መስከረም ፳ ቀን ፳፻፲፰
September 27, 2025
ማሳሰቢያ:- ከዚህ በታች የቀረቡት መዝገቦች፣ ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ ለፓትርያኩ አቡነ ማትያስ፣ ለቀሳውትና ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሕዝበ ክርስቲያን እያቀረቡ ሳይሳኩ የቀሩና ያልተሳኩባቸውን ምክንያቶች የሚገልጹ መዝገቦች ናቸው፡፡ ፓትርያርኩ ህዝቡን እያሰፈጁ ወደ መቃብር ከመሄድ በቀር ከሳቸው መፍትሄ እንደማይመጣ ሁሉም ተስፋ በቆረጠበት ወቅት ማሰስቢያነቱ የሚጠቅም መሰለኝ፡፡ ማሳሰቢያነቱ ለሁሉም ሕዝበ ክርስቲያን ቢሆንም አሁን ንቅናቄውን በመምራት ላይ ላላችሁት ቀሳውስት የጀመራችሁትን ንቅናቄ የቀረቡት መዛግብቶች ከግቡ ለማድረስ የሚያስችል ጠቃሚ ሀሳቦች ታገኙባቸዋላችሁ። መዛግብቱን በትግስትና በማስተዋል አንብቧችው። በመዛግብቶች የቀረቡት ማብራሪያወች ቀሲስ አስተርአየ ከፃፏቸው ዉስጥ የተወሰዱ ናቸው፡፡
(ዶ/ር መኮንን ባይሴ mekonen.bayssie@gmail.com የቀሲስ አስተአየ ፅሁፎችን በቅርብ የሚከታተል ስለሆነ አንባቢያን ያተርፋባቸዋል ብሎ ይህንን መጠቆሚያ አቅርቧል።)
ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ ቢያንስ ለሶስት አስርት ዓመታት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ክብር ባዋረደና ሰባዊነት በጎደለበት ቦታ ሁሉ ሳያሰልሱ አባታዊ ተግሳፅና ምክራቸውን ሲለግሱ ቆይተዋል። ቀሲስ አስተርአየ እውነትን እንደሚናገሩ የተገነዘቡ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በቤተክርስቲያን ላይ ከበድ ያለ ችግር ሲፈጠርና ከአጥቢያቸው ሊቀ ጳጳስና አገረ ስብከት መፍትሄ ማግኘት ስያቅታቸው መፍትሔ ፍለጋ ከእኝህ አባት ዘንድ ይመጣሉ። የተፈጠሩት አለምግባባቶች ተጣርተው በቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና ችግሩን ለመቅረፍ ጫፍ ላይ ሲደረስ አብረው የጀመሩት ቄሶች እሳቸውን ለብቻቸው አጋፍጠው ይሸሻሉ።
ከሳቸው ጋራ የተሰለፉት ቄሶች ወደ ኋላ ሲሸሹ፤ ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ ግን ወደኋላ ሳይሉ ሳይሳኩ የቀሩባችውን ምክንያቶች በጽfhፍ እያስቀመጡ “ጥምረት ለቤተ ክርስቲያን ዓለም አቀፍ የበይነ መረብ የካህናትና ምእመናን ውይይት መድረክ” እስከተከሰተበት ድረስ ዘልቀዋል።
ጥምረቱ መስከረም ፲ ቀን ፳፻፲፰ ዓ.ም. (Septmeber 20, 2025) ንቅናቄውን ይፋ ባደረገበት መድረክ ላይ ቀሲስ አስተርአየ አጭር መልዕክት አስተላልፈዋል። የመልእክታቸው መደምደሚያ በካህናቱ ንቅናቄ ደስ እንዳላቸው ተልዕኳቸውንም እንደጨረሱና ተስፋም እንዳደረጉ ተናግረዋል፡፡
ለቀሲስ የሚቀርበው ጥያቄ በቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና ችግሩን ለመቅረፍ ጫፍ ላይ ሲደረስ አብረው የጀመሩት ቄሶች እርሰወን አጋፍጠው እንደሸሹት እንደተዚህ ቀደሙ ዛሬስ የጥምረቱ መሪወች ወደኋላ ሸርተት እንደማይሉ ምን ያህል እርግጠኛ ነዎ? ወይስ ጥምረቱን የሚመሩት ቄሶች ከዚህ ቀደም በተከሰቱት ጉዳዮች ላይ አብረወ ተሰልፈው ከሸሹት ቄሶች የተለዩ ናቸው?
የሚቀጥለው ጥያቄ ንቅናቄውን ለምትመሩት ቄሶችና፡ መስከረም 10 ቀን 2018 ዓ/ም በቅናቄው የተካሄደውን ውይይት ለሰማችሁ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ነው፡፡ የጥምረቱን ንቅናቄ በመምራት ላይ ያላችሁ ቄሶች ከዚህ ቀደም ጀምራችሁ ከግቡ ሳታደርሱ የሸሻችሁ ናችሁ? ወይስ ከሸሹት ቄሶች የተለያችሁ ናችሁ? በንቅናቄው የተካሄደውን ውይይት ለሰማችሁ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖችስ ምን ትገምታላችሁ? ከግቡ ያደርሳል? ወይስ የውሀ ሽታ ሆኖ ይቀራል?
ቄስ አስተርአየ የመልእክተወን መደምደሚያ ተልዕክዎን እንደጨረሱና በቄሶች ንቅናቄ ደስ እንዳለዎ ተስፋም እንዳደረጉ ተናግረዋልና ተስፋ የቆረጡባቸውን ጽfhፎቸዎን እንዲቃኙ ለራሰዎ አቅርቤለወታለሁና ግምተወን ይመዝኑ፡፡
መከረም 10 ቀን 2018 ዓ/ም በንቅናቄው የተካሄደውን ውይይት የሰማችሁ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖችም ቀሲስ አስተርአየ በተላያዩ ጊዜወች ቦታወች ወቅቶች፣ ቀኖች፣ ወራቶችና ዓመተ ምህረቶች በመግለጽ ያቀረቧቸውን ጦማሮች እናስብ፡፡ ጦማሮች ለተጀመረው ንቅናቄ ቀራቢወችና አቅጣጫ ማሳያወች ይመስላሉ፡፡ የንቅናቄውን ሂደትና መጨረሳ ታዝበን ለመተቸትም ለማመስገንም የሚያስችሉትን ከብዙወቹ መዛግብቶች ውስጥ ከዚህ በታች ከ 1 እስከ 7 የተዘርዘሩን መርጬ አቀርቤአለሁ።
መዝገቦች
1ኛ . ቨርጂንያ ኪዳነ ምሕረት ሚስቱን ፈትቶ፣ የሌላ ሰው ሚስት እያማገጠ ለብዙ ዓመታት ይቀድስ የነበረው የቄስ ታደሰ ሲሳይ ጉዳይ ነው። የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ አቡነ ፋኑኤልና ሀገረ ስብከቱ ካህኑን በማገድ ፈንታ ቆሞስ አደረጓቸው፡፡ አባ ፋኑኤል ጵጵስናውን ገዝተው ከገቡት ጳጳሳት አንዱ በመሆናቸው ቀኖናውንና ዶክትሪኑን አላስከበሩም፡፡ ከቀኖናውና ከዶክትሪኑ ጋራ በመጣረሳቸው የካቲት 2 ቀን 2009 ዓ/ም “አዲስ ተክል” በሚል ርዕስ ቀሲስ የጻፉትን ይመልከቱ፡፡ ‘ቄስ ታደሰ ሲሳይ’ን ዉግዘት በተመለከተ በአባ ፋኑኤል ላይ የተሰጠ መግለጫ በዓለም የሚሰራጭ። ሕዳር 7 ቀን 2007፡፡
2ኛ .አቡነ ኤወስጣቴወስ በነበሩበት ት/ ቤት በብዙ ተማሪወች ፊት በዝሙት ወድቀው April 9, 2013 ከተባረሩ በኋል አቡነ ፋኑኤል ህገ ቤተክርስቲያን የተላለፉትን አቡነ ኤዎስጣቴዎስ በጥፋታቸው እንዲቀጥሉ 2009 በዓለ ጥምቀቱን አብረዋቸው እንዲባርኩና እንዲቀድሱ ፈቀዱላቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ከዚህ በታች የቀረበው ጽfhፍ ተጻፈ (ሙሉውን ጽሁፍ ይህንን ሰንሰለት በመጫን ያንብቡ)።
3ኛ . የፊልደልፍያ ምእመናን ዛሬ ተለያይተው ከሚገኙበት በፊት አብረው ‘በኪዳነ ምሕረትና አማኑኤል’ ስም አንድ ሆነው በሚጽልዩበት ወቅት በመካከላቸው ችግር ተፈጠረ፡፡ ችግሩን ለመፍታት ቄስ አስተራይ የነበሩብት ብዙ ካህናት ተሰብስበው ነበር፡፡ የተሰበሰቡት ካህናት ከዳር ሳያደርሱ ተበተኑና ቄስ አስራይ ብቻቸውን ቀሩ፡፡ ቄስ አስተራይ አዝነውና ተበሳጭተው የሚቀጥለውን ጻፉ፡፡ (ይህንን ሰንሰለት በመጫን ያንብቡ)፡፡
4ኛ . አቡነ ማትያስ በራሳቸው የተቀዳጁት አክሊልና እስከ ጥፍራቸው የተጎናጸፏቸው አልባሳት በደስታ ጊዜ የቤተ ክርስቲአኗን ማለትም የመላ ሕዝበ ክርስቲያን ክብር ሞገስና መንፈሳዊ ልዕልና ለማንጸባረቅ ሲሆን በመከራ ጊዜ በቤተ ክርስቲያኗ (በሕዝበ ክርስቲያን) ላይ የሚደርሰውን መከራ ለመመስከሪያና ለመከላክያ መሳሪያ (ንዋየ ሀቅል) እንዲሆነ ነበር፡፡ አቡነ ማትያስ ግን በተዋህዶ ክርስትና የተጠመቀ ሁሉ አንድ የሆነበትን ሥልጣን ተሸክመው ማዳላት አሳይተዋል፡፡ ወያኔዎች ለነጻነቱ ይታገላቸው የነበረውን ሁሉ ኢትዮጵያዊ በተለይም አማራውን ታራሚ እያሉ በሚደበደቡበት በሚገሉበትና በሚያፈናቅሉበት ጊዜ እሳቸውም ታራሚ እያሉ ተባብረዋል፡፡ በሥጋና በቋንቋ በቀረባቸው በትግርይ ሕብረተ ሰብ ላይ መከራው ጠንከር ሲል ምሬታቸውን ገልጽዋል፡፡ ቀሲስ አስተራየ አድላዊነታቸውን በመገሰጽ “ልፋፈ ጽድቅ” በሚል ርዕስ ሐምሌ 18 ቀን 2013 ፓትራያርኩ የተሸከሟቸው አልባሳትና የተደራረቡ መጥሪወቻቸው ስሞች በመግለጽ የጻፉትን ከዚህ በታች ይመልከቱ፡፡
ሀ)፦በምንኩስናዎ በገዳማት ላሉት መነኮሳት፣አበምኔታቸው ለ)፦የመላ ኢትዮጵያውያን ፓትርያርክ
ሐ)፦ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት (የብጹአን ጳጳሳት መሪ) መ)፦የሲኖዶስ ሊቀመንበር
ሠ)፦የደብረ ሊባኖስ እጨጌ ረ)፦የአኩስም ሊቀ ጳጳሳት
ሰ)፦በአዲስ አበባ ከተማ ላሉት ሁሉ አድባራት ሊቀ ጳጳስ ሙሉውን ጽሁፍ እዚህ ላይ ይገኛል)።
5ኛ . ራሳቸው ቀሲስ በሚገኙበት አገረስብከት በOmha, Nebraska ስላሴ ቤተ ክርስቲያን አስመሳይ መነኩሴ በሕዝበ ክርስቲያን ላይ ችግር ፈጥሮ ሕዝበ ክርስቲያኖችን ማመስ ጀመረ፡፡ በጳጳሱ አቡነ ናትናኤልና በሀገረ ስብከቱ ተስፋ የቆረጡት ክርስቲያኖች ቀሲስ አስተአየን በቀርብ ያውቋቸው ስለነበር በቄሳቸው አንማካይነት ቄስ አስተራየን ጠሯቸው፡፡ ቄስ አስተራየም ጳጳሱንና የሚመለከታቸውን አነጋግረው በቦታው ተገኝተው ችግሩን አጥንተው አቀረቡ፡ የመለኩሴው ኃጢአት እጅግ ገንፍሎ ሕዝቡ እስኪያባርረው ድረስ ጳጳሱም፣ የሀገረ ስብከቱም ጽ/ቤት ጸጥ፣ ዝም ከማለት በቀር ምንም ያሰሙት ድምጽ አልንበረም። ቀሲስ አስተአየ ጽጌ የሚቀጥለውን ትዝብት እንዲህ ሲሉ ለህዝበ ክርስቲያኑና ለተመልካች አቅርበው ነበር፡፡ ቀሲስ አስተርአየ በመጨረሻ የፃፉትን መግለጫ ይህንን ሰንሰለት በመጫን ያንብቡ።
6ኛ . በህዛባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይና በጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ መካከል ጦርነት ተቀስቅሶ በመፎካከር ላይ ሳሉ፡ አባ ሠረቀ የሚባሉት መለኩሴ የትግራይ ካህናትን በመምራት ቤተ ክርስቲያን ከመገንጠል ታግሰው ለሁሉም በሚበጀው ላይ በማተኮር ለትውልድ እንዲያስቡ ቀሲስ አስተራየ ለቆሞስ አባ ሠረቀ ብርሃን የካቲት 12 ቀን 2015: የጻፉላቸውን በተለይ የደመደሙበትን ቅኔ (ይህንን ሰንሰለት በመጫን ያንብቡ)።
7ኛ . የኢትዮጵያ ህዝበ ክርስቲያን ሊፈታው ሊያስወግደው ካቅሙ በላይ የሆነ ችግር ሲደርስበት “ኧረ ቄስ ጥሩ” ይላል፡፡ ይህ አባባል ለብዙ ዘመናት ስለኖረ ባሕል ይመስላል፡፡ በመለመዱ ባህል ይምሰል እንጅ “ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤተ ክርስቲያንን ቀሳውስት ይጥራ”(ያዕ 5፡14) ብሎ ቅዱስ ያዕቆብ ያዘዘው ሐዋርያዊ ትውፊት ነው፡፡ ጥሪውን የሚሰማ ቄስ ባይኖርም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ ትውፊቱን (ልማዱን ) ተከትሎ በገጠመው ዛሬም ቄስ ጥሩ እያለ ነው፡፡ በሕግ ደባ ተስርቶበት ፍርድና ስርአት ተነፍጎት ቄስ ጥሩ እያለ በሚጮኸው ህዝብ ፊት የአምላክን ሕግና ስርአት መነሻና መድረሻነቱን በቃላችን ሳንመሰክር በተግባራችን ስናረጋግጥ የዘንድሮውን የሆሣዕናውን ቅዳሴ መቀደስ ኧረ ቄስ ጥሩ የሚለውን ህዝብን ንቆ መርገጥ በአግዚአብሄር ላይም መሳለቅ መሰለኝ በማለት ለቀሳውስት (መጋቢት 29 ቀን 2015 ዓ/ም ያቀሩቡትን ጽfhፍ ለማንበብ ከፈለጉ እዚህ ላይ ይገኛል)።
ከዚህ በላይ የቀረቡት መዝገቦች ቄሱ እየሞከሩ ሳይሳኩ የቀሩትንና ምክንያቶቻቸውንና ፓትርያክ አቡነ ማትያስ ቀኖናውን ተከትለው የህዝበ ክርስቲያኑን መከራ ባለመስማታቸው መከራው እየከፋ መቀጠሉንና ቄሶችም ችላ በማለታቸው የተባበሩ ይመስላል። ሁላችንም የቀረቡትን መዝገቦች በትኩረት ብናነባቸው በተለይ ቄሶች፣ ቅኔወችን በጥልቀት ብትመረምሯቸው ከቀጣይ ጥፋት ጎዳና የሚያድነን ይመስለኛል።
ቀሲስ አስተርአየ በሶስት አስርት ዓመታት ዉስጥ በጣም ዘለግ ያሉ ጦማሮችን ያካፈሉን ሰለሆነ ወደፊት እነዚህ ጦማሮችን ለአንባብያን በሚጠቅም መልክ ለማቅረብ እንሞክራለን።