ሢሣይነሽ መንግሥቴ
(የአርታዒ ማስታወሻ፦ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የቀረቡ አስተያየቶች የደራሲው ግል አመለካከቶች ብቻ ሲሆኑ፣ የZehabesha.com አቋም ወይም አመለካከት አይወክሉም።)

እንደመንደርደሪያ
በአሁኑ ወቅት ጋዜጠኝነትን በመርኆው እና በንድፈ ሐሳቡ ልክ ለመስራት መሞከር ፈታኝ ነው፤ በተለይ እንደኢትዮጵያ ባለ ጭቆና ስሩን በተከለበት አገር ውስጥ። ከመንግስታዊ ጫናው ሌላ፣ በሞያው አማካይነት የሚገኘው ደመወዝ አይረቤ ነው። የቤት ኪራይ ለመክፈል ይቅርና የተሻለ ስራ በራስ ተነሳሽነት ለመጀመር የሚበቃ አይደለም። ይህን ሃቅ ሁሉም ያውቀዋል፤ ይረዳዋል።
ከሁለት ሳምንታት በፊት በጋዜጠኞች ዙሪያ የተጻፈ አንድ ጽሑፍ ውስጤን ስላናወጠው ይህቺን ጦማር መጻፍ ተነሳስቼአለሁ። ጽሑፉ በፌስቡክ መተግበሪያ አማካይነት የተሰራጨ ሲሆን፣ ጸሐፊው ደግሞ በቅርብ ሩቅ የምናውቀው የሸገር 102.1 ጋዜጠኛ ተህቦ ንጉሴ ነው።
(በግሌ ከዚህ ቀደም ለተህቦ የነበረኝ አክብሮት ቀደም ሲል በጠቀስኩት ጽሑፍ ሙሉ በሙሉ ፈራርሷል። ምክንያቱን ደግሞ እንደሚከተለው አሰፍረዋለሁ!)
“ለአዋጁ አዋጅ” — ለጽሑፉ ምላሽ
ይህ ጽሑፍ የተጻፈው ከሁለት ሳምንታት በፊት በሸራተን አዲስ ሆቴል የኢትዮጵያው ሚድሮክ እና የፈረንሳዩ “ካርፉ” (Carrefour) ኩባንያ በጋራ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት የፈጸሙበትን ሁነት መነሻ በማድረግ ነው።
የጽሑፉ መጀመሪያ ገጽ የሚነሳው በዚህ ‘አሳሳቢ’ አገላለጽ ነው፣
“በየቦታው መግለጫ የምትሄዱ እንግዶች፤ጋዜጠኞች ፤የስብሰባ ተሳታፊዎችም ሆናችሁ ሌሎች እራሳችሁን ከሰርጎገብ መንታፊ ፤ ጋዜጠኞች ነን ከሚሉ ተጠበቁ!”
ምን ተፈጥሮ ነው ተህቦ እንዲህ ሊል የደፈረው?
ተህቦ እዚህ መርሐ ግብር ላይ ቀድሞ የተገኘው በግምት ወደ 4:00 ገደማ ነው። በዚያ ሰዓት የዕለቱ የክብር ዕንግዳ የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ እየተጠበቁ ስለነበር፣ መርሐ ግብሩ በቶሎ አልጀመረም። መርሐ ግብሩ የሚከናወነው ላሊበላ አዳራሽ ነው። ሁሉም ጋዜጠኛ ቁጭ ብሎ የሁነቱን መጀመር እየተጠባበቀ ነው።
በርግጥም፣ ተህቦ “በየቦታው የሚፈዝ ሰው” በመሆኑ፣ አይፎን (Iphone) ስልኩን ቢጥል አይገርምም። እናም፣ ተህቦ ራሱ ላይ እንደተነበየው ሁሉ፣ የእጅ ስልኩ ከኪሱ ሾልኮበት የተቀመጠበት ወንበር ስር ወደቀ። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ማንም ሰው የተህቦ “ውድ” ስልክ አፈትልኮ ስለመውደቁ ልብ አላለም።
ይሁንና ይህ የራሱን ተፈጥሯዊም ይሁን ሰዋዊ ግድፈት በመካድ ተህቦ ሁኔታውን ቀኝ ኋላ ጠምዝዞ በዚህ መልኩ ይገልጸዋል፣
“በዚህ መኃል የእጅ ስልኬ ተጠለፈች! ማን እንደጠለፋት ሳልረዳ ቀረሁ!
ስልኪቱ ጠፋች!”
እኔም ከምሰራበት የብዙሃን መገናኛ ተቋም ወደ ስፍራው ተልኬ ሁኔታውን በቅርበት ስለተከታተልኩ፣ የተህቦ አገላለጽ ሐሰተኝነት አልጠፋኝም። ምክንያቱም የሚከተሉትን ትዕይንቶች በዓይኔ በብረቱ ስላስተዋልኩ:-
ተህቦ ስልኩ በመንታፊ እንደተሰረቀ ተናግሮ፣ በስፍራው ግርግር ቢጤ ፈጠረ። አጠገቡ ተቀምጦ የነበረውን፣ ለ”ጌጡ ተመስገን” የፌስቡክ ገጽ የሚሰራውን ዘጋቢ ወደ ጠፋው የእጅ ስልኩ እንዲደውል ነገረው። ስልኩ አይሰራም፤ አገልግሎት አይሰጥም።
ተህቦ የአዳራሹን ድባብ በራሱ የጭንቀት ውልብታ ወጠረው!
ለስራ የመጡት ጋዜጠኞች ሁሉ ተጨነቁ፤ ተረባረቡ!
እርሱም ሁኔታውን እንዲህ ይተርከዋል፣
“ወዲያው ለሴክዩሪቲ ነገርኩ ወሬው እዛችው ክፍል እና በአካባቢው ናኘ!
በሸቅኩኝ !
የበሸቅኩት፤ ቤቱ ለሁሉም ሰው ክፍት መሆኑን በመረዳቴ ነው!
ከ ጠሪውም ማን ምን እንደሆነ አይጠይቅም ፤ መታወቅያ አይፈተሽም !
ጠሪና ተጠሪ አይተዋወቁም!”
ተህቦ በዚህ ልክ መብሸቅ አያስፈልገውም ነበር፤ ምክንያቱም ሸራተን አዲስ በጥንቃቄ ፍተሻ የሚከናወንበት ደሕንነቱ የተጠበቀ ሆቴል ነውና። ሌላው ጉዳይ ስለመታወቂያ ያነሳው ነጥብ ነው። ይህም እንደየተቋሙ አሰራር የሚወሰን ነው፤ ሁነቱን እንደሚያዘጋጀውም ሰው። የጠራቸውን የመገናኛ ብዙሃን ባለሞያዎች አሳምሮ የማያውቅ ሁነት የሚያዘጋጅ ተቋም የለም፤ ያለም አይመስለኝም። ዞሮ ዞሮ የተህቦ ስልክ መጨረሻ ምን እንደሆነ እንመልከት፣
“የእጅ ስልኬ ከመቅፅበት የፈለኩት ቦታ ላይ በድጋሚ ተገኘች!
ሌባው ምኑ ሞኝ ነው ስልኳን ወረወራት?!
እኔስ ምኔ ሞኝ ነው!”
ተህቦ “ብልጥ ሌባ” አልነበረም የገጠመው፤ ይልቁንም ራሱ እንዳመነው የዝንጋኤ ባሕርይው ነው ጉድ የሰራው። እንዳጋጣሚ እርሱ የተቀመጠበት ቦታ ላይ ስልኩ አልተፈለገም፤ ይልቁንስ ፈጥኖ ወደ ሆቴሉ የደሕንነት ሰዎች ገስግሶ፣ የአዳራሹ የጥበቃ ካሜራ የቀረጸውን ሁሉ እንዲያሳዩት ተማጸናቸው እንጂ!
“ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ!” እንዲሉ፣ ተህቦ ተጨንቆ፣ ሌሎችንም አስጨንቆ የእጅ ስልኩን ሲያፈላልግ የነበረው ቀድሞውኑ ባልጠፋበት ቦታ ስለመሆኑ ግልጽ ነው። ይህን አጋጣሚ በመጠቀም መግቢያዬ ላይ እንደገለጽኩት፣ ከየአቅጣጫው ጡጫ የበረታበትን ጋዜጠኛ ለመነረት ሞክሯል። በጽሑፉ መደምደሚያ ላይ፣
“እባካችሁ የምትጠሩትን እወቁ!
እንደው ይህ ጋዜጠኛ ፈረደበት!” በማለት የጻፈው ይህን ድብቅ ዓላማውን ለመሸፋፈን ነው፤ ከእርሱ በላይ ጋዜጠኛውን በሌብነት እና በዘራፊነት የፈረጀ ማን አለና?
እዚህ ጋ ሌላ ነገር ላንሳ። በዕውኑ ተህቦ እና ጓደኛው (በሸገር 102 ነጥብ 1 የዜና ክፍል ውስጥ የሚሰራው) በስራ ዘመናቸው የጋዜጠኝነትን ስነ ምግባር ጠብቀው ያውቃሉን? ከጣቢያው ሪፖርተሮች ከየተቋማት የሚላኩትን የሁነት ደብዳቤዎችን ለራሳቸው ደብቀው በማስቀረት እና ቀኑን በሙሉ በየሆቴሉ በመዞር፣ የጋዜጠኝነት ክብር ማረጋገጥ ይችላሉን?
ከሁሉም በላይ ተህቦ ያን ዕለት መርሐ ግብሩ ሳይጀምር ከሸራተን ሆቴል ቅጥር ግቢ በድንጋጤ መኪናውን አስነስቶ የወጣው ለምንድን ነው? መቸም የራሱ ሕሊና የሚሰጠው ምላሽ የታወቀ ስለሆነ እዚህ ላይ አልጽፈውም!
መውጫ
እኔ ይህንን ጽሑፍ የጻፍኩት ከተህቦ ጋር ግላዊ ንትርክ ስላለብኝ አይደለም። ይልቁንስ በፌስቡክ ገጹ ላይ ያሰፈረው የተሳሳተ ሃሳብ በርካቶችን ወደ ተንሸዋረረ ድምዳሜ እየወሰደ በመሆኑ፣ ዕውነታውን በደምሳሳው ለማሳወቅ ነው። በመጀመሪያ ያ ችግር የተፈጠረው በራሱ ስሕተት መሆኑ እየታወቀ ለምን ምስኪኖቹን ጋዜጠኞች የቂሌ መጫወቻ ሊያደርጋቸው ፈለገ? እርሱስ ለመፍረድ ምን ዓይነት ውክልና (legitmacy) ኖሮት ነው ሌባ ጣቱን ወደ ሌሎች የሞያ ጓዶቹ ላይ የቀሰረው?
ምላሹን ለራሱ ትቼ፣ የእኔን አጭር ምልከታ ላስፍር። ጋዜጠኛው በጥቅሉ በሌብነት እንዲፈረጅ የሚጥሩ “ጋዜጠኞች”፣ ራሳቸው በሃላፊነት በሚመሩት ጣቢያ ውስጥ የጋዜጠኝነትን መርህ በአፍጢሙ የተከሉ ናቸው። አዲስ ጋዜጠኛ ሞያውን እንዲለምድ መንገዱን የማይከፍቱ፣ እነርሱ የደረሱበት የኑሮ ከፍታ ላይ እንዳይደርስ ጭንቅላቱን በኩርኩም የሚነርቱ ናቸው። የተህቦ ጽሑፍ የዚህ ኩርኩም ዓይነተኛ መገለጫ ነው። ግን እስከመቼ?
ጋዜጠኛው በምቀኝነት እና በስም ማጥፋት ጥቃት የሚሰቃየው እስከ መቼ ድረስ ነው?