አንዱ ዓለም ተፈራ
ቅዳሜ፣ መስከረም ፲ ቀን ፳ ፻ ፲ ፰ ዓ. ም. (09/20/2025)
አንዱ ዓለም ተፈራለአቶ ባይሳ ዋቅ-ወያ፤ “ጋኖች አለቁና ……….. ” ጽሑፍ ምላሽ
በዚህ በዘሐበሻ ድረገጽ ላይ የአቶ ባይሳ ዋቅ-ወያን ጽሁፍ ሳነብ፤ ሁለት የተለያዩ ጽሑፎችን የማነብ መሰለኝ። የመጀመሪያው ክፍል ትንተናዎቹ ማስረጃ እየቀረበላቸው፣ ፈሰሳቸው የሚያጓጓ ሆኖ ሳበኝና ተከተልኩት። ግማሹ ላይ ስደርስ፤ የዚያ ሁሉ ገለጣ እውነተኛ ዓላማ በትክክል ታውጆ፤ “አለሁ!” አለኝ። ታዲያ ያ ሁሉ የመጀመሪያው ድርደራ ለካ፤ ዶክተር ኃይሌ ላሬቦን ለመኮነን ሳይሆን፤ በሥልጣን ላይ ያለውን ገዢ ቡድን ሕጋዊነት ለመሥጠትና የሚኮሩበትን “ሕግ-መንግሥት” ጣዖት አድርጎ ለማምለክ እንደሆነ ተረዳሁ። እኔ የዶክተር ኃይሌ ላሬቦ ጠበቃ አይደለሁም። ያቀረቡትንም አልጋራቸውም። የኔ ፍላጎት፤ እንደ አቶ ባይሳ ዋቅ-ወያ፤ ዶክተር ኃይሌ ላሬቦ አይደሉም። ላስረዳ!
የዚያ የስድሳዎቹ ትውልድ ጉዳይ፤ ዛሬም፣ ለወደፊትም የሚጠናና የሚያነጋግረን ነው። እኔ ስለነበርኩበት፤ በዚያ ዙሪያ የሚደረጉ ውይይቶችን ለመካፈልና የሚጻፉትን ለመከታተል ሁሌም እጓጓለሁ። የአቶ ባይሳ ዋቅ-ወያንም ጽሑፍ ያነበብኩት ከዚህ ፍላጎቴ ተነስቼ ነበር። አንዳንድ ወዳጆቼም፤ ደጋግመው ሃሳቤን ስለጠየቁኝ፤ እስኪ ረጋ ብዬ ላንብበው! አልኳቸውና በትኩረት አነበብኩት። ለነሱም፣ እዚሁ ላይ መልሴን እንዲያገኙት እጠቁማቸዋለሁ።
መቼም ብዙ ጎኖች ያሉት ጉዳይ ሲነሳ፤ ረዘም ያለ ጽሑፍ መከተሉ ግዴታ ነው። የሚነሱ ነጥቦች ብዙ ከመሆናቸው ሌላ፤ አንድምታቸው የተለያዩ ጉዳዮችን ስለሚነካ፤ ማብራሪያ መሥጠቱ አሌ የማይባልና የግድ መታለፍ ያለበት በር ነው። ለማሳጠር እሞክራለሁ። እዚህ የማቀርበው፤ የስድሳዎቹ ተማሪዎች ስላደረግነው ወይንም ስለ እንቅስቃሴያችን ትክክለኝነት አይደለም። ሆኖም ግን እንቅስቃሴያችንን አሁን ካለው የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር፤ አቶ ባይሳ ዋቅ-ወያ ሊያስተሳስሩ የሞከሩበት ሐረግ የሌለ መሆኑን አሳያለሁ። ሊያስተሳስሩ የሞከሩበት ሐረግ አልበቀለምና። መቼም የፈለጉትን የፖለቲካ ዓላማ ሕጋዊነት ለማስገኘት፤ ምሁራን ወይንም በዚህ ጽሑፍ ባለቤት እንደታየው ሹም፤ የማይሻገሩት ወንዝ የለም። እሾሁን አበባ ብሎ ማቅረብ፤ አበባውን አስፈሪ መልክ መሥጠታቸው የታወቀ ነው። እናም አቶ ባይሳ ዋቅ-ወያ ያደረጉት ይሄንኑ ነው። ራሱን ችሎ ሕገ-መንግሥቱ አስፈላጊ ነው፣ ትክክለኛ ነው፣ እንከን አይወጣለትም ማለትና ያንን ማቅረብ ሲችሉ፤ መግቢያ ሽፋን ፈለጉ። የምሁር ደካማነት ማለት ይሄ ነው። ዶክተር ኃይሌ ላሬቦ የተሾነቀሩት፤ ለዚሁ ዓላማ ሲባል ነው።
እስኪ ስለ “ሕገ-መንግሥታቸው” የሚሉትን እናንብብ። በመጀመሪያ በትክክል ያስቀመጡትን ላስቀድም፤ “የሕገ መንግሥቱን ቀረጻና ማጽደቅ ሂደትን የመራው የኢሕአዴግ መንግሥት ራሱ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ያልተመረጠና ማንንም የማይወክል ስለሆነ፣ ሕገ መንግሥቱን ለማርቀቅና ለማስጸደቅ የመለመላቸው ግለ ሰቦች በሕዝብ የተመረጡ መሆን ነበረባቸው ብሎ መከራከር ደግሞ ከእባብ ዕንቁላል እርግብ የመጠበቅ ያህል ነው።” ምነው ታዲያ በነካ እጅዎ፤ ከዚህ ገዢ ቡድንም ትክክለኛ ሕገ-መንግሥት መጠበቅ ከእባብ ዕንቁላል እርግብ መጠበቅ ነው! የሚለውን አብረው አላከሉበትም! ልቀጥል፤
በሳቸው ግንዛቤ፤ “. . . በአንዳንድ ክልሎች እየተከሰተ ያለው ማንነትን መሠረት ያደረገ የእርስ በርስ ግጭትና ብሎም መገዳደል፣ ምክንያቱ የፌዴራል አወቃቀሩ በክልል መደረጉ ሳይሆን፣ የሕገ መንግሥቱ ቃልና መንፈስ በትክክል ሥራ ላይ ባለመዋሉ ነው።” አቶ ባይሳ ዋቅ-ወያ! ይሄን ዘፈን ከዚህ ቀደም ሌሎች አዚመውታል። አሁንም እርስዎ እያሉን ያሉት፤ ሕገ-መንግሥቱ ትክክል ሆኖ፤ በበቂ ግን አልተተገበረም! ነው። እስከ ሕጉ ጥግ ድረስ አልሄድንም! ነው። እሺ! ይቀጥሉ!
“የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 32(1) በቀላል አማርኛ፣ የክልሉ ተወላጅ ብሔሮች የክልሉ የፖሊቲካ ሥልጣን ባለቤት ናቸው ይላል እንጂ የክልሉ ባላቤት ናቸው አይልም።” (አንድ) ቆይ! እንዴት ነው የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤት የሆነ፤ የክልሉ ባለቤት ያልሆነው?
“የሕገ–መንግሥቱ አንቀጽ 32(1) በግልጽ ያስቀመጠው እንኳን ኢትዮጵያዊ ዜጋ ይቅርና የውጭ አገር ዜጎች እንኳ ሳይቀሩ በማንኛውም የኢትዮጵያ ክልል ውስጥ ሊኖሩ እንደሚችሉ ሲያረጋግጥ፣ ‘ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወይም በሕጋዊ መንገድ በሃገሪቱ ውስጥ የሚገኝ የውጪ ዜጋ በመረጠው የሃገርቱ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖርያ ቤት የመመሥረት ነጻነት አለው’ ብሎ ይደነግጋል።” (ሁለት) ከኛ ክልል ውጣ! ተብሎ የተፈናቀለና የተገደለ ዐማራ፤ ይሄንን አላነበበም! ወይንም ኢትዮጵያዊ አይደለም፣ በሕጋዊ መንገድም በአገሪቱ አይገኝም! አሁን ገባኝ!!! እሺ ይቀጥሉ!
“የኦሮምያ ክልላዊ ሕገ መንግሥት 34(1) ለምሳሌ፣ ‘ኢትዮጵያውያን የሆኑ የሌሎች ክልሎች ተወላጆች በዚህ ክልል ውስጥ እንደ ማንኛውም የዚህ ክልል ተወላጅ ሠርቶ የመኖር፣ ከሥፍራ ሥፍራ በነጻ የመዘዋወር፣ ሃብትና ንብረት የማትረፍና የመያዝ መብት አላቸው ይልና፣. . .” (ሶስት) ዐማራ ኢትዮጵያዊ ስላልሆነ ነው ንብረቱ የተዘረፈበት፣ የተገደለበት፣ የተሰደደበት! አላወቅሁም!!!
“የኦሮምያ ክልላዊ ሕገ መንግሥት 34(1) ለምሳሌ፣ ‘ኢትዮጵያውያን የሆኑ የሌሎች ክልሎች ተወላጆች በዚህ ክልል ውስጥ እንደ ማንኛውም የዚህ ክልል ተወላጅ ሠርቶ የመኖር፣ ከሥፍራ ሥፍራ በነጻ የመዘዋወር፣ ሃብትና ንብረት የማትረፍና የመያዝ መብት አላቸው’ ይልና፣ . . .” (አራት) ይሄንን አልተገብርም ያለው ሺመልስ አብዲሳ ነዋ!
“በአንቀጽ 34(2) ሥር ደግሞ፤ ‘የክልሉን የሥራ ቋንቋ የሚያውቅ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ (የክልሉ ብሔር ተወላጅ ያልሆነ ማለት ነው) በማንኛውም የክልሉ መንግሥታዊ ሥራ ውስጥ ተመርጦ ወይም ተመድቦ የመሥራት መብት አለው’ ብሎ ይደነግጋል።” (አምስት) እንዴት ያለ ዕዳ ገባሁ! ላምን የሚገባኝ፤ አቶ ባይሳ ዋቅ-ወያን ነው ወይንስ በተጨባጭ ያለውን ሀቅ!
እንግዲህ፤ በኢትዮጵያ የሚኖር አንድ የገዢው ቡድን አባልና ባለሥልጣን ያልሆነ ኢትዮጵያዊ፤ ከእንቅልፉ ሊነቃ ይገባዋል። አቶ ባይሳ ዋቅ-ወያ የሚገልጧት አገርና ሌሎቻን እያየናት ያለችው ኢትዮጵያ አንድ ሊሆኑ አይችሉም። እስኪ ይቀጥሉ፤
“ለምሳሌ፣ የኦሮሞ ቄሮዎች አንድም ጥይት ሳይተኩሱ የተሰካ ሰላማዊ ትግል አካሄደው ሕወሃት ወራሹን መንግሥት ሲገረስሡ ‘ሕገ መንግሥታዊ መብታችን ይጠበቅ” “የኦሮሞ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በተመረጡ ሕጋዊ ተውካዮቹ ይተዳደር’ ነበር እንጂ ያሉት፣ በትግሉ ሂደት ውስጥ 5000 ወጣቶች ተሠውተባቸውም፣ አንድም ቦታ ላይ የመገንጠል ጥያቄ ኣላነሱም። ዛሬም የትጥቅ ትግል እያካሄደ ያለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፣ በፌዴራል ኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ማዕቀፍ ውስጥ ለድርድር ሲቀመጥ፣ ዓላማው ሕገ መንግሥታዊ መብትን ለማስከበር እንጂ ለመገንጠል አይደለም። ኦነግም ከ1991 ወዲህ አንድም ጊዜ የመገንጠል ጥያቄ አላነሳም፣ በሕገ መንግሥቱም መሠረት በምርጫ ቦርድ ተመዝግቦና ሕጋዊ ሰውነት አግኝቶ ዛሬም በሰላማዊ መንገድ እየታገለ ይገኛል።”
ይቺን ሰፋ አድርገን እናጢናት። በመጀመሪያ፤ ሕወሓት መራሹን መንግሥት “እኛ ቄሮውች፣ እኛ ዖሮሞዎች ጣልነው!” ይሉናል! ምነው! ምነው! ሌሎች አልታገሉም ለማለት ነው! ጎንደር ከተማ፤ “የኦሮሞዎች ደም የኛ ደም ነው!” ያሉት ወጣቶች አይፋረዱዎትም። የመጀመሪያዋ ጥይት የተተኮሰችው ኮሎኔል ደመቀን ከከበባ ለማውጣት ከላይ እስከታች ታጥቆ የተነቃነቀው የጎንደር አርበኛ ብን ብሎ ይጠፋል! ብለው ያስባሉ!
“ቄሮዎቹ በሰላማዊ መንገድ ሲታገሉ 5000 ወጣቶች አልቀውብናል!” ይሉናል። አዎ! በአፄ ሚኒሊክ ዘመን ከነበሩት የኦሮሞ ተወላጆች ቁጥር አስር እጥፍ ተገድሎብናል! ብለው ዘመዶችዎ አቅርበዋል!!!
“አዲስ አበባ እንዳይገባ ተብሎ የተከለከለው ዐማራ፤ ኢትዮጵያዊ ወይንም በሕጋዊ መንገድ በኢትዮጵያ የሚገኝ አይደለም! እናም መከልከሉ ከዚህ የመነጨ ነው!፡ ይሄን እያሉን ነው ሹም ባይሳ ዋቅ-ወያ?
ቀጥለው፤ እያንዳንዱ የኦሮሞ ድርጅት፤ “የመገንጠል ጥያቄ አላነሳም!” ይሉናል። ታጥቆና ራሱን “የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር!” ብሎ የሰየመው ድርጅት፤ በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ለመኖር ይፈልጋል! ይሉናል። የስሙን ትርጉም ነው ያጡት ወይንስ የኛን የማንበብና የመረዳት እውቀት እየናቁ ነው! ይቀጥሉ፤
“ሕወሓትም ወደ ነበርኩበት የፖሊቲካ ሥልጣን ከፍታ ልመለስ ብሎ ከመንግሥት ጋር ተጋጨ እንጂ የመገንጠልን ጥያቄ አላነሳም።” አቶ ባይሳ ዋቅ-ወያ፤ ሕወሓት ስሙ፤ ለኔ ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ፤ ወይንም በትክክል ስተረጉመው፤ የትግራይ ነፃ አውጪ ሕዝባዊ አመፀኛ፤ ወይንም የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጪ ሲሆን፤ ነፃ የሚወጣው ከኢትዮጵያ ከሆነ፤ እንዴት አድርገው ነው የመገንጠል ጥያቄ አላነሳም የሚሉን!!!
“መ) ሕገ መንግሥቱ፣ ከጥንስሱ ጀምሮ በአንድ ሕዝብ ላይ ያነጣጠረና ያንን ሕዝብ ለመጉዳት ታስቦ የተዘጋጀና ሂደቱ ሁሉንም አካታች ስላልሆነ፣ መፍረስ አለበት የሚሉ ወገኖች አሉ። በዚህ ጉዳይ ላይ፣ ከጥቂት መኃይም ኤሊቶች፣ ከዩቲዩብና ቲክቶክ ፖሊቲከኞች አደዳቢ ክርክርና ጽሁፍ ሌላ ሕገ መንግሥቱ በአንድ ብሔር ላይ ያነጣጠረ ለመሆኑ አንዳችም ማረጋገጫ የለም።”
አሁን እርስዎ ከእንቅልፍዎ ይንቁ! ሌላ ምንም አልልም። የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ዓላማው፤ “በዐማራ መቃብር ላይ የትግራይን ሪፑብሊክ እመሠርታለሁ!” ብሎ ነው።
አሁን ያለንበት ተጨባጭ እውነታ የሚነግረን፤ የዚሁ ሁሉ ባለቤት ገዢው፣ በአገራችን የተቀመጠውና እርስዎ በሰፊው የሄዱበትን “ሕገ-መንግሥት” ነው። ጥሩ ስም በመሥጠት መልከ ጥፉን ማሳመር አይቻልም።
ሲያጠቃለሉና ማስሪያ ሲያበጁ፤ መቼም ሁሉ ነገር ሰላም ነው! ብለው መዘመር አይደል የያዙት፤ ለዶክተር ኃይሌ ላሬቦ፤ እውነቱን ከሆነ ደግሞ ለሁላችን፤ እንዲህ ይሉናል፤ “መቃወም ወይም መደገፍ ያለበት፣ ያኔ ማኅበረ ሰባዊ ጥያቄው ለውይይት በቀረበበት ጊዜ፣ ቦታና ሁኔታ ነው እንጂ፣ የማኅበረ ሰቡ ጉዳይ የሆነ መፍትሔ ከተገኘለት ከአምሳ ዓመት በኋላ፣ ወደ ኋላ ተመልሶ፣ ለችግሩ መፍትሔ ፍለጋ ሲዋትቱ የነበሩበትን ማኅበረ ሰባዊ ለውጥ ፈላጊዎችንና የመፍትሔ ሃሳባቸውን ዛሬ ላይ ሆኖ መንቀፍ የምሑር አድር ባይነትን ጎልቶ የሚያሳይ ስለሆነ፣ ዶ/ር ኃይሌን ክፉኛ እወቅሳቸዋለሁ።”
እዚህ ላይ አንድ ነገር ልበል፤ እርስዎ እንደሚሉት፤ ሁሉ ነገር መፍትሔ ያገኘው ከሃምሳ ዓመታት በፊት ከሆነ፤ አሁን ያለንበትን እርስዎ አያውቁም! ብዬ ልመን? ወይንስ “የሚባለውን ሁሉ አትመኑ፤ እኛ ሁሉን ካስተካከልነው ሃምሳ ዓመታት አልፏል!” የሚለውን የርስዎን ገለጣ እንቀበል! እውነት የምሑር አድርባይነትን እርስዎስ ያውቃሉ! ወቃሽስ መሆን ይችላሉ!
መቼ በቀላሉ የሚለቁ ሆነና! አስከትለው፤
“እርስዎ የማኅበረሰቡን ፖሊቲካዊ፣ ኤኮኖሚያዊና ማኅበረ ሰባዊ ቀውሶችን ይፈታሉ ተብለው የሚቀርቡ ሃሳቦችን መቃወምም ሆነ መደገፍ የሚያምረው ያኔ ጥያቄዎቹ አስፈላጊ በሆኑበት ወቅትና ቦታ መሆኑን እያወቁ፣ ጥያቄውም መፍትሔ አግኝቶ የጥያቄው አራማጆችም በአካል ከዚህ ምድር ከተለዩ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በኋላ . . . ” ብለዋል። ይገርማል! ኧረ እባክዎ አሁን ጦርነት ላይ ነን። ለአገራችን ጉዳይ መፍትሔ መቼ ቀረበለትና!!!