ሐሙስ፣ መስከረም ፲ ፭ ቀን ፳ ፻ ፲ ፰ ዓ. ም. (09/25/2025)
አሁን ያለንበትን የአገራችን ሁኔታ፤ ይሄን ለሚያነብ አገር ወዳድ፣ እኔ በዝርዝር ለመግለጥ አልቃጣም። ገሃድ፣ ፍንትው ብሎ የወጣና፣ ገጦ የሚታይ ስለሆነ! እዚህ ላይ ማተኮር የምፈልገው፤ ምን መደረግ አለበት! በሚለው ላይ ነው። ያለንበት ሁኔታ፤ የመዋዠቅ፣ ምን ይከተል ይሆን! ብሎ የመጨነቅና የአገራችንን የወደፊት ዕጣ ባለቤት ሆነን ከመሳተፍ ይልቅ፤ ዝም ብለን የሚከተለውን የምንጠብቅበት ሀቅ ነው። ይህ ሊቀጥል አይችልም። የዚህ ሁኔታ ዕድሜ፤ አጭር ነው። ምን ሊከተል ይችላል! እኛስ ምን እንዲከተል እንፈልጋለን? ሊከተሉ የሚችሉት እውነታዎች ግልጥ ናቸው።
አራት ሊከተሉ የሚችሉ ሁኔታዎች አሉ። ተንባይ ባልሆንም፤ ከኒህ የተለዬ ሳይሆን፣ በነዚህ አራት ሊከተሉ የሚችሉ ሁኔታዎች አካባቢ ወይንም የመሰለ እንጂ፤ ሌላ አይታየኝም። አሁን ያለው የአገሪቱ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሁኔታ ወደ ዝቅጠት እያሽቆለቆለ ነው። እናም ባጭር ጊዜ ይፈነዳል። ታዲያ ምን ይከተላል? የመፈንቅለ መንግሥት ሂደቱ ጨለማ የተላበሰ ነው። የውጪ ኃይሎችም ሆኑ የአገር ለውጥ ፈላጊዎች፤ ወታደራዊ እውቅ መሪ የላቸውም። በዚያ ደረጃ ወታደሩን አሰባስቦ ሊያስከትል የሚችል ቁመና ያለው የለም። እናም ከእነዚህ አራቱ የዘረዘርኳቸው ሁኔታዎች አንዱ ሲከሰት፤ ምን ማድረግ አለብን? ይህን ጠለቅ ብለን ልናስብበት የሚገባ ጉዳይ ነው። እኔም መንደርደሪያ የሚሆን ሃሳብ አቅርቤያለሁና ውይይቶችን እናድርግበት።
ሊከሰት የሚችሉ አራት ሁኔታዎች፤
ሀ) የአብይ አክራሪ ኦሮሞ ገዢ ቡድን በአጥቂነት ይወጣና አዲስ አገር ይፈጥራል።
የአብይ አክራሪ ኦሮሞ ገዢ ቡድን፣ በብልፅግና ስም፣ የዐማራን የህልውና ትግል እና ርዝራዥ የኢትዮጵያዊ ስሜት ያላቸውን ኢትዮጵያዊያን በጣም አዳክሞ፣ ብዙ ዐማሮችን ገድሎ፣ ብዙዎችን አሳድዶ፣ ንብረታቸውን አውድሞ፣ አሁን እየተጠቀመበት ያለውን መንግሥታዊ መዋቅር፤ ሙሉ በሙሉ ከኢትዮጵያዊነት ወደ ኦሮሞነት ለውጦ፤ ለሌሎችም ዐማራ ላልሆኑ ኢትዮጵያዊያን የዐማራን ዕጣ አልብሶ፤ ኦሮሚያ የምትባል አዲስ አገር ይፈጥራል።
ለ) የአክራሪው ኦሮሞ ገዢ ቡድን ከውስጡ ተፈረካክሶ፤ አገር ትበታተናለች።
ባለበት ሁኔታ ብዙ መቆየት የማይችለው የአብይ አክራሪ ኦሮሞ ገዢ ቡድን ከውስጡ ተፈረካክሶ፤ አንዳንዶቹ የየራሳቸውን የታጠቁ አካላት አበጅተው፣ ሌሎች የታጠቁ ክፍሎች በየራሳቸው ጠንክረው፤ አገር የምትፈራርስበትና የተቆራረሱ አገራት ተፈጥረው፤ እርስ በእርሱ የሚፋጁበት እውነታ ይነግሣል።
ሐ) የአገራችን የፖለቲካ ሁኔታ በጣም በመክፋቱ፤ የውጪ ኃይላት እና መንግሥታት ጣልቃ ገብተው አሻንጉሊት መንግሥት ያቋቁማሉ።
የአገራችን የፖለቲካ ሁኔታ በጣም በመክፋቱ፤ የውጪ ኃይላት እና መንግሥታት፤ እጃቸውን በመስደድ፤ የተለያዩ ቢሆኑም፤ “ለኛ ይጠቅሙናል!” የሚሏቸውን ሆድ አደሮችና ሥልጣን የቋመጡ ግለሰቦችን በማሰባሰብ፤ ከውጪም ይሁን ከውስጥ “አገር አድን!” የሚል የመንግሥት መዋቅር አበጅተው፤ አዲስ አበባ ላይ ይተክላሉ።
መ) የዐማራ ህልውና ትግል መሪ ፋኖ፤ ተጠናክሮ ወደ አንድ በመጠቃለል፣ ሌሎችን አስተባብሮ አገሪቷን ያድናታል።
የዐማራ ህልውና ትግል መሪ ፋኖ፤ ተጠናክሮ ወደ አንድ በመጠቃለል፣ ሌሎች ታጋዮችን በማካተት አገር አቀፍ ትግል በማድረግ፤ አገራዊ የሽግግር መንግሥት ይመሠርታሉ።
እንግዲህ እኒህን እያንዳንዳቸውን በተናጠል እንመልከት።
የመጀመሪያው ሁኔታ አሁን ካለንበት ብዙም አይርቅም።
ታጋዮች በመኖራቸው፤ የአብይ አክራሪ ኦሮሞዎች ገዢ ቡድን፣ ያፈተተውን ማድረግ አልቻለም። በዋናነት የሚፈልገው ኢትዮጵያን ኦሮምያ ማድረግ ነው። ይሄን እንዳያደርግ ያገደው በዋናነት የፋኖ ኃይል ነው። በርግጥ ከአክራሪ ኦሮሞዎች የባሱ ኦነግ ሸኔን የመሰሉ ደግሞ፤ አሁኑኑ ዐማራን ጨርሰህ፣ ኦሮምያን ፍጠር ባዮች አሉ። እነሱ ታጥቀው ጦርነት በዐማራው ላይ ከፍተዋል። ከኦሮሞ ምድር ዐማራን ጠራርጎ ለማጥፋት ዓላማቸው ነው። በዐማራ የህልውና ትግል ዙሪያ ባለነው በኛው ድክመት እና በዓለም አቀፍ እርዳታ፤ የአብይ አክራሪ ኦሮሞ ገዢ ቡድን ጥንካሬ አግኝቶ ከወጣ፤ የትም ቦታ ለወደፊቱ ጠላት ይሆኑኛል የሚላቸውን ጨምሮ፤ ዐማራን ያጠፋል። በየተራ ሌሎች ኢትዮጵያዊያንን ያጠፋል። የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ዕሴትና ባህል ይቀይራል። ይህ በጣም አሳሳቢ ጉዳይ ነው። ለዚህ ከፍተኛ ትኩረት ሠጥተን በምንችለው ሁሉ በማድረግ መረባረብ አለብን። ፋኖ ወደ አንድ መሰባሰብ አለበት። የዐማራ የፖለቲካ ድርጅት ቶሎ መፈጠር አለበት። ይህ የፖለቲካ ድርጅት፤ ከወታደራዊ ድሉ ጎን የፖለቲካ ድሎችን ማስመዝገብ አለበት። በመላ ዐማሮች ዘንድ መረቡን ዘርግቶ፤ ቀጥተኛ የትግሉ አካል እንዲሆኑ ማዘጋጀት አለበት። ከሌሎች የኢትዮጵያ ሕዝብ ታጋዮች ጋር የዝምድና ግንኙነቶችን መፍጠር አለበት። በዓለም አቀፍ የፖለቲካ እንቅስቃሴ መሳተፍ አለበት። የዲፕሎማሲና የጥብቅና ሥራዎችን ማፋጠን አለበት። አገራዊ ራዕዩን እና የመንግሥት ሥልጣን ለመረከብ የሚያደርገውን ዝግጅት ማጠናቀቅ አለበት።
ሁለተኛው የአክራሪው ኦሮሞ ገዢ ቡድን ከውስጡ ተፈረካክሶ፤ አገር የመበታተኗ ጉዳይ ነው።
ይሄ ከሌሎቹ የበለጠ የመሆን ዕድል አለው። ይሄን የምልበት ምክንያት፤ አሁን እየሄድንበት ያለው መንገድ፤ ወደዚያ የሚወስድ ስለሆነ ነው። የአገራችን ኢኮኖሚ በጣም ያልተረጋጋና ሥር የሌለው ነው። ረሃቡ፣ ድህነቱና የሥራ አጦች ቁጥር መብዛት ብቻ አይደለም። የመብለጭለጭ ጥረቱ፤ ሥራ ሊፈጥሩና ገቢ ሊያስገኙ የሚችሉ ዝግጅቶችን ይደፍናል። እናም አገራችን አምራች ሳትሆን፤ ተጠቃሚና ሸማች ብቻ እንድትሆን ያደርጋታል። ያ ደግሞ በተራው፤ ገንዘብ ካገር ወደ ውጪ እንዲሄድ እንጂ ወደ አገር እንዳይገባ ያደርጋል። የድህነት ሽክርክሪቱን ተቀማጭ ያደርገዋል። አሁን እየከፋው የሄደው የኅብረተሰብ ክፍል እየጨመረ ነው። ደሞዝ መክፈል የማይችልበት ጊዜ ሩቅ አይደለም። እናም ውስጡ ለራሳቸው የሚሯሯጡ የቢሮ ሠራተኞች ይበዙበታል። ሙስናና አድልዖ ቤታቸውን በአገራችን ከሠሩ ቆይተዋል። በደሃና በሀብታም መካከል ያለው ክፍተት እያሻቀበ ነው። ታዲያ ይሄንን ተሸክመን ብዙ መጓዝ አንችልም። እናም ውጥረቱ አይሎ ይፈነዳል። ያለፈው ምዕተ ዓመት የስድሳ ስድስቱ ክንውን ነገ ይደገማል። በዚያ ጊዜ ሁሉም በሚችለው መንገድ ይሯሯጣል። በሹማምንቶች ዙሪያ፤ የየራሳቸውን ጦር ማግበስበስ ይይዛሉ። ሁሉም የሚያደርገው ለበላይ ለመሆን ሩጫ፤ የአገራችንን የፖለቲካ መድረክ ያጣበዋል። የዚህ ትርፉ፤ የየራሱን የግዛት አካባቢ ማበጀት ይሆናል። ዘመነ መሳፍንት የሚደነቅበት ሁኔታ ይነግሣል። የዩጎዝላቪያና የሶማሊያ ዕጣ የተሻለ ይሆናል።
ሶስተኛው ደግሞ፤ የአገራችን የፖለቲካ ሁኔታ በጣም ክፍቶ፤ የውጪ ኃይላት እና መንግሥታት ጣልቃ ገብተው አሻንጉሊት መንግሥት የሚያቋቁሙበት ሁኔታ ነው።
ኢትዮጵያ ብቻዋን አትኖርም። በአካባቢዋና በዓለም ዙሪያ ካሉ አገራት ጋር ተሳስራ ነው። በመሠረቱ እያንዳንዱ አገር ከሌላ አገር ጋር የሚያደርገው ግንኙነት፤ አገሬ ምን ትጠቀማለች! የሚል ግንዛቤ በጀርባው ሸጎጦ ነው። የኛ አገር ደግሞ፤ ዙሪያዋን የታጠረችው፤ ለራሳቸው ቅድሚያ የሚሠጡ ብቻ ሳይሆን፣ ለኛ በጎ በማይመኙ አገራት ነው። እዚህ ላይ ግብፅን እና የአረብ ሊግን ልብ ይሏል። ምንም አጋጣሚ ሲያገኙ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም እንዳይኖር፤ የተረጋጋ መንግሥት እንዳይመሠረት እና ሁልጊዜ እኛ በነሱ ውሳኔ ሥር እንድንሆን ይጥራሉ። ይህ በጎረቤቶቻችን ብቻ ሳይሆን በሩቅም ባሉ፤ በተለይም ዐማራን እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሒዶ ቤተክርስትያንን ነክሰው በያዙ መንግሥታትም ያለ ነው። ቅኝ ገዢዎች የኛን ነፃነትና ሌሎችን ለነፃነታቸው አበረታታችነት፤ በቁጭት ነው የመዘገቡት። እናም ግብፅን በመርዳትም ሆነ አገር ውስጥ መጠቀሚያ የሚሆኑ ሥልጣን ወዳዶችን በማነሳሳት፤ ማዕከላዊ መንግሥቱን ለማዳከም ጥረታቸውን አባርተው አያውቁም።
እኒህ የውጪ ኃይሎች፤ ከኦሮሞና ከዐማራ የተወሰኑ ግለሰቦችን በመሰብሰብ፤ ፋኖ አዲስ አበባ እንዳይገባ፤ ተሽቀዳድመው የሽግግር መንግሥት ሊመሠርቱ ይችላሉ። ይህ የአሻንጉሊት መንግሥት፤ ዕድሜው አጭር ቢሆንም፤ ጊዜያዊ የሕዝብ ድልን ያዘገያል። የአቀናባሪዎቹ አሽከር የሆነ ገዢ ቡድን ይኖራል። የሕዝቡ የኑሮ ሁኔታ አይቀየርም። እየከፋ ይሄዳል። ከወዲሁ የምንችለውን በማድረግ ያ እንዳይሳካ ማድረግ አለብን።
አራተኛ ሊከሰት የሚችለው ሁኔታ፤ በፋኖ መሪነት አገራችን ሰላም መፈጠሩ ነው።
በዚህና ከሞላ ጎደል ሁላችን እንዲከተል በምንፈልገው ሁኔታ፤ የዐማራ ህልውና ትግል መሪ ፋኖ፤ ተጠናክሮ ወደ አንድ በመጠቃለል፣ ሌሎችን አስተባብሮ አገሪቷን ያድናታል። አሁን በአገራችን ዋና የገዢው ቡድን ተቀናቃኝ ኃይል፤ ፋኖ ነው። ፋኖ የዐማራ ሕዝብ ክንድ ነው። ፋኖ የዐማራ ህልውና ትግልን እየመራ ያለ ኃይል ነው። በዚህም ፋኖ የዐማራ ሕዝብ፤ የዐማራ ሕዝብ ደግሞ ፋኖ ነው። በመካከላቸው ቀዳዳ የለም። ይህ፤ አገራችን እንደ አገር እንድትቀጥል አስተማማኝ መንገድ ነው። የፋኖን ስኬት ከሌሎች የሚለየው፤ ፋኖ ጠቅላላ የዐማራ ሕዝብ እንጂ፤ አንድ በርዕዩተ ዓለም እና በሥልጣን ዓላማ የተዋቀረ ፖለቲካ ድርጅት አለመሆኑ ነው። ስለዚህም፤ ፋኖ አደርጋለሁ ያለውን የሚያደርግ፤ ለርዕዩተ ዓለም ተገዢ ያልሆነ ድርጅት ነው። ፋኖ የዐማራ ሕዝብን ህልውና አንግቦ የተነሳ ሕዝባዊ ተቋም ነው። እናም ለፋኖ፤ ዐማራ ሲል፤ አንድ የኢትዮጵያ ሕዝብ አካል የሆነን ክፍል ማለቱ ነው። እናም ሌሎች የኔ ብለውት፣ አብረው ሊቆሙ የሚችሉበት ተቋም ነው። ነግ ለኔ! ብለው ቀድመው አብረው ሊስለፉ ይገባል። ያ ቁመናው፤ የወደፊቷ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አሠራርን እንድትከተል መሠረት ነው።
ይሄ ሊሆን የሚችለው፤ ዛሬውኑ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን፤ ፋኖ የኔ ነው! ብለው አብረው ሲቆሙ ነው። ኢትዮጵያ ሁላችን በአንድነት የምንኖርባት አገር ናት። አብረን በእኩልነት የምንኖረው፤ አብረን በእኩልነት ታግለን ለድል ስንበቃ ነው። ፋኖ አሁን ወደ አንድ እየተሰባሰበ ነው። ቀጥሎ ሌሎች ከፋኖ ጋር አብረው የሚነሱበት አስፈላጊ ጉዳይ ነው።
እንግዲህ ሊከተሉ የሚችሉ የተለያዩ አራት ሁኔታዎች አሉ። አንዱ ከሌላው የከፋ ወይንም የተሻለ ነው። የምንፈልገው እንዲከተል፤ የትግሉ አካል በመሆን አስተዋፅዖዋችንን ማድረግ አለብን። የሽግግር መንግሥት አቋቁመን፣ አገር እንዲኖረን፣ ሰላም እንዲሰፍን፣ ልማት እንዲከተል፣ አብረን እንድንኖር፤ ዛሬ መተባበር አለብን። መንግሥትን መመሥረት፤ ዋናው የአገር ጉዳይ ነውና!