በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከኢሕአፓ የተሰጠ መግለጫ
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 መሰረት የፖለቲካ ፓርቲዎችን ማስተዳደር፣ በአመራሩና በአባላቱ ላይ የሚደርስ ማናቸውም ጉዳይ መከታተልና መፍትሄ መስጠት ቦርዱ ከተጣለበት ሀላፊነቶች መካከል አንዱና ዋነኛው መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ብሄራዊ ምርጫን በተመለከተ
በኢፌድሪ ህዝብና ቤት ቆጠራ ኤጀንሲ እንደሚታወቀው የድሬዳዋ ከተማ ህዝብ ከምርጫ 2013 ዓ.ም በፊት የ9 ቀበሌ ህዝብ ሲቆጠር ከገጠሩ 38 ቀበሌ ጋር ሲነፃፀር 82 በመቶ ሲሆን የገጠሩ ህዝብ ብዛት 18 በመቶ ነው፡፡
የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር መተዳደሪያ ቻርተር የሚያውቀው የድሬዳዋን ከተማ 9 ቀበሌ ብቻ ሲሆን የገጠሩን 38 ቀበሌ ግን ቻርተሩ አያውቃቸውም፡፡ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ጠቅላላ ወንበር ብዛት 192 መቀመጫ ሲሆን የድሬዳዋ ምርጫ ቦርድ በባለፈው ምርጫ 2013 ዓ/ም ለድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ም/ቤት ከተወዳደሩ ፓለቲካ ፓርቲዎች የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር መተዳደሪያ ቻርተር ለሚያውቃቸው 9 የከተማ ቀበሌዎች በ26 ምርጫ ጣቢያ የሰጠው 78 መቀመጫ ነው፡፡ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በመተዳዳሪያ ቻርተር ለማያውቃቸው 38 የገጠር ቀበሌዎች በ38 ምርጫ ጣቢያ የሰጠው መቀመጫ ደግሞ በተቃራኒው 114 ነው፡፡
በወቅቱም እነዚህ የምርጫ ስህተቶች አንዲታረሙ ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት አሳውቀን ተገቢ ምላሽ የተሰጠን ባይሆንም በእኛ በኩል በወቅቱ የዲሞክራሲ መድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታ እንዲዳብር፣ ህዝባችን በመረጠው ፓርቲ መተዳደር እንዳለበት ትምህርት መውሰድ እንዲችልና በሌሎችም በርካታ ምክንያቶች መንግስትን ከሚወክለው ፓርቲ በስተቀር ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ለመግባት ወንበር እንደማናገኝ እያወቅን ለሀገራችን ሰላም ስንል ምርጫው ሰላማዊና ፍትሀዊ ሳይሆን ከነ ክፍተቱ ወደ ምርጫ ገብተናል፡፡
ይሁን እንጂ በመጪው ምርጫ ይህ ስሁት አካሄድ በፍጹም መቀጠል የሌለበት በመሆኑ፡
ከዚህ በፊት በነበረው የህዝብና ቤት ቆጠራ መሰረት ለከተማው ህዝብ የተነፈገውን የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ም/ቤት የውክልና ወንበር ቁጥር እንደ ህዝብ ብዛቱ አብላጫውን ወንበር ለከተማው ህዝብ እንዲሰጥ እንዲደረግ እናሳስባለን፡፡ ምክንያቱም ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች በድሬዳዋ ውስጥ የምንወዳደረው በአብዛኛው ከተማ ውስጥ ስለሆነና ደጋፊዎቻችንም ያሉት በከተማ ስለሆነ፤ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያለውም ከገጠረ ይልቅ በድሬደዋ ከተማ ውስጥ ስለሆነ ተወዳድረን ም/ቤት የመግባት ዕድል ስለሚፈጥርልን እንዲሁም በጋራ የአገራችን ጉዳይ እኩል የመምከር መብት ያለን መሆኑ ሊረጋገጥ ይገባል፡፡
የድሬዳዋ የገጠር ቀበሌዎች የተሰጣቸው የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት የውክልና ወንበር ተገቢ ስላልሆነ የድሬዳዋ መስተዳደር መተዳደሪያ ቻርተር ባያውቃቸውም እንደ ህዝብ ብዛታቸው ታይቶ የምክር ቤት ውክልና ወንበር በተገቢው ሁኔታ እንዲሰጣቸው በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በኩል ለሚመለከታቸው አቅጣጫ እንዲሰጥልን እየጠየቅን ያቀረብነው ቅሬታ በአግባቡ ታይቶ የማይፈታ ከሆነ ግን በቀጣይ ምርጫ ለመሳተፍ የምንቸገር መሆኑን ከወዲሁ እንገልፃለን፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ከህግ አግባብ ውጪ ምርጫ ማድረግን በተመለከተ
መጋቢት 2013 ዓ/ም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳር በሚንቀሳቀሱ 9 የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተፈረመው የቃል ኪዳን ሰነድ ክፍል 2 ንዑስ ቁጥር 2.3.1 እና 2.3.2 ስር የምክር ቤቱ ሰብሳቢ በምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባኤ ይመርጣል፡፡ የስራ ዘመኑም አንድ አመት ይሆናል ይላል፡፡
ይሁን እና አንዴ በድጋሚ ሊመረጥ ይችላል፡፡ ለምክር ቤቱ የሚቀርቡ አጀንዳዎችን ከምክትል ሰብሳቢውና ከጸሓፊው ጋር በመሆን ያዘጋጃል፡፡ ለአባላቱም ከስብሰባ በፊት እንዲደርስ ያደርጋል የሚለውን በመተላለፍ፡ ምክትል ሰብሳቢውንና ጸሓፊውን ሳያማክር ብቻውን በደብዳቤ ቁጥር ድ/ዳ/ፖ/ፓ/የጋ/ም/ቤት/102/17 በቀን ህዳር 6/2017 ዓ/ም የጠቅላላ ጉባኤ ምርጫ ከመጠራቱ በፊት ቅድመ ምርጫ መስፈርት
ሀ. የየፓርቲዎቹን የስራ አስፈፃሚ ዝርዝር
ለ. የየፓርቲዎቹን የጋራ ም/ቤት ተወካይ
ሐ.የየፓርቲዎቹን ወቅታዊ የምርጫ ቦርድ ህጋዊ የምዝገባ ሰርተፊኬት የሚያረጋግጥ ማስረጃ እስከ ህዳር 20/2017 ዓ/ም ለጋራ ምክር ቤቱ አስቀድማችሁ እንድታቀርቡ ብሎ ራሱ የሰጠውን የጊዜ ገደብ እንኳን ሳይጠብቅ 3 ቀን ቀደም ብሎ ህዳር 17/2017 ዓ/ም የድሬዳዋን ምርጫ ቦርድ ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊና ተወካይ በደብዳቤ ጉባኤ ልናደርግና ምርጫም ልናካሂድ ነው በታዛቢነት ተገኙልን በማለት በደብዳቤ ጠርቷቸው ለአባል ፓርቲዎች ግን በፀሀፊዋ አማካኝነት በዕለቱ ጠዋት አስቸኳይ ስብሰባ አለ ከሰዓት 10 ሰዓት እንድትገኙ የሚል የስልክ ጥሪ ብቻ በማድረግ ጉባኤም ምርጫም እንደሚደረግ ሳይናገር፣ የፓርቲ ስራ አስፈፃሚዎች እና እሱ ከምርጫ በፊት እንዲቀርብ የጠየቀውን ያሟላው የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ ኢሕአፓ ባልተገኘበት የፓርቲ ውክልና የሌላቸውን ግለሰቦች ጭምር በህገ ወጥ መንገድ እንዲሳተፉ በማድረግ እራሱ አስመራጭ እራሱ ተመራጭ አድርጎ ያካሄደው ምርጫ ህገ-ወጥ ከመሆኑም በላይ ዓመታዊ የስራ አፈፃፀም ሪፖርትና የሁሉም ፓርቲዎች ከ3 በላይ የስራ አስፈፃሚዎች ባልተገኙበት የቃል ኪዳን ሰነዱን በመጣስና ወደጎን በመተው የኢዜማ አባል የሆኑት ሰብሳቢው አቶ ዮናስ በትሩ አራት አመት ጨርሰው አምስተኛ አመት ለመጨመር ሲል ያደረጉት አሻጥር ያለበት ህገ-ወጥ የዕርስ በዕርስ ምርጫ ስለሆነ እንዲሰረዝ እንዲደረግና በገለልተኛ አካል ትክክለኛ ጉባኤ በአግባቡ ተጠርቶ የኦዲት ሪፖርት፣ የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦና አስመራጭ ኮሚቴም ተመርጦ በህግ አግባብ መሰረት ትክክለኛ ምርጫ ማድረግ እንድንችል የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ቅድመ ሁኔታዎችን እንዲያመቻችልን ጠይቀን በመጠባበቅ ላይ እያለን በድጋሚ ከህግ አግባብ ውጪ ምርጫ አድርጓል፡፡
በመሆኑም፡
1. ከዚህ በፊት በነበረው የህዝብና ቤት ቆጠራ መሰረት ለከተማው ህዝብ የተነፈገውን የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ም/ቤት የውክልና ወንበር ቁጥር እንደ ህዝብ ብዛቱ አብላጫውን ወንበር ለከተማው ህዝብ እንዲሰጥ ያሳስባል፡፡
2. የድሬዳዋ አስተዳደር የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ህጋዊ ምርጫ እንዲያካሂድ ይጠይቃል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ – ኢሕአፓ
ሕዳር 12 ቀን 2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ