ከአዳዲስ ነገሮች ጋር የመላመድ፣ ልዩነቶችን የማስተናገድ፣ እና የጋራ መግባባትን የመፍጠር ልምዶችን ማዳበር፡ ኢትዮጵያ ከኢኳዶር፣ ከጋላፓጎስ፣ እና ከአሜሪካ የምትቀስማቸው ልምዶች (ክፍል አንድ)
የሰው ዘር መገኛ ተደርጋ የምትታመነው ኢትዮጵያ፣ አሁን ባለንበት ዘመን እጅግ አሳሳቢ ትግል ውስጥ ትገኛለች። የሰው ልጅ አመጣጥን ከሚጠቁመው ጥልቅ ታሪኳ እና በጥንታዊ ልማዶች ከተሞላው ሕያው ቅርሷ ዛሬም ድረስ የሚታይ ቢሆንም፣ ሀገሪቱ በተደጋጋሚ ግጭቶችና መከፋፈሎች ውስጥ ተዘፍቃ ትገኛለች። እነዚህ ግጭቶች እንዲሁ በአጋጣሚ የተከሰቱ አይደሉም። ከብሔር-ተኮር ፌዴራሊዝም ሥርዓት ጋር የተያያዙ ቅጦችን ይከተላሉ። ይህ የፖለቲካ አደረጃጀት ያለፉ ስህተቶችን ለመፍታት ታስቦ የተቋቋመ ቢሆንም፣ አሁን ግን ለማጠናከር ዓላማ ያደረገችውን አገር ራሷን የመበታተን አደጋ ላይ ጥሏል።
ይህ ጽሑፍ ከዚህ በፊት ያልተለመዱ ምንጮችን እንደማነፃፀሪያ ወስዶ የሚቀርብ ይሆናል። ፅሁፉ በኢኳዶር ውስጥ በአስደናቂው የተፈጥሮ ብዝሃ ሕይወት ውስጥ አንድነትን ለማጠናከር የተደረገውን ጥረት፣ የዳርዊንን ዝርያዎች በጋላፓጎስ እንዴት እንደሚላመዱ የገለጸበትን አመለካከት፣ ከምድር ወገብ ጋር የተያያዘውን ጉልህ ተምሳሌት፣ የሰው ልጅ ከአፍሪካ ቀድሞ እንዴት ሊሰደድ እንደቻለ የሚታትን ታሪክ፣ እንዲሁም በአሜሪካ አህጉር ያሉትን የተለያዩ የቅኝ ግዛት ታሪኮችን ይመረምራል።
እነዚህን የተለያዩ የአስተሳሰብ መስመሮች በአንድ ላይ ስናሰባስብ፣ የኢትዮጵያ እንደ ሀገር መረጋጋት ትልቅ ለውጥ እንደሚያስፈልገው በግልፅ ያስረዳናል። አሁን ያለው ከፋፋይ የብሔር-ተኮር ፌዴራሊዝም ሞዴል፣ በጋራ ዜግነት ላይ በተመሠረተ ሁሉን አቀፍ ሥርዓት መተካት አለበት። ዳር ላይ ለምትገኝ አገር፣ አንድነት የፖለቲካ ምርጫ ብቻ ሳይሆን፣ ለመኖር የሚያስፈልጋት ዋነኛ ፍላጎቷ ነው።

- መግቢያ፡ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ለማቆየት የሚደረገው ትግል
ኢኳዶርን እና የጋላፓጎስ ደሴቶችን ከጎበኘሁ በኋላ፣ የተፈጥሮ ገጽታው ትኩረቴን የሳበው ወዲያውኑ ነበር። ወደ ሰማይ የተሰነጠቁ የሚመስሉት ረዣዥም የአንዲስ ተራሮች፣ በደመና በተሸፈኑ ጥቅጥቅ ደኖችን የሚያቆራርጡ ወንዞችን፣ እንዲሁም ደማቅ የሆነው የፓሲፊክ ባህር ዳርቻ የማይረሳ ስሜት ፈጥረውብኛል። ሆኖም ግን በእነዚህ ቦታዎች ከነበረኝ ቆይታየ በኋላ በውስጤ የቀረው የተፈጥሮ ውበታቸው ብቻ አልነበረም። ከምንም በላይ ጎልቶ የታየኝ፣ ሰዎች እነዚህን የጋራ ቦታዎች እንዴት በአክብሮት ይዘው እና አብሮነታቸውን በጥንቃቄ አስቀጥለው መዝለቅ መቻላቸው ነበር።
መጨናነቅ በሚበዛባቸው የኢኳዶር አካበቢዎች እና በትላልቅ ከተማዎች ውስጥ፣ የሰዎች ስብጥር እና የታሪኮች ብዝሃነት ሕያው ሆኖ መኖሩ መቻሉን በየቀኑ መመልከት ይቻላል። ኢኳዶራውያን ከብዙ ዓይነት ወገኖች የተውጣጡ ናቸው። ከእነዚህም መካከል የስፔን ቅኝ ገዥዎች ዘሮች፣ አፍሮ-ኢኳዶራውያን፣ በደጋ እና በአማዞን የሚኖሩ የአገሬው ተወላጆች፣ እንዲሁም ከእስያ እና ከመካከለኛው ምስራቅ በቅርቡ የደረሱ አዲስ መጤዎች ይገኙበታል። እነዚህ ሰዎች የሚኖሩት ተነጣጥለው አይደለም። እንደ አንድ የተገናኘ ማኅበረሰብ አካል ሆነው አብረው ይኖራሉ፣ በጋራ ይነግዳሉ፣ ይሠራሉ እንዲሁም ሃሳቦችን ይለዋወጣሉ።
በእነዚህ አካባቢዎች ሰዎች በብሔር ማንነታቸው አይከፋፈሉም። በቤተሰብ የኋላ ታሪክ ምክንያት ጎረቤቶቻቸውን በጠላትነት አይመለከቱም። በቅርብ ጊዜ ውስጥ ቤተሰቦችን የሚነጣጠል የእርስ በእርስ ጦርነት አልተካሰተም። ከምንም በላይ አስገራሚ ሆኖ ያገኘሁት በተፈጥሮ ውስጥ ያለው አስደናቂ ልዩነት ብቻ ሳይሆን፣ ሰዎች አብረው የሚኖሩበት መንገድም ጭምር ነው። በመካከላቸው ያለውን ልዩነት በህይወታቸው ዋጋ የሚጨምር የዕለት ተዕለት የሕይወት ክፍል አድርገው እንጅ እንደ አደጋ አድርገው አይቆጥሩትም።
ይህ ተግባራዊው የአብሮነት መለያቸው አእምሮዬን ወደ ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ መልሶታል። ይህ ወቅታዊ ሁኔታ የሰው ዘር መገኛ ተብላ ለምትጠራው የትውልድ አገሬ ኩራትም ሐዘንም በተመሳሳይ ጊዜ እንዲሰማኝ ያደርጋል። የኢትዮጵያ ታሪክ ከኢኳዶር የረዘመ ታሪክ እና ጥልቀት ያለው ነው። ቀደምት የሰው ልጅ ቅድመ አያቶች ሆሞ ሳፒየንስ ለመጀመሪያ ጊዜ የኖሩባት እና የሰው ዘር በዓለም ዙሪያ ጉዞውን የጀመረባት መነሻ ነች። እንደ አክሱም ያሉ ጥንታዊ ሥልጣኔዎች ብዙ የአውሮፓ አገሮች ከመኖራቸው በፊት በኢትዮጵያ ነበሩ። እንደ 1888ቱ የአድዋ ጦርነት ያሉ ጊዜያት ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃነት እና የሉዓላዊነት ምልክት እንድትሆን አረጋግጧዋል።
ዛሬ ኢትዮጵያ የተከፋፈለች ትመስላለች። በማኅበረሰብ ውስጥ ያሉ ሰዎች የመተማመን እጦት እንዳለ ይሰማቸዋል፣ የኢትዮጵያም ብሔራዊ አንድነት ስጋትም ከገደቡ የተጠጋ ይመስላል። የፖለቲካ ሥርዓቷ ብሔርን የሀገረ-መንግሥት ምስረታው ዋነኛ መንገድ ማድረጉ በሀገሪቷ ያለውን ውጥረት ከፍ አርጎታል። በዚህም ምክንያት አነስተኛ ታሪክ እና የቅርብ ጊዜ የቅኝ ግዛት ታሪክ ያላት ኢኳዶር በተለያዩ ቡድኖቿ መካከል ሰላምን ማስጠበቅ ከቻለች፣ ኢትዮጵያ በበለፀገ ቅርስዋ፣ በሚያምሩ የተፈጥሮ ገጽታዎቿ እና በሚያስደንቅ ጥንካሬዋን ተመሳሳይ አንድነት ማግኘት ለምን ይቸገራታል? የሚል ረፍት የሚነሳ ጥያቄ ወደ አዕምሮዬ ይመጣል።
እንዲህ ያለው ችግር የሚመጣው በኢትዮጵያውያን መካከል ካለው የባሕርይ ወይም በጎ ፈቃድ ቅንነት ማጣት አይመስለኝም። ችግሩ የተሻለ የፖለቲካ አቅጣጫ ለመገመት የሚያስችለንን እድል ማጣታችን ነው። ዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ሰፊውን ልዩነቷን ወደ ጠንካራ የዜግነት ማኅበረሰብ ከማዋሃድ ይልቅ፣ በውጭ ርዕዮተ ዓለሞች እና በንጉሠ ነገሥታዊ ታሪኳ ላይ በተሰጡ ግብረመልሶች ልትቀረፅ ችላለች። እነዚህ ተጽዕኖዎች በብሔር ፌዴራሊዝም አማካኝነት የብሔር ልዩነቶችን ወደ ሥርዓታማ አደረጃጀት ቀይረውታል። ይህ ውሳኔ ሀገሪቱን ቀጣይነት ባለው እምነት የማጣት እና አመጽ ግጭቶች ውስጥ አስሯታል። እነዚህ ዑደቶች አሁን በኩራት የተሞላ ታሪኳ ላይ ጥላ ያጠሉበት ሲሆን በታሪክ ያገኘችውን ታላላቅ ስኬቶችም ለአሳሳቢ አደጋ ያጋለጡ ሆነዋል።
ይህ ጽሑፍ አንድ እንቆቅልሽ በመጥቀስ ይጀምራል። አራት የተለያዩ ንጽጽሮችን በመጠቀም ሐሳቡን ያጠናክራል። የመጀመሪያው ግንዛቤ ሰዎች ሥነ-ሕይወታዊ እና ባህላዊ ብዝሃነትን በማጣመር አብሮ መኖርን እንደ ዕለታዊ ልምምድ በሚቆጥሩባት ኢኳዶር ላይ ያተኩራል። ሁለተኛው ግንዛቤ የሚመጣው የዳርዊን የጋላፓጎስ ጥናቶች ሲሆን፣ ህልውና በዙሪያችን ለሚለዋወጡ ሁኔታዎች መላመድ ላይ እንደሚመሰረት ያሳያል። ሦስተኛው ግንዛቤ ከምድር ወገብ ከሚጠቆመው አማካይ ቦታ በመነሳት፣ የሰው ልጅ አፍሪካን ለቆ ከመውጣት ታሪክ ጋር በማገናኘት፣ ኢትዮጵያ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ያላትን ሚና ይጠቁማል። የመጨረሻው ግንዛቤ ደግሞ በአሜሪካ ውስጥ የነበረውን የስፔን እና የፖርቱጋል ቅኝ ግዛት በመጥቀስ፣ ትብብር የሌለው ቁጥጥር የሚያስከትለውን አደጋ ያመላክታል።
እነዚህን ጉዳዮች ከመረመርን በኋላ፣ ኢትዮጵያ በዘመናዊው ዘመን ለማደግ የግድ መለወጥ እንዳለባት ግልጽ ይሆናል። ሀገሪቷ ከብሔር-ተኮር ፌዴራሊዝም ሥርዓት ወደ ዜግነት-ተኮር ሕገ መንግሥት መሸጋገር አለባት። ቀጣዮቹ ክፍሎች ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት መዋቅራዊ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ይህንን ፍላጎት በጥልቀት ይመለከታሉ።
- የተፈጥሮ ብዝሃ ሕይወት፣ ፈተናን የመቋቋም ችሎታ እና አብሮነት
የኢኳዶር ከባቢ በዓለም ላይ ካሉ እጅግ በጣም ብዝሃነትን ከሚያስተናግዱ አካባቢዎች አንዱ ነው። የአንዲስ ተራሮችን፣ የአማዞን ጫካን፣ የባሕር ዳርቻ ሜዳማ ቦታዎችን፣ እና አይነተኛውን የጋላፓጎስ ደሴቶች ሥነ-ምህዳር ያካትታል። ይህ የከባቢዎች ቅልቅል ህይወት ያላቸው ነገሮች ከጊዜ ጋር እንዴት እንደሚላመዱ የሚያስረዳ የእውነተኛው ዓለም ምሳሌ ሊሆን ይችላል።
በጋላፓጎስ ደሴቶች፣ ዳርዊን አነስተኛ የአካባቢ ልዩነቶች እንኳ ዝርያዎች በሚለዋወጡበት መንገድ ላይ ትልቅ ለውጦችን እንደሚያስከትሉ አስተውሏል። ትንንሽ ወፎች የተወሰኑ የምግብ ዓይነቶችን ለመመገብ የተለያዩ የመንቆር ቅርጾችን አዳብረዋል። ኤሊዎች በየደሴቶቻቸው ላይ ከሚገኙት ተክሎች ጋር የሚስማሙ ዛጎሎችን ማብቀል ችለዋል። ከእነዚህም መሀል አንዳንዶቹ ደግሞ ረዣዥም ተክሎች ላይ ለመድረስ ኮርቻ የሚመስል ዛጎል ሲኖራቸው፣ ሌሎች ደግሞ አጫጭር ተክሎችን ለመመገብ የሚስማማ ጉልላት የሚመስል ዛጎል ነበራቸው። የባሕር ኢንሽላሊቶን ጨው እንዲያስወግዱ የሚያስችላቸው እጢዎችን በማግኘታቸው አልጌ ለመመገብ ወደ ውቅያኖስ ዘልቀው መግባት ችለዋል።
ተፈጥሮ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ሥርዓቶች እንዴት መሥራት እንደሚችሉ የሚያሳይ ጠንካራ ምሳሌን ይሰጣል። ሥርዓቶች ቀጣይነት የሚኖራቸው ትርፍ ክፍሎቻቸው አጠቃላይ መዋቅሩን ሳይሰበሩ ለአካባቢያዊ ፍላጎቶች እና መሰናክሎች ሲስተካከሉ ነው። ትንንሽ ወፎች ወደ ሌላ ዝርያ አልተለወጡም፤ በትልቁ ቡድናቸው ውስጥ እየቆዩ ተቀያይረዋል። በመዋሃድ ውስጥ እየቆዩ መስተካከል ከጊዜ ጋር ጠንካራ ሆኖ ለመቀጠል ቁልፍ ነገር ነው።

የኢኳዶር ሕዝብ የተፈጥሯዊ ስብጥርነት ምንነትን በጉልህ የሚያንፀባርቅ ነው። ሕዝቡ በርካታ የሀገሬው ተወላጅ ብሔሮችን፣ አፍሮ-ኢኳዶራውያንን፣ ሜስቲዞዎች (የተቀላቀሉ ዘር ያላቸው) እና አዳዲስ ስደተኛ ቡድኖችን በአንድ ላይ አቅፎ የያዘ ነው። እነዚህ ማኅበረሰቦች በዜግነት ላይ በሚያተኩር እና የሀገሪቱን ብዝኃነት እና ለብዝኃ-ብሔራዊ ማንነት እውቅና በሚሰጥ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ይተዳደራሉ። ምንም እንኳ ሥርዓቱ ፍጹም ባይሆንም፣ የእኩልነት መጓደል እና አድሎዎች አሁንም ቢኖሩም፣ ግጭቶችን ለመፍታት በኃይል ወይም ውዝግብ በሚነሳባቸው የግዛት አለመግባባቶች ላይ ከማተኮር ይልቅ እንደ ምርጫን፣ ማኅበራዊ ውጥኖችን፣ እና ፍርድ ቤቶችን በመሳሰሉ ብሔራዊ ተቋማት እንደ መፍትሔ የመሳሪያ ይገለገሉባቸዋል።
ሁሉንም ዜጎች በማካተት ላይ ያተኮረው ይህ ብሔራዊ ስርዓት በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ውስጥ በጉልህ ይታያል። እንደ ኪቶ እና ጉዋያኪል ያሉ ከተሞች በብሔር ቡድኖች የተከፋፈሉ ሳይሆኑ አንዱ ከአንዱ ቅይጥ በሆነበት ማኅበረሰባዊ መስተጋብር ውስጥ ለመኖር የቻሉበት ሁኔታ አለ። እንደ ኦታቫሎ ባለው ታዋቂ ገበያ እና የሰዎች እንቅስቃሴ በሚበዛባቸው ቦታዎች የሀገሬው ተወላጅ የእጅ ጥበብ ባለሙያዎች፣ የሜስቲዞ ነጋዴዎች እና ከመላው ዓለም የመጡ ተጓዦች በጋራ በፈጠሩት የኢኮኖሚ ትስስር እርስ በርስ ይደጋገፋሉ። እንደ መንገዶች፣ ሆስፒታሎች፣ እና ትምህርት ቤቶች ባሉ የሕዝብ አገልግሎቶች ላይ ሰዎች እንዲደጋገፉ እና እንዲተባበሩ ያስገድዳሉ። ይህ ልዩነትን በሀገሪቱ እንደ የለት ተለት የሕይወታቸው አካል ማድረግ የቻለ የአስተዳደር ስርዓትን ማሳያ እንጅ በአብሮነታቸው ላይ የተጋረጠ አደጋ እንዳይሆን አድርጓል።
2.1 ከአግላይነት ወደ ብዝኃ-ማንነት ሀገረ-መንግሥት መሸጋገር
ኢኳዶር ወደዚህ የአስተዳደር መርህ እንዲሁ በአጋጣሚ አልደረሰችም። ወደዚህ ምዕራፍ ለመሸጋገር ሀገሪቱ ልክ እንደ ሌሎች የላቲን አሜሪካ ብሔሮች ሁሉ ጉልህ የሆነውን የአገሬውን ነባር ሕዝቧ ለበርካታ ዘመናት በመገለል ውስጥ ለማለፍ ግድ ሆኖበት ነበር። ኃያል የነበረው ሜስቲዞ ገዥ መደብ (የተቀላቀሉ ዘር ያላቸው ገዥዎች) የኢኳዶርን ፖለቲካዊ እና ባህላዊ ማንነት በመበየን፣ ኢኳዶራዊ መሆን ማለት ምን ማለት እንደሆነ የሚስረዳ ወጥነት ያለው ብያኔን ማስፈን ቻለ።

ይህ ለውጥ የተከሰተው የሀገሬው ነባር ተወላጆች ማለትም የኢኳዶር ተወላጅ ብሔረሰቦች ኮንፌዴሬሽን (CONAIE) ቆራጥ እና የተደራጀ ንቅናቄ መጀመሩን ተከትሎ ነው። ኮንፌዴሬሽኑ በ1986 ከተመሰረተ በኋላ፣ የመንግሥት የአግላይነት ታሪክ ጥያቄ እንዲነሳበት የኢኳዶር ብዛሃነት እውቅና እንዲሰጠው ለዓመታት በተቃውሞዎች፣ በፖለቲካዊ ጥረቶች እና በምሁራዊ ንቅናቄዎች ላይ ሲሰራ ኖሯል። ጥረታቸው ኢኳዶርን የብዝኃ-ማንነት ሀገረ-መንግሥት እንደሆነች ስር-ነቀል በመሆነ መንገድ እውቅና ያስገኘውን የ2008 ሕገ መንግሥት አዋልዷል።
ብዝኃ-ማንነት (Plurinational) የሚለው ፅንሰ ሐሳብ እጅግ ወሳኝ ነው። ፅትሰ ሐሳቡ የራሳቸው ቋንቋዎች፣ ልማዶች እና ታሪኮች ያላቸው ብዙ “ማንነቶች” ብሔሮች እና ልዩ መገለጫ ያላቸው ቡድኖች በአንድ አገር ውስጥ አብረው መኖር እንደሚችሉ ይቀበላል። እንዲያም ሆኖ ፅንሰ ሐሳቡ ግዛቶችን ወደ ራስ ገዝ ብሔር-ተኮር ክልሎች ከሚከፋፍለው የብሔር ፌዴራሊዝም የተለየ ነው። ብዝኃ-ማንነት ይህንን ልዩነት ወደ ሀገሪቱ ፖለቲካዊ እና ሕጋዊ ሥርዓቶች ለማምጣት ይሠራል። ይህም በሚከተሉት ግልጽ መንገዶች ይከሰታል፡
- ለነባር የሀገሬው ተወላጅ የፍትህ እውቅናን ያጎናፅፋል፦ሕገ መንግሥቱ ነባር የፍትህ ሥርዓቶችን በማፅደቅ ማኅበረሰቦች በብሔራዊው ሕገ መንግሥት ወሰን ውስጥ የቆዩ የውስጥ ችግሮቻቸውን በባህላዊ ልማዶቻቸው እንዲፈቱ ያስችላቸዋል።
2.2 በባህል የመላመድ ትምህርት፡ የካያምቤ ቢዝኮቾዎች
የኢኳዶር የዕለት ተዕለት ሕይወትን ስንመለከት ሰዎች ነባር ልማዶችን ጥቅም ላይ በማዋል በሕግ ብቻ ከመዳኘት ባሻገር እንዴት የማኅበረሰቦችን ማቀራረቢያ መንገድ መፍጠር እንደሚቻል ያሳያል። የደጋማ ከተማዋ ካያምቤ በቢዝኮቾዎቿ (Bizcochos) ትላቅ ምሳሌ ሆና የምትጠቀስ ሲሆን፣ ከቅኝ ግዛት ዘመን አንስቶ የመጡ እና በዓለም ዙሪያ ታዋቂ የሆኑ ኩኪሶች ናቸው።
የቅኝ ግዛት አሸናፊነት ምልክቶች አድርገው ከመተው ይልቅ፣ በካያምቤ የሚኖሩ ሰዎች ቢዝኮቾዎችን የባህላቸውና የኢኮኖሚ ጥንካሬያቸው መለያ አድርገው ቀይረዋቸዋል። አሁን በሁሉም ቤተሰብ ማለት በሚቻል ደረጃ ተወዳጅ ሲሆኑ ጎዳናዎች ደግሞ በዳቦ መጋገሪያዎች የተሞሉ ናቸው። ከመላው ኢኳዶር እና ከሌሎች አገሮች የመጡ ተጓዦች ቢዝኮቾዎችን ከትኩስ አይብ እና ትኩስ ቸኮሌት ጋር ለመመገብ ወደ ካያምቤ ይመጣሉ። በአንድ ወቅት በቅኝ ግዛት ዘመን ተጭነውባቸው የነበሩ እነዚህ ቀለል ያሉ ምግቦች፣ ዛሬ ወደ ውድ ባህል፣ የሚያድግ ንግድ፣ እና ከነገሮች ጋር የመላመድ ችሎታቸውን ማስረጃ ሆነዋል።
ይህ ታሪክ በኢኳዶር ያሉ ሰዎች አስቸጋሪ ታሪኮችን ወደ ጥንካሬ እንዴት እንደሚቀይሩ ያሳያል። ካያምቤ አንድነት የሚያድገው ያለፈውን ታሪክ በማጥፋት ሳይሆን ወደ የጋራ ባህል በመቅረጽ እንደሆነ ያስተምረናል። ዛሬም ድረስ ብሔር-ተኮር ፌዴራሊዝም በሚያሳድረው ተጽዕኖ ውስጥ የምትገኘው ኢትዮጵያ፣ ከዚህ ልምድ ጥሩ ትምህርት ልትወስድ ትችላለች። ማዋሃድ እና መላመድ መለያየት እና መጣል ከሚያመጣው በላይ እድገትን መፍጠር ይችላል።
2.3 የጋራ ዜግነት ሳይኖር አካታችነትን ለማምጣት የመጣር ፈተና
የኢትዮጵያን ሁኔታ በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት፣ አንድ ተጨማሪ ንጽጽር ማድረግ ይበልጥ ይረዳል። የስፔን እና የፖርቱጋል መንግሥታት በኃይል እና ወረራ የአሜሪካን አህጉር ተቆጣጥረው ነበር። ቦታዎችን ለመቆጣጠር በዘመነ መሳሪያ መደራጀትን እና አደገኛ ወረርሽኞችን እንዲስፋፉ ማድረግን እንደ ሁነኛ ስልት አድርገው ተጠቀሙባቸው። እነዚህ መንግሥታት የሀገሬውን ተወላጆች የአስተዳደር ሥርዓት እና ባህል አደቀቁ፣ አስወገዱ ብሎም ጠቅልለው ወረሱ። ከዚህ በኋላ የተከተለው ጥብቅ በሆኑ የሥልጣን ደረጃዎች ላይ የተመሰረተ ማኅበረሰብን መፍጠር ነበር። ለእኩልነት የተደረገው የረዥም ጊዜ ትግል፣ ከጅምሩ እነርሱን ታሳቢ ባላደረጉ መንግሥታት ውስጥ የተጨቆኑ ቡድኖች እውቅና እና መብቶችን እንዲያገኙ በማድረግ ላይ ያተኮረ ነበር።
የኢትዮጵያ ታሪክ በአንፃሩ በተለየ መንገድ ውስጥ ያለፈ መሆኑን እንረዳለን። ዘመናዊው ሀገረ-መንግሥት ቅይጥ እድገትን፣ ሽርክናን፣ እና ስምምነቶች ያቀፈ ነበር። ብዙ ጊዜ የተለያዩ ቡድኖችን ያካተተ ቢሆንም የአካባቢ መሪዎቻቸውን ወይም ልማዶቻቸውን ግን አላጠፋም። ዛሬ ያለው ችግር የጠፉ ቡድኖች ቅሪቶችን ስለመያዝ አይደለም። ነገር ግን ዛሬ ላይ እየኖሩ ያሉትን እንዲሁም የተለየ ማንነት ያላቸውን ማኅበረሰቦች በአብሮነት የመምራት ጉዳይ ነው። ባለፉት ጊዜያት የነበሩ ጭቆናዎችን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ መቻሉ ለኢትዮጵያ ጥቅም አስገኝቶ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ግን ፈተናን ያስከተለ ጉዳይ ሆኗል። የቤት ስራ የሆነው የየራሱ ሰፋፊ ታሪኮች ያሉትን ሕዝብ ለጅማሮ ያህል እንኳን አንድ ወጥ የሆነ የዜግነት እምነት ሥርዓት ባይኖርም ወደ አንድ የጋራ የዜግነት ማዕቀፍ የማምጣት ኃላፊነትን መወጣቱ ላይ ነው። ብሔር-ተኮር ፌዴራሊዝም ይህንን ችግር ለመፍታት ሞክሮ ነበር፣ ነገር ግን ችግሩን ከማስተካከል ይልቅ ውጥረት እና ፍትጊያ ውስጥ የገቡ የፖለቲካ ኃይሎችን በመፍጠር ችግሩን ይበልጥ ሊያባብሰው ችሏል።
- 3. አንድነትን ለመገንባት የሚያስችሉ ቁልፍ ሐሳቦች
ኢትዮጵያ ፈጣን የፖለቲካ መፍትሄዎችን አልፋ ቀጣይነት ባላቸው መርሆዎች ለውጧን መሠረት ማድረግ አለባት። እንደ ምድር ወገብ ያሉ ሐሳቦች እና የሰው ልጅ ስደትና ለውጥን የሚመለከቱ እውነታዎች ይበልጥ የተሳሰረ የወደፊት ሕይወትን ለመሳል የራሳቸውን ትርጉም አላቸው።
3.1 አማካይ ስፍራ ላይ ሚዛንን ጠብቆ መቆየት፡ የምድር ወገብ እና ኢትዮጵያ
የምድር ወገብ ምናባዊ መስመር ይሁን እንጅ ራሱን የቻወ አካላዊ እና ተምሳሌታዊ ትርጉም ይዟል። የምድር ሁለቱ ንፍቀ ክበቦች የሚገናኙበትን መሃል ያመለክታል፤ በስበት እና በማሽከርከር ኃይሎች አማካኝነት ልዩ ሚዛንን ይፈጥራል። በኢኳዶር “ሚታድ ዴል ሙንዶ” (“የዓለም መሃል”) በሚባለው ሐውልት ላይ፣ አስጎብኚዎች እንቁላልን በምስማር ላይ ቀጥ አድርጎ በማቆም ይህን ሚዛን ያሳያሉ።
ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ ተብላ በተደጋጋሚ የምትጠቀስ ሲሆን ይህም ለሰው ልጅ መነሻ ታሪክ ጥልቅ የሆነ ጠቀሜታ ያላት ሀገር ያደርጋታል። ዛሬ ላይ ግን የራሷን የፖለቲካ ሚዛን ፈልጎ የማግኘት አስቸጋሪ ፈተና ገጥሟታል። የብሔር ልዩነቶች አገሪቱን ጎትቶ ለመበታተን ጫፍ ያደረሳትን ኃይል ማቆም የሚቻልበትን መንገድ መፈለግ የግድ የሚላት ሲሆን፣ ይሄንን ከማድረግ ጎን ለጎን ደግሞ የዜግነት እና ሕገ-መንግሥታዊ አንድነትን መፍጠር ይገባታል።
ሐሳቡ ቀላል ነው፣ አገሮች የሚበለጽጉት እና የሚዘልቁት ሰዎችን የሚያሰባስቡ ተቋማት እንደ የጋራ ሕጎች፣ የኢኮኖሚ ግቦች፣ እና ሁሉንም የሚያካትቱ ብሔራዊ ምልክቶችን ማፅናትን የብሔር ክፍፍልን ወይም ሌሎችን በመውቀስ ከሚመጡ የልዩነት ታሪኮች ማስቀደም ስለቻሉ ነው። ኢትዮጵያ ነባር ባህሎችን እና ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን አስጠብቃ ሕዝቧን ከከፋፈለውን “የብሔሮች እና ብሔረሰቦች” ስርዓትን ከማስቀጠል ይልቅ በሕዝቡ ዘንድ የጋራ ማንነት በመገንባት ዙሪያ የበለጠ ትኩረት የሚያደርግ ሕገ-መንግሥታዊ ስርዓትን መከተል ይኖርባታል።
3.2 ከስነ-ሕይወት ወደ ዜጋዊ ማንነት መሸጋገር፡ ዳርዊን፣ ስደት እና ህልውና
የሰው ልጅ ታሪክ ከአዳዲስ ነገሮች መላመድን ሲያስተምረን ኖሯል። በኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ የተገኙ ቅሪተ አካላት የመጀመሪያዎቹ ሰዎች እዚያ ይኖሩ እንደነበር እና ከጊዜ ጋር ይለዋወጡ እንደነበር ያሳያሉ። ከ60,000 እስከ 80,000 ዓመታት በፊት የተከሰተው ሰፊው “ከአፍሪካ የመውጣት ስደት” የሰው ልጆች ፈተናዎችን መቋቋም እንደሚችሉ አሳይቷል። የሆሞ ሳፒየንስ ቡድኖች ዓለምን ሲያቋርጡ፣ እንደ በረዷማ ምድር፣ የሚያቃጥሉ በረሃዎች እና ጥቅጥቅ ያሉ የዝናባማ ደኖች ያሉ አስቸጋሪ አካባቢዎችን ተጋፍጠዋል። የተሻሉ መሣሪያዎችን እና አዳዲስ የአደን ዘዴዎችን በመፍጠር ህይወትን ለማስቀጠል ያስቻሏቸውን መንገዶች አግኝተዋል። ከዚህም በላይ እንደ የተሻለ መግባቢያ ቋንቋ፣ የቤተሰብ ምስረባ፣ እና የንግድ ልውውጥ ባሉ ነገሮች እርስ በርስ ለመገናኘት አዳዲስ መንገዶችን ገንብተዋ። እነዚህ ነገሮች በሙሉ ትላልቅ ቡድኖች አብረው እንዲሠሩ ረድተዋቸዋል።
ይህ ከስነ-ሕይወት ወደ ፖለቲካ የተደረገው ጉዞ አንድ ቁልፍ ሐሳብን ይገልጻል። የዳርዊን ጽንሰ ሐሳቦች ዘመናዊ የሀገር ግንባታ ተቋማዊ ለውጦችን በማምጣት የሚደረግ ህልውናን የማስጠበቅ ሐሳብ መሆኑን ያሳየናል። ኢትዮጵያ ህልውናዋን ለማስቀጠል ማንነትን እና የሥልጣን ተዋረድን ከእንደገና የሚበይኑ የፖለቲካ ሕጎችን እንደ አዲስ መንደፍ ይኖርባታል። በኢትዮጵያ ያሉ ልዩነቶች የችግር መንስኤዎች ከመሆን ይልቅ የአብሮነት መሰረት የሚሆኑበትን ሥርዓት መገንባት ያስፈልጋል። የስነ-ሕይወት ዝግመተ ለውጥ በሳንባ አየርን እንድንተነፍስ ወይም ዘር ተሰንጥቆ እንዲያድግ እና የመሳሰሉ የአካላዊ ገጽታዎችን እድገት ያሳያል። ማኅበራዊ ዝግመተ ለውጥ እንደ ሕጎች፣ የምርጫ ሥርዓቶች፣ እና የመሬት ባለቤትነት መብቶች ያሉ ተቋማዊ ገጽታዎችን ያሻሽላል። አዳዲስ ፈተናዎችን ለመቋቋም ሥርዓቶቻቸውን የማያስተካክሉ ማኅበራት ደግሞ የፖለቲካዊ ጥፋትን የሚያስከትል የመፍረስ አደጋ ይገጥማቸዋል።
- ወደፊት ያለው መንገድ፡ ሰላማዊ የወደፊት ሕይወትን ለመገንባት መርሆዎች
ከብሔር-ተኮር ፌዴራሊዝም ወደ በዜግነት ላይ ያተኮረ ሞዴል መሸጋገር ጠንካራ እና ብልህነት የተሞላበት ዕቅድ መንደፍን ይጠይቃል። ይህ ለውጥ ማንነቶችን ስለማጥፋት ሳይሆን እነዚህ ማንነቶች ያለ ግጭት አብረው የሚኖሩበትን እና የሚያድጉበትን ሥርዓት በመገንባት ላይ ያተኮረ ነው። ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ የሚጠቁሙ መርሆዎችን በመከተል ሕገ መንግሥቱን እና ነባር ተቋማትን ለማሻሻል የሚያስችለውን መንገድ ለመጥረግ ይረዳል።
4.1 ሕገ-መንግሥታዊ መዋቅር፡ ከብሔር ክፍፍል ወደ ብሔራዊ ውህደት
ሕገ-መንግሥት የአንድ ሀገር የጀርባ አጥንት ሆኖ በማገልገል ለሚከተሉት ፖለቲካዊ ውሎች መሠረታዊ ግቦችን ያስቀምጣል። የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንድነትን ለማጠናከር በዜጎቿ ላይ ትኩረት ማድረግ አለበት።
- በዜግነት ላይ ቀዳሚ ትኩረት ማድረግ። እንደ መቅድም እና ሉዓላዊነት ላይየሚያተኩሩ የሕገ-መንግሥቱ አስፈላጊ ክፍሎችን እንዲሁም የሉዓላዊነት ባለቤት “የኢትዮጵያ ሕዝብ” በጥቅሉ እንደሆነ በግልጽ ማሳየት እንዲቻል አድርጎ ሕገ-መንግሥቱን ከእንደገና መጻፍ ያስፈልጋል። ይህ በአሁኑ ጊዜ “ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች” ላይ ያለውን ትኩረት መቀየር ይችላል።
- ከብሔር ክፍፍል መራቅ። የክልል ወሰኖችን በብሔር ማንነት ላይ ተመስርቶ ከመወሰን ይልቅ፣ እንደመልከዓምድራዊ አቀማመጥ፣ ዋነኛ የሕዝብ ማዕከላት፣ እና ኢኮኖሚያዊ ቀጠናዎች ባሉ ተጨባጭ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ከእንደገና ማካለል ያስፈልጋል። ይህ አስተዳደርን ከብሔር ማንነት በመለየት በግዛት ወሰን ላይ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ይቀንሳል።
- ሊጠበቁ ለሚገቡ መብቶችንዋስትና መስጠት። የግል ነፃነቶችን እና የጋራ የባህል እና የቋንቋ መብቶችን ለመጠበቅ ብሔራዊ የመብት ረቂቅ ሕግ መፍጠር። ጠንካራ ነፃ የፍርድ ቤት ሥርዓት ሕገ መንግሥቱን የመገምገም እና በሀገር ውስጥ ያሉ ሁሉንም አናሳ ቡድኖች የመጠበቅ ሥልጣን በመያዝ ይህንን መደገፍ አለበት።
4.2 የሥልጣንን ክፍፍልን ከብሔር አጥር ውጭ ማድረግ
የተረጋጋ መንግሥት በማንነቶች መካከል ፉክክርን ከመቀስቀስ ይልቅ አብሮ መሥራትን የሚያበረታቱ የሥልጣን ክፍፍል መንገዶች ያስፈልጉታል።
- የሁለት-ምክር ቤት ሥርዓቱን እንደገና መንደፍ። የሕግ አውጪው አካል በሁለት ክፍሎች የተከፈለ ሆኖ እንዲቆይ ማድረግ። ታችኛው ምክር ቤት የመምረጥ መብት የሕዝብን እኩልነት እንዲያንጸባርቅ ማድረግ። የላይኛው ምክር ቤት ከብሔር ማንነት ጋር ያልተቆራኙ ክልሎችን እንዲወክል ማዋቀር። ይህ አደረጃጀት ፍትሃዊ ሚዛንን የሚያረጋግጥ ሲሆን ለብሔር ግጭቶች መንስኤ ከመሆንም ይርቃል።
- በምርጫ ወቅት ለመተባበር ማበረታቻዎችን መፍጠር። እንደ ደረጃ የተሰጣቸው የምርጫ ሥርዓቶች (ranked-choice voting) ወይም ተለዋጭ የምርጫ ሥርዓቶች (alternative vote systems) ያሉ የድምፅ ውህደት ዘዴዎችን መጠቀም። እነዚህ ዘዴዎች እጩዎች ከዋና ደጋፊዎቻቸው ውጪ ካሉ መራጮች ሁለተኛ ወይም ሦስተኛ ምርጫዎችን እንዲያገኙ ያስገድዳሉ፤ ይህም መካከለኛ አካሄድን እና በቡድኖች መካከል ጥምረቶችን ያበረታታል።
4.3 ግጭቶችን ለመቆጣጠር መዋቅሮችን መገንባት
በሀገሪቱ ያለው የረዥም ጊዜ ያለመግባባት ታሪክ ግጭቶችን ለመከላከል እና ለመፍታት ጠንካራ እና ገለልተኛ ሥርዓቶችን ማቋቋም እጅግ አስፈላጊ ያደርገዋል።
- ገለልተኛ ኮሚሽኖችን ማቋቋም። የድንበር ውዝግቦችን ለመቆጣጠር እና ምርጫዎችን ለመቆጣጠር ከአድልዎ የፀዱ ኮሚሽኖችን መገንባት። የሕዝብን አመኔታ ለማግኘት ከፖለቲከኞች ይልቅ ብቃት ያላቸው ባለሙያዎችን እና የሲቪክ መሪዎችን መቅጠር።
- የግልግልባህልን አስቀድሞ ማስተዋወቅ። አለመግባባቶች ወደ አመጽና ግጭት እንዳይለወጡ ለመከላከል ብሔራዊ የግልግል አገልግሎት እና የአካባቢ ሰላም ቡድኖች ገብተው ውዝግቦችን ቀደም ብለው እንዲቆጣጠሩ ማድረግ።
- የመረጃ ሥርዓቶችን ከተግባር ዕቅዶች ጋር ማገናኘት። ስለ ጥላቻ ንግግርን፣ መፈናቀልን፣ እና የታጣቂዎችን የእንቅስቃሴ መረጃበመከተታል ሲቪሎችን ለመከላከል ከሚረዱ ፈጣን ምላሽ ስልቶች ጋር የሚያገናኝ የቅድመ ማስጠንቀቂያ አሠራር መፍጠር።
4.4 ቋንቋ፣ ትምህርት እና የሥራ እንቅስቃሴ
ብሔራዊ ማንነት በትምህርት ቤቶች፣ በሕዝብ ቦታዎች፣ እና በመላ ሀገሪቱ በሚደረጉ የሰዎች እንቅስቃሴዎች ይፈጠራል።
- በርካታ ቋንቋዎችን ለማስተማር የሚያስችል ፖሊሲ መፍጠር። ባህላዊ ማንነት እንዳይጠፋ ለማድረግ ወጣት ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማራቸውን ማረጋገጥ። ቀጥሎ መግባባትን ለማሻሻል እና ሰዎች በነፃነት እንዲዘዋወሩ ለማስቻል የጋራ ብሔራዊ ቋንቋ እና ዓለም አቀፍ ቋንቋን ማስተዋወቅ።
- አንድነትን የሚያመጡ ትምህርቶችን ማቀድ። የኢትዮጵያን የጋራ ሕገ-መንግሥታዊ ታሪክን ከአካባቢያዊ እና ከማኅበረሰቧ ልዩ ታሪኮች እና ባህሎችን በትምህርት ቤቶች የሚያጎላ ሥርዓተ ትምህርትን መገንባት።
- በየትኛውም ቦታ የመኖር እና ተዘዋውሮ የመሥራት ነፃነትን ማስጠበቅ። የፌዴራል እና ክልላዊ መሪዎች ዜጎች ምንም ገደብ ሳይደረግባቸው በሀገሪቱ ውስጥ በማንኛውም አካባቢ እንዲኖሩ፣ እንዲሠሩ፣ እና ንብረት እንዲፈሩ ማረጋገጥ አለባቸው።

4.5 የሽግግር ፍትህ እና ማኅበራዊ ጥገና
ወደ እድገት መሄድ ያለፉ ጉዳቶችን መጋፈጥ እና እንደገና እንዳይከሰቱ ለመከላከል ሥርዓቶችን መፍጠር ማለት ነው።
- እውነትአፈላላጊነትን ከተጠያቂነት ጋር ማጣመር። ሁኔታን ያማከለ የምህረት አዋጅን ከሕዝባዊ እውነት ማጋራት ጋር የሚያገናኝ እና የፖለቲካዊ አመጽ ሰለባዎችን ለመደገፍ ካሳ የሚያካትት የሽግግር ፍትህ እቅድ ማቋቋም። ግለሰቦችም ሆነ ማኅበረሰቦች የደረሰባቸው ጉዳት እንዲጠገን ቅድሚያ መስጠት።
- ለተቋማዊ ለውጦችቅድሚያ መስጠት። የፀጥታውን ዘርፍ እንደገና በማዋቀር እና የአካባቢ እና የክልል መንግሥታትን ያለ ፖለቲካዊ አድልዎ አገልግሎት እንዲሰጡ በማሠልጠን ወደፊት የሚፈጠሩ የመብት ጥሰቶችን መከላከል።
4.6 ዕድገት እንደ የሰላም ጥቅም
ለጋራ የኢኮኖሚ ዕድገት መደጋገፍን ማጎልበት ሰዎችን ሊያሰባስብ የሚችል ሲሆን፤ ይህ ሁኔታ ግጭትን ማስተናገድ አክሳሪ ምርጫ ያደርገዋል።
- መሠረተ ልማቶችን መገንባት። ክልሎችን እርስ በርስ የሚያቀራርቡ እንደ መንገዶች፣ የባቡር መስመሮች፣ እና የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ባሉ ፕሮጀክቶች ላይ ማተኮር። እነዚህ ጥረቶችየእርስ በርስ እና የፋይናንስ ትስስርን በማሳደግ የጋራ ጥቅሞችን ሊያሳድጉ ይችላሉ።
- በሁሉም ክልሎች በየአካባቢው ያሉ የሥራ ዕድሎችን ማበረታታት። በብዙ አካባቢዎች ብዙ ሠራተኞችን የሚቀጥሩ ፕሮጀክቶችን ማስጀመር። ይህ ወጣቶችን ወደታጣቂነት ከመገፋፋት ይልቅ ህይወትን የሚለውጡ የሥራ ዕድሎችን ይሰጣል።
- ዳያስፖራውን አንድነትን ለመገንባት መጠቀም። ዳያስፖራው በርካታ ክልሎችን እና ብሔረሰቦችን የሚያካትቱ ፕሮጀክቶችን እንዲደግፍ የሚያነሳሱ የኢንቨስትመንት ዕቅዶችን መንደፍ። ከዚህም በተጨማሪ ልማትን በአንድ ቡድን ብቻ ውስጥ መገደብን ማስወገድ።
5. የማጠቃለያ ማስታወሻ፡ ለማደግ መላመድ፣ ለማደግ መተባበር።
ፊንቾች በጋላፓጎስ የእሳተ ገሞራ ደሴቶች ላይ መኖሪያቸውን አድርገው ይበለጽጋሉ። በኢትዮጵያ ደግሞ ገበሬዎች ህይወታቸውን ለማስቀጠል ደጋማ ቦታዎች ላይ የእርሻዎች መሬቶችን ይቆፍራሉ። እዚህ ላይ ተለዋዋጭ ሥርዓቶች ዘላቂ ናቸው የሚል አንድ መልዕክት ደጋግሞ ይመጣል። ኢኳዶር ግለሰቦች ወጥ የዜግነት ማንነት እንዳላቸው ሲሰማቸው በውስጣቸው ያለው ማኅበራዊ ልዩነት እንዴት ጠንካራ እንደሚያደርጋቸው ታሳያለች። የኢቤሪያ አሜሪካ ታሪክ ደግሞ ያለ እውነተኛ ትብብር ለማስተዳደር መሞከር ማኅበረሰቦችን እንደሚከፋፍል ትምህርትን ይሰጣል። ኢትዮጵያ ያለፈችበት ስርዓት የተለያዩ ቡድኖችን አንድ ማድረግ እንዳልቻለ ግልፅ ማሳያ ነው። የጋራ የዜግነት መሠረትን መጣል የማይቻል ከሆነ ግጭቶች ባሉበት መቀጠላቸው አይቀርም።
ወደፊት ያለው ሥራ አንድ አይነትነት እንዲፈጠር ማስገደድ ወይም ኖሮን የማያውቀውን በሁሉም ነገር ምቹ የሆነ ታሪክ መመኘት አይደለም። ይልቁንስ ጥረቶች የሀገሪቱን ሕገ-መንግሥታዊ እና ባህላዊ ሥርዓቶች ለመለወጥ አቅደው መነሳት አለባቸው። ዜግነት ቀዳሚው የፖለቲካ ማንነት መሆን አለበት። ሰዎች የሰውን ልዩነት እንደ መልካም ነገር አድርገው ሊመለከቱት ይገባል። አመፅ ሥልጣንን ለማግኘት መሳሪያ እንዳይሆን የሚያደርጉ ሥርዓቶች ከእንደገና መገንባት አለባቸው። በውስብስብ እና መተንበይ በማይቻል ዓለም ውስጥ፣ ይህንን ማሰብ ቅዤት ሳይሆን ሀገረ-መንግሥቱን አንድ ላይ ለማቆየት አስፈላጊ የሆነ ስትራቴጂ እንደሆነ መታወቅ ስላለበት።
አንድን ሀገር በአዲስ ማዕቀፍ መለወጥ አስፈሪ ፈተናዎችን ሊፈጥር እንደሚችል ይጠበቃል። ፖለቲካዊ ቁርጠኝነትን ይጠይቃል እንዲሁም ውስብስብ የታሪካዊ ውጥረቶችን መቆጣጠርን ይፈልጋል። የዚህ ፅሁፍ የመጀመሪያው ክፍል ከዚህ ጀርባ ያሉትን ሐሳቦች አብራርቷል። ሁለተኛው ክፍል ደግሞ ሀገርን አንድ ለማድረግ እውነተኛ እድገትን ለማምጣት በነባራዊው የዓለም ስርዓት ውስጥ ተስማሚ ሊሆን በሚችል ግልጽ እና ተግባራዊ ዕቅድ ላይ ያተኩራል።