31/01/2026
የዐማራ የህልውና የትጥቅ ትግል በጎበዝ አለቃ አመራር ሰጪነት ተጋድሎውን ከጀመረ እነሆ አራት ዓመት አስቆጥሯል ። የዐማራ ፋኖ ያለ መሪ ድርጅትና ትጥቅ በጀመረው ራስን የመከላከል ውጊያ ታንኩንም ባንኩንም የተቆጣጠረውን አፓርታይድ አገዛዝ መውጫና መግቢያ አሳጥቶት ሰራዊቱን ከጥቅም ውጭ አድርጎበታል ።
“ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው” እንዲሉ ሆድ አደር የዐማራ ተወላጆችን ፣ የኦህዴድ ብልጽግና ካድሬዎችን እና ጎጠኞችን በፋኖ ውስጥ አስርጎ በማስገባት ልዩነት እየፈጠረ “ማምሻም አዳር ነው” በሚል ፈሊጥ እየከፋፈለ እድሜውን ለማራዘም ቢጥርም በቆራጥ የዐማራ ልጆች ጥበብ በተሞላበት ስልታዊ አካሄድ ውስጡን እያጠራ አንድነቱን በማጠናከር ላይ ይገኛል ።
ያለፉትን ድክመቶች አንስቼ አንዱን በማጀገን ሌላውን ለመኮነን ፍላጎቱም ሆነ የሞራል ልዕልና ስለሌኝ ያንን ለታሪክ ጸሓፊዎች እተወውና ይህቺን አነስተኛ የግል አስተያዬት ለመስጠት ወደአነሳሳኝ የምስራች እገባለሁ ።
ከሁሉ በማስቀደም የዐማራን የቁርጥ ቀን የበኩር ልጅ የዐማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን) በመውለድና በማዋለድ የተሳተፋችሁ ዐማራዊያን ወገኖቼ ከፍ ያለ ወገናዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ ። አፋብን የተመሰረትው እንዲሁ አልጋ በአልጋ አይደለም የህይወት መስዋዕትነት ተከፍሎበታል ፤ ሀብት ንብረት ወድሟል ፤ የድሉን ቀን አራዝሞታል ፤ በአርበኞች መካከል መቃቃርንም ፈጥሯል ።
ይህ ሁሉ ዋጋ ተከፍሎም ቢሆን ወደሚፈለገውና ወሳኙ አንድነት በመምጣቱ ቅንና ሀቀኛ የዐማራ ተወላጆች ደስታችንን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ገልጽናል በመግለጽም ላይ እንገኛለኝ ።
ውድ የተከበራችሁ አፋብንን በመውለድና በማዋለድ የተሳተፋችሁ ዐማራዊያን ወገኖቼ “መውለዱንማ እበትም ትል ይወልዳል” ተብሎ እንዳይተረትብን ወሳኙ እና እልህ አስጨራሹ ተግባር ኮትኩቶ ማሳደጉ በመሆኑ የእለ ተእለት ስራችሁ መሆን ያለበት በስነምግባር እንዲያድግ ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል የሚል እምነት አለኝ ።
በተለይ አንድነቱ እውን እንዲሆን በሽምግልና የተሳትፋችሁ የዐማራ ምሁራን ወገኖቻችን አረረም መረረም፣ ቀጠነም ወፈረም የድርሻችንን ተወጥተናል ብላችሁ ፈረሱንም ሜዳውንም ለቃችሁ ተመልካች መሆን አለባችሁ የሚል እምነት የለኝም። ይህንን ስል ከላይ ሆናችሁ አመራር ስጡ እያልኩኝ አይደለም ነገር ግን እኛ ማንዴታችንን ጨርሰናል ካሁን በኋል እንደ ፍጥርጥራችሁ በማለት ነገረ ዓለሙን እርግፍ አድርጋችሁ እንዳትተውት ለማሳሰብ ፈልጌ ነው ።
መዋቅር ዘርግተው ፣ የስራ ኋላፊነታቸውን ተከፋፍለው የሚመለከታቸውን የስራ ድርሻ ይዘው ለተጠያቂነትና ግልጽነት ቦታ ሰጥተው ወደ ተግባር ለመግባት ጊዜ ያስፈልጋል ። ይህ እስከሚሆን መሰራት ያለባቸው ጉዳዮች መተግበር አለባቸው ነገር ግን ከልምድ ማነስም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች ጥቃቅን የሚመስሉ ነገር ግን ድርጅቱን ሊጎዱ የሚችሉ ስህተቶች ሲፈጠሩ ወዲያውኑ የማስተካከያ ሀሳቦችን በማቅረብ እርምት እንዲደረግ የማድረጉን ተግባር ያሸማገሉት ምሁራን ቢያደርጉ አግባብ ነው የሚል እምነት አለኝ ።
ለምሳሌ ፦
ሀ/ “ከአያያዝ ይቀደዳል ከአነጋገር ይፈረዳል” እንደሚባለው መግለጫዎች በሚወጡበት ወቅት ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፣ አድማጭን እና ተመልካችን ብሎም ድርጅቱን የሚመጥን መሆን አለበት ፣ ባለፈው ሚዲያን በተመለከተ የወጣው መግለጫ ጫጫታን ፈጥሯል ወቅታዊ ማብራሪያ መሰጠት ይኖርበት ነበር በዝምታ ነው የታለፈው ። ዲያስፖራን በተመለከት ተገቢ ያልሆነ የቃላት አጠቃቀም ከአፋብን አመራር የማይጠበቅ ተነግሯል መታረም አለበት ዲስፕልን ያስፈልጋል ። የራስን ጓድ አርበኛ ወይንም ፋኖ ብሎ መጥራት ቢከብደው እንኳን ስሙን ጠርቶ መናገር ሲገባው ስም የለሽ ይመስል በተደጋጋሚ “ግለሰቡ” ማለት አግባብ አይደለም ራስንም ስለሚያስገምት ሊመከር ይገባል።
ለ/ የአንድ ትልቅ የዐማራ ድርጅት አመራር የሆነ በማህበራዊም ሆነ መደበኛ ሚዲያዎች ላይ ለሚጽፈውም ሆነ ለሚናገረው ጉዳይ የግሌ ነው ያሻኝን እላለሁ ማለት የማይችል ስለሆነም ሊነገረው ይገባል ።
ሐ/ በሚዲያዎች ቀርቦ ቃለ ምልልስ ማድረግን በተመለከተ ማንኛውም ሚዲያ የሚያውቀውን ፋኖ እየጋበዘ ስለ ትግሉም ሆነ ስለድርጅቱ እንዲያብራራ ማድረግ አግባብ አይደለም ከአሁን ቀደም ወጥ አመራር ባለመኖሩ ሲደረግ እንደነበረው መሆን የለበትም ። አሁን መሆን አለበት ብዬ የማምነው እያንዳንዱ የኃላፊነት መስክ የራሱ አመራር ስላለው በዚያ መሰረት የተመደብ ሰው ቢሆን መልካም ነው ምክንያቱም ሁሉም ሰው ሁሉን ነገር ያውቃል ማለት አይደለም እና ነው ።
መ/ ከፋኖዎቻችን መካከል ማህበራዊ ሚዲያዎችን የሚጠቀሙ አሉ ያ ክፋት አለው እያልኩኝ አይደለም ነገር ግን አንድ በአፋብን የታቀፈ ፋኖ እኔ ሀሳቤን የመግለጽ መብት አለኝ በሚል ሽፋን ያልተገቡ ነገሮችን በማቅረብ ስህተት እንዳይፈጽም ሊመከር ይገባል ።
ሠ/ ዲያስፖራ ጋር የሚኖርን ግንኙነት አስመልክቶ ካለፈው ስህተት በመማር ተወካዮችን ሲመርጡ ወይንም ሲወክሉ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ሊመከሩ ይገባል ። በውጪው ዓለም የዐማራ ጉዳይ ያገባኛል ብለው ራሳቸውን አደራጅተው የአቅማቸውን አስተዋጽዖ የሚያደርጉ የዐማራ ማኅበራት እያሉ ከምንም ሳይቆጠሩ ሌላው ቀርቶ ምክረሀሳብ እንኳን ሳይጠየቁ በተለያዩ ትውውቆች ተጠሪ እየሰየሙ መተመመን እንዳይኖርና ድጋፍ እንዳይደረግ በር የከፈተ መሆኑ ታውቆ በዚህ ጉዳይ የማኅበራትን ምክረ ሀሳብ ጠይቀው ሰዎችን ቢመድቡ መተማመን ይኖራል የሚል እምነት አለኝ ።
ከንጉሤ አሊ