አንዱ ዓለም ተፈራ
ሐሙስ፣ ኅዳር ፳ ፭ ቀን ፳ ፻ ፲ ፰ ዓ. ም. (12/04/2025)
የዐማራ ህልውና ትግል እና ታጋዮቹ፤ ራሱን “የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር” ብሎ ከሚጠራው ቡድን ጋር ያላቸው ግንኙነት፤ ጊዜያዊ ወይንም የስልት ቀመር አይደለም። ራሱን “የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር” ብሎ የሚጠራው ቡድን፤ የዐማራ አንደኛና ዋና ጠላት ነው። አሁን ይሄ ጠባብ፣ ፀረ ዐማራና አገር አፍራሽ ቡድን እያካሄደ ያለው ጦርነት፤ ወልቃይትን ወደ ትግራይ ለመመለስና “ምዕራብ ትግራይ” ብሎ ለመውሰድ ነው። ራያን የራሱ አድርጎ፤ ለመሰልቀጥ ነው። በኢትዮጵያ ምድር ያስቀመጠውን፤ አገርን በዘር ከፋፋይ ሕገ−መንግሥት፣ በራሱ ቁጥጥር ሥር ዘለዓለማዊ ለማድረግ ነው። በኢትዮጵያ፤ አሁን ፋኖ እየመራው ያለው ሕዝባዊ ትግል ተሳክቶ፣ በቦታው ያስቀመጠው ከፋፋይ ሕገ−መንግሥት ተወርውሮ ተጥሎ፣ እውነተኛ አገር ማስተዳደሪያ ሕገ−መንግሥት በቦታው እንዳይተካ ነው። ተረኛ ነኝ ብሎ እንደሱው አገር እያጠፋ ያለውን አክራሪ የኦሮሞ ገዢ ቡድን፤ ለመተካት ነው። ታዲያ ይሄ ሁሉ፤ ለዐማራ ምን ያደርግለታል? ዐማራስ ይሄን እኩይ ተግባሩ እንዲሳካለት ለምን ያበረታታዋል? ኢትዮጵያን ለዚህ የዳረጋት ማን ሆነና ነው፤ አሁን ከዚህ አጥፊ ቡድን ጋር መገናኘት የታሰበው? መታወቅ ያለበት፤ የትግራይ ሕዝብና ራሱን “የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር” ብሎ የሚጠራው ቡድን የተለያዩ ናቸው።
በትክክል ስንመለከተው፤ የዐማራ ህልውና ትግል እና ታጋዩ ወገን፤ ራሱን “የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር” ብሎ ከሚጠራው ቡድን ጋር ያለው ግንኙነት ከላይ ያስቀመትኩት ነው። አጥፊውን የሚረዳ፤ ራሱን የጠላ ብቻ ነው። ተመሳሳይ የሆነ ዓላማ ያላቸውን በሚመለከት፤ “ከዝንጀሮ ቆንጆ ምን ይመራርጧል!” ነው ያሉት ዘመዶቻችን። “ግም ለግም አብሮ ያዝግም!” ነው ማለት ያለብን። አንዱን ግም ይዘን ወደሌላው ግም አንዘምትም፤ ያገማናል። በርግጥ የዐማራ ጠላቶች እርስ በእርሳቸው ቢተላለቁ፤ እስዬው! ነው። ዐማራን በሚመለከት ሁለቱም አንድ ዓይነት አቋም ነው ያላቸው፤ ትሕነግም! ኦነግም!
ትሕነግ ኢትዮጵያን ሲገዛ የነበረው፤ “የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ነኝ!” ብሎ እንጂ ኢትዮጵያዊ ሆኖ አልነበረም። በግልጥ ያንን እያወጀ፤ በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች መደኅየት ትግራይን ለማበልጠግ ነበር ሲገዛ የነበረው። ታላቋን ትግራይን ለመፍጠር ነበር። በትሕነግ ዘመን የከፍተኛ ባለሥልጣናትን ዝርዝር የተመለከትን እንደሆን፤ ከሞላ ጎደል የትግራይ ርስት ጉልት ነበር። የጦር መሪዎችን ዝርዝር ራሱ አብይ በአድባባይ ተናግሮታል። ለትምህርት ወደ ውጪ ይላኩ የነበሩትን ብንመረምር ትግሬዎች ነበሩ። በሚገርም ሁኔታ፤ በገቡ በመጀመሪያው ዓመት (፲ ፱ ፻ ፹ ፮ ዓ. ም.) አባቴ ለሕክምና ውጪ መጥቶ አረፈ። ቀብሩ አገሩ እንዲሆን ይፈልግ ስለነበር፤ አዘዞ፣ ጎንደር ለቀብር አስከሬኑን ይዤ ሄድኩ። ከቀብሩ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ፣ ጎንደር አየር ማረፊያ ስደርስ፤ ዘበኛው በትግርኛ ያዘኝ ጀመር። እኔም መልስ መሥጠት ስላልፈለግሁ ዝም አልኩ። “ትግርኛ አትሰማም?” ትዕዛዝ አይሉት ጥያቄ ወረወረብኝ። “እየተናገርክ ነበር እንዴ!” ብዬ መለስኩለት። የዐማራ ክልል በተባለው እንኳ! ገና የገቡበትን ልብስ ሳይቀይሩ፤ እኔን በገዛ መንደሬ በትግርኛ እንድናገር ፈለገ። ዘበኛውም ሆዱ ተነፋ! ያ ነው የትግራይ መንግሥት ማለት።
ኦነግም ራሱን “የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር” ነኝ ብሎ በትግሬዎች ስም አገር ሲገዛ የነበረው ቡድን ሲጫወትበት፤ ኦሮሞ ነኝ ብሎ፣ በኋላም እኛ ተረኞች ነን! ምናለ እኛ ብንገዛ! ብሎ አዎጆ! በኦሮሞነት ነው እየገዛ ያለው። ትሕነግ ያደረገውን በሙሉ፤ ትግሬ የሚለውን ኦሮሞ በሚለው ለውጦ ቀጠለ። የጦር መኮንኖችን ብንቆጥር፣ የዲፕሎማሲ ግለሰቦችን ብንመለከት፤ በትግሬዎች እግር የተተኩ ኦሮሞዎችን ነው የምናገኘው። ኦሮሚያን ለመፍጠር እንጂ፤ ኢትዮጵያ እንድትቀጥል አይደለም ሌት ተቀን የሚሠራው። ዐማራ ከነኚህ መምረጥ የለበትም! ሁሉም አገር አጥፊዎች ናቸውና!
ራሱን “የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር” ብሎ የሚጠራው ቡድን፤ ታሪኩ ሌላ፤ እሱ ስለራሱ የሚናገረው ሌላ ነው። እኔ ሲመሠረት ጀምሮ በትክክል አውቀዋለሁ። ይህ ቡድን፤ የሚጨበጥና ቋሚ የሆነ የፖለቲካ ግባና ዓላማ የለውም። በውስጡ ያሉ መሪዎች፤ ለአሁን ይጠቅመናል ያሉትን የሚያራምዱበት መሳሪያ ነው። ስሙን ስንት ጊዜ እንደቀየሩት መቁጠር አቁሜያለሁ። ዛሬ የሚለውን ነገ አይደግመውም። ዛሬ ተስማምቶ ነገ አላየሁም! አላውቅም! ይላል። መዋሸትና ማምታታት፤ የሥራ መመሪያዎቹ ናቸው። ከማን ጋር ተወዳጅተው ማንን እንደወጉ ጠንቅቄ አውቃለሁ። ከኤርትራ ሕዝባዊ ግንባር (ሸዓቢያ) ጋር ሆነው የኤርትራ ነፃነት ግንባርን (ጀብኀ) ሲወጉና ወደ ሱዳን ሲያባርሯቸው ከሰላ ነበርኩ። በውስጣቸው እንኳ፤ መሪ ለመሆን እርስ በርሳቸው ሲበላሉ አውቃለሁ።
በርግጥ! ቋሚ የሆነ ነገር ቢኖራቸው፤ የዐማራ ጥላቻቸው ነው። ገና ሲነሱ፤ “በዐማራ መቃብር ላይ የትግራይን ሩፑብሊክ እንመሠርታለን!” ብለው ነው። “የትግራይ ተራሮች የዐማራ መቀበሪያ ናቸው!” ብለው ሲዘፍኑ በቦታው ተገኝቼ ሰምቻቸዋለሁ። ተከዜን ተሻግረው ወልቃይት ሲገቡ፤ በቦታው ነበርኩ። ያን ጊዜ፤ “ከዛሬ ጀምሮ እናንተ ትግሬዎች ናችሁ! ዐማራ መጥቶ ነው ማንነታችሁን የነጠቃችሁ! ካሁን በኋላ አቤቱታችሁን በትግርኛ ጽፋችሁ ለኛ ታቀርባላችሁ! በትግርኛ ብቻ ነው የምታለቅሱትና የምትፅፉት!” የሚል አዋጅ አዲ ረመጥ ገበያው ላይ ሲያውጁ፤ በቅርብ ርቀት ላይ ነበርኩ። ከገበያው የተመለሱት ይሄን ነግረውኛል። ይህ ቡድን፤ ኢትዮጵያን ለማጥፋት የተተከለ መርዝ ነው። የነካውን ሁሉ ይበክላል። ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊይንን ለዚህ ያበቃው ይሄ ቡድን ነው። እርስ በርሱ የሚባላ፤ ለሌላ ይተርፋል ብሎ ማመን፤ የየዋኅነት ጥጉ ነው።
የዐማራ ህልውና ትግል፤ የተወሳሰቡና የተቆላለፉ ጉዳዮች አሉት። ባጠቃላይ ሕዝባዊ ትግል፤ ውጣ ውረዶቹ ብዙ ናቸው። ሆኖም ግን፤ መሠረታዊ የተባሉ እውነታዎች፤ ምን ጊዜም ገዢ ናቸው። በትክክል፤ የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ከኮሚንታንግ ጋር ጊዜያዊ ትብብር አድርጓል። ያንን ያደረገው፤ በመካከላቸው ያለው ልዩነት ተቀርፎ ሳይሆን፤ አገር አጥፊና ሁለቱንም አደጋ ላይ የሚጥል ጠላት፤ የጃፓን ወራሪ ኃይል በሁለቱም ላይ ስለመጣባቸው ነበር። ምዕራባዊያን መሪዎች፤ ለኛም ባተረፉልን የነሱ “ሁለተኛው የዓለም ጦርነት”፤ ከስታሊን ጋር ሽርክና ፈጥረው ነበር። ያም የሆነው፤ ሂትለር ሁለቱንም አጥፊ ኃይል ስለሆነባቸው ነበር። እኛ አሁን፤ አብይ ደብረጽዮንን ቢያጠፋ ወይንም ደብረጽዮን አብይን ቢያጠፋ፤ ምንም የምናዝንበት ነገር የለም። በርግጥ ሁለቱም ቢጠፉ እንወዳለን። ያም ካልሆነ አንዱ አንዱን ቢያጠፋ ለኛ ልዩነት የለውም። እናም ከማናቸውም ዝምድና ማድረግ፤ የነገ መታረጃችንን መሳል ይሆናል።
እኒህ ሁለቱ፤ ከኛ አንጻር ሲታዩ፤ በመካከላቸው ያለው አንድነት፤ በመካከላቸው ካላቸው ልዩነት በጣም ያነሰ ነው። የሥልጣን ጉዳይ እንጂ፤ የአገር አገዛዝ፣ የሕገ መንግሥት፣ የክልል አወቃቀር፣ የሙስና፣ የአድልዖ፣ የፀረ ዐማራና ፀረ ኢትዮጵያዊነት፤ ልዩነት የላቸውም። እኔ ኮርቻው ላይ ልቀመጥ! የለም እኔ ልቀመጥ! ብቻ ነው ልዩነታቸው። “ይሄ ትኋን ይብላህ! ወይንስ ያኛው!” ብሎ ለሚጠይቀኝ፤ “ሁሉም ይቅሩብኝ!” ነው መልሴ። ዐማራ የትምህርት ዕድል እንዳያገኝ፤ በሁለቱም ጊዜ ወደ ውጪ ለትምህርት የመላክ ዕድሉ ጠባብ ነው። ተሹሞ ወደ ውጪ አገር የመላክ ዕድሉ ወለል ላይ ተነጥፏል። የትግራይ መንግሥት ነበር። ቀጥሎ የኦሮሞ መንግሥት ተተክቷል። ይሄንን ሀቅ የማያይ ኢትዮጵያዊ፤ ኢትዮጵያዊነቱን እጠራጠራለሁ።
አሁን አብይ፤ ራሱን “የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር” ብሎ የሚጠራውን ቡድን፤ እየከፋፈለ እርስ በእርሳቸው እያፋጃቸው ነው። በራሱ ለአብይም፤ በኦሮሞ ብልፅግና በኩል፣ ከፍርሃትና ፋኖን ከመስጋት የመነጨ፤ መከፋፈል ገብቶበታል። ፋኖ የነዚህ አገር አጥፊዎች ትብብት ሳይሆን፤ “መቼ ይሆን ፋኖ የሚደርስልን!” እያለ የሚጠብቀውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ትብብር ነው የሚፈልገው። እኒህ ደግሞ፤ ፋኖ ራሱን ሠውቶ እንዲመጣላቸው ከመጠበቅ ይልቅ፤ በያሉበት ቦታ ፋኖ ሆነው፤ የፋኖን ሥራ መሥራት ነው ያለባቸው። ትግሉ እንዲሳካና የፈለጉት እንዲመጣ፤ ራሳቸው የትግሉ አካል በመሆን፤ በያሉበት ይሄን አገር አፍራሽ ሊወጉት ይገባል። መሳሪያ ያለው በመሳሪያው፣ የሌለው ደግሞ በሚውልበት ቦታና በሙያው፣ በመንደሩና ባለው የኅብረተሰብ መስመር ፋኖን ይተባበር። አገራችን የሁላችን ናት። አገርን ማቆየትና ባለቤት መሆን የሁላችን ኃላፊነት ነው። ከዚህ አገር አፍራሽ የምንድነው አብረን ስንታገለው ነው።
በመጨረሻ፤ በተደጋጋሚ የሚነገረውን እውነታ ላንሳ። ሕዝብ ያቸንፋል። ፋኖ የሕዝብ አካል ነው። ፋኖ የሕዝባዊ ትግሉ መሪ ነው። ፋኖ የሕዝብ ጠባቂ ነው። ፋኖ ያቸንፋል። አሁን በአገራችን ባለው ሀቅ፤ የአብይ አክራሪ ኦሮሞ ገዢ ቡድን ወደ መቃብሩ፣ ፋኖ ደግሞ ወደ ድል እየሄደ መሆኑ የታወቀ ነው። ለያንዳንዳችን ጥያቄው፤ ከፋኖ ጋር ነን? ወይንስ ከሟቹ አብይ? ነው።