ይህ መልእክት ለህልውና የሚታገለውን ፋኖና ህልውናው እንዲሰምር የሚመኘውን፣ በተለይም በተናጥል የሚብሰከሰከውን ዐማራና ምሁሩን ይመለከታል። ስለአገሩና ዐማራ ብሎ የሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል ወገኑ ከሞትና ስደት እንዲድን የሚታገለውን ፋኖ ለመርዳት በተለይም በነፃው ዓለም ያሉት ዳያስፖራዎችና የሜዲያ አርበኞችን የሚገራ መርህ ያስፈልጋል። መለኪያ በሌለበት ትክክለኛውንና በውንዥንብር ወላፈን ውስጥ የሚነጉደውን መለየት ስለማይቻል በተለይም የዋሀን ወገኖቻችንን የባህር ውስጥ ዓሣ ስለሚያደርጋቸው፤ ትግል የሚደረግለት ዐማራ ከልሂቅ እስከደቂቅ የዚህ ተውኔት ባይተዋር መሆን ስለሌበትና በአውሬ እንዳይጠመድም ጉልህና ግልጽ የሆነ መንገድ በማሳየት መርዳት ይገባል። ።
ዐማራ ደሙን አፍሶ ባቈየው አገር የዜግነት መብቱን ተነፍጎትና አጽመ እርስቱን ተነቅሎ በጅምላ እየተገደለና እየተሰደደ ይገኛል። በዐማራ ላይ የሚደረገው በደል ብዙ አሠርተ ዓመታትን ያስቈጠረ ሲሆን፣ በተለይ እልቂቱ ከ2010 ዓም ወዲህ እየተባባሰ ሄዶ ከ2013-15 የወያኔ ጦርነት በኋላ ዐማራን ያገለለ ድርድር ተደርጎ፣ ወያኔ ትጥቅ ሳትፈታ ዐማራ ትጥቁን እንዲፈታ በመወሰን የብልፅግና መንግሥት ጦር አዝምቶበታል። በአንድ በኩል በነፃነት ስም አገር ለማፍረስ እየታገሉ ያሉ ቡድኖች በመንግሥት ከለላ ዐማራን በጅምላ እየጨፈጨፉ የቀረውን ለስደት ሲዳርጉ፣ በሌላ በኩል የአገሪቱ ብሔራዊ ድንበር ተወሮ በባዕድ አገር ተይዟል። ምሁራን በየግላቸውና በተለያዩ ቡድኖች ለተለያዩ የውስጥና ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች ስለፍትሕ ድምፃቸውን ሲያሰሙ ቈይተዋል። ምሁራንና የዲያስፖራው ኅብረተሰብ በተናጥል ድምፃቸውን ቢያሰሙም የሚጠበቀው አጥጋቢ ውጤት ካለመገኘቱም በላይ ከዚህ በባሰ ሁኔታ አገራዊ ራዕዩንም ለመጉዳት ስልታዊ ሴራ እየተሠራበት ይገኛል። በውጭ ወራሪዎች ሕዝብን ከፋፍሎና አዳክሞ አገርን ለመግዛት በታለመው መሠረት እነሱ ትንንሽና አቅመደካሞች እንድሆን የፈለጉትን እኛ በስሜት እየፈጠርንላቸው ኢትዮጵያ በብሔር-ብሔረሰብ እየተከፋፈለች ለእጅ አዙር ቅኝ ገዥዎች ጣልቃገብነት እየተመቸች ትገኛለች። በሜዳ ላይ ያሉ ታጋዮች አንድነት በመዘግየቱ ሜዳ ላይ ባለው ትግል ላይም አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ የሕዝቡን ሰቆቃ እያስቀጠለ ይገኛል። ለትግሉ መስመር የዳያስፖራው ኅብረተሰብ በጎ አመለካከት ቢኖረውም አንድ ወጥ በሆነ ጠንካራ አደረጃጀት የትግሉ አጋር ለመሆን ባለመቻሉ በጎ አስተሳሰቡ እንደሚጠበቀው በተግባር ሊታይ አልቻለም። ስለሆነም የዳያስፖራው ኅብረተሰብ ቆም ብሎ በማሰብ በተናጥል ትግል የተደረውን መስዋዕትነትና በአንፃሩ ሊገኝ ይችል የነበረውን ድል በማነፃፀር ግላዊ ፍልስፍናውን ወደጎን በመተው የጋራ መፍትሔ ላይ መተባበር ይኖርበታል። ወያኔ ጸረ-ሕዝብ የሆነ ማኒፌስቶን ወደሕገመንግሥት ለማድረስ ስትችል ቅንና ፍትሐዊ ምክንያት ያለው የሕዝብ ትግል እንዴት ወደፍትሐዊ ግብ ለመድረስ አቅም እንዳነሰው ማሰብና ማመዛዘን ያስፈልጋል።
“በድሮ በሬ የሚያርስ ዘመኑን የሚዋጅ ምርት አያገኝም”
አንዱና ትልቁ ችግራችን እኔ አውቃለሁ፣ እኛ ልክ ነን፣ በሚል ሀሳብ የየግል ወይም የቡድን ፍልስፍናችንን ከማክረር በዓላማ ተመሳሳይ ሆነው የሀሳብ ልዩነት ካላቸው ወገኖች ጋር ለጋራ የአገር ጉዳይ ቅድሚያ በመስጠት፣ መልካም ቅርስን ጠብቆ ባህሉን በማዳበር የየግላችንን አመለካከት ወደማዕከል በማምጣት `ለጋራ ዓላማ በሆደሰፊነት በጋራ መርህ ለመሥራት ከልብ አለመነሳሳት ነው። ዐማራንና የክርስትና ሃይማኖትን፣ ቋንቋውንና ተያያዥ ቅርሶችን በማጥፋት ኢትዮጵያ እንድትፈራርስ የሚመኙ የሕዝቡን ባላንጣዎች የማያቋርጥ መሠሪ በመረዳት በተለይ በዳያስፖራው በኩል አንድነትን የሚጋርዱ አጥሮችን አለመስበር አንዱና ትልቅ የትግሉ እንቅፋት ነው።
ለዳያስፖራውም ሆነ በሜዳ ላይ ላለው የህልውና ታጋይ ጠቃሚ የሚሆነው አንድ ጠንካራ የጋራ መርህ /ፖሊሲ/ መኖር ነው። ገዥ መርህ ከሌለ እነእከሌ ልክ ናቸው እነእከሌ ተሳስተዋል ለማለት ምን መለከያ ወጥቷል? ገዥ ሰነድ ሁሉንም የአገር ጉዳይና ተያያዥ ነገሮችንም ጭምር በየፈርጅ በየፈርጃቸው አስቀምጦ እንደሕግ ሊታይና መመሪያ ሊሆን ይችላል። በሰነድነት የሚቀመጥ የጋራ መርህ ካለ በየጊዜው አፈንጋጭ ቡድኖች በየጎጡ እንዳይፈጠሩ ይገታቸዋል፤ ያሉትንም ያሰተባብራል። የጋራ መርህ ካለ በማናቸውም ጊዜ በውጭም ሆነ በውስጥ ያሉ ታጋዮች የሚጠቅሱትና የሚከተሉት ስለሚሆን ከመርሁ የሚያፈነግጥ ቢኖር በቀላሉ ስለሚጋለጥ መርሁን እንዲከተል የሚያስገድደው ይሆናል። የጋራ መርህ ከሌለ ታጋዩን የሚከፋፍሉ ነገሮች እንጂ የሚያስተሳስሩት ነገሮች ስለማይኖሩ፣ ለሕዝቡ ጠላቶች መግቢያ በሮችንና አዳዲስ ክፍፍሎችን በመፍጠር የሕዝቡን ሥቃይና ትግሉን ያራዝማሉ።
የጋር መርህ መፍጠር በቀጥታ ለዐማራው ብቻ ሳይሆን አሁንም ሆነ በኋላ ለዐማራው እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ አካላት ሊኖሩ ስለሚችሉ የፖሊቲካ ድርጅቶችም ተገቢውን ግንዛቤ ይዘው እንዲንቀሳቀሱ በመመሪያነት ሊያገለግል የሚችል ሰነድ ማዝጋጀት እጅግ ጠቃሚ ነው።
የኢትዮጵያዊነትና ዐማራነት ውዥንብር፤
ዐማራ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ከፍተኛ ሚናና ውለታ የሚዘነጋ እንዳልሆነ ስለሚታወቅ ያንን ለዐማራው ማስረዳት ለቀባሪው እንደማርዳት ይሆናል። ሆኖም የዐማራ ዐማራነትና ኢትዮጵያዊነት ግልጽ ሆኖ በሕጋዊ፣ በማኅበራዊ፣ በዜግነት መልክ እንዲሁም በፖሊቲካ መስክም ታይቶ ትክክለኛው ግንዛቤ ሊወሰድበትና በመርህ ደረጃ ሊቀመጥ ይገባል።
ዐማራን ከኢትዮጵያዊነት መነጠልና በብሔርተኝነት ብቻ መለየት ጥሩ ነገርም አደጋም አለበት፤ ዐማራ በዐማራነቱ ርስቱን አስከብሮ በነፃነት ለመኖር የሚያደርገው የህልውና ትግል እንዲሠምር ማኅበረሰቡን አስተባብሮ በዐማራነቱ ለኅልውናው ተደራጅቶ መታገሉ ተገቢና ጥያቄ ሊያስነሳ የሚገባው ጉዳይ አይደለም፤ በመጀሪያ ራሱን ሊያድን ያልቻለ ለማንም ሊተርፍ አይችልምና። ሆኖም በዐማራ ትግል ውስጥ ኢትዮጵያዊነቱ ተፍቆ እንዲገለል የሚደረገው አዝማሚያ በመርህ መስተካከልና ግልጽ መሆን ያለበት ጉዳይ ነው። ምክንያቱም የዐማራ ትግል ከሌሎች ማኅበረሰቦች ጋር ያለውን ግንኙነት ይፋ አለማድረግ ወደጎጥ ጉድጓድ ውስጥ እየወረወሩት በጠላትነት ለሚፈርጁት ባላንጣዎቹ ትልቅ ቀዳዳ ከመክፈቱም በላይ፤ ዐማራን ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖች ለይቶና የሌሎች ወገኖቹ ጉዳይ ከሱ ጉዳይ ጋር ግንኙነት እንደሌለው አድርጎ ማስቀመጡ የትግል አጋር የሚያሳጣው ብቻ ሳይሆን በጠላትነት ለሚፈርጁት ባላንጣዎቹ ትልቅ መረጃ ይሆናል። በሥልጣን ላይ ያለው አካል ጽንፈኛ የሚል ስም በመስጠቱ በሚፈጠር ፕሮፓጋንዳ የሚታለሉ የሉም ማለት ሞኝነት ብቻ ሳይሆን እየተደረገ ያለውን ነገር በአሸዋ ውስጥ ራሷን ቀብራ ችግርን ላለማየት እንደፈለገች ሰጎን መሆን ነው። የዐማራውን ትግል ብዙሐን ኢትዮጵያን በተስፋ የሚጠባበቁት ሲሆን ጥቂት የማይባሉት ከራሱ ከዐማራው ጭምር በተስፋቢስነት የብልጽግና ጀሌዎች ይታወቃል። ስለዚህ ይልቅስ እውነትን በሥርዓትና በሕጋዊ መንገድ መጋፈጥ ለዘላቂ መፍትሔ መሠረት ነውና።
የዐማራ ትግል እንዲሰምርም ሆነ ሰምሮ ወይም ሌሎች ሁኔታዎች ተፈጽመው ይህ ጨቋኝ መንግሥት ቢወገድ የዐማራው ትግል ውጤት ምን ሊሆን እንዲሚችል ተገቢውን ግንዛቤ በቅድሚያ ማስተዋል ይገባል። ይህ መንግሥት ቢወገድ በኢትዮጵያ ላይ ሥልጣን የሚኖረው ማን ሊሆን ነው? ሌላ ጎጠኛ የፋኖን ትግል ስላለማሰናከሉና ዐማራ የሚመኘው የአገር ጉዳይ ስኬታማ ስለመሆኑ ምን ዋስትና አለ? ዐማራ በዐማራነቱ ሲታገል ቈይቶ በሌላ በኩል ኢትዮጵያዊነቱን ወደጎን ትቶና ሌሎች ጭቁኖችን ሳያስተባብር ለብቻው ታግሎ መንግሥት ፈርሶ ሌላ መንግሥት ሲመሠረት ስለመቻል አለመቻሉና በዚህ ውስጥ ዐማራ የሚኖረው ሚና ምን እንደሚሆን በቅድሚያ በመርህ ተለይቶ መቀመጥ ይኖርበታል። ዐማራ አጽመርስቱን አስመልሶ በራሱ አገር በነጻነት መኖር ይችላል? በኢትዮጵያዊነት ራሱን ሳይገልጽና ሌሎችን በመርህም በተግባርም ሳያስተባብር ቁይቶ ያለው መንግሥት ሲወገድ ዐማራ የኢትዮጵያን መንግሥት ለመቈጣጠር የሚያስችለው ለሥልጣን የሚሄድበት መንገድ በአምባገነናዊነት ከመታየቱ ውጭ አሳማኝ አካሄድ አለወይ? ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ስለሚኖረው ግንኙነት አስፈላጊውን ዝግጅት ስላላደረገና በመርህም ደረጃ ያስቀመጠው ዓላማ ስለሌለ ተቀባይነት ይኖረዋል ብሎ መገመት አይቻልም፤ ምክንያቱም ጦርነትን ማሸነፍና ሥልጣን ይዞ አገርን በሰከነ ሁኔታ መምራት የተለያዩ ነገሮች ስለሆኑ ወደፊት ለአገር አመራር ላይ ብቁ መሆኑን በማሳየት ተአማኒነት እንዲኖረው በትግል ሜዳ ላይ ያለው ኃይል በአንድ አገራዊ ተቋም ሥር ቆሞና ለዲሲፕሊን ተገዝቶ ለጋራ ዓላማ ማሳየት ይኖርበታል። ዛሬ ዐማራ በዐማራነቱ ለህልውናው መታገሉ ከባንዶች በስተቀር በሌሎች ኢትዮጵያውያን ይታመንበታል። ሆኖም ታሪካዊ ወገናዊነቱ በሌሎች ማኅበረሰቦች ውስጥ ሥር ሰዶ እንዲቈይ ዝንታለም ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር ተሳስሮ፣ ታግሎና ደሙን አፍሶ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ነፃነት ያደረገው ውለታ ሁሉ ተፈቆ በአንፃሩ ባላንጣዎቹ የሰጡት ቅጽሎች ተጠናክረው ሌሎች ኢትዮጵያውያን ማኅበረሰእቦች ከጎኑ ተሰልፈው ለድል እንዲያበቁት ሳይሆን በባላንጣነት የሚፈርጁት እንዳይሆን ጠቃሚውን መንገድ መከተል ይገባል፤ ከድል በኋላም የጋራ አገር በመመሥረት ረገድ ሁሉም በመተማመን የሚሄዱበትን ጥርጊያ መንገድ ለማዘጋጀት ተገቢው በመርህ ደረጃ መቀመጥ ይኖርበታል።
አሁን ያለው በኦዴፓ የሚመራው የኦሮሙማ ብልጽግና መንግሥት አካሄድ ሥርዓተ አልበኝነትን ሊያስከትል ስለሚችል ሁሉን አቀፍ መንግሥት የመፍጠር ዕድሉም የባሰ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። የቀድሞ ፋኖዎች በጦር ሜዳ ተባብረው ኢጣሊያን በመውጋት እንጂ በጋራ መንግሥት ስለማቋቋም ምንም ሀሳብ ስላልነበራቸው ሊመሠረት ይችል የነበረው ዲሞክራሲ ቀርቶ ኃይለሥላሴ ከስደት ከተመለሱ በኋላ “የሞተለሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ” እንደተባለው ሁሉንም እንደጠቀለሉትና፤ ቀጥሎም በሸዋ፣ በወሎ፣ በጎጃም፣ በትግራይና በባሌ የደረሱትን ክስተቶች ማስታወስ ስህተትን ላለመደገም ይጠቅማል። የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ይታወቃል እንደሚባለው የፋኖ አገራዊ ራዕይ ግልጽና ይፋ መሆን አለበት። አንድ ድንቅ ነገር ይዤልህ እመጣለሁ ተብሎ እንደሚነገረው ትንሽ ልጅ ሕዝብን ባልታወቀ ተስፋ ደግፈኝ ማለት አይቻልም፤ ፋኖም በጭፍን ተስፋ ሳይሆን የተሸራረፈ ክልሉን አስመልሶ በአፅመ እርስቱ ላይ ህልውናውን ለማረጋገጥና በወደፊቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ሊኖረው የሚገባው ሚናም በመርህ በታወቀ ሂደት ግልጽ መሆን ይኖርበታል።
አሳሳቢው ችግርና የመፍትሔ ሀሳብ
ፍጹም የሆነ የፖሊቲካ ድርጅት መፍጠር ወይም ያሉትን ፍጹም ማድረግ የዚህ መልእክት ዓላማ አይደለም፤ ዓላማው ተደራጅቶ የሚታገለውም ሆነ ትግሉን የሚደግፈው ወገን ሁሉ የሚከተለው አንድ ገዢ መርህ እንዲኖረው ማድረግ ነው። የተከፋፈለች ቤት አትቆምም ተብሎ በመጽሐፍ ቅዱስና በተለያዩ የጥበብ ሰዎች ተግልጿል፤ ተግባራዊ ካልተደረገ ግን የጋን ውስጥ መብራት ሆኖ መቅረት ሊሆን ይችላል።
የትግራይ ነፃ አውጭ ድርጅት ገና ሲመሠረት የአቋቋመው ማኒፌስቶ መመሪያ ሆኖ የኢትዮጵያ “ሕገመንግሥት” አካል እንደሆነ ይታወቃል። ወያኔ ልታፈርስ በምትሻው አገር ሥልጣን ስትይዝ ኢትዮጵያዊነትን ይዛ ሌሎችን ቡድኖችም አጫፋሪ /መናጆ/ አድርጋ እንደነበር መገንዘብ ይገባል። መርህ ካለ ታጋዩም ደጋፊውም የሚከተለው ግልጽ መመሪያ ይሆንለታል ማለት ነው። የኢኮኖሚክስ፣ አስተዳደር፣ ፖሊቲካ፣ ሕግና ማኅበራዊ ሳይንስ…ወዘተ ሙያ ያላቸው ኢትዮጵያውያን ምሁራን ተቀናጅተው አንድ “think tank” ሆነው ሕዝባዊ ትግሉ ምን መምሰል እንዳለብት ማርክስና ሌኒን እንደጻፉት ሰነድ፣ ወይም የጋራ መመሪያ የሚሆን መርህ /ዶክትሪን/ ቢጽፉ፡ 1ኛ ብዙ ምሁራን ተውጣጥተው የሠሩት ስለሚሆን አገራዊ ጉዳዮችን በሙሉ አካቶ ከሙያ አንፃር የሚዘጋጅ ስለሚሆንና ቅቡልነት ስለሚኖረው፤ አሳታፊ በመሆኑም ስለተቀባይነቱ አከራካሪ ስለማይሆን እንኳንስ በትግል ላይ ያለው ሕዝብ ቀርቶ መንግሥትም ቢሆን በመመሪያነት የሚጠቅሰው ሊሆን ይችላል። ለዚህ ምሳሌ የሚሆነው በአሜሪካ “Financial Standards Accounting Board” የሚባል የግል ድርጅት መንግሥት የሂሣብ አሠራር ደረጃውን የሚከታተልበት ሰነድ ነው። እንዲሁም የሕግ ባለሙያዎች የሠሩት ሰነድ በመመሪያነት እየተጠቀሰ በብዙ አገሮች እንደሚያገለግልና ኮንቬንሽን እየተባሉ የሚጠቀሱ ብዙ ደንቦች ከመንግሥት ውጭ ያሉ አካላት ያወጧቸው ደንቦች ሆነው ሳለ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደመመሪያ የሚያገለግሉ መሆናቸው ይታወቃል። ስለሆነም ባለሙያዎቻችን ተገናኝተው ለትግሉ የሚበጅና ወቅቱን የሚዋጅ ተመሳሳይ የፖሊሲ ሰነድ ማውጣት ያቅታቸዋል? አያቅታቸውም እላለሁ። ጥሩ ጥሩ ጽሑፎች ወጥተው የነበሩ ቢሆንም ሰዎቹን እንጅ ስብስቦችን አያመለከቱም፤ ለምሳሌ ዶክተር ሲሳይ አሰፋ፣ ዶክተር ተስፋዬ መንግሥቱ፣ ዶክተር አክሎግ ቢራራ፣ ዶክተር አሰፋ ምህረቱ፣ ዶክተር በፈቃዱ ደግፌና ሌሎች የጻፏቸው ከብዙዎቹ ጥቂቶች ናቸው። እንደዚህ ያሉ አያሌ ምሁራን የውጭውን ዓለም ከሚጠቅሙት የተወሰነውን እንኳ በአገራችን ላይ ቢያውሉት ላለው ችግር አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚችል ይታመናል። በግል የሚደረጉ ሥነጽሑፎችና ትንታኔዎች ለብዙ አሥረተ ዓመታት እንደታየው በተለያዩ ባለሙያዎች በመቅረባቸው ግለሰቦችን ከማስደነቀ አልፎ አገራዊ ፋይዳ ሊፈጥሩ አልቻሉም። ባለሙያዎች ሞያቸውን አጠናቅረው በጋራ ስላላዳበሯቸው በአገራዊ የመመሪያ ሰነድነት አላገለገሉም። ብዙኃን በተለያዩ ሙያዎች ተጠናቅረው የሚሠሩት የጋራ ሰነድ ግን በሙያና አስተሳሰብ ዳብሮ የሚሟላ ከመሆኑም በላይ ሕዝብ የሚያምንበት ሰነድ ይሆናል።
ስለሆነም ዐማራነትና ኢትዮጵያዊነት የሚያሳስበን አገር ወዳዶችና ምሁራን በአንክሮና በቅድሚያ አስበንበት በጋራ ውይይቶች የጋራ ፖሊሲ በማውጣት በአገራችን ላይ የተንዣበበውን ችግር ለማስወገድ፣ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ባለሙያዎችን በማገናኘት በተለይ ታጋዩ ኅብረተሰብ በጋራ አመለካከት ለጋራ ዓላማ ታግሎ ህልውናውን በማስከበር ጭቈናን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አስወግዶ በዲሞክራሲያዊ ማዕቀፍ ተሳስሮ በሰላም ወደጋራ ልማት ለማተኮር የሚረዳው ገዢ መርህ / ፖሊሲ/ መቅረጽ የሚቻል ስለሆነ ይህን በመፈጸም ማንኛውም አገር ወዳድ ሁሉ እንደ ርዕሰ-ሕግ እየጠቀሰና እየተከተለ የሚመራበት ሰነድ መሥራት የአገር ወዳድ ምሁራን የታሪክ ኃላፊነት ነው። ስለሆነም ለዐማራው ሕዝብ ትግል ስኬት በዐማራውና በሌላው ኢትዮጵያዊ ውስጥ ያለውን ውዥንብር በገዥ የጋራ መርህ ለማስተካከል ሁላችንም የትግሉ ደጋፊዎች በግልና በጋራ ልናስብበትና ይህን ገዥ የጋራ መርህ ጉዳይ ወደተግባር ልንለውጠው የሚገባን ስለሆነ ቅድሚያ እንዲሰጠው ሀሳቤን አቀርባለሁ።