ማለዳ ነው፤ ዕለቱ ቅዳሜ።
እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት ከሚገኘው ማሪዮት ሆቴል ጎን ሚኒባሶች ተደርድረዋል። መኪኖቹ ጋዜጠኞችን ሸክፈው ወደ ዓለምገና ለመክነፍ ቋምጠዋል። በሱፐር ደብል ቲ ጄኔራል ትሬዲንግ ስምሪት የተሰጣቸው አስተባባሪዎች ወደ ሚኒባሶች የሚገቡ ጋዜጠኞችን ይቆጣጠራሉ።

“አስተባባሪ” ተብለው ከተመደቡ ሰዎች ውስጥ ዋልተንጉሥ አብነህ አንደኛው ነው። በማሕበራዊ ሚዲያ ላይ ጋዜጠኛ ሆኖ እየሰራ በመገኘቱ እና ለአቶ ጸጋዬ ደበበ የተወሰነ ቅርበት ስላለው የማስተባበር ሃላፊነቱ ተበርክቶለታል። ሌሎችም የድርጅቱ ሰራተኞች በዚሁ የማስተባበል ዘመቻ ውስጥ ሁነኛ ተሳታፊ ናቸው።
እኔ ከተመደብኩበት ሚዲያ ለዚህ ስራ እንድንቀሳቀስ መመሪያ ሲሰጠኝ፣ ሁለት ልብ ሆኜ ነበር። አንዱ ይህ ተቋም በሰራተኞቹ ላይ የሚፈጽመው ዕመቃ እና በደል አገር ያወቀው ጸሐይ የሞቀው ጉዳይ መሆኑን ግምት ውስጥ አስገብቼ ከዚሁ ጉዞ ለመቅረት ግማሽ ልቤ ወስኖ ነበር። ሆኖም በዚሁ ጉዞ ሳቢያ የሚኖረው የውሎ አበል ሁኔታ ቀልቤን ስለሳበው ለመጓዝ ልቤ ተነሳሳ።
ከዚያም ከምኖርበት ሰፈር ወደ ማሪዮት ሆቴል አካባቢ ሄድኩ። ከዋልተንጉሥ ጋር ሰላምታ ተለዋውጬ ወደ ተመደበልን አንደኛው ሚኒባስ አመራሁ።
ሚኒባሱ በጋዜጠኞች ተጠቅጥቋል። ካሜራ የታጠቁ የአሻም እና አርትስ ቲቪ ሰራተኞች ከእነጋዜጠኞቻቸው ይታያሉ። የራዲዮ ጣቢያዎች ሪፖርተሮችም አሉ። በማሕበራዊ ሚዲያ ላይ የሚጽፉ ግለሰቦችም አልጠፉም። ይህ ሁሉ የሚዲያ ሰራዊት ነው እሳት ማጥፋት ስራ ላይ የተሰማራው።
ጉዞ ተጀመረ፤ ጉዞ ወደ ዓለምገና።
ዓለምገና ስንደርስ፣ ዓለም ሆቴል ጋ ሚኒባሱ ቆመ። እኛ ብቻ ሳንሆን ሁለቱ ሚኒባሶችም ቦታቸውን ያዙ። ከሚኒባሱ ወርደን ወደ ሆቴሉ የውስጥ ምግብ ቤት ዘለቅን። አረፍ ከማለታችን ጾመኛ መሆን አለመሆናችን ተጠየቅን። እንደማንጾም ስንነግራቸው፣ በደቂቃ ልዩነት ዱለት እና ዕንቁላል ፍርፍር መጣልን። ለስላሳ ተሰጠን።
ምግቡን እያጣጣምን፣ ለስላሳውን እየጠጣን ሳለ፣ ከፊት ለፊታችን ታዋቂ ቲክቶከሮችን አየን። አንደኛው ቲክቶከር “ያያ ዘልደታ” በመባል የሚታወቀው በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጉዳይ ላይ ግንባር ቀደም ተሰላፊ የሆነው ግለሰብ ነው። “አሃ፣ ያያ ዘልደታ አለ። ጥሩ አበል አለ ማለት ነው” አልን።
ከቁርስ በኋላ፣ ከሆቴሉ በስተጀርባ በብዙ ሜትሮች ርቀት ላይ ወደሚገኘው የሱፐር ደብል ቲ ፋብሪካ ቅጥር ግቢ አመራን። የፋብሪካው ግቢ በር ወለል ብሎ ሲከፈት፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ በየአቅጣጫው ተሰቅሎ ጠበቀን። ከሚኒባሱ ወርደን በአስተባባሪዎቹ መሪነት ወደተዘጋጀው መድረክ አቅራቢያ ወሰዱን። መስታወት በመስታወት የሆነች ጠባብ ክፍል ውስጥ አስገብተውን ተቀምጠን ለትንሽ ደቂቃ እንድንጠባበቅ ተነገረን። በመጨረሻም የኩባንያው ባለቤት አቶ ጸጋዬ ደበበ በበርካታ ሰዎች ታጅበው መጡ። ንግግራቸውን ጀመሩ፣
“ይህ ክፍል የኔ ቢሮ ነው። ማንም ይሁን ማን ከፍ ዝቅ አይልም። እዚህ ነው ስራዬን የምሰራው”
በአንድ ጥግ የተቀመጡ ዋንጫዎች እና ሰርተፊኬቶችን ገርመም አደረጉና፣
“ከጋዜጣዊ መግለጫው በፊት ፋብሪካውን መጎብኘት አለባችሁ። ጊዜ ሳንፈጅ ወደ ጉብኝቱ እንሂድ” አሉና ፊት ፊት እየመሩን ማስጎብኘት ጀመሩ።
በየክፍሉ፣ በየማምረቻ ስፍራው ተመርጠው የተቀመጡ ሰራተኞች ነበሩ፤ “ንግግር ይችላሉ” የተባሉ። እነርሱ የተወሰነ ነገር ሲናገሩ፣ አቶ ጸጋዬ ጣልቃ ይገቡና ነገሩን ያሰፉታል። እንዲህ እያልን የተወሰነውን የፋብሪካው ክፍል ጎበኘን።
በዚህ ጉብኝታችን ላይ ሁለት ነገሮችን ታዘብኩ። አንደኛው አቶ ጸጋዬ በየንግግሮቻቸው ጣልቃ የሚያስገቡት “የእግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን” የሚለው ቃል ነው። “እንደዛሬው ቀን የእግዚአብሔር ስም በባለሃብት ዘንድ አልተመሰገነም” አልኩ፣ በልቤ።
በተቋማቸው ውስጥ “ብልሹ አሰራር ወይም የስነ ምግባር ጥሰት” የፈጸሙ ሰራተኞችን ተቀጣሪዎቻቸው እንዲጠቁሙ እና እንደየጥፋቱ ደረጃ ታይቶ ለጠቋሚዎች ከ1 ሺሕ እስከ 6 ሺሕ ብር እንዲሸለሙ የሚያነሳሳ ጽሑፍ የለጠፉ ሰው፣ በዕውኑ የእግዚአብሔርን ቃል ተረድተውታልን? አይመስለኝም!
ሲቀጥልም፣ ማስቲካ ላላመጠ፤ ስልክ ላወራ እና ሌሎች “ስሕተቶችን” ለፈጸመ ሰው በሺሕ ብሮች የሚገመት ቅጣት ከደመወዙ ላይ በመቁረጥ መፈጸምም አግባብነቱ ምን ያህል አዋጪ እንደሆነ መረዳት አያዳግትም፤ የሕግ ባለሞያዎችም በጉዳዩ ላይ አስተያየት ቢሰጡበት መልካም ነው። እንደእኔ አመለካከት ግን፣ አክሳሪ አሰራር ነው፤ ሰራተኞች በትጋት እንዳይሰሩ የሚያደርግ!
የደህንነት ካሜራዎችን የሚቆጣጠረው ክፍል ጋ ደረስን። አንዲት ሰራተኛ እንድትናገር አቶ ጸጋዬ ዕድል ሰጧት። በሃይል ትናገር ጀመር።
“ከ400 በላይ የደህንነት ካሜራዎች በግቢው ውስጥ ይገኛሉ። የትኛውንም ዕንቅስቃሴ በካሜራዎቹ እንቆጣጠራለን” እያለች ቀጠለችና፣
“መሰረት ሚዲያ ለምን የድርጅታችንን ስም እንዳጠፋ አውቃለሁ። የፕሮሞሽን ጥያቄ አቅርቦ ተቀባይነት ስላላገኘ ነው። በንዴት የውሸት ዜና ሰራ” አለች።
አቶ ጸጋዬ ከእርሷ ተቀብለው የራሳቸውን ሃሳብ ከጨመሩ በኋላ፣ ወደ ሌሎች የስራ ክፍሎች ለጉብኝት ተጓዝን። ለሰዓታት ከአቶ ጸጋዬ ጋር ስንኳትን ቆየን። በመጨረሻ መባዘኑ አበቃና ወደ ጋዜጣዊ መግለጫው አመራን።
ስለጋዜጣዊ መግለጫው ይዘት የምናገረው ተጨማሪ ዕሴት ያለው መረጃ የለም። ነገር ግን የመድረክ አስተዋዋቂው ለሁለት ጋዜጠኞች ብቻ የጥያቄ ዕድል እንደሚሰጥ ቢናገርም፣ የትኛውም ጋዜጠኛ ለጥያቄ እጁን አላነሳም።
በጥቅሉ፣ የነበረው ጉብኝትም ሆነ የአቶ ጸጋዬ ገለጻ የሚያሳብቀው ነገር ቢኖር፣ በመሰረት ሚዲያ በኩል የተሰራጨው መረጃ ትክክለኛ መሆኑን ነው። ከንግግራቸው እና ከእጅ አወናጫጨፋቸው አንጻር፣ አቶ ጸጋዬ ስሜታዊነት ይንጸባረቅባቸው ስለነበር፣ ምናልባት “ለምን ተጋለጥኩ?” የሚል ቁጣ በውስጣቸው ይንተከተክ እንደነበር ገምቼአለሁ። በሌላ በኩል፣ “ምስክርነት” የሰጡት ሰራተኞች ገጽታ ላይ የሚስተዋለው የመገደድ እና የፍርሃት ስሜት ጥርጣሬያችንን የጨመረ እንጂ የቀነሰ አይደለም። ዥጉርጉር የወታደር መለዮ የለበሱ የፋብሪካው ዋርድያዎች እኛን እየተከተሉ እግር በእግር የምናወራውን ነገር ሁሉ ለማዳመጥ የነበራቸው ጉጉት በጣም አሰቃቂ ነበር።
ሁሉም ነገር ተጠናቅቆ ዓለም ሆቴል ገብተን ምሳችንን እየበላን ሳለ፣ አስተባባሪው ዋልተንጉሥ አብነህ መጣና ወደ አንድ መነጽር ያደረገ፤ ጸጉሩን እንደአቤሴሎም የሚያዘናፍል ባለሃብት ሰው ጣቱን ቀስሮ፣
“ክፍያውን እርሱ ይጨርሳል። እናንተ አታስቡ፤ ሰኞ ይከፈላችኋል” አለን።
ውስጣችን በተስፋ እና ስጋት ተሞላ። ተስፋው ሰኞ ብሩን ወደ አካውንታችን ለማስገባት ሰዎቹ ይተጉ “ይሆናል” የሚል ሲሆን፣ ስጋቱ “አጠቃላይ ለክፍያ የተመደበው ብር ዋልተንጉስ አፍኖ ይዞ በኋላ ላይ ለጓደኞቹ ብቻ ከፍሎ፤ እኛን ቢተወንስ?” የሚል ነበር። ለቲክቶከሮቹ ያያ ዘልደታ እና ለጓደኛው በነፍስ ወከፍ 100 ሺሕ ብር እንደተከፈላቸው ስለሰማን፣ ተስፋችንን ሙሉ በሙሉ አልቆረጥንም፤ “ለእኛም ይዘንማል” በሚለው ፈሊጥ!
በዚህ የስሜት ሁኔታ ውስጥ ነበር ወደ አዲስ አበባ የተመለስነው። የሆነው ሆኖ የአንድ ቀን ልፋታችን እንዳልሰመረ እንኳን እኛ፤ እናንተ አንባቢዎቻችን ጭምር የታዘባችሁት ነው። ዕውነት ጉልበቷ የማይበገር፤ ጥልቀቷ የማይመተር መሆኗን ያሳየ ክስተት ነው። በርግጥም፣ “ማስተባበያው ማስተባበል አልቻለም”!