መግቢያ
ማኅበረ ሰቦች በተለያየ ፍጥነት ይሁን እንጂ ማደጋቸው አይቀሬ ነው። ብዙዉን ጊዜ ለማኅበረ ሰባዊ ለውጡ ብሎም ለዕድገቱ ፋና ወጊዎቹ በተፈጥሮም ይሁን በሌላ ምክንያት ከመደበኛው ሕዝብ በበለጠ የአንድን ማኅበረ ሰብ ነባራዊ ፖሊቲካዊ፣ ማኅበረ ሰባዊና ኤኮኖሚያዊ ሁኔታዎችን አስቀድመው ተረድተው፣ ማሕበረሰቡን ከፍ ወዳለ ደረጃ ያደርሳል ብለው የዕድገት ጉዞውን የሚመሩት በተፈጥሮ ዕውቀት ወይም በትምህርት የላቁ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ናቸው። ማኅበረ ሰብ የግለ ሰቦች ስብስብ ነው። ግለሰቦች ደግሞ የተለያየ ጭንቅላት ያላቸውን ያሕል የተለያየ አስተሳሰብ ስለሚያስተናግዱ፣ ለማኅበረ ሰቡ ዕድገት ይበጃል ብለው በቀየሷቸው አቅጣጫዎቻቸው መሠረት የተለያዩ የዕድገት ፍኖተ ካርታዎችን ይቀይሳሉ። ይህ የተለያየ ፍኖተ ካርታ ነው እንግዲህ በግለ ሰቦች መካከል አንዳንዴ ከሃሳብ ግጭት አልፎ በጉልበት አለመግባባትን ለመፍታት ነፍስን ወደሚያጠፋፋው የርስ በርስ ግጭት የሚያደርሰው። በአጭሩ አነጋገር፣ ለአንድ ማኅበረ ሰብ ዕድገት አንድ ወጥ የሆነ የማኅበረ ሰብ ዕድገት ፍኖተ ካርታ የለም ማለት ነው። የስድሳዎቹ ኢትዮጵያውያን “የያኔው ትውልድ” አባላትም የዚሁ ተፈጥሮያዊ ሂደት አስፈጻሚም ሰለባም ነበሩ። ለኢትዮጵያ የነበራቸው የዕድገት ፍኖተ ካርታ በስትራቴጂም ባይሆን በታክቲክ የተለያየ ሆኖ እስከ መገዳደልም አድርሷቸዋል። የደርግ ምህረት የለሽ ጎራዴም ተጨምሮበት ያ ምርጥ ትውልድ ለወሬ ነጋሪ እንኳ እንዳይቀር ተደርጎ እንደ ቅጠል ረገፈ።
ይህ ጽሁፌ ዶ/ር ኃይሌ ላሬቦ በቅርቡ የኢሕአፓንና የመሬት ለአራሹን አምሳኛ ዓመት መታሰቢያን አስመልክተው ለታተሙ የተለያዩ ጽሁፎች መልስ እንዲሆን ከማለት ላሳተሟቸው ሁለት የ “ውግዝ” መጣጥፎች የራሴን አስተያየት ለመሠንዘርና በሂደትም “የዚያን ትውልድ” የፖሊቲካ እንቅስቃሴና የትግል ዓላማቸውን ለወጣቱ ትውልድ ዕውነተኛውን ገጽታ ለማሳየት ነው። በግሌ እንደ እሳቸው የዚያ ትውልድ አባል ባልሆንም፣ ትውልዱ ሲያስተናግድ የነበረውን ተራማጅ አስተሳሰብ ግን ባአንዳንድ የታክቲክ ጥያቄዎች ላይ ባልስማማባቸውም፣ ስትራቴጂያቸውን በተመለከተ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አምኜበት፣ ለማሕበረ ሰባዊ ዕድገትና አስተዳደር የራሴ የሕይወት መመርያ አድርጌ እጠቀምበት ስለነበርና ዛሬም በሙሉ ልቤ ስለማምንበት፣ ዶ/ር ኃይሌ፣ የአንድ ትውልድ ቁንጮ እንደ ዋዛ ከረገፈ ከአምሳ ዓመት በኋላ፣ ዛሬ ላይ ሆነው ድፍረት በተሞላበት አኳኋን ትውልዱን መንቀፋቸው እንደ ግል ጉዳይ አሳስቦኝ ተገቢውን መልስ ለመስጠት ብዕሬን አሾልኩ። እነኝያ ከኢትዮጵያም አልፈው ለዓለም ወዛደሮችና አርሶ አደሮች ጥቅም ሲሉ ራሳቸውንና ሕዝቡን አደራጅተው ሰፊውን ሕዝብ ከመደብና ከብሔር ጭቆና እንገላግለዋለን ብለው በረጅሙ ያልሙ የነበሩትን የቆራጥ ትውልድ አባላት፣ ዛሬ ስማቸው በአንድ አልባሌ አድር ባይ ምሑር ሲረክስ አይቼ ዝም ከምል ብዬ ለማያውቁኝና ለማላውቃቸው፣ ግን ደግሞ ሲያራምዱ የነበሩትን የትግል ዓላማ ሙሉ በሙሉ እጋራቸው ለነበረ የያኔው ትውልድ አባላት ዋቢ ለመቆም ከማለት ይህንን መጣጥፍ ለመጻፍ ተነሳሳሁ። እግረ መንገዴን ደግሞ እንደ ዶ/ር ኃይሌ የያኔውን ትውልድ የትግል ዓላማ አውቀውም ሆነ ሳያውቁ ለሚወቅሷቸው ግለሰቦችና ቡድኖች የትውልዱን ዓላማና ግብ በትክክል ለማቅረብና ለታሪክም ቢሆን እውነተኛው የያኔው ትውልድ የትግል ዓላማን መልዕክት ለማስተላለፍ አስቤ ነው።
ጽሁፌ በዶ/ር ኃይሌ ሁለት መጣጥፎች ላይ የሚያተኩር ቢሆንም፣ እግረ መንገዴንም ደግሞ የሃሳብ ተጋሪዎቻቸው ሁሌም የሚያነሷቸውን ተጓዳኝና ለዛሬው አገራዊ ቀውስ ምክንያቶች ናቸው በሚሏቸው፣ ጉዳዮች ለምሳሌ፣ ሕገ መንግሥቱን አስመልክቼ አንዳንድ አስተያየት ለመሠንዘር እሻለሁ። የመሬት ላራሹን ጥያቄን በተመለከተ በወቅቱ የነበሩ ታዋቂ ኢትዮጵያውያን በቂ ጥናትና ትንተና አድርገውበት በተግባር የተረጎሙት ስለ ሆነና ከመሬት ጋር ተያይዞ የነበረው የገባር ሥርዓት ላንዴና ለመጨረሻ ስለ ተገረስስ በሱ ላይ አንዳች አስተያየት መሠንዘር የራሴንና የአንባቢያንን ጊዜ ማባከን ስለሚሆንብኝ ትቼዋለሁ። የመሬት ለአራሹ ዓዋጅ ስኬት ያሳየ የክፍለ ዘመኑ ሥር ነቀል ዓዋጅ ነው ብዬ ከማምንባቸው ምክንያቶች አንዱ ቀደም ሲል በተለያዩ ጊዜያት በታወጁ ዓዋጆች እንዲጠፋ ታስቦ ያልተሰካው የባርነት ሥርዓት ለአንዴና ለመጨረሻ ከኢትዮጵያ ምድር ማጥፋቱን ነው። በዚህ ዓዋጅ ምክንያት ያኔ “ባሮች” ወይም “ሻንቅሎች” ይባሉ የነበሩ የኒሎቲክና የኦሞቲክ ሕዝቦቻችን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ ከሌሎች የኢትዮጵያ ኩሽ ሕዝቦች እኩል መሬትን ለመጠቀም ችለዋል። አዎ! የመሬት ዓዋጁ የያኔው ትውልድ እንደተመኙት አርሶ አደሩን የመሬት ባለቤት ለማድረግ ባይችልም፣ የገባርነት ሥርዓት መጥፋት በራሱ እጅግ በጣም ትልቅ ለውጥ ስለሆነ፣ ይህንን ታሪካዊ ዓዋጅ አለማድነቅ፣ ሰዋዊ አለ መሆን ይመስለኛል። ዶ/ር ኃይሌን የምሞግታቸው ከዚያ በመነሳት ነው።
ማንም ግለ ሰብ የግሉ የሆነ ሃሳብ ወይም አስተሳሰብ አለው። አስተሳሰብን ያለ አንዳች ገደብ በማንኛውም ቦታና ወቅት በነጻነት የማሰማት መብት ደግሞ “ተፈጥሮያዊ” ተብለው በዓለም ዓቀፍ ሕግ ሳይቀር ከተደነገጉት ጥቂት ሰብዓዊ መብቶች አንዱ ነው። ቮልቴር “ሃሳብህን ልቃወም እችላለሁ፣ ግን ደግሞ በነጻና ያለ አንዳች ገደብ እንድትገልጸው በቁርጠኝነት እሟገትልሃለሁ” ያለው ይህ ተፈጥሮያዊ/ሰብዓዊ መብት ምንኛ አስፈላጊ እንደ ሆነ ለሰው ልጆች ለማስረዳት ነበር። በግሌ፣ ዶ/ር ኃይሌ ሃሳባቸውን በነጻነትና ያለ አንዳች ገደብ በጽሁፍም ሆነ በቃል በተመቻቸው መንገድ ለሕዝብ የማጋራት መብታቸውን እያከበርኩ በቁርጠኝነት እሟገትላቸዋለሁ። የዚያኑ ያህል ደግሞ፣ ሃሳባቸውን በሙሉ ልቤ የመቃወምና የመተቸት ያልተገደበ መብት አለኝ። ተቃውሞዬና ትችቴ እሳቸውን በግል ሳይሆን፣ ሃሳባቸውን ብቻ እስከ ሆነ ድረስ!
አንዳንድ የኢትዮጵያ ፖሊቲከኞች እና ፖሊቲከኞች ነን ባዮች፣ ይህ በስድሳዎቹ ትውልድ የተቀየሰው የእድገትና ዲሞክራሲ ጎዳና የከሸፈ ስለሆነ ዛሬ ላይ ስለ እሱ መወያየት ምን ፋይዳ አለው ሲሉ ይስተዋላሉ። አግባብ ያለው አስተያየት ነው። በኔ ግምት ግን፣ አንድ ሕዝብ ያለፈውን ታሪኩን ማወቁ፣ የመጀመርያ ሙከራው የከሸበትን ምክንያት ጠንቅቆ መረዳት ለወደፊት ለሚቀይሰው የዕድገት፣ የፍትሕና የዲሞክራሲ ፍኖተ ካርታ ያንን የውድቀት መንገድ ዳግመኛ እንዳይሄድበት ይረዳል ባይ ነኝ። የያኔው ትውልድ የሄደበትን የስሕተት ጎዳና መልሰን እንዳንሄድበት ለማለት ነው። የታሪክ ዋነኛ ፋይዳም ይኸው ነው። የያኔው
ትውልድ አባላት፣ ፈረንጆች ምርጥ ትውልድ (crème of the society) የሚሏቸው ዓይነት ሆነው እያለ፣ በአገራችን የፖሊቲካ ባሕል ካለ መዳበሩ የተነሳ ልዩነቶቻቸውን አቻችለው ለትልቁ አገራዊ ዓላማ አብረው ከመጓዝ ይልቅ፣ በጥቃቅን የስትራቴጂ ልዩነቶች ምክንያት እርስ በርስ ሲገዳደሉ ደርግም ተጨምሮበት ሁለቱንም ወገን ጨፍጭፎ አገሪቷን የአንድ ትውልድ ምሑር አልባ ምድር አደረጋት። በዚህም ምክንያት፣ የትውልዱን ዓላማ በትክክል ለሚቀጥለው ትውልድ የሚያካፍል ቡድን በመጥፋቱ ዛሬ ይኸው እንደ ዶ/ር ኃይሌ ዓይነት አድርባዮች ሜዳውን ለብቻ አግኝተውት ያንን ትውልድ በተሳሳተ ትርክት ሲኮንኑና አዲሱን ትውልድ ደግሞ በዚያው ልክ በተንሸዋረረ ትርክት ሲያወናበዱ ይስተዋላሉ።
ሁለቱ የዶ/ር ኃይሌ ጽሁፎች በጣም አጫጭር ግን ደግሞ እጅግ በጣም መርዘኞችና፣ ሆን ተብሎ ወጣቱን ትውልድ ለማደናገር ታስበው የታተሙ ይመስለኛል። እንዲህ ይላሉ ዶክተሩ፣
““የዛሬ ዐምሳ ዓመት በደርግ መንግሥት የተካሄደው የመሬት ዐዋጅ እንደ ታላቅ ቅጅት ሁኖ ሲታይ በጣም ገረመኝ፣ አስደነቀኝም። በኔ ዕይታ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እንኳን ኢዮቤልዩአቸውን ማክበር ይቅርና ርኩስ እንደአርዮስ ተብለው መወገዝ ያለባቸው ክሥተቶች ቢኖሩ፣ አንደኛው የዋለልኝ የብሔር ብሔረሰቦች ንግግር፣ ሁለተኛ ደግሞ የ “መሬት ላራሹ ዐዋጅ ናቸው” ይሉናል በአንደኛው መጣጥፋቸው ላይ። ጽሁፎቹ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚጎዳኙ ነጥቦችን ያወሳሉ። እስቲ ነጣጥለን እንመርምራቸው።
- ዋለልኝ ስለ ኢትዮጵያ ብሔር/ብሔረ ሰቦች ግንኙነት የሠነዘራቸው አስተያየቶች፣
ዋለልኝ ጽሁፉን በአደባባይ ለአዲስ አበባ ዩኒቬርሲቲ ተማሪዎች ባቀረበበት ዘመንም ሆነ ዛሬ፣ አገራችን ከሰማኒያ በላይ የተለያዩ የየራሳቸውን ቋንቋና ባሕል ያላቸውን ብሔር/ብሄረሰቦችን በአንድ ባንዲራ ሥር አሰባስባ የምታኖር ብሔረ-አገር ናት። በሌሎች የተለያዩ ሕዝቦች ይኖሩባቸው እንደ ነበሩ አገራት ለምሳሌ እንደ ጣሊያን፣ ፈረንሳይ ወይም ስዊዘርላንድ የተከሰተው የሕዝቦች አንዳቸው በአንዳቸው ውስጥ ቀልጠው አንድ ሕዝብ፣ አንድ ቋንቋና አንድ አገረ-ብሔር ለመመሥረት እንደ ተሳካላቸው፣ ሳያድለን ቀርቶ በአገራችን ለዘመናት በሰፈነው የፊውዳሉ ሥርዓታችን ምክንያት፣ አንድም አናሳ የኢትዮጵያ ብሔረ ሰብ በሌላው ኃይለኛ ብሔር ወይም ብሔረ ሰብ አልተዋጠም። ሰማኒያዎቹም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዛሬም ቋንቋቸውንና ባሕላቸውን እንዳለ ጠብቀው አንዳቸው ከአንዳቸው ጋር ሳይዋሃዱ ውሃና ዘይት ሆነው ጎን ለጎን እየኖሩ ነው። ዋለልኝ ጽሁፉን በአደባባይ ለዩኒቬርሲቲ ተማሪዎች ባቀረበበት ወቅት በቁጥር የአገሪቱ አብላጫ የሆኑት ሶስቱ የኢትዮጵያ የኩሽ ነገዶች የሆኑትና አገሪቷን በፈረቃ ሲገዟት የነበሩ የአማራ፣ የኦሮሞና የትግራይ ብሔሮች፣ ሌሎች ኒሎቲክ ወይም ባንቱ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን “ሻንቅላ” ወይም “ባርያ” እያሉ እንደ ዕቃ ሲገዟቸውና ሲለውጧቸው እንደ ነበር ታሪክ ብቻ ሳይሆን እኛም ሕያው ምሥክር ነን። ዶ/ር ኃይሌም የደቡብ ብሔር ተወላጅ እንደ መሆናቸው መጠን በልጅነት ዕድሜያቸው ይህንን አስጸያፊ የአገራችንን ታሪክ ዕውኔታ በኖሩበት አካባቢ ሲያዩ እንዳደጉ እገምታለሁ።
ለዘመናት ሰፍኖ የነበረው የባርያ ንግዱም በሕግ ታግዶ የሰውን ልጅ እንደ ዕቃ መሸጥና መለወጥ ከቆመበት ከብዙ አሥርተ ዓመታት በኋላ ዛሬም በኩሽና በሌሎቹ የኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል ያለው እኩልነት በሕገ መንግሥት ከመካተቱ ባሻገር ዕውን ሆኖ ሲተገበር አይታይም። አፋችንን ሞልተን መናገር ይከብደናል እንጂ፣ “ተጋብተን” ተዋልደን” ከሚለው አሰልቺ ትርክት ባሻገር ብዙዎቻችን ኒሎቲክ እና ኦሞቲክ የኢትዮጵያን ሕዝቦች ዛሬም ቢሆን በእኩል ዓይን አናያቸውም። በሌላ አነጋገር፣ ኢትዮጵያ እንደ አገር የነበረችው፣ ሕዝቦቿ በሙሉ ተስማምተው ወይም ደግሞ የሁላቸውም ሰብዓዊና ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው እኩል ተከብሮላቸው አብሮ የሚኖሩ አልነበሩም ማለት ነው። ዋለልኝ ጽሑፉን ባቀረበበት ዘመን “ሕዝቦቿ ተስማምተው፣ ተጋብተውና ተዋልደው አብረው ይኖሩባታል” ተብሎ የሚዘመርላት አገራችን ዛሬም እምብዛም ለውጥ ሳታሳይ
ያንኑ የተዛባ ግንኙነትን የሙጥኝ ብላ አገረ-መንግሥት መመሥረት አቅቷት ተከታታይ የፖሊቲካና ማኅበረ ሰባዊ ቀውሶችን እያስተናገደች ትገኛለች። የዋለልኝ ጽሑፍ ይህንን ያልተስተካከለና አስጸያፊ የነበረውን የሕዝቦቻችንን ግንኙነት ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ለማስረዳት የሞከረው እንጂ ዶ/ር ኃይሌና አንዳንዶች እንደሚሉት ተስማምቶ የነበረውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመከፋፈል አልነበረም። ዋለልኝ በጊዜው ““አሁን ባለችበት ደረጃ ኢትዮጵያ አንድ ብሔር አይደለችም። ይልቁንስ ኢትዮጵያ፣ የራሳቸው ቋንቋ፣ የአለባበስ ሥርዓት፣ ማኅበራዊ አደረጃጀትና ግዛታዊ ማንነት ያላቸው የደርዘን ብሔረ ሰቦች ውጤት ናት” ነበር ያለው። በዋለልኝ ግምት፣ በኢትዮጵያ ነግሦ የነበረው ብሔርተኝነት “በገዢ መደቦች የተፈጠረውና ሳይፈልጉ የተጫነባቸው እንዲሁም አልፎ ተርፎ ምንም በማያውቁ ተጓዦች ብዙ የተባለለት ሃሳዊ የሆነው ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት” ነበር። ይህንን ሃሳዊ የሆነውን ብሔርተኝነትን ነው እንግዲህ የሥርዓቱ አቀንቃኞችና ደጋፊዎች “ኢትዮጵያ አንድ ብሔር ናት” “ሕዝቦቿም ተዋድደውና ተጋብተው በሰላም ይኖሩባታል” እያሉ ይተርኩ የነበሩት!
ዋለልኝ በጽሁፉ ውስጥ ያነጣጠረው በአማራና በትግራይ ገዢ መደቦች እንጂ በአማራ ወይም በትግራይ ሕዝብ ላይ አልነበረም። ትኩረቱና ዓላማው ያንን የገዢ መደብ በአብዮታዊ ትግል አፍርሶ በምትኩ እኩልነት የሰፈነባትን እውነተኛዋን አንድ “አገረ ብሔር” ለመመሥረት ነበር። ዋለልኝ የአማራን ገዢ መደብ ሲያወግዝም፣ ገዢና ጨቋኝ መሆናቸው ግን አማራ ልዩ ጨቋኝ ሕዝብ በመሆኑ አይደለም ብሎ የጅምላ ፍረጃን ይቃወማል። በሱ አባባል፣ “በርግጥ በአማራዎችና ተከታይ አጋራቸው በሆነው ትግሬዎች የተደረገው የኤኮኖሚና የባሕል ወረራ የታሪክ አጋጣሚ ብቻ ነው። አማሮች የበላይ የሆኑት በተፈጥሮ ኢምፔሪያሊስትነት የተጠናወታቸው ስለሆኑ አይደለም። ዕድሉን ቢያገኙ ኦሮሞዎችም ሊያደርጉት ይችሉ ነበር። ወላይታዎች ስሊያደርጉት ይችሉ ነበር። ታሪክም ይህን ሊያደርጉ እንደ ነበረ ይመሠክራል። ነገር ግን ለዚህ ሁኔታ መቀጠል ምክንያት ሊሆን አይገባም። አጣዳፊው ጉዳይ “በቃ” ብለን ማወጅ አለብን። እናም እውነተኛውን ብሔራዊ አገር (Nation State) መገንባት አለብን” ይላል።
አገራችን እንድትሆን የሚመኛትን “ብሔራዊ አገር” ምን መምሰል እንዳለባት ዋለልኝ እንደሚከተለው በግልጽ አስቀምጦታል።
“ብሔራዊ አገር ስንል ሁሉም ብሔረ ሰቦች በአገር ጉዳይ ላይ በእኩልነት የሚሳተፉበት እያንዳንዱ ብሔረ ሰብ የራሱን ቋንቋ፣ ሙዚቃና ታሪክ ለመጠብቅና ለማሳደግ እኩል ዕድል የሚያገኝበት አገር ማለት ነው። አማራዎች፣ ትግሬዎች፣ ኦሮሞዎች፣ አደሬዎች፣ ሱማሌዎችና ወላይታዎች፣ ጉራጌዎች ወዘተ በእኩል የሚስተናገዱበት አገር ማለት ነው። በኤኮኖሚውም ሆነ በባሕል አንደኛው ብሔር ሌላውን ብሔር የማይጫንበት ሃገር ማለት ነው” ይለናል።
ይህንን የዋለልኝን አስተሳሰብ በጊዜው የነበሩት የኢትዮጵያ ተማሪዎች አባላትና ኋላም አብዮቱ ከፈነዳ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው በመኢሶንና በኢሕአፓ ሥር ተደራጅተው የአብዮቱ አካል ሆነው ሕዝቡን ሲያነቃቁና ሲያደራጁ የነበሩ የተማሪ ማሕበራት አባላት አስተሳሰቡን የራሳቸው አድርገውት ይታገሉለት እንደ ነበረ ብዙ የታሪክ ማስረጃዎች አሉ። ለምሳሌ ያሕል፣
የመኢሶን አመራር አባል የነበረው ኃይሌ ፊዳ ግንቦት 7 ቀን 1969 ዓ/ም የሰፊው ሕዝብ ድምጽ በተባለው የድርጅቱ መጽሔት ቁጥር 35 ላይ፣ “መኢሶን የሚፈልገው እኩልነትና ነጻነት የሰፈነባት፣ የሕዝቦቿ አንድነት ከብረት የጠነከረባትና ብሔረ ሰቦቿ ሁሉ ያበቡባት፣ የማንም ተመጽዋች ያልሆነ፣ በራሱ የሚተማመን፣ በማንም ፊት የበታችነት ስሜት ሊኖረው የማይችል፣ በትግሉና በመሥዋዕትነቱ ውጤቶች የሚኮራ፣ በዓለም ሕዝቦች ሸንጎ ተገቢውን ቦታ የያዘ ሕዝብ የሚኖርባት አዲስ ሕዝባዊት ኢትዮጵያ እንድትመሠረት ነው” በማለት የኢትዮጵያ ብሔሮች ግንኙነት ተስተካክሎ በዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ውስጥ በሰላምና በእኩልነት መኖር አለባቸው ነበር ያለው።
በወቅቱ የተማሪው ማኅበርና ማኅበሩ የወለዳቸው የፖሊቲካ ድርጅቶች፣ በተለይም እኔ እደግፈው የነበረው የመኢሶን ቡድን ያኔ ይመራበት የነበረውና ዛሬም ድረስ የማምንበት መሪህ፣ “የብሔር ጥያቄ የዲሞክራሲ ጥያቄ ነው፣ ስለዚህ በኢትዮጵያ ውስጥ የዲሞክራሲው ጥያቄ ከተፈታ የብሔር ጥያቄውም አብሮ ይፈታል” የሚለው ነበር። የያኔው የብሔር ጥያቄን ያነሱ የነበረው በሕዝቦች መካከል እኩልነት እንዲሠፍን እንጂ አንድም ቦታ ላይ በፕሮግራማቸውም ሆነ በቀን ተቀን ቅስቀሳቸው ላይ የሕዝቦችን የመለያየት ወይም የኢትዮጵያን መፍረስ አልሰበኩም።
ዛሬ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች በተለይም በአማራ፣ በኦሮሚያና በትግራይ ክልሎች ዘንድ የማንነት (የብሔር) ጥያቄ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ጎልቶ ከመታየት አልፎ በየእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ከትቶናል። በአራቱም አቅጣጫ፣ በተለይም ከላይ የጠቀስኳቸውን ሶስቱን ታላላቅ የኩሽ ሕዝቦችን እንወክላለን በሚሉ ታጣቂ ቡድኖች ፊታውራሪነት፣ “በማንነታችን ተጠቅተናል” ብለው መንግሥትን በነፍጥ በመገዳደር ሂደት በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩትን የወገኖቻችንን (በተለይም የወጣቱን) ሕይወት መቅጠፍ፣ የአጋጣሚ ሳይሆን መደበኛ ክስተት እየሆነ ከመጣ ሰንብቷል። ክስተቱ ግን የሚያሳየው ዋለልኝ ያለውን፣ በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል የነበረው ግንኙነት ጤናማ አለመሆኑንና፣ አንዲት አገረ ብሔር ለመፍጠር እንቅፋት መሆኑን እንጂ የማንነት ጥያቄውና መገዳደሉ የዋለልኝ ጽሁፍ የቀሰቀሰው ጉዳይ አለ መሆኑን ነው። አዎ! የሰው ልጅ መቅረፍ ላቃተው ወይም መቅረፍ ለማይፈልገው ማኅበራዊ ቀውስ፣ ሁሌም ሰበብ መፈለጉ አዲስ ነገር አይደለም። ዋለልኝ ያነሳውን ጥብቅ ጉዳይ መርምሮ ተወያይቶ ብሔራዊ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ፣ “ችግሩን ያመጣብን የዋለልኝ ጽሁፍ ነው” ብሎ መደምደሙ የሚቀልላቸው ሰነፍና ጸረ ሕዝብ የሆኑ ብዙ ምሑራን አሉ። ዋለልኝ በዚያች ቀን ያቺን አጭር ጽሁፍ ለዩኒቬርሲቲ ተማሪዎች ባያቀርብ ኖሮ፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ተዋድደውና ተከባብረው በሰላም አንዲት ምድራዊ ገነት የሆነች ኢትዮጵያ የምትባል አገረ-ብሔር መሥርተው ይኖሩ ነበር ሊሉን የሚዳዱ መኃይም ምሑራን በጣም ብዙ ናቸው!
ዋለልኝ በጽሁፉ ውስጥ ያኔ በኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ጥያቄን አንስተው የመገንጠል ዓላማን ሲያራምዱ የነበሩትን ለምሳሌ የባሌና የኤርትራ ነጻ አውጪ ድርጅቶችን እንቅስቃሴን አስመልክቶ “የኤርትራ ነጻነት ግንባርና የባሌ ትጥቅ ትግል ግባችንን ያሳኩልናል? ግባችንን የሚያሳኩልን አሁን ባሉበት ዓላማም ሆነ አኳኋን አይደለም” ብሎ ያለ አንዳች ማወላወል አቋሙን ግልጽ አድርጎ ነበር የተናገረው። ምኞቱ፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች እንዲገነጣጠሉ ሳይሆን፣ የፊውዳሉ ሥርዓት የከፋፈላቸውንና “በጌታና ባርያ” መካከል የነበረውን የተዛባ ግንኙነት አስወግዶ የተለያዩ የኢትዮጵያን ሕዝቦችን በእኩልነት በሰላምና በፍቅር የሚኖሩባትን አንዲት አገረ-ብሔር፣ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ የሚረዳ ፍኖተ ካርታ ለማቅረብ ነበር።
ዋለልኝ ያነሳው የብሔር ጥያቄ፣ እነዶ/ር ኃይሌና መሰሎቹ ሊያሳምኑን እንደሚሞክሩት ሆን ብሎ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳና ውሸትን የሀቅ ማቅ ለማልበስ በቅቶ አገሪቷን በጐሣ ክፍፍል ለማናወጥ አልነበረም። ከሱም አስቀድሞ የብሔርን ጥያቄ በአገር ውስጥም ሆነ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የጉዳዩ አሳሳቢነት የታያቸውና ትልቅ ትኩረት ሰጥተውት ይወያዩበት የነበሩ ግለ ሰቦችና ቡድኖች / ማኅበራት እንደ ነበሩ ታሪክ ይመሠክራል። ዋለልኝ በርግጠኝነት ያደረገው ከሱ በፊት የነበሩት ግለሰቦችና ማኅበራት የብሔሮችን (ሕዝቦችን) መብት ጉዳይ በተለያዩ መድረክ ያቀረቡትን ማኅበረ ሰባዊ ጉዳይ ዕውቅና ሰጥቶት በራሱ መንገድ ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር አዛምዶ አቀረበው እንጂ እሱ የፈጠረው ጉዳይ አልነበረም። ከዋለልኝ ወረቀት በፊት የብሔር ጥያቄን አንስተው ለውይይት ያቀረቡ አገር በቀልና ዓለም ዓቀፋዊ ምሁራንና ተቋማት ብዙ ነበሩ። ለማስረጃም ያሕል፣
ሀ) አቶ ሓዲስ ዓለማየሁ ስለ ኢትዮጵያ ሕዝቦች የጻፉት፣
በፖሊቲካና ማኅበረ ሰባዊ ዕውቀትና ልምዳቸው፣ እንዲሁም በአስተዳደር እና በደራሲነት ብቃታቸው ታላቅ ቦታ ከሚሰጣቸው የአገራችን ታዋቂ ግለሰቦች መካከል በመጀመርያ ተርታ ከሚመደቡት አንደኛው አቶ ሓዲስ ዓለማየሁ ናቸው። እኚህ ታላቅ
ሊቅ፣ በ1953 የንዋይ ወንድማማች የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በኋላ፣ ንጉሠ ነገሥቱ የወቅቱን የአገሪቷን ሁኔታ ገምግመው ምክረ ሃሳብ እንዲያቀርቡ ከታዘዙት የአገሪቷ ሊቆች መካከል አንዱ ነበሩ። አቶ ሓዲስም በታዘዙት መሠረት ጥናቱን አጠናቅቀው በዚያው ዓመት ለንጉሠ ነገሥቱ ባቀረቡት ምክረ ሃሳብ ውስጥ ስለ ኢትዮጵያ ሕዝብ ያላቸውን ሃሳብ እንደሚከተለው አቅርበው ነበር፣
“በፖሊቲካ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የምንለው ከአማራ፣ ከትግሬ ከኦሮሞና ከሌሎችም ልዩ ልዩ ቋንቋ፣ ልማድ፣ ዘር ወይም ኃይማኖት ካላቸው ክፍሎች አንድ ላይ ሆኖ በኢትዮጵያ ዘውድ ሥር የሚተዳደረው ነው። ነገር ግን፣ እነዚህ ልዩ ልዩ ቋንቋ ልማድና ዘር ወይም ኃይማኖት ያላቸው ክፍሎች ምንም እንኳ በአንድ ላይ “የኢትዮጵያ ሕዝብ” የሚል ስም ቢሠጣቸውና በአንድ ዘውድ ሥር ቢተዳደሩም በደስታም ሆነ በመከራ፣ በመልካም ይሁን በክፉ ጊዜ አንድ ላይ የሚያስተሳስረውና ሕዝብን አንድ የሚያሰኘው የሕብረት ማሠርያ ያላቸው ናቸው ለማለት አያስደፍርም” ነበር በማለት በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል የነበረውን ግንኙነት ብቻ ሳይሆን ደፍረው “የኢትዮጵያ ሕዝብ” አለ ብሎ መናገር አይቻልም ብለው ነበር የደመደሙት።
“የኢትዮጵያ ሕዝብ” የሚባል ነገር የለም ከማለትም አልፈው፣ በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካክል የነበረው ግንኙነትም በጣም “የተዛባ” መሆኑን ሲያስረዱ፣
“በኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ክፍሎች የሚኖሩ ሕዝቦች በቋንቋ፣ በልማድ፣ በዘርና በኃይማኖት እንደ መለያየታቸው መጠን የሕይወት ዓላማቸውም የተለያየ ነው። ከመካከላቸው አንዳንዶቹ ከሁሉም የበላይነት ስሜት የሚሰማቸውና ይህ የበላይነት እንዲሁ እንዳለ እንዲኖር የሚመኙ ናቸው። ሌሎች ደግሞ የበላይ ነን ከሚሉት ባንበልጥ አናንስም የማለት ስሜት የሚሰማቸውና ይህንኑ ለማረጋገጥ አጋጣሚ ጊዜ ለማግኘት የሚመኙ ናቸው። ሶስተኛ፣ የበታችነት ስሜት የሚሰማቸውና የበላይ ነን የሚሉትን ክፍሎች ኃይል ሰብሮ ነጻ የሚያወጣቸውን ክፉ ቀን የሚጠብቁና የሚመኙ ናቸው” ብለው ነበር ምክረ ሃሳባቸውን የለገሱት።
(አቶ ሓዲስ ዓለማየሁ “መወሰድ ስላለባቸው የፖሊሲ እርምጃዎች፣ ለግርማዊ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ጥር 23 ቀን 1953 ዓ/ም የቀረበ ማስታወሻ፣ ገጽ 13)
አቶ ሓዲስ ዓለማየሁ ይህንን ምክረ ሃሳብ በጽሁፍ ለጃንሆይ ያቀረቡት ዋለልኝ የራሱን ጽሁፍ ለአዲስ አበባ ዩኒቬርሲቲ ተማሪዎች ከማቅረቡ ከዘጠኝ ዓመት አስቀድሞ ነበር።
እንደ አቶ ሓዲስ ቅን አእምሮና መጠነኛ የፖሊቲካ ዕውቀት ላለው ማንኛውም ኢትዮጵያዊ፣ የዚያን ጊዜን የኢትዮጵያን ሕዝቦች የእርስ በርስ ግንኙነት ከዚህ በተለየ መልኩ መሳል እንደማይቻል ጠንቅቆ ይረዳል። ሊቁ ሓዲስ ዓለማየሁ፣ ብዙዎቻችን አውቀንም ሆነ ሳናውቀው ሸፋፍነው የምናልፈውን “የኢትዮጵያን ሕዝብ” አንድ ያለ መሆን ጉዳይ ኮለል ባለ አማርኛ ነበር ለንጉሠ ነገሥቱ የነገሯቸው። በአቶ ሓዲስ ዓለማየሁና በዋለልኝ ጽሁፍ መካከል ያለው ልዩነት የአቶ ሓዲስ ዓለማየሁ ጽሁፍ ከቤተ መንግሥት ግቢ ውጭ ያልተሠራጨ ሲሆን፣ የዋለልኝ መኮንን ጽሁፍ ግን በአደባባይ ለሰፊው የተማረው ሕዝብ መነበቡ ነው። በተረፈ ግን፣ ሁለቱም ያነጣጠሩት የኢትዮጵያ ሕዝቦች በእኩልነት ደረጃ ሳይሆን የበላይና የበታች ሆነው በአንድ ዘውድ ሥር የሚተዳደሩ መኖራቸው ላይ ነው።
ለ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ስለ ሕዝቦች የነበረው አቋም
የዋለልኝ ጽሁፍ በአደባባይ ለዩኒቬርሲቲ ተማሪዎች ከመቅረቡ አራት ዓመት አስቀድሞ፣ ኢትዮጵያ መሥራችና ሙሉ አባል የሆነችበት የተባባሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) አባላት፣ ታኅሳስ 7 ቀን 1959 ዓ/ም ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔው ላይ፣ የብሔር (ሕዝቦችን) የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት በጥልቅ ከተወያዩበት በኋላ ያለ አንዳች ተቃውሞ በመላው አባላት የተደገፉ ሁለት ሥር ነቀል የሰብዓዊ መብቶች ኮንቬንሽኖችን አጽድቋል። እነዚህ ሁለት ኮንቬንሽኖች ማለትም “ዓለም ዓቀፍ የሲቪልና የፖሊቲካ መብቶች ኮንቬንሽን” እና “ዓለም ዓቀፍ የኤኮኖሚ፣ ማኅበረ ሰባዊና ባሕላዊ መብቶች ኮንቬንሽን”
(በእንግሊዝኛ ICCPR and IESCR) በመባል የሚታወቁት፣ ሁለቱም በመጀመርያው አንቀጾቻቸው ላይ “ማንኛውም ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመሰን መብት አለው። ይህንንም መብቱን ተጠቅሞ የየራሱን ፖሊቲካዊ፣ ኤኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ባሕላዊ ዕድገቱን መወሰን ይችላል” የሚል አንድ ዓይነት ይዘት ያላቸውን ሁለት አንቀጾች በኮንቬንሽኑ አንቀጽ አንድ ሥር በማስቀመጥ የብሔሮች (የሕዝቦች) መብት ጥያቄ መፈታት ምንኛ አስፈላጊ እንደሆነ ለዓለም ዓውጀዋል። አገራችን ኢትዮጵያን
ጨምሮ 175 አገራት በፊርማቸው ያጸደቋቸው እነዚህ ሁለት ዓለም ዓቀፍ ውሎች፣ ዛሬ የግለ ሰብና የቡድን መብት ማረጋገጫ ሕያው ሰነድ ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው። ከላይ እንዳልኩት፣ እነዚህ ሁለት የተመድ ዓለም ዓቀፍ ውሎች በአባል አገራት የጸደቁት ዋለልኝ ጽሁፉን ከማቅረቡ ከአራት ዓመት በፊት ነበር።
እነዚህ ሁለቱ ማስረጃዎች፣ ማለትም የአቶ ሓዲስ ዓለማየሁና የተመድ ዓለም ዓቀፋዊ ውሎች፣ ዋነኛው ዓላማቸው፣ ልክ ዋለልኝ እንዳለው፣ ማንኛውም ሕዝብ/ብሔር የራሱን ዕድል በራሱ እንዲወስን (የራሱን መንግሥት መምረጥ፣ ተፈጥሮያዊ ሓብቱን ከሌሎች ምዝበራ አድኖ ራሱ እንደሚመቸው እንዲጠቀምበት፣ የራሱን ባሕልና ቋንቋ ያላንዳች ገደብ ለማሳደግ እንዲችል ወዘተ የታቀደ እንጂ በምንም መልኩ የሌላውን ሕዝብ/ብሔር መብት እንዲነካ ወይም አንድን አገረ ብሔር ለመከፋፈልና ለማፍረስ አልነበረም።
እንግዲህ፣ እንደ ዶ/ር ኃይሌ ዓይነቶቹ ወጣቱን ትውልድ ለማሳመን ሳይሆን ለማወናበድ እንደሚሞክሩት፣ ዛሬ በአገራችን እየተከሰተ ላለው ማኅበረሰባዊና ፖሊቲካው ቀውስ ተጠያቂው ዋለልኝ መኮንን አይደለም። ከላይ ከጠቀስቋቸው ሁለት ዓቢይ ሰነዶች እንደምንረዳው፣ ከዋለልኝ በፊት ይህንን ሃሳብ ያነሱት ተመድና አቶ ሓዲስ ዓለማየሁ፣ ዓላማቸው “ሕዝቦች (ብሔሮች) የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው ይወስኑ፣ አንዳቸው አንዳቸውን ሳይጨቁኑ በእኩልነት በሰላም ይኑሩ” ነው እንጂ ያሉት፣ አገራት እንዲገነጣጠሉ ወይም በጎሳ ተከፋፍለው የእርስ በርስ ጦርነት እንዲያካሄዱ አልነበረም። የዋለልኝም ሕልም ይኸው ነበር። ዋለልኝ በጽሁፉ ውስጥ ለሕዝቦች (ብሔሮች) እኩልነት ጠንቅ የሆነው በጊዜው የበላይነትን ይዞ ሌሎችን ብሔሮችን ሲጭቁን በነበረው የአማራ ገዢ መደብ ላይ እንጂ አንድም ቦታ በአማራም ሆነ በሌሎችም ሕዝቦች ላይ አላነጣጠረም። እንዲገረሰስም የተመኘው ጨቋኙን የገዢ መደብ እንጂ፣ የአማራው ወይም የትግሬም ሕዝብ እንደ ማንኛውም የኢትዮጵያ ሕዝብ የተጨቆነና በሥርዓቱ የተበደለ መሆኑን በግልጽ ሲያስቀመጥ፤
በርግጥ በአማራዎችና ተከታይ አጋራቸው በሆነው ትግሬዎች የተደረገው የኤኮኖሚና የባሕል ወረራ የታሪክ አጋጣሚ ብቻ ነው። አማሮች የበላይ የሆኑት በተፈጥሮ ኢምፔሪያሊስትነት የተጠናወታቸው ስለሆኑ አይደለም። ዕድሉን ቢያገኙ ኦሮሞዎችም ሊያደርጉት ይችሉ ነበር። ወላይታዎች ሊያደርጉት ይችሉ ነበር። ታሪክም ይህን ሊያደርጉ እንደ ነበረ ይመሠክራል። ነገር ግን ለዚህ ሁኔታ መቀጠል ምክንያት ሊሆን አይገባም። አጣዳፊው ጉዳይ “በቃ” ብለን ማወጅ አለብን ይላል።
የያኔውን የኢትዮጵያ ሕዝቦች ግንኙነት በቅንነት ለመረዳት ለሚሞክር ማንኛውም የነቃ የማኅበረ ሰቡ አካል፣ በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል የነበረው ግንኙነት የተዛባ ብቻ ሳይሆን፣ አንዳንዶቹ “የበላይ ነን” የሚሉ ብሔሮች / ሕዝቦች ሌሎቹን የኢትዮጵያን ሕዝቦች ማንነት፣ ቋንቋና ባሕል በበታችነት ከማየት ባሻገር፣ “ባርያ” ወይም “ሻንቅላ” ብለው ፈርጀዋቸው፣ እጅግ
በጣም አስከፊ በሆነ መልኩ እንደ ዕቃ ሲሸጧቸውና ሲለውጧቸው እንደ ነበር ማስተዋል ቀላል ነበር። ዋለልኝ፣ ይህንን ዓይነቱን በመላው የዓለም ዓቀፉ ማኅበረ ሰብ ዘንድ ሳይቀር ያዋረደንን ተግባር ነበር እንዲገረሰስ በአደባባይ ያወጀው! እነ ዶ/ር ኃይሌ ዓይነቱ ደግሞ እንኳን ያኔ ዋለልኝ ለተናገረው ሓቅ ዕውቅና መስጠት ይቅርና፣ ዛሬም የአንዳንድ ብሔር ተወላጆች ኢትዮጵውያን ባርያ ተብለው ይሸጡ ነበር ብለው ለመናገር አይደፍሩም። እንዲያውም “ባርነት ኢትዮጵያ ውስጥ አልነበረም” ብለው ለመከራከር ሲዳዱ ይስተዋላሉ። “እንደው ዝም ብለን፣ እነ ዋለልኝ ዓይነት በጥባጮች ናቸው፣ ወይም ደግሞ ይኸ የወያኔ ሕገ መንግሥት በጎሣ ከፋፍሎት ነው እንጂ “የኢትዮጵያ ሕዝብማ ተዋልዶና ተጋብቶ፣ ተዋድዶ አብሮ ይኖር ነበር” እያልን ራሳችንን ከማታለል ባለፈ፣ ያኔ ይቅርና ዛሬም ድረስ የኒሎቲክና ኦሞቲክ ሕዝቦቻችንን በእኩልነት እንደማናያቸው ከላይ የጠቀስኩት ክስተት ተጨባጭ ማስረጃዎች ነው። እንደ ሌሎች አገሮች ለምሳሌ የአሜሪካ፣ የካናዳና የአውስትራሊያ መንግሥታት፣ ባለፉት ምዕተ ዓመታት መጤ አውሮፓውያን አያት ቅድመ አያቶቻቸው በነባሩ የነዚህ ሶስት አሕጉራት ነባር ሕዝቦችና ጥቁር ሕዝቦች ላይ የፈጸሙትን በደል አስመልክተው በሕዝቦቻቸው ስም ያለፈውን ጠባሳና ቁስል እንዲጠግግ ሲወስኑ፣ ተከታታይ የኢትዮጵያ መንግሥታት ግን እስከ ዛሬም ድረስ በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም እነዚህን ተጨቋኝ ነባር ሕዝቦችን እንኳን ይቅርታ መጠየቅ ይቅርና፣ ጭቆናው ራሱ ነበረ ብሎ እውቅና ለመስጠት ዝግጁ አይደሉም።
ዶ/ር ኃይሌ የዚያኛውን ትውልድ የሚከሱበት ሌላኛው ነጥብ ደግሞ፣
“የትውልዱ ዓይነተኛ ጠባይ የሚያሳየው የባዕድ በተለይም የፈረንጅ አምላኪዎችና ለገዛ ራሳቸው ታሪክን ባሕል ተጸያፊ” “ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን የሚያንቋሽሹ፣ አባቶችንና ታሪክን የሚያዋርዱ፣ በአጉል ትምክህትና ትዕቢት ያበጡ፣ ለሥልጣንና ለገንዘብ ሲሉ አገር ከመሸጥ ወይንም ከጠላት ጋር ወግነው የገዛ አገራቸውን ከመውጋት ወደ ኋላ የማይሉ አረመኔ መሆናቸውን ታሪካቸው ይመሠክራል” ይላሉ።
ይህ መቼም ዓይናችሁን ጨፍኑና ላሞኛችሁ ከማለት በቀር ቅንጣት ታሕል እውነትነት የሌለው ተራ አሉባልታ ነው። የትውልዱ ዓይነተኛ ጠባይና ዋነኛው የትግል ዓላማ የውጪ ኃይላት በተለይም የኢምፔሪያሊስቱ የአሜሪካ መንግሥት ጫና በኢትዮጵያ እንዳይኖር ያለ አንዳች ማወላወል መታገላቸው ነው። “ያንኪ ጎ ሆም” የሚለው የዘወትር መፈክራቸውን በተግባር ሲተረጉሙ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቬርሲቲ በአሜሪካኖች ግፊት ይዘጋጅ የነበረውን የቁንጅና ውድድር እንኳ ሳይቀር ተቃውመው ሰልፍ ይወጡ ነበር። ኢምፔሪያልስቷ አሜሪካ በቬትናም የምታካሄደውን ጸረ ሕዝብ ጦርነትና አውሮፓውያን በአፍሪካ ላይ የነበራቸውን የቅኝ ግዛት ፖሊሲ በአደባባይ ተቃውመው የማያቋርጥ ሰልፍ ከማዘጋጀታቸው ሌላ በአካልም ከጥቁር ጓዶቻቸው ጋር ሆነው አውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎችን ለመዋጋት የሄዱ ወይም ደግሞ እንደ ጌራና ጓደኞቹ ዓይነት በጉዞ ላይ እያሉ ታሥረው የተሰቃዩ ብዙ የያኔው ትውልድ አባላት ነበሩ።
በውጭ አገር ይገኙ የነበሩ እንደ ዶ/ር ኃያሌ ዓይነቱ ከአገር ጉዳይ ይበልጥ የግል ጥቅምን ሲያሳድዱ ከነበሩ እፍኝ የማይሞሉ አድር ባዮች በስተቀር አብዛኛው በውጭ አገር የሚኖሩ የተማሩ ኢትዮጵያውያን፣ ሁኔታዎች ተቀይረው ወደ ኢትዮጵያ በፍጥነት የመመለስ ዓላማቸውን እንዳያዘገይባቸው ከማለት፣ ትዳር ወይም ቋሚ ሥራ ከመያዝ ይልቅ፣ ትናንሽ ጊዜያዊ ሥራዎችን እየሠሩ ወደ ኢትዮጵያ የሚመለሱበትን አመቺ ቀን ይጠባበቁ እንደ ነበር ዶ/ር ኃይሌ ራሳቸው ምሥክር ናቸው። እነዚያ ንቁ
ኢትዮጵያውያን፣ ትምሕርታቸውን ለማጠናቀቅ አንድ ሴሚስተር እንኳ የቀራቸው አገር ወዳዶች የ1966ቱ አብዮት ሲፈነዳ ሁሉን ነገር እርግፍ አርገው ትትው ነበር ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት! የተመለሱት ደግሞ የፖሊቲካ ሥልጣን ፈልገው ወይም ቁሳዊ ፍላጎታቸውን ለማርካት ሳይሆን በፍኖተ ካርታቸው መሠረት ከሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን በመቆም ከላይ የተወሳውን ዓይነት የብሔርና የመደብ ጭቆና ለመታገል መሆኑ ለአገራቸውና ለሕዝባቸው የነበራቸውን ፍቅር በተግባር ለማሳየት ነበር።
አንድ ሌላው እንደ እነዶ/ር ኃይሌና ቡድኖቹ በየአጋጣሚው የሚያነሱት ጉዳይ ደግሞ “የያኔው ትውልድ” አባላት የውጭ አገር አይዲኦሎጂና እምነትን ከአገሪቱ ሁኔታ ጋር ሳያገናዝቡ ዝም ብለው ከየዩኒቨርሲቲው ሸምተው ለአገራችን ጠቃሚ ነው ብለው ያመጡት የባዕድ አምልኮ ነበር” የሚለው ነው። አዎ! ምሑራኑ አይዲዮሎጂዉን በትምሕርት ሂደት ገብቷቸው ለአገራችን ጠቃሚ ነው ብለው ወስነው ይሆናል። ይህ ደግሞ ከመማር ዓላማዎች አንዱ ስለሆነ አያስወቅስም። ከዚያም በላይ ደግሞ በዓለማችን ያሉ አይዲዮሎጂዎችና ኃይማኖቶች ሁሉ በአንድ ጊዜ በሁሉም አሕጉር የበቀሉ ሳይሆን፣ በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ አሕጉራት በሚኖሩ ግለ ሰቦች ወይም ቡድኖች የተፈጠሩ ናቸው። ሶሺያሊዝም በአንድ አሕጉር ተፈጥሮ ወደ ሌሎች አሕጉሮች የተዛመተ ነው። የክርስትና እምነት በመካከለኛው ምሥራቅ ተፈጥሮ፣ በአራተኛው ክፍለ ዘመን በግብጽ ፊታውራሪነትና በሶርያ የወንጌል ዘማቾች ነበር ወደ ኢትዮጵያ የገባው። የእስልምና ኃይማኖትም እንድሁ በሰባተኛው ክፍለ ዘመን ነው ወደ ኢትዮጵያ የመጣው። በአጭሩ፣ የክርስትናና የእስልምና ኃይማኖቶች የተውሶ (መጤ) እምነቶች የመሆናቸውን ያሕል፣ እነ ዋለልኝ የታገሉለት ሶሺያሊዝምም ለአገሪቱ መጤ አይዲዮሎጂ ነበር። ክርስትናም ሆነ እስልምና ሀገር በቀል ኃይማኖቶችን አሸንፈው ቅቡልነት አግኝተው ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ኃይማኖቶች ሆኑ እንጂ መጤ ኃይማኖቶች ናቸው። የሶሺያሊዝም አይዲዮሎጂም እንደዚሁ! ስለዚህ የያኔው ትውልድ የሶሺያሊዝምን አይዲዮሎጂ ወደ ኢትዮጵያ ማስገባታቸው አዲስ ክስተት አይደለም ለማለት ያህል ነው።
ሕገ መንግሥቱን በተመለከተ
ሕገ መንግሥት የአንድ ማኅበረ ሰብ መተዳደርያ ደንብ ነው። ሕገ መንግሥቶች ከሃሳብ ማመንጨት፣ ማርቀቅንና ማጽድቅን ጨምሮ ብዙ የአስተሳሰብ ግጭቶች የሚስተናገዱበት ሂደት ነው። ሕገ መንግሥትን ማርቀቅ፣ በሙያና በልምድ አስፈላጊውን ዕውቀት ያካበቱ ግለሰቦች ሥራ ነው። በመሠረቱ አርቃቂዎቹም ሆን አጽዳቂዎቹ የሚመመረጡት በወቅቱ የፖሊቲካ ሥልጣን ወንበር ላይ በተቀመጠ አካል ነው። በነዚህ ሙያተኞች የረቀቀው ሰነድ በሕዝቦች ቀጥተኛ ተሳትፎ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ሕዝቡ ወክሎ በሚልካቸው ግለሰቦች አማካይነት ጸድቆ ሥራ ላይ ይውላል።
በ1995 ዓ/ም የጸደቀው የፌዴራል ኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በይዘቱና ሆነ በቅርጹ ከፊተኞቹ ያገራችን ሕገ መንግሥታት ሁሉ የተለየ መሆኑን ብዙዎቻችን እንገነዘባለን። በተለይም የግለ ሰቦችንም ሆነ የቡድን መብቶችን በማያሻማ መልክ በማካተቱ! በአንጻሩ ደግሞ፣ ልክ እንደ ፊተኞቹ ሕገ መንግሥታት የማርቀቅና የማጽደቅ ሂደት፣ አርቃቂዎቹንም አጽዳቂዎቹንም ራሱ ከማኅበረ ሰቡ መሃል መልምሎ ያዋቀረው የፖሊቲካ ሥልጣኑን የጨበጠው ወያኔ መራሹ የኢትዮጵያ መንግሥት ነበር። ወያኔ መራሹ የኢሕአዴግ መንግሥት የሥልጣን መንበሩን አረጋግቶ የሽግግር መንግሥት ካቋቋመ በኋላ ሕገ መንግሥቱንም እንደሚመቸው አስረቅቆ ማጽደቁ ከነጻ አውጪ ብሔርተኛ ድርጅቶች የሚጠበቅ ነበር። ሕወሃት ነፍጥ አንግቶ ለዓመታት በየዱሩ ማዕከላዊውን መንግሥት ሲገዳደር የነበረው ይህንኑ የነጻነት ዓላማውን ከግብ ለማድረስ ስለ ነበር በሕገ መንግሥቱ
ውስጥ አንቀጽ 39ን የመሰለ ሥር ነቀል የሕዝቦችን መብት ጉዳይ ማካተቱ የሚጠበቅ ነበር። አራት ኪሎ ደርሶ ፌዴራል ኢትዮጵያን የመገንባት ሃሳብ እስኪመጣለት ድረስም፣ እወክለዋለሁ ብሎ ያወጀውን ሕዝብ “ነጻ ለማውጣት” ይተጋ ስለ ነበር የሚያጸድቀው ሕገ መንግሥት ዋነኛ ትኩረቱ የብሔሮች የራስን ዕድል በራስ ከመወሰን ያነሰ ይዘት ይኖረዋል ብሎ መገመት የፖሊቲካ መኃይም መሆን ይመስለኛል።
የሕገ መንግሥቱ ተቃዋሚዎች ከሚያነሷቸው ቁርጥ ነጥቦች አንዳንዶቹ፣
ሀ) “ሕገ መንግሥቱ የአገሪቷን አስተዳደራዊ መዋቅር በክልል ሲከፋፍል፣ ሕዝቦች በብሔር እንዲከፋፈሉና እርስ በእርስ እንዲጣሉ አድርጎ አገሪቷን ከዳር እስከ ዳር በእርስ በርስ ግጭት እያናወጣት ይገኛል” ይሉናል እነ ዶ/ር ኃይሌና መሰሎቹ። ዛሬ በየክልሎቹ እየተከሰተ ያለውን የእርስ በርስ ግጭት ዕውን ሆኖ ስናስተውል፣ ቅያሜው ቅንጣት ታክልም ቢሆን እውነትነት አለው። ሆኖም ግን የግጭቶቹ መንሥዔ ፌደራላዊ ሥርዓቱና በሕገ መንግሥቱ የተደነገገው ብሔርና ቋንቋ ተኮር የክልል አወቃቀር ፖሊሲ ነው ወይ ብለን ብንጠይቅ፣ መልሱ ሌላ ሆኖ እናገኘዋለን። ሕገ መንግሥቱ በትክልል ያስቀመጠው ክልሎች
የክልሉ ተወላጅ ብሔሮች ብቻ ሃብት አለመሆኑን ነው። የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 32(1) በቀላል አማርኛ፣ የክልሉ ተወላጅ ብሔሮች የክልሉ የፖሊቲካ ሥልጣን ባለቤት ናቸው ይላል እንጂ የክልሉ ባላቤት ናቸው አይልም። የፖሊቲካ ሥልጣን ባለቤት መሆን ማለት ደግሞ ከክልሉ ብሔር ተወላጆችና በክልሉ በሕጋዊነት ከሚኖሩ በስተቀር የሌላ ክልል ብሔር ተወላጆች በክልሉ የፖሊቲካና የኤኮኖሚ ሕይወት ጣልቃ መግባት አይችሉም ማለት ነው።
ለ) “ሕዝቦች የየራሳቸውን ክልል ባላቤትነት ለራሳቸው ብሔር ተወላጆች ብቻ አድርገው ከመቁጠራቸው የተነሳ የሌሎች ክልል ብሔር ተወላጆች እንደ ልባቸው እንዳይዘዋወሩና ኑሮአቸውን እንዳይመሠርቱ አድርጓል” ይላሉ። እውነቱ ግን ሌላ ነው። የሕገ
መንግሥቱ አንቀጽ 32(1) በግልጽ ያስቀመጠው እንኳን ኢትዮጵያዊ ዜጋ ይቅርና የውጭ አገር ዜጎች እንኳ ሳይቀሩ በማንኛውም የኢትዮጵያ ክልል ውስጥ ሊኖሩ እንደሚችሉ ሲያረጋግጥ፣
“ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወይም በሕጋዊ መንገድ በሃገሪቱ ውስጥ የሚገኝ የውጪ ዜጋ በመረጠው የሃገርቱ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖርያ ቤት የመመሥረት ነጻነት አለው” ብሎ ይደነግጋል።
የኦሮምያ ክልላዊ ሕገ መንግሥት 34(1) ለምሳሌ፣
“ኢትዮጵያውያን የሆኑ የሌሎች ክልሎች ተወላጆች በዚህ ክልል ውስጥ እንደ ማንኛውም የዚህ ክልል ተወላጅ ሠርቶ የመኖር፣ ከሥፍራ ሥፍራ በነጻ የመዘዋወር፣ ሃብትና ንብረት የማትረፍና የመያዝ መብት አላቸው” ይልና፣
በአንቀጽ 34(2) ሥር ደግሞ፤
የክልሉን የሥራ ቋንቋ የሚያውቅ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ (የክልሉ ብሔር ተወላጅ ያልሆነ ማለት ነው) በማንኛውም የክልሉ መንግሥታዊ ሥራ ውስጥ ተመርጦ ወይም ተመድቦ የመሥራት መብት አለው” ብሎ ይደነግጋል።
የአማራ ክልላዊ ሕገ መንግሥትም በተመሳሳይ መልኩ በአንቀጽ 32 ሥር እንዳስቀመጠው፣
“ማንኛውም የክልሉ ነዋሪ ወይም በሕጋዊ መንገድ በክልሉ ውስጥ የሚገኝ ሰው በመረጠው የክልሉ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖርያ ቤት የመሥራት፣ ሠርቶ የመኖር፣ ሃብት የማፍራትና የመያዝ እንዲሁም በፈለገ ጊዜ ከክልሉ የመውጣት መብት አለው” ይልና፣
በአንቀጽ 33 ሥር ደግሞ፣ “የክልሉን የሥራ ቋንቋ የሚያውቅ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በማንኛውም የክልሉ ሕዝባዊና መንግሥታዊ ሥራዎች ተመርጦ ወይም ተመድቦ የመሥራት መብት አለው” ይላል።
ስለዚህ ዛሬ በአንዳንድ ክልሎች እየተከሰተ ያለው ማንነትን መሠረት ያደረገ የእርስ በርስ ግጭትና ብሎም መገዳደል፣ ምክንያቱ የፌዴራል አወቃቀሩ በክልል መደረጉ ሳይሆን፣ የሕገ መንግሥቱ ቃልና መንፈስ በትክክል ሥራ ላይ ባለመዋሉ ነው። ሕገ መንግሥቱ ቢከበርና በትክክል ቢተገበር ኖሮ፣ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሁሉም ክልሎች በነጻ የመዘዋወርና የመኖር መብት አለውና። ስለዚህ መኮነን ያለብን ሕገ መንግሥቱን ሳይሆን ሕገ መንግሥቱን በትክክል መተግበር ያልቻሉትን ወይም ያልፈለ ገውን መንግሥትንና ተጓዳኝ ተቋማት ብቻ መሆን አለበት። በፍጥረት ለምናምን ሰዎች፣ በማኅበረ ሰብ ታሪክ ውስጥ የመጀመርያዎቹ የመተዳደርያ ደንቦች ለምሳሌ አሥርቱን የአምላካችን ትዕዛዛት፣ ዛሬ ብዙ የክርስትና እምነት ተከታዮች በትክክል በተግባር ሲያዉሉ አይታይም። ሥርቆት፣ ግድያ፣ ማመንዘር ገሃነም የሚያስገባ ጥሰት መሆኑ እየተነገራቸው፣ በምድራችን ላይ፣ አገራችንንም ጨምሮ የሰው ልጆች ዛሬም ይሠርቃሉ፣ ይገድላሉ፣ ያመነዝራሉ ወዘተ። ስለዚህ፣ የሰው ልጆች ሕግጋቱን ጥሰው ስለሚጋደሉና ስለሚሠርቁ ብቻ፣ አሥርቱ ትዕዛዛትን ያቀፈው መጽሃፍ ቅዱስም ፈርሶ ትዕዛዛቱም በሌሎች ሕግጋት ይተኩ ማለት ሕገ ወጥ መሆናችንን ያሳይ እንደው እንጂ ጉድለቱ አሥርቱን ትዕዛዛት ካቀፈው ከመጽሃፍ ቅዱሱ ሊሆን አይችለም። አሥርቱ ትዕዛዛት በሰው ልጆች ተጥሰው ሰዎች ቢገዳድሉ፣ ቢሠራረቁና አመንዝራነት ቢስፋፋ መለወጥ ያለበት የሰው ልጆች ጠባይና ግንዛቤ ነው እንጂ መጽሓፍ ቅዱሱ መሆን የለበትም። መሆን ያለበትና ትክክለኛው አካሄድ፣ የሰው ልጆች ሕግጋቱን ጥሰው ገሃነም እንዳይገቡ ባለ ድርሻ አካላት አንዳች ዓይነት ማሕበረ ሰባዊ መርሃ ግብር ቀርጸው ሕዝቡ አምላካዊ ትዕዛዛትን አክብሮ ወደ ገነት እንዲገባ ይደረጋል እንጂ፣ መጽሃፍ ቅዱስን ኮንኖ ሌላ መጽሃፍ ቅዱስ እንዲጻፍ መወትወት የለበትም ለማለት ነው።
ሐ) ሌላው የሕገ መንግሥቱ ተቃዋሚዎች ደጋግመው የሚያነሱት ጉዳይ፣ በሌሎች አገራት እምብዛም ያልተለመደውን የአንድን ብሔር ተገንጥሎ የራሱን አገር እንዲመሠርት የሚገፋፋ አንቀጽ 39 በሕገ መንግሥቱ ውስጥ መካተቱ ነው። በኔ ግምት፣ አንቀጽ 39 የኢትዮጵያ ሕዝቦች አንዳቸው ሌላውን ሳይጨቁኑ በእኩልነት እንዲኖሩና፣ አንደኛው ግን በሌላኛው ተጨቁኜያለሁ፣ መብቴ ተጥሷል፣ አብሬ በእኩልነት ለመኖር የሚያስችለኝ ዕድል ተሟጥጦ አልቆአል ካለ የመገንጠል መብቱ እንደተጠበቀለት ዋስትና እንዳለው ለማስረገጥ እንጂ አገር እንድትከፋፈል ተብሎ የተካተተ አይደለም። በታኅሳስ 1992 ዓ/ም በጸደቀው የኢትዮጵያ የቤተሰብ ሕግ ውስጥ ላምሳሌ፣ ለአንድ ትዳር መፋታት ሁለቱም ወገኖች በእኩል ደረጃ የፍቺ ጥያቄ ለፍርድ ቤት ለማቅረብ የመቻል መብት የሚያረጋግጡ አንቀጽ 76 እና 81(1) መካተታቸው “መብቴ ተጥሶብኛል፣ ተፋትቼ የራሴን የወደ ፊት ዕድል ራሴ እውስናለሁ” ብሎ ለመወሰን ሴቲቷም ከወንድ እኩል የፍቺ ጥያቄ ለማቅረብ ለመቻሏ ዋስትና ለመስጠትና ባልየው ሚስቲቱ ከሱ ተፋትታ የራሷን ዕድል በራሷ የመወሰን መብት እንዳላት አውቆ መብቷን ከመጣስ እንዲቆጠብ ታስቦ እንጂ የኢትዮጵያውያንን ትዳር ለማፈራረስ አይደለም። በዚያው ልክ፣ ከታሪክ እንደምንረዳው፣ አንድ ብሔር ተገንጥሎ የራሱን ግዛት ለመፍጠር ከፈለገ በግድ የሕገ መንግሥቱን መሥፈርት ተከትሎ ጉዳዩን ለፌዴራሉ ፓርላማ ማቅረብ የለበትም። በጉልበትም ሕገ መንግሥቱን ጥሶ የራሱን አገር መመሥረት ይችላል። ኤርትራ ከኢትዮጵያ ተገንጥላ የራሷን አገር የመሠረተችው የሕገ መንግሥቱን መሥፈርት አሟልታና አንቀጽ 39ን ተጠቅማ ሳይሆን በራሷ ወታደራዊ ጥንካሬ ብቻ ነው። ስለዚህ የአንቀጽ 39 በሕገ መንግሥቱ ውስጥ መካተቱ ዛሬ በማንነት ላይ በተመሠረቱ አለመግባባቶች እየተከሰተ ላለው የእርስ በርስ ግጭቶች አንዳችም አስተዋጽዖ አላበረከተም ባይ ነኝ።
ሕገ መንግሥቱ ከጸደቀበት ጊዜ ጀምሮ ማለትም ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ውስጥ ለምሳሌ አንቀጽ 39ን አንስቶ ለመገንጠል ጥያቄ የቀረበ አንድም የኢትዮጵያ ብሔር ወይም ክልል የለም። በየጊዜው የተነሱ ተቃዋሚ ቡድኖችም ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው እንዲጠበቅላቸው እንጂ አንዳቸውም የመገንጠልን ጥያቄ አላቀረቡም። ለምሳሌ፣ የኦሮሞ ቄሮዎች አንድም ጥይት ሳይተኩሱ የተሰካ ሰላማዊ ትግል አካሄደው ሕወሃት ወራሹን መንግሥት ሲገረስሡ “ሕገ መንግሥታዊ መብታችን ይጠበቅ” “የኦሮሞ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በተመረጡ ሕጋዊ ተውካዮቹ ይተዳደር” ነበር እንጂ ያሉት፣ በትግሉ ሂደት ውስጥ 5000 ወጣቶች ተሠውተባቸውም፣ አንድም ቦታ ላይ የመገንጠል ጥያቄ ኣላነሱም። ዛሬም የትጥቅ ትግል እያካሄደ ያለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፣ በፌዴራል ኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ማዕቀፍ ውስጥ ለድርድር ሲቀመጥ፣ ዓላማው ሕገ መንግሥታዊ መብትን
ለማስከበር እንጂ ለመገንጠል አይደለም። ኦነግም ከ1991 ወዲህ አንድም ጊዜ የመገንጠል ጥያቄ አላነሳም፣ በሕገ መንግሥቱም መሠረት በምርጫ ቦርድ ተመዝግቦና ሕጋዊ ሰውነት አግኝቶ ዛሬም በሰላማዊ መንገድ እየታገለ ይገኛል። ፋኖም “የአማራ ሕዝብ ለጥቃት ተዳርጓል” እና ሕገ መንግሥታዊ መብቱ ይከበርለት ነው እንጂ የሚለው፣ የአማራ ሕዝብ/ክልል ከኢትዮጵያ ተገንጥሎ የአማራን ሬፑብሊክ ይመሠርት ብሎ አንድም ቦታ ላይ የመገንጠል ጥያቄን ሲያነሱ አይሰተዋልም። ሕወሓትም ወደ ነበርኩበት የፖሊቲካ ሥልጣን ከፍታ ልመለስ ብሎ ከመንግሥት ጋር ተጋጨ እንጂ የመገንጠልን ጥያቄ አላነሳም። የኦጋዴን
ነጻ አውጭ ድርጅትም እንደዚሁ። የነጻ አውጪ ድርጅቶች በተለይም ኦነግና ሕወሓት በ1991 ዓ/ም የደርግ መንግሥትን ገርስሠው የፖሊቲካ ሥልጣን ሲረከቡ፣ ፍላጎቱ ቢኖራቸው ኖሮ እንወክለዋለን የሚሉትን ሕዝብ ይዘው ከኢትዮጵያ ተገንጥለው የየራሳቸውን ነጻ አገር ከመመሥረት የሚያግዳቸው አንዳችም ምድራዊ ኃይል አልነበረም። ግን አላደረጉም።
መ) ሕገ መንግሥቱ፣ ከጥንስሱ ጀምሮ በአንድ ሕዝብ ላይ ያነጣጠረና ያንን ሕዝብ ለመጉዳት ታስቦ የተዘጋጀና ሂደቱ ሁሉንም አካታች ስላልሆነ፣ መፍረስ አለበት የሚሉ ወገኖች አሉ። በዚህ ጉዳይ ላይ፣ ከጥቂት መኃይም ኤሊቶች፣ ከዩቲዩብና ቲክቶክ ፖሊቲከኞች አደዳቢ ክርክርና ጽሁፍ ሌላ ሕገ መንግሥቱ በአንድ ብሔር ላይ ያነጣጠረ ለመሆኑ አንዳችም ማረጋገጫ የለም።
የሕገ መንግሥቱ 107 አንቀጾች ውስጥ አንድም ቦታ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አንድን ብሔር በስም ጠርቶ ዛሬም ሆነ ጥንት ለተከሰተው ማኅበራዊና ፖሊቲካዊ ቀውስ ተጠያቂ ያደረገበት አንቀጽ የለም። በቅንነት አባባሌን በውል ለመረዳት በጉዳይ እየተቆረቆሩ ያሉ ወገናት ሕገ መንግሥቱን እንዲያነቡ እየጠየቅሁ፣ በደፈናው ግን፣ የሕገ መንግሥቱን ቃልና መንፈስ ለመረዳት የሕገ መንግሥቱን መግቢያ እንደሚከተለው ጠቅሼ አስቀምጫለሁና አንድም ቦታ ላይ ቃሉም ሆነ መንፈሱ በአንድ ብሔር ላይ አለማነጣጠሩን አንብባችሁ ተረዱት፣
እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረ ሰቦችና ሕዝቦች፣
“በሃገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላም፣ ዋስትና ያለው ዲሞክራሲ እንዲሰፍን ኤኮኖሚያዊና ማኅበረ ሰባዊ እድገታችን እንዲፋጠን የራሳችንን ዕድል በራሳችን የመወሰን መብታችንን ተጠቅመን በነጻ ፍላጎታችን፣ የሕግ የበላይነት እና በራሳችን ፈቃድ ላይ የተመሠረተ አንድ የፖሊቲካ ማኅበረ ሰብ በጋራ ለመገንባት ቆርጠን በመነሳት፣
ይህን ዓላማ ከግብ ለማድረስ የግለሰብና የብሔር/ብሔረሰባዊ መሠረታዊ መብቶች መከበራቸው፣ የጾታ እኩልነት መረጋገጡ፣ ባሕሎችና ኃይማኖቶች ካለ አንዳች ልዩነት እንዲራመዱ የማድረጉ አስፈላጊነት ጽኑ እምነታችን በመሆኑ፣
ኢትዮጵያ አገራችን የየራሳችን አኩሪ ባሕል ያለን፣ የየራሳችን መልክዓ ምድር አሰፋፈር የነበረንና ያለን፣ ብሔር ብሔረ ሰቦችና ሕዝቦች በተለያዩ መስኮችና የግንኙነት ደረጃዎች ተሳስረን አብረን የኖርንባትና የምንኖርበት አገር በመሆንዋ፣ ያፈራነው የጋራ ጥቅምና አመለካከት አለን ብለን ስለምናምን፣
መጪው የጋር ዕድላችን መመሥረት ያለበት ከታሪካችን የወረስነውን የተዛባ ግንኙነት በማረምና የጋራ ጥቅማችንን በማሳደግ ላይ መሆኑን በመቀበል፣
ጥቅማችንን መብታችንና ነጻነታችንን በጋራ እና በተደጋጋፊነት ለማሳደግ አንድ የኤኮኖሚ ማኅበረ ሰብ የመገንባቱን አስፈላጊነት በማመን…….. ይህንን ሕገ መንግሥት አጽድቀናል ይላል። (ሥርዝ የኔ)
ከላይ በጠቀስኩት የሕገ መንግሥቱ መግቢያ ውስጥ የተካተተው “ከታሪካችን የወረስነውን የተዛባ ግንኙነት” የሚለው አባባል፣ ሕገ መንግሥቱ በአንድ ብሔር ላይ አነጣጣሮአል ለሚሉ ወገኖች እንደ ማሳመኛ ሰበብ እንደሚቀርብ ብዙ ጊዜ ይስተዋላል። አባባሉ በርግጥ በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል የነበረው ግንኙነት የተዛባ መሆኑን ይገልጻል። በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል የነበረው ግንኙነት ደግሞ በርግጥም የተዛባ መሆኑን ቀደም ብዬ ያቀረብኳቸው አሳማኝ ታሪካዊ ማስረጃዎች ስለነበሩ፣ ሕገ መንግሥቱ ውስጥ ግንኙነቱ የተዛባ መሆኑን መግለጹ በአንድ ብሔር ላይ ያነጣጠረ ነው ማለት ሆን ብሎ ለሆነ የፖሊቲካ ግብ ማሳካት ከማለት ሕዝቦችን ለማወናበድ ጽንፈኛ ኤሊቶች በየጎጣቸው የፈበረኩት ርካሽ ሸቀጥ ይመስለኛል። በኔ ግምት እንኳን ያኔ፣ ዛሬም ቢሆን ከሕገ መንግሥቱ ቃላትና መንፈስ ውጭ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ግንኙነት ያልተዛባ ነው ብሎ ለመናገር የሚቻል አይመስለኝም።
መ) “ሕገ መንግሥቱ ሲቀረጽም ሆነ ሲጸድቅ የኔ ብሔር ተወካዮች አልተካፈሉበትም፣ ስለዚህ ሕገ መንግሥቱ በኛ ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት የለውምና እንዳለ ተሠርዞ አዲስ ሕገ መንግሥት ይቀረጽ” ይላሉ የአንዳንድ ብሔር ኤሊቶች። ቅሬታቸው በተወሰነ መልኩ እውነትነት አለው። ግን ደግሞ፣ የሕገ መንግሥቱን ቀረጻና ማጽደቅ ሂደትን የመራው የኢሕአዴግ መንግሥት ራሱ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ያልተመረጠና ማንንም የማይወክል ስለሆነ፣ ሕገ መንግሥቱን ለማርቀቅና ለማስጸደቅ የመለመላቸው ግለ ሰቦች በሕዝብ የተመረጡ መሆን ነበረባቸው ብሎ መከራከር ደግሞ ከእባብ ዕንቁላል እርግብ የመጠበቅ ያህል ነው። በያኔው ሂሳብ፤ ወያኔ መራሹ መንግሥት፣ ልክ እንደ ፊተኞቹ የኢትዮጵያ መሪዎች፣ አስቀድሞ ባስቀመጠው መሥፈርት መሠረት ከሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ተወካዮችን ራሱ መርጦ አዲስ አበባ ድረስ አስመጥቶ በማርቀቁና በማጸደቁ ላይ አሳትፏቸዋል። ከታሪክ ሰነድ የምንረዳው፣ የአመራረጥ ሂደቱ ግልጽ አይደለም እንጂ፣ ኅዳር 29 ቀን 1987 ዓ/ም ሕገ
መንግሥቱን በማጽደቅ ሥነ ሥርዓት ላይ ለምሳሌ የአማራ ክልል (ጎንደር፣ ወሎ፣ ጎጃም እና ሰሜን ሸዋ) በ182 ሰዎች ሲወከል፣ ከተካፋዮቹ አንዱ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አለነ የደላንታን የምርጫ ወረዳ ወክለው በበዓሉ ላይ ተገኝተዋል። ስለሆነም፣ ሕገ መንግሥቱ የረቀቀውና የጸደቀው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ራሳቸው በወከሏቸው ግለ ሰቦች ሳይሆን ኢሕአዴግ በራሱ መሥፈርት መሠረት በመረጣቸው መጽደቁ ነው እንጂ ሕገ መንግሥቱን በማርቀቅና በማጽደቅ ሂደት ውስጥ ያልተካፈለ የኢትዮጵያ ሕዝብ/ብሔር ነበረ ብሎ መከራከር ትክክል አይመስለኝም።
መደምደምያ
አንድ ምሑር፣ በተለይም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተውና የዚያው ማኅበረ ሰብ አባል የሆነ ለዚያውም ፊደል የቆጠረ ሰው፣ የፖሊቲካና ማኅበረ ሰባዊ ቀውስን አስመልክቶ በወቅቱ በሚካሄደው የመፍትሔ ፍለጋ ውይይት ላይ ተካፍሎ መተቸት፣ መቃወም ወይም መደገፍ ያለበት፣ ያኔ ማኅበረ ሰባዊ ጥያቄው ለውይይት በቀረበበት ጊዜ፣ ቦታና ሁኔታ ነው እንጂ፣ የማኅበረ ሰቡ ጉዳይ የሆነ መፍትሔ ከተገኘለት ከአምሳ ዓመት በኋላ፣ ወደ ኋላ ተመልሶ፣ ለችግሩ መፍትሔ ፍለጋ ሲዋትቱ የነበሩበትን ማኅበረ ሰባዊ ለውጥ ፈላጊዎችንና የመፍትሔ ሃሳባቸውን ዛሬ ላይ ሆኖ መንቀፍ የምሑር አድር ባይነትን ጎልቶ የሚያሳይ ስለሆነ፣ ዶ/ር ኃይሌን ክፉኛ እወቅሳቸዋለሁ።
ዶ/ር ኃይሌ፣ እስቲ ጠበቅ አድርጌ ልጠይቅዎት፣
የኢትዮጵያ ተማሪዎች በአውሮፓና በአሜሪካ ተደራጅተው የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ ለማጥናትና ለነበረው ማኅበራዊ፣ ኤኮኖሚያዊና ፖሊቲካዊ ቀውስ ሁለንተናዊ መፍትሄ ይሆናሉ በሚሏቸው ሃሳቦች ላይ ሲወያዩና የትግል ዓላማቸውን ሲቀይሱ፣ እስዎ እዚያው በአውሮፓ በጣሊያን ከተማ፣ ያውም የኢሕአፓ አመራር አባል የነበሩ ግለሰቦች ይማሩበት በነበረበት ዩኒቬርሲቲ ተማሪ የነበሩ የያኔው ትውልድ አባላት እያሉ እስዎ እንዴት የተማሪው እንቅስቃሴ አባል ወይም ደጋፊ ሳይሆኑ ቀሩ የሚለውን ጥያቄ ማንሳት አግባብ ያለው ይመስለኛል። በካቶሊክ ዩኒቬርሲቲው ይማሩ የነበረው መለኮታዊ የትምሕርት ዘርፍ የያኔው ትውልድ አንግቦ ይንቀሳቀስ የነበረውን የትግል ዓርማ እንዳይደግፉ ወይም አባል እንዳይሆኑ አድርጎዎታል እንዳይባል በዚያው እርስዎ ይማሩ በነበሩበት ዩኒቬርሲቲ ተመሳሳይ ኮርስ ላይ የነበሩ ግለሰቦች በኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ኋላም የፓርቲዎች አመራር አባል ሆነው ሠርተዋል። እስዎ አባል ወይም ደጋፊ እንኳ ባይሆኑ፣ በጊዜው የነበረውን የተማሪዎቹን የትግል ዓላማቸውን ለማሳካት፣ መስተካከል አለባቸው ብለው በሚገምቱት ጉዳዮች ላይ (ለምሳሌ የመሬት ላራሹና የብሔር ጥያቄዎችን በተመለከተ) በታጠቅና ትግላችን መጽሔቶቻቸው ላይ በሰፊው ሲጽፉና በየሰላማዊ ሰልፉ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ሲያዉጁ፣ እስዎ ወይ በስብሰባቸው ላይ ተገኝተው አለያም ደግሞ በነዚህ መጽሔቶቻቸው በኩል፣ ለኢትዮጵያ የሚበጃት ታጋዮቹ ያነሷቸው የነበሩትን የመፍትሔ ሃሳቦችን ተቃውመው የራስዎን የመፍትሔ ሃሳብ ለምን አላቀረቡም? ለምንስ ተማሪዎቹ ያኔ አንገብጋቢ ናቸው ብለው ያነሷቸው የነበሩ አገራዊ ጉዳዮችን ለመረዳት አምሳ ዓመት ፈጀብዎት? እርስዎ የማኅበረሰቡን ፖሊቲካዊ፣ ኤኮኖሚያዊና ማኅበረ ሰባዊ ቀውሶችን ይፈታሉ ተብለው የሚቀርቡ ሃሳቦችን መቃወምም ሆነ መደገፍ የሚያምረው ያኔ ጥያቄዎቹ አስፈላጊ በሆኑበት ወቅትና ቦታ መሆኑን እያወቁ፣ ጥያቄውም መፍትሔ አግኝቶ የጥያቄው አራማጆችም በአካል ከዚህ ምድር ከተለዩ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በኋላ ጥያቄውንም ሆነ ለጥያቄው መፍትሔ ለማግኘት በተደረገው እልህ አስጨራሽ ጦርነት ሂደት ውስጥ የተሰው የያኔን ትውልድ አባላት ወቅሶ፣ ራስዎን ግን “አገር ወዳድ” አስመስሎ ማቅረብ ጥያቄውንና ጠያቂዎቹን በጅምላ ማውገዝ አንድም አድርባይነት ብሎም አረመኔነት አይመስልዎትም?
የመሬት ዓዋጁን አስፈላጊነት በአዲስ አበባና በተለያዩ የውጭ አገር ዩኒቬርሲቲ መድረኮች ላይ የኢትዮጵያን ዕድገት ይመኙ
የነበሩ ተማሪዎች ውይይት ሲያደርጉ በነበረበትና በ1975 ዓም ደግሞ የተመኙት ዓዋጅ በተግባር ሲተረጎም፣ እስዎ ባጣሊያን አገር የማስትሬት ዲግሪዎን አግኝተዋል። ያኔ እንደኔ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዎች የነበርን ልጆች አብዛኞቻችን ማኅብረሰባዊውንና ፖሊቲካው ቀውሱን በደንብ ለመረዳት ብቃት ስላልነበረን የፖሊቲካ አቋማችንን እንወስን የነበረው በብስለት መንፈስ ሳይሆን በጓደኝነት ወይም በትውውቅ ነበር። እርስዎ ግን ከኛ ከጩጬዎቹ እጅግ በጣም የላቀ የትምሕርት ደረጃ የነበረዎት፣ ከፊውዳሉ ኢትዮጵያ ውጪ ዲሞክራሲ ባደገበት አገር ለዘመናት የኖሩ ግለሰብ ስለሆኑ፣ ይህን ሁሉ ዕውቀት ያካበቱ የኢትዮጵያ ምሑር ያኔ በወቅቱ በቦታው የድጋፍም ሆነ የታቃውሞ ድምጽዎን ለማሰማት ያገደዎ ነገር ምን ነበር?
እራስዎ በማኅበራዊ ሚዲያ ባሰፈሩት የግል ታሪክ መረጃ (BIO DATA) መሠረት፣ የመጀመርያ ዲግሪዎን ከሮማ የካቶሊክ ዩኒቬርሲቲ የተቀበሉት በ1965 ዓ/ም (በፈረንጆች አቆጣጠር በ1973 ዓ/ም) የኢትዮጵያ አብዮት ከመፈንዳቱ ከአንድ ዓመት
በፊት ነው። የሁለተኛ ዲግሪዎን ከዚያው ዩኒቬርሲቲ በ1967 ዓ/ም (በፈረንጆች በ1975 ዓ/ም) እንደ ተቀበሉ መረጃው ያመለክታል። የኢትዮጵያ ተማሪዎች በአገር ውስጥና በውጭ አገር በግልም ሆነ ተደራጅተው የታገሉለት የመሬት ላራሹ ጥያቄ መፍትሔ ያገኘበት ሥር ነቀሉ የኢትዮጵያ የመሬት ዓዋጅ በታወጀበት ዓ/ም ነው እስዎ የማስትሬት ዲግሪዎን ያገኙት።
በያኔውም ሆነ ባዛሬው ስሌት፣ የ1975ቱ የመሬት ዓዋጅ ሲታወጅ፣ እስዎ እጅግ በጣም ልቀው ከተማሩ ጥቂት የኢትዮጵያ ልጆች አንዱ ነበሩ ማለት ነው። የዩኒቬርሲቲ ትምህርትዎንም ከመጀመርያው ጀምሮ የተከታተሉት በአውሮፓ ስለሆነና አውሮፓ ደግሞ አንጻራዊ ዲሞክራሲ የሰፈነበትና ማንኛውም ግለ ሰብ ሃሳቡን ያለ አንዳች ገደብ በነጻ የሚገልጽበት፣ ልዩነቶች በውይይት ብቻ እንጂ በጠብመንጃ የማይፈቱበት አህጉር ስለሆነ፣ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ስለ ኢትዮጵያ ችግር መፍትሔ ይሆናል ብለው የነደፉትን ፍኖተ ካርታ በተመለከተ፣ እርስዎ የድጋፍም ሆነ የተቃውሞ ሃሳብዎን የመሠንዘር ያልተገደበ መብት ነበረዎት ማለት ነው። በጊዜው “የያኔው ትውልድ” የተማረውን ክፍል የተለያዩ ሃሳቦችን ያስተናግድበት በነበረው የ “ታጠቅ” እና የ “ትግላችን” መጽሔቶች ላይ ግን እስዎ አንድም ጊዜ በወቅቱ የኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ሃሳብዎን የሰነዘሩበት አሻራ አይታይም። “የያኔው ትውልድ” አባላት አንግበው ይታገሉለት የነበረው የመደብና የብሔር ጭቆና ጥያቄዎቹ ይዘት አልገባዎት ይሆናል እንዳይባል፣ ተወልደው ያደጉት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። እንኳን በእስዎ ደረጃ የተማረ ይቅርና እኛ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችም በግል ተሞክሮም ይሆን በጓደኞቻችን ቅስቀሳ ምክንያት የጥያቄዎቹን ይዘት በተወሰነ ደረጃ ተረድተን እንደየአቅማችን ሌሎችን ጓደኞቻችንን እንቀሰቅስ ስለ ነበር እስዎ ጉዳዩ አልገባዎትም ለማለት በጣም ያዳግታል።
ብዙዎች የያኔው ትውልድ አባላት ልክ አብዮቱ እንደ ፈነዳ ትምሕርታቸውን እንኳ ሳይጨርሱ በመሃል አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ እስዎ ግን ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ባመኑበት መንገድ እና ለሕዝቡ ጠቃሚ ነው የሚሉትን አሳብ (ከነበረዎት ብዬ ነው) በተግባር መተርጎምን ትተው የፒኤች ዲግሪዎን አግኝተው የግል ሕይወትዎን ለማሻሻል ወደ ሎንደን አቀኑ። የፒኤች ዲግሪዎን ካገኙ በኋላም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው፣ ይቺ እርስዎ ዛሬ እንደዚያ በሚኮንኗቸው “ትውልድ ምክንያት” ቀውስ ላይ ለነበረችው ውድ አገርዎ ተመልሰው፣ ከፖሊቲካ ነጻ ሆነው የሚወዷትን የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙያዎ ለምን ለማገልገል አልፈለጉም? ያኔ ራዕይዎ በውጭ አገር በቀሰሙት ዕውቀት ያስተማረዎን ሕዝብ ችግር ለመቅረፍ ከመሞከር የግል ሕይወትዎን ለማሻሻል ወደ አሜሪካ አገር አምርተው ማስተማር ጀመሩ። ዛሬም እነዋለልኝን የሚኮንኑት ከዚያው ተደላድለው ከሚኖሩበት ከአሜሪካ አገር መሆኑ፣ ለአገራችን ያለዎት ፍቅር ምንኛ የላይ ላይ ለመሆኑ አመላካች ሆኖ አይታይዎትም?
በኔ ግምት፣ ዶ/ር ኃይሌ፣ እስዎ ስለ ኢትዮጵያ ሕዝብ ችግር ምንም አያገባኝም ብለው በትምሕርትዎ ልቀው መገኘትን ያስቀደሙ ግለ ሰብ ነበሩ። ትምሕርትዎን በዶክትሬት ደረጃ እንኳ ካጠናቀቁ በኋላ ቀሪውን የሕይወት ዘመንዎን ያለ አንዳች ሃሳብ በደስታና በተድላ ለመኖር ወደ አሜሪካ ማቅናት መረጡ እንጂ የያኔው ትውልድ አባላት ግልብጥ ብለው ተመልሰው ለእናት አገራቸው የቀየሱትን ፍኖተ ካርታ በተግባር ለመተርጎም ከተቃራኒ ኃይላት ጋር ትንቅንቅ ላይ ወዳሉበት ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ አልፈለጉም። ይህም ተፈጥሮያዊ መብትዎ ነው። ተፈጥሮያዊ የማይሆነው ግን፣ ዛሬ እንደሚሉት ያኔም የኢትዮጵያ ፍቅር ከነበረዎት፣ በዚያች በቀውጢ ሰዓት ኢትዮጵያን ዓይንሽ ላፈር ብለው ወደ አሜሪካ መፈርጠጥዎ ነው። ከአምሳ ዓመት በኋላ ዛሬ ላይ ቆመው የያኔው ትውልድ አባላት፣ የግል ኑሮያቸውን የማሻሻል ጉዳይ ወደ ጎን አድርገው፣ ይኖሩ የነበሩባቸውን አገር ዜግነት ይቅርና ቋሚ የመኖርያ ፈቃድ እንኳ መውሰድ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የነበራቸውን ፍቅርና የትግል እንቅስቃሴያቸውን ያዳክምብናል ብለው ያስቡ በነበረበት ወቅት፣ እርሶዎ በተመሳሳይ ቦታ የነበሩ ግለ ሰብ፣ የሕይወት ዓላማዎ የዶክትሬት ዲግሪ አግኝቶ የግል ሕይወትዎን ለማሻሻል ብቻ ይጥሩ ስለ ነበር፣ የያኔው ትውልድ አባላት ስለ ኢትዮጵያና ስለ ኢትዮጵያ ሕዝብ የነበራቸውን ፍቅር እንኳን ለማጥላላት ቀርቶ ለማሞገስም ቅንጣት ታህል የሞራል ብቃት የለዎትም ባይ ነኝ።
ግን እስዎ፣ በዚያች በቀውጢ ሰዓት ያገራችን ሕልውናና የወደፊት ዕጣ ፈንታዋ ከተለያዩ ጎራዎች ጥቃት ሲፈጸምባት፣ ዝምታንና ገለልተኝነትን መረጡ። ዝምታና ገለልተኝነት ደግሞ አድርባይነት ነው። ስለዚህም ነው የዕድሜ እኩዮችዎ የፍትሕና ዲሞክራሲን ጥያቄ አንስተው በቆራጥነት ከሕዝባቸው ጎን ቆመው ለመታገል የከፈሉትን መሥዋዕትነት እርስዎ ዛሬ በባዶ ሜዳ እነዚያን ምርጥ የኢትዮጵያን ልጆች መኮነንዎ ጥግ የረገጠ አድር ባይነት ነው ብዬ የምኮንንዎ። “ጆሮ ያላት ውሻ እንኳ ሊጤን በበላችብኝ ኖሮ” አለች አሉ ጆሮ የሌላት ውሻ ሊጧን የበላችባት ሴትዮ! አገር ወዳድ የኢትዮጵያ ልጆች ውድ ሕይወታቸውን ሲከፍሉ እስዎ ድምጽዎን አጥፍተው የግል ኑሮዎን ሲያዳብሩ የቆዩ ምሁር፣ ዛሬ ላይ ቆመው ያንን ቆራጥ ትውልድ ለመኮነን ሲሞክሩ ማየቱ እውነትም ጋኖች አለቁና ምንቸቶች ጋን ሆኑ ያሰኛል። ምንቸት ደግሞ ምን ጊዜም ምንቸት ነው። ጋን ሆኖ አያውቅም! ሊሆንም አይችልም።
********
- ጸሃፊው ቀድሞ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለ ሥልጣን የነበሩ የዓለም ዓቀፍ ሕግ ባለ ሙያ ናቸው።
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 2025 ዓ/ም
WAKWOYA2016@GMAIL.COM