አሁን ባለው ማህበራዊ-ፖለቲካዊ አለመረጋጋት፣ የታጠቁ ፀረ-መንግስት ኃይሎች የከበደ ተጽዕኖ እና በአገሪቱ ከሚታየው ከፍተኛ የኢኮኖሚ ውድቀት አንፃር፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ሥር ነቀል ለውጦች እየተጸነሱ ነው ብሎ መገመት ከእውነታው የራቀ ትንበያ አይደለም። ብዙ ሁኔታዎች ሊከሰቱ ይችላሉ፣ ከእነዚህም በጣም የከፋው፣ ኢትዮጵያን ወደ መፈራረስ የሚወስድ አጥፊ የእርስ በርስ ጦርነት ሊክሰት መቻሉ ነው። በዚህ ጽሑፍ ውስጥ “ተስማሚ” በማለት የማቀርበው ምናባዊ ሳይሆን እውን ሊሆን የሚችል አማራጭ መንገድ ነው። “በኢትዮጵያ ውስጥ ለሥርዓታዊ የፖለቲካ ሽግግር ዜጎችን ማዕከል ያደረገ ፖለቲካዊ የመንገድ ካርታ” በሚል ርዕስ በእምቢልታ ቡድን የተጻፈውን እና የተሰራጨውን ሀሳብ ሳነብ የዚህ ጽሁፍ ንድፍ በአእምሮዬ ውስጥ ሊቀረጽ ችሏል። ሰነዱ ብዙ ማራኪ ፅንሰ-ሀሳባዊ እና በተግባር ሊተገበሩ የሚችሉ ሀሳቦችን ይዟል። በተለይ የሚያስደስተው በፋኖ የተደገፈ “የሽግግር” ሂደት በመቀየስ “በዜግነት ላይ የተመሰረተ ህገ መንግስት” ለመቅረጽ አስፈላጊ የሆኑትን ተቋማትና እና የአሠራር ለውጦችን ለማመቻቸት የሚያስችሉ ሀሳቦችን መቅረባቸው ነው። (ከእምቢልታ ሀሳብ ጋር የተያያዙ ጥቅሶች ሁሉ የተወሰዱት ከ https://imbylta.org/wp-content/uploads/2024/01/ImbyltaTransition-Program-2024.pdf) ነው።
በፋኖ መከታነት የሚደረገ የሽግግር ሀሳብ በተለይ ለእኔ ተስማሚ ነበር፣ ምክንያቱም ከእምቢልታ ቡድን ጋር የምንስማማበት ነጥብ ነው። ስለሆነም፣ የአሁኑን መንግስት በአዋላጅ መንግስት የመተካትን እቅድ ያጠናክራል (መሳይ ከበደን ይመልከቱ፣ https://zehabesha.com/ethiopia-shifting-from-moralization-of-power-to-containment-the-idea-of-caretaker-government-in-ethiopia/)። በተጨማሪ ጽሑፉ በእምቢልታ ቡድን ሰነድ ውስጥ የሚታዩትን ክፍተቶች የመሟላት እንዲሁም አንዳንድ ግልጽ ያልሆኑ አባባሎቹን የማስተካከል ሙከራ ነው። ሙከራው ከቡድኑ ለወርስኩት ሃሳብ እውቅና ይሰጣል፤ እንዲሁም ኢትዮጵያ የተሻለ ሽግግር እንድታደርግ ለሚደረገው ክርክር አስተዋፅዖ ያበረክታል።
ዘመናዊነት ፈሩን ሲለቅ
በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን በርካታ እና ጥልቅ የሆኑ ችግሮችን ስንፈትሽ፣ ማድረግ ያለብን የመጀመሪያው ነገር መንስኤዎቻቸውን መለየት ነው፣ ምክንያቱም ችግሮቹን ማስወገድ የሚቻለው በዋነኛነት ትክክለኛ ምንጫቸው ሲታወቅ ነው። በዚህ ረገድ የእምቢልታ ቡድን የብዙ ኢትዮጵያውያንን አመለካከት ይጋራል፤ እሱም የችግሮቹን ዋና መንስኤ በህወሃት እና በተባባሪዎቹ ኢትዮጵያ ላይ የተጫነው የዘውግ ፌዴራሊዝምን ነው ይላል። ሆኖም፣ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ይህንን አመለካከት አይጋሩም። ብዙ የኢትዮጵያ ልሂቃን አሁን ያለው ሕገ መንግሥት በመሰረቱ ዴሞክራሲያዊ ነው፤ ችግሩ ያለው አተገባበሩ ላይ ነው ብለው ይከራከራሉ።
እምቢልታ የኢትዮጵያን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲተነትን፣ ዋናው የችግሮች ምንጭ “የንጉሣዊ ተቋማት ከዘመናዊ ተቋማት ጋር መዋሃዳቸው” ነው ይላል። የኃይለ ሥላሴን አገዛዝ የዘመናዊ ባህሪያት እና ትውፊታዊ አካላት ቅይጥ መሆኑ አስተማሪ ነው፣ ምክንያቱም አገዛዙ በማይጣጣሙ አካላት በመዋቀሩ ዘመናዊነትን ፈጥኖ ከማምጣት ይልቅ ያዳክማል፣ አልፎም ከመስመርም ያስወጣል። በእርግጥም፣ ይህ ዓይነት ቅይጥ ባህርይ በዝቅተኛ ልማት የሚወሰነውን የዳርቻ ካፒታሊዝም (peripheral capitalism) እና ኢ-ዲሞክራሲ ይዘት ያለውን ስርአት ይውልዳል። እንደ ማርክሲያዊ ትንታኔ የዳርቻ ማኅበራዊ ቅርጾች የሚፈልቁት በዋናው የካፒታሊዝም የምርት ዘዴ እና ካፒታሊስት ባልሆኑ የበታች የምርት ዘዴዎች ጥምረት ነው” (ዴቪድ ጉድማን እና ሚካኤል ሬድክሊፍት፣ ከገበሬው እስከ ፕሮሌታሪያን፣ ኦክስፎርድ፣ ገጽ 54)።
አንድ የኅብረተሰብ ክፍል ሌሎች ክፍሎችን ከማሟላት ወይም ከማነቃቃት ይልቅ እንቅፋት ሲሆን፣ ውጤቱ የለውጥን ፍጥነት መቀነስ ብቻ ሳይሆን ጭራሽኑ አቅጣጫውን ሊያስቀይር ይችላል። ትውፊታዊ አካላት በዘመናዊ አካላት ሲጠቀምሙ የተለየ ማህበራዊ ስርዓት መፍጠር ይችላሉ። ዘመናዊ አካላትን በቁጥጥሩ ሥር በማድረግ፣ ትውፊታዊ ክፍል (ከሁሉም ርዕዮተ ዓለማዊ፣ ባህላዊ እና ፖለቲካዊ ባህሪያቱ ጋር) እውነተኛ ዘመናዊነትን በማጨናገፍ እራሱን ያቆያል፣ ያጠናክራል። ትውፊታዊ እና ተዋረዳዊ የፖለቲካ ስርዓት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ፣ ቢሮክራሲ፣ ዘመናዊ ወታደራዊ፣ ፖሊስ፣ የስለላ ኃይሎች እና ሚዲያ ሲደገፍ፣ ወደ ላቀ የበላይነት ደረጃ ከፍ ይላል። ውህደቱ እስካለ ድረስ፣ እንዲህ ዓይነቱ ስርዓት በተከታታይ የአምባገነን አገዛዝ የማፍለቅ ጠባይ ይኖረዋል።
የሁለቱ ስርዓትች መገጣጠም የመንግሥትን ኃይል በዘመናዊ መሳሪያዎች ስለሚያጠናከር፣ ከፍተኛ የሆነ ማህበራዊ አለመመጣጠን ይፈጥራል፣ ምክንያቱም የዜጎችን ኃይል በመንጠቅ መንግስት ስልጣን ያከማቻልና። በሌላ አነጋገር፣ ዴሞክራሲያዊ ለውጦችን ማፈን ህዝቡን ህጋዊ መብቱን መንፈግ ስለሆነ፣ መንግስት በጠነከራ መጠን ህዝቡ አቅመቢስ ይሆናል። ካለ ተዛማጅ ዴሞክራሲያዊ ለውጦች ዘመናዊ ሂደቱ በመካሄዱ፣ አምባገነናዊ አገዛዝን ደጋግሞ ቢያመጣ ሊገርመን አይገባም። ሥልጣኑን የጨበጠው ቡድኑ ወይም ግለሰብ፣ ምንም ዐይነት ስነልቦናዊ ወይም ስነምግባራዊ ባሕሪ ይኑረው፣ ጥሩም ይሁን መጥፎ፣ መዋቅሩ የሚያስገድደውን አምባገነናዊ አሠራር ከማራመድ አያመልጥም።
ቀደም ሲል የተለየ ውጤት እንደሚያስገኙ ቃል ቢገቡም፣ ወደ አምባገነንነት የተሳቡ የመሪዎችን ምሳሌ፣ ኢትዮጵያ በአንፀባርቂ ሁኔት ታሳያለች። እነዚህ “ዘመናዊ” የተባሉት መሪዎች አምባገነናዊ አገዛዝን ለመተግበር ለይት ባሉ ዘዴውች ቢጠቀሙም፣ ተመሳሳይ ውጤት አምጥተዋል። ለዚህም ማስረጃ በኢትዮጵያ የዘውግ ልዩነት ላይ የተመሰረተው ከፋፈሎ የመግዛት ስትራቴጂ ነው። በአፄ ኃይለ ሥላሴ የግዛት ዘመን፣ ልዩነት ላይ ባለው ጥርጣሬ የተንሳ፣ የአገሪቱን አንድነት ለመጠበቅ አስፈላጊ እንደሆነ የታመነበት ጠንካራ እና የተማከለ የኢምፔሪያል ስርዓት ማቋቋም ነበር። ንጉሠ ነገሥቱ የማኅበራዊ ስርዓቱ መሰረት እንደሆኑ ተደርጎ ስለታስበ ለብዙ አሥርተ ዓመታት ሥልጣነቸው አይነኬ ነበር። በደርግ ዘመን፣ በተማሪዎች ንቅናቄ የተነሳ የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም ተወዳጅ መሆን የመደብ ልዩነትና ትግል ጽንሰ-ሀሳብ አምባገነን እና ኢ-ዴሞክራሲያዊ መንግሥት እንዲቋቋም ምክንያት ሆነ። በሕወሃት ጊዜ፣ የዘውግ ክፍፍሎችን በመፍጠርና ዘውጋዊ ብሔርተኝነትን በማቀጣጠል፣ በተለይም ኢትዮጵያን የፈጠረውን የአማራ ዘውግ በማጥላላት፣ የመከፋፈል ዘዴ ሊንሰራፋ ችሏል። አሁኑ ያለው አገዛዝ ተመሳሳይ ስትራቴጂና ሥርዓት ከመከተል በላይ ይበልጥ አጠናክሮታል።
በእነዚህ ሁኔታዎች ሁሉ፣ በእያንዳንዱ አገዛዝ የታቀዱ ለውጦችን ተግባራዊ ለማድረግ ግትርና አግላይ ደንቦች አስፈላጊ ሆነው ተገኝተዋል። በሥርዓቶቹ ሁሉ ማደናገሪያ ዘዴው፣ ለውጦቹን ሥራ ላይ ለማዋል ብቸኛው መንገድ አምባገነናዊ ደንቦችን መከተል ነው የሚለው አነጋገር ነብር። ተጨባጭ እውነቱ ግን አወንታዊ ለውጦችን ማምጣት ሳይሆን በማጭበርበር አምባገነናዊነትን መላልሶ ለመትከል ነው። በዚህም የተነሳ በኢትዮጵያ የለውጥ ትክክለኛ ትርጉም አይታወቅም እስከማለት እደርሳለሁ። በኢትዮጵያ ለውጥ የሚባለው በተመሳሳይ ነገር መተካት ነው። ፍጹማዊ የፕሬዚዳንት ወይም የጠቅላይ ሚኒቴርነት ሥልጣን የንጉሣዊ ፍጹማዊ አገዛዝን ተክቷል፤ ዘውጋዊ ብሔርተኝነትን የመደብ ትግልን ቦታ ወርሷል። በእያንዳንዱ የሽወዳ ለውጥ፣ ሥር ነቀል ለውጥ አረግን እያል እንናገራላን፣ ምንም እንኳን አንድ ዓይነት አምባገነናዊነትን በሌላ ዓይነት የተካን ቢሆንም። ከላይ የተጠቀሱት ማብራሪያዎች ፍሬ ነገር የሚያሳየው የዘውግ ፌዴራሊዝም መሳሪያ እንጂ ዋናው ግብ እንዳልሆ ነው ፥ ዋናው ግብ አምባገነንነት ነው። ይህ አባባል በኢትዮጵያ ችግሮች ውስጥ ያለውን ትክክለኛውን ቅደም ተከተል ያሳያል። ዋናው ምንጭ ኢትዮጵያ የዘመናዊነት መስመር መሳቷ ሲሆን እሱም የመጣው በአደገ ማህበራዊ ስርአትና ባልተሻሻለ፣ ባልተስተካከለ ትውፊታዊ ስርዓት መካከል የተፍጠረው ቅንጅት ነው። እዚህ ላይ በደንብ ማስተዋል ያለብን መስመር መልቀቁ ዘመናዊነትን የሚያዘገይ ብቻ ሳይሆን፣ የማይጣጣሙ ክፍሎች ውህደት አገሪቱን ወደ ተለየ፣ አዋጭ ባልሆነ አቅጣጫ እንደሚመራ ነው። መንገዱ የዜጎችን መብቶች በመንጠቅ መንግስት አፈና ኃይሉን ባልተመጣጠነ ሁኔታ እንዲፈረጥም ያስችለዋል። እምቢልታ እንደሚለው “ተስፋ ሰጪ ጅምሮች ቢኖሩም፣ እነዚህ ወደ ዘመናዊ የፖለቲካ ሥርዓት የሚያሸጋግሩ መስኮቶች ፍጹማዊ ሥልጣንና የጅምላ ድህነትን ለማስወገድ የፈጠሩት እድሎችን በአምባገነኖች ተዘግተውል”። አባባሉ ትክክል ቢሆንም የተዘጉት እድሎች መስመር የመሳት ውጤቶች መሆናቸው አብሮ መገለጽ አለብት፣ ማለትም ከፍጹማዊ ሥልጣን ውጪ ሌላ ማንኛውንም መንገድ ለመከተል መዋቅራዊ አለመቻል መደቀኑ መታወቅ አለበት።
ያመለጡ እድሎችን ለመጠቆም እምቢልታ የተጠቀመውን ምሳሌ ልውሰድ፤ ማለትም የሃይማኖትን ጉዳይ። ምሳሌው ለኢትዮጵያውያ ጥልቅ ሃይማኖታዊነት እውቅናውን ከመስጠት ጋር “ሁሉን ነገር ለአምላክ መተው ነው” የሚለውን እምነት ያያይዛል። ይህም “የማህበረሰቡ ግማሽ አባላቱ በቂ ምግብ ስለማያገኙ እና ያልተማሩ ስለሆኑ” የሚጠበቅ ነው ይላል። በሌላ አነጋገር፣ አውሮፓውያን እንዳደረጉት ኢትዮጵያ ዘመናዊነትን ለመደገፍ ጥልቅ ሃይማኖቷን አልተጠቀመችም፤ ይልቁንም ዘመናዊነትን ወደ ሚቃወመው ሁሉ ነገር ከአምላክ የሚመጣ ስለሆን ለእሱ እንተወው ወደሚል እምነት ተለወጧል። በዚህም የተነሳ ውጤቱ ከአውሮፓ ታሪክ በጣም የተለየ ሆኗል፣ ምክንያቱም በአውሮፓ በበቂ ሃይማኖት ተሃድሶ ስላደረገ ዘመናዊነትን እንዲደግፍ አስችሎታል፣ ለምሳሌ እንደ ፕሮቴስታንት ተሃድሶ (ዌበርን ይመልከቱ) ወይም የካቶሊክ እምነት ተቃራኒ-ተሃድሶ (Counter-Reformation)።
እዚህ ላይ በደንብ እንግባባ። በዘመናዊነት ሂደት ውስጥ ትውፊታዊ ባህሪያት መኖራቸው በራሱ ችግር አይደለም። የዘመናዊነት ቅድመ ሁኔታ ትውፊትን ማስወገድ ነው የሚለውን እምነት አልደግፍም፥ እምነቱ የአውሮፓን መንገድ ማዕከልና ብቸኛ ደንብ የሚያደርግ ነውና። በተቃራኒው፣ በበርካታ የጽሑፎቼ ውስጥ፣ የአውሮፓ ተምሳሌትነት ታዳጊ ለሚባሉ አገሮች ጎጂ ነው ብዬ እከራከራለሁ። በመሆኑም የምተቸው ዘመናዊ ዘዴዎች ራሱን ለማሻሻል ፈቃደኛ ካልሆነ ማህበራዊ-ባህላዊ ስርዓት ጋር መጣመራቸውን ነው። ትችቱ የሚጎትቱን ገጽታዎችን በማስወገድ በሚያበረታቱ እና ለውጡን በሚያመቻቹ ገጽታዎች መተካት ማለት ነው። ባጭሩ የምመክረው፣ ትውፊታዊ አካላትን አገሪቱን ማዕከል ወደ ሚያደርጉ ንብረቶች መለወጥ እና፣ በአውሮፓ ሃይማኖትን በተመለከት እንደታየው፣ ዘመናዊ ዘዴዎችን በመቀበል እና በመፍጠር ረገድ ጥቅም እንዲሰጡ ማድረግ ነው።
የዘውጋዊ ብሄረተኝነት አምባገነናዊ ዝንባሌ
አምባገነንነትን መሰራታዊ ማድርግ የኢትዮጵያን ችግሮች ዝቅ አድርጎ ማየት ሊመስል ይችላል። ቀደም ሲል እንደተገለጸው፣ በብዙ ልሂቃን ዘንድ፣ የዘውግ ፌዴራሊዝም ዋነኛው ችግር እና የሁሉም ችግሮች ምንጭ ነው ተብሎ የሚታመነው። እምቢልታ ይህንን አመለካከት ይጋራል፤ ዋናው ምክሩም የዘውግ ፌዴራሊዝምን “ጂኦግራፊ፣ ኢኮኖሚ እና ታሪክን ያገናዘቡ ራስገዝ ፌዴራላዊ ክፍሎች ወይም የአስተዳደሮች” መተካት ነው ይላል። የእዝያኑ ያህል፣ የኢትዮጵያ ደጋፊዎች “በማንነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ ማሰባሰብ ኃይልን ዝቅ አድርገው [ብዙውን ጊዜ እንደሚያደርጉት] እንዳይገምቱ ያሳስባል። በመቀጠልም፣ እራሳቸውን የሰየሙ ልሂቃን ያላቸውን በመደብ የመከፋፈል እና በጋራ ጥቅም ዙሪአ የመሰባሰብ ችሎታቸውን እንዳይጋንኑ” ይጠቃል።
ከዚህ ማስጠንቀቂያ በኋላ የሚጠበቅው ምክር የኢትዮጵያ ወዳጆች የዘውግን ጉዳይ በጥንቃቄ እንዲያዩት ነው። እምቢልታ ግን፣ አሁን እንዳየነው፣ የሚደግፈው ፈጽሞ የተለየ፣ ኢዘውጋዊ የክልል ክፍፍልን ነው። ሀሳቡ ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ ያላገኘችውን ዴሞክራሲ ከግምት ውስጥ ያስገባ ይመስላል። ነገር ግን ራስን በራስ የማስተዳደር አሃዶች እንዲኖሩ፣ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ዴሞክራሲያዊነት ቀድሞ መጎናጸፍ የለበትምን? አሮጌው የስልጣን መዋቅር እስካለ ድረስ አዲስ የፌዴራል ሥርአት መዘርጋቱ ትርጉም የለውም። በንጉሠ ነገሥቱ ሥርዓትና በደርግ ዘመን፣ ኢትዮጵያ ጂኦግራፊያዊና ታሪካዊ መስፈርቶችን የተከተሉ ክልሎች ነበሯት። እነሱን “ፌዴራላዊ” ብሎ ማደስና መሰየም የኢትዮጵያን ፖለቲካ ሥርዓት ዲሞክራሲያዊ አያደርገውም። በሕወሃትና በብልጽግና አገዛዝ ሥር የክልል ራስን በራስ የማስተዳደር መብት የሚገኝበትን አሳዛኝ ሁኔታ ስናይ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ከሌለ እውነተኛ ፌዴራሊዝም የማይቻል ለመሆኑ በቂ ማስረጃ አይደለምን? ዴሞክራሲያዊ ያልሆነ የፌዴራል ሥርዓት ካለጥርጥር እርስ በርሱ የሚጋጭ ነው።
በመሆኑም የኢትዮጵያ ሥርአቶች የነበራችውን እና አሁንም ያላቸው መሰረታዊ ፀረ-ዴሞክራሲያዊ መዋቅርን በማሳነስ የዘውጋዊነት አሉታዊ ውጤቶችን አጋነን ማየት የለብንም። የዴሞክራሲያዊነት እጦት ዘውጋዊ ያልሆነ የፖለቲካ ሥርዓትን እንደሚያበላሽ ሁሉ፣ ዘውግ ላይ የተመሰረተ ሥርዓትም በዴሞክራሲያዊ መሰረት ላይ ካልተገነባ ብለሹ ከመሆን አያመልጥም። የእምቢልታ ጽሁፍ የኢትዮጵያን ዘውጋዊ ሥርዓትን ከጎጂ ተግባራት፣ እንደ ከባድ ሙስና፣ ሥርዓታዊ ጥቃት፣ ደንበኛነት፣ የበላይንት፣ ወዘተ፣ በማገናኘት ረገድ ጥሩ ስራ ይሰራል። ሆኖም ግን፣ ተግባራቱን እንደ ዘውጋዊነትን ተፈጥሯዊ ባህርያት ይቆጥራቸዋል፣ ማለትም የዴሞክራሲያዊ አስተዳደር እና የተጠያቂነት እጦት ውጤት አድርጎ አያያቸውም። ተፈጥሮ ለዓመፅ የተጋለጠ፣ በሕግ ፊት የእኩልነት መርህን የሚጻረር እና የዜጎችን ሉዓላዊነት በፖለቲካዊ ውሳኔ የሚጥስ” ነው ይላል። ዘውግን ከታሪክ እና ከአፈናዊ የፖለቲካ ሥርዓቶች ጋር ሳናያይዝ ቀርተን የተወሰኑ መብቶችን እውቅና ለማግኘት ከሚቀርቡ ጥያቄዎች ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው በተፈጥሮ የተዛባ መለያ ነው ካላልን በስትቀር፣ የኢትዮጵያን ሕመሞች በሙሉ የልዩነት ጥያቄ ላይ መለጠፍ የተሳሳተ አካሄድ ነው።
አብዛኛው ሰው ዘውግን ተጠያቂ እንደማያደርግ ወይም ተጠያቂ ነው ለማለት እንደማይደፍር እና ይልቁንም አተገባበሩን እንደሚወቅስ ስለማውቅ፣ እውነተኛው ችግር የዴሞክራሲያዊ ህጎች አለመከበር መሆኑን አምኖ መቀበል አለበት። ቀደም ብዬ እንደጻፍኩት፣ የመበላሸቱ ሁኔት፣ የኢትዮጵያ ተከታታይ ስርአቶች፣ የዘውግ ፖለቲካን ቢከተሉም ባይከተሉም፣ የመስመር መሳት ውጤት ነው። የሃሳብ ወጥነት ሕግ ይህንን ድምዳሜ ይጥይቃል፣ ምክንያቱም የሁሉም ስርአቶች የጋራ ባህሪ፣ ዘውጋዊ ይሁኑ አይሁኑ፣ የሰዎችን መብቶች ሥርአታዊ በሆነ መንገድ ማፈን ነውና።
ስለ ወጥነት ከተናገርን ዘንዳ፣ ከሁሉም በላይ ከፍተኛውን የሃሳብ አለመጣጣም ገና አላጋለጥንም። እሱም ፋኖ በዜጎች ላይ የተመሰረተ ሕገ መንግሥትን የሚደግፍና እና ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው በሰፊ መነገሩ ነው። ሆኖም፣ የመሪዎቹ እና የአብዛኛዎቹ ተከታዮቹ መግለጫዎች በተደጋጋሚ የሚያሰምሩት ፋኖ በአማራ ብሔርተኝነት እንደሚመራ መሆኑን ነው። የዘውግ ፌዴራሊዝምን ያስወግዳል የሚለው ትንበያ፣ የማናውቀው የተደበቀ አጀንዳ ከሌለ በስተቀር፣ እርስ በርሱ የሚጋጭ ነው። ተወደደም ተጠላም፣ ፋኖ እንደ አንድ ብሔርተኛ ንቅናቄ፣ ዋና ግቡ የአማራን ማንነት እና መብት ማስከበር ነው። ንቅናቄው የተመሰረተው ቀደም ሲል የነበሩት የኢትዮጵያ ወይም የፓን-ኢትዮጵያ ንቅናቄዎችን በግልጽ በመቃውም መሆኑን አንዘንጋ። እንዲሁም ቀደም ሲል ዘውጋዊ ፌዴራሊዝም በመቃወም አብላጫ ድምጽ ለማሰባሰብ የተደረጉት የፓን-ኢትዮጵያ ሙከራዎች በሙሉ እንዳልተሳኩ እናስታውስ።
ተቃውሞው በይፋ የታወቀው በሜጀር ዳዊት የተሰራጨው “መነሻችን አማራ፣ መድረሻችን ኢትዮጵያ” የሚለው መፈክር በፋኖ ቡድኖች እና ተደማጭነት ባላቸው አክቲቪስቶች ከተተቸ በኋላ ነው። ይህ መፈክር የዘውግን ጉዳይ ዝቅ አድርጎ ስለሚመለከት ውድቅ ተደርጓል። እንደ መፈክሩ ከሆነ፣ “አማራ” የሚለው ስያሜ ከፍ ያለ ግብ፣ ማልትም ኢትዮጵያን፣ ለማዳን የሚያስችል መሳሪያ ይመስላል። ከዚህም በላይ፣ ምንም ስለ ሌሎች ዘውጎች ተሳትፎ ስለማይናገር፣ ኢትዮጵያን ከዘውጋዊ ብሔርተኝነት በኃይል ማላቀቅ እቅድ የተያዘ ያስመስላል። ይህን ስሜት የሚያጠንክረው ከሌሎች ዘውጎች ጋር ኅብረት ለመፍጠር የሚያስችል ፍኖተ ካርታ መኖሩን አለማመላከቱ ነው።
ይህ እንዳለ ሆኖ፣ እኔ እስከማውቀው ድረስ፣ የማይካደው ሃቅ ፋኖን ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሄርተኛ ንቅናቄዎች የሚለየው ለኢትዮጵያ ምንም አይነት ጥላቻ አለማሳየቱ ነው። ይልቁንም፣ የፋኖ መሪዎች እና ብዙ ተከታዮቻቸው የአማራ ማንነትን ከኢትዮጵያዊነት ጋር ለማጣመር ጽኑ ፍላጎት ያላቸው ይመስላሉ። ኢትዮጵያ በአብዛኛው የአማራ ህዝብ እና ልሂቃን የስራ ውጤት መሆኗ ለእንደዚህ አይነት ጥምረት የበለጠ ቁርጠኝነት ይፈጥራል። በዚህም ምክንያት፣ ኢትዮጵያዊነት የአማራ ማንነት አካል እና ውርስ ነው። ይህን እውነታ ነው የኦሮሞ እና የትግራይ ልሂቃን ኢትዮጵያን በዘውግ በመከፋፈል ለማጥፋት የሞከሩት። ለዚህም ነው ፋኖ፣ የዘውግ ፌዴራሊዝምን ከመሰርዝ ይቆጠባል የሚለውን ተስፋ ይዤ፣ በእምቢልታ የቀርውበውን በፋኖ መከታነት የሚደረግ የማህበራዊ ለውጥ ሀሳብ በሙሉ ልብ የምቀበለው። ተስፍዬንም በመተማመን ፋኖ በተቻለው መጠን የኢትዮጵያን ህልውና እና የክልል ነፃነት መጠበቅ ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ዴሞክራሲያዊ እና አካታች ሥርዐት ይመራታል የምለው።
ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊነት ተመራጭ መንገድ
በፋኖ ጠባቂነት የሚደረገውን የዴሞክራሲ መንገድን በጋለ ስሜት ለመደገፍ ያነሳሳኝን ምክንያት በጥልቀት ለመመርመር በመጀመሪያ የኢትዮጵያን ህልውና እና እድገት በማረጋግጥ ረገድ ተመራጩ መንገድ የትኛው አንደሆነ ማቅረብ ያስፈልጋል።ስለ ምርጡ መንገድ ስናገር፣ ሁለት ነገሮችን እመለከታለሁ ፥ (1) ዴሞክራሲያዊ አቅጣጪያ ለመያዝ አዋጩ መንገድ የትኛው ነው? (2) ውጤቱስ አሳተማማኝ የሚሆነው እንዴት ነው? እነዚህን ሁለት መመዘኛዎች ለማሟላት የሚቃረበው፣ ፋኖ “በግልጽ ድል ሲቀዳጅ ወይም ወታደራዊ ሁኔታው አንድ ግለጽ አሸናፊ ሲያጣ ነው”። ሁለቱም መንገዶች የአማራ ብልጽግና ፓርቲ መወገድን እና የኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ እጅግ መዳከምን ያስከትላሉ። በመጀመሪያው ሁኔታ ውስጥ ፋኖ ውሳኔ ሰጪ ይሆናል፤ በሁለተኛው ደግሞ አንድ አሸናፊ ስላልወጣ በዋና ተፎካካሪ ኃይሎች መካከል ድርድር ይሻል።
እኔ እንደማየው፣ አንድ አሸናፊ አለመኖሩ ወደ ድርድር ሊወስድ ይችላል። ነግር ግን፣ በተፎካካሪዎች መካከልም ረጅም ጦርነትም ሊቀሰቅስ ይችላል። ይህ ደግሞ ወደ መለያየት እና ወደ መገንጠል ማምራቱ አይቀርም። በመሆኑም ያለው አንድ ተመራጭ ሁኔታ ብቻ ነው። እሱም ፋኖ አሸናፊ ሆኖ የበላይነት ሲያገኝ ነው። ተመራጭነቱ ለአማራ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያም ጭምር ነው።እምቢልታ እንዳስቀመጠው፣ ፋኖ “የፓን-ኢትዮጵያን የፖለቲካ ራዕይ የሚያካትት አስፈጻሚ የመሆን ብቃት አለው”።
ፋኖ አካታች ኃይል እንዲሆን፣ ዋናው ቅድመ ሁኔታ በዴሞክራሲያዊ መንፈስ ራሱን ቀርጾ አንድነቱን እውን ማድረግ አለበት። በዚህ መንገድ ብቻ ነው በሽግግር ወቅት ወታደራዊ በላይነቱን ይዞ ሰላምን ለማስፈንና እና በተፎካካሪዎች መካከል ዴሞክራሲያዊ እና ሁሉን አቀፍ ድርድር እንዲካሄድ ሊያደርግ የሚችለው። ሁሉን አቀፍ ድርድር ውጤቱ ነጻ የሲቪል መንግሥት ከመመስረት ውጪ ሊሆን አይችልም። እዚህ ላይ አፍጦ የሚመጣው አንገብጋቢ ጥያቄ አሸናፊ የሆነ ወታደራዊ ኃይል ራሱን የቻለ የሲቪል መንግሥት እንዲቋቋም ይፈቅዳል ወይ የሚል ነው። ከደርግ እና ከህወሃት ጋር በተያያዘ እንዳየነው፣ ደንቡ የሚያሳየው አሸናፊው ወታደራዊ ኃይል ወይም ወታደራዊ ኃይል ያለው ፓርቲ ራሱን ወደ ስልጣን ባለቤትነት እንደሚቀይር ነው።ከኢትዮጵያ ውጭም ተመሳሳይ ሁኔታ በብዛት ተከስተዋል፥ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥቶች እና የሽምቅ ተዋጊ እንቅስቃ አሸናፊዎቹ እራሳቸውን ወደ ገዢ ፓርቲ በተደጋጋሚ ቀይረዋል።
አጠቃላይ ሂደቱ ብዙውን ጊዜ እንደተገለጸው ቢሆንም፣ ሊጠቀሱ የሚገባቸው ለየት ያሉ ውጤቶችም መኖራቸው የሚካድ አይደለም። እነዚህን ልዩ ውጤቶች ስንመረምር፣ አንዳንድ ወታደራዊ ድል የተቀዳጁ ኃይሎች የተለየ አቅጣጫ የወሰዱበትን ምክንያቶች ላይ ማተኮር የለብንም፤ እንዲሁም ከወታደር ወይም ወታደራዊ ፓርቲ መንግስትነት በመውረድ ለሲቪል አገዛዝ ስልጣን ያስረከቡ ያስገኟቸው ተጨባጭ ውጤታችው ላይ ማተኮር አያስፈልገንም። ትክክሉ አቀራረብ የተሳኩ ወይም ያልተሳኩ ሙከራዎች አድርገን ማየቱ ነው።
አንድ ጉልህ ስኬት ያስመዘገበው የዩናይትድ ስቴትስ አካሄድ ነው። በብሪታንያ የቅኝ አገዛዝ ላይ የተደረገው ጦርነት ሲያበቃ በወታደራዊ የበላይነት የሚመራ መንግሥት እንዲቋቋም አልተደረገም። ይልቁንም ዋሽንግተን እና ሌሎችም ወታደራዊ መሪዎች የጦር ኃይሉ የኮንግረስን የበላይነት መቀበል አለበት የሚለውን መርህ ደገፉ። ዋሽንግተን ወታደራዊ አዛዡነቱን በፈቃደኝነት ለኮንፌዴሬሽን ኮንግረስ ሲያስረክብ፣ በወታደራዊ ኃይል ላይ የሲቪሉን የሥልጣን የበላይነት አበሰረ። በተለየ ሁኔታ ቢከሰተም፣ ሌላው ስኬታማ ምሳሌ የደቡብ ኮሪያ ጉዳይ ነው። በሲቪል የሚመራ መንግሥት ለዓመታት የቆየውን ወታደራዊ አገዛዝን በመተካቱ ለዴሞክራሲያዊ መንገድ በር ከፍቷል።
ከወታደራዊ ኃይል ወደ ሲቪል ስልጣን ሽግግር ተደርጎ ውጤታቸው ያላመረ ምሳሌዎችም አሉ። እነሱም በዲሞክራሲያዊ ለውጦች ረገድ ውጤቶቻቸው አስተማማኝ ሊሆኑ ያልችሉ ወይም ወደ ወታደራዊ አገዛዝ እንደገና በመመለሳቸው የተገለበጡ ናቸው። ጥሩ ምሳሌ ምያንማር ነው፥ በ2011 ገዥው ወታደራዊ ጁንታ ስልጣንን ለተመረጠ የሲቪል መንግስት በፈቃደኝነት አስተላለፈ፣ ነገር ግን በ2021 የተደረገው መፈንቅለ መንግስት በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠውን መንግስት በመገልበጥ ወታደራዊ አገዛዝን መልሶታል። ከአፍሪካም ናይጄሪያን ብንወስድ፣ በ1999 ከወታደራዊ አገዛዝ ወደ ሲቪል መንግስት ሽግገር ቢደረግም፣ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደርን በማቋቋም ረገድ ብዙም ወይም ምንም ስኬት አልታየም። እንደ ብራዚል፣ አርጀንቲና፣ ቺሊ በመሳሰሉ በላቲን አሜሪካ አገሮችም በተለያዩ ጊዜያት ተመሳሳይ ሂደቶች ተካሂደዋል። ምንም እንኳን በአፍሪካ እና የላቲን አሜሪካ ወደ ሲቪል መንግስታት የተደረጉ ሽግግሮች ዴሞክራሲያዊ ውጤታቸው ብዙውን ጊዜ ተስፋ አስቆራጭ ቢሆኑም፣ ሽግግሮች መከሰታቸው ግን እሙን ነው።
የመከታነት ጽንሰ ሃሳብ
ፋኖን የዴሞክራሲያዊ ለውጦችን መከታ ማድረግ ያለውን አዋጭነት ከመፈተሻችን በፊት፣ የመከታነትን ትክክለኛ አግባብ ግልጽ ማድረግ ያስፈልጋል። ከላይ እንደተጠቀሰው፣ መከታነት ራሱን የቻለ የሲቪል መንግሥት መመስረትን እና በንቃት መደገፍን ያጠቃልላል። ቢሆንም ይህን ዓይነት ተልእኮን ፋኖ በትክክል ሊያሟላ የሚችለው በምን ዓይነት አካሄድና ተግባር ነው? እንደ እምቢልታ ገለጻ፣ ሁለት ዓይነት ሂደቶች ሊኖሩ ይገባል፥ (1) የብልጽግና አስተዳደር ከወደቀ በኋላ አንድ የሞግዚት መንግሥት ማቋቋም እና (2) የሽግግር ፓርላማ መሰየም። ለመጥቀስ ያህል፣ “በቅድሚያ ሰላምን ወደነበረበት ለመመለስ እና የፈረሰውን መንግሥት እና ወታደራዊ ኃይል በሞግዚት መንግሥት ለመተካት ሕጋዊ የሽማግሌዎች እና የመሪዎች አካል መፍጠር፣ ሁለተኛ በሽግግር ቻርተር መሠረት ጊዜያዊ ፓርላማ በማቋቋም ለሥርዓታዊ ተሃድሶ መንገድ ማመቻቸት ነው።” የመጀመሪያው ሥራ ሰላምን ወደነበረበት ለመመለስ እና የአንድ የመንግሥት አካል የዕለት ተዕለት ጉዳዮችን የማካሄድ ኃላፊነት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግም አስፈላጊውን ተሃድሶ የማስጀመር ተግባር ነው። ይህ ተወካይነት ያላቸው ቴክኖክራቶችን፣ ሽማግሌዎችን እና ወታደራዊ ባለሙያዎችን ያቀፈ የሞግዚት መንግሥት ሌላው ሥራው የጊዜያዊ ፓርላማ አባላትን መምረጥ ነው።
እምቢልታ በግልጽ ያላስቀመጠው፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የታጠቁ ንቅናቄዎች አባላት የሞግዚት መንግሥት ወይም የሽግግር ፓርላማ አካል መሆን አለመሆናቸውን ነው። በእኔ አመለካከት፣ በጠቀስኩት ጽሑፌ ላይ እንደተብራራው፣ ሁለትዮሽ ሂደት አስፈላጊ አይደለም። ይልቁንም፣ የመንግሥት ሥራን ከማከናወን በተጨማሪ ሕጋዊና ነጻ ሕዝባዊ ምርጫ በተቻለ ፍጥነት ለማድረግ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት የማሟላት ከባድ ኃላፊነትን የሚረከበውን ተወካይነት ያለው የሞግዚት መንግስት በማቋቋም የሽግግር ሂደቱ ያብቃ ባይ ነኝ። በተጨማሪም የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የታጠቁ ንቅናቄዎች አባላት፤ ገለልተኛ መሆን ስለማይችሉ፤ የሞግዚት መንግሥቱ አካል አይሆኑም እላለሁ። መሰረታዊ ነጥቤ የሚለው፣ ከሕዝብ ምርጫ ውጪ ሕጋዊ የሆነ አካል ስለሌለ፣ ሕግ የሚያወጣ ጊዚያዊ ፓርላማ የሚለው ሃሳብን መደገፍ ይከብደኛል ነው።
የጠቅስኩትን ጽሁፍ ባቀረብኩ ጊዜ ሰላምን እና የሞግዚቱ መንግሥት ውሳኔዎችን የሚያስከብር ኃይል ይህ ነው ብዬ አለመጠቆሜ የፕሮጀክቴ ደካማ ነጥብ እንደነበር አውቅ ነበር። የጽሑፌን ድክመት ለማስወገድ የሚያስፈልገኝ በፋኖ መከታነት የሚካሄድ የሽግግር ሂደት ነበር። ይህ ማለት ፋኖ የሞግዚት መንግሥትን ሥልጣን ከመቀበል በተጨማሪ የሰላምን አስከባሪና እና የመንግሥት ውሳኔዎችን አስፈጻሚ ሆኖ ያገለግላል ማለት ነው። የዚህ ከትያ ደግሞ ፋኖ አሸናፊ ቢሆንም፣ ልክ እንደሌሎች የፖለቲካ ተወዳዳሪዎች፤ የሞግዚቱ መንግሥት አካል አይሆንም ማለት ነው። በሌላ አነጋገር፣ ለፖለቲካ ሥልጣን የሚወዳደሩ ሁሉ ነፃና ፍትሃዊ የምርጫ ደንቦች እንዲሁም ቀናት በይፋ እስኪገለጹ ድረስ በጊዜያዊው መንግሥት ውስጥ በቀጥታ ከመሳተፍ መቆጠብ አለባቸው።
እዚህ ላይ ወሳኝ የሚሆነው የፋኖ ምስሌ ነው፥ በጦር አሸናፊ ሆኖ ነገር ግን የፌዴራል ስልጣንን ከመያዝ በማፈግፈግ ገለልተኛ ጊዜያዊ መንግስት ለመሾም ከተስማማ፣ ሌሎቹ ወገኖች የእሱን ምሳሌ መከተል ይጠበቅባቸዋል። ይህ ሲሆን ብቻ ነው ጥበበኛ ተወካዮችን መምረጥ እና ሰፊ ምክክር ከተደረገ በኋላ፣ ለሀገር አቀፍ ድምጸ ምርጫ የሚቀርቡ የሕገ መንግሥት ማሻሻያዎችን ማቅረብ እና በጥንቃቄ በማሰብ አስፈላጊ እና ለሁሉም እኩል የሆኑ ደንቦችን ማውጣት የሚቻለው። በዚህ መንገድ ብቻ ነው እየተገበረ ይለው አሉታዊ ልምድ፣ ማለት አሸናፊ የሆነው የታጠቀ ንቅናቄ ስልጣ የመያዝ እና ስልጣኑን (ሌላ የታጠቀ አመፅ እስከሚገለብጥው ድረስ) ለዘላለም የማቆየት ጣጣ የሚያበቃው። ይህ አሠረር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ የመንግስት ስርዓት እንድትወልድ ያስችላታል። ሌላ መንገድ መከተል አንድ አምባገነን ስርዓትን በሌላ አምባገነን ስርዓት ከመተካት አዙሪት አያድነንም።
ለዴሞክራሲያዊነት ማበረታቻዎች
የመከታነት ትርጉም ስለተብራራ፣ የቀረበውን ሃሳብ አዋጭነት መመርመር እንችላለን። እርግጥ ነው፣ ፋኖ የዴሞክራሲያዊ ለውጦችን ለማስጀመርና ለመንከባከብ አስፈላጊ የሆኑትን ሁኔታዎችን ማስቀመጡ አንድ ነገር ነው፤ ተልዕኮው እውን ሊሆን ይችላል ብሎ መናገር ደግሞ ሌላ ነው። ፋኖ የዴሞክራሲያዊነት አራማጅ ተልዕኮውን እንዲወጣ ለማድረግ አንድ መንገድ ብቻ ነው ያለው፤ እሱም ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ለመሸጋግር የሚያስችሉ ጠንካራ ማበረታቻዎችን መኖራቸውን ማሳየት ነው። ማበረታቻዎቹን እሩቅ ቦታ መፈለግ የለብንም፥ የኢትዮጵያ ያለችበት ከባድ የፖለቲካ ቅርቃር፤ ስልጣንን በቀጥታ ከመያዝ ይልቅ፤ የመከታነት ተልዕኮ እንዲቀበል ፋኖን ይጠይቃል።
ከባድ የፖለቲካ ቅርቃር የምለውን የሚያመለክተው፣ የኢትዮጵያን ቀጣይነት ለማረጋገጥ፣ በተፎካካሪዎች መካከል ስልጣን ከመጋራት አማራጭ ውጪ ሌላ መንገድ አለመኖሩን ነው። የኢኮኖሚ ብልጽግና ማምጣት ይቅርና፣ ዘላቂ የውስጥ ሰላም ተግባራዊ ካልተደረገ በስተቀር አገሪቱ ወደ መሰባበር ደረጃ ትደርሳለች። እንዲሁም ቅርቃሩ የዘውግ ቡድኖች ጽንፈኛ የፖለቲካ አቋማቸውን እንዲያስተካክሉ ይመክራል፣ ምክንያቱም ጦርነት ካልቆመ ውጤቱ ከእቅዳቸው ጋር የማይስማማ ሊሆን ይችላልና። እንዲህ ዓይነቱ አስቸጋሪ ሁኔታ ጋብ ማለትን አጥብቆ ይጠይቃል፣ ማልት ተፎካካሪዎች በስሜታቸው ወይም በአክራሪ አቋማቸው ከመመራት ይልቅ ምክንያታዊ ተጫዋቾች መሆን እንዳለባቸው ያሳስባል።
በዚህ ረገድ፣ አብዛኞቹ ተፎካካሪዎች ወደ መገንጠል ስለሚያዘነብሉ፣ ፋኖ ባለው የኢትዮጵያን አንድነት የመጠበቅ ቁርጠኝነት፣ የተለየ ሚና ሊጫወት ይችላል። በተጨማሪም፣ ቁርጠኝነቱ ጽኑ በመሆኑ፣ ፋኖ መካከለኛ እና ሁሉን አቀፍ አቋም እንዲይዝ ይጠይቃል። ባጭሩ፣ ፋኖ ከሚከተለው ሁለቱ ዋና ግቦች፣ ማለትም የአማራ ህዝብ ጥቅምና ደህንነት እንዲሁም የኢትዮጵያን አንድነትና መጠበቅ፣ ጋር ፍጹም በሆነ መልኩ የሚጣጣም ስለሆነ የሞግዚት መንግስት መከታ የመሆንን ኃላፊነት መቀበል የሚሳነው አይደለም። በእርግጥም፣ ፋኖን ከሌሎች የታጠቁ ዓማፅያን የሚለየው የአንድ ዘውግ ደጋፊ ብቻ አለመሆኑ ነው፥ ትኩረቱ ኢትዮጵያንም ይጨምር። ሁለቱንም ግቦች ለማሳካት ብቸኛው መንገድ ወደ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት የሚያመራ መንገድ መከተል ነው። ይህ ሳይሆን ቀርቶ በፋኖ ፍጹም የበላይንት የሚመራ መንግሥት የመመስረት ምርጫ ከተወሰደ እና በማይቀረው የኃይል እርምጃ መጠቀም ከተጀመረ ግን ሰላምን መልሶ ማምጣት እና ኢትዮጵያን ከአምባገነንነት አዙርት ነፃ ማውጣት መቻሉ በጣም አጠራጣሪ ነው።
የሞግዚት መንግስት ሀሳብ እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያ እና ሌሎች አገሮች ከተከተሉት የተለየ መንገድ ያሳያል። እሱም በጦር አሸናፊው ተወዳዳሪ የመንግስትን ስልጣን በቀጥታ አለመያዙ ነው። እንዳየነው፣ በኢትዮጵያ እና በአብዛኛዎቹ ሌሎች ሀገራት የታየው አካሄድ አሸናፊው ዴሞክራሲ አመጣለሁ ቢልም የገባውን ቃል በተደጋጋሚ አለማክበሩ ነው። ከእምቢልታ ሀሳብ የምለየው፣ “አንድነትን ለማጠናከር የማዕከላዊ መንግስትን ሥልጣን መያዝ አናሳ ቡድኖች የራሳቸውን ፖለቲካ የመመስረት ፍላጎት ይበልጣል” ሲል ነው። ከጥቅሱ ሁለተኛ ክፍል ጋር እስማማለሁ፣ ከመጀመሪያው ክፍል ጋር ግን እለያለሁ። የሚያስፈልገው በጦር አሸናፊ የሆነው ቡድን የመንግስት ስልጣን መያዙ ሳይሆን ህዝቡ ስልጣንን ለመረጣቸው ተወዳዳሪዎች እንዲያስረክብ የሚያስችል ጊዚያዊ ሸምጋይ መንግስት በቅድሚያ መመስረት ነው። ለውድቀታችን ሁሉ ምክንያት የህዝብን የስልጣን ባልቤትንት ስላላከበርን መሆኑን አንርሳ።
ሞግዚት መንግሥት ማለት በሕጋዊ መንገድ ሥልጣን ለመያዝ የሚያስፈልጉ ሕጋዊ ሁኔታዎችን ከማስቀመጥ ውጪ ሌላ ትልእኮ የለውም። በዚህም የተነሳ፣ ማንኛውም ተወዳዳሪ በኃይል አይገለልም፣ ወይም ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ ሕጋዊ መብቶችን አይነፈግም። ስልጣንን በቅድሚያ የተቆጣጠርው ኃይል ለእሱ አመቺ የሆኑ ደንቦችን የማወጅ ተለምዶ፣ በዚህ ጊዜያዊ አሠራር ያበቃል። አሸናፊው የገዢ ቡድን ደንቦችን ስለሚያወጣ እና የራሱን ስኬት ለማረጋገጥ ሁሉንም መንገዶች ስለሚጠቀም፣ አሠራሩ ለሌሎች ተወዳዳሪዎች ምንም እድል የማይሰጥ ነው። ስለዚህ፣ ለሁሉም ተወዳዳሪዎች ፍትሃዊ ደንቦችን የሚያወጣ እና አፈፃፀማቸውን የሚከታተል ራሱን የቻለ፣ በነፃነት የሚዳኝ መንግሥት ያስፈልጋል።
በልምድ በኢትዮጵያ ያሉ ሁሉም ዘውጎች ግጭቶች በሽምግልና መፍታት ፍትሃዊ ዘዴ ነው ብለው ያምናሉ። የሞግዚት መንግሥት ሃሳብ የዚህ የጋራ ባህል አንጸባራቂ ስለሆነ እንደ ዋና ማበረታቻ የሚታይ ነው። ስለሆነም ሁሉም ተፎካካሪዎች ዘለው የመንግስት ስልጣንን ከመያዝ ወደ ኋላ በማፈግፈግ፣ በገለልተኛነት፣ በአካታችነት እና በግብረ ገብነት የሚታወቁ ግለሰቦችን፣ በጥበብ በመምረጥ ሞግዚት መንግስት መመስረት ላይ መስማማት አለባቸው። ስምምነቱ ለሁሉም ነው፣ ለጽንፈኞችን ጭምር፣ ምክንያቱም ምርጫው የሞግዚት መንግሥት ወይም ትርምስምስ ስልሆነ። በብዙዎች እይታ አሸናፊው ፋኖ የበላይ ለመሆን ከመሞከር ይልቅ ወደ ሽምግልና ማዘንበል አለበት የሚለው ሃሳብ ምናባዊ እንደሚመስል አውቃለሁ። ሆኖም እስቲ እራሳችንን እንጠይቅ፥ ውስጣዊ ግጭቶች ለመፍታት መንግስታት ድርድር ሲያካሄድ ወደ ሽምግልና መምጣታቸው አይደለምን?። በዚህ ጊዜ የሚፈለገው ዋና ጉዳይ የፍትሃዊነት ዋስትና ነው። ሁለት ታጋዮች ውጊያቸው ወደ ገደል የሚወስዳቸው መሆኑን ሲገነዘቡ በስምምነት እርቅ እንዲፈጠር ይጠቃሉ። ጀርመናዊው ገጣሚ ሆልደርሊን እንዳለው፣ “አደጋው እየጨመረ ሲሄድ፣ የማዳን ኃይልም አብሮ ይጨምርል”።