ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ nigatuasteraye@gmail.com ታህሳስ 20/2025
መምህራችን ዶክተር ጌታቸው መታፈሪያ “Ethiopia and the Judeo christian Tradition Antiquity to Modernity” በሚል ስያሜ የቤተ እስራኤል ልጆች የጻፏቸውን ጦማሮች በስምንት ምዕራፎች በሁለት ክፍሎች አሰናስለው ስላቀረቡልን ምስጋና ይገባቸዋል፡፡
በትምህርት ሙያቸው ባደረጉት ሰፊ ዳሰሳ፡ እንደ ብዙወቹ ምሁራን ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖችም በሩቅ በመሳለም ብቻ ራሳቸውን ሳወስኑ፡ በዋሸንገተን ዲሲ የቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር በሊቀ መንበርነት ከ2009 እስከ 2015 ዓ/ም ለ6 ዐመታት ሲያገለግሉ በቆዩባቸው አመታት፤ እውቀታቸውን ለማካፈል ከአሜሪካ ወደ ኢየሩሳሌም እየሄዱ በመቆየት የገጠማቸው እድል፤ በቤተ እስራኤሎችና በማህበረ ገዳሙ መካከል የለውን መራራቅ፡ በሰፊው ተመልክተዋል፡፡
በመጽሐፉ ተሰናስለው የቀረቡት ተወልጄ ባደኩበት ደብር ባዘቦት፤ በበዐላት፤ በዘፈን፡ በእንጉርጉሮ፡ በቅራርቶ፡ በሽለላ፤ በሐዘን በደስታ በሰርግ በክርስትና በልቅሶ ከሕዝቡ የሰማኋቸው፤ ከየጉባዔ ቤቶች መምሕራንም በመደበኛና መደበኛ ባልሆኑ ጉባዕያት ስማራቸውና ስሠማቸው የነበሩት እሴቶች “Oral literature and material culture” ተብለው በዚህ መጽሐፍ የተገለጹት ናቸው፡፡ ከልጅነት እስከ እውቀት እየሰማኋቸውና እየተካፈልኳቸው ስላደኩ ስሜቴን ቀስቅሰውብኛል፡፡
ስለ ቤተ እስራኤልም ሲነገር የሰማሁት “Oral literature and material culture” የተባለው ከሚያጣምረ ሕብረተ ሰብ ክትግሬው ከአማራው ከአገው ከጉራጌው ከቅማንቱና ከቀረው ሁሉ ኢትዮጵያዊ ዜጋ የተልዩ አንዳልሆኑ ነው ሲነገር የሰማሁት፡፡ ልዩነታቸው ክርስትናን ከተቀበሉት ወገኖች በኦሪቱ ጸንተው በመቆየት እንጅ በሥጋ በደም ባጥንት በባህል ልዩነት የላቸውም፡፡ ፈላሲ የሚለው ቅጽልም፡ ልዩ ቅዱስ ጽዩፍ ታዛቢ መናኝ ማለት ሲሆን፡ ከአባት አብራክ መከፈልን፡ ከናት ማሕጸን በወሊድ መለየትን፡ ከዚህ ዓለም በሞት መለየትን ሁሉ የምታሳይ አመለካች ቅጽል እንጅ ለዝቅተኝነትና ለውርደት ማሳያ አይደለችም፡፡ በተፈጥሮ ለሰው ልጅ ሁሉ የተሰጠ ስም ነው፡፡ አሁንም ከኢትዮጵያ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄዱ ፈልሰው ነውና፡ አሁንም ይህ የተፈጥሮ ስም የከተላቸዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄዱ ፈልሰው ነውና፡ ይኖሩበት አካባቢ የሚኖረው ቀሪው ሰው የሚያስታውሳቸው ፍልሰው በመሄድ ነው፡፡
ያሁኑ ፍልሰታቸውም ረዥሙ ዘመን ካላስረሳቸው በእለት ምግባችን፤ በአመት ልብሳችን) በሌሊቱ ጸሎታችን፡ በአርበኝነታች (ፋኖነታችን) እና በቀብር ስርአታችን ከቤተ እስራኤል ጋራ ከምንጋራቸው “Oral literature and material culture” ከተባሉ እሴቶች ላይ ተደምሯል፡፡
ትኩረት ያደረኳባቸው በቤተ እስራኤላውያንና በኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ተተካኪው ትውልድ ላይ ሲፈሱ የኖሩት እያንዳንዳቸው የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ እሴቶች፡ ሌሎችን የተሰናሰሏቸውን እሴቶች እየጎተቱ በማምጣት ጭንቅላቴን አንድ ብቻ መውጭ በር እንዳለው አዳራሽ አድረገውታል፡፡
ሊይዘው ከሚችለው ቁጥር በላይ ሰወች በተሰበሰቡበት ባለ አንድ ጠባብ በር አዳራሽ፡ አንድ ሰው በበሩ ፊት ለፊት እሳት ለኩሶ ሁሉንም አንድ ጊዜ ውጡ ! ቢል፡ ሁሉም በዚያው ቅጽበት ባንዷ ጠባብ በር ለመውጣት ሲሽቀዳደም እዚያው እበሩ ላይ እርስበርሱ በተጠባበቀው አካሉ በሩን ከመዝጋት በቀር የሚወጡት በጣም ጥቂት ናቸው፡፡
እራሴም በተግባር የተካፈልኳቸው፡ ካካባቢም የሰማኋቸውና ከሊቃውንቱም የተማርኳቸው ሁሉ ከመረጥኳቸው እሴቶች ጋራ በትዝታ እየተጓተቱ ተሰናስለው በመጉረፍ ጭንቅላቴን አጣበው አስጨነቁት፡፡ ከጭንቅላቴ ለመውጣት በሚያደርጉት እሽቅድምድም ሐሳቤን የማፈልቅበትን የጭንቅላቴን ጉሮሮ ጥርቅም አርገው የዘጉት መሰለኝ፡፡ ከመረጥኳቸው እሴቶች ጋራ እየተቆላለፉ ተሰናስለው የመጡትን ትዝታወች በብዙ ትግል ፈልቅቄ እየለየሁ ከጭንቅንቅ አጣብቂኝ አምልጠው የወጡትን ጥቂት እሴቶችን ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡
ከላይ እንዳልኩት የመረጥኳቸው እሴቶች በዐይን የሚታዩ በእጅ የሚዳሰሱ ባደባባይ፡ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ በቤታችን በሰውነታችን በየእለቱ የሚታዩ ሲሆኑ፡፡ ወቅታውያን መነጋገሪያ የሆኑት አርብርኝነትና ፋኖ ግን በጊዜና በጋጣሚ ሕዝባዊ ኩነት ተጸንሰው የሚወለዱ ናቸው፡፡ ከነሱም ውስጥ ሰፊወን ጊዜ የወሰደብኝ የወጣትነት ጊዜየን ካጠፋሁባቸው ሙያወቼ አንዱ ሰምናወርቅ ቅኔያች ነው፡
፡ የመረጥኳቸው እሴቶች የቤተ እስራኤልንና የኢትዮጵያውያን ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖችን ጥምረት የሚንጸባረቁትን በAntiquity, Modernity እና በሰምናወርቅ ቅኔያችን የተሰናሰሉትን ከዚህ በታች አቀርቤያቸዋለሁ፡፡
ጥንትነታዊነት በዘመናዊነት (Antiquity to Modernity)
“Ethiopia and the Judeo christian Tradition Antiquity to Modernity: የሚለው የመጽሐፉ ርእስ አለቃ አስረስ የኔ ሰው “Language is an Image, and an Image is a Ianguage, a language is a Fidel. Fidele is a statue, a satatue is is a Fidel. Fidele is a father and a Father is a Fidel. Fidel is national symbole . National symbole is source of pride”(27). ብለው የእሴቶቻችን መሰናሰል የገለጹበት ፈሊጥ ከብዙ መንገድ ቅኔወቻችን መካከል ሠረዝ የሚባለውን ቅኔ ይመስላል፡፡
በአለቃ አስረስ የኔሰው ሠረዝ መሳይ ቅኔ ተሰናስለው የተገለጹት እሴቶች ጥንታዊነትን በዘመናዊነት፡ ዘመናዊነትን በጥንታዊነት አሰናስለው ቤተ እስራኤልንና ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሕዝበ ክርስቲያንን አጣምረው እንዴት ኢትዮጵያዊ ኩራት እንደሆነልን ዶ/ር ጌታቸው “Ethiopia and the Judeo christian Tradition Antiquity to Modernity” ብለው ባቀረቡልን መጽሐፍ ተረድተናል፡፡
አምሳሉ ተፈራ “The unsion manifestion of the old and the new testament in the Thiopian orthodoch church” ሲሉ በተናገሩት፦ በኦሪት ውስጥ የሚኖሩት ቤተ እስራኤል በሐዲስ ኪዳን ውስጥ ለምንኖረው ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ጥንትነታችንን፡ በአዲስ ኪዳን ውስጥ የምንኖረው እኛ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ለቤተ እስራኤል ዘመናዊነታቸውን እንደምናንጸባርቅ ገልጸውልናል፡፡
እነዚህ ሁሉ ጥምረቶቻችን ከሚታዩባቸው ማሳያወቻችን አንዱና ዋናው ጃንደረባው ነው፡፡ ጃንደረባው “አነ አአምን ከመ ኢየሱስ ክርስቶስ ውእቱ ወልዱ ለአግዚአብሔር”(8፡38)፡፡ ብሎ ክርስትናን
ተቀብሎ ሲጠመቀ የአንቲኩዪነትና የሞደርኒቲነት ገጽታወች በሱነቱ ተሰናስለው ሕልዋን ሆነዋል፡፡ ቤተ እስራኤሎች እኛን በጃንድረባው ውስጥ ያውናል፡፡ እኛም ቤተ እስራኤሎችን በጀንደረባው ውስጥ እናያቸዋለን፡፡ይህም ማለት ቤተ እስራኤሎች በኛ ውስጥ፡ እኛም በነሱ ውስጥ ሕልዋን ሆነን እንኖራለን ማለት ነው፡፡
የቤተ ክህነቱ መሪወችና የቤተ ምኩራቡ መሪወች ትኩረት የጎደላቸው ባይሆኑ በሰውነቱ ኦሪትንና ሐዲስ ኪዳንን ሰምና ወርቅ ባደረገው በጃንደራባው ስም ቤተ እስራኤሎች የሚጸልዩበት ኦርቶዶክሳውያን የሚቀድሱበት ባለ ሁለት ቤተ መቀድስ አንድ ሕንጻ ጀንዳ ላይ መመስረት ነበረበት፡፡
በክርስትና ስም በዓለም የተፈለፈሉት አዳዲስ ድርጅቶችና፡ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችንንም ለመዋጥ ይገዳደሩን የነበሩት ሁሉ የእምነት ድርጅቶች ኢትዮጵያን ባጥለቀለቁበት ዘመን በantiquity እና በ modernity ኢትዮጵያ የተሰራችበት ቤተ ምኩራብ በኢትዮጵያ ከፍ ብሎ የሚታይ ቤተ ጸሎት አለመሰራቱ ያሳዝነኛል፡፡ በውጭ በሚኖሩት ወገኖች አነሳሽነት በጳጳሱ በብጹዕ አቡነ ዕንባቆም፡ በገዳሙ መጋቢ አባ ዘበአማንና በቤተእስራኤል ጥረት በ2002 ዓ/ም ለመጀመሪያ ጊዜ ታሪካዊ የጋራ ጥምረት ተጀምሮ ነበር፡፡
ጠንክሮ በመቀጠል በጃንደረባው ውስጥ ያለውን ጥምረታችንን አጉልቶ የሚያሳይ ታሪክ ይሰራል ብለን ተስፋ አድርገን ነበር፡፡ የአቡነ እንባቆም ከቦታው መወገድ የነበረንን ተስፋ አደረቀው፡፡ አቡነ እንባቆምንና አባ ዘበአማንን የጠቀስኳቸው ከዚያ በፊት ተደርጎ የማያውቅ ቤተ እስራኤልንና ኢትዮጵያውያን ኦርቶዶክሶችን የሚያገናኝ ጉባኤ መጀመራቸው ነው፡፡ “ወብዙኃን ይዌድስዎ እንበይነ ጥበቢሁ ወኢይደመሰስ ለዐለም ወኢይጠፍእ ዝክሩ ወይቀውም ስሙ ለትውልደ ትውልድ”(ሲራ39፡9) የሚለውን የጠቢቡን ምክር በተግባር ካዋሉት በሕይወት ከሌሉት ከአቡነ ፊልጶስና ከአቡነ ማቴዎስ በቀር፡ ከሲኖዶሱ ወደ ገዳሙ የተላኩት ጳጳሳትን ይህን የመሰለ ታሪክ ሊያስቡና ሊሰሩ ቀርቶ፡ በገዳሙ ላይ የሰሩት ስህተት እየተጠቀሰ በገዳሙ ቆይታየ ሲወቀሱ ስለሰማሁ ነው፡፡
ያምሆነ ይህ የጋራ ሁለንተናችን በሰምና ወርቅ ቅኔ እየተቀመረ በፊደላችን ተጽፎ ለኢትዮጵያዊነት ኩራታችን statue የሆኖው ጃንደረባ መጽሐፍ ቅዱስ በሚነበብባቸው ኦርቶዶክሳውያን ቤተ መቀደሶች፡ በፕሮቴስታንቱ ፑልፒቶችና በየግል ቤቶች ሲነበብ ይኖራል፡፡ በጀንደረባው ውስጥ የተካተቱት የAntiquity እና የmodernity ገጽታወች “ wax and Gold Qene as a bridge between traditions” (26) እንደተባለው በሰምና ወርቅ ቅኔያችን ለቤተ እስራኤልና ለኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ተተካኪ ትውልድ አሸጋጋሪ ድልድዮች ከሆኑን እሴቶቻችን አንዱ ሆኖ በታሪክነቱ ይቀጥላል፡፡
የጃንድረባውን ታሪክ ከማንበባቸው በፊት “ነቅ ንጹሕ ዘእም አንቅእተ ሕግ” ብለው አውጀው፡ ንባቡን ከፈጸሙ በኋላ “መልዐ ወዐብየ ወተለዐለ ቃለ እግዚአብሔር ወበዝሐ ወተወሰከ ውስተ ቤተ ክርስቲያን ቅድስት”(ሥራተ ቅዳሴ) የሚለውን እያነበቡ ጀርባቸውን ለህዝብ ልባቸውን በፖለቲካ ለሚሽከረክረው ሲኖዶስ ለሚሰጡ ጳጳሳትና ቀሳውስት ግን ወዮላቸው፡፡
ዛሬም ባለንበት ዘመን ባንድነት በመቆም የሰምናወርቅ እሴቶችን ለህዝበ ክርስቲያኑና ለቤተ እስራኤል ማስተማር የሚገባቸው የቤተምኩራብ ረቢወች፡ በሲኖዶስ ውስጥ የተሰገሰጉት ጳጳሳት ከሰምና ወርቁ ቅኔ የራቁ በመሆናቸው የግዕዙን ፊደል በሚንቁ፤ የላቲኑን ፊደል በሚያደንቁ፤ ኦርቶዶክስ
ክርስቲያኖችና ቤተእስራኤሎች በሚገናኙባቸው እሴቶች ላይ በሚሳለቁ ወራሪወች ኢትዮጵያ ስትወረር እነሱም አብረው የሚወሩና የሚሳለቁ ሆኑ፡፡
እሴቶቹ በኦርቶዶክሱ ክርስቲያንና በቤተ እስራኤላውያን ደም ውስጥ ሕልዋን ሆነው ለተተካኪው ትውልድ የመሸጋገሪያ ድልድይ ሆነው ቢኖሩም፡ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያን ለመውረር የሞከሩ ቅኝ ገዥ ወረራወች በህብረተ ሰቡ መካከል የሚደቀሉትን መንፈሰዲቃሎች በመጠቀም የእሴቶችን ድልድይነት እያፈረሱ ትርጉማቸውን እያደበዘዙ የጥንት አባቶቻችንን ይገዳደሩ እንደነበር፡ ዛሬም ባባእዳን የተቀመሩትን ትርክቶች እየተቀበሉ ድልድይነታቸው አፍርሰዋል፡፡ ትርጉማቸውንም አፋልሰዋል ፡፡
ትርጉሞቻቸውን ካደበዘዟቸው እሴቶች አንዱ የኢትዮጵያውነታችን መገለጫ የሆነው ሰምና ወርቅ ቅኔ ነው፡፡ ሰምናወርቅ ቅኔ “bridge between traditions” እንደተባለው፦ የኢትዮጵያ ተተካኪው ትውልድ የኢትዮጵያዊነትን ርእዮተዐለም ከሚቀባበልባቸው ምሥጢራውያን ድልድዮች አንዱ ነው፡፡ የሰምናወርቅ ቅኔን የተውልድ አሸጋጋሪነትንና ምንጩ ማን እንደሆነ፡ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እንዴት እንደተከሰተና አባቶች እንዴት እንደሚተርኩት ከዚህ በታች እንመልከት፡፡
“Wax and Gold Qene as a Bridge Between Traditions”
“wax and Gold Qene” ሰምና ወርቅ ቅኔ ሰምናወርቅ ቅኔን እነ ቅዱስ ያሬድ እነ ተዋናይ ጀመሩት እየተባለ በብዙሐኑ የሚነገረው እንዳለ ሆኖ፦ በተለምዶ ከሚነገረው ለየት ያለውን በሊቃውንት አባቶች ጉባዔ ሲነገር የሰማሁትን ለመመስከር ከዚህ የተሻለ አጋጣሚ የማገኝ አይመስለኝም፡፡ የሰማኋቸው በደብረ ሊባኖስ ገዳም በመምህር ገ/ኢየሱስ ስም በተመሠረተው በአንድምታው ትርጓሜ ቤት በነበርኩበት ጊዜ ነው፡፡
በነገራችን ላይ፦በሕይወት ባሉት ሕይወታቸውን ሕጸጽ የሌለበት ሰምና ወርቅ ቅኔ አድርገው ባቀረቡልን በገዳሙ የቅኔ መምህር በየኔታ አባ ገ/ሥላሴ ፊት ስለ ሰምናወርቅ ቅኔ ስናገር እያፋቸልኩ መሆኔን ስለማውቅ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ በዚህች ጦማር ያቀረብኩትን እንዲያረሙልኝም በትህትና እየጠየኩ ሐተታየን እቀጥላለሁ፡፡
ባንድማታው ት/ቤት በነበርኩበት ወቅት ትኩረቴ በአንድምታው ትርጓሜ ላይ ቢሆንም፡ ከጎጃም ወደ ደብረ ሊባኖስ ላንድምታው ትምህርት ስሄድ የሸኙኝ የቅኔ መምህራን “በገዳሙ ካሉት ቅኔ ከሚዘረፍባቸው፡ ግሥ ከሚገሰስባቸው፡ የቅኔ አገባቦች ከሚተነተኑባቸው ጉባዔ ቤቶች እግሮችህ እንዳየነቀሉ ብለው መከሩኝ፡፡ ከቅኔ ጉባዔቤቶች መራቅ፡ ከደመና የሚወርደውን ዝናብ ከራስ እያከንባለለ ወደ መሬት እንደሚደፋው ገሳ (የዝናም ልብስ) ከመምህራን የሚጎርፈውን ትምህርት ጭንቅላትን ሳይነካ ከመሬት እንዲፈስ ያደርጋል” ብለው የሰጡኝን ምክር ተቀብየ ደብረ ሊባኖስ በቆየሁባቸው ዐመታት ቀን ቀን ያንድምታውን ትምህርት እየተከታተልኩ ማታ ማታ ከቅኔ ትምህርት ጉባዔ አልተለየሁም ነበር፡፡
በገዳም ውስጥ በተለያዩ ሙያወች ጉባኤ ዘርግተው የሚያስተምሩ አባቶች ብቻ የሚሳተፉበት በየኔታ ፍስሐ ዘልቱት ልሳኑ ቤት፤ በራሳቸው በየኔታ ፍስሐ የምትመራ ምሥጢር ማደላደል በሚባል ስም በየሳምንቱ ዐርብ ከሰአት በኋላ የሚያካያሄዱባት ጉባዔ ነበረቻቸው፡፡
በጉባዔዋ ተሳታፊወች ሊቃውንት አበው መካከል በተለያዩ የቅኔ ስልቶች ሊቅነታቸው የታወቁ ሁለት ዐይነ ስውራን መምህራን ነበሩ፡፡ ሁለቱንም መምህራን ከሚኖሩባቸው ቤቶች እየመራሁ ወደጉባዔዋ ቤት እወስዳቸው ነበር፡ ጎዳና በሚባለው የቅኔ እውቀት ተጠያቂ የነበሩት የኔታ ዓምዴ ከገዳሙ ማእከል ራቅ ብለው ፍኖተ ጽድቅ (ውሻ ገደል) አካባቢ ይኖሩ ነበር፡፡ በሰምና ወርቅ እና ሠረዝ ለሚባሉት የቅኔ ሙያወች ተጠያቂ የነበሩት የኔታ አንዳርጌ የአዲስ አበባ ባለሀብቶች በገዳሙ ክልል ውስጥ የሰሩትን አዳራሻ ለቅኔ ትምህርት መስጫ አድርገው በታዛ ይኖሩ ነበር፡፡ ወደየ ቤታቸው ለመመለስ ጉባያቸውን እስኪጨርሱ በነበረኝ ቆይታየ በሚነጋገሩባቸው እሴቶች ላይ የሚለዋወጧቸውን ሐሳቦች በሰምናወርቅ ድርብርብ ሐተታወች እያሰናሰሉ ሲቋጯቸው እሰማ አዳምጥ ነበር፡፡
ለመወያየት የሚጠቅሷቸውን እሴቶች በሰምናወርቅ እያሳሳቡና እያጓተቱ ትንታኔያቸውን የሚያሰናስሉበት ፈሊጥ፡ ወደ አስኳላው ትምህርት መጥቼ በወስድኳቸው ኮርሶች ፈረንጆቹ በAntiquity እና በModernity (በቀደምትና በደሐርት) እያሰናሰሉ ከሚተነተኑባት ፈሊጥ ጋራ ተመሳሳይነት እንዳላት ተረዳሁ፡፡ ከዚህ ቀጥየ ወደ ሰንሰላዊት ሰምናወርቅ ቅኔያችን እሻገራለሁ፡፡
ሰንሰላዊት ሰምና ወርቅ ቅኔያችን “Oral literature”
በደብረ ሊባኖስ ገዳም የነበሩት ምሥጢር ማደላደል በተባለችው ቤተጉባዔ ይሰበሰቡ ከነበሩት ሊቃውንት አባቶች እንደ ሰማሁት ሰምናወርቅ ቅኔ ከፈጣሪ ወደሰው ወርዷል፡፡ በ Oral literature የምትፈረጀው የሰምናወርቅ ቅኔያችን ጀማሪውና ዘራፊው እግዚአብሔር ነው፡፡ በእግዚአብሔር ተዘርፈው “እም ኀበ አልቦ ኀበ ቦ” የመጡት ፍጥረታት የግዚአብሔር ሰምናወርቅ ቅኔ ናቸው፡፡
በመጀመሪያ ይህችን ዐለም በውስጠ ወይራ፡ በውስጥዘ ጎዳናና ሠረዝ ቅኔ ፈጥሮ፦ የቅኔ ምንጭ አድርጎ የፈጠራትን ዓለም አብጃት ተቀኛት ብሎ፡ ነፍሱን ወርቅ፡ ቁሳካላዊ ሥጋውን ሰም አርጎ፡ ሰውን በመፍጠር የቅኔ ተማሪው አድርጎታል፡ አብሉዲስ የተባለው ሊቅ “ንታመን በፍጡር በተዋህዶተ ፈጣሪ ምስሌሁ ሶበ ኀብረ ፈጥሪ ምስለ ፍጡር፡፡ ኮነ አሐደ ሕላዌ ጽኑዐ በአሐዱ አካል፡፡ ወአኮ በክልኤ ሕላዌ” (39፡23_14) እንዳለው፡ በንፍስ በሥጋው ሰምናወርቅ ሆኖ የተፈጠረ ሰው ወርቅነቱን አጥቶ በሰምነቱ ሲቀልጥ ክርስቶስ መልሶ የሰራው መለኮቱን ወርቅ፡ ከቅድስት ድንግል ማርያም የነሳትን ትስብእ ሰም አርጎ በተዋህዶ ነው፡፡
ሰምና ወርቅ ቅኔያቸውን እንደ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት የእምነታቸው መተርጎሚያ ባያደርጉትም፡ ኢትዮጵያ የምትጋራቸው የጥንት ሰወች አካባቢያቸውን ይገልጹበት ነበር፡፡ በግሪክና በሌሎችም አካባቢ ከተሞች አርዮስፋጎስ በሚባል ጉባኤ የቅኔው ትምህርት ይካሄድ ነበር፡፡ በባቢሎንና ባካባቢው ከተሞችም ሰምና ወርቅ ወይም ውስጠዘ ወይም ውስጠ ወይራ ወይም ጎዳና ወይም ሠረዝ ከሚባሉት ከቅኔ አይነቶች የቱ የቅኔ አይነት በየት አካባቢ ይሰጥ እንደነበረ ተለይቶ ባይታወቅም፡ አሁን በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታዛወች በመካሄድ ያሉት የቅኔ አይነቶች ይካሄዱ ነበር፡፡
ሰምና ወርቅ ቅኔ ቆጥሮ የተቀኘ ሁሉ የቅኔ ፊደል ቆጠረ እንጅ፡ ቅኔ አውቋል አይባልም፡፡ አንድ ሰው ቅኔ አወቀ የሚባለው የቅኔ መጻሕፍት ተብለው በተለይም እንደ ኢዮብ ያሉትን መጻሕፍት ይዘታቸውን አድቅቆ መማርና ሥረወ ነገራቸውን መረዳት አለበት ይላሉ፡፡
ኢዮብን እንደማሳያ አርገው ይጠቅሱታል፡፡ ኢዮብ ከሊቃውንቱ አንዱ ነበረ፡፡ በታመመ ጊዜ ሊጠይቁት ሊያጽናኑት ከየቦታቸው ወደሱ የሄዱት ሶፋር ኤልፋዝ በልዳዶስና ኢሊሁ ተብለው የተጠቀሱት አቻወቹ የቅኔ ሊቃውንት ፈላስፎች ናቸው፡ የፍልስፋናቸው አካሄድ ወደ agnostsizm የተጠጋ ነበር፡፡ የኢዮብ ጥበብ ግን በፈጣሪ ሕልውና የተደገፈ ስለነበረ፦ አቻወቹ በራሳቸው ፍልስፍና ብቻ በመመራት ኢዮብን ተገዳደሩት፡፡ ይሁን እንጅ በፈጣሪ የተደገፈው የኢዮብ ቅኔ ነጥቆ ወጣ፡፡ የነ በልዳዶስ ፍልስፍናና ምክር እንኳን ለኢዮብ ለራሳቸውም አልጠቀማቸውም፡፡ በኢዮብ እግር ስር ከመበርከክ አላዳናቸውም፡፡ በነፍሱና በሥጋው ሰምና ወርቅነት ላይ የተመሰረተው የኢዮብ ቅኔ፡ እስኪሞት ድረስ በሰምናወርቅነት ማለትም በሞራልና በቁስአካል ጸጋ ምድራዊ ዘመኑን ፈጸመው (ኢዮብ 42፡7_17)፡፡
ነቢዩ ዮናታን ንጉሥ ዳዊትን ይግባኝ የሌለው ሞት በራሱ እንዲፈርድ ያንበረከከው በሰምናወርቅ ቅኔ ነው ነበር፡፡ ዳዊት የኦርዮንን ሚስት ስለፈለገ ማንም አያውቅብኝም ብሎ በሴራ ኦርዮንን አስገደለው፡፡ ነቢይ ዮናታን የኦርዮንን ሚስት በተዘረፈች በግ፡ ንጉሥ ዳዊትን በዘራፊው ግፈኛ መስሎ በተቀኘው ሰምናወርቅ ቅኔ ራሱን ዳዊትን አስቆጥቶ የሞት ፍርድ በራሱ ላይ እንዲፈርድ ያደረገው በሰምናወርቅ ቅኔ ነበር፡፡ ንጉሥ ዳዊት በራሱ ላይ ተፈጽሞ የሚቆም ፍርድ ብቻ አለነበረም የፈረደው፡፡ ፍርዱ በሌላ ሰው ላይ የሚወድቅ መስሎት “ይህን ያደረገ ሰው ሞት ይገባዋል” ካለ በኋላ፡ የገዳዩን ዳብዛ ጭራሽ ለማጥፋት “ስለታረድችውም በግ አራት እጥፍ መክፈል አለበት”(6) ብሎ የፍርዱን ሸከም እጅግ አከበደው፡፡ ዮናታንም “ያ ይህን ከባድ ፍርድ ያከበደክበት ሰው አንተነህ! ብሎ የፍርዱን ጽዋ ዳዊትን ከጋተው በኋል፤ ዳዊት በፈረደበት ልክ፡ የራሱን መንግሥት ዳብዛ የሚያጠፋ “ሰይፍ ለዘላለም ከቤትህ አይርቅም” (2ኛ ሳሙ 12፡10) የሚለው መርገም ከነቢዩ ዮናታን አንደበት ተሰነዘረበት፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት የቅኔ አይነቶች የትኛው እንደነበረ ባይታወቅም ሙሴ ወደ ፈሮን ቤተ መንግሥት ተወስዶ ባደገበት ዘመን፡ በግሪክ በሮም በከለዳውያን ይካሄድ የነበረው በፈሮን ቤተ መንግሥት ይሰጥ ስልነበረ እንደ ቤተ ምንግሥት ልጅነቱ እድሉ ገጥሞት ከግብጽ ወደ ምድያም ተሰዶ እስከሄደበት ዘመን ለ40 አመት ተማረው፡፡ በዚህም ሳይወሰን ፤ ምድያም በምትባለው ከተማ በስደት ሄዶ ዮቶር ከሚባለው ኢትዮጵያዊ ሊቅ ተጠግቶ የኖረበትን 40 አመት ቅኔ በመማር ተጠቅሞበታል፡፡
ቅኔው በተላላቅ ከተሞች የማመለኪያ እና አብየተ መንግስታት ታዛወች ይካሄድ እንደነበረ በመጽሐፈ ዳንኤል ተገልጧል ናቡከደነጾር የማረካቸው ወጣቶች የነበራቸው እውቀት በፍሮን ቤተ መንግሥት ከነበረው ጋራ ተመሳሳይ መሆኑ ባይረጋገጥም፡፡ ወጣቶቹ አገራቸው በተማሩት ብቻ ለአመራር ስለማያበቃቸው የባቢሎንን ቅኔ እንዲማሩ ናቡከደነጾር አዝዟል (ዳንኤል፡3_5)፡፡ ወጣቶችም “ጥበብና ኃይል ለእርሱ ነውና ነገሥታትን ያፈልሳል ያስነሳል ጥበብን ለጠቢባብ እውቀትንም ላስተዋዮች ይሰጣል”(2፡20_) ብለው የቅኔ ምንጭ አምላክ መሆኑን እየገለጹ የባቢሎናውያንን ግብዝነት በማውገዝ መፈክር አሰምተውበታል፡፡
ስለ ቅኔም ሆነ ስለተልያዩ የፍልስፍና አይነቶች የተጻፉባቸው የሚጠቀሱ ሌሎች መጻሕፍት ቢኖሩም፡ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት የበለጠ የሚያተኩሩት ከብሉያትና ከሐዲሳት በሚያገኟቸው ምልክቶች ላይ ነው ከሚጠቅሷቸው ምልክቶች መካከልም የመጀመሪያወቹን ክርስቲያኖች የተገዳደሯቸው ናቸው፡፡ በክርስትና ይሰበክ የነበረው ዘላለማዊ ሕይወት አጥብቀው ይቃወሙ የነበሩት ለኦሪቱ እምነት ጠበቆች ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ብቻ አልነበሩም፡፡ በየቤተ ምኩራቡ ታዛ በነበሩት ጉባኤ ቤቶች እየተሰበሰቡ
ስለ አገር ስለ ሕብረተ ሰብ በቅኔያቸው የሚነጋገሩ መምህራንና ተማሪወች እንደነበሩ ከሚያስረዱት አንዱ የክርስትናው መጽሕፍ ነው፡፡
ክርስትና በየቤተ ምኩራቡ እየሰረሰረ ሲገባ ዓለምን ከሚረዱበት ቅኔያቸው ጋራ ስለተጋጨባቸው ክርስትናን አጥብቀው የተቃወሙት የኢዮብን ሳይሆን የነ በልዳዶስን ቅኔ የተማሩ ነበሩ፡፡ እንዚህን ምfhራን ካንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እንዲሄዱ ያደረጋቸው የሚከሰተውን ሁሉ ትርክት በቀላሉ አለመቀበላቸው ነበር፡፡ የመጀማሪውን ክርስቲያን ቅዱስ እስጢፋኖስን የገጠመው ተግዳሮት በአካባቢ በነበረችው ቤተ ምኩራብ እየተሰበሰቡ ይወያዩ የነበሩ በቅኔ ምርምራቸው በዘመናቸው የሚካሄደውን ፖለቲካና የተከሰተውን ክርስትናን ጭምር በቀላሉ አለመቀበላቸው ነው፡፡
ጠ/ምንስቴር ዓቢይ ምእመናንን ያስፈጇቸውን ተኩላወች ሰብስበው በበጎች ምስለው እየጎተቱ የጠፉ በጎች አመጣሁለዎ ብለው ወደ ፓትርያርኩ ሲወስዱ፡ ፓትርያርኩ “በጎችማ አይደሉም፡፡ ተኩላወች ናቸው” እርሰዎም ተኩላወችን በጎች ብለው መሰየመዎ ትክክል አይደሉም” ማለት ሲገባቸው የተነገራቸውንም የቀረቡላቸውንም ተቀብለው ማጽደቃቸው፤ ጠቅላይ ምንስቴሩ በሚመሩት መንግሥትም፡ ራሳቸው በሚመሯት ቤተ ክርስቲያንም “ሰይፍ ለዘላለም ከቤትህ አይርቅም” የሚለውን መርገም አስከተለ፡፡
የዘመኑን ፖለቲከኝችን የሚመስሉ “የነጻ ወጭወች በተባለችው ምኩራብ ከቀሬናና ከእስክንድርያም ከኪልቅያም ከእስያም(የሐ 69) የሚሰበሰቡ ነበሩ፡፡ ከተጠቀሱት አገሮቻቸው በፖለቲካ ተሰደው እንዴት ነጻ እንደሚወጡ ይወያዩ ነበር፡፡ እስጢፋኖስን የተገዳደሩት እነዚህ የፖለቲካ ስደተኞች ሲሆኑ ለኦሪቱ እምነት ጠበቆች የነበሩትን ጸሐፍት ፈሪሳውያንን አንሳስተው እስጢፋኖስን ያስገደሉት የጊዜውን ፖለቲካ በቅኔ ስልታቸው የሚመራመሩ ነበሩ፡፡ (የሐ 7፡57_59)፡፡
ቅዱስ ጳውሎስንም የተቃወሙት “ወቦ እምውስተ ጠቢባን እለ እምትምህርተ ኤፊቆሮስ ወካልዐን ይሰመዩ ረቃይያን እለ የሀዝወ ወመንፈቆሙ ይብሉ ምንተ ይፈቅድ ዝ ዘራኤ ነቢብ ወካልዐን ይቤሉ ትምህርተ አምላክ ሐዲስ ይሜህር እስመ ሰበከ ሎሙ በእንተ ኢየሱስ ወትንሣኤሁ እሙታን”(የሐዋ 17፡18)፡ እንዳለው፡ የክርስቶስን አምላክነቱንና ከሙታን ተለይቶ መነሳቱን በራሳቸው ፍልስፍና እየለኩ ስለተጋጨባቸው የተገዳደሩት በዚያው በቅኔው ስልት የዘመናቸውን ሁኔታ በመቃኘት ላይ የነበሩ ምfhራን ነበሩ፡፡ በየ አደባባዩ በየፍርድ ቤቱ በነቅዱስ ጳውሎስ ላይ ምስክር እየሆኑ ቀረቡ፡፡ በቅዱስ ጳውሎስ ንግግር እየተማርኩ አዲሱን የክርስትናን ትምህርት የተቀበሉ ዲዮናስዮስና ድማርስ የሚባሉም እንደነበሩ ተመዝግቧል፡፡ (የሐዋ 17፡34)፡፡
በአርዮስፋጎስና በከለዳውያን ፍልስፍና የሰለጠኑት እነሱ አካባቢያቸውን ከሚከተረጉሙበት ለየት ያለውን የክርስትናን ሐሳብ ለመቀበል ፈቃደኞች ባለመሆናቸው ቅዱስ ጳውሎስን ተቃወሙት፡፡ “ወቆመ ጳውልስ ውስተ አርዮስፋጎስ ወይቤሎሙ አንትሙ ሰብአ አቴና እሬእየክሙ ተአብዱ በኩሉ”(22) እንዲል፦ ከሌሎች ሐዋርያት ይልቅ የሕግና የቅኔ ምfhር ስለነበረ ቅዱስ ጳውሎስ ታገላቸው (1ኛ ቆሮ 1፡ 18_28)፡፡ በእግዚአብሔር ላይ ከነበረው ፍጹም እምነቱ ጋራ ሙሴን ያጠነከረውና ባሸናፊነት እንዲዘልቅ ያደረገው ከነ ዮቶር ይቀሰመው እውቀት እንደነበር እነ ቅዱስ ጳውሎስንም ሳይበገሩ ተልእኳቸውን እንዲወጡ የረዳቸው በ antiquity modernity እየተጓተተ ከኛ ደርሶ የምንማረው ሰምናወርቅ ቅኔ ነው፡፡ ሰምናወርቅ ቅኔያችን ከነፍስና ከሥጋችን ውህደት ተነስታ የባልንና የሚስትን ጥምረት መሰረት በማድረግ
ከቤተ ሰብ ወደ ጠቅላላ ብሔረ ስብ በመሻገር ኢትዮጵያዊነትን የምታስተምር ከዘመናችን ሲኖዶስና ከትውልዱ የተሰወርች ረቂቅ ምሥጢር ናት፡፡
ቅኔያችን ኢትዮጵያውነትን የምታስተምር፣ ከዘመናዊው ትውልድ የተሸሸገች ረቂቅ ምሥጢር ናት፡፡
ኢትዮጵያዊ ሕብርነታችን እንደተገነባባት እንደኛ ቅኔ “lense of binery opposition” ተብላ ለንጽጽር የተጠቀሰችው የደርዳ ስልት፡ የፈረንሳይ ሕብረተው ሰብ የተገነባበት አይመስለኝም፡፡ “lense of Derrida’s binery opposition” የሚለው የደርዳ ሀሳብ ከኛ ቅኔ ቀመር ጋራ ተቀራራቢነት ያለው ቢመስልም፦ እንደኛ ቅኔ ከነፍስና ከሥጋ ተነስቶ እስከ ማህበራዊ ትስስር ዘልቆ የሚሄድ አይመስለኝም፡፡ አባቶቻችን የሰምናወርቅ ቅኔን ሂደት በብዙ ምሳሌ ይገልጹታል፡፡
የባለቅኔን ራስ ከሴት ማሕጸን ጋራ፡ ቅኔን ከጽንስ ጋራ እያነጻጸሩ፤ የቅኔን አካላዊ ጥንቅር ይገልጹታል፡ የናት ሰፋድል ከውጭ የሚቀበለውን የወንድ ዘር ከራሱ እንቁላል ጋራ አዋህዶ፤ አርግዞ ያልነበረ አካል በመውለድ ለህብረተ ሰቡ እንደሚያቀብል፡ ባለ ቅኔም ከህብረተ ሰቡና አካባቢው የሚነጸባረቁትን ክስተቶች ተቀብሎ ከራሱ ሐሳብ ጋራ አዋህዶ አዲስ አሳብ ለሕብረተሰብ ያቀርባል፡፡ የተረገዘ ጽንስ ለመወለድ የናቱን ፈቃድ አይጠይቅም፡፡ በባለ ቅኔ ራስ የተጸነሰ ሀሳብም ፈንቅሎ ለመውጣት የባለቅኔውን ፈቃድ አይጠይቅም፡፡ በዚህ ሂደት የሚከናወነውን በጽfhፍ ገልጦ ለማሳየት አቅም እንደሚጠይቅ የቀረበውን አንብቦ ለመረዳት ደግሞ የበለጠ አቅም ይጠቃል፡፡ በጽfhፍ ለመግለጽ አቅሜን ፈትኖታል፡፡ አንብቦም ለመረዳት አንባቢን እንደሚፈትን እረዳለሁ፡፡ አማራጭ የለምና ለምሳሌ ያህል በዚህ መጽሐፍ በተጠቀሰችው ጉባዔቃና በኩል ወደ ጥልቁ ቅኔያችን ሰምጬ እገባለሁ፡፡
“ለጸብሕ ሞት ጸዋሚ መላከ ሰማይ ኃደጋ፡ ጸብሕ ሞት እስመ ተሠርዐት በሥጋ” የምትል ጉባዔ ቃና በመጽሐፉ ተጠቅሳ አይቻለሁ፡፡
ቅኔዋ የሕብረተሰብን ውጥን የምትገልጽ ጥሩ ሰምና ወቅር ናት፡፡ በአራት ሐረጎች ላይ ተመስርታ ጋ በተባለችው ፊደል በሚያልቁ ሁለት ስንኞች ቤት የምትገጥም ናት፡፡ የመጀመሪያዋ ስንኝ በ ኃደጋ ግሥ አልቃለች፡፡ ሁለተኛው ስንኝ ጋ በተባለች ፊደል ባለቀችው በ ሥጋ ቤት ተሰርታለች፡ ሁለቱም ስንኞች ሰምና ወርቅ ሆነው በጋ ፊደል ገጥመዋል፡፡ ቤት ሰርተዋል፡፡ የህበረተስብ ውጥን ሆነዋል፡፡
መላኩና ጸዋሚው ሰው ሰምና ወርቅ ሆነው በገቢርነት (active )ቀርበዋል፡፡ ወጥና ሞት ሰም ሆነው በተገብሮነት (pasive) ቀርበዋል፡፡ “ተሠርአ” የምትለው ግሥ በሕብርነት ሞትንና ወጥን ያቆላለፍች ማሰሪያ ግስ ናት፡፡ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን በጾም ወቅት በሥጋ የተሰራ ወጥ አይቀምስም፡፡ ሞት የተሰራው ለሥጋ ለባሽ ስለሆነ መላኩ ሞትን አይቀምስም፡፡ ማለት ነው፡፡ የማይገናኙት ሞትና ወጥ የተቆላለፉበት ፈሊጥ “lense of Derrida’s binery opposition” ተብሎ የተገለጸው ደርዳአ ከተባለው ፈርንሳዊው ፈሊጥ ጋራ ይቀራረባል፡፡
በአራት ሐረጎች ተመስርታ በሁለት ግጥሞች ቤት በመምታት(በመግጠም) የተዋቀረችው ጉባዔ ቃና የሕብረተሰብ መነሻ የሆነችውን የአንዲትን ቤት (ጎጆ) ትወክላለች፡፡ ባንዲት ቤት ወይም ጎጆ ተጋብተው በባልና ሚስትነት ተጋጥመው በጋብቻ አንድ ላይ የሚኖሩባትን ቤት ሰርተው በሰምናወርቅነት ተጣምረው መኖራቸውን ታሳያለች፡፡
ጉባኤቃና ቅኔ ስታድግና ስትሰፋ ከሁለት ግጥምነት ወደ ስምንት ግጥምነት፡ ከአራት ሐረጎች ወደ 16 ሐረጎች ዘልቃ ትሄዳለች፡፡ ስሟም ተለውጦ መወድስ ትሆናለች፡፡ በነፍሷ ወርቅ በሥጋዋ ሰም ሆና የተሠራችው ሚስት እሷነቷን ይዛ፡ በነፍሱ ወርቅ በሥጋው ሰም ሆኖ የተፈጠረው ባልም እሱነቱን ይዞ ሲገናኙ ሰምናወርቅ ይሆናሉ፡፡ ከነሱ የሚወለደው ልጅ የሁሉንም ሰምና ወርቅነት ሰውነት ይዞ ወላጆቹን ሕብር ያደርጋቸዋል፡፡
በአራት ሐረጎች በሁለት ግጥሞች የተዋቀረችው ሰምናወርቅ ጉባኤቃና፡ አድጋና ስፍታ በ 16 ሐረጎች ላይ ተመሥርታ በ8 ቤቶች ተጋጥማ እንድምትቀመረው መወድስ ቅኔ፡ ከጽንፍ እስከ ጽንፍ በኢትዮጵያ ምድር የሚኖረው ዜጋ ሁሉ ከሁለት ባልና ሚስት ጥምረት ግጥም ከምትሰራ ቤት ተነስቶ፡ ከሚስት እናትና አባትም ከፍ ሲል ወንድና ሴት አያቶችና፡ እንዲሁም ከባል እናትና አባት ከፍ ሲል ከባል ወንድና ሴት አያቶችና ቅድመ አያቶች ሐረግ እየተሳሰረ በመስፋት ፡ ከጽንፍ እስከ ጽንፍ ያለው ሁሉ ዜጋ በሥጋ በደምና ባጥንት መተሳሰሩን ያሳያል፡፡ ይህም ማለት መላው ሕብረተ ሰብ አንድ መወድስ ቅኔ ሆኗል ማለት ነው፡፡
በብዙሐኑ የምትታወቀው የጉባኤቃናዋ ቅኔያችን ይዘት ወደመወድስ ሲሻገር ድርብርብነቱን እየላጡ ለማላቀቅ “ከመ ቅርፍተ ስጉረድ” ማለት እንደ ቀይ ሽንክርት አሰልች ይሆናል፡፡ antiquity በ modernity ውስጥ እንዳለና modernityም በ antiquity ውስጥ ህልውነትን እንደሚወራረሱ፡ በኢትዮጵያ ምድር የሚኖሩትም ማለትም፡ ትግሬ ባማራው፤ባፋሩ በኦሮሞው በውራጌውና በሌላው፡ አማራውም በትግሬው በአፋሩ በሱማሌው በኦሮሞው በጉራጌና በቀሩት ሁሉ ሕዳጣን ዜጎች ተሠራርጓል፡፡ ሌሎችም ሕዳጣን ጎሳወች በአማራው በኦሮሞው በትግሬው ባፋሩና ደም ሥጋና አጥንት በተደራረበ በሰምና ወርቅ ቅኔ ተጋግረዋል፡፡
በጀነራል ውንጌትና በወይዘር ስሒን መምህራን የተመረዙ ያስኳላ ተማሪወች “ብሔር ብኄረ ሰቦች፡ ሕዝቦች ” እያሉ በሰምና ወርቅነት ተደራርቦ የተሰራውን ሕዝብ በግድ እየፈለቀቁና እየለያዩ እስከበተኑትና ኢትዮጵያንም እስከከፋፈሏት ድረስ በአዘቦት በዐላት በዘፈን በእንጉርጉሮ በቅራርት በሐዘን በደስታ በሰርግ በክርስትና በልቅሶ ከሕዝቡ የሚሰሙት ሁሉ ሕብረተ ሰባዊ ሰምናወርቅነት ነበር፡፡
ባለንበት ዘመን ባንድነት በመቆም የሰምናወርቅ እሴቶችን ለህዝበ ክርስቲያኑና ለቤተ እስራኤል ማስተማር የሚገባቸው የቤተምኩራብ ረቢወች፡ የእግዚአብሔርን በረከት ወደ ሕዝብ የማሻጋረ ብቃት የሌላቸው አቡኖች፡ ከሰምና ወርቁ ቅኔ የራቁ በመሆናቸው የግዕዙን ፊደል በሚንቁ፤ የላቲኑን ፊደል በሚያደንቁ፤ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖችና ቤተእስራኤሎች በሚገናኙባቸው እሴቶች ላይ በሚሳለቁ ወራሪወች ኢትዮጵያ ስትወረር እነሱም አብረው የሚወሩና የሚሳለቁ ሆኑ፡፡
ኢትዮጵያዊቷ ሰምናወርቅ ቅኔ የተሰወረችበት የዚህ ዘመን ፖለቲከኞች፦ ኢዮብን ሊያጽናኑት ከየቦታቸው ወደ ኢዮብ የሄዱትን የሶፋርን የኤልፋዝን የበልዳዶስንና የኢሊሁን በ agnostsizm የተመሰረተውን ቅኔ የተቀኙ መሰሉ፡፡ በዚህ ዓይነት ቅኔያቸው ኢዮብን ሊረዱት ቀርቶ ራሳቸው በኢዮብ በታች እንደወደቁ፡ የዘመናችን ኢሊቶችም በ agnostsizm ላይ በተመሰረተው ቅኔያቸው ኢትዮጵያን ሊያድኑ ይቅርና ራሳቸው እህታችን ጅጅ ሽባባው በተመራቸው ቅኔ ሥር ወደቁ፡፡
ጂጂ “ከመ ፋጻ ቀጢን” በተባለው ድምጿ የተመራቸው ባለ ቅቤ ጂጂን ተመሪ የኢትዮጵያን ሕዝብ ጭንቅላት አውደ ምህረት አደረገው፡ በዚህ ዘመን ያለን ቄሶች መቀኘት ቀርቶ መረዳት የማይችል ስለሆነበት ቅኔውን ከቅኔ ማህሌት አውጥቶ ራሱን መሪ ጂጂን ተመሪ አድርጎ አቀረበው፡፡
በጂጂ ቅላጼ የቀረበው ቅኔ ዘመን የማያሽረው ነው፡፡ የዘመናችን ሲኖዶስም፡ የፖለቲካ ሰዎችም አፋቸውን ዘግተው ከ ጂጂ ሽባበው እግር ስር ቁጭ ብለው፡
“ቅኑት ባለቅኔ ቅኔ የተቀኘው፡
ወርቁን በሰሙ ላይ ደራርቦ ጋገረው” ብላ የምታንጎራጉረውን ቢያዳምጡ፡ ከኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አመራርና ከኢትዮጵያውነት ፖለቲካ ምን ያህል ኋላ ቀሮች መሆናቸው እንዲታዘቡ ይረዳቸዋል ብየ እገምታለሁ፡፡
አለቃ አስረስ የኔ ሰው “Language is an Image, and an Image is a Ianguage, a language is a Fidel. Fidele is a statue, a satatue is is a Fidel. Fidele is a father and a Father is a Fidel.
Fidel is national symbole . National symbole is source of pride”(27). ብለው የቋንቋችንና የፊደላችን እሴትነት የገለጹበት ፈሊጥ ከብዙ መንገድ ቅኔወቻችን መካከል ሠረዝ የሚባለውን ቅኔ ይመስላል” ብየ ነበር፡፡ ከግዕዙ ቅኔ የተወረሱ፡ ኢትዮጵያዊነትን አሰርናስለው የያዙ ሲነገሩ የማይሰሙ የዘመኑ ፖለቲከኞች የበጣጠሷቸው የአለቃ አስረስን ፈሊጥ የሚያንጸባርቁ እሴቶች ባመረኛ ቋንቋችን አሉ፡፡ እንመልከታቸው፡፡ ባለ፤ ደም፤ ጋራ፤ አምጣ፤ ቤትና አገር የተባሉት ስድስት ቃላት ናቸው፡፡
አምስቱ ቃላት፦ በኛ አገባብ የምንላትን በእግሊዘኛ article የምትመስለውን “ባለ” የምንላትን እየተንተራሱ ኢትዮጵያዊት ሕብርነታችንን የሚገልጹ ናቸው፡፡ እነዚህ አምስቱ እሴቶች ባስኳላ ተማሬወች የፈረሱ ሲሆ ያስኳላ ተማሪወች ምን አፈረሳችሁ? ተብለው ቢጠቁ እንኳ ያፈረሷቸው በእነዚህ በአምስቱ ቃላት ላይ የተመሰረቱት ትርጉሞች መሆናቸውን አያውቁም፡፡
ዝርዝር ትርጉማቸው እንደሚከተለው ነው፡፡
ባለ፦ደም፡ እያንዳንዱ ዜጋ ለሁሉም ዜጋ ባለደም ነው፡፡ ሁሉም ዜጋ ለእያንዳንዱ ዜጋ ባለ ደም ነው፡፡ የግል የሆነ ደም የለም፡ ሁሉም በደም ተቀላቅሏል፡፡ ያልተቀላቀለ ንጽሕ ደም የለም፡፡ ያስኳላው ተማሪ ግን ትርጉሙን ገልብጦ በግድያ የሚፈላለግ በጠላትነት ገለበጠው፡፡
ባለ፦ጋራ እያንዳንዱ ዜጋ ደምን ቤትን ንብረትን አገርን ይጋራል፡፡ ማለትም የግሉ የሁሉም ነው፡፡ የሁሉም የሱ ነው፡፡ ያስኳላው ተማሪ መገዳደል መካካድን መዋሸትን መጋራት አድርጎ ገለበጠው፡፡
ባለ፦አምጣ እያንዳንዱ ዜጋ ለሁሉም ዜጋ ባለአምጣ ነው፡፡ አንዱ ላንዱ የሚያመጣለት የሚሰጣጣው የሚቀባለው የሚዋዋሰው ነገር አለው፡፡ ያስኳላው ተማሪ በጠላትነት ፈረጀው፡፡
ባለ፦ቤት እያንዳንዱ ዜጋ ከጽንፍ እስከ ጽንፍ በየደረሰበት ቤት እየሰራ ባለቤት ነው፡፡ ቤት የእግዚአብሔር ነው ፡ ያስኳላው ተማሪ ሞኝነት አደረገው፡፡
ባለ፦አገር እያንዳንዱ ዜጋ ከጽንፍ እስከ ጽንፍ ላለቸው አገር ባለ አገር ነው፡፡ ያስኳላው ተማሪ ራሱን ከተሜ እያደረግ የቀረውን ሕዝብ ኋላ ቀር አድርጎ ለመግለጽ ባለአገር አለው፡፡ “ብሔር ብሔረ ሰቦች፤ ሕዝቦች” እያለ በፈጠረው ትርክት ራሱን ካገር ባለቤትነት ቆርጦ ከሕብረተ ሰቡ ራሱን አገለለ፡፡
ከላይ “ወቅታውያን መነጋገሪያ የሆኑት “አርብርኝነታና ፋኖነት በጊዜና በጋጣሚ ሕዝባዊ ኩነት ተጸንሰው የሚወለዱ ናቸው” እንዳልኩት፡፡ ኢትዮጵያዊ አርባኛነትና ፋኖነት ከሕብረተሰቡ የሚፈልቁት እነዚህ ባምስቱ ቃላት የተዘረዘሩት እሴቶች በጠላት ሲበጣጠሱ፡ አፍራሾችን ተዋግቶ አሸንፎ ሕብረተሰቡን በነዚህ እሴቶች መልሶ ለማስተሳሰር ነው፡፡ ያምስቱ እሴቶች መፍረስ ጽንሶ የሚወልዳቸውን አርባኛነትንና ፋኖነትን ቀጥለን እንመልከት፡፡
ኢትዮጵያዊ አርበኛነት (ፋኖነት) — “Oral and Material Culture”
ፈንታሁን መላኩ “The Meccabean revolt impacted Chrstians who experienced oppration and religious persecution under political and religious forces”( 83) እንዳሉት መቃብያን የወደቃባቸውን ጭቆና ከላያቸው ለማስወገድ ያካሄዱትን መፋለም ቤተ እስራኤልና ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች የደረሰባቸውን ወረራና ጭቆና ከሚያሰውግዱባቸው ምሳሌ አንዱ አድርገው ተጠቅመውበታል፡፡
መቃብያን በኃይልም የነገር መወደድ ነበራቸው፡፡ ከሁሉም የምትበልጥ የልቡና ደም ጋባት ነብራቸው፡፡ ኃይል ሊቋቋማቸው ያልቻለ አርበኞች ናቸው፡፡ ጠላት ሊገላቸው ሲል ወደ ተራራ እያመለጡ ተዋጉ፡፡ በነሱ ምክንያት ካላመጣችሁ እየተባለ ህዝብ የሚጭነቅባቸው ነበሩ፡፡ (2፡1_14) በንጉሥ ቅጣት ያልተበገሩ (3፡3) “ለእውቀትህ ማነስና ስለ ልቡናህ ድንቁርና የኛን ሞራል ታየህ፡፡ የገደልከን መስሎህ ነበር ግን ደህንነትን አዘጋጀህልን”(4፡16) ይሉ ነበር፡፡ የዚህ ስነባህርያ ምሳሌ አርበኛነትና ፋኖነት ከሌሎች እሴቶች ጋራ ወደ ኢትዮጵያውያ ተሻግሯል፡፡
ኢትዮጵያውያን አርበኞች ወይም ፍኖወች ከዚህ በታች የተገለጸውን የመቃብያንን ባህርይ የተላበሱ ናቸው፡ “ወሶበ ፈቀዱ የአኀዝወሙ ለእሉ ቅዱሳን አምሰጡ እምእዴሆሙ ወአልቦ ዘነከዮሙ ወሖሩ እንዘ ይጸውሩ ነዋየ ሐቅሎሙ፡፡ እስመ እሙንቱ ወራዙት ጽኑአን ወኅያላን ፈድፋደ”(1ኛ መቃ 2፡7) ጠላት ሊይዛቸው ከዘረጋብቸው ወጥመድ አመለጡ፡፡ መሳሪያቸውን እየመዘዙ ሸፈቱ፡፡ በአርብርኞች መካከል በስም አጠራራቸው በጀግንነታቸው የታውቁ አርበኞች ነበሩ፡፡ “ወቦ እምኔሆሙ በውስተ ቀትል ዘይቀትል ምዕተ በአሐቲ ጊዜ በአሐዱ ሰይፍ ወከመዝ ስሞሙ ወንዒዎቶሙኒ ዝኩር በኩሉ ምድረ ሞአብ ወከለዳውያን”(1ኛ መቃ 2፡10) አርበኝነትን በተራራ በሸለቆ ተለማመዱ፡፡ “ወዓዲ መንክር ሥነ ላሕዮሙ ወምኩሉሰ ዝይኄይስ ሥነ ልቦሙ በእንተ ዘአምለክዎ ለእግዚ ወኢፈርህዎ ለሞት” (መቃ 2 ፡12) እምነታቸውን ቆራጥነታቸውን ደም ግባት ማለትም (የሕሊና ውበት) “ጭቋኞችን እምቢ እንድንላቸው የመንፈስ ጥናቱን ስጥን ብለው ፈጣሪያቸውን ለመኑ (17)፡፡ “ንህነሰ ኢንፈቅድ ንስማእ ቃሎ ለውእቱ ዕልው ዘኢተአመኖ ለሕግከ አላ በወርቅ ውብሩር በዕጽ ወበእብን ግብረ ዕደ ሰብእ ” 18 ፡፡ የፈለገው ይምጣብን እንጅ ሕግን ከሚጥስ ነፍስ ከሚገድል አመጸኛ ጋራ አንደራደርም አሉ “ከመብላት ከመጠጣት በብርና በወርቅ ከማጌጥና እግዚ የማይወደውን ሁሉ ኃጢአት ከመሥራት መራቅና ከሕሊና ዳኝነት ጸንቶ ከመኖር በቀር ሌላ ሕግ የላቸውም”(መቃ 23፡8) “ገንዘብ አለ በተባለበት ቦታ እየዘረፉ የራሳቸው የሚያደርጉ፤ ባይናቸው ያዩትን ሁሉ ለመብላት የጎመጁ አልነበሩም” (24፡12)፡፡
ኢትዮጵያውያን ኦርቶድኮስ ክርስቲያኖች ከላይ በተገለጸው ባህርይ ኢትዮጵያን ጥብቀዋታል፡፡ በቅኝ ግዛት ይሰቃዩ ለነበሩት ለአጎራባች አገሮች ምሳሌና አርማ እንድትሆን አድርገዋታል፡፡ በጥንትነት (በAntiquity) ከሚፈረጁት አገሮች ከግሪክ ከሮም፡ ከግብጽና ከባቢሉን ጋራ ተወዳዳሪ ተጠቃሽ ለመሆን
አብቅተዋታል፡፡ ቤተ እስራኤልና ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች የተጣመሩበትን አርባኝነትንና (ፋኖነትን) በየትውልዱ ሥነ ልቡና እንዲሠርጽ ማድረጓ የኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንችንን ከሁሉም ልዩና በሁሉም ተደናቂ አድርጓታል፡፡
የሙሴ የሕይወት ታሪክ ጸሐፊው ጥሩ አርገው አቅረበውታል፡፡ “In contrast to the western Cuhurch which distanced itself frm its Hebraic orign and came to identify itself as not Jewish, EThiopian Chrstianity retained its Hebraic elements for centuries.” (77) ክዕብራዊው ጥንትነት ራሳቸውን ካገለሉ ከምዕራባውያን ክርስቲያኖች ይልቅ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዕብራዊውን ባህል ለዘመናት ጠብቃለች ያሉትም ልክ ነው፡፡ የምዕራቡ ክርስትናም የሚነቅፈን በዚሁ ነው፡፡
የምዕራቡ ክርስትናም የሚነቅፈን ስለሰንበት በምንሰጠው ትርጉም ክርስትናው እምነት በኦሪቱ ተዋጠ ብሎ አሳስቦት አይደለም፡፡ ከሙሴ ስም ጋራ ተያይዘው ከሚካሄዱት ከሰንበቴና ከየጽዋ ማህበራት ላይ ያላቸውን ጥላቻ ለማንጸባረቅ ነው፡፡ አፍሪካን የወረሩ እነዚሁ የሚነቀፉን ራሳቸው ከሂብሩ ባህል የራቁ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች አገራቸውን የጠበቁ በሙሴ ስም የተደራጁት የጽዋና የሰንበቴ ማህበራት ናቸው፡፡ የተዋጓቸውም እነሱ ናቸው፡፡ ይህ አይነት ድርጅት ያልነበራቸውን አፍሪቃውያንን ሲወሩ ችግር ያልገጠማቸው፡ እንደኛ አባቶች በሙሴ ስም የተደራጁ የሰንበቴና የጽዋ ማህበራት ስላልነበራቸውና ስለ ሰንበት ያላቸው ግንዛቤ ከኛ የተለየ በመሆኑ ጭምር ነው፡፡
በኢትዮጵያውያን ኦርቶዶክስ ክርስቲያንች ሰንበት በ antiquity እና በmodernity የምትገለጽ ናት፡፡ የመሻርም ያለመሻርም ኩነት አላት፡፡ የተሻረችው ሰው ስለአስገደለች ከነበራት ክብር ዝቅ ብላለች፡፡ (ዘኁ 12፡35_36)፡፡ይልተሻረችው ክብሯን ለሰው ልጅ ለቀቀች እንጅ ጨርሳ አልጠፋችም፡፡ (ማቴ12፡8)፡፡
በሙሴ ስም የተዋቀሩት የጽዋ ማህበራትና ሰንበቴወች ሰንበት ክብሯን በለቀችለት በሰው ክብርና ልዕልና ላይ መሠረቱት፡፡ “በሰንበት መልካም መሥራት ተፈቅዷል”(12) ብሎ ክርስቶስ ባዘዘው መሠረት ሰንበት በግለሰብ በሕብረተ ሰብና በአገር ላይ የሚደርሰውን ተግዳሮት የመዋጊያ ሰንበት አድርገውታል፡፡
ሰንበት በጥንትነትና በድሀሪነት ሁለት ገጸ ባህርያት አሏት ፡፡ እንደ ኦሪቱ ለግል ተግባር ባለ መንቀሳቀስ እናከብራታለን፡፡ እንደ ክርስቶስ ትምህርት አጥሩ ቤቱ የፈረሰበትን በመስራት፡ ከቅም እጠረት ለጎደለበትን ሰው የጎደለበትን በመሙላት በምናደርገው መንቀሳቀስ እንሽራታለ፡፡ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ኦርቶዶክሱን ማሕበረስብ ሰንበትን በሚተኩት ሰንበቴንና የጽዋ ማህበራት ያደራጀችው በግልም በአገርም የሚደርሰውን ሁሉ ፈተና እንዲያሰወግድበት ነው፡፡
ኦርቶዶክስ ክራስቲያኖች “lense of Derrida’s binery opposition” በሚለው አተረጓጎም ከኦሪቱም ከምዕራቡም ክርስትናም ርቀታቸውንና ቅርበታቸውን ጠብቀዋል፡፡ እንደ ኦሪቱ ክግል ተግባራቸው ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ በመራቅ ሰንበትን አክብረዋል፡፡ እንደ ክርስትና ለአገር፡ ለሰው ልጅ ክብር በመስጠት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሰንበትን ሽረዋል፡፡
ቤተ እስሬሎች ተስፋ ወዳደረጓት ምድራዊት ኢዩሩሳሌም ስለገቡ አርፈዋል፡፡ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች በሰምናወርቅ አተረጓጎማቸው ምድራዊቷ ኢየሩሳሌም ክርስቶስ ሲመጣ የምትቀልጥ ሰም ናት፡፡
ሰማያውቷ ኢየሩሳሌም የምትባለው ለዘላለም የምናርፍባት መንግሥተ ሰማያት ወርቅ ናት፡፡ በዚህ ዓለም እስካለንና በተስፋ የምንጠብቃት ሰማያዊት ኢየሩሳሌም እስክትመጣ ድረስ በግልም በማህበርም በአገርም የሚመጣውን ቅኝ ገዥ ጠላት በሰንበቴና በጽዋ ማህበር ተደራጅተን እንዋጋለን፡፡ በዚህ አንምታ ትርጓሜ ኢትዮጵያ ተጥብቃ ኖራለች፡፡ እነ አጼ ምንይልክና እነ ነበላይ ዘለቀ የክተት ጥሪ እያስተላለፉ ኢትዮጵያን ከወራሪወች ያተረፉት በሙሴና በዮቶር አደረጃጀት በጽዋ ና በሰንበቴ ማህበራት የተደራጀውን ኦርቶዶክስ ክርስቲያኑን ነው፡፡
ልብሳችን “ግበሩ ዘርፈ በጽንፈ አልባሲክሙ” material culture
ስላማዊት ፍስሀ “The relationship between the logos in new Testament and the Torah laws/gram in the old Testament is one of the binary opposition; they are not truly separated but interdependent. Thie Symbolic interdendent relationship beteween Chrstianity and Judaism is beautifully encapsulated in the poetry of wax and gold Qene” (25) እንዳሉት፦ ኦርቶዶክስ ኢትዮጵያውያን ከቤተ እስራኤል ጋራ የተለያዩ ቢመስልም በእርግጥ አልተልያዩም ይልቁንም አንዳቸው ባንዳቸው ይገለጣሉ እንዳሉት እርስበርሳችን ከምንተረጓጎምባቸው አንዱ ልብሳችን ነው፡፡
“ግበሩ ዘርፈ በጽንፈ አልባሲክሙ፡፡ ይኩንኩም ውስተ ዘፈሩ ከመ ትዜከሩ ትእዛዞ ለግዚአብሔር” ”በዘኁ 15፡37 ተብሎ በታዘዘው መሠረት፦ ድሮ ኦርቶዶክስ ክርስቲያን የሆነ ሁሉ ወንዱም ሴቱም በልብሱ ጫፍ የጥለት ምልክት የሌለው ቀሚስ ኩታ ሸማ ሳይልብስ ከቤት የሚወጣ አልነበረም፡፡
በዐለም አቀፍ የቅብብሎሽ ተወራራሽነት የቆዩት ባህሎች ይለወጣሉ፡፡ በቀላሉ ከሚለወጡ ብዙ ነገሮች አልባሳት ናቸው፡፡ በልብስ ላይ የሚታየው ጥለት በቀላሉ የተገፋው ኢትዮጵያዊነትን አሰርናስሎ ከያዘው ከባለ አገርነት ጋራ ያስኳለው ተማሪ ዘመቶበታል፡፡ በተግባርም በቃልም ከባለአገርነት አስቀድሞ የራቀ ያስኳለው ተማሪ ስለሆነ ጥለት ካለው ልብስ መራቅን ተጽእኖ አሳድሯል፡፡
በዚህ ዘመን ኦርቶዶክሱ ክርስቲያን በየደረሰበት ተተከታታይ መከራ ብዙ እሴቶችን አጣ፡፡ ብዙ ከማጣቱም የተነሳ እጅግ በጣም ያዘነበት ዘመን ነው፡፡ ድሮ የደረሰበትን ሐዘን ለመግለጽ በክብር የለበሰውን በርኖስ በመግለብጥ የደረሰበትን ሐዘ ይገልጥ ነበር፡፡ ድሮ በርኖስ ገልብጦ እንዲለብስ ከሚያደርገው መከራ እጅግ የከፋ መከራ ስለደረሰበት ከቤተ እስራኤል ጋራ የሚጋራውን ጥለት ጥሎ “ጎጃም አዘነ” የተባለ ልብስ ለበሰ፡፡
በምግባችን እንጀራ material
ቤተ እስራኤልና እኛ በእለት ምግባቸው ተቆላልፈናል፡፡ የእለት ምግባችን በሩቅ ዘመን ዳሕጸ ልሳን እንጀራ ይባላል፡ቀዳሚ መጠሪያ ስሙ መና ማለት “እንጃ_ኧረ”ነው፡፡ “ወርእዩ ደቀቀ እስራኤል፡፡ ወይቤ አሐዱ ለካልዑ ፡ ምንት ውእቱ ዝ እስመ ኢያእመሩ፡ ወይቤሎሙ ሙሴ ዝ ውእቱ መና ዘእግዚአብሔር ወሀበክሙ”(ዘጸ 16፡15) እንዲል ይህም ማለትም፦ እስራኤላውያን የወረደላቸውን መና ከዚያ በፊት አይተውት ስለማያውቁ ይህ ምንድነው ተባብለው ተጠያየቁ፡፡ “ኧረ እኛም አናውቅም” ብለው ተመላለሱ፡፡ ወይም ‘ኧረ እኔ እንጃ’’ ማለት ነው፡፡ እንድትበሉት እግዚአብሔር የሰጣችሁ ብሎ የተናገረውን ባንዲት ቃል ጸጋ ሊለው ሲችል፡ እነሱ “ምንድነው? ብለው የተመላለሱትን ቃል አሳጥሮ ሙሴ መና(እንጃ ኧረ) የሚል ስም ሰጠው፡፡ ቤተ እስራኤል በ antiquity በ modrnity ከኛ ጋራ ከተጣመሩባቸው አንዱ የሆነውን እንጀራ ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም ገብተዋል፡፡
በጸሎት Oral literature
ዛሬ ከኢትዮጵያ ፈልሰው ወደ ኢየሩሳሌም የሄዱት ቤተ በ ኢትዮጵያ በነበሩበት ዘመን ግን እኛ ኦርቶዶክሳውያን በሰአታቱ ጸሎታችን “ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ እስራኤል ዘገብረ ዓቢየ ወመንክረ ብሕቲቱ” ብለን በምንጸልየው ጸሎት በሞት የተለየውን ወገን “ውስተ ሕጽነ አብርሃም ይስሐቅ ወያዕቆብ” ብለው ይሸኙታል ብለው አባቶች ሲናገሩ ሰምቻለሁ፡፡
ኢየሩሳሌም ሲደርሱ ከተለያዩ አገሮች ወደ ኢየሩሳሌም በገቡ ሰወች ተጽእኖ ይቀይሩት ወይም ይቀጥሉት አላውቅም፡፡ ሆኖም ከምዕራቡ ክርስትና ተለይተን ወደ ሂብሩ እንደምንቀርብ በጸሎታችንም አቀራረብ ከምዕራቡ ክርስትና ወደ ሂብሩ እንቀርባለን፡ የምዕራቡ ክርስትና የጀመረውን ጸሎት “በኢየሱስ ስም ይጨርሳል፡፡ የምዕራቡ ክርስትና ስለእኛ ካለው የመረዳት እጠረት በዚህም ይንቀፈናል፡፡ እኛ ደግሞ እነሱን የመረዳት እጥረታቸውን እንነቅፋለን፡፡
“በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ” ብለን እንጀምራለን፡፡ ዘላለማዊ ኃይልና መንግሥት ያንተ ናት” ብለን እንዘጋለን፡፡ በመንፈስ ቅዱስና በአብ መካከል የወልድ ስም በጸሎታችን ተጠርቷል፡፡ “መንግሥት ያንተ ነውና ኃይልም ክብርም ለዘላለም” ብለን ጸሎታችንን እንዘጋለን፡፡ ጽሎታችንን የምዘጋበትም፦ እራሱ ክርስቶስ ጸሎት ባስተማረበት አንቀጽ እንድንጨርስ የነገረንን ተከትለናል (ማቴ 6፡13) ፡፡ “በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ አጥምቁ” ብሎ የሐዋርያትን ተልእኮ ያወጀበትና ጥምቀታችን የታተመችበት ማሕተም ናት፡ “በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ መንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ” የምትለው ሐረግ በ antiquity ነት እና modernity ከሁሉም የሚያጋራንና ከሁሉም ልዩ የሚያደርገን ነው፡፡ ከሁሉም የተሻለ መሠረታዊ ሲሆን በሁሉም እንነቀፈበታለን፡፡
በሁሉም እንነቀፋለን
ከቤተ እስራኤል ጋራ በምንጋራቸው እሴቶች የሚነቅፉን ምዕራባውያን አብያተ ክርስቲያናት ብቻ አይደሉም፡፡ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ሰወችም ይነቅፉናል፡፡ ሁሉም የሚነቅፉን ከነሱ በተሻልንባቸው እሴቶቻችን ነው እንጅ ለነቀፋ የሚያበቁ ነገሮች ሆነው አይደለም፡፡
አባቶቻችን የራሳቸውን እምነት ካልነኩባቸው ማንንም በምነቱ አይነቅፉም፡፡ ቤተ እስራኤሎችም እንኳ ሳይቀሩ እንደተቀፉ ሲናገሩ ይሰማሉ፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች በቤተ እስራኤል ላይ እንኳን ነቀፋ ሊሰነዝሩ “ለመቅደስ ማገልግየ ሥራ ሁሉ ያደርጉ ዘንድ እግዚአብሔርን ጥበብንና ማስተዋልን የሰጣቸው የባስሌልና ኤልያብ” (ዘጸ 36፡1) የሚለውን መነሻ በማድረግ እግዚአብሔር የኤልያብን በረከት ያሳደረባቸው ልጆች ናቸው እያሉ የሚገልጿቸው በማክበር ነው፡፡፡፡
የሙሴን ቃል መሠረት በማድረግ “ወእሉ ኩሎሙ ይሴፈው በተግባረ እደዊሆሙ፡፡ ወኩሎሙ ይጠበቡ በግብሮሙ ወዘእንበሌሆሙ ኢይትከሀል ነቢረ በሀገር (ሲራክ 38፡31_32) ብሎ ሲራክ በተናገረው ይገልጿቸውል፡፡ ይህም ማለት፦ሁሉም በእጅ ሙያ የተራቀቁ ናቸው፡፡ያለነሱ አርሶ ማምረት፡ ነግዶ ማትረፍ፡ አጭዶ መከመር፡ አዝምሮ ማምረት አይቻልም፡፡ አገር እነሱ ናቸው፡፡ እነሱም አገር ነቸው” ያለነሱ
አገር የለም” ሲሉ ነው የምንሰማቸው፡፡ ነቀፌታውን የዘሩት እኛን የሚከፋፍሉ፡ በምንጋራቸው እሴቶች የዘመቱ ወይም በሐሰት ትርክት ከነሱ እንደወረስናቸው የሚያስመስሉ የውጭ ባእዳን ናቸው፡፡
Iris Habib el Masri የተባሉ የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊ “The sheep of Ethiopia have been delivered from the hyena of the west by the doctrine of st Ciril the great pillar of the Holy Orthodox Church of Egypt” (the history of the Copts 1982 pp 262) የሚል የሐሰት ትርክት በታሪክ መጽሐፋቸው ጽፈዋል፡፡
ይህ ትርክት ከቤተ እስራኤል ጋራ የምንጋራውን በደማችን የሠረጸውን አርባኝነት ከግብጽ ቤተ ክርስቲያን የወረስነው አድርጎ ያቀረበ የተሳሳተ ትርክት ነው፡፡ አባቶቻችን እንደሚነግሩን አርበኝነት ሙሴ ከኢትዮጵያዊው ከዮቶር የተማረው ከሌሎች እሴቶች ማለትም ከሰምና ወርቅ ቅኔያችን ጋራ የተሰናሰለ የመቃብያንን ባህል የሚያንጸባርቅ እንጅ ከግብጽ ቤተ ክርስቲያን ከምንጋራባቸው እሴቶች ጋር ምንም ግ ንኙነት የለውም፡፡
ከላይ እንደገለጽኩት አርበኝነት ጠቢቡ ሲራክ “ወጸሎቶሙኒ ከመ ይጠበቡ በውስተ ኪን”(ሲራ 38፡34) እንዳለው፦ “ኪን” የተባለችው “ተኬነወ” ከምንለው ግሥ የተወለድች ቅጽል ናት፡፡ ኪነት በጉሉህ የምትገልጸው ያፈጣጠርን ያስተዳደርን ያመራርን ሂደት ነው፡፡ ጠቢቡ ሲራክ ኪንን ከጸሎት ጋራ አያይዞ የጠቀሳት ሕዝባዊ አመራር በጸሎት ውስጥ፡ ጸሎት በህዝባዊ አመራር ውስጥ ያለ የማይለያዩ መሆናቸውን ለማሳየት ነው፡፡
በሙሴ ስም የተደራጁት ሰንበቴና የጽዋ ማህበራት አደረጃጀታቸው ኪነታዊነት ነው፡፡ የጸሎቶቻቸው መነሻና መድረሻ ኢትዮጵያ የተሰራችባቸው እሴቶች (ኪነታቶች) ላይ የተመሰረቱ ናቸው፡፡ አገር ሲወረር ዳር ድንበር ሲደፈር የህዝብ መሪወች ማለትም የሰንበቴ የጽዋ ማሕበራት መሪወች የማህበራቱ አባላት የጎበዝ አለቆች የክተት ጥሪ የሚያስተላልፉት በኪነታዊነት ለተደራጁት ማሕበራት ነው፡
፡ እነዚህ የመሰሉ ድርጅቶች የግብጽ ቤተ ክርስቲያን የላትም፡፡ ኢትዮጵያ ከምዕራቡ ጅብ የተረፈችውም የግብጽ ጳጳሳት “doctrine of st Ciril the great pillar of the Holy Orthodox Church of Egypt” እንዳሉት አይደለም፡፡ እንዳሉት ቢሆንማ የቅዱስ ቄርሎስን መጽሐፍ የሚጠቀሙ ኦርቶዶክሳውያን ሁሉ በተለይም ግብጾች ራሳቸው በተለያዩ ወራሪወች ከመቀጥቀጥ በዳኑ ነበር” ይላሉ አባቶቻችን፡፡
ጸሐፊው ይህን የሐሰት ትርክት የሰማው ከሕሊናቸው ወቀሳ ለመሸሽ ከሚሞክሩ የዘመናችንን ጳጳሳት ከሚመሰሉ ከግብጻውያን ጳጳሳት እንደሆነ ይነገራል፡፡ የግብጽ ክርስቲያኖች ግን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስን አመራር ምሳሌ በመከተል በፓትርያርክ የሚመራውን ሲኖዶሳዊ አመራር ከቤተ ክርስቲያን አስተዳደራቸው አስወግደው በሊቃውንት ክርስቲያኖች እንዲመራ እንቅስቃሴ ያደርጉ እንደነበሩ Hggai Erlich የተባሉት ዕብራዊ ጸሐፊ እንዲህ ብለው ጽፈዋል፡፡
“The majlis, perhaps the first manifestation of modern Coptic life, was the embodiment of the educated youth’s desire to be accepted by modern Egyptian society. In time this modern waing of the Coptic community would develop its own Ethiopian ideas, quite different from those of the patriarchate, the Holy Synod, and the Coptic Church establishment” (The Cross and the River page 68).
Erlich የተባሉት “In time this modern waing of the Coptic community would develop its own Ethiopian ideas, quite different from those of the patriarchate, the Holy Synod, and the Coptic Church establishment” እንዳሉት፦ከነ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በኋላ በፓትርያርክ የሚመራ በጳጳሳት ስብስብ አስተዳደር የተመሩ ክርስቲያኖችች እንኳን አገር ራሳቸውን አጡ ተሰደዱ፡፡ በፓትርያርክ የሚመራ ሲኖዶስ የሌላት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ራሷንም ኢትዮጵያን ከወራሪወች ተክላክላ ድልን ነጻነትን ለትውልዱ ያወረሰችው በሊቃውንቶቿ በመመራቷ ነው እያሉ ምሳሌነቷን ወደራሳቸው ለመውሰድ የሚታገሉ ግብጻውያን ሊቃውንት እንደነበሩ ጽፈዋል፡፡
ከነገረ ማርያም፡ ከጽዋ ማህበራት፡ ከሰንበቴወች ማሕበራት አደረጃጀት እና ከመቃብያን በተወረሰው ከቤተ እስራኤል ጋራ በምንጋራው አርባኛነታችን መሆኑን ሰውረው ከጵጵስና ጋራ ከነሱ እንደወርስነው ለማሳየት ያደረጉትን ሸፍጥ አባቶቻችን “እኛ ኢትዮጵያውያን ነጻነታችንን ያስከበርነው ግብጻዊው ጸሐፊ እንዳለው በቅዱስ ቄርሎስ ዶክትሪን ሳይሆን ሙሴ ከዮቶር የተማረውን ማኅበራዊ ሥርአት በመቃብያን የተገለጸውን አርበኝነት እና ቅድስት ድንግል ማርያም እመቤታችን ክርስቶስ በማሕጸኗ ሲያድር ያሰማቸውን መፈክር ከስነ ሕሊናችን ጋራ በማዘመዳችን ነው” ብለው መልሰዋል፡፡ ከዚህ ቀጥየ ዶክተር ጌታቸው ሰብስበው ያሳተሙትን መጽሐፍ በደመደሙት ምክራቸው ይህችን ጦማር እቋጫለሁ፡፡
የዶክተር ጌታቸው ምክር አዘል ድምዳሜ
“ብእሲ ምfhር ዘተገሰጸ ብዙኃ የአምር ወዘፈድፈደ ሕማመ ጥበበ ይነግር”(21፡9)” እንዳለው ጠቢቡ ሲራክ፦ ዶ/ር ጌታቸው ይህን መጽሐፍ የደመደሙበት በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በሕጻንነታቸው ተጠምቀው የሕይወት ጉዞ ከጀመሩባት ቅጽበት ጀምረው በግላቸውም በማህበራዊ ጥምረትም ካሰለፏቸው ብዙ ተግዳሮቶች የመነጨ ምክር ነው፡፡
“ወሀቦሙ ዕሤቶሙ ለዕለ ተሰፈውከ ከመ ይእመንዎሙ ለነቢያቲከ”(36፡21) ማለትም፦ስለ ቀደሙ እሴቶችም ሆነ ታሪኮች ለሰወች ስትናገር፡ ለመመስከር አቅምና ብቃት አለው ብለው የምትናገረውን በጉጉት ለመስማት ለሚጠብቁ ሰዎች ታሪካቸውን እንዲያስታውሱ ከራሳቸው ጋራ እንዲያገናዝቡና እንዲጠቀሙበትም በሚመጥናቸው ልክ ምከራቸው፡፡ የሚለውን መርሆ በመከተል የሚከተለውን ምክር ለሚመለከተው ሁሉ ሰጥተዋል፡፡
ከእምቅ ምልክታቸው የፈለቀው ምክር አዘል ሀሳብ፡ ለቤተ እስራኤሎችና በኢየሩሳሌም ላሉት እስራኤላዉያን ብቻ የተሰጠ ምክር ሳይሆን፡ ለሁላችንም አይን ገላጭ ሆኖ ስሜት የቀሰቀሰ ነው፡፡ በ2002 ዓ/ም ኢየሩሳሌምን በጎበኘሁበት በሁለት ሳምንት ብቻ ቆይታየ ያየሁትና የሰማሁት በተለይም በGrand Court Hotel Jerusalem በተደረገው ታሪካዊ ጉባኤ የተካፈልኩት “ኢይመልእ እዝን እመሰሚእ፡ ወኢይጸግብ ዐይን እምርእይ” የሚለውን መወድስ ቅኔ ከጭንቅላቴ ከአስፈነጠረው፡ ዶ/ር ጌታቸው እላይ በገለጽኳቸው ተደራራቢ እድሎች ካዩአቸው ከሰሟቸውና ከታዘቧቸው በመነሳት ይህን መጽሐፍ ከማዘጋጀታቸው ባሻገር ብዙ ይጠበቅባቸዋልና ብዙ አላስገረመኝም፡፡ ይልቁንም እጅግ ያሰደነቀኝ የታሪክ ንክኪ ያለንን የሁላችንንም መንፈስ የቀሰቀሰው እኛ ያላደረግነውንና ወደፊት ልናደርገው የሚገባንን ያሳዩበት ምክር አዘል ሐሳባቸው ነው፡፡
ቤተ እስራኤልን እንዲቀበሏቸው በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ነጮች እስራኤላውያን “They are the repository of the Jwish relgion and must not be labled as not being Jewish enough
because of their pigmentions”. ብለው በሰጡት ምክር በአማራኛ ቋንቋቸው በቆዳ ቀለማቸው እንዳያገሏቸው ይልቁንም ተጠብቆ የኖረውን የኦሪት እምነትና ስርአት ይዘውላቸው እንደሄዱ በመንገር ጭመር ነው፡፡ የተወደደ ወገን ተለይቶ ሲሄድ፡ የሚሄድበት አካል በክብር በፍቅር እንዲቀበለው የሚሰጥ ሐዋርያዊ የአደራ ቃል ነው፡፡ ይህ ያደራ ሸኜ ቃል ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ የሚጠበቅ ነበር፡፡
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ የሚጠበቅ ነበር ያልኩት፡ ቅዱስ ጳውሎስ የሚወደው አናሲሞስ ተለይቶት ወደ ፊልሞና ሲሄድ ፊልሞና የተባለው በክብር በፍቅር እንዲቀበለው “አኮ እንከ ከመ ገብር አላ ዘይሔይስ እምግብር እመሰ ኮነ ሊተ እኁየ እፎ ፈድፋደ ይኄይስ በኀቤከ በሥጋሁኒ በዘይደልዎ ይርዳእከ ወበሃይማኖትኒ ዘበእግዚእነ፡፡ ወእመሰ እኁየ ተወከፎ ከማየ፡፡ ወእመቦ ዘአእበሰ ለከ፡ አው እመቦ ዘየፈድየከ ላእሌየ ረሲ”(ፊል 16_18)፡፡ ብሎ ያስተላለፈው የአደራ ምልእክት ትዝ ስላለኝ ነው፡፡
ቤተ እስራኤሎች ከመሠረቷት ኢትዮጵያ አገራቸውና ቀዳሚነትንና ድሐሪነትን (antiquity and modernity) ከሚጋሯቸው ኦርቶዶክሳውያን ወገኖቻቸው ተለይተው በቋንቋ በቆዳ ቀለም ወደ ማይመስሏቸው ፈልሰው ሲሄዱ የሚጠብቃቸውን፦“Meanwhile, identity politics and social discourse would be exbected to continue at diverse levels against those who do ot look and speak like those who are the majority in all its manifestations.”(163) ብለው መክረዋል፡፡
ለቤተ እስራኤል እህቶቻችም “ኦ አዋልደ ኢየሩሳሌም ኢትርአየኒ እስመ አነ ጸላም፡፡ ጸላም አነ ወሠናይት፡፡እስመ ኢርእየኒ ጸሐይ” (መኃልይ 1፡5_6) ማለትም፦እንደ ሱላማጢስ “እናንት የኢየሩሳሌም ቆነጃጅት ሆይ እኔ ጥቁር ነኝ፡፡ነገር ግን ውብ ነኝ፡እንደ ቄዳር ድንኳኖች እንደ ሰሎሞን መጋረጃወች፡፡ ጸሐይ መልኬን አክስሎታልና ጥቁር ስለሆንኩ አትዩኝ” እያላችሁ ኑሮውን ታገሉ! ብለው ያበረተቷቸው መሰለኝ፡፡
ምክራቸው በኢየሩሳሌም ቤተ ምኩራብ ቤተእስራኤልን በማገልገል ላይ ያሉትን ካህናት ረባይዎችንም ያካተተ ይመስለኛል፡፡ ይህ ምክር ሙሴ የመምህሩን የዮቶርን ልጅ ኢትዮጵያዊቷን በማግባቱ የራሱ እኅት ባሳየችው ጥላቻ የደረሰበትን ያሳስባል፡፡ የሙሴ እኅት በፈጠረችው ዘረኝነት የደረሰባትን ቅጣት ተመልክቶ ”ከእናቱ ሆድ በወጣ ጊዜ ግማሽ ሥጋው ተበልቶ እንደ ሞተ እርስዋ አትሁን”(ዘኁ 12፡12) ብሎ አሮን ያሰማውን ድምጽ፡ በቤተ እስራኤል እህቶቻን ላይ ጥላቻና ነቀፌታ ለሚሰነዝሩት እስራኤላውያት ሴቶች እንዲያሳስቡ ለቤተእስራኤል ካህናት ይመክራሉ፡፡
በኢትዮጵያ ሳለን ፈላሻ እንባል ነበር እያሉ በመማረር ላይ ላሉትም፡ ዶ?ር ጌታቸው በሰጡት ምክር ፍልሰት ሰባዊ ኩነት እንደሆነ እያሳሰቡ መሰለኝ፡፡ ይህም ማለት ፍልሰት ካባት አብራክ ወደ እናት ማሕጸን ስንቀዳ፡ የመጀመሪያ ፍልሰት ነው፡፡ በናት ማሕጸን ከ9ኝ ወራት ቆይታ በኋላ በወሊድ ስንለይ ሁለተኛ ፍልሰት ነው፡፡ በዚህ ዓለም ቆይታ በኋል በሞት ይህችን ዐለም ስንለይ የመጨረሻ ፍልሰት ነው፡ እትብታችን ከተቀበረበት ቦታ ለቀን በሌላ ቦታ የምንኖር ሁላችን ፈላሾች ነንና በኩራት ተቀበሉት፡፡
ዶ/ጌታቸው ምክራቸውን በመቀጠል፦ አሁንም ከተወለዳችሁበት ቦታ ነቅላችሁ ወደ ኢየሩሳሌም የሄዳችሁበት የሚገለጸው በፍልሰት ነው፡፡ በAntiquity እና በ modernity የምትጋራችሁ ኢትዮጵያዊት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በዚያው ምድር ስትኖር በቀትር ለጸሀይ ሐሩር፡ በክረምት ለዝናም
መከላካያ የሚዘረጋውን ጥላ በህንጻው ውስጥ ዘርግታ የምትንቀሳቀሰው ፈላሲነትን እየመሰከረች ነው፡፡ ይልቁንም አምርረን በጋራ ልንጸየፈውና ልናወግዘው የሚገባ ከናንተ ጋራ በመሰረታት በሞተላት በኢትዮጵያ ምድር በኦርቶዶክስ ክርስቲያንና ባማራው ላይ እየተካሄደ ያለውን ፍልሰት ነው” የሚሉ መሰለኝ፡፡
“ይትባረክ እግዚአብሔር አምላከ እስራኤል”