነው እኛ ኢትዮጵያዊያን የፖለቲካ፣የኤኮኖሚና ማህበራዊ ኑሯችንን የምድር ላይ ሲዖል ያደረገብንን ሰው ተሸክመን የምንጓዘው? በምዕራብ በኩል ጎረቤታችን የሆነው የሱዳን ህዝብ አልበሽርን ያባረረው የዳቦ ዋጋ ተወደደ ብሎ ነው፣የኬኒያው ፕሬዚደንት ሩቶ ከአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ጋር ተስማምቶ ተግባራዊ ለማድረግ ያሰበውንና እኛ አንገታችንን ደፍተን የተቀበልነውን ፖሊሲ፣የኬንያ ህዝብ በነቂስ ወጥቶ እምቢ በማለቱ ፕሬዚደንቱ ሳይወዱ በግዳቸው ፖሊሲውን ሰረዘዋል።እኛ ምን አይነት ፍጡሮች ብንሆን ነው የርስበርስ ጦርነቱን፣የኑሮ ውድነቱን፣ድህነቱን፣ረሃቡን፣ መፈናቀሉን፣ዝርፊያውን፣አፈናዉንና ግድያውን አንድ ላይ ተሸክመን በቃ የማንለው?
የኢትዮጵያ ህዝብ የጠሚ አቢይ አህመድን መንግስት ከሚገባው በላይ ታግሷል፣ይህ ትዕግስቱ ደሞ ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለው ነው። አገር ውስጥና በውጭ አገሮች የሚኖረው ኢትዮጵያዊ የኢትዮጵያ መንግስት ከአማራ-ፋኖና ከኦነግ-ሸኔ ኃይሎች ጋር ተደራድሮ በሁለቱ ክልሎች ውስጥ የሚካሄደው ጦርነት እንዲቆም ማድረግ አለበት እያለ በሚጮህበት በአሁኑ ወቅት፣ ጠሚ አቢይ አህመድ ጭራሽ ሦስተኛውን የእርስ በርስ ውጊያ ግንባር ለመክፈት ወታደርና የጦር መሳሪያ ወደ ትግራይ ድንበር እያስጠጋ ነው። በባሌም በቦሌም የባህር በር ማግኘት አለብን በሚል ከኤርትራም ጋር ጦርነት ለመግጠም ዝግጅት እንደተጀመረ የሚያሳዩ ብዙ መረጃዎች አሉ። በየጦሩ ግንባር ተሰልፎ የህይወት መስዋዕትነት የሚከፍለው ወጣት፣የዚህ ወጣት ወላጆችና ባጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ለምንድነው ትግራይ፣አማራና ኦሮሚያ ክልል ውስጥ እርስበርስ የምንዋጋው? ከኤርትራስ ጋር በሰላማዊ መንገድ ቁጭ ብለን ተደራድረን በሰጥቶ መቀበል ሂደት የባህር በር ማግኘት እያቻልን ለምንድነው ወደ ጦርነት ውስጥ የምንገባው ብሎ እራሱንም መንግስትንም መጠየቅ አለበት፣ ከሁሉም በላይ ደሞ የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ችግሮችን ከጦርነት ውጭ በሌሎች አማራጮች ለመፍታት ለምን እንደማይሞክር መጠየቅ አለበት። መንግስት ህዝብ በአደራ የሰጠውን ሥልጣን ተቀብሎ አገርን ያስተዳድራል እንጂ የአገር ባለቤት አይደለም፣ ብቸኛ የአገር ባለቤት ህዝብ ነው። መንግስት ህዝብ በአደራ የሰጠውን ሥልጣን አግባብ ባለው መልኩ ካልተጠቀመና ጭራሽ ይህንኑ ሥልጣን ተጠቅሞ ህዝብን የሚረግጥና የሚበድል ከሆነ፣ህዝብ የአገር ባለቤትነት ሥልጣኑን ተጠቅሞ እንዲህ አይነቱን መንግስት የማስወገድ ተፈጥሮአዊ መብት አለው። የኢትዮጵያ ህዝብ ይህንን ተፈጥሮአዊ መብቱን ለመጠቀም ከአሁን የተሻለ ግዜ ያለ አይመስለኝም. . . . . ይህንን ማድረግ ተስኖን ለጠሚ አቢይ አህመድ ቀን በሰጠነው ቁጥር ተፈጥሮአዊ መብታችንን መጠቀም የምንችልበት አገር ላይኖረን ይችላል!!!