ሕወሓት እና ኦህዴድ/ብልጽግና በአማራ ሕዝብ ላይ የማይለዋወጥና ወጥ የጋራ አቋም አላቸው፡፡ ሁለቱም እርስ በርስ የማይስማሙ ቢመስሉም፤ የአማራን ሕዝብ ለመግፋትና ለመበደል ሲሆን ግን በጥቅሻ የሚግባቡ፤ ፀረ አማራ እና ፀረ ኢትዮጵያ ኃሎች ናቸው፡፡
እነዚህን ሁለት ኃይሎች ለማስወገድ የአማራ ሕዝብ ነገ ዛሬ ሳይል ራሱን እንዲያደራጅ፤ በተለይም የወልቃይት፣ ጠለምትና ራያ ሕዝብ በሙሉ ልቡ የአማራ ፋኖን በመደገፍ፤ ከእነዚህ ሁለት ፀረ አማራ ኃይሎች ራሱን ማዳን ይኖርበታል::
የኦህዴድ/ብልጽግና ሥርዓት ከሕወሓት ጋር የዶለተው ሴራ፤ ወልቃይትን አሳልፎ ለመስጠት ነው::
የኦህዴድ ብልጽግና ሥርዓት ካልተደመሰሰ በስተቀር ሰላምና እርጋታ፤ ፍትህና ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ ምድር አይታሰብም። ሥርዓቱ ፍጹም የሆነ የፖለቲካዊ ኦሮሞ የበላይነትን (Total Oromo Hegemony over Ethiopia) የማስፈን ጉዞውን፤ ቀስ በቀስ ስሟን ወደ ኦሮሚያ መቀየር እና፤ የእርስ በእርስ የብሄር ጦርነትን መሳሪያ ያደረገ ጉዞ ነው።
ዓላማው ተቀናቃኝ ኃይሉን ሁሉ በመምታትና በማምከን የኦሮሙማን አጀንዳ ስኬታማ ማድረግ ነው። ይህንን የሚያደርገው ደግሞ፤ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ጊዜ በጽሁፎቼ እንደገለጽኩት፤ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ባለሥልጣናት ጋር በመሻረክ መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው።
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ባለሥልጣናት ደግሞ ከአገራት ጋር የሚመሠርቱትን ግንኙነት፤ ተቋማዊ ወይም መንግሥታዊ በሆነ መንገድ ሳይሆን፤ ግለሰባዊ በሆነ የጥቅም ሰለባዎችን በመደለል የሚፈጽሙት መሆኑ ይታወቃል፡፡ የብልጽግናው ዋናው ሰው ዐቢይ አህመድም እንደ ሱዳኑ ጄኔራል ዳጋሎ ሁሉ፤ ለተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፍላጎት፤ አገራቸውን አሳልፈው የሰጡ ግለሰብ ናቸው፡፡ የዐብይ ኦህዴድ መንግሥት ሉአላዊ ሥልጣን አለኝ በሚል ሰበብ፤ የአማራውን ሕዝብ የኢኮኖሚ ጥቅም በያለበት የማምከን ስልቱን በወልቃይት፤ ጠገዴ፤ ጠለምትና ራያም እያካሄደው ነው፡፡
በተመሳሳይ፤ ህወሃትም፤ አጥፍቶ ጠፊ፤ ወንጀለኛ፤ ቀማኛ፤ ዘረኛ፤ ጸረ-አማራና ጸረ-ኢትዮጵያ፤ ተገንጣይ ድርጅት ነው። የህወሃት የመጨረሻ ግቡ ወልቃይትን ከተረከበ በኋላ፤ ከኢትዮጵያ መገንጠል መሆኑን የሚያረጋግጡ ብዙ ምልክቶች አሉ። ራሱ የቀረጸው ህገመንግሥት መገንጠልን የሚደግፈው፤ ብዙዎች እንደሚሉት ኤርትራን ለማስገንጠል ሳይሆን፤ ራሱ ጊዜ ጠብቆ ትግራይን ለመገንጠል መሆኑን ተግባሩ ያረጋግጥልናል፡፡
ባሁኑ ወቅት በሁሉም መስፈርቶች አጣብቂኝ ውስጥ የገባው የዐብይ አህመድ ሥርዓት፤ ወልቃይትን ለህወሃት አሳልፎ ለመስጠት የፈለገበት ዋና ምክንያት፤ ለትግራይ ሕዝብ ተጨንቆ ሳይሆን፤ በአማራ ፋኖና በኦሮሚያ ክልል ደግሞ የኦነግ ሸኔ ሠራዊት ያደረሱበት ምት ከባድ በመሆኑ ነው።
በህወሃትና በዐብይ አህመድ ቡድን ቀስቃሽነት በተካሄደው ጦርነት፤ ከ600 ሺህ እስከ አንድ ሚሊየን ልጆቹን ያጣው የትግራይ ሕዝብ፤ ሌላ ጦርነት ይፈልጋል የሚል ተንኮለኛነት ከየት መጣ? ብለን መጠየቅ አለብን። የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው የሚለውን ብሂል የሚያንጸባርቀው ሴራ፤ ግቡ የአማራውን ዘላቂ ጥቅም ከስሩ ለመንቀል ነው።
የወልቃይት ጠገዴን፤ ጠለምትን፣ አበርገሌንና ራያን የማንነት፤ የባለቤትነት፤ የነጻነት፤ የሰብአዊ መብትና የዴሞክራሲ ጥያቄ፤ ከአማራው ማንንትና የህልውና ትግል ጋር አግባብ ባለው መልክ በመረጃ ተደግፌ ከዚህ በፊት አቅርቤዋለሁ።
በጥቅሉ ስገመግመው፤ የዘውግና የቋንቋ ፌደራል ስርዓት እስካልተቀየረ ድረስ፤ እንኳን ልማት ሊረጋገጥ ይቅርና፤ ሰላም፣ እርጋታ፣ ፍትህና እኩልነት አይታሰብም። የዘውግና የቋንቋ ፌዴራል ሥርዓት የሚቀየረው ደግሞ፤ በኦህዴድ/ብልጽግና ሥርዓት መቃብር ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የአማራ ሕዝብ የጀመረው የህልውና ማስጠበቅ ትግልም ዓላማው፤ እንደዚህ አይነት ከህዝብ እድገትና ከዘመን ሥልጣኔ ጋር የተቃረነ ፌዴራላዊ መዋቅርን፤ በህዝቦች ስምምነት በተመሠረተ የመንግሥት ሥርዓት ለመቀየር ያለመ ነው፡፡
የአማራ ፋኖን ውህደት ስቀሰቅስ የቆየሁትና ምስረታውን በደስታ የምቀበለው ስር ነቀል ለውጥ ስለሚያስተጋባ ነው፡፡ ስር ነቀል ለውጥ ለሁሉም ይበጃል የሚል እምነት አለኝ፡፡
የውልቃይትን ጉዳይ በሚመለከት ከዚህ በታች ድምዳሚዎችና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን አቀርባለሁ።
ለችግሩ መፍትሄ አለ ወይንስ የለም?
ቅንነትና የፖለቲካ ፈቃደኛነት ካለ መፍትሄ አለ። የአካባቢው አባቶች፤ እናቶች፤ ወጣቶች፤ የጎበዝ አለቆች፤ የአካባቢ ስብስቦችና ሌሎች የሚሏቸውን ሃሳቦች ማንጸባረቅ ግዴታችን ነው። ይህ የሚያሳየው ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በእኩልነት፤ በፍትህ፤ በወዳጅነት የሚኖሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው። በተጨማሪ፤
አንድ፤ በአገር አቀፍ ደረጃ ስመረምረው፤ ህወሓትና ደጋፊዎቹ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ስልጣን፤ ዘመናዊ ኢኮኖሚና የተፈጥሮ ሀብት ማርከውት ከቆዩ በኋላ፤ አሁን ኦህዴድ/ብልጽግና ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮታል። ይህ ቡድን ከህወሃት የባሰ ጨካኝ፤ ሥስታም፤ ሆዳምና አምካኝ ነው። አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ በቅርቡ በቃለ ምልልሳቸው፤ ‹‹ብልጽግና ማለት፤ ፈሪ፣ ስግብግብ፣ ውሸታምና አድርባይ ነው›› ሲሉ የተናገሩትን ልብ ይሏል፡፡ ከዚህም ባበሰ፤ በድንቁርና የተበከለም ነው። ስለሆነም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ መሰረታዊ የሆነ የስርዓት ለውጥ ያስፈልገዋል። ይህ ተግዳሮት የሚጠይቀው ሕዝባዊ አመጽ ሲሆን፤ ለዚህ ደግሞ መተባበርን ይጠይቃል። የኦህዴድ/ብልጽግና ሥርዓት በድርድር አያምንም። የሚያምነው ፍጹም በሆነ በአንድ ብሔር የበላይነት ነው። ለዚህ ዓላማው ሲል ደግሞ የትኛውንም ብሔረሰብና ክልል ወደ ጦርነት ማስገባት ይፈልጋል፡፡ የትግራይ ሕዝብ መጠንቀቅ ያለበት ህወሃት፤ ከብልጽግና ጋር ሆኖ ወደ ሌላ ጦርነት ቢገባ፤ ብዙ መቶ ሺዎች እንደሚሞቱ ነው።
ሁለት፤ የህወሓት የመሬት ነጠቃና ተስፋፊነት በእቅድ የተሰራ፤ ዘላቂነት እንዲሆን በጦር መሳሪያ ኃይል የተደገፈ ነው። ህወሓት ለሥልጣኑና ለፖለቲካ ፍላጎቱ ሲል፤ በዚህ ጉዳይ ለትግራይ ሕዝብ ቃል ኪዳን የገባበት ስለሆነ፤ በድርድር የሚፈታ አይመስለኝም።
ሶስት፤ ጎንደሬው፤ ወሎየው፤ ጎጃሜውና የሸዋው አማራ እና የሌላ ብሄር ነዋሪ የገጠመው ችግር የመኖር- አለመኖር፤ ማለትም፤ የህልውና ጥያቄ ሆኗል። ችግሩን ሊወጣው የሚችለው በመተባበር፤ አንድ ወጥ ድርጅትና አመራር ሲኖረው፤ አቅሙን ሲያጠናክርና ሌሎች ኢትዮጵያዊያን እንዲተባበሩት ያልተቆጠበ ጥረት
ሲያድርግ ነው። ችግሩ የሚፈታው፤ ነዋሪው የአማራ ሕዝብ የማንነቱ፤ የዜግነቱና የመሬቱ ባለቤት ሲሆን ነው። ይህ ቀይ መስመር ለድርድር እንዲቀርብ መፍቀድ የለብንም። የወልቃይት አማራነት በታሪክ የተደገፈ እንጂ፤ የኔ የፈጠራ ታሪክ አይደለም።
አራት፤ የመጀመሪያው ትኩረት በያካባቢው አቅምን ማጠናከር፤ መደራጀት፤ ጠንካራና የማይበገር ሕዝባዊ አመራር መፍጠር ነው፤ ይህ እየተፈጠረ መሆኑን አውቃለሁ። ከቀያቸው የተፈናቀሉት አማራዎች ሁሉ፤ ወደ ጥንታዊ መሬቶቻቸው እንዲመለሱ የመልሶ ማቋቋም ስራ መሰራት አለበት።
አምስት፤ የወልቃይት-ጠገዴና ተመሳሳይ ጥያቄዎች ብሄራዊ ወይም አገራዊ ችግሮች ናቸው። የወልቃይት ጉዳይ የአንድ አካባቢ ጉዳይ ብቻ አይደለም። የኦህዴድ/ብልጽግና ልሂቃን ይህን መሰረታዊ መርህ መቀበል ግዴታ አለባቸው። ካልሆነ ቀጠናው በሙሉ በዘላለም ጦርነት ይበከላል። ሌሎች ኢትዮጵያዊያንም ጉዳዩን እንደራሳቸው ጉዳይ እንዲቆጥሩትና እንዲታገሉበት አደራ እላለሁ። በየአካባቢው ብቅ ብቅ ያሉት እንቅስቃሴዎች የሁላችንም ትኩረትና ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል።
ስድስት፤ የወልቃይት የአማራ ማንነት፤ የባለቤትነት፤ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥያቄ የህልውና ጥያቄ ነው። ከላይ እንዳሳሰብኩት፤ ይህ ጥያቄ ሁሉንም አማራ፤ ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን ያገባቸዋል። በተለይ፤ ተቃዋሚ ነን የሚሉ ምሁራን፤ ልሂቃን፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ሌሎችም አቋም መውሰድ አለባቸው። አማራውም ቢሆን ጥቃቅን ልዩነቶችን ወደ ጎን ትቶ መረባረብ አለበት። ኦህዴድ ብልጽግና ወልቃይትን ለይቶ ከአማራው ሊነጥል የሚመኘው፤ አማራው የኢኮኖሚ አቅም እንዳይኖረውና ከውጭ አገሮች ጋር ወሰን እንዳይኖረው ለማድረግ ነው። ይህን ፈረንጆች starvation and strangulation ወይም ማስራብ እና አንቆ መግደል ይሉታል። በአዲስ አበባ የሚያደርገውን ተመሳሳይ ነውር፤ በወልቃይትም ሊደግመው ሰለፈለገ ነው። ስለዚህ የአማራ ሕዝብ ንቃ፣ ድፈር፣ ተነሳ። ከዚህ የባሰ ነገር ሊመጣብህ አይችልም።
ሰባት፤ ህወሓትና ደጋፊዎቹ ሰላምና እርጋታ ከፈለጉ የትግራይ ድንበር ተከዜ መሆኑን መቀበል አለባቸው። ህወሓቶች ይህን አማራጭ ይቀበላሉ የሚል ግምትና እምነት የለኝም። ምክንያቱም በተደጋጋሚ ጊዜ ይህን እውነት ክዶ ሲከራከርና በድርቅና ሲሟገት አይነነዋል፡፡ የአማራ ሕዝብም ይህ አማራጭ ይሰራል ብሎ እንዳይሞኝ አሳስባለሁ።
ስምንት፤ ሰባተኛው አማራጭ የኦህዴድ/ብልጽግናን ሥርዓት እውቅና እስካላገኘ ድረስ ሕዝባዊ አመጹ ይቀጥላል። የአማራ ፋኖ ትግሉን እሰከመጨረሻው ድረስ ያካሂደዋል የሚል እምነት አለኝ። ለወልቃይት፤ ጠገዴ፤ ጠለምትና ራያ ታጋዮችና ወገኖቸ አደራ የምለው፤ ‹‹በዐብይ አህመድ አትታለሉ። ድፈሩ፤ ባንድነት በቃ ብላችሁ የአማራ ፋኖን ደግፉ›› ማለት እፈልጋለሁ፡፡ ለአማራው ወጣት ትውልድ የምመክረው ደግሞ፤ ከአሁን በኋላ በቃኝ፤ ድንበሬንና ጥቅሜን መስዋእት እየከፈልኩ አስከብራለሁ በል። የአማራ ፋኖን ፍትሃዊ ትግል ተቀላቀል። ኦህዴድ ብልጽግና ባሪያም ሆነህ እንዳትኖር ፈርዶብሃል።
ዘጠኝ፤ አንድ የታሪክ ምሁር ባደረገው ጥናት፤ “ምርምሮችና ጥናቶች የሚያሳዩት ሃቅ አንድ ነው። ህወሓት በረሀ ከነበረበት ዘመን ጀምሮ የአማራን ዘር፣ ባሕልና ማንነት ከአካባቢው በማጥፋት በማፈናቀልና በማሳደድ፣ የትግራይ ተወላጆችን በገፍ በማስፈር፤ ብዙ የአማራ፤ የቅማንትና ሌሎች ተወላጆችን
በማሳደድ፤ በድብቅ በመግደል፤ እንዲሰደዱ በማድረግ እየተስፋፋ ከሄደና ሥልጣን ከያዘ በኋላም፤ የትግራይ ተወላጆችን በማስፈር የአካባቢውን ዲሞግራፊ (ነባራዊ ምኅዳር) ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚያስችል ደረጃ ቀይሮታል። የአካባቢው የአማራና ሌሎች ነዋሪዎች ከቤታቸው፤ ከንብረታቸው፤ ከመሬታቸው በገፍና በግፍ ተፈናቅለዋል…. የመሬት ነጠቃና የነዋሪዎችን ባህል፤ ልምድ፤ ታሪክ፤ ምሳሌዎች፤ ስሞች ወዘተርፈ እንዳልነበሩ ማድረግና በሚፈለገው ዘዴ መተካት የተለመደ የዘር ማጥፋት ሂደት ነው›› ሲል ይገልጸዋል፡፡
ይህ የጥናት ሪፖርት ትክክል መሆኑን በመረጃዎች አረጋግጫለሁ። አንዱና ዋናው የህወሓቶች እና የኦህዴድ/ብልጽግና እቅድ፤ የአማራውን ሕዝብ ማዋረድ፤ ዘሩንና ባህሉን ማጥፋት፤ መሬቱን መንጠቅ፤ ከቀየው በገፍ ማባረር ሆኗል። የደመደምኩትም ጎንደሬው፤ ወሎየው፤ ጎጃሜው፣ ሸዋየው እና የሌላ ብሄር የዘር ማጥፋት ዘመቻ እንደተካሄደበትና ወደፊትም እንደሚካሄድበት ብዙ መረጃዎችን አይቻለሁ፤ እመሰክራለሁ። ችግሩ፤ የመኖር! አለመኖር! የህልውና ጥያቄ ነው የሚለው አግባብ አለው።
የኦህዴድ ብልጽግና ሥርዓት የአማራውን ሕዝብ በጅምላ ከአዲስ አበባ መንጥሮ አስወጥቶታል፤ ወደፊትም ያስወጣዋል። ህወሃትና ኦህዴድ/ብልጽግና የጸረ አማራነት አቋማቸው ተመሳሳይ ነው።
አስር፤ የመረምርኳቸው ጥናቶችና መጽሃፍት ያረጋገጡት የትግራይ ድንበር ተከዜ መሆኑን ሲሆን፤ ጥናቶች የሚያሳዩት፤ ህወሓት አዲስ ታሪክ መፍጠሩን ነው። ይህንን ያደረገበት ዋና ምክንያትም የነጠቀውን መሬት ህጋዊ ለማድረግ ነው። ”ምእራብ ትግራይ” የሚለው ትርክትም የፈጠራ ትርክት ነው።
ይህንን የሃሰት ፋብሪካ በሚመለከት፤ ከአስር ዓመት በፊት ኢሳት ቴሌቪዥን በሜልበርን አውስትራሊያ ከአቶ ፈረደ መብራቱና ከአቶ ደሳለኝ ታየ ጋር ባደረገው ሰፊ ቃለ ምልልስ፤ “የወልቃይት ጠገዴና የሌሎች በአማራው ክልል የሚገኙ፤ አሁን የተነጠቁ አካባቢዎችን የአስተዳደር፤ የነዋሪዎች ብሄር፤ የመሬት ባላቤትነት፤ የጎበዝ አለቃዎች፤ የድንበር ይዞታና የግብር ክፍያ” ወዘተርፈ ታሪክ በማያሻማ መረጃ አቅርበውታል።
ለማጠናከር፤ መረጃው የሚያሳየው “የትግራይ ክልል ወሰኑ ተከዜ” መሆኑን ነው። ህወሓቶች “ነጩን ጥቁር ነው፤ በሬ ወለደ፤ የዳሸን ተራራ የትግራይ ነው ወዘተርፈ” ካሉ በኋላ፤ ሃቁን የማይቀበሉት ህወሓትና ደጋፊዎቹ አዲስ ታሪክ ፈጥረው፤ “የትግራይን ሕዝብ እንዲሰለፍ አድርገው፤ አዲስ ካሪኩለም ጸንሰው፤ መሬቱ ከጥንት ጀምሮ “የእኛ ነው” ይላሉ። ልክ ኦህዲድ ብልጽግና አዲስ አበባን የኦሮሞ ብቻ ነው ከሚለው ብሂል ጋር የተያያዘ ነው።
ይህን የፈጠራ ታሪክ (Make Believe) እኔም ሆነ ሌሎች የአካባቢው ተወላጆች አንቀበልም። የምከራከርበት መሰረታዊ ወይም የፖሊሲ ልዩነት ይኼው ነው። ሕዝብ ለማንነቱና ለመሬቱ፤ ለህይወቱ፤ ለህልውናው፤ ለመብቱ፤ ለነጻነቱ በገፍ እየሞተና እየተሳደደ የሚሞትበትን ምክንያት፤ በሰከነ አእምሮ መመርመር፣ ቢቻል መቀበል አስፈላጊ እየሆነ ሄዷል። የምደመድመው፤ ‹‹የዚህን አስደናቂ ሕዝብ ጩኸት እንስማው፤ ድጋፍ እንለግስ›› በሚል ነው። ድጋፍ ለማን እንስጥ? የሚለው ለአማራ ፋኖ መሆኑን በተግባር ተመልሷል፡፡ ለአማራ ፋኖ የሚደረገውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ፤ በተጠናከረ መልኩ ማድረግ እንደሚገባ ለመላው የአማራ ሕዝብ እና አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን በዚህ አጋጣሚ በድጋሚ ማሳሰብ እፈልጋለሁ፡፡
በግፍ የተፈናቀሉት የተሰደዱትና እንዲጠፉ የተደረጉት፤ በአብዛኛው የአማራው ሕዝብ ወገኖች በጅምላ ያጡትንና ለሰፋሪ ተላልፎ የተሰጠባቸውን ቤት ንብረትና መሬት፤ መልሰው እንዲያገኙ ሳይደረግ፤ ጎንደሬውና ሌላው አማራ፤ ቅማንቱና ሌላው መስዋእት እየሆነ ባለበት ሁኔታ፤ “ይህ ጉዳይ በሕዝበ ውሳኔ እልባት ያግኝ!” ብሎ ማለት፤ ኢ-ፍትሐዊ፤ ግፈኛና ጭካኔነትን የሚያሳይ ብያኔ ነው። ይህ ከሆነ ለምን የአዲስ አበባ ሕዝብ ያለምንም ጫና ድምጽ ሰጥቶ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር አይደረግም?
አግባብ የሚኖረው መፍትሄ ነባር ተወላጆቹን ብቻ የሚያሳትፍና ድምጻቸውን የሚሰጡበትን ሁኔታ ለመፍጠር የሚያስችል ፖሊሲና ውሳኔ ነው። ድምጽ የነዋሪው ሕዝብ እንጂ የሰፋሪዎች ሊሆን አይችልም።
ኤርትራ እንድትገነጠልና የኢትዮጵያ የባህር በር እንዲዘጋ ያመቻቸው ህወሓት፤ አሁንም መሬት ነጥቆ ኢትዮጵያን የሚያፈራርስበት እድል ይሰጠዋል። ዐብይ አህመድና ቡድኑ እንዲያስብበት የምፈልገው፤ ወልቃይትን አሳልፎ ለወያኔ ማስረከብ ለኢትዮጵያ የውጭ ጠላቶች፤ ግብጽን ጨምሮ የሚመኙት ውጤት እንደሚሆን ነው። ችግሩ በሪፈረንደም ይፈታ የሚለው ሃሳብ፤ ከኤርትራው ሁኔታ አይለይም። ህወሓቶች ረሱት እንጂ፤ ኤርትራን ሲያስገነጥሉ ድምጽ እንዲሰጥ ያመቻቹት ኤርትራዊያንን ብቻ ነው።
የአዲስ አበባውን የማስተር ፕላን ያስለወጠው፤ የኦሮሞው ሕዝብ ድምጽ፣ ግፊትና አመጽ ነው። ህወሓት ፈቅዶ ያደረገው አይደለም። ህወሓት ፈቅዶና ወዶ የነጠቀውን መሬት፤ ከሕግ ውጭ ያካበተውን ኃብት ለሕዝብ አይመልስም። ወልቃይትን ጠገዴን በተመለከተ፤ ሪፈረንደም የሚለው ብሂል አግባብነት የሌለው መሆኑን በዚህ ፅሁፍ በመረጃ አሳይቻለሁ።
አስራ አንድ፤ በአማራ ክልል የመሬት ነጠቃ ጉዳይ፤ የሚያገባው የአማራውንና ሌላውን ነዋሪ ሕዝብ ነው። የሕግ የበላይነት የለም እንጂ የህግ የበላይነት ቢኖር ኖሮ፤ መሳተፍና ድምጽ መስጠት የሚችለው ነዋሪው ሕዝብ ብቻ ነው። ሁለት አይነት ፍትህ ሊኖር አይችልም።
አስራ ሁለት፤ በመሰፈርቶች እንዳሳየሁት፤ የህወሓት የመሬት ነጠቃና ተስፋፊነት ሕገ-ወጥ ነው። በመረጃ የተደገፈ አይደለም። የትግራይ ድንበር ተከዜ ነው። የተነጠቀው መሬት ለነዋሪው ሕዝብ ካልተመለሰ፤ ሰላምና እርጋታም ሆነ፤ ብሄራዊ አንድነት አይኖርም። በትግራይ ሕዝብና መሬታቸውን በተነጠቁት ነዋሪዎች መካከል ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ጥላቻና ግጭት ይቀጥላል። ስለሆነም፤ ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን ይመለከታል።
አስራ ሶስት፤ ህወሓት ያካሄደው የ1994 የሕዝብ ቆጠራና ዘገባ በህወሓት ተመርጦ እንደ መረጃ የሚቀርበው በህወሓት በተነጠቁት ለም መሬቶች፤ ማለትም፤ በሰቲት ሁመራ፣ በጠለምት፣ በወልቃይትና በጠገዴ የሚኖረው “አብዛኛው ሕዝብ ትግሬ” መሆኑን ዘግቧል። የአማራውና የሌላው ሕዝብ ቁጥር በማይታመን ደረጃ እንዲቀንስና በራሱ መሬት አናሳ እንዲሆን፤ በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ፈጽሞ እንደማይኖር ተደርጎ እንደተበየነበት ያሳያል። ይህ የፖለቲካ ስልጣንን ተጠቅሞ በኃይልና በጫና የተደረገ ውሳኔ ነው። ይህ በፖለቲካ የተወሰነ የሕዝብ ቆጠራ የተካሄደው ህወሓት ስልጣን ከመያዙ በፊት አካባቢውን ስለተቆጣጠረው ሰፊ
የትግራይ ሕዝብ፤ የቀድሞ ታጋዮችን ጨምሮ አስፍሮበታል። የአካባቢውን ነዋሪዎች በሚዘገንን ደረጃ ገድሏል፤ እንዲሰወሩ አድርጓል፤ እንዲሰደዱ አስገድዷል።
እነዚህን ጥንታዊ ነዋሪዎችና የአካባቢው ባለቤቶች፤ በገፍ አስወግዶ፣ የገደለውን ገድሎ፣ በምትካቸው ስልጣን ከመያዙ በፊትና ስልጣን ከያዘ በኋላ በትንሹ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ትግሬዎችን አስፍሮበታል። ካሰፈረ በኋላ መሬቱ “የትግሬዎች ነው፤ አካባቢው የትግራይ ክልል አካል ነው” ማለቱ አያስደንቅም።
ዋናው ነጥብ ግን ለብዙ ሺህ ዓመታት በአካባቢው የኖረውና ህወሓት በትጥቅም መሬቱን ከመንጠቁ በፊት እነዚህ መሬቶች የትግራይ ክልል ሆነው አያውቁም የሚለው በብዙ መረጃ የተደገፈው ነው። ሙሉ በሙሉ የአካባቢው ነዋሪም የትግራይ ብሄር አባል አልነበረም፤ የአማራ ሕዝብ እንጂ፡፡
አስራ አራት፤ የወልቃይትና የሌሎች የተነጠቁ መሬቶች ጉዳይ በአሁኑ የሕዝብ ስርጭት ቆጠራ ይወሰን ከተባለ፤ ህወሓት ያካሄደው በፖለቲካ ውሳኔና በመሳሪያ ኃይል ጫና አግባብ አለው የተባለው የ1994 የሕዝብ ቆጠራና የብሄር ስርጭት ተቀባይነት የለውም። በኃይል የተያዘ ይዞታ ነው (Occupation and Annexation of Lands By Force) አግባብ የሚኖረው በደርግ መንግሥት የነበረው የሕዝብ ስርጭትና እውቅና ያለው ድንበር ነው።
አስራ አምስት፤ በመጨረሻ ለማሳሰብ የምፈልገው፤ የወልቃይት ጠገዴና ሌሎች የጎንደር፤ የወሎ፤ የጎጃም፤ የሸዋ፣ የአፋርና ሌሎች የተነጠቁ መሬቶችና የነዋሪዎች ችግር የአስተዳደር አይደለም። የህወሓት የመሬት ነጣቂነትና ተስፋፊነት ችግር ነው። የጠባብ ብሄርተኛው፤ ጎጠኛውና ዘረኛው የህወሓት የስርዓት የበላይነትና አዛዥነት ችግር ነው። የአምባገነንነት ችግር ነው። ወልቃይት ጠገዴ “የትግራይ” ነው የሚለውን አዲስ ብሂልና ታሪክ የጎንደር ሕዝብ መስዋእት እየሆነ፤ “ይህን አዲስ የፈጠራ ታሪክ አንቀበልም” ብሎታል። የህወሓት ተተኪዎችም የተወረረና የተነጠቀ መሬት ይገባኛል ካሉ ከህወሓት በምንም አይለዩም።
ያቀረብኩት ሰፊ ትንተና የነዋሪዎቹንና ከቀያቸው የተባረሩትን ጎንደሬዎች ብሶትና የሰብአዊ መብት አግባብነት ፍትሃዊ መልስ የሚያመለክት ጥያቄ ይደግፈዋል። ዛሬ የወልቃይት የማንነትና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ፤ የመላው አማራ ብቻ ሳይሆን፤ የመላው ኢትዮጵያዊያን የሰብአዊ መብት መታፈን ጥያቄ ሆኗል። አማራው “የኦሮሞ ወንድሞቻችን ደም ደማችን ነው” እንዳለው ሁሉ፤ የወልቃይት የማንነትና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄና እንቅስቃሴ የመላው ኢትዮጵያዊያን የነጻነት፤ የፍትህ፣ የርትእ፤ የሕግ የበላይነት፤ የዴሞክራሲ ጥያቄ ሆኗል።
መፍቴውስ ምን ይሁን?
- የወልቃይት፤ጠገዴ፤ ጠለምት እና ራያ ጉዳይ መወሰን ያለበት በነዋሪውና ከመሬት፤ ከንብረቱ ተገድዶ በተሰቃየው ሕዝብ ነው፤ ህወሓትን ወይንም ወራሾቹን አይመለከትም።
- ሕዝቡ ምርጫ አድርጎ የራስ ገዝ አስተዳደር ይኑረኝ ካለ መብቱ ይጠበቅ። ሕዝቡ የአማራው ክልልአካል ነኝ ካለ ይህም ድምጽ ይከበር።
- እጅግ የሚዘገንን ግፍና በደል ተካሂዶበት የፌደራል መንግሥት መሬትህ አይገባህም ሊል የሞራል ብቃት የለውም።
በመጨረሻ፤ ህወሓት ለዚህ ሕዝብ ሰላም ስለማይሰጠው፤ የውስጥ ቅጥረኞችንም ስለሚጠቀም፤ ሕዝቡ መደራጀትና መታጠቅ አለበት። የተደራጀንና የታጠን ሕዝብ ማንም አይደፍረውም። ከእስራኤል ለመማር መቻል አለብን።
See Mass Graves and Grave Sites—TPLF Atrocities in Setit-Humera, Wolkait, Tegede, Telemt
https://www.google.com/maps/d/viewer?mid=13vMM1foRpg3i3_ikBskqtbPgTmnPcNAK& hl=en&usp=sharingkBskqtbPgTmnPcNAK&hl=en&usp=sharing
See alsoTPLF madness of expansion as depicted in the attached maps. Annexes
Updated January 2026