በፈተና የታጀበው ታላቁ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ድል
በፈረንጆቹ ሐምሌ 3፣ 2025 ዓ.ም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ግዙፍ የሆነውን እና በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ደግሞ ታላቅ ሊባል የሚችለውን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ (GERD) አጠናቅቃለች። በጥቁር ዓባይ ወንዝ በላይ የተገነባው የህዳሴ ግድብ 5,150 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው ሲሆን፣ ይህም ከሁቨር ግድብ ጋር የሚስተካከል እና ለመጪው ጊዜ የአፍሪካ ኃይል ፍላጎት መሟላት ኢትዮጵያን ግንባር ቀደም ሀገር ያደርጋታል።
የታላቁን ህዳሴ ግድብ የበለጠ ልዩ የሚያደርገው ግዝፈቱ ብቻ ሳይሆን ግንባታውን ለማጠናቀቅ ያስፈልግ የነበረው የገንዘብ ምንጭ እና የግድቡ የግንባታ ሂደት ነው። የህዳሴ ግድብ በአፍሪካ ከሚገኙ ሌሎች መጠነ-ሰፊ የልማት ፕሮጀክቶች በተለየ፣ ከዓለም ባንክ፣ ከዓለም የገንዘብ ድርጅት ወይም ከሌሎች ዓለም አቀፍ ለጋሾች የገንዘብ ድጋፍ አልተደረገለትም። ይልቁንም የኢትዮጵያ ሕዝብ በራሱ አበርክቶ ከመንግስት ላይ ቦንድ በመግዛት፣ ከወርሃዊ ደመወዝ ላይ ተቀናሽ በሚደረግ መዋጮ እና ከሕዝብ በሚሰበሰብ የገንዘብ ድጋፍ የገነባው ነው። ለብዙዎች፣ ግድቡ ከሲሚንቶ ግብዓት እና ከኃይል ማመንጫ ተርባይኖች ያለፈ ትርጉም አለው። የብሔራዊ ኩራት፣ የሉዓላዊነት እና የጋራ ቁርጠኝነት ምልክት ነው።

ይሁን እንጅ፣ ይህ ትልቅ እና የብሔራዊ ህልም መገለጫ የሆነው ሐውልት በኢትዮጵያ ውስጥ እየተከሰተ ባለው ውስጣዊ አለመረጋጋት ለከፍተኛ ችግር የተጋለጠ ነው ለማለት ይቻላል። ፕሮጀክቱ ይዞት የመጣው ብሔራዊ ተቃርኖ ግልጽ ነው፤ የህዳሴው ግድብ ብሔራዊ አንድነትን ለማምጣት የተገነባ ፕሮጀክት ቢሆንም፣ ግድቡን በበላይነት የተቆጣጠረው ኃይል ግን ኢትዮጵያና ሕዝቧን ለክፍፍል የሚዳርግ የፖለቲካ ስርዓትን ገንብቷል። የምህንድስና ድል የፖለቲካ ውድቀትን ሊተካ አይችልም። ራዕይ በሌለው አመራር እና ዘላቂ ሠላም ማግኘት ባልቻለች ሀገር ውስጥ፣ የህዳሴው ግድብ ምንም ያህል የኤሌክትሪክ ኃይል ቢያመነጭ ብሔራዊ አንድነትን፣ ሀገራዊ መረጋጋትን እንዲሁም ብልጽግናን ማምጣት ስለማይቻል ግድቡ ትርጉም የሌለው ሐውልት የመሆን አደጋ ተጋርጦበታል ማለት ይቻላል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የጠንካራ ሕልም ምልክት
የህዳሴው ግድብ የኢትዮጵያን ታሪካዊ አይበገሬነትን የሚያመላክት ነው። ኢትዮጵያ ለብዙ አሥርተ ዓመታት እንደ ግብፅ እና ሱዳን ያሉትን የታችኛው የዓባይ ወንዝ ተፋሰስ ሀገራትን ጥቅም ብቻ በአድሎአዊነት በሚያስጠብቅ በቅኝ ግዛት ዘመን የውሃ ስምምነቶች ተገድባ ኖራለች። ግድቡን መገንባት ደማቅ የሉዓላዊነትን ማረጋገጫ እርምጃ ተደርጎ የሚታይ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በራሷ ግዛት ውስጥ የሚመነጩ የውሃ ሀብቶችን የመጠቀም መብት እንዳላት የሚያረጋግጥ መገለጫ ነው።
ከቴክኒካል ሁኔታዎች አንፃር ሲታይ፣ ግድቡ ብሔራዊ ድል ነው። እ.ኤ.አ. በ2025 አጋማሽ፣ ወደ 3,400 ሜጋ ዋት የሚጠጋ ኃይል እያመነጨ ሲሆን ይህም ከኢትዮጵያ አጠቃላይ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ውስጥ አንድ ሦስተኛውን ይሸፍናል። ከአገር ውስጥ ጥቅሞች በተጨማሪ ኢትዮጵያ ለኬንያ እና ለጅቡቲ ኤሌክትሪክ መላክ የጀመረች ሲሆን በየዓመቱ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ታገኛለች። ትንበያዎች እንደሚጠቁሙት የወደፊት ገቢ በዓመት እስከ 2 ቢሊዮን ዶላር ሊደርስ እንደሚችል የሚጠበቅ ሲሆን፣ ይህም የኤሌክትሪክ ኃይል ከቡና በመቀጠል እጅግ ጠቃሚው የኢትዮጵያ የኤክስፖርት ምርት ያደርገዋል።
ግድቡ የስነ ልቦና ክብደትም አለው። የህዳሴ ግድብ “ትውልድ ተሻጋሪ ትሩፋት” ተብሎ መገለጹም ኢትዮጵያውያን ሲተባበሩ ታላቅ እምርታን ማምጣት እንደሚችሉ የሚያሳይ ነው። የህዳሴ ግድብ በብዙ መልኩ፣ ከድህነት ለመውጣት እና የቀጠናው ኃያል ለመሆን የሚያስችል የብሔራዊ ምኞት ምልክት መሆን የሚችል የሚዳሰስ ምልክት ነው። ነገር ግን ምኞት ብቻውን ስኬትን አያረጋግጥም።
በጅምር የቆመው ብሔራዊ ቃልኪዳን እና ዛሬም በጨለማ ውስጥ ያለችው ሀገር
ምንም እንኳን የህዳሴው ግድብ ከፍተኛ አቅም ያለው ፕሮጀክት ቢሆንም፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ዛሬም ድረስ በጨለማ ውስጥ ይኖራሉ። እ.ኤ.አ. በ2025፣ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያገኘው ዜጋ ከአጠቃላይ ሕዝቡ ግማሽ የሚሆነው ወይም ከ44 እስከ 55 በመቶ የሚሆነው ብቻ ነው። ይህም ማለት ከ70 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው ሕዝብ የኤሌክትሪክ አቅርቦት አያገኝም ማለት ሲሆን፣ እንዲያም ሆኖ ግን ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ለውጭ ሀገራት ታቀርባለች።
ይህ ሁኔታ ግልጽ የሆነ ተቃርኖ የሚያሳየን ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትልቅ ግድብ እያላት በገጠር የሚኖረው የሕዝብ ክፍል ግን በማገዶ እንጨት በማብሰል እና የሻማ ብርሃንን በመጠቀም ህይወቱን ይገፋል። የዚህ ችግር ምክንያት ከኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ጋር ሳይሆን ከኃይል ስርጭት ጋር የተያያዘ ነው። የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮች እና የገጠር ኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ፕሮጀክቶች ወደ ኋላ በመቅረታቸው ምክንያት የኢትዮጵያ ሰፋፊ ክልሎች ሳይቀር ከብሔራዊ የኤሌክትሪክ ማማዎች ጋር እንዳይገናኙ አድርጓል።
ይህ ግልፅ ክፍተት ባለበት ሁኔታ መንግሥት በክርፕቶከረንሲ (cryptocurrency) ማዕድን ማውጣት ላይ ለተሰማሩ አካላት ትርፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ ውሳኔ በማሳለፉ ምክንያት ከኃይል አቅርቦት ጋር ለተያያዙ ቅሬታዎች መፈጠር ምክንያት ሆኗል። ይህ ችግር ከፍ ሲል ደግሞ፣ በኢትዮጵያ ዝቅተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ወጪን ታሳቢ ያደረጉ የክሪፕቶ ኩባንያዎች ከሀገሪቱ ኃይል አንድ ሦስተኛውን ያህል እንዲጠቀሙ አስችሏቸዋል። ይህ ሁኔታ የአጭር ጊዜ የውጭ ምንዛሪ ገቢን የሚያስገኝ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያውያን ያለ ኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት በጨለማ ውስጥ እንዲኖሩ በማድረግ የኤሌክትሪክ ኃይል በቀዳሚነት ለቢትኮይን ምርት ጥቅም ላይ እንዲውል መደረጉን ያሳየናል። ይህ ችግር በስተመጨረሻ የሕዝብ ቁጣን አስከትሎ መንግስትን ውሳኔውን እንዲቀይር ያስገደደው ቢሆንም፣ ስርዓቱ ቅድሚያ ስለሚሰጣቸው ጉዳዮች በጥልቀት ያሳየናል። በዚህም የአጭር ጊዜ ትርፍ ለማግኘት ሲባል ዘላቂ ትኩረት የሚያስፈልጋቸው ሀገራዊ የልማት ጉዳዮች ወደ ጎን ተደርገዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሲጀመር ሁሉንም ሰው በእኩልነት ሊያስተናግድ እና የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ለሁሉም መንደር ሊያዳርስ የታሰበ ነበር። ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ተራው የኢትዮጵያ ዜጋ ወደ ጎን እየተደረገ እየተገለለ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ለውጭ ኩባንያዎች እና ለጎረቤት ሀገራት መዳረሱ የሚቀጥል ከሆነ፣ ግድቡ የብሔራዊ ቁጣ እና የመገፋት ምንጭ የመሆን አደጋ የሚጋረጥበት ይሆናል።
ፖለቲካዊ ስሱነት
በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በጅምር የቆመው ብሔራዊ ቃልኪዳን በቴክኒካዊ ወይም በገንዘብ ችግሮች ብቻ ሊገለጽ አይችልም። የግድቡ እጣ ፈንታ በኢትዮጵያ የተዘዘጋው የፖለቲካ ስርዓት ከሚፈጥረው መከፋፈል ጋር የማይነጣጠል ነው።
ከፈረንጆች 1995 ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያ በጎሳ “ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች” በሚል ብያኔ በሚመራ የፌዴራሊዝም ስርዓት በተቀረፀ ሕገ-መንግስት በመተዳደር ላይ ትገኛለች። ይህ ሕገ-መንግስት ለክልሎች የመገንጠል ሕገ-መንግስታዊ መብትንም ያጎናፀፈ ነው። ሕገ-መንግስቱ በንድፈ ሀሳብ ደረጃ የራስን ዕጣ ፋንታ በራስ የመወሰን መብትን በመስጠት የአንድ ብሔራዊ የበላይነትን ለመከላከል ታስቦ ነበር የፀደቀው። በተግባር ሲታይ ግን ለሀገራዊ ማንነት ከመታመን ይልቅ ለብሔር ማንነት መታመንን ያስከተለ፣ ኢትዮጵያውያን በመካከላቸው ያለው መተማመን ዝቅተኛ እንዲሆን ያደረገ፣ እንዲሁም የእርስ በርስ ግጭት አሳሳቢ ሁኔታ ላይ የደረሰበትን የፖለቲካ አውድ ፈጥሯል።
የዚህ ውጤት ሁሉ ግልጽ ነው። በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች በትጥቅ የታገዙ ግጭቶችን በማስከተል ለኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት አስፈላጊ የሆኑ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች፣ የንዑስ ማከፋፈያ ጣቢያዎችን እና ሌሎች የኃይል ማመንጫ መሠረተ ልማቶችን ቀጥተኛ የጥቃት ዒላማ እንዲሆኑና ጉዳት እንዲደርስባቸው ሆኗል። በሠላም እጦት ምክንያት ኮንትራክተሮች ጣቢያዎችን ለቀው ለመውጣት ተገደዋል። እነዚህ ግጭቶች የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ማዘግየት ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ክብርም ያበላሹ ናቸው። ግብፅ እና ሱዳን ኢትዮጵያ መከፋፈሏን በመረዳታቸው ለድርድር በሚቀመጡበት ወቅት ጥንካሬ እንደሌላት በመቁጠር በዓባይ ውሃ ዙሪያ በተደረጉ ድርድሮች ላይ ላይ ብልጫ ለመውሰድ ጫና ሲያደርጉ ተስተውሏል።
ባጭሩ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥታዊ ክፍተት ሰለባ ጭምር ነው። አንድነትን ለማሳየት የተገነባው ግድብ ለመከፋፈል ዋስትናን በሰጠ የፖለቲካ ሥርዓት በአግባቡ እንዳንጠቀምበት እክል ገጥሞታል።
ከሌሎች ሀገራት የተገኙ ትምህርቶች
ኢትዮጵያ በመሠረተ ልማት አማካኝነት የለውጥ ጉዞ የጀመረች የመጀመሪያዋ ሀገር አይደለችም። የሲንጋፖር፣ የቻይና፣ እና የቬትናም ልምድ ጠቃሚ ትምህርቶችን ይሰጣል።
ሲንጋፖር፣ ሲንጋፖር በ1965 ነፃነቷን ስታገኝ በጎሳ የተከፋፈለች እና የተበታተነች ሀገር ነበረች። የሊ ኩዋን ዩ መንግስት እያንዳንዱ ዜጋ በሕግ እኩል እንዲሆን በማድረግ በማኅበረሰብ-ተኮር ብሔራዊ ማንነት ላይ በትጋት ሰርቷል። መሠረተ ልማት በተለይም ግዙፍ የሕዝብ መኖሪያ ቤቶች ፕሮጀክቶች ማህበረሰቦችን ለማዋሃድ እና የባለቤትነት ስሜትን ለማጠናከር ጥቅም ላይ ውለዋል። በሀገሪቱ ትምህርት እና የሁለት ቋንቋ ተናጋሪ ሕዝብ መኖሩ የአንድነትን ስሜት የበለጠ አጠናክረዋል። ውጤቱም የኢኮኖሚ እድገት ብቻ ሳይሆን ከጎሳ ይልቅ በዜግነት ላይ የተመሰረተ ብሔራዊ አንድነት እውን እንዲሆን አድርጓል።
ቻይና፡ ከ1978 በኋላ ቻይና ወደ ዓለም ሁለተኛ ትልቅ ኢኮኖሚነት የቀየራትን ማሻሻያ ተግባራዊ ማድረግ ጀመረች። ከመንገዶች እስከ ገጠር የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ድረስ መሠረተ ልማት የቻይና ማዕከላዊ ትኩረት ነበር። ምንም እንኳን የጎሳ ብዝሃነት ቢኖርም፣ መላውን የቻይና ክፍል አንድ ወጥ በሆነ ራዕይ እንዲንቀሳቀስ በማድረግ የ“ቻይናውያን ዘመናዊነት” የሚል ታሪክ ተፈጠረ። ይህ ሂደት አመራሩ መረጋጋትን እና የጋራ እጣ ፈንታ ስሜት እንዲፈጥር ስላስቻለው ድህነትን ባልተጠበቀ ደረጃ መቀነስ ተቻለ።
ቬትናም፡ የቬትናሙ “ዶይ ሞይ” ማሻሻያዎች በ1986 በገበያ ላይ ያተኮረ እድገት ከሀገር አቀፍ የገጠር ኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ጋር ተጣምሮ ነበር። ይህንን ተከትሎ እ.ኤ.አ. በ1975፣ 2.5% የሚሆኑ ቤተሰቦች ብቻ ኤሌክትሪክ የነበራቸው ሲሆን፤ በ2023፣ ወደ 100% የሚጠጉ ቤተሰቦች የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት ቻሉ። ቬትናም ለአሥርት አመታት የዘለቀውን ጦርነት በመቋቋም የፖለቲካ መረጋጋት እና ጠንካራ የጋራ ማንነት ለልማት ቅድመ ሁኔታዎች እንደሆኑ ተረድታለች። መሠረተ ልማት ለኢኮኖሚ እድገት ብቻ ሳይሆን ለእርቅ እና ለሀገር ግንባታም መሳሪያ ሆኖ ለቬየትናም አገልግሏ።
ከነዚህ ልምዶች የምናገኘው ትምህርቱ የሚከተለው ሲሆን፣ መሪነት አንድነትን፣ መረጋጋትን እና የጋራ ዓላማ ስሜትን ሲፈጥር ብቻ የመሠረተ ልማት ውጥን ይሳካል። ይህ መሰረት ከሌለ፣ በኢንቨስትመንት ላይ የሚገኘው ትርፍ ይቀንሳል እንዲሁም ፕሮጀክቶች ባዶ ሐውልቶች የመሆን አደጋ ይጋረጥባቸዋል።
ኢትዮጵያን የገጠማት የአመራር ቀውስ
የኢትዮጵያ መሪዎች የሲንጋፖርን፣ የቻይናን ወይም የቬትናምን ምሳሌ አልተከተሉም። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ለአንድነት መነሻ ከማድረግ ይልቅ፣ ኢትዮጵያ እየተፈራረቁ ያስተዳድሩ መንግስታት መከፋፈል እና ግጭት የሀገሪቱን ዕጣ ፈንታ እንዲወስኑ አድርገዋል።
እ.ኤ.አ. በ2018 ስልጣን ላይ የወጡት የሰላም እና የማሻሻያ ተስፋ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ኢትዮጵያ እያስተዳደሩ ባለበት የሥልጣን ዘመናቸው ለዓመታት የዘለቀ ጦርነት፣ መፈናቀል እና ብዜጎች መካከል መተማመን የጠፋበት ሀገራዊ ሁኔታ እንዲፈጠር አድርገዋል። የህዳሴው ግድብ በስራ ዘመናቸው የተጠናቀቀ ቢሆንም፣ አስተዳደራቸው ይህንን ስኬት ከፖለቲካዊ እርቅ ወይም ተቋማዊ ማሻሻያ ጋር ማጣመር አልቻለም።
ይልቁንስ፣ የኃይል ፖሊሲው ከአመራር ውድቀት ጋር ተያይዞ በመቀጠል ለክርፕቶ ማዕድን ቅድሚያ ከመስጠት ጀምሮ እስከ ዜጎች የኃይል አቅርቦት ሳይኖራቸው የኤሌክትሪክ ኃይልን ወደ ውጭ መላክ የደረሰበት ሁኔታ ተፈጥሯል። መንግሥት የህዳሴውን ግድብ የአንድነት ምልክት አድርጎ ትርክት ቢገነባም የግድቡ ግልጋሎት ሚዛናዊነቱ ለተጓደለ የኃይል ስርጭት ተጋላጭ ከሆነ እና ቀጣይነት ባለው የሀገር ውስጥ ጦርነት ከተሸፈነ ግድቡ ትርጉም የለሽ ይሆናል።
መሪነት ማለት የሐውልቶች መገንባት ሳይሆን የመተማመን፣ መረጋጋት እና የጋራ ብልጽግናን መገንባት ነው። ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያን የገጠማት ቀውስ ቴክኒካዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ ነው።
የአመራር ብቃትን እና ሰላም እንደ ቅድመ ሁኔታ ያቀፈ መፍትሔ
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ቃልኪዳን አሁንም የመሳካት እድሎች ቢኖሩትም ይህ እውን የሚሆነው ግን ኢትዮጵያ ደፋር የፖለቲካ ምርጫዎችን ካደረገች ብቻ ነው።
- የፖለቲካውን ማዕቀፉን ማሻሻል፦ ኢትዮጵያ ከጎሳ ፌደራሊዝም በመራቅ በዜግነት ላይ በተመሰረተ ሲቪክ ሕገ-መንግስት መተዳደር አለባት። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ማንነት “ብሔሮች እና ብሔረሰቦች” ሳይሆን “እኛ ሕዝቡ” መሆን አለበት። ይህ በቀደመው ስርዓት ሥር የሰደዱ የፖለቲካ ልሂቃንን ለመጋፈጥ እና ለአንድነት ቅድሚያ ለመስጠት ፍላጎት ያለው ደፋር አመራር ይጠይቃል።
- ለሰላም ቅድሚያ መስጠት፦ ያለ ሰላም ምንም አይነት ልማት ማምጣት አይቻልም። በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች በመካሄድ ላይ ያሉ ጦርነቶችን ማስቆም ከሁሉም በፊት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆን አለበት። የታጠቁ ቡድኖችን ጨምሮ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ሁሉን አቀፍ ውይይት ማድረግ አስፈላጊ ነው። ያለ ሰላም፣ የህዳሴው ግድብ የሚያመነጨው እያንዳንዱ ኪሎዋት ለሕዝቡ ፋይዳ ቢስ ነው።
- እኩል ተደራሽነትን ማስፋፋት፦ የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ክፍተቱን መሙላት እጅግ ወሳኝ ጉዳይ ነው። ወደ ውጭ በሚላኩ ምርቶች የሚገኘው ገቢ በገጠርማው የሀገሪቷ ክፍል የኤሌክትሪክ ኃይልን ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል መዋዕለ ንዋይ መሆን አለበት። የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታዎች መስፋፋት እና የፀሐይ ኃይል አማራጮች በመፍትሄነት ሊወሰዱም ይገባል። የህዳሴው ግድብ ስኬት የሚለካው በኤክስፖርት ገቢ ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ የኢትዮጵያ ቤተሰብ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ማግኘቱን በማረጋገጥ ነው።
- የዓባይን ዲፕሎማሲ እንደገና ማጤን፦ የዓባይ ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት አሁን በስራ ላይ በመዋሉ፣ ኢትዮጵያ ከግብፅ እና ሱዳን ጋር የሚደረገውን ድርድር ከግጭት ይልቅ ለትብብር እንዲሆን የማድረግ እድል አላት። የዚህ አይነት የኃይል ትስስር ዓባይን ከውጥረት ምንጭ አውጥቶ ወደ የጋራ ብልጽግና መድረክ ሊለውጠው ይችላል። ነገር ግን ኢትዮጵያ በዚህ
ወደፊት ያለው ምርጫ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ላይ እንደተጫነ ትልቅ የብሔራዊ ሕልም ዘውድ ነው። ግድቡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ሕልም ሊያይ፣ በአንድነት መስዕዋትነት ሊከፍል እና የተለየ እምርታ ማምጣት የሚችልን ነገር ሊገነባ እንደሚችል ማሳያ ነው። ነገር ግን ትሩፋቱ የሚገለፀው በተርባይኖች ወይም በሜጋ ዋት ብቻ አይደለም። የሚገለፀው በመሪነት እና በሰላም መረጋገጥ ነው።
ያለ አንድነት እና መልካም አስተዳደር፣ የህዳሴው ግድብ ብሔራዊ ተቃርኖ ሆኖ ሊቀር የሚችል እና በግጭት ምክንያት በተከፋፈለ እና በጨለመ ሀገር ውስጥ የተተከለ የኤሌክትሪክ ምልክት ሆኖ ሊቀር ይችላል። ነገር ግን ቁርጠኛ ማሻሻያዎችን፣ ሁሉን አቀፍ መሪነት እና ዘላቂ ሰላምን ማሳየት ከተቻለ፣ ግድቡ እንደታሰበው እውነተኛ የብርሃን፣ የብልጽግና እና የሀገር አንድነት ምንጭ ሊሆን ይችላል።
ስለዚህ ያለው ምርጫው ግልጽ ነው። የህዳሴው ግድብ በመከፋፈል የተጋረደ የምኞት ሐውልት ሆኖ ሊታወስ ይችላል ወይም ራሷን ማደስ ለምትችል ኢትዮጵያ መሰረት ሆኖ ሊታወስ ይችላል። የግድቡ እጣ ፈንታ እና የኢትዮጵያ ነገ የተመረኮዘው በድርድር ሲሚንቶ ወይም በውሃ ላይ ሳይሆን የአመራር ጥበብን በማሳየት ላይ ነው።